ስብከተ ወንጌል
ቅዱስ ዳዊት “ኢትዝክር ለነ አበሳነ ዘትካት ፍጡነ ይርከበነ ሣህልከ እግዚኦ እስመ ተመንደብነ ፈድፋደ፤ የቀደመውን በደላችንን አታስብብን፥ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፥ እጅግ ተቸግረናልና” እንዳለ የቀደመ በደላችንን ሳያስብብን ጭንቀታችንን ችግራችንን ይቅር ብሎ ወደ እዚህ ምድር መጥቶ የምሥራች፣ ብርሃን፣ መንገድ፣ መስታወት፣ የሕይወት ዛፍ የሆነችውን ወንጌልን ሰበከን፤ አስተማረን። (መዝ.፸፰፥፰) ሐዋርያትንም “ሑሩ ውሰተ ኩሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት፤ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” በማለት በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌም፣ በሰማርያና እስከ ዓለም ዳርቻ እንዲያስተምሩ ላካቸው። (ማር.፲፮፥፲፭)