የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የአዲስ ዓመት አባታዊ መልእክት !!!
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የ፳፻፲፰ ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል መግባትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል፣ የቅዱስነታቸው ሙሉ መልእክት የሚከተለው ነው።
ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰንመቱ ዓመተ ምሕረት፤
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ኣሜን!
- በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
- ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
- የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
- በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
- እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት በሙሉ፣
አምላክነቱን ኣውቀን እንድናመልከው ዕድሜንና ዘመናትን የሚሰጠን እግዚብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺህ ዐሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት የርእሰ ዐውደ ዓመት በዓል አደረሰን አደረሳችሁ!
‹‹ወገብረ ኵሎ ኅቡረ ወኵሎ ኣሕዛበ እምአሐዱ ዕጓለ እመሕያው ከመ ይንበሩ ዲበ ኵሉ ገጸ ምድር፤ ወሠርዐ ዕድሜሁ ወዓመታቲሁ መጠነ ይነብሩ በዘየኃሥዎ ለእግዚአብሔር፤ እመ ይረክብዎ፤ ወያደምዕዎ፤ ወኢኮነ ርሑቀ እምኵልነ፡-
ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከኣንድ ፈጠረ፤ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ደረጃ መደባላቸው፤ ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ ኣይደለም›› (የሐ. ሥራ. ፲፯÷፳፮)፤
ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር ትዕይንተ ዓለምንና በውስጡ የሚገኙ ፍጥረታትን የፈጠረ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት የሚታዩና የማይታዩ ተብለው በጥቅል በቅዱስ መጽሓፍ ተገልጸዋል፤
የሰው ልጅ ከፍጥረታት መካከል ሆኖ ከኣንድ ወገን የተገኘ እንደሆነ በዚህ ጥቅስ ተጽፎአል፤
የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ የተለየ ክብርና ደረጃ እንዳለው በቅዱስ መጽሓፍ በተደጋጋሚ ተገልጾአል፤ ልዩ የሚያደርገውም ከኣፈጣጠሩ ጀምሮ ነው፤
ሰው ልዩ ፍጡር መሆኑን ከሚገለጽባቸው መካከል እግዚአብሔር በሦስትነቱ “ሰውን በኣርኣያችንና በኣምሳላችን እንፍጠር” በሚል ልዩ ኣገላለጽ መፈጠሩ፣ ኣፈጣጠሩም በእግዚአሔር መልክና ኣምሳል መሆኑ፣ በእግዚአብሔር እፍታ ሕያው ነፍስ እንዲኖረው መደረጉ፣ በሥልጣንም የፍጥረታት ሁሉ የበላይ ሆኖ መሾሙ ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ ያደርገዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ሰው በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ነው፤ የሁሉም ገዥ ነው፤ በተለይም በዚህ ዓለም ከሰው በላይ ሆኖ የፍጡራን ገዥ የሆነ ፍጡር እንደሌለ ሁላችንም የምናየውና የምናውቀው ነው፤
በላይኛው ዓለምም ቢሆን መላእክትን ጨምሮ ሰማይና ምድርን ከነግሣንግሡ እየገዛ ያለው ሰው የሆነ ጌታ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ገዥ ነው፤ እሱ ሰብእናችንን በፍጹም ተዋሕዶ የተዋሓደ በመሆኑ ሰብእናችን በተዋሕዶተ ቃል ኣምላክ ሆኖ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሆኖኣልና ነው፤
ቅዱስ መጽሓፍም “ወተኰነኑ ሎቱ መላእክት ወሥልጣናት ወኵሉ ኃይል፡- መላእክት፣ ሥልጠናትና ኃይል ሁሉ ተገዙለት” በማለት ይህንን ያረጋግጣል፤ ይህ እግዚአብሔር ለኛ ለሰዎች ያጐናጸፈን ግሩምና አስደናቂ ጸጋ ነው፤ ለዚህም ነው “ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት፡- ሰው ከፍጥረት ሁሉ ይከብራል” ተብሎ የሚዘመረው፤
- የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያት!
እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ሆነን እንድንኖር በእግዚአብሔር ስንፈጠር በሕይወት እንድንኖር ነው፤ እግዚአብሔር በምድር ላይ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሰውን ከኣንድ ፈጠረ የሚለው መጽሓፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮም ይህንን ያመለክታል፤
ሰዎች በምድር ላይ በሕይወት እንዲኖሩ የተፈጠሩ ሆነው እያለ በሕይወት እንዳይኖሩ ማድረግ ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር መጋጨትን ያስከትላል፤በዘመናችን ዓለማችንን እየፈተነ ያለው ተቀዳሚ ፈተና ሰዎች በሕይወት እንዳይኖሩ የማድረግ ዝንባሌ ነው፤
እንደዚህ ዓይነቱ ዝንባሌ በዓለም ባይኖር ኖሮ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ድሆች ባሉበት ዓለም ለሰው ልጅ ሕይወት ማጥፊያ የሚሆን መሳሪያ ለማምረት ኁልቈ መሣፍርት የሌለው ገንዘብ አይወጣም ነበር፤
ይህ ክፉ የዓለም ዝንባሌ እንደ ክፋት ብቻ ሳይሆን እንደ ሞኝነትም የሚያሳይብን ነው፤ማንኛችንም ሰዎች ‹‹ሰው ማጥፋት ይሻላል ወይስ ማዳን›› ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ምን እንደሚሆን ይታወቃል፤
ነገር ግን ኣንፈጽመውም፣ ሞኝነት የሚያሰኘውም እዚህ ላይ ነው፤ የሚጠቅመንንና የመሰከርንለትን ትተን የሚጐዳንንና፣ ያልመሰከርንለትን እንፈጽማለንና ነው፤ ስለሆነም በሕይወት እንዲኖር የተፈጠረውን ሰው በሕይወት የመኖር መብቱን ከመንፈግ መቆጠብ የኣዲሱ ዓመት ትልቁ ኣጀንዳ ኣድርገን ብንወስድ ለሁላችንም ይበጀናልና እንቀበለው እንላለን፤
- የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!
ሰው በሕይወት እንዲኖር በእግዚአብሔር ሲፈጠር እግዚአብሔርን የሚፈልግበትና የሚያገኝበትን ዕድሜና ዘመንም እንደተሰጠው ከተጠቀሰው ክፍለ ንባብ እንገነዘባለን፤ መቼም እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረ በስራ ለስራ እንደሆነ የምንስተው ኣይሆንም፤
እግዚአብሔር ዕድሜና ዘመን ለሰዎች ሲሰጥ ሊሠራበት ነው፤ ስራውም መንፈሳዊና ዓለማዊ ነው፤ ተደምሮ ሲታይ ደግሞ ለሰው ጥቅም የሚውል ነው፤
እኛ ሰዎች በተሰጠን ዕድሜና ዘመን በመንፈሳዊው ሥራችን እግዚአብሔርን ፈልገን እንድናገኝ ተፈጥረናል፤ እሱን ማግኘት የማይቻል የሚመስለን ካለንም እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም ተብለናልና በመንፈስ ከፈለግነው በመንፈስ እንደምናገኘው መጽሐፉ ያስረዳናል፤ ስለሆነም በተሰጠን ዘመን ይህንን ሥራ መሥራት ይኖርብናል፤
በሌላ በኩል ለኑሮኣችን የሚያስፈልገንን ፍጆታ በበቂ ሁኔታ እንድናገኝ ላባችንን ኣንጠፍጥፈን መስራት ይገባናል፤ ይህም ከሰራን ያለጥርጥር የምናገኘው ነው፤ ሁለቱም የጐደሉብን በኛ አስተሳሰብ፣ አሠራርና አጠቃቀም እንጂ እግዚአብሔር ሳይፈቅድልን ቀርቶ ወይም ነፍጎን አይደለም፤
እግዚአብሔር የሰጠን ምድር በልዩ ልዩ ሀብተ ጸጋ የተሞላች እንደሆነች፣ የምንረግጠው መሬትም ወደ ሀብት መቀየር እንደሚቻል የተረጋገጠ ነው፤
ነገር ግን እኛ በምንራመድበት በእግራችን ሥር ያለውን ሀብት ትተን በሩቅ ያለውን ስንመለከት ሁሉን ያጣን ሆነን በችግር ወድቀን እንገኛለን፤ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ እየተፈታተነን ያለው ይኸው የተሳሳተ እሳቤ ነው፤
ኢትዮጵያ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ኣድርገን በማመን በእኩልነት፣ በኣንድነትና በስምምነት ከመጠቀም ይልቅ ያ የኔ ነው ያም የኔ ነው በሚል ኣባባል ምን ያህል ዋጋ እየተከፈለ እንደሆነ እያየን ነው፤
ይህ ግለኝነት ያየለበት አስተሳሰብ ገታ አድርገን በእኩልነትና በአብሮነት የሚያሳድገንን አስተሳሰብ በእጅጉ ይጠቅመናል፤ ይህንንም የአዲሱን ዓመት ምርጥ እሳቤ ኣድርገን ብንወስድ የተሻለ መግባቢያ ሊሆን ይችላል፤ አዲሱ ዓመት በኣዲስ እሳቤ ካላጀብነው አዲስ ሊሆን አይችልምና ነው፤
ስለሆነም ኣዲሱን ዓመት መልካም በሆነ ኣዲስ ኣሳብ ፣እግዚአብሔርንና ሰውን በሚያገናኝ ቅዱስ ተግባር፣ በልማት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በዕርቅና በስምምነት እንድንቀበለው ወቅታዊ ጥሪያችን ነው፤
በመጨረሻም፣ አዲሱ ዓመት ለሀገር ሰላምና ልማት፣ ለሕዝቦች ኣንድነትና ስምምነት እንደዚሁም ኣለመግባባትን በፍትሕና በዕርቅ ለመፍታት ከልብ የምንተጋበት መልካም የስኬት ዘመን እንዲሆንልን እንጸልይ፣ በዚህም መላ ሕዝባችን ጠንክሮ እንዲሠራ ለመላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፤
እግዚአብሔር ኣምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
መስከረም ፩ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ