ታቦተ እግዚአብሔርን ከጣዖት ጋር አንድ የሚያደርግ ማን ነው? (፪ኛ ቆሮ. ፮፥፲፮)

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ

በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ዋና ክፍል የተዘጋጀ

የካቲት ፳ ቀን ፳፻፲ .

‹ታቦት› ማለት ‹የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ፣ የእግዚአብሔር የክብሩ ዙፋን› ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሙሴን በታቦት ላይ ኾኖ ያነጋግረው ነበር (ዘፀ. ፳፭፥፳፪፤ ዘኍ. ፯፥፹፱)፡፡ ሕገ እግዚአብሔር በወረቀት ላይ መጻፍ ሲጀምር ብዙ ምሥጢራት በእግዚአብሔር አንደበት ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ተነግረዋል፡፡ ነቢዩ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል ከተነጋገረባቸው አንዱ ምሥጢር ደግሞ ‹‹እንደ ቀደመው የድንጋይ ጽላት ቅረፅ›› የሚለው ትእዛዝ ነው፡፡ ኃይለ ቃሉም ‹‹እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ ሁለት የድንጋይ ጽላት እንደ ፊተኛው አድርገህ ቅረፅ፤ ወደ እኔም ወደ ተራራው ውጣ፡፡ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃላት እጽፍባቸዋለሁ፤›› የሚል ነው (ዘፀ. ፴፬፥፩-፪)፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ንባብ ውስጥ በማያሻማ መልኩ እንደ ተመለከትነው ሙሴ በቀደሙት ጽላቶች ፈንታ ሌላ ጽላት እንዲቀርፅ ትእዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ዝቅ ብሎም ‹‹ሙሴም ሁለት ጽላት እንደ ቀደመው አድርጎ ቀረፀ›› በማለት ይደመድማል (ዘፀ.፴፬፥፬)፡፡

እንግዲህ ይህን ቃል እንዲሁ በዓይነ ሥጋም ኾነ በዓይነ ልቡና (ነፍስ) ለተመለከተው እግዚአብሔር በአንደበቱ ‹‹ታቦት ቅረፅ›› ብሎ ለሙሴ ሲናገር፣ ሙሴም ‹‹አሜን›› ብሎ ትእዛዙን ሲፈጽም ያሳያል፡፡ ይህም ብዙ ምሥጢር እንዳለው ግልፅ ነው፡፡ ለምን ቢሉ? አንደኛ ታቦት እንዲቀርፅ ሙሴ መታዘዙ ታቦት ለጊዜው ለእስራኤል ዘሥጋ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያና መማጸኛ እንዲኾን ነው፡፡ ሁለተኛ የፊተኛው ታቦት ከተሰበረ በኋላ ሁለተኛ ታቦት እንዲቀርፅ ሙሴ መታዘዙ ታቦት በቅዱሳን ስም እየተቀረፀ ለትውልደ ትውልድ እንደሚተላለፍ ለመግለጽ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የቀደሙት ጽላቶች በጣዖት ምክንያት ከተሰበሩ በኋላ ዳግመኛ እንዲቀረፁ ማዘዙ ታቦት አንድ ጊዜ ብቻ ለአምልኮት የሚፈለግ ከዚያ በኋላ የሚጣል እንዳልኾነ ለማስተማር ነው፡፡ የዚህ ዂሉ የምሥጢር መሠረት ግን ታቦቱ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን እስከ ወዲያኛው ሊኖር ከእግዚአብሔር መሰጠቱን እንድናውቅ ይረዳናል፡፡ ይህም ‹‹እንደ ቀደሙት ዂሉ ዐሠርቱ ቃላትን በዚህ ላይ እጽፋለሁ›› ማለቱ ነው፡፡

ስለዚህ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን ታቦቱ ላይ ዐሥሩ ቃላት መኖራቸው ነው፡፡ ከዐሥሩ ቃላት አንዱ ደግሞ ‹‹ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ›› የሚለው ትእዛዝ አንደኛው ነው (ዘፀ. ፳፥፫)፡፡ ከታቦቱ ላይ የእግዚአብሔር እንጂ የጣዖት ስም አልተጻፈበትምና፡፡ ለታቦት መስገዳችንም ይህን ሥርዓተ ምሥጢር በማወቅ እንጂ ባለማወቅ ለቅርፃ ቅርፅ ወይም ለጣዖት እየሰገድን አምልኮ ባዕድ እየፈጸምን አይደለም፡፡ እንግዲህ ስሙ ስመ አምላክ ከኾነ፣ ትእዛዙም ጣዖታዊ ሳይኾን አምላካዊ ከኾነ፣ በእግዚአብሔር ቃል አንደበት ታቦት እንዲቀርፅ ለሙሴ መለኮታዊ ትእዛዝ ከታዘዘ፣ ታቦት የስሙ ማረፊያ ኾኖ ሊኖር እንጂ በዘመን ሊሻር የሚችል አይደለም፡፡ ለምን ቢሉ በሊቀ ነቢያት ሙሴ ጊዜም ኾነ ዛሬ ከታቦቱ ላይ የታተመው ስመ አምላክ (የአምላክ ስም) ነውና፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ በተሰጠው ታቦት አምልኮተ እግዚአብሔርን ሲፈጽምበት ኑሮ ዐረፈ፡፡ ከእርሱ ቀጥሎ ኢያሱም እንደ ሙሴ ካህናቱን ታቦት አሸክሞ ወደ ምድረ ርስት ገባ፡፡ በኋላም ዳዊት ከአቢዳራ ቤት ወደ ኢያቡስ አስመጥቶ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ዘመረ፡፡ (ኢያ. ፫፥፩-፲፯፤ ፪ኛ ሳሙ. ፮፥፲-፲፪)፡፡ ቤተ አቢዳራ (የአቢዳራ ቤት) በታቦቱ እንደ ከበረ ዳዊትም በታቦቱ ሊከብር መፈለጉ የታቦቱን ክብር በመንፈሰ ትንቢት በማወቁ ነው፡፡ ስለዚህ ከሙሴ እስከ ዳዊት፣ ከዳዊት እስከ ልደተ ክርስቶስ ታቦት የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ኾኖ ሲሰገድለት ኑሯል፡፡ ወደፊትም በዚህ ሥርዓት ይቀጥላል፡፡

በሐዲስ ኪዳን ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ በከርሠ መቃብር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት አድሮ፣ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ዙፋኑ ሲያርግ ዐረገ፡፡ ከዚህ በኋላ አበው ሐዋርያት ወንጌልን አስተማሩ፡፡ በአንድ ቀን ትምህርት በእልፍ የሚቈጠሩ ምእመናን አመኑ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የቆሮንቶስ ምእመናን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የቆሮንቶስ ምእመናንም አምነው ከተጠመቁ፣ ከጨለማ ከወጡ በኋላ የለመዱት ልማድ እንዲህ ቶሎ ሊለወጥ አይችልምና በቅዱስ ጳውሎስ መዋዕለ ስብከት እየሾለኩ ወደ ቤተ ጣዖት መሔዳቸው አልቀረም፡፡

ይህን የተረዳው ቅዱስ ጳውሎስ የታቦትን ቅዱስነት የጣዖትን ርኩስነት ሲገልጽ ታቦቱን ‹‹ታቦተ እግዚአብሔር›› ብሎ ጣዖቱን ‹‹ርኩስ›› በማለት ገለጸው፡፡ ይኸውም ‹‹የእግዚአብሔርን ታቦት በጣዖት ቤት ውስጥ የሚጨምር ማን ነው?›› (፪ኛ ቆሮ. ፮፥፲፮) ብሎ ካነጻጸረ በኋላ ወደ ጣዖት የሚገሰግሱ ባዕዳንን ሲመክር ደግሞ ‹‹ወደ ረከሱት አትቅረቡ›› ሲል መክሯቸዋል፤ አስተምሯቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ርኩስ›› ብሎ  የነቀፈው ጣዖቱን ሲኾን፣ ‹‹ታቦተ እግዚአብሔር›› ብሎ የገለጸው ደግሞ ታቦቱን ነው፡፡ እንግዲህ ታቦትና ጣዖት በቅዱስ ጳውሎስ አንደበት እንዲህ የሰማይና የምድርን ያህል ርቀት አላቸው፡፡

በሐዲስ ኪዳን ታቦት አያስፈልግም ለሚሉ ዂሉ ይህ ‹‹ታቦተ እግዚአብሔር›› ተብሎ በቅዱስ ጳውሎስ አንደበት የተመሰከረለት ታቦት ለመኖሩ በቂ ምስክር ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ በቅዱስ ጳውሎስ ዘመን ጣዖት እንደ ነበረ ታቦትም ነበረ፡፡ ነገር ግን አለፈ ብሎ በማስተማር ፈንታ ታቦቱን ከጣዖት ክርስቶስን ከቤልሆር ለይቶ አያስተምርም ነበር፡፡ እርሱ ግን ‹‹ክርስቶስና ቤልሆር በማንኛውም ነገር ኅብረት እንደሌላቸው ታቦትና ጣዖትም እንዲሁ ናቸው›› ብሎ ታቦቱን ‹‹ታቦተ እግዚአብሔር››፣ ጣዖቱን ‹‹ርኩስ›› ብሎ ለይቶ አስተማረ፡፡ እንግዲህ ይህ ቃል አማናዊ እንጂ የምሳሌ ትምህርት ስላልኾነ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን  ታቦት መኖሩን በሚገባ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታቦቱ መኖሩ በዚህ ቃል መሠረት ነው እንጂ አላዋቂዎች እንደሚሉት በስሕተት አይደለም፡፡

ታቦቱ ላይ ስመ አምላክ ታትሞበታል፡፡ ስመ አምላክ የታተመበት እንዴት ‹‹ቅርፅ ቅርፅ›› ተብሎ ሊጠራ ይችላል? እርግጥ ነው ራሱ እግዚአብሔር ታቦት እንዲቀርፅ ‹‹እንደ ቀደመው አድርገህ ቅረፅ›› በማለት ሙሴን አዝዞታል (ዘፀ. ፴፬፥፩-፪)፡፡ ታቦቱ ስመ አምላክ ከተጻፈበት በኋላ ታቦት እንጂ ‹‹ቅርጻ ቅርፅ›› ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ አልተመዘገበም፡፡ ቅርፃ ቅርፅ የሚባለው ስመ አምላክ ያልተጻፈበት ተራ ነገር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም አክብሮ ‹‹ታቦተ እግዚአብሔር›› ብሎ ጠራው እንጂ ‹‹ቅርፃ ቅርፅ›› ብሎ አላሳነሰውም፡፡ ለምን ቢሉ ስሙ ታትሞበታልና ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ስሙን በወደደው ላይ ጽፎ ማስተማር ይችላልና፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ ሲነግረው ‹‹በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ፤ በፊቱም ተጠንቀቁ፡፡ ቃሉንም አድምጡ፡፡ ስሜም በእርሱ ስለ ኾነ ኀጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት›› ብሎታል (ዘፀ. ፳፫፥፳-፳፪)፡፡

በዚህ ኹኔታ ስንመለከተው ደግሞ ታቦቱ ላይ ስሙ ታትሞበታል፡፡ ስሙ የታተመው ደግሞ የምናመልከው እግዚአብሔር ለመኾኑና የምንሰግደውም ለስመ እግዚአብሔር እንጂ ለሌላ እንዳልኾነ ምስክር ሊኾነን ነው፡፡ እናም አምላካችን እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን ታቦት ለሙሴ ሲሰጠው ታቦቱ ላይ ስሙ ተጽፎ ነበር፡፡ ይህም የክብሩ መገለጫ ሊኾን  እስራኤል ዘሥጋ ስሙን እየጠሩ እንዲያመልኩት ነው፡፡ ዛሬም በሐዲስ ኪዳን ለታቦት እንሰግዳለን፤ ስሙ ተጽፎበታልና፡፡ አምልኮ ባዕድ አልፈጸምንም፡፡ ‹‹ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ፤ የጌታችን እግር በቆመበት ዂሉ እንሰግዳለን›› ብሎ ቅዱስ ዳዊት እንዳስተማረን (መዝ. ፻፴፩፥፯)፡፡ ምክንያቱም ታቦት እግዚአብሔር በጸጋ፣ በረድኤት የሚያድረበትና የሚገለጽበት ነውና (ዘፀ. ፳፭፥፳፪፤ ዘኍ. ፯፥፹፱)፡፡

በዘመነ ኦሪት የእግዚአብሔር ታቦት የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ ኾኖ አግልግሎት ሰጥቷል፡፡ ይኸውም ስመ እግዚአብሔር ስለ ተጻፈበት ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ታቦተ እግዚአብሔር የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ስመ እግዚአብሔር ተጽፎበታልና ነው፡፡ ዛሬም በሕገ ወንጌል ክብሩ ሊገለጽ የሚችለው ስመ እግዚአብሔር ስለ ተጻፈበት ነው፡፡ ስመ እግዚአብሔር ደግሞ ትናንት በብሉይ ኪዳን ዛሬም በሐዲስ ኪዳን አንድ ነው፡፡ አንድ ነው ማለትም ያው ስሙ ሌላ እርሱ ሌላ አይደለም ማለት ነው፡፡ እናም ዛሬም ኾነ ነገ ስመ እግዚአብሔር መጥራት ለስሙ መስገድ ሃይማኖታዊ ምሥጢራችን ነው፡፡ ‹‹በሰማይም ኾነ በምድር ለስሙ ጕልበት ዂሉ ይንበረከካል፤ ይሰግዳል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ፊል. ፪፥፲)፡፡ እስራኤልም በታቦቱ ፊት ስግደት ያቀርቡ ነበር (ኢያ. ፯፥፮)፡፡

ሕዝበ እስራኤል ታቦቱን ለማክበር ሲሉ ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው ሲሔዱ ሕዝቡ ከታቦቱ ሁለት ሺ ክንድ ያህል ይርቁ ነበር (ኢያ. ፫፥፬) ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ለእግዚአብሔር ክብር ሲሉ ከታቦቱ ራቅ ይበሉ የሚባለው ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ሰሎሞን ታላቁን ቤተመቅደስ ከሰራ በኋላ ታቦቱን በታላቁ ቤተመቅደስ ውስጥ በክብር አስቀምጦታል (፩ኛ ነገ. ፰፥፮)፡፡ ከዚያም አገልግሎቱ ቀጥሏል፡፡ የዚህ ታቦት ክብር በሐዲስ ኪዳን በሰማይ ታይቷል (ራእ. ፲፩፥፲፱)፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ በተለይ በሐዲስ ኪዳን የታቦት ክብር በምድር ብቻ ሳይኾን ሰማያዊ ኾኗል፤ ‹‹የእግዚአብሔር ታቦት በሰማይ ታየ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ራእ. ፲፩፥፲፱)፡፡ ይኸውም ከብሉይ ኪዳን ዘመን ይልቅ በሐዲስ ኪዳን ዘመን የታቦት ክብር እጅግ የበለጠ መኾኑንና በሐዲስ ኪዳን ልንገለገልበት እግዚአብሔር የፈቀደ መኾኑን ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር ባይፈቅድ ኖሮ ክብሩን በሰማይ አይገልጽም ነበርና፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ታቦት ማለት ለዓለም ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሰጠ ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም የክብር ዙፋን (መሠዊያ) ነው፡፡ በታቦቱ ላይ የሚጻፈውም ቃልም ‹‹አልፋ ዖሜጋ›› (ፊተኛውና ኋለኛው፤ መጀመሪያውና መጨረሻው የዘላለም አምላክ) የሚለው ቅዱስ ስሙ ነው (ራእ. ፳፪፥፲፫)፡፡ በታቦቱ ፊትም የሚሰገደው ለዚህ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ‹‹በላይ በሰማይ፣ በታች በምድር የማናቸውንም ምሳሌ እና ቅርፅ በፊትህ አታድርግ፤ አትስገድላቸውም፤›› (ዘፀ. ፳፥፬-፭) የመሳሰሉትን ኃይለ ቃላት በመጥቀስ ታቦት፣ ሥዕል፣ መስቀል አያስፈልግም የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ኾኖም ይህ ኃይለ ቃል በእግዚአብሔር ፈንታ ለሚመለክ ጣዖት እንጂ የክብሩ መገለጫ ለኾነው ታቦትና እርሱ ፈቅዶ ለሰጠን የቅዱሳን ሥዕልና መስቀል የሚጠቀስ አይደለም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በትንቢተ ኤርምያስ ፫፥፲፮ ላይ ‹‹ከእንግዲህ የእግዚአብሔርን ታቦት ብላችሁ የማትጠሩበት ጊዜ ይመጣል›› ተብሎ ስለ ተጻፈ በሐዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ታቦት ብለን መጥራት የለብንም የሚሉ ሰዎችም አሉ፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ቃል የተናገረው ለእስራኤል ነው፡፡ እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበትን፣ ጠላትን ድል የሚያደርጉበትን፣ ከእግዚአብሔር በረከት የሚያገኙበትን የቃል ኪዳን ታቦቱን እየተዉ ወደ አምልኮ ጣዖት ተመለሱ፡፡ በዚህ ጊዜ ግልጥ አድርጎ ከባቢሎን ናቡከደነፆር ይመጣል፤ ኢየሩሳሌምን ይወራል፡፡ ቤተ መቅደሱን ያፈርሳል፡፡ እናንተንም ማርኮ ወስዶ ሰባ አመት ይቀጠቅጣችኋል ብሎ ትንቢት ተናገረባቸው፡፡ የተናገረው አልቀረም፤ ናቡከደነፆር መጣ፤ ኢየሩሳሌምም ተወረረች፤ ቤተ መቅደሱም ፈረሰ፤ ንዋያተ ቅድሳቱም ተዘረፉ፤ እስራኤልም ተማረኩ፡፡ አሁን በሰው አገር ጠላትን ድል የሚያደርጉበት፣ ከእግዚአብሔር የሚገናኙበት የእግዚአብሔር ታቦት አልተገኘም፡፡ ያን ጊዜ የነቢዩ ቃል ተፈጸመ፡፡ የእግዚአብሔር ታቦት አልተገኘምና የታቦቱን ስም መጥራት አልቻሉም፡፡ ይህን ትንቢት ለምን ተናገረ ብለው ኤርምያስን የገዛ ወገኖቹ ከመጸዳጃ ቤት ከተውታል፡፡ የተናገረው ግን አንዱም አልቀረም፤ ተፈጸመ፡፡

እኛ የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ግን ታቦታችን አልጠፋብንም፤ ምናልባት የጠፋባቸው ለማያምኑ ነው እንጂ፤ ታቦተ ጽዮን በኢትዮጵያ አሁንም ትገኛለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡