gebi 2006 1

ማኅበረ ቅዱሳን ከ40,000 በላይ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን አስመረቀ

 ሐምሌ 15 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

ማኅበረ ቅዱሳን በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ከ40,000 በላይ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን አስመረቀ ፡፡

gebi 2006 1ማኅበረ ቅዱሳን ካሉት 46 የሀገር ውስጥ ማእከላት መካከል በ38ቱ ማእከላት አስተባባሪነት በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች አብዛኛዎቹ ዩኒቨርስቲዎች ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከዩኒቨርስቲ ትምህርታቸው በተጓዳኝ መንፈሳዊ ዕውቀትን እንዲገበዩ በማድረግ ወደ ሥራ በሚሰማሩበትም ወቅት ራሳቸውን በመንፈሳዊውም በዓለማዊው ዕውቀት አዳብረው፤ በሥነ ምግባር ታንጸው ቤተ ክርስቲያንና ሀገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ እንደሚረዳቸው በርካታ ተመራቂ ተማሪዎች ይገልጻሉ፡፡

የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ካስመረቃቸው 250 ተማሪዎች መካከል 50ዎቹ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ 17ቱ በማዕረግ የተመረቁ ናቸው፡፡ በአምቦ ዩኒቨርስቲ የወሊሶ ካምፓስ በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቀው የሜዳልያ ተሸላሚ ከሆኑት 6ቱ ተመራቂዎች ውስጥ 4ቱ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መሆናቸውን ከየማእከላቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ሁለት ትምህርት ክፍሎችን ብቻ በዚህ ዓመት የሚያስመርቅ ሲሆን፤ ከሚመረቁት 70 ተማሪዎች መካከል 14ቱ ከፍተኛ ማዕረግ የሚመረቁ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ሲሆኑ ከ1-3 በመውጣትም የሜዳልያና የዋንጫ ተሸላሚዎች ናቸው፡፡ በተያያዘ ዜና ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል ከ7 ዮኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች 3 የወርቅ ሜዳሊያ 2 ዋንጫ ያገኙት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ናቸው፡፡