የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በደማቅ መርሐ ግብር መከበር ይጀምራል፡፡

ሚያዚያ 20/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ዓለም አቀፋዊ ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት የጀመረበትን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ማክበር ይጀምራል፡፡

የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ አክሊሉ ለገሠ እንደገለጹት ማኅበሩ 20ኛ ዓመት  የበዓል ዝግጅቱን ሚያዝያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚያከብር ሲሆን በዓሉንም በሁሉም ማእከላትና ወረዳ ማእከላት በልዩ ልዩ መርሐ ግብራት ይካሄዳል፡፡

 

በዓሉን የተመለከተ ዘጋቢ ፊልም እና ትራክት የመጽሔተ ተልዕኮ ልዩ እትም መጽሔት መዘጋጅቱን የገለጹት ሓላፊው በዓሉ በአንድ ቀን የሚጠናቀቅ ሳይሆን በቀጣይ ተከታታይ መንፈሳዊ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን “ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት በጋራ እንሥራ” በሚል መሪ ቃል በሚያከበረው በዓል ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች ማኅበራትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚገኙ መሆኑን ታውቋል፡፡