ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – የመጀመሪያ ክፍል
አባ ጊዮርጊስ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል፤ የሚበዙት የምስጋና ድርሰቶች ናቸው፡፡ ከጻፋቸው ብዙ መጻሕፍት መካከል አንዱ መጽሐፈ ምሥጢር ነው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢር በቤተ ክርስቲያናችን ከሚጠቀሱ የዕቅበተ እምነት መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ሲሆን የአባ ጊዮርጊስ የነገረ ሃይማኖት ሊቅነቱ የተመሰከረበት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ አባ ጊዮርጊስ በነገረ እግዚአብሔር ላይ ጽርፈት የተናገሩ መናፍቃንን ለመገሠጽና ለእነርሱ መልስ ለመስጠት የጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ በምን ዓይነት ቅንዐተ መንፈስ ቅዱስ ተነሣሥቶ መልስ እንደሰጠ ሲነግረን “… የቅዱሳንን ዜናቸውን ለመናገር ፍቅር ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ከሐዲዎችን እነቅፋቸው ዘንድ ያስገድደኛል፤ ፍቅር ክርስቶስን እንዳመሰግነው ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ሰይጣንን አወግዘው ዘንድ ያስገድደኛል፤ ፍቅር የክርስቶስን ሐዋርያት እንድከተላቸው ያስገድደኛል፤ ቅንዐትም ዝንጉዎችን እንድዘልፋቸው ግድ ይለያኛል፤ ፍቅር ሰማዕታትን አወድሳቸው ዘንድ ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ጠንቋዮችን እንድዘልፋቸው ያስገድደኛል” በማለት ይገልጽልናል፡፡