‹‹የሞተ ሰውስ ዐረፈ፤ ነገር ግን መታሰቢያውን አድርግለት›› (ሲራክ ፴፰፥፳፫)
ሰዎች ሕያው ሆነን በፈጣሪ አምሳል እንደተፈጠርነው ሁሉ በኃጢአት ሳቢያ የተፈረደበትንን ሥጋዊ ሞት እንሞት ዘንድ አይቀሬ ነው፤ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህና›› እንደተባለውም የሰው ዘር በሙሉ ወደ አፈርነት ይመለሳል፡፡ በሕፃንነትም ይሁን በጎልማሳነት እንዲሁም በእርጅና ሰዎች ይሞታሉ፡፡ በበሽታ፣ በአደጋ ወይንም በግድያ የሰዎች ሕይወት በየጊዜው ይቀጠፋል፡፡ በተለይም በዚህ ትውልድ ዓለማችን በየጊዜው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አያጣች ነው፡፡ በእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት እንዲሁም የሰዎችን ሕይወት እንደ ቅጠል እያረገፈ ባለው ኮሮና በሽታ እጅግ ብዙ ሰዎች ሞተዋል፡፡
