ሚያዝያ 24/2004 ዓ.ም.
ከሰሞኑ ለሰሚ የሚያሳፍር፤ አንድ ጉዳይ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ተፈጽሟል፡፡ ጉዳዩን በአንክሮ ለተመለከተው በእጅጉ ያሳስባል፡፡ የሰላ አንደበት ይዘው ያልኾኑትን ነን በማለት የሌላቸውን ሥልጣንና ዕውቀት እንዳላቸው በማስመሰል ደግ አባቶችን የሚያታልሉ፤ ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን የሚያስቀድሙ ወረበሎች አሉ፡፡ እነዚህ ጆቢራዎች በደጋግ አባቶቻችን አእጋር ሥር እየተርመሰመሱ፤ ዕውቀት መንፈሳዊ ሳያቋርጥ የሚያፈሰውን የእናት ቤተ ክርስቲያን ጡት እየጠቡ አድገውና ጐልምሰው ሊያገለግሉ በተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከል እየተሹለከለኩ ተንኮላቸውን ያለድካም ለመፈጸም ሲኳትኑ ይታያሉ፡፡ ከሰሞኑ የሰማነው ግብዝነትን ከአላዋቂነት ጋር አስተባብሮ የያዘ ከንቱ ተግባር፤ እነዚሀን መሰሪዎች አበው በበሰለ አመራራቸው ለይተው በመጠረቅ ከጉያቸው የሚያባርሩበት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም በዕውቀት ሚዛን መዝነው ማኔ ቴቄል ፋሬስ ብለው ለይተው የሚጥሉበት ሰዓት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መድረሱን የሚያመለክት ነው፡፡ ጊዜ ለሚሰጠው እንጂ ለማይሰጠው ጉዳይ መዘግየት ጉዳቱ ለራስ ነውና፡፡
ጉዳዩ በማኅበረ ቅዱሳን እንቅስቃሴ ጥቅማቸው የተነካ ወይም የሚነካ በመሰላቸው ሰዎች ተቀነባብሮ የነበረ ሴራ ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ማኅበሩ በአባቶች መመሪያና ምክር እንዲሁም ጸሎት እየታገዘ የነበረ አገልግሎቱን በተጠናከረ መንገድ ቀጥሎ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ከሕግና ትእዛዝ ፍጹም እንደወጣ አድርገው በማቅረብ በአገልግሎቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያመጣ ደብዳቤ ተፈርሞ እንዲበተን ለማድረግ ያደረጉት ከንቱ ሙከራ ነው፡፡ ግለሰቦቹ ይህንን እኩይ፣ በእግዚአብሔርና በሰው ሕግጋት የሚያስጠይቅ ተግባር ለማሳካት ያላደረጉት ጥረት ለአባቶችም ያልቀባጠሩት ማሳመኛ የሚመስል ነገር የለም፡፡ የእኩይ ተግባራቸው መነሻ ያደረጉት ለማኅበሩ እንዲደርስ ያሉትን ማሩን የሚያመር ወተቱን የሚያጠቁር የክስ ደብዳቤ ማርቀቅ ነው፡፡ ለደብዳቤው ርዕሰ ጉዳይነት የመረጡት ዐረፍተ ነገር «ለሕግ የበላይነት ሥልጣን ታዛዥ ሆኖ አለመገኘትን በሚመለከት ይሆናል» የሚል የአማርኛ ሰዋስው ሀሁን ያላለፈ በዚህም የጆቢራዎቹን ማንነት የገለጠ ያልተሟላ ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይነት የታሠረው ከንቱ ደብዳቤ በወግ ባልተጻፈ፤ ርዝመታቸው በትልልቅ አናቅጽ ማሠሪያ የተገታ ከሳሽ ዐረፍተ ነገሮች ታጅሏል፡፡ የደብዳቤው ፍሬ ሐሳብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ፊርማ በጸደቀ ደንብ የተቋቋመው፤ በደንቡም ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዐን አበው ተግሣጽ፣ ምክርና መመሪያ እየታገዘ አገልግሎቱን እየፈጸመ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያኗ ማእከላዊ አስተዳደር ቁጥጥር ውጪ ነው፤ በዚህም የሚሰጠውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ አልኾነም የሚል ነው፡፡ ደብዳቤው ይኽንኑ እንቢተኝነት ለመቀልበስ በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና በማኅበሩ መካከል «በዕለት፣ በሳምንት፣ በወርና በዓመት ያልተገደበ የመጻጻፍ ተግባር» ሲካሔድ እንደቆየ ያትታል፡፡ ደብዳቤ መጻጻፉ አሁንም «ከመቼውም ጊዜ ጐልቶ የታየበት ወቅት» እንደኾነም ያስረግጣል፡፡ ይህም የማኅበሩን «የበላይ ተጠሪ የሆነውን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያን» ለወቀሳ የዳረገ መኾኑን ይጠቅስና፤ ማኅበሩ በዚህ ተግባሩ የመምሪያውንም ኾነ የቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ አስተዳደር ህልውና እየተፈታተነ እንደኾነ በሬ ወለደ አሉባልታውን ይነዛል፡፡ ለዚህም ማሥረጃ ይጠቅሳል፡፡