ሕፃኑ ሰማዕት

ጥር ፲፬፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ግብዝና ደካማ የሆነው የሰውን ሥጋ አሸንፎ፣ መከራን ተቀብሎ፣ ችግርን ተቋቁሞ፣ ፈተናን አልፎ መንፈሳዊ ሕይወትን ለመኖርና ክርስቲያን ለመሆን የሚደረገው ትግል እራሱን የቻለ ተጋድሎ እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው፡፡ እውነተኛ ለሆነው የክርስትና እምነተና ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት የሚከፈለው መሥዋዕትም የተለየ ስፍራ አለው፡፡

እሳት ሰንሰለቱን ሳይፈሩ፣ እራሳቸውን እጅግ ለበዛ ሥቃይ አሳልፈው የሚሰጡ ሰማዕታት የተለየ ክብር አላቸው፡፡ ፍጹም በሆነው የክርስቶስ ፍቅር ዓለም የሚያመጣባቸውን መከራ ለመቀበል በሙሉ ፈቃደኝነት ቆርጠው ተነሥተው ከአላውያን ነገሥታት አልያም ከመኳንንቶች ደግሞም ከከሃድያን ደርሰው በግልጽ ለእውነተኛው ጌታ በመመስከር እውነተኛ ምስክሮች ይሆናሉ፡፡

ከሁሉም የሚደንቀው ደግሞ ከእሳት ምድጃ ቢጥሏቸው፣ ከፈላ ውኃ ውስጥ ቢጨምሯቸው፣ ለአንበሳ እና አውሬ መብል አሳልፈው ቢሰጧቸው እምነታቸው ምንም አለመቀየሩ ነው፡፡ ለሚያምኑበትና ለሚመኩበት ኃይል ብርታት የሚሆን፣ መሐሪና ይቅር ባይ አምላካችን  ጻድቃንን ቅዱሳንን ሰማዕታት ለጠላት አሳልፎ የማይሰጥ ነውና መላእክቱን ልኮ ውኃውን እንደ ውርጭ የሚያቀዘቅዝ፣ እሳቱን ውኃ የሚያደርግ፣ የተራቡ አራዊት የቅዱሳንን እግርና እጅ እንዲልሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ዳግመኛም ለልዩ ልዩ ለሥቃይ አሳልፈው ቢሰጧቸውም የክብር ባለቤት እራሱ ከሰማየ ሰማያት ከእልፍ አላፋት መላእክት ጋር ወርዶ እንዳጽናናቸው እንዲሁም እንዳጸናቸው ገድላቸው ይናገራል፡፡ (ገድለ ቅዱሳን)

በከበረች ሐምሌ ፲፱ ቀን የጌታችን ዕጹብ ድንቅ ሥራ በተገለጠባት ዕለት የሚያስደንቅ ገድል ያደረገ የሦስት ዓመቱ ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስ ገድልም ፍጹም ድንቅ ነው፡፡ በዚህች ቀን በፈላ የጋን ውኃ ውስጥ ቅዱሳኑ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ውኃውም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ይህንም ያደገረው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

የዘመኑ የአረማዊው መኰንን የእለእስክንድሮስ ወታደሮች ከሮም ወደ ወደ ተርሴስ ከእናቱ ጋር ሸሽቶ የገባውን ሕፃኑ ሰማዕት ይዘው ፈጣሪን ክዶ ከጣዖት እንዲሰግዱ በዓይነቱ ቢያሠቃዩትም ስላልተቀበላቸው በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲሆን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡

ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ሕፃኑ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብሎ ጥር ፲፭ ቀን አንገቱ ተቆርጦ የሰማዕትነት አክሊል ተቀብሏል፡፡ በተመሳሳይም እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ሰማዕት ሆናለች፡፡ ግሩምና ድንቅ የሆነው የሰማዕታት ገድል የሁላችንም አስተማሪና አስማሪ ነው፡፡ በእነርሱ ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት የእኛ ኃጢአት ይስተሠረይልናልና፡፡

የቅዱሳኑ ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጥር፣ ፲፭ ቀን