እኔስ ሰው አማረኝ

በመዝሙርና ሥነ-ጥበባት ክፍል

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የጸና
ጀግና ሰው አማረኝ ጠላት አሳፋሪ
ንጽሕት ድንግል ብሎ ለእምነቱ መስካሪ

ነቢያት በመጋዝ የተሰነጠቁት
ሐዋርያት ቁልቁል የተዘቀዘቁት
ሰማዕታት በእሳት የተለበለቡት
ቅዱሳን በገዳም ደርቀው የተገኙት
ምሥጢሩ ምን ነበር አበው ይናገሩት

ይናገር ዝቋላ ግሸን ላሊበላ
የቅዱሳንን ዐፅም ለምን እንዳልበላ
ዋልድባ ይናገር ዜጋመልም ሳይቀር
እንባቸው መፍሰሱ ለምን እንደነበር

ነበር ወይ ፈልገው ሹመት ሽልማት?
ወይስ ሀብት ንብረት የተሟላ ቤት?
ወይስ አምሯቸው ነው ፈልገው መሞት?
እናንተ ገዳማት ምሥጢሩን አውሩት

ጐበዝ ሰው አማረኝ በእምነቱ የጸና
ምግባር ሃይማኖቱ በእጅጉ የቀና

እንጦንስ የወለደው በምግባር በእምነት
ተምሮ ያደገ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት

የጊዮርጊስ ወገን የት ነው የማገኘው?
በመሀል ከተማ በአራዳ ውስጥ ነው?
በደብረ ሊባኖስ ወይስ በደብረ ዳሞ ነው?
ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ሰው አማረው
የሃይማኖት አርበኛ የትነው የማገኘው?

ልግባ ወይ ዋልድባ ጫካ ካለበት
ማኅበረ ሥላሴ ከቅዱሳን ቤት?
አክሱም ግሸን ማርያም ከቃል ኪዳን ቦታ
ይገኛል ወይ ጀግና ጠላት የሚረታ?
ፈሪሃ እግዚአብሔር በልቡ ያደረ
ቤተ ክርስቲያንን ያልተደፋፈረ

የት ነው የማገኘው ለሃይማኖቱ ሟች
ለተዋሕዶ እምነት ጠበቃ ተሟጋች

እስኪ ጠይቋቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብ ምን ነበር ምሥጢሩ?
የክርስቲያን ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ?
መቃብሩ ሲከፈት አበው ይመስክሩ

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ሰው አማረው
በእምነቱ የጸና የትነው የማገኘው?
በጐችን ከተኩላ ነቅቶ የሚጠብቅ
መከራ ቢከበው ከቶ የማይሰቃቅ
የሃይማኖት አርበኛ ቆራጥ ሰው ገበሬ
እንደዚያ እንደ ጥንቱ ይገኛል ወይ ዛሬ?

የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው
የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው
የዓለም አሸክላ ልቡን ያልማረከው
የክርስቶስ ወዳጅ እርሱ ጀግና ማነው?

እንደ መስኖ ውኃ ከነዱት መነዳት
ዓላማው ምንድነው የዘመኑ ወጣት

ጾም ጸሎት ነበረ የሃይማኖት ጋሻ
መልከስከስ ምንድነው እንደ አበደ ውሻ?

ምሥጢርን ከምሥጢሩ አንድ አድርጐ ቀምሮ
ወልድ ዋሕድ ብሎ ስለሃይማኖት መስክሮ
እንጦንስን መቃርስን በልቡ ያኖረ
ከአትናቴዎስ ከቄርሎስ ጥበብ የተማረ

ድንግል እመቤቴ ብሎ የሚመሰክር
መሆኗን የሚያምን ማኅደረ እግዚአብሔር

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የጸና
ዐይኔን ሰው አማረው ጀግና ሰው ገበሬ
ሃይማኖት መስካሪ እንደ ጥንቱ ዛሬ