lidetaleMariam 1

“መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፡- መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው” /መዝ.86፥1/


በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ

lidetaleMariam 1ይህ ቃል የእመቤታችንን አያቶቿን የቀደሙ ወላጆቿን ንጽሕና፣ ቅድስና፣ ክብር አስመልክቶ ቅዱስ ዳዊት የተናገረው የምስክርነት ቃል ነው፡፡ ይህ ምስክርነት አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ለኩነተ ሥጋ የመረጣት ቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆቿ ንጹሐን፣ ቅዱሳን መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ሲመላለስ፡- “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያፈራል፡፡ መልካምም ዛፍ ክፉ ፍሬን ማፍራት፥ ክፉ ዛፍም መልካም ፍሬን ማፍራት አይችልም” ማቴ.7፥17-18፡፡ በማለት እንደተናገረው እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተገኘችባቸው ወላጆቿ ሁሉ ቅዱሳን ንጹሐን፣ እግዚአብሔርን የሚወዱና የሚያከብሩ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ለመሆኑ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዘር ሐረግና የትውልድ ታሪኳ ምን ይመስላል?

 

በነገረ ማርያም ሰፍሮ ከምናገኘው ሰፊ ታሪክ ከፊሉን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ!

የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ በጥሪቃ ይባላሉ፤ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጸጎች ነበሩ፤ ብዕላቸውም የወርቅ፣ የብር፣ የፈረስ፣ የበቅሎ፣ የሴት ባሪያ፣ የወንድ ባሪያ ነው፡፡ ከወርቁ ብዛት የተነሣ እንደ አምባር እንደ ቀለበት እያሠሩ፤ ከበሬው ከላሙ ቀንድ ያደርጉት ነበር፡፡ ይህን ያህል አቅርንተ ወርቅ፤ ይህን ያህል አቃርንተ ብሩር ተብሎ ይቈጠር ነበር እንጂ፤ የቀረው አይቈጠርም ነበር፡፡ ከዕለታት ባንደኛው በጥሪቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘቡን ብዛት አይቶ፤ “ቴከታ እኔ መካን፤ አንቺ መካን ይህ ሁሉ ገንዘብ ለማን ይሆናል?” አላት “እግዚአብሔር እንጂ ከኔ ባይሰጥህ ወይ ከሌላ ይሰጥህ ይሆናል፤ አግብተህ አትወልድምን?” አለችው፡፡ “ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል” አላት፤ በዚህ ጊዜ አዘኑ፤ ወዲያው ራእይ አይተዋል፤ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስታወጣ፣ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስታደርስ ስድስተኛይቱ ጨረቃን፣ ጨረቃ ፀሐይን ስትወልድ አይተው፥ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም /ሕልም ተርጓሚ/ አለና ሂደው ነገሩት፤ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል” አላቸው፡፡ እነርሱም “ጊዜ ይተርጉመው” ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ፀነሰች፤ ወለደች ስሟን ሄኤማን አለቻት፤ ሄኤማን ማለት ረካብኩ ስእለትየ ረከብኩ ተምኔትየ /የፈለግሁትን የለመንኩትን አገኘሁ/ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፣ ቶና ሲካርን፣ ሲካር ሄርሜላን፣ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፣ ምክነት ወርዶ እንደ አያቶቿ ሆናለች፤ ብዕሉ ግን በመጠን ሆኗል፡፡

 

ከጎረቤቷ በዝሙት የምትኖር አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ሐና “ዛሬ ቤተ ክርስቲያን እስማለሁ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን የምለብሰው ልብስ የለኝም” አለቻት፡፡ እርሷም “ልብስማ የኔ ካንድ ሁለት ሦስት ልብስ አለልሽ አይደለም? ያንን ለብሰሽ አትሄጅምን?” አለቻት፡፡ “ያንቺ ልብስ የተሰበሰበ በዐስበ ደነስ በዐስበ ዝሙት ነው፡፡ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ንጹሕ ነገር ይወዳል፤ ይህን ለብሼ ብለምነው ምን ይሰማኛል ብዬ ነዋ” አለቻት፡፡ “ሐና፤ እኔ በምን ምክንያት ልጅ ነሣት እያልሁ ሳዝንልሽ እኖር ነበር፤ ለካ እንደ ድንጊያ አድርቆ ያስቀረሽ ይህ ክፋትሽ ነው” አለቻት በዚህ አዝናለች፡፡

 

በሌላ ጊዜም ሐናና ኢያቄም “መሥዋዕት እናቀርባለን” ብለው ከቤተ መቅደስ ሄዱ፤ ሊቀ ካህናቱ ሮቤል ይባል ነበር፡፡ “ወኢይተወከፍ መሥዋዕቶሙ ለመካናት እንጂ ይላል፤ “እናንተማ ብዝኁ ወተባዝኀ… ብሎ ለአዳም የነገረውን ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? ቢጠላችሁ ነው እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን? መሥዋዕታችሁን አልቀበልም” ብሏቸው በዚህ እያዘኑ ተመልሰዋል፡፡ …. ከዛፍ ሥር ተቀምጠው አርጋብ /ርግቦች/ ከልጆቻቸው ጋራ ሲጫወቱ ዕፅዋት አብበው አፍርተው አይታ “አርጋብን በባሕርያቸው እንዲራቡ፣ ዕፅዋትን እንዲያብቡ እንዲያፈሩ የምታደርግ የኔ ተፈጥሮዬ ከድንጋይ ይሆን ልጅ የነሣኸኝ” ብላ አዘነች፡፡ ከቤታቸው ሂደው “ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ አርሶ ቆፍሮ ይርዳን አንልም ለቤተ እግዚአብሔር አንጣፊ፤ ጋራጅ ሆኖ ይኖራል፤ ሴት ብንወልድ ዕንጨት ሰብራ ውኃ ቀድታ ትርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር መሶበ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ትኑር” ብለው ብፅዓት ገብተዋል፡፡

 

የሐምሌ  30 ዕለት እሷ ለሱ “ፀምር ሲያስታጥቁህ መቋሚያህ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየሁ” ብላ፤ እሱ ለሷዋ “ጻዕዳ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፤ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ” ብሎ ያዩትን ራእይ ተጨዋውተዋል፡፡ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም አለና ሂደው ነገሩት፡፡ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ” አላቸው፡፡ “አንተስ አልፈታኸውም ጊዜ ይፍታው” ብለው ተመልሰዋል፡፡ በነሐሴ 7 ቀን መልአክ መጥቶ ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ ብሏቸው በብሥራተ መልአክ በፈቃደ አምላክ እመቤታችን ተፀነሰች፡፡ በተፀነሰችም ጊዜ ብዙ ተአምራት ተደርጓል፡፡

 

በርሴባ የምትባል አክስት ነበረቻት አንድ ዐይና ነች፤ “ሐና እግዚአብሔር በረድኤት ጎበኘሽ መሰለኝ” ብላ ማኅፀኑዋን ደሳ ዐይኗን ብታሸው በርቶላታል፡፡ ይህን አብነት አድርገው ሕሙማን ሁሉ ማኅፀኑዋን እየዳሰሱ የሚፈወሱ ሆነዋል፡፡ ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል ያጎቷ ልጅ ነበር ሞተ፤ ትወደው ነበርና ያልጋውን ሸንኮር ይዛ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት “ሰላም ለኪ ኦ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ” ብሎ ከመፈክረ ሕልም የቀረውን ተርጉሞላታል፡፡

 

ከዚህ በኋላ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና “ቀድሞ ከነዚህ ወገን የሚሆኑ ዳዊት ሰሎሞን አርባ አርባ ዘመን እንደሰም አቅልጠው እንደ ገል ቀጥቅጠው ገዙን፡፡ አሁን ደግሞ ከዚህች የተወለደ እንደምን ያደርገን ይሆን?” ብለው በጠላትነት ተነሡባቸው፤ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለኢያቄም “አድባረ ሊባኖስ ይዘሃት ሂድ” ብሎት እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡ ይህም አስቀድሞ እግዚአብሔር ባወቀ “እምሊባኖስ ትወፅእ መርዓት … ሙሽራ /እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም/ ከሊባኖስ ትወጣለች” በማለት ጠቢቡ የተናገረው ቃለ ትንቢት ነው፡፡ /መኃ.4፥8/

 

ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በእመቤታችን ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ፡፡

በግንቦት 1 ቀን /5ሺ ከ5መቶ የመከራው ዘመን ሊያልቅ 15 ዓመታት ሲቀሩት/  ሊባኖስ በሚባል ተራራ ከፀሐይ የምታበራ ሴት ልጅ ተወለደች፡፡ ይህቺውም ፍጥረት ሁሉ /ደቂቀ አዳም ሁላቸው/ ተስፋ ሲያደርጓትና ሲጠባበቋት የነበረች የድኅነታቸው ምልክት እመቤታችን ናት፡፡

 

ሶሪያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም “አክሊለ ምክሕነ ወቀዳሚተ መድኀኒትነ፡፡ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል፡- የመመኪያችን ዘውድ የደኅንነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት በድንግል ማርያም ሆነልን” በማለት መናገሩ ስለዚህ ነው፡፡

 

  • አክሊል ምክሐነ፡- አላት ይህም አክሊል የወዲህኛው፣ ምክሕ የወዲያኛው ነው፡፡ ከነገሥታት መካከል እንደ ዳዊት የከበረ የለም፡፡ ምንም እንኳን ቅዱስ ዳዊት የከበረ ቢሆን የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለውም፡፡
  • ወቀዳሚተ መድኀኒተ አላት፡- ቀዳሚተ የወዲህኛው መድኀኒት የወዲያኛው ነው፡፡ ከመሳፍንት ወገን የሚሆን ኢያሱ ምንም የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ቢሆን የደኅንነታችን መጀመሪያ መሆን አልተቻለውም፡፡
  • ወመሠረተ ንጽሕና አላት፡- መሠረት የወዲህኛው፤ ንጽሕ የወዲያኛው ከነቢያተ እግዚአብሔር ወገን የሚሆን ኤልያስ በድንግልና በንጽሕና መኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ንጹሕ ድንግል ቢባል የንጽሕናችን መሠረት መሆን አልተቻለውም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችን መጀመሪያ፤ የንጽሕናችን መሠረት ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤” በማለት ተናግሯል፡፡ በእርሷ ምክንያትነት መድኀኒዓለም የሚፈጽምልንን ካሳ ነቢያትና የቀደሙ አበው ሁሉ የእርሷን መወለድ በናፍቆት ሲጠባበቁ ነበር፡፡ ከነቢያት አንዱ የሆነ ኢሳይያስም “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ጎሞራም በመሰልነ ነበር፡፡” በማለት መናገሩ በእርሷ መገኘት ከጥፋት መዳናችንን ሲገልጽ ነው፡፡ ኢሳ.1፥9

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ተወለደች የሐና ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ በሰሙ ጊዜ ፍጹም ደስ ብሏቸው ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰበሰቡ፡፡ ሕፃኗን /እመቤታችንን/ ተመልክተው ፍጹም አደነቁ፡፡ እርስ በርሳቸውም እንደዚች ያለች ብላቴና ከቶ አየተን አናውቅም ተባባሉ፤ ጸጋ እግዚአብሔር በርሷ አድሯልና፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በሰውነቷ ሁሉ መልቷልና፡፡

 

ከኢያቄምና ከሚስቱ ከሐና ጋራ ደስ እያላቸው የእግዚአብሔርን ቸርነት እየተናገሩ ሰባት ቀን ተቀመጡ፤ ያችንም ብላቴና ስምዋን ማርያም አሏት ይኸውም የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው፡፡ ሰባቱንም ቀን በፈጸሙ ጊዜ በፍቅር ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡

 

በዚህ ትውፊት መሠረት ኢትዮጵያውያን ምእመናን በየዓመቱ ግንቦት 1 ቀን የእመቤታችንን ልደት ከቤታቸው ወጥተውና ከያሉበት ተሰባስበው ንፍሮ ቀቅለው፣ አነባብሮ ጋግረውና ሌላም እንደ አቅማቸው /ዝክር አዘጋጅተው/ በመንፈሳዊ ደስታ ዛሬም ድረስ ያከብሩታል፡፡

 

የእመቤታችን ስሞችና ትርጓሜያቸው፡፡

ማርያም ማለት ፍጽምት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው መልክ ከደምግባት አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ ፍጻሜው ግን ንጽሐ ሥጋ ከንጽሐ ነፍስ ድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ አንድም ማርያም ጸጋ ወሀብት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው ለእናት ለአባቷ ጸጋ ሆና ተሰጥታለች፡፡ ፍጻሜው ግን ለሰው ሁሉ ጸጋ ሁና ተሰጥታናለችና፡፡

 

አንድም፡- ማርያም ማለት መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው፡፡ ምእመናንን መርታ ገነት መንግሥተ ሰማያት አግብታለችና፡፡ አንድም ማርያም ማለት ልዕልት ማለት ነው፡፡ ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ ናትና አንድም ማሪሃም ማለት እግዝእተ ብዙኀን ማለት ነው አብርሃም ማለት አበ ብዙሃን እንደሆነ ማለት ነው፡፡

 

እንግዲህ ለነቢያተ ዜና ትንቢታቸው ለሐዋርያት ስብከታቸው ለክርስቲያኖች ሁሉ ተስፋቸው የሆነች እመቤታችን የተወለደችበትን ቀን ሁላችን ምእመናን በፍጹም ፍቅርና ደስታ እናከብረዋለን፡፡

 

ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ለተዋሕዶ ከመረጣት ከዓለመ አንስት ተለይታ በንጽሕና በቅድስና አጊጣ የመመኪያችን ዘውድ ከሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ይክፈለን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር