Entries by Mahibere Kidusan

ከማግሥተ ሆሣዕና እስከ ዕለተ ረቡዕ

የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ ልዩ ልዩ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ዅሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ‹‹የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፮፥፳፬)፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ ‹‹ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው፤›› ተብሎ አንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማልና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ‹‹ይህን ዓለም ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል?›› ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡

 ሰሙነ ሕማማት (ከዕለተ ሰኑይ እስከ ቀዳሚት ሰንበት)

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልዕት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት፣ ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡ መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታህ›› አይሉም፡፡ ሥርዓተ ፍትሐት አይፈጸምም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመኾኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምፅ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መኾናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

ስግደትና ሰላምታ በሰሙነ ሕማማት

ጌታችን በዚህ ኹኔታ ከተያዘ በኋላ ነው እስከ ሞት ድረስ ያን ዅሉ መከራ የተቀበለው፡፡ ስለኾነም ከሰሙነ ሕማማት እስከ በዓለ ትንሣኤ (ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን) እስከሚባል ድረስ መስቀል ወይም መጽሐፍ መሳለም እንዳይገባ ‹‹ወኢይትአምኁ በበይናቲሆሙ ዘእንበለ በዕለተ ፋሲካ ወኢየአምኁ መስቀለ ወወንጌለ፤ ያለ ፋሲካ ቀን እርስ በእርሳቸው አይሳሳሙ፤ መስቀልንና ወንጌልንም አይሳለሙ፤›› ተብሎ ተደንግጓል (ፍት.መን. ገጽ ፪፻፳፯)፡፡ ጸዋትወ ዜማም ‹‹ይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ሳመው ወይም በመሳም ስላስያዘው እርስ በርሳቸው አይሳሳሙ፤ ወንጌልንና መስቀልንም አይሳለሙ፡፡ የሞቱትንም ሰዎች አይፍቱ፤›› ይላል (ገጽ. ፺፬-፺፯)፡፡

በግብረ ሕማማት ገጽ ፵፯ እና ፭፻፺፭ ‹‹ወኢይትአምኁ በበይናቲሆሙ ወኢይአምኁ ወንጌለ ወመስቀለ በእንተ ዘአምኆ ይሁዳ ወኢይዝክሩ ሰሞሙ ለእለ ኖሙ ቅዱሳን አበው ወኢይበሉ ሐዳፌ ነፍስ›› ይላል፡፡ ይህ ትእዛዝ በእነዚህ ዅሉ መጻሕፍት እየተደጋገመ መጠቀሱ ለአጽንዖተ ነገር ነው፡፡ በሰሙነ ሕማማት እርስበርስ መሳሳም ከይሁዳ ሰላምታ ጋር የተያያዘ ስለ ኾነና የይሁዳ ተባባሪ ስለሚያሰኝ እስከ ትንሣኤ ድረስ መሳሳምም ኾነ ወንጌልንና መስቀልን መሳለም ተከልክሏል፡፡

ምሥጢረ ሆሣዕና

ጌታችን በአህያ መቀመጡ ስለ ምን ነው ቢሉ ትንቢቱ፣ ምሳሌው ሊፈጸም ነው፡፡ እርሱ ባወቀ (በአምላካዊ ጥበቡ) ትንቢቱን አስቀድሞ አናግሯል፤ ምሳሌውንም አስመስሏል፡፡ ትንቢቱ፡- ‹‹ሠረገላዉንም ከኤፍሬም፥ ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም ያጠፋል፤›› ተብሎ አስቀድሞ ተነግሯል (ዘካ. ፱፥፲)፡፡ የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ ጌታችን በፈረስና በሠረገላ ሳይኾን በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ምሳሌው፡- ቀድሞ ነቢያቱ ዘመነ ጸብዕ (የጦርነት ዘመን) የሚመጣ እንደ ኾነ በፈረስ ተቀምጠው፣ ዘገር ነጥቀው (የጦር ትጥቅ ይዘው)፤ ዘመነ ሰላም የሚመጣ እንደ ኾነ ደግሞ በአህያ ተቀምጠው፣ መነሳንስ ይዘው ይታያሉ፡፡ ጌታችን የሰላም አምላክ ነውና የሰላም ዘመን መድረሱን፣ ሰላምን ይዞ መምጣቱን ሲያስረዳ በአህያ ላይ ተቀምጦ ታየ፡፡ ምሥጢሩስ ምንድን ነው ቢሉ በአህያ ላይ የተቀመጠ ሸሽቶ ማምለጥ፣ አሳዶ መያዝ አይችልም፡፡ ጌታችንም ለሚፈለጉት (ለሚያምኑበት) እንደሚገኝ፤ ለማይፈልጉት (ለሚክዱት) እንደማይገኝ ሲያመላክት በአህያ ላይ ተቀምጦ ታየ፡፡ አንድም በንጹሓን መሃይምናን ላይ አድሮ እንደሚኖር ሲያጠይቅ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – የመጨረሻ ክፍል

ጌታችን ለኒቆዲሞስ እንዲህ በማለት የነገረው ይመስላል፤ ‹‹ኒቆዲሞስ ሆይ እየነገርሁህ ያለሁት ስለ ሌላ ልደት ነው፡፡ ስለምን ነው ንግግሬን ወደ ምድራዊ ነገር የምታወርደው? የምነግርህ ነገር ስለምን በተፈጥሮ ሕግ እንዲገዛ ታደርጋለህ? ይህ ልደት በሥጋ (በምጥ) ከሚደረገው ትውልድ የተለየ ነው፡፡ አጠቃላይና የተለመደ ከኾነ ልደት ራስህን አውጣ፡፡ እኔ ሌላ ልደት በሚገኝበት መንፈሳዊ ዓለም ሾሜሃለሁና፡፡ ሰዎች ዂሉ ከዚህ አዲስ ልደት እንዲወለዱ እወዳለሁ፡፡ አዲስ ዓይነት ልደትን ይዤ ወደ ምድር መጥቻለሁ፡፡ ሰውን የፈጠርሁት ከምድር አፈርና ከውኃ ነበር፡፡ ይህ ያገለግለኛል ብዬ የፈጠርሁት ምርጥ ዕቃ የተፈጠረበትን ዓላማ ዘንግቶ አግኝቸዋለሁና እንደገና ከአፈርና ከውኃ ልሠራው አልፈቅድም እንደገና በውኃና በመንፈስ እንዲወለድ እፈቅዳለሁ እንጂ፡፡››

ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – ሦስተኛ ክፍል

ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ መጣ፤ ከፍ ያሉ ነገሮችን አዳመጠ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ተራ ሰው የሚገልጣቸው አይደሉም፡፡ ማንም ሰውም ከዚህ አስቀድሞ ሰምቷቸው አያውቅም፡፡ በቅፅበት ኒቆዲሞስ ወደ ከፍታ ወጣ፤ ነገር ግን መረዳቱ ጨለማ ነበር፡፡ ነገር ግን በራሱ ማስተዋል ገና የቆመ በመሆኑ ሊሸከማቸው ስላልቻለ ወደቀ፤ የጌታን ቃል እንዴት ሊሆን ይችላል? በማለት ጠየቀ፡፡ ጌታ የተናገረውን ነገር እንዲያብራራለት ሰው ከሸመገለ በኋላ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን በማለት ማብራሪያ ጠየቀ፡፡ ኒቆዲሞስ ስለ መንፈሳዊ ልደት ሰምቷል፡፡ ነገር ግን በመንፈስ አልተለማመዳቸውም (አያውቀውም)፡፡ የተማመነውም ቁሳዊ መረጃ ላይ ነው፤ ይህን ትልቅ ምሥጢር ለመረዳትና ለመተርጐም ምሳሌ አድርጎ ያቀረበው የሰውን የሥጋ ልደት ነው፡፡ ይህን ኹኔታ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፤ ‹‹ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፡፡ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ኾነ ሊያውቀው አይችልም›› (፩ኛ ቆሮ. ፪፥፲፬)፡፡

ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – ሁለተኛ ክፍል

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ኒቆዲሞስን ‹‹ኒቆዲሞስ ሆይ፥ ስለ ምን በምስጢር በምሽት መጣህ? ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣ የእግዚአብሔር የሆነውንም ነገር እንደሚናገር እያወቅህ፡፡ ስለምን ከእርሱ ጋር ነገሮችን በግልጽ አልተወያየህም?›› ዓይነት ጥያቄዎችን አልጠየቀውም፡፡ አልወቀሰውምም፡፡ ነቢዩ እንዲህ ይላል፤ ‹‹አይጮኽም፤ ቃሉንም አያነሣም፡፡ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም፡፡ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ የሚጨስንም ክር አያጠፋም›› (ኢሳ. ፵፪፥፫)፡፡ ጌታ ራሱ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ዓለሙን ላድን እንጂ በዓለሙ ልፈርድ አልመጣሁም›› (ዮሐ. ፲፪፥፵፯)፡፡ የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትሕትና ተመልከቱ! ‹‹እኔ ዂሉን በራሴ ማድረግ ይቻለኛልና የማንም ርዳታ አያስፈልገኝም፡፡ እኔ ራሴ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ የያዝኩት ኀይል የአባቴን ኀይል ነው …›› አላለም፡፡ ይህንን ቢል ለሚያዳምጡት ወገኖች ቃሉን መቀበል ከባድ በኾነ ነበር፡፡

ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – የመጀመሪያ ክፍል

ወንጌላዊው እንደ ነገረን ኒቆዲሞስ ጌታ ከእግዚአብሔር እንደ መጣ አወቀ፤ አመነም (ዮሐ. ፫፥፪)፡፡ ነገር ግን ምናልባት ኒቆዲሞስ ጌታ ትምህርቱን ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያስተምር ሊያስብ ይችላል፡፡ የሕጉን ጥሬ ትርጕም እንጂ ፍካሬያዊ ትርጕም አልተገነዘበም፡፡ የአይሁድን ኑሮ ሊያሻሽል የመጣ ነው ብሎም ሊያስብ ይችላል፡፡ የኒቆዲሞስ አመለካከቱና ልምዱ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን አዲስ ሕይወት ለመቀበል አያበቃውም፡፡ በአዲሱ ልደት የሚገኘው የጸጋ ልጅነት አይገነዘበውም፡፡ የመንፈሳዊው ሕግ ጥቅም ግን ይህ ነበር፡፡ ሥጋዊውን ከመንፈሳዊ ምድራዊውን ከሰማያዊ መለየት ያስችላል፡፡ ጌታ የኒቆዲሞስን አሳቡን፣ ልቡን፣ ስሜቱን፣ ዕውቀቱን ዂሉ ወደ ሰማያዊ ነገር እንዲያሸጋግረው ፈቀደ፡፡ ይህን በማድረግ ከሰማይ የወረደው እርሱም በሰማይ የነበረው እንደ ኾነ ይገነዘባል፡፡ ወደ ሰማይ መውጣትም የሚቻለው እርሱ ነው፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ወገኖችን ከፍ ከፍ የሚያደርጋቸው፤ ከፍ ያለውንም ነገር እንዲመለከቱ የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፡፡

ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – የመጨረሻ ክፍል

በአጠቃላይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር መጽሐፉ የመናፍቃንን ስሕተትና የስሕተታቸውን ምክንያት ነቅሶ በማውጣትና መጽሐፋዊ የሆነ መልስ በመስጠት መናፍቃንንና ስሑታንን ገሥጿል፡፡ የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ለተነሡ ኑፋቄዎች መልስ መስጠት ቢሆንም ሌሎችንም ጉዳዮች በማንሣት መልስ እንደ ሰጠ ከላይ ተመልክተናል፡፡ “አዲስ መናፍቅ እንጂ አዲስ ኑፋቄ የለም” እንደሚባለው በመጽሐፉ የተጠቀሱ መናፍቃን ትምህርቶች ዛሬም ድረስ በተለያዩ አካላት እንደ አዲስ ሲጠቀሱና ሲነገሩ እንሰማለን፡፡ በዘመናችን የተነሡ መናፍቃንና ግብረ አበሮቻቸው የሚያስተምሩትም ቤተ ክርስቲያን አውግዛ የለየችውና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንት መልስ የሰጡበት እንጂ አዲስ የተገለጠላቸው ትምህርት አለመሆኑን መረዳት ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡ ትምህርቷን ያልሰሙ አላዋቂዎች ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን እንደማትሰብክ አድርገው ይናገራሉ፡፡

ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – ሦስተኛ ክፍል

አባ ጊዮርጊስ የክርስቶስን አምላክነት በመሰከረበት በዚህ አንቀጹ የሚከተለውን ትምህርት አስተምሯል፤ “ስለ ትሕትና ነገር መናገርን እናስቀድም፤ ኃይል በሴት ማኅፀን አደረ፤ እሳትም በሥጋና በደም መጐናጸፊያ ተጠቀለለ፡፡ ሕፃናትንም የሚሥል በሕፃናት መልክ ተሣለ፤ የሔዋን አባት ከሔዋን ሴት ልጅ ተወለደ፤ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ በጉልበት ታቀፈ፤ እሳት በተሣለባቸው በአራቱ እንሰሳ ላይ የሚጫን በላምና በአህያ መካከል ተኛ፡፡ ሥጋዊን ሁሉ የሚመግበው የጡት ወተትን ተመገበ፡፡ በጊዜና በዘመናት የሸመገለ በየጥቂቱ አደገ፤ በታናሽነታቸው ጊዜ ሕፃናትን የሚጠብቃቸው በሜዳ ላይ ዳኸ፤ ለዓመታቱ ቁጥር ጥንት የሌለው በሰው መጠን ጐለመሰ፤ ተራሮችን በኃይል የሚያቆማቸው ደከመ፣ ወዛም፡፡ ኪሩቤል ሊነኩት ሱራፌልም ሊዳስሱት የማይቻላቸው እግሮቹ በአመንዝራይቱ ሴት፣ ልብሶቹም ደም በሚፈስሳት ሴት ተዳሰሰ፡፡”