“መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው?” (ቅዱስ ያሬድ)

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
መጋቢት ፲፭፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ፈልፈለ ማኅሌት ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው እንዲህ እያለ ይዘምራል፤ “ገብር ኄር ወገብር ምእመን ገብር ዘአሥመሮ ለእግዚኡ፣ መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወገብር ምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኵሉ ንዋዩ ወካበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኀድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሓሁ ለእግዚእከ፤ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ሁሉ ላይ የሚሾመው የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል፡፡” (ጾመ ድጓ) ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብር ኄር ልጆቿን ስለ አገልግሎትና የአገልግሎት ዋጋ በስፋት የምታስተምርበት ሳምንት ነው።

ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ ሲያስተምር እንዲህ አለ፤ “ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ፤ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፤ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ።” (ማቴ.፳፭፥፲፬-፲፯) ጌታው ከሄደበት አገር ሲመለስ የሰጠኋችሁን የት አደረሳችሁ በማለት ጥያቄ አቀረበላቸው። ባሮችም እንዲህ በማለት መለሱ። በሰጠኸኝ አምስት መክሊት ወጥቼ ወርጄ ነግጄ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍኩ አለ አምስት መክሊት የተሰጠው። ባለ ሁለት መክሊቱም እንዲሁ ወጥቼ ወርጄ ነግጄ ሁለት አተረፍኩኝ ብሎ አራት አቀረበ። አንድ መክሊት የተሰጠው ግን ሌባ ይወስድብኛል ብዬ ቆፍሬ ደብቄዋለሁ ብሎ አውጥቶ ሰጠ። የተሰጠውን አለተጠቀመበትም ይልቁንም ቀብሮ መልሶ አስረከበው እንጂ በዚህም ጌታ ላለው ይጨመርለታል በማለት ለባለ ዐሥሩ ጨመረለት።

ክርስቲያኖች ሙሉውን የወንጌል ክፍል እንድታነቡ እየጋባዝኩኝ “እስመ ለዘቦ ይዌሥክዎ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ ለሌለው ግን ያለውም ይወሰድበታል” የሚለውን አምላካዊ ቃል ወደ እኛ ሕይወት አምጥተን እንመልከተው ዘንድ ወደድኩኝ። ለእኔና ለእናንተ የተሰጠን ምንድን ነው? እናተርፍበት ዘንድ ዋጋችንም እጥፍ ይሆን ዘንድ ምን ተሰጠን? እኔ ግን እላለሁ ጌታችንንና አምላካችንን እናገለግለው ዘንድ ያልተሰጠን ምንድን ነው? እስኪ እግዚአብሔርን እናመሰግነው ዘንድ ከተሰጡን ሥጦታዎች ሦስቱን እናንሣ፡፡

፩.ሃይማኖት፦ ሐዋርያው ይሁዳ በመልእክቱ “ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” በማለት በተሰጠን ሃይማኖት እንጋደልና እንጠብቃት ዘንድ ይነግረናል። (ይሁዳ ፩፥፫) ክርስቲያኖች እባብ ራሱን እንደሚጠብቅ ራስ የተባለችውን ሃይማኖት ልንጠብቃትና ልንጋደልላት አይገባንምን? ምንስ አትርፈንባት ይሆን? ሁላችን በሃይማኖት ያለን ሰዎች ሃይማኖታችንን እንዳናስወስድ ከፊቱ ይልቅ ልንትጋ ይገባል። ዛሬ ካልበረታንና ካልተጋን ወጥተን ወርደን ሃይማኖታችንን ካልጠበቅን አብዝተን ምግባር ትሩፋት ካልሠራን እንደ ገብር ሀካይ ተወቃሾች ዋጋ ቢሶች ልንሆን እንችላለን ስለሆነም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው በሃይማኖት ያለን ሁላችን ራሳችንን ልንመረምር ይገባል። ላለው ይጨመርለታል ነውና ሃይማኖታችንን ስንጠብቅ እምነት ይጨመርልናል፡፡ ስለዚህ የማይታየውን የምናይባት ገቢረ ታምራት ወመንክራት የምናደርግባት እምነት ትጨመርልን ዘንድ ዘወትር ይበልጥ መትጋት ይኖርብናል።

፪. ሥልጣነ ክህነት፦ እግዚአብሔር መንግሥተ ሰማያትን ሲፈጥር መግቢያ በር አዘጋጅቶ ነው፤ የሠራት መክፈቻ ቁልፉን ደግሞ በምድር ላይ ላሉ ካህናት ሠጥቷቸዋል፡፡ ይህ ምን ይደንቅ ምን ይረቅ? ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ምን ያህል እንደወደደን ተመልከቱ! እንዳመነን እስኪ ጥያቄ ልጠይቃችሁ? እናንተ የቤታችሁንና የሳጥናችሁን ቁልፍ ለማን ነው የምትሠጡ? ለልጆቻችሁ አይደል? “አንተ አቡነ ወአንተ እምነ፤ አንተ አባታችን አንተም እናታችን” የተባለ ጌታም የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻ ቁልፍ ሰጠን።
ካህናት ሆይ የተሰጣችሁን እንዳታስወስዱ ክህነታችሁን አጽንታችሁ ያዙ! በክህነታችሁ አልጫውን ዓለም አጣፍጡ እንጂ እናንተ አልጫ አትሁኑ። ክህነቱን የጠበቀ በክህነቱ በጎችን (ምእመናንን) የጠበቀ ምን ይሰጠዋል ቢሉ ንጉሡ በደብረ ጽዮን ግብዣ ባደረገ ጊዜ በቀኝና ግራ ቆመው ከንጉሡ ጋር አብረው አገልጋይ ይሆናሉ፡፡ (ቅዳሴ አትናቴዎስ)

፫. ሥጋ ወደሙ፦ የሰው ልጅ በሕይወት ይኖር ዘንድ እግዚአብሔር ሕግ ሠራለት፤ ይኸውም ከዕፀ በለስ አትብላ የሚል የሰው ልጅ ግን መብላት ሽቶ ያልተፈቀደለትን በላ የሞትሞትም ሞተ መሓሪው አምላክ ግን ከሞት አዳነን፤ ድኅነታችንን የሚሻ አምላክ ዛሬ ደግሞ እንዲህ አለን፤ መብላትን ፈልጋችሁ ከሆነ ብሉ፤ ስትበሉ ደግሞ እኔን ብሉኝ፤ ጠጡኝ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ በማለት ሕያው ሆነን የምንኖርበትን ሥጋውን ደሙን ሰጠን። ስለሆነም ይህን ሕይወት ልንጠብቀው ይገባናል። እንዴት እንጠብቀዋለን ቢሉ ኃጢአት ባለ መሥራት ነው። ክርስቲያኖች እኛ ሁላችንም የክርስቶስን ሥጋና ደም ተቀብለናል ክርስቶስ የተቀበረበት ጎልጎታ የእኛ ሆድ ነው። እናም የሆድ አዲስ መቃብር የኃጢአት ብልየት ያላገኘው ሊሆን ይገባል። እኔ ግን እላለሁ ኃጢአት በሠራን ቁጥር ክርስቶስን ርቃኑን እየሰቀልነው በንጹሕ በፍታ ገንዘው የቀበሩትን ሳንሆን ልብሱን የገፉትን አይሁድን እየሆን ነውና ከኃጢአታችን እንመለስ።
ለመሆኑ ታማኝ አገልጋይ ማን ነው?

፩. እንደ ሙሴ ለተሾመለት ሕዝብ እኔ ልሙት የሚል፦ “አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ፤ ከባለሟልነትህም አውጣኝ።” (ዘፀ. ፴፪፥፴፩) ታማኝ አገልጋይ “እኔ ልሙት፤ ሌሎች ይዳኑ” የሚል እንጂ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም አይደለም። የሌሎቹ መራቆት፣ መራብ፣ መጠማት፣ መሰደድ፣ መንገላታት፣ ሁል ጊዜ የሚያስጨንቀው ለእነርሱም ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው። ሊቀ ነቢያት ሙሴም ይህንን ሁሉ ያደረገው፣ ባሕርን ከፍሎ ያሻገረው፣ መናን ከሰማይ ያወረደው፣ ፵ ቀንና ፵ ሌሊት የጾመውና፣ የጸለየው፣ ለራሱ አይደለም ለሚመራቸው እስራኤላውያን ነው እንጂ። ይህንን ማድረጉም በእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ አሰኝቶታል። “በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፤ በሕልምም አናግረዋለሁ፤ ባርያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤት ሁሉ የታመነ ነው።” እንዲል (ዘኁ.፲፪፥፮)

፪. እንደ ቅዱስ ዳዊት ያለ የበጎቹን እረኛ፦ “እኔ ባርያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፤ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር፤ በኋላው እከተለውና እመታው ነበር፤ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ ከተነሳብኝም ጉሮሮውን አንቄ እመታው እገድለው ነበረ” እንዲል፡፡ (፩ኛሳሙ. ፲፯፥፴፬) በዚህ ትጋቱም እስራኤልን እንዲጠብቅ ተመረጠ። ለእስራኤልም ፵ ዘመን ነገሠላቸው። እንደ ልቤም ለመባል የበቃ ድንቅ መሪ (አገልጋይ) ሆነ። ዛሬም ታማኝ አገልጋይ እንዲህ ያለ መንጋዎቹን የሚጠብቅ በለመለመ መስክ የሚያሰመራ የጠፉትን ፈልጎ የሚያገኝ ሊሆን ይገባል።

፫. እንደ ዮሴፍ ባለበት ሁሉ በፈሪሐ እግዚአብሔር የሚኖር፦ “ቀዳሚሃ ለጥበብ፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር፤ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” እንደተባለው እግዚአብሔርን ዘወትር በመፍራት በጾምና በጸሎት መኖር መቻል አለብን። (ምሳ.፩፥፯) ዮሴፍ በግብጽ ምድር እያለ የፈርዖንን ሚስት የዝሙት ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፤ የፈርዖንን ሚስት ቁጣና እስራት እግልት ትቶ እግዚያብሔርን የመረጠ ድንቅ አገልጋይ ነው። ዮሴፍ ለፈርዖን በትንሹ ታመነ ፈርኦንም በብዙ ሾመው። (ዘፍ.፴፱፥፯)

እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን እንደ አቅማችን ሥጦታ ሰጥቶናል እንዲሁ ወደዚህ ምድር የመጣ የለም። የሰውነት ክፍሎቻችን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው ዓይን ማየት የምትችለው ከአካል ተለይታ አይደለም ብቻዮን እቆማለሁ ብትል ከብለል ከብለል ስትል ፈርጣ ትቀር ነበር፡፡ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችንም እንዲሁ ጀሮ መስማት፣ ምላስ መቅመስ፣ እግር መራመድ የሚችሉት ከአካል ክፍላችን ሳይጎድሉ እንደሆነ ነገር ግን ሁሉም የተሰጣቸውን አገልግሎት እንዲሠሩ እኛም ክርስትና ኅብረታችን አካል ክርስቶስ ራሳችን እኛ እያንዳንዳችን ሕዋሳት ነን። ከእኛ መካከል ለቤተ ክርስቲያን ዓይን የሆነ አለ፤ ጀሮም የሆነ አለ፤ እግር እጅ የሆነ አለ። ክርስቲያኖች እናንተ ለቤተ ክርስቲያን ምንድን ናችሁ?

በእጃችን ያለው መክሊት ምንድን ነው? እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በሙሴ መሪነት ከባርነት ነፃ ሲያወጣ ሙሴን አገልጋይ አድርጎ ተጠቅሞት ነበር። ሙሴም እስራኤላውያንን እየመራ ወደ ምድረ ርስት ሲጓዝ ከፊቱ የኤርትራን ባሕር አገኘ ሙሴ ተጨነቀ በኋላው ፈርዖንና ሠራዊቱ ከፊቱ ደግሞ የኤርትራ ባሕር በዚያ ላይ ደግሞ የሕዝቡ ቊጣ እጅግ የበረታ ነበር፡፡ ነገር ግን ታማኝ አገልጋይ ነውና ወደ እግዚአብሔር አመለከተ እግዚአብሔር ሙሴን በእጅህ ምን አለ በማለት ነበር የሙሴን ጥያቄ የመለሰት። ሙሴ በያዛት በትር የኤርትራን ባሕር ከፈለ፤ እስራኤላውያንንም አሻገረ፤ እኛም በተሰጠን መክሊት ሁሉ እግዚአብሔርን እናገልግለው ለእርሱም እንገዛው ያን ጊዜ በትንሹ ታምነሀልና በብዙ እሾምሀለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለናል።

አምላካችን በቸርነቱ በሰጠን ሁሉ እርሱን አገልግለን የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን ይርዳን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።