የዐብይ ጾም ስብከት /ክፍል 6/

መጋቢት 20/2004 ዓ.ም.

በአያሌው ዘኢየሱስ

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

 

በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ውስጥ የምናነበው ወንጌል የሚያሳስበን ስለ በጎና ታማኝ አገልጋይ የተነገረውን ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ የወንጌል ንባብ ውስጥ ጌታ በምሳሌ አድርጎ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ሰዎች እንደ ሥራቸው እንደሚዳኙ በሰፊው አስተምሯል፡፡ በዚህ ምሳሌ ውስጥ አንድ ጌታ ለሦስት ባሮቹ ለእያንዳንዳቸው እንደ አቅማቸው ለአንዱ አምስት መክሊት፣ ለአንዱ ሁለት መክሊትና ለሌላው ደግሞ አንድ መክሊት ከሰጣቸው በኋላ ነግዱና አትርፉ በማለት እርሱ ወደ ሌላ አገር መሄዱ ተገልጦአል፡፡ በዚህም መሠረት አምስት መክሊት የተቀበለው የመጀመሪያው ባሪያ በተሰጠው አምስት መክሊት ቆላ ወርዶ ደጋ ወጥቶ ከነገደ በኋላ አምስት ተጨማሪ መክሊቶችን በማትረፍ አኖረ፡፡ ሁለት መክሊቶችን የተቀበለው ሁለተኛው ባሪያም በተሰጡት አምስት መክሊቶች ከነገደ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አስቀመጠ፡፡ ሦስተኛው ባሪያ ግን ከእነዚህ ሁለት ባሪያዎች በተለየ ሳይወጣና ሳይወርድ፣ ሳይደክምና ሳያተርፍ በአቅሙ መጠን በተሰጠው አንድ መክሊት ሥራ ሳይሠራ እንዲሁ ወስዶ ጉድጓድ በመቆፈር ቀበረው፡፡

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ለእነዚህ ሦስት ባሪያዎች በመጠን የተለያዩ መክሊቶችን ሰጥቶ ወደ ሩቅ አገር ሄዶ የነበረው ጌታቸው ወደ እነርሱ ተመልሶ መጣ፡፡ ከዚያም እያንዳንዳቸው በየተራ ወደ እርሱ እያስገባ በተሰጧቸው መከሊቶች ምን እንደሠሩ ይጠይቃቸውም ይቆጣጠራቸውም ጀመር፡፡ በዚህ መሠረት አምስት መክሊቶችን የተቀበለው የመጀመሪያው ባሪያ በጌታው ፊት ቀርቦ በተሰጡት አምስት መክሊቶች ሌሎች ተጨማሪ መክሊቶችን በማትረፍ በድምሩ አሥር መክሊቶችን ለጌታው አስረከበ፡፡ ሁለተኛውም እንዲሁ በተሰጡት ሁለት መክሊቶች ሌሎች ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አሁን በእጁ ላይ ያሉትን አራት መክሊቶች ለጌታው አስረከበ፡፡ በዚህ ጊዜ የእነዚህ ሁለት ባሪያዎች ጌታ በእነርሱ ደስ በመሰኘት ለሁለቱም አንተ መልካም፣ በጎና ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ ስለምሾምህ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ በማለት ወደ መንግሥቱ አስገባቸው፡፡

ምንም ሥራ ሳይሠራና ሳያተርፍ የተሰጠውን አንድ መክሊት ጉድጓድ ውስጥ የቀበረው ሦስተኛው ባሪያ ግን ባዶ እጁን መቅረቡ ሳያንሰው በድፍረት ጌታ ሆይ፡- ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ስለማውቅና ስለ ፈራሁ መክሊትህን ጉድጓድ ቆፍሬ በመቅበር አቆይቼልሃለሁና እነሆ ተረከበኝ የሚል መልስ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ስለ ተቆጣ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፤በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ሰው መሆኔን ታውቃለህን? ካወቅህ ደግሞ ገንዘቤን ለሚነግዱበት ወይም ለሚለውጡ ሰዎች በመስጠት እነርሱ እንዲያተርፉበት ማድረግና እኔ ተመልሼ ስመጣ ከነትርፉ ከእነርሱ መቀበል እንድችል ማድረግ ትችል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ሳታደርግ ጭራሹኑ በድፍረት እነዚህን በእውነት ላይ ያልተመሠረቱ ክፉ ቃላትን ስለ ተናገርህ ቅጣት ይገባሃል በማለት ለወታደሮቹ፡- ያለውን መክሊት ውሰዱና አሥር መክሊት ላተረፈው ጨምሩለት፤ ላለው ይሰጠዋል ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ ስለዚህ የማይጠቅመውን ባሪያ ወደ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ ውጪ አውጡት በማለት አዘዛቸው፡፡

ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሳለ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ ትምህርቱን ቃል በቃል ወይም በሰምና ወርቅ ወይም በምሳሌ አስተምሮአቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት እርሱ ይህን ትምህርት ያስተማረው በምሳሌ ነው፡፡ ጌታ ትምህርቱን በምሳሌ ያስተምር የነበረው አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት «አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ተምሳሊት እናገራለሁ፡፡» (መዝ 77፥2) ተብሎ የተነገረውን የትንቢት ቃል ለመፈጸምና ቃሉን የሚሰሙት ተማሪዎቹ የሚማሩት ትምህርት ሳይገባቸው እየተጠራጠሩ ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ ለማድረግ ነበር፡፡ በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ከሰባት በማያንሱ ምሳሌዎች ስለምትመጣው መንግሥቱ በስፋት አስተምሯል፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌልን ቃል በዚህ ዓለም ላይ ሲዘራ ዘሩ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ በተሠማሩ ሰዎች ልብ ውስጥ በተለያዩ ምሳሌዎች አማካኝነት ይዘራ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑም ጌታ ቃሉን ለገበሬዎች በዘርና በእንክርዳድ እንዲሁም በሰናፍጭ ቅንጣት፣ ለእናቶች በእርሾ፣ ለነጋዴዎች በመዝገብና በዕንቁ፣ ለዓሣ አጥማጆች በመረብ. . . ወዘተ እየመሰለ በምሳሌ ያስተምራቸው ነበር፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በአሥሩ ቆነጃጅት፣ በሰርግ ቤት፣ በበግና በፍየል. . . ወዘተ በተመሳሳይ ሁኔታ ስለ መንግሥቱ በስፋት በምሳሌ አስተምሯል፡፡ ጌታ ይሁን ያደርግ የነበረው ትምህርቱ ለተማሪዎቹ እንዲብራራላቸውና ግልጽ እንዲሆንላቸው ነበር፡፡

በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ሰንበት ውስጥ የምናነበው ንባብ፣ የምንሰበከው ስብከትና የምንዘምረው መዝሙር የሚነግረንም ስለ አንድ በጎናና ታማኝ ባሪያ በምሳሌ የተነገረውን ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የወንጌል ቃል መሠረት «ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው» ተብሎ የተጠቀሰው ሰው በዳግም ምጽአቱ ወደዚህ ምድር ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት ወደ ቀደመ ክብሩ የተመለሰውን ቅን ፈራጅ አምላካችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት ባሪያዎች የሚወክሉት ምዕመናንን ወይም እኛን ነው፡፡ መክሊት የተባለው በጎ የሚያሰኘው በጎና መልካም ሥራ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሪያዎች ወይም አገልጋዮች የሚመሰሉት ሥራን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረው የያዙትን ጻድቃን ሲሆን መክሊቱን ጉድጓድ በመቆፈር የቀበረው ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ደግሞ ምግባርና ሃይማኖት የሌላቸው የኃጢአተኛ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት በመካከላችን ተገኝቶ ስለ መንግሥተ የምትናገረውን ወንጌል ከሰበከልን በኋላ ለእያንዳንዳችን አንድ፣ ሁለትና አምስት መክሊቶችን በመስጠት ለፍርድ እስከምመጣ ደረስ ነግዳችሁና አትርፋችሁ ጠብቁኝ ብሎን በዕርገቱ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ  ሄዷል፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ከእግዚአብሔር የተለያዩ መክሊቶችን ተቀብለናል፤ እንድንነግድባቸውና እንድናተርፍባቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- «ለአንዱ ጥበብን መነገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፤ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፤ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፤ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፤ለአንዱም ትንቢትን መናገር፤ለአንዱም መናፍስትን መለየት፤ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፤ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል፡፡» 1ኛ ቆሮ.12፥8-11፡፡

እግዚአብሔር ለልጆቹ የሰጣቸው መክሊት ይህ ብቻ አይደለም፤ለአንዱ መስበክ ለሌላው የማስተማር ለሌላው የመቀደስ ለሌላው የመዘመር ለሌላው የመባረክ ለሌላው የማገልገል. . . ወዘተ መክሊቶችን ወይም ስጦታዎችን ሰጥቶአል፡፡ በፍርድ ቀን ሁሉም ሰው የሚፈረድበት በተሰጠው መክሊት ትርፍ መሠረት ነው፡፡ አንድ ሰው የሚሰጠው አንድ መክሊት ብቻ አይደለም፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ መክሊቶች ሊሰጡት ይችላል፡፡ እንደ ምሳሌ አድርገን ብንወስድ ለመጥምቀ መለኮት የተሰጡት መክሊቶች ብዙ ናቸው፤ በብሕትውና መኖር፣ ማጥመቅ፣ ነቢይነት፣ ንስሓ ተቀባይ ካህን፣ ስብከት፣ የሰዎችን ልብ ለጌታ የተስተካከለ መንገድ አድርጎ ማዘጋጀት፣ . . .፡፡ ዮሐንስ በተሰጡት በእነዚህ ሀብቶቹ ወይም መክሊቶቹ የብዙዎችን ልብ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ እጅግ ስላተረፈ ጌታ ስለ እርሱ «ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤. . .» (ማቴ.11፥11) በማለት መስክሮለታል፡፡

ይህን ስብከት ስለ ታማኝ አገልጋይ የሚናገረውን የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ስብከት ሳዘጋጅ ከሦስት ቀናት በፊት በሞት የተለዩንን በጎና ታማኝ አገልጋይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ መንፈሳዊ ሕይወት እያሰብሁ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለእኚህ ታላቅ አባት ብዙ መክሊቶችን ስለ ሰጧቸው በእነዚህ መክሊቶች ብዙ ሰዎችን ለእግዚአብሔር አፍርተውለታል፡፡ ይህን በማስመልከት ስለ እርሳቸው የአገልግሎት ዘመናት በሚናገር መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ተብሎ የተጻፉትን ቃላት አንብቤያለሁ፡- «ከምንም ነገር በላይ ቅዱስነታቸው ታታሪ ሰባኪ፣ እጅግ ጎበዝ መምህር፣ ጥበበኛ ጸሐፊ፣ ተሰጥኦ ያላቸው ገጣሚ፣ መናኝ መነኩሴ፣ የዋህ ባሕታዊ፣ የሚያነቃቁ ጳጳስ፣ ታላቅ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናንን በስብከቶቻቸው ያነሣሡና በታላላቅ ሥራዎቻቸው የሚመሩ ብሩህ ኮከብ ናቸው፡፡» መክሊት ተቀብሎ በተቀበለው መክሊት ሌሎች መክሊቶችን የሚያተርፍ ሰው በፍርድ ቀን በኢየሱስ ክርስቶስ «መልካም፤ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙም እሾምሃለሁ፤ወደ ጌታህ ደስታ ግባ. . .» ይባላል፡፡ መክሊቱን መሬት ቆፍሮ የሚቀብረው አገልጋይ ግን በውጪ ባለው ጨለማ ውስጥ ተጥሎ በዚያ በልቅሶና ጥርስ በማፋጨት እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

ዛሬ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉም አንድ ከሆነው ከእግዚአብሔር መንፈስ የተለያዩ ስጦታዎችን ወይም መክሊቶችን ተቀብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም መክሊቱን ቆፍሮ ስለ ቀበረ ለእግዚአብሔር ምንም ሊያተርፍ አልቻለም፡፡ በወንጌል ላይ የተጠቀሰው ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ የተሰጠውን መክሊት ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠራበት ወይም ሳይነግድበት ወይም ሳያተርፍበት በመሬት ውስጥ ቆፍሮ በማስቀመጡና ጌታው ሲመጣ በማስረከቡ በዚህ ዘመን ከምንገኝ ሰዎች እጅጉን ይሻላል ብዬ አስባለሁ፤እኛ መክሊቶቻችንን ጠብቀን በማቆየት ለእግዚአብሔር ማስረከብ እንኳ አልቻልንምና፡፡ ዛሬ የተቀበለ ሁሉ ቀብሯል ወይም ጥሏል፡፡ አንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ በተሰጠው የመቀደስ መክሊት መቀደስ ሲገባው የሚዘፍን ከሆነ መክሊቱን ጥሏል፡፡ አንድ የመዘመር መክሊት የተሰጠው አገልጋይ ለእግዚአብሔር መዘመር ሲገባው ሰዎችን የሚያማ ወይም የሚሳደብ ከሆነ መክሊቱን ጥሏል፡፡   ትክክለኛውን የወንጌል ትምህርት እንዲያስተምርና ሰዎችን በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲያስገባ የማስተማር መክሊት ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለ ሰው በዚህ መክሊቱ የኑፋቄ ስብከት በመስበክ የዋህ የሆኑ ሰዎችን ወደ ሲዖል ለመምራት የሚያስተምርበት ከሆነ መክሊቱን ሙሉ ለሙሉ ጥሎታል ወይም አጥፍቶታል እንጂ አልቀበረውም፡፡ በተሰጠው የመባረክ መክሊት ወይም ሥልጣን ምዕመናንን መባረክና ኃጢአታቸውን መናዘዝ ሲገባው ለጥንቆላ ሥራ ተቀምጦ እፈርዳለሁ የሚል ከሆነ መክሊት የተባለ ክህነቱን አቃሎአታል አጥፍቷታልም እንጂ አልቀበራትም፡፡ በእግዚአብሔር መድረክ ላይ ወንጌልን መናገር ሲገባው ተራ ወሬ ወይም ፖለቲካ የሚደሰኩር ከሆነ ይህ ሰው መክሊቱን ጥሏል፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ፡፡ ለዚህ ነው በዚህ ዘመን ውሰጥ ያለን ሰዎች መክሊቱን ከቀበረው ሰው የምናንስ ክፉና ሃኬተኛ ሰዎች ነን እንጂ ከእርሱ የምንሻልበት ምንም ዓይነት ነገር የለንም የምንለው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ በወንጌል እንደ ተነገረለት ለጻድቃን ሊፈርድላቸውና በኃጥአተኞች ላይ ሊፈርድባቸው ይመጣል፡፡ ከፍርዱ በፊት ሁላችንንም በሰጠን መክሊቶች መጠን ይቆጣጠረናል፡፡ አንድ መክሊት የተሰጠው ሰው ሁለትና ከዚያም በላይ ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ ሁለት የተሰጠው ደግሞ ሁለት ወይም ከዚያም በላይ የሆኑ መክሊቶችን ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ አምስት የተቀበልነው ደግሞ አምስትና ከዚያም የሚበልጡ መክሊቶችን ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ ታዲያ እኛ ያተረፍነው ምንድር ነው? በዕርቅ ፋንታ ጠብን የምናባብስ ስለሆንን በመክሊታችን ሰዎችን አጉድለናል እንጂ ማትረፍ አልቻልንም፡፡ በመመረቅ ፋንታ የምናረገም ከሆንን መክሊታችንን ጥለናል፡፡ በመጸለይ ፋንታ ለመደባደብ የምንጋበዝ ከሆንንም የተሰጠንን መክሊት አጥፍተናል፡፡ ታዲያ የገብርኄርን ሰንበት ዛሬ ስናከብር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ እያንዳንዳችንን ታተርፉበት ዘንድ የሰጠኋችሁን መክሊት እስከነ ትርፉ አስረክቡኝ ቢለን ምንድር ነው የምናስረክበው? የምንሰጠውስ መልስ ምንስ የሚል መልስ ነው?

በወንጌል ላይ የተጠቀሰው ያ ሃኬተኛ ባሪያ መክሊቱን መቅበሩ ሳያንሰው  ለጌታው የሰጠው ክፉ መልስ ለከፍተኛ ቅጣት ዳርጎታል፡፡ እርሱ ለጌታው «ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፡፡» የሚል መልስ ነበር የሰጠው፡፡ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ከዚህ ባሪያ ጋር የሚመሳሰል ጠባይ አላቸው፤ እነርሱ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምንም ነገር ሳያውቁ የእግዚአብሔርን ጠባይና እውቀት በእነርሱ የእውቀት ሚዛን ላይ ይሰፍራሉና፡፡ አንድ ሰው በጠና ሕመም ከታመመ ወይም ከልጆቹ አንዱ በሞት ቢለየው ወይም ንብረቱን በእሳት ቃጠሎ ቢያጣ ይህን አደጋ ያደረሰበት እግዚአብሔር እንደ ሆነ አድርጎ ለእርሱ በእርሱ ላይ ለእርሱ የማይገባ ቃላትን የሚሰነዝር ሰው አለ፡፡ ከዚህ አንጻር እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ሕልውና ላይ በመምጣት «እግዚአብሔር ቢኖር ኖሮ ይህ ሕመም ወይም አደጋ በእኔ ላይ አይደርስም ነበር፡፡» ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ «እግዚአብሔር እንደዚህ የጨከነብኝ ምን አድርጌው ነው;» እያሉ እግዚአብሔርን እንደ ሃኬተኛው ባሪያ ጨካኝ የሚያደርጉት ሰዎች አሉ፡፡ እግዚአብሔርን «የለህም» ወይም «ጨካኝ» ማለት ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨለማ የሚያስገባ ክፉ መልስ ነው፡፡ ሰዎች ሁለት ጊዜ ሳያስቡና አንድ ጊዜ ሳያውቁ በቸልተኝነት በእግዚአብሔር ላይ የሚሰነዝሩአቸው ቃላት ከባድ ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡

የጻድቁ የኢዮብ ሚስት እርሷ በእግዚአብሔር ላይ በልቧ ስትሰነዝራቸው የነበሩትን ቃላት ባሏም እንደ እርሷ ይሰነዝራቸው ዘንድ «እግዚአብሔርን ስደበውና ሙት» በማለት በእርሱ ላይ ልታነሣሣው ሞክራ ነበር፡፡ ሊነቀፍ ወይም ሊወገዝ ወይም ሊኮነን የሚገባው ሰይጣን እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቸር፣ ርኅሩኅ፣ ታጋሽ፣ ይቅር ባይ፣ መዓቱ የራቀና ምሕረቱ የበዛ አምላክ ነው እንጂ «ጨካኝ» አምላክ አይደለም፡፡ እርሱ በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ያልዘራነውን የጽድቅ ፍሬ እንድንዘራና እንድናጭድ፤ያልበተንነውንም መልካም ዘር በመበተን በፍርድ ቀን ምርቱን እንድንሰበስብ የሚፈልግ ጌታ ነው፡፡ እኛ ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ በማፍራት የእነዚህ ፍሬዎችን ምርት በመሰብሰብ ሰማያዊ መንግሥቱን እንድንወርስ ስለሚፈልግ «ጨካኝ» አምላክ አይደለም፡፡ እርሱ ለሚያምኑትና ለሚታመኑት ሁሉ የሚታመን ታማኝ ጌታ ነው እንጂ የሚያምኑትን የሚክድ «ጨካኝ» ፈጣሪ አይደለም፡፡ ካልዘራበት የሚያጭድና ካልበተነበት የሚሰበስብ ሰው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፤ ጨካኝ፣ ከሀዲና የማይታመንም ሰው ነው፡፡

ዛሬ እግዚአብሔር በጎና ታማኝ አገልጋይ አጥቶአል፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታመን አገልጋይ አጥታለች፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ «ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም፡፡» (መዝ 13፡3) ተብሎ የተነገረው ለዚህ ዘመን አገልጋዮች ነው፡፡ ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔርና ለቤተ ክርስቲያን ታማኝ ሊሆን አልቻለም፡፡ በጥቂቱ ታምኖ በብዙ ላይ ሊሾም የሚችል ሰው ስለ ጠፋ እግዚአብሔር አምላክ የሰው ያለህ እያለ ነው፤ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ፡፡ አገልጋዩም ሆነ ምዕመኑ በአንድነት ተባብሮ ከዳተኛ ሆኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በቃሉ የሚገኝ ሰው ማግኘት ተቸግራለች፡፡ ሁሉም የተሰለፈው የቤተ ክርስቲያንን ሙዳይ በመቦጥቦጥ የግል ብልጽግናውን ለማዳበር እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ ለምዕመናን መዳንና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ሲል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አገልጋዮችን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሾማቸውና የሚሾማቸው ግን ራሳቸውን፣ ቤተ ክርስቲያንንና መንጋውን ከጥፋት እንዲጠብቁ ነው፤ ሐዋ.20፥28፡፡ ለመጠበቅ ተሾሞ የሚያጠፋ ጠባቂ ዕድል ፈንታውና ዕጣ ተርታው ትሉ በማያንቀላፋበትና እሳቱ በማይጠፋበት ዘላለማዊ ሲዖል ውስጥ ነው፡፡ ይህን የሚያደርግ አገልጋይ ቅጣቱ ዘላለማዊ መሆኑን ከወዲሁ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡ እርሱ ጌታው በዳግም ምጽአቱ እስከሚገለጥ ድረስ መንጋውን በመመገብ፣ ውኃ በማጠጣትና በማሳረፍ ፋንታ ለራሱ ብቻ የሚበላና የሚጠግብ፤ የሚጠጣና የሚሰክር፤የሚያርፍና ዘና የሚል ከሆነ ጌታው ባላሰባት ሰዓት ተገልጦ ከሁለት ይሰነጥቀዋል፤ዕድሉንም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ባለበት ጨለማ ውስጥ ያደርግበታል፤ ማቴ. 24፥45-51፡፡ ዛሬ ጌታ አይመጣም ወይም ይዘገያል ብሎ ቤተ ክርስቲያንን በተለያያ መልኩ የሚዘርፍና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን አገልጋይም ሆነ ተገልጋይ ከዚህ ጠባዩ ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡  የቤተ ክርስቲያን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለው ለዚህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በጥፊ የተመታላት፣ ርኩስ ምራቅ የተቀበለላት፣ የሾህ አክሊል የተቀዳጀላት፣ የተንገላታላትና ሞተላት ለዚህች ቤተ ክርስቲያንና ለዚህ ምዕመን ነውና አገልጋዮች በጎና ታማኞች ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡

ይቆየን፡፡

በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡