የዐቢይ ጾም ስብከት (ክፍል 3)
የካቲት 24/2004 ዓ.ም.
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ በሦስተኛው ቀን በገሊላ አውራጃ በቃና መንደር ከእናቱ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ከአሥራ ሁለት ሐዋርያቱ ጋር በዶኪማስ ቤት ሠርግ ተጠርቶ ነበር፡፡ በዚያም ወይን ጠጅ አልቆባቸው አፍረውና ተሸማቀው የነበሩትን ጋባዦች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ውኃውን የወይን ጠጅ አድርጎ በመቀየር ከዕፍረት አድኗቸዋል፤ ክብሩን በመጀመሪያ ተአምሩ ገልጧል፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አምነዋል፤ዮሐ 2፥1-11፡፡

ብፁዕ አቡነ አብሳዲ በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ቅዳሜ የካቲት 10/2004 ዓ.ም. ለእሑድ አጥቢያ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ብፁዕነታቸው በትግራይ ክፍለ ሀገር ሽሬ በ1912 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በ1926 ዓ.ም ከሽሬ ወደ ኤርትራ በመሔድና ደብረ ማርያም ገዳም በመግባት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመከታተል ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ፣ ቅስናን ደግሞ ከአቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል፡፡ በደብረ ማርያም ገዳም ውስጥ በቆዩባቸው ዐሥር ዓመታት ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ዲያቆናትንና ካህናትን በማስተማር አፍርተዋል፡፡