ገዳሞቻችንን ለሁሉ ዓቀፍ ልማት አናዘጋጃቸው፡፡

ታኅሣሥ 5 ቀን 2005 ዓ.ም.

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበርካታ ገዳማት ባለቤት ነች፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር ከ5ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ እየተስፋፉና እያደጉ የመጡት እነዚሁ ገዳማት የምናኔና የጸሎት እንዲሁም ድኀነተ ሥጋ ወነፍስ የሚገኝባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ከመስጠት ጎን ለጎን የሊቃውንት መፍለቂያና የበርካታ ቅዱሳን ምንጭ በመሆንም ሲያገለግሉ እንደኖሩ ይታወቃል፡፡ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አዎንታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠራቸውም በላይ የሀገሪቱ የትምህርትና የሥልጣኔ ማእከላት በመሆን አገልግለዋል፡፡

 

የብዝኀ ሕይወት መገኛና መጠበቂያ ማእከላት መሆናቸው በተጨባጭ የሚታይ ሲሆን ለሥጋም ለነፍስም ስንቅ የሆኑ ትምህርቶች መቅሰሚያ ሕያዋን ትምህርት ቤቶች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ለኪነ ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕድገት መሠረት ከመሆናቸውም በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና በቱሪስት መስህብነትና በምጣኔ ሀብት ምንጭነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ መላው ዓለም የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡

 

ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት በተለያዩ አዝማናት በሀገሪቱና በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በደረሱ ውጪያዊና ውስጣዊ የጥፋት ዘመቻዎች ቀጥተኛ ተጠቂዎችም ነበሩ፡፡ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ችግሮችም እንደየአካባቢው መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ተጋላጭ ሆነው ኖረዋል፡፡ አጽራረ ቤተ ክርስቲያንም በየጊዜው በተለያየ ስልት የገዳማውያኑን አኗኗር፣ ሥርዓትና ትውፊት ለመበረዝ ሲንቀሳቀሱና ገዳማቱን ሲዋጉ እንደኖሩ ግልጽ ነው፡፡

 

በእኛ ዘመንም ገዳማቱ በሀገሪቱ ሕዝብና መንግሥት የነበራቸውን መልካም ስምና ታሪክ ለማደብዘዝ እያበረከቱት ያለውን መንፈሳዊና ሀገራዊ አስተዋፅኦ ወደጎን በማለት በረቀቀ ስልት በኢትዮጵያ ገዳማት ላይ ዘርፈ ብዙ ዘመቻ እንደተከፈተባቸውም እንገነዘባለን፡፡ ከዘመቻውም በተጻራሪ የዘመኑን ችግር በዘመኑ ጥበብና ዕውቀት እየፈቱ እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ ሁሉ አገልግለው በክብር ያረፉ መንፈሳውያን አርበኞች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ ይልቁንም በወሳኝና አስቸጋሪ ወቅቶች እግዚአብሔር እያነሣሣ ሥራ የሠራባቸውንና የሚሠራባቸውን አባቶች፣ እናቶችና ተተኪ ልጆች ያጣችበት ጊዜ እንደሌለም በሚገባ እንረዳለን፡፡

 

በዘመነ ሉላዊነት ዓለማዊነት በገነነበት በዚህ እጅግ አስቸጋሪ ወቅት የገዳሞቻችን ተግዳሮቶችም የዚያኑ ያህል የረቀቁ፣ በቀላሉ ለመለየት የሚያስቸግሩና የተወሳሰቡ እንደሚሆኑ እሙን ነው፡፡ ከዚሁ አንጻር የመንፈሳዊ ሕይወት፣ የመልካም ሥነ ምግባራት፣ የልማት፣ የትምህርትና የዕድገት መሠረትነታቸውንና ማእከልነታቸውን ጠብቆ ለማስቀጠል፣ ብሎም ይህን ገዳማዊ እሴት አጥተው በስም ብቻ የሚጠሩትን ገዳሞቻችንን ስምና ግብራቸው የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ የዚያኑ ያህል በአግባቡ የታሰበበት፣ የተደራጀ፣ በዕቅድ የሚመራ፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ፣ በየደረጃው ያሉ ወገኖችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠና ቀጣይነት ያለው ተግባር ለማከናወን ቆርጦ መነሣት ጊዜው የሚጠይቀው ሰማዕትነት እንደሆነ እናምናለን፡፡

 

ከዚህ አንጻር በገዳማት ዙሪያ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በተዋረድ ባሉ የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ሥር ያሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን በተደራጀ መንገድም ሆነ በተናጠል ያደረጉት፣ እያደረጉት ያለውና ለማድረግ ያቀዷቸው በርካታ ተግባራት የሚያስመሰግኑ ቢሆኑም ከችግሩ ስፋት፣ ግዝፈትና ጥልቀት አኳያ ሲታይ ደግሞ በቂ ሥራ ሠርተናል የሚያሰኝ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 

እናም ዕውቀታችንን፣ ሙያችንን፣ ጉልበታችንንና ገንዘባችንን ከምንም በላይ ደግሞ በጎ ፈቃዳችንንና ጊዜያችንን አቀናጅተን በዘመናት ርዝመት በገዳሞቻችን ላይ የሚታዩትን ተጨባጭ ችግሮች ለመቅረፍ ረጅምና አድካሚውን ጉዞ በጋራ መጀመር ይጠበቅብናል እንላለን፡፡ ይህን ስንል ደግሞ በአንድ ጊዜ የገዳማቱን ችግሮች ሁሉ ማስወገድ ይቻላል በማለት ሳይሆን፤ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን እየመረጡ በተለይ ወሳኝ ችግሮች ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ እያነጣጠሩ ተራ በተራ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ማለታችን እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡ ገዳማቱም ከጸሎቱ፣ ከውስጥ አገልግሎቱና ከትህርምቱ (ከተጋደሎው) ጎን ለጎን ዘመኑን እየዋጁ ምእመናንን ከኋላቸው አሰልፈው የበረከተ ሥጋ ወነፍስ ተቋዳሽ ለማድረግ የፊት አውራሪነቱን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

በዚህ ረገድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ገዳማት አንዱ የሆነው ታላቁና ታሪካዊው የደብረ ሊባኖስ ገዳም ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ የሆኑና የገዳሙን መንፈሳዊ እሴት የሚያስጠብቁ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን አስቀርፆ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ በእጅጉ የሚያስደስት ጅምር ሥራ ነው፡፡ ይህም ድርጊት ገዳሙን በአርአያነት የሚያስጠቅሰው ከመሆኑም በላይ በአረንጓዴ ልማትና በብዝኃ ሕይወት ጥበቃም (ሀገሪቱ ከምታራምደው ፖሊሲ ጋር የተዛመደ ሆኖ ቦታውን በዚህ ዘርፍ) ከሀገሪቱ ተመራጭ ቦታዎች አንዱ እንደሚያደርገው ጽኑ እምነታችን ነው፡፡

 

ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር ኅዳር 9 ቀን 2005 ዓ.ም በተዘጋጀው የምክክር መርሐ ግብር ላይ ገዳሙ ይፋ ያደረጋቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች የገዳሙን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከመፍታት አንጻር ታላቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ በየገዳማቱና በየአብነት ትምህርት ቤቶቹ የተጀመሩ የመታደግና የማልማት ፕሮጀክቶች እየቀጠሉ እንዲህ ያለውን መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት ከማስፈጸም አንጻር ከገዳሙ ጋር አብሮ መሰለፍ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ሥራ ነው እንላለን፡፡ በቀጣይም በየአህጉረ ስብከቱ ለሌሎች ገዳማትና አድባራት ምሳሌ የሚሆኑ ቢያንስ አንዳንድ ገዳማትን በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ደንብ መሠረት ማደራጀት፣ ማልማትና በሁለንተናዊ ዘርፍ ማብቃት ይዋል ይደር የማይባል ጉዳይ እንደሆነም እናምናለን፡፡

 

በጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም የኖሩትንና አሁንም ያሉትን ችግሮች በቅደም ተከተል ለመፍታትና ገዳሙን ለመታደግ በመንፈሳውያን አባቶቻችንና በቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሙያ ልጆች «ብዝኃ ሕይወትና ሁሉን ዐቀፍ መሪ ዕቅድ» በሚል ስያሜ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት መዘጋጀቱ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ መሪ ዕቅድ የገዳሙን ብዝኃ ሕይወት ባሕላዊ አጠባበቅ ማጥናት፣ መጠበቅና ለቱሪዝም ያለውን ዋጋ ማስተዋወቅ፣ ለገዳሙ ማኅበረሰብ አማራጭ የኀይል አጠቃቀም አሳብ ማቅረብ፣ የተደራጀና የተቀናጀ የገዳም አስተዳደርን ማጠናከር፣ ገዳሙን ለምናኔ ሕይወት አመቺና ተመራጭ የሚያደርጉና የመሳሰሉት ተግባራት ተካተውበት የቀረበ መሆኑ መልካም ነው፡፡ ይህ መሪ ዕቅድ ወደ ተግባር ሲተረጎም የሚያስጠብቀው የገዳሙን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመላው ሀገሪቱን ብሎም የአህጉሪቱንና የዓለምን ጥቅም ጭምር መሆኑን በቅድሚያ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መሪ ዕቅዱ በሥራ ተተርጉሞ የታሰበውን ሁሉ ዐቀፍ ጠቀሜታ ያስገኝ ዘንድም የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም መላው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ቀርቦ በማየትና በመረዳት የድርሻችንን ለመወጣት በቁርጠኝነት ልንነሣ ያስፈልጋል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳንም እንደ ቤተ ክርስቲያን አካልነቱ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አማካኝነት ባለፉት 10 ዓመታት ባካሄዳቸው ጥናቶች መሠረት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በ105 ገዳማት እንደየችግሮቻቸው ዓይነትና መጠን እያየ ለአብነት ትምህርት ቤች የመማሪያና የመኖሪያ ግንባታ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የዕደ ጥበብ ማእከላት ግንባታና ሥልጠና እንዲሁም የወፍጮ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በእርሻ ፕሮጀክት ዘርፍም የንብ ማነብ፣ የወተት ከብት እርባታ፣ የከብት ማድለብ፣ የዶሮ ዕርባታና የመስኖ አገልግሎትን በሳይንሳዊና ዘመናዊ መንገድ እንዲጠቀሙና ምርታማነትን በማሳደግ ራሳቸውን ችለው ለሌሎችም እንዲተርፉ ለማድረግ የበኩሉን ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ለተለያዩ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ስምንት ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት በመተግበር ላይ ሲሆኑ ጥናታቸው ያለቀላቸው ዘጠኝ ፕሮጀክቶችን ደግሞ የበጎ አድራጊ ማኅበራትንና ምእመናንን ድጋፍ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ማኅበራችን እየተገበራቸው ያሉትንና የሚተገብራቸውን ቀጣይ ሥራዎች ሳያጓድል በሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል በኩል ከገዳሙ አስተዳደር ጋር ያጠናውን ይህን ሰፊ ሥራ ለመጀመርና ከዳር ለማድረስ የልጅነቱን ድርሻ የሚወጣ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል፡፡

 

ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች በሂደት እየተቀረፉ የልማት፣ የትምህርት፣ የመንፈሳዊ ሕይወት፣ የምናኔና የመልካም ሥነ ምግባራት ማእከልነታቸው እንዲጠበቅ ከማድረግ አኳያ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ሁላችንም በመንፈሳዊ ቅንዓት መረባረብ አለብን፡፡ ይህን ማድረግ የምንችል ከሆነ የጸሎት፣ የዕውቀትና የበረከት ምንጭ ከሆኑት ገዳሞቻችን ሀገሪቱም ሆነች ሕዝቦቿ ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡ የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪክ በማስተዋወቅ የጽሑፍና ታሪካዊ፤ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ከማድረግ አንጻርም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ዘላቂና አስተማማኝ ማድረግ እንችላለን፡፡ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከሚያስገኙት የማይነጥፍ ገቢ ጎን ለጎን በእርሻና በዕደ ጥበብ ምርታቸው የሀገሪቱን አጠቃላይ ዕድገት ደግፈው በምግብ ራስን የመቻል መርሐ ግብር ዕውን ከማድረግ አንጻር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እናግዛቸዋለን፡፡ ገዳማቱ ጧሪ ቀባሪ ለሌላቸው ወገኖቻችንና ለዕጓለማውታ ሕፃናት የሚሰጡትን አገልግሎት ለማቀላጠፍና ቅዱሳን አባቶቻችን የደነገጉት /የሠሩት/ ሥርዐተ ገዳም በሚመለከታቸው ሁሉ በአግባቡ እንዲፈጸም ለማስቻል ሁለንተናዊ አቅማቸውን በተቀረፁና በሚቀረፁ ፕሮጀክቶች አማካኝነት እንዲያሳድጉ መደገፍ ከሁላችንም የሚጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ ነው እንላለን፡፡

 

  • ምንጭ፡- ጽምዐ ጽድቅ 20ኛ ዓመት ቁጥር 6 ከታኅሣሥ 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.