ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ምን ይላሉ?
ታኅሣሥ 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
-
“እግዚአብሔር ከእኛ በላይ የሚመለከታቸው አባቶች አሉ”
ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ
ከሰሜን አሜሪካ ከኮሎራዶ ስቴት
ቤተ ክርስቲያን የሚጠብቅ የሚመራ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ቅዱስ አባታችን በማረፋቸው የተነሣ ሀገራችን ትልቅ ሐዘን ላይ ናት፡፡ በዚህ ወቅት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የጸሎቱ ጉዳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመንበሩ ደግ አባት እንዲያስቀምጥ በጸሎት ሊለመን ይገባል፡፡ አሁን ቤተ ክርስቲያን ጥንቃቄ ልታደርግበት ይገባል ብዬ የማስበው በሰው ሰውኛ መንገድ በመጓዝ ለቤተ ክርስቲያን የሚሆነውን አባት ለመምረጥ ከተሞከረ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሙሴን፣ አሮንን እንደጠራቸው ሁሉ የሚመረጡት አባት እግዚአብሔር የጠራቸው አባት እንዲሆኑ መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን፤ ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ነን፤ ሁሉም አባቶቻችን የቤተክርስቲያን አባቶች ናቸው፡፡ «እገሌ ከእገሌ» ሳይባል መንፈስ ቅዱስ የጠራው አባት ለዚህች ቤተ ክርስቲያን መሪ እንዲሆን መጸለይ ያስፈልጋል፡፡
በሰው ሰውኛውን ተመልክተን “አቡነ እገሌ” ቢሆኑ ይሻላል የምንለው የሚጠቅም አይሆንም፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ በላይ የሚመለከታቸው አባቶች ስለሚኖሩ “እገሌ ከእገሌ” ይሻላል ብሎ መምረጥ ያለበት እግዚአብሔር ነው፡፡ መብቱን ለመንፈስ ቅዱስ ከሰጠነው ትክክለኛ አባት ሊመርጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በኅብረት ሆነን ሥራው ውጤታማ እንዲሆን መተባበር በምንችለው አቅም ማገልገል፣ መጸለይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ ነገ ሊጸጽተን የሚችል ሥራ መሥራት የለብንም፡፡ ነገ የሚጸጽተን ሥራ መሥራት ቤተ ክርስቲያናችንን ሊጎዳ ይችላል፡፡ ሰው ይጠቅመኛል ብሎ የሚያስቀምጠው ሰው ሰውኛውን ይሆንና ቤተ ክርስቲያንን ሊጎዳ ይችላል፡፡ ትልቁ ነገር ቤተ ክርስቲያንን የማይጎዳ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ነው እግዚአብሔር የሚያግዘን፣ በረከቱን የሚያበዛልን፡፡