ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንዳለበት ተገለጸ
ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሮችን በውይይትና በውይይት ብቻ በጋራ የመፍታት ባሕልን መደገፍና ማጎልበት እንደሚገባው ተገለጸ፡፡
በዛሬው ዕለት ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአሁኑ ጊዜ በጥልቀት፣ በማስተዋልና የሓላፊነት መንፈስ በተላበሰ ወኔ፣ አጥብቆ ሊወያይባቸውና ሊወስንባቸው፤ ከውሳኔ በኋላም ለተግባራዊነታቸው ሊረባረብባቸው የሚገቡ በርከት ያሉ ጉዳዮች እንዳሉ አመልክተዋል፡፡