የበረሓው ኮከብ

ያቆን ተስፋዬ ቻይ

መጋቢት ፬፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ፈጣሪ ዓለማት እግዚአብሔር በነቢዩ አንደበት አድሮ ‹‹ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴትች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያን ስም እሰጣቸዋለሁ›› በማለት እንደተናገረው በሕግ በሥርዓቱ ተጉዘው፣ ተጋድሏቸውን ፈጽመው፣ ዓለምን ንቀው፣ ከኃጢአት ሥራ ርቀው፣ በጽቅ ሥራ ደምቀው፣ የባሕሪው ቅድስናውን በጸጋ ተቀብለው፣ በቤቱና በቅጽሩ መታሰቢያ ከሰጣቸው አባቶቻችንን መካከል አንዱ ርእሰ ባሕታዊ ጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንዱ ናቸው፡፡

ጻድቁ አባታቸንን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ከቅዱስ ስምዖን ወገብ ዘርን ከፍሎ በቅድስት አቅሌሲያ ማኅፀን በኪነ ጥበቡ ከውኖ ልዩ ስሙ ንኂሳ በተባለ አውራጃ በአገረ ግብፅ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ተወለዱ፡፡ በዚያኑ ዕለት “ከጨለማ ወደ ብርሃን ላወጣኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምሥጋና ይሁን” እያለ ስግደትን አቀረበ፡፡ (ስንክሳር ዘወርኃ መጋቢት አምስት) ዕድሜው ሦስት ዓመት ሲሆነው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእናቱ እቅፍ ተቀብሎ ባሕታውያን ካሉበት ገዳም ወስዶ አባ ዘመደ ብርሃን ለተባለ አባት ከሰጠው በኋላ እግዚአብሔር ስለ ሕፃኑ ያዘዘውን ሁሉ ነገረው፤ አባ ዘመድ በርሃን ሕፃኑን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ብሉይና ሐዲሳት እያስተማረ አሳደገው፤ በወቅቱ ከነበረው አብርሃም ከተባለው ሊቀ ጳጳስ ዘንድ ወሰደውና ማዕረገ ክህነትን እንዲቀበል አደረገው፤ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹…እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ ዕዳ አለብን፤ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለንም፤ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ..›› በማለት እንደገለጸው የክርስትናን ሕይወት ይጠራባት ብቻ ሳይሆን ይኖራት ዘንድ በጾም በጸሎት ተጋድሎውን ጀመረ፡፡ (ሮሜ ፰፥፲፪)

የበረሓው ኮከብ ርእሰ ባሕታዊ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከተወለደ ጀምሮ እህል ቀምሶ አያውቅም፤ በበረሓ ሆኖ የሥጋውን ፈቃድ ለነፍሱ አስገዝቶ ሥጋው ከአጥንቱ እስኪጣበቅም ጸንቷል እንጂ፤  በዚህም ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና ብርሃን ሠረገላው ይሆንለት ዘንድ ጸጋውን አጎናጸፈው፤ ሀገረ እግዚአብሔር መካነ ቅዱሳን የድንግል ዐሥራት ከሆነች  ኢትዮጵያ ምድር እንዲሄድም ነገረው፤ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአምላኩ ትእዛዝ መሠረት በብርሃን ሠረገላ ተጭኖ ስድሳ አናብስትና ስድሳ አናብርት አስከትሎ ወደ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ በመልአኩ እየተመራ መጣ፡፡ ወደ ምድረ ከብድ ከዚያም ወደ ዝቋላ ተራራ ሄደ፡፡

ጻድቁ አባታችንም ርእሰ ባሕታውያን አቡነ ገበረ መንፈስ ቅዱስ በአገሪቷ ላይ ያሉት ሕዝቦቿ ውለታ ረስተው በኃጢአት ተጠምደው ተመለከተ፤ በራሱም ተዘቅዝቆ ወደ ባሕሩ ገባ፤ ሕዝቡን ይምርለት ከኃጢአት አዘቅት አውጥቶ በምሕረቱ ይጎበኛቸው ዘንድም ተማጸነ፤ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው በትምህርቱና በአማናዊ ቃሉ ‹‹ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል..›› በማለት እንደተገለጸው (ማቴ.፲፥፵፩) በስሙ የተማጸነውን መታሰቢያውን የሚያደርገውን እንደሚምርለት በመልአኩ አማካኝነት ቢገልጽለትም የበረሓው ኮከብ ጽኑ ተጋዳይ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ግን መላው ኢትዮጵያን ይምርለት ዘንድ በራሱ ተዘቅዝቆ ከጠለቀበት ባሕር እንደማይወጣ ገለጸ፤ አጋንንት ጾር እያመጡ በቀስታቸው እየነደፉት መከራ ቢያጸኑበትም እርሱ ግን ኃይልን በሚሰጥና ሁሉን በሚያስቸል በእግዚአብሔር ፈተናውን ተቋቁሞና በተጋድሎው በተማጽኖው ጸና፤ እምነቱን፣ ጽናት ገድል እንዲሁም ትሩፋቱን ፈጣሪ ተመልክቶ ተገለጸለት፤ የጠየቀው ይፈጸምለት ሕዝቡንም ይምርለት ዘንድ ቃል ኪዳን ገባለት፡፡

አባታችን ከባሕር ተዘቅዝቆ በጸሎት በነበረበት ጊዜ ሰውነቱና አጥንቶቹ እንደ ወንፊት ተበሳስተው ነበር፤ ጌታችንም በድንቅ ተአምራቱ እንደ ቀድሞ አደረገለት፤ በሰውነቱ የበቀለው ጸጉር ልብስ ሆኖሎት በትምህርቱ በጸሎቱ ነፍሳትን ከኃጢአት ወደ ጽድቅ እየመራ ተጋድሎውን ቀጠለ፤ እንደ አባታችን አብርሃም ፈጣሪ ዓለማት ቅድስት ሥላሴ በአረጋውያን አምሳል ተገልጠውለት በጀርባው ለማዘል የታደለ ሆነ፡፡

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ወደ ዝቋላ ገዳም በመሄድ አጋንንት በጾም በጸሎት ይዋጋ ጀመር፤ ቅዱሳን መላእከት እየተራዱትም ድል አደረጋቸው፤ አባታችን በዘመኑ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ፣ ለሰዎች እየራራ፣ በተሰጠው ጸጋ ሕሙማን እየፈወሰ፣ ያላመኑት አስተምሮ እያጠመቀና ከሕይወት አገር እየመራ በጽኑ ተጋድሎ ኖረ፤ የማይስማሙ ነብርና አንበሳን አስማምቶ የእግሩን ትቢያ እየላሱ አብረውት እንዲኖሩ የታዘዙለት ጸጋው የበዛ ለብዙዎች የተረፈ በቃል ኪዳኑ የሚያስምር ነው፡፡ ሩኅሩኅ ጌታ ‹‹ከእኔ ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና..›› በማለት በነገረን መሠረት ጻድቁ አባታችን ትሕትና ነበረው፡፡ (ማቴ ፲፩፥፳፱)

በአንድ ወቅት ጣዖት የሚያመልክ አላዊ ንጉሥ በተገዳደረው ጊዜ ድንቅ ተአምራትን ሲያደርግ የተመለከቱ የንጉሡ ባለሟሎች ባደነቁትና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባመኑ ጊዜ ንጉሡ ተበሳጭቶ በሰይፍ እንዲቀሉት አደረገ፤ ንጉሡንና ቀሪ ሠራዊቱን መብረቅ ወርዶ አጠፋቸው፤ የሞቱን ነፍሳት መላእከተ ጽልመት ወደ ሲዖል ባወረዷው ጊዜ “እነዚህ ነፍሳት በእኔ ምክንያት ወደ መካራ ወረዱ” በማለት አዘነ፤ ስለነዚያ ነፍሳ ምሕረትን ለመነ፡፡ ‹‹..የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይልን ታደርጋለች…›› እንዲል (ስንክሳር ዘወርኃ መጋቢት ፭፣ ያዕ.፭፥፲፮)

አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በቅድስት አገር ኢትዮጵያ ተዘዋውሮ አስተምሯል፤  በስሙ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ያሉ ሲሆን በተለይ በዝቋላ ገዳም ቃል ኪዳንን የተቀበለበት እና በምድረ ከብድ የምድራዊ እንግድነት ኑሮውን ፈጽሞ ያረፈበት ገዳማት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ ሲደርስም ‹‹ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ…››  በሚል ቃሉ መሠረት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ እንደሚምርለት ቃል ኪዳንን ሰጠው፤ (መዝ.፹፰፥፫) መጋቢት አምስት ቀንም ዐረፈ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ልደታቸውን፣ ጥቅምት አምስት ቀን ቃል ኪዳን የተቀበሉበትን፣ መጋቢት አምስት ቀን ደግሞ ዕረፍታቸውን ታዘክራለች፡፡ ምእመናን ደግሞ ከተሰጣቸው ቃል ኪዳን በረከትን ለማግኘት ዝክራቸውን ይዘክራሉ፡፡ በስማቸው ለተራበ ያበላሉ፤ ይመጸውታሉ፤ ገድላቸውን አንብበው፣ መልካቸውን ደግመው፣ በስማቸው በተሰየመ ጸበል ተጸብለው፣ ከሕመማቸው ይፈወሳሉ፤ በረከታቸውን ይቀበላሉ፤ ከቃል ኪዳናቸው ተካፋይ ይሆናሉ፡፡

ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ከጻድቁ አባታችን ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት በረከታቸውን ያድለን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!