ማኅበረ ቅዱሳን በሰቆጣ ማእከል ለመማር ዐቅም ለሚያንሳቸው ተማሪዎች ከ363 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን በሙያ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት በኩል በማኅበራዊ ቀውሶች የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ ዘርፍ ብዙ ማኅበራዊ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ የሚገኝ ሲሆን በዚህም በድርቅ፣ በመፈናቀልና መሰል ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ማኅበራዊ ቀውሶች በመጎዳታቸው ምክንያት የትምህርት ቁሳቁስ አሟልተው ትምህርታቸውን መቀጠል ለሚቸገሩ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል፡፡
በመሆኑም ለ2019 ዓ.ም የት/ት ዘመንም በመላ ሀገሪቱ በ14 ሀገረ ስብከቶች ለሚገኙ ተማሪዎች ይህ ድጋፍ እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን በሰቆጣ ማእከል ሥር በሚገኙ በሰባት ወረዳዎች በተፈናቃይ ጣቢያዎች ለሚገኙ፣ ከአብነት ት/ት ጎን ለጎን ሳይንሳዊውን ት/ት ለሚማሩ ተማሪዎች በድምሩ 443 ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑ የዜማ ተማሪዎቹ ከአሁን በፊት የመማርያ ደብተር ባለማግኘታቸው እስከ ዛሬ ድረስ ትምህርት ቤት እንዳልተገኙ የተናገሩ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን አስተባብሮ የትምህርት ቁሳቁስ በመደገፉም ተስፋችን ለምልሟል ሲሉ ገልጸዋል።
የስምንት ልጆች እናት የሆኑት ሌላኛዋ ወ/ሮ ዘነቡ ኪሮስ ልጆቻቸውን ለማስተማር ተቸግረው በነበረበት ወቅት ማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ በማድረጉ መደሰታቸውን በመግለጽ ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ለመግዛት ዐቅም በማጣታቸው የሁለቱ ልጆቻቸውን ትምህርት ለማቋረጥ አስበው እንደነበር አስታውሰው ስለተደረገው ድጋፍም ምስጋናቸው አቅርበዋል።
ለዚህ ድጋፍ ከ363,000 (ሦስት መቶ ስልሳ ሦስት ሺህ) ብር በላይ ገንዘብ ወጭ መሆኑን የጠቀሱት የማኅበረ ቅዱሳን ሰቆጣ ማእከል ሰብሳቢ አቶ ፈንታ ዓለምሰገድ ድጋፉ በአሜሪካ ሀገር ከሚገኘው የሜሪላንድ ኆኅተ ምሥራቅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እና ከሌሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ በጎ አድራጊ ወገኖች የተገኘ መሆኑን ገልጸው ፣ ስለድጋፍም በተማሪዎችና በማኅበረ ቅዱሳን ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በዞኑ ከ200 ሺህ በላይ ተማሪዎች የተመዘገቡ ቢሆንም በወቅታዊ የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉትን ጨምሮ ከ80 ሺህ በላይ ተማሪዎች አሁንም የት/ት ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በድጋፍ ርክክብ ወቅት የተገኙት የመንግሥት ኃላፊዎች ተናግረዋል።
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ዲያቆን ሥዩም ገብረ ኪዳን ማኅበረ ቅዱሳን የዋግ ኽምራን ችግር ለዓለም በማሳወቅና መሰል ድጋፍ በማድረግ በኩል የዘወትር አጋዣችን ነው በማለት የተናግረዋል፡፡ እንዲሁም የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሥራ ኃላፊዎች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ሰቆጣ ማእከል ሥራ አስፈጻሚ አባላት እና የመንግሥት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ለእነዚህ እና መሰል ማኅበራዊ ድጋፎችን ለማገዝ ፣ በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሒሳብ ቁጥሮች፡-
1. በአሐዱ ባንክ – 0025393810901
2. በአቢሲንያ ባንክ – 37235458
3. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ – 1000309803648
4. በወጋገን ባንክ – 0837331610101
5. በአዋሽ ባንክ 01329817420400 መጠቀም የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን።
