ቅዱስ ዑራኤል በግሸን አምባ
ጥቅምት 29 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ
- ‹‹መስቀሉ በአዳል ሜዳ በር እንዲገባ ያመላከተው ቅ/ ዑራኤል ነው››
- ‹‹ጥር 22 ቀን ቤተ ክርስቲያኑ ይመረቃል››
ቅዱስ ተብለው የሚጠሩት ደገኛው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ካሌብ የሀገረ ናግራን ክርስቲያኖችን ለመታደግ ዘምተው የአሕዛቡን ንጉሥ ፊንሀስን ድል አድርገው ሲመለሱ በነበራቸው መንፈሳዊ ፀጋ እንዲሁም በአበ ነፍሳቸው ፈቃደ ክርስቶስ ምክር የግሸን ደብረ ከርቤን ክብር በመረዳት ፤በ517 ዓ.ም ታቦተ እግዚአብሔር አብንና ታቦተ ማርያምን ከሀገረ ናግራን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በግሸን አምባ ላይ ቤተ መቅደስ ሠርተው ቀዳሽና አወዳሽ መድበው ደብረዋታል፡፡ በወቅቱም አምባው መግቢያ ካለመኖሩ የተነሣ ተራራውን ሲዞሩ የንብ መንጋ በማየታቸው “አምባ አሰል” ብለውታል፡፡ ትርጓሜውም የማር አምባ ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አካባቢው አምባ ሰል ሲባል ይኖራል፡፡