ልደቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት

በብንያም ነጋሽ

ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር ሆኖ የሥላሴን መንበር ያጠነው ጻድቁ አባት አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተወለዱበት ዕለት የተቀደሰች ናት፤ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ለአባታቸው ካህኑ ጸጋ ዘአብና ለእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኀረያ ባበሠራቸው መሠረትም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ ኢቲሳ በሚባል ቦታ በታኅሣሥ ፳፬፤ ፲፪፻፲፪ ዓ.ም ተወለዱ፡፡  በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ     ወርደው    ‹‹አሐዱ  አብ  ቅዱስ፤   አሐዱ  ወልድ  ቅዱስ፤  አሐዱ  ውእቱ  መንፈስ  ቅዱስ፤  አንዱ አብ  ቅዱስ  ነው፤  አንዱ  ወልድ  ቅዱስ  ነው፤  አንዱ  መንፈስ  ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ‹‹ፍሥሐ ጽዮን››  የሚል ቢሆንም ‹‹ተክለ ሃይማኖት››  ደግሞ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያወጣላቸው ስም ነው፡፡ በ፲፭ ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡

ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በወጣትነቱ ከጅማ ወንዝ ማዶ በነበረው የዳሞት አረማዊ ንጉሥ ማቶሎሚ በርካታ አውዳሚ ጥቃቶች ደርሶበት ነበር፡፡ ከእነርሱም መካከል አንዱ እግዚአብሔር ኀረያን  መጥለፋ ሲሆን እነርሱ ግን በእግዚአብሔር መልእክ ቅዱስ ሚካኤል  ረዳትነት አመለጡት፤ ማቶሎሚም ማምለጣቸውን ሰመቶ አሳዶ ሊገላቸው ወደ እነርሱ አቅጣጫ ጦር ቢወረውርም ጦሩ እርሱ ወዳለበት አቅጣጫ ተመልሶ ዞሮ እራሱን ገደለው፤ በሊቀ መላእክት ሚካኤል አማላጅነትም ከጸጋ ዘአብ ጋር እንደገና መገናኘት ችለዋል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀንም ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጦላቸው ሐዲስ ሐዋርያ ተብሎም ቃሉን እንዲያስተምሩ ወንጌልን  ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸው ነገራቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም አጋንንትን የማውጣትና ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደተሰጣቸው፤ ስማቸውም ተክለ ሃይማኖት እንደሚባልና ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራ፣ ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፣ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፣ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ ማለት በመሆኑ ብዙ ደቀ መዝሙሮች እንደሚያፈሩና ለብዙዎች ድኅነት እንደሚሆኑ አስረዳቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ወደ በአታቸውም ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ከሰጡ በኋላ ‹‹አቤቱ   ጌታዬ   ኢየሱስ  ክርስቶስ ሆይ!  የመንግሥተ  ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን  እንደ ተከፈተ ተውኩልህ በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፤ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡ ሐዲስ ሐዋርያ› የተባሉትም በዚህ ተልእኳቸው ነው፤ ትርጕሙም ሐዲስ ኪዳንን ወይም ሕገ ወንጌልን እየተዘዋወረ የሚያስተምር ሰባኬ ወንጌል፤ በክርስቶስ ስም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን የሚያደርግ የክርስቶስ ተከታይ (ሐዋርያ) ማለት ነውና፡፡

ቅዱሱ አባታችን በተወለደባት ዕለት ቅዱሱን ከማመስገን በዘለለ በቅዱሱ ስም የተራቡትን ብናበላ፣ የታመሙትን ብንጠይቅ፣ የተጠሙትን ብናጠጣ፣  የታሠሩትን ብንጎበኝ የዚህን ጻድቅ አባት በረከት እንደምናገኝ ክርስቶስ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ቃል ገብቶልናል። ዳሩ ግን እንዲህ ዓይነት መልካም የቅድስና ሥራ ስንሠራ አውሬው የተጣለው ዘንዶ ደስተኛ አይሆንም። በዘመናችን በዓላትን ማክበር የድኅነት ምንጭ የሆነው ለዚህ ነው፤ ነገር ግን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው በሚል መናፍቃን ትውልዱን ከቅዱሳን አንድነት ለመለየት የአእምሮ ሥራ በሰፊው እየሠሩ ያሉት። ይህንንም እኩይ ሥራቸውን መዝሙረኛው ዳዊት አስቀድሞ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ  ላይ ‹‹አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው ኑ፤ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ›› ብሎ ተናግሮ ነበር። ትውልዱን ለሰይጣን አሳልፎ በሚሰጡ የሚያነፍዙ የምዕራባውያን በዓላትን እንዲያከብር ቀን ከሌት ሢሰሩ ይታያል። (መዝ. ፸፫፥፰)

‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ›› ተብሎ እንደተነገረው ዘመኑን እየቃኘን እጅግ ተቀይሮና ዘምኖ የመጣውን የአውሬውን ውጊያ ስልት በመረዳት እራሳችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ በቅዱስ ቃሉ እያነጽን በንስሓ እየተመላለስን በቁርባን እየቀደስን በንቃት የምንኖርበት ዘመን ላይ መሆናችንን መረዳት ያስፈልጋል። ‹‹አንተ የምትተኛ ንቃ›› እንዲል፤ (ኤፌ. ፭ ፥ ፲፬፣፲፮)

ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል›› ብሎ እንደተናገረው የዚህን ቅዱስ አባት በተወለደበት ዕለት የሚገባውን ክብር በመስጠት፣ ቤተ ክርስቲያኑን በመሳለም እና የተቸገሩትን በመርዳት በማሳለፍ ለክርስቲያን የሚገባ በጎ ተግባር በመፈጸም በዓሉን እናክብር፡፡  (ሮሜ ፪፥ ፲)

 የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አማላጅነት እና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ወለወላዲቱ ድንግል!

ወለመስቀሉ ክቡር!

አሜን!