ሚያዚያ 25፣ 2003ዓ.ም
/ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ሚያዝያ 2003ዓ.ም/
ፕሮቴስታንቶችና ፕሮቴስታንታዊ መንገድ የሚከተሉ አንዳንዶች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን አልሰበከችም የሚል ክርክር ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ዝግጅት ክፍላችን ጥያቄያቸውን ለመመለስ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን በምላሹ እንዲሳተፉበት ጋብዘናል፡፡ ለዚህ እትም የያዝነውን እነሆ!
“ቤተክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ወንጌል ነው”
ቤተክርስቲያን ወንጌልን ስትሰብክ ሁለት ሺሕ ዓመታት አልፏታል። ይህንንም ሊቃውንቱ ምእመናንም ያስረዱትና የተረዱት ነው። ወንጌል ካልተሰበከ ክርስቲያኖች እንዴት ለአሁን ዘመን ደረሱ? ወንጌል መሠረት፣ በጎ እርሾ ሳይሆነው፣ ወንጌል ብርታት ሳይሆነው ይህን ሁሉ ዘመናት አቆራርጦ፣ ድልድዩን አልፎ እንዴት እዚህ ደረሰ? ወንጌል ቤተ ክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ነው፡፡
በቤተክርስቲያን ሊቃውንቱ የሚያነቧቸው፣ የሚተረጉሟቸው፣ ምእምናን የሚሰሟቸው፣ የሚታነጹባቸው ድርሳናት፣ ተአምራት ወንጌል ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት ወንጌልን የሚፈቱ፣ የሚተረጉሙ፣ የሚያመሰጥሩ ናቸው። ከዚህ ውጭ የሆኑ መጻሕፍት በቤተክርስቲያን አይነበብም፣ አይተረጎምም፣ አይሰማም። ቤተክርስቲያን ወንጌልን የምትሰብከው በቃል፣ በመጽሐፍ ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው። ጥምቀት ወንጌል ነው። ቤተክርስቲያንም ጥምቀት የዘወትር ሥራዋ ነው። ወንጌል ስለ ጥምቀት ነው የሚነግረን። የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙም በየዕለቱ ይቀርባል፤ ይህ ወንጌል ነው። ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን የተቀደሰውን ጋብቻቸውን በተቀደሰው ቦታ፣ በተቀደሰው ጸሎት በምስጢረ ተክሊል ይፈጽማሉ። ይህም ወንጌል ነው። እናቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን ከዚህ ዓለም ሲሸኙ በሥርዐተ ፍትሐት፤ ብሉያትና ሐዲሳት እየተነበቡ፣ ያሬዳዊ ዜማ እየተዜመ ነው። ይህ ወንጌል ነው። አላዛርን ከመቃብር ተነሥ እንዳለው፤ የታሰረበትን ፍቱት እንደተባለ እንደተ ፈታ ሁሉ፤ ካህናትም ከኃጢአት እስራት እየፈቱ ሕዝባቸውን መሸኘት፤ “አቤቱ እግዚኦ ይቅር በለው ሲያውቅ፣ ሳያውቅ በሠራው ኃጢአት ይቅር በለው” እያሉ መሸኘት ወንጌል ነው።