የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ ማኀበረ ቅዱሳን በግዮን ሆቴል ባዘጋጀውና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት አውደ ጥናት ላይ የቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ሥራዎቹ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት /UNESCO/ ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ፡፡
ቅዳሜ ግንቦት 10 ሙሉ ቀን በተደረገው በዚህ ዐውደ ጥናት ላይ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡባዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ከየአድባባራቱና ገዳማት ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቃለምዕዳን ዐውደ ጥናቱ ተከፍቷል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሠጡት ቃለ ምዕዳን ማኅበሩ የቅዱስ ያሬድን 1500ኛ መታሰቢያ በዓልን ማዘጋጀት በመቻሉ አመስግነው በአሁኑ ወቅት በቅዱስ ያሬድ የዜማ ትምህርት ከፍተኛ እውቀት ያላቸው አባቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱንና በሀገረ ስብከታቸው ከሚገኙ 1000 ገዳማትና አድባራት ውስጥ በጣም ጥቂት የድጓ መምህራን ብቻ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ይህም አሳሳቢነቱን ከፍ ስለሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡