aleka 2006 1

ሊቁ አለቃ ወልደ ሰንበት ተገኝ አረፉ

 ሐምሌ 15 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

aleka 2006 1የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ እንዲሁም በርካታ ጳጳሳትንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በማስተማር የሚታወቁት ሊቁ አለቃ ወልደ ሰንበት ተገኝ በተወለዱ በ99 ዓመታቸው ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. አረፉ፡፡ ስርዓተ ቀብራቸው ለ35 ዓመታት ሲያገለግሉበት በነበረው ሽሮ ሜዳ መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት፤ ቤተሰቦቻቸውና ምእመናን በተገኙበት ሐምሌ 9 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ተፈጽሟል፡፡

አለቃ ወልደ ሰንበት ተገኝ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመማር፤ እንዲሁም ወንበር ዘርግተው በማስተማር በርካታ ሊቃውንትን በማፍራት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቀሰሙትን እውቀት ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍ የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡

በተለያዩ ቦታዎች በመማርና በማስተማር በርካታ ዓመታትን አሳልፈው ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ በሚገኘው መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እስከ እለተ እረፍታቸው ድረስ በመሪ ጌታነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡አለቃ ወልደ ሰንበት ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 19ኛ ዓመት፤ ቁጥር 22/ ቅጽ 19፤ ቁጥር 254 ከነሐሴ 1- 15 ቀን 2004 ዓ.ም. እትም ለአብርሐም ቤት ዓምድ የሰጡትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቀናብረነዋል፡፡

ሰኔ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. “ዝክረ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ” የተሰኘ መርሐ ግብር በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አስተባባሪነት በቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ ጥናት አቅራቢነት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ተካሒዶ ነበር፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ከተገኙት ተጋባዥ እንግዶች መካከል አንድ አባት ላይ ዐይኖቼ አረፉ፡፡ የሀገር ባሕል ሙሉ ነጭ ልብስ ለብሰው፤ከላይ ጥቁር ካባ ደርበዋል፡፡ ጥቁር መነጽር አጥልቀው፤ ከዘራቸውን ተመርኩዘው በዕድሜ የበለጸገውን ሰውነታቸውን በጥንቃቄ እየተቆጣጠሩ፤ በቀስታ እግሮቻችን አንስተው እየጣሉ ወደ አዳራሹ ዘለቁ፡፡

ውስጤ ማነታቸውን በማወቅ ጉጉት ተወረረ፡፡ ይዟቸው የመጣው ወንድም ከመድረኩ ፊት ለፊት ካለው የመጀመሪያ ረድፍ ወንበር ላይ እንዲቀመጡ ረዳቸው፡፡ ተከትያቸው በመግባት ሲረዳቸው የነበረውን ወንድም ማንነታቸውን ጠየቅሁት፡፡ አንዲት ቁራጭ ወረቀት ከኪሱ አውጥቶ ሰጥቶኝ ወደ እንክብካቤው ተመለሰ፡፡

አነበብኩት፤ በአግራሞት እንደተሞላሁ ደጋግሜ ተመለከትኳቸው፡፡ በዕድሜ ገፍተዋል፤ በዝምታ ተውጠው የመርሐ ግብሩን መጀመር በትእግስት ይጠባበቃሉ፡፡ በአዕምሯቸው የተሸከሙት የዕውቀት ዶሴ ማን ገልጦ አንብቦት ይሆን? ለዘመናት ሲጨልፉት ከኖሩበት ከቤተ ክርስቲያን የዕውቀት ባሕር ለስንቱ አጠጥተው አርክተው ይሆን? ከሕሊናዬ ጋር ተሟገትኩ፡፡ ከዚህ በፊት ታላላቅ ቤተ መጻሕፍቶቻችን የተባሉት አባቶች ለገለጣቸው ሁሉ ተነበዋል፡፡ ለትውልድ ዕውቀታቸው ተላልፏል፤ በመተላለፍም ላይ ይገኛል፡፡ እኚህ አባት ከደቂቃዎች በኋላ የማጣቸው ስለመሰለኝ ውስጤን ስጋት ናጠው፡፡

መርሐ ግብሩ እንደተጠናቀቀ ቀረብ ብዬ ላናግራቸው ብሞክርም ለረጅም ስዓት ከመድረኩ የሚተላለፉ መልእክቶች ሲከታተሉ በመቆየታቸው ተዳክመዋል፡፡ ማነጋር አልቻልኩም፡፡ ነገር ግን የሚገኙበትን ደብር ማንነታቸው ከሚገልጸው ወረቀት ላይ ስላገኘሁ ተረጋጋሁ፡፡

ከቀናት በኋላ ታላቁን ሊቅ ሽሮ ሜዳ ከሚገኘው መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አገኘኋቸው፡፡ በሕይወት ተሚክሯቸው ዙሪያም ቆይታ አደረግን፡-

ስምዐ ጽድቅ፡- ስለ ሕጻንነት ዘመንዎ ቢያጫውቱን?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- የተወለድኩት ዋድላ ደላንታ ሸደሆ ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ በዐፄ ምኒልክ ዘመን በ1907 ዓ.ም ነው፡፡ አባቴ ተገኝ፤ እናቴ ደግሞ እንደሀብትሽ ትባላለች፡፡ የሕፃንነት ዘመኔ አስቸጋሪ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሕፃንነቴ ገና ዳዴ እያልኩ ነው ሁለቱም ዓይኖቼ ባልታወቀ ምክንያት የጠፉት፡፡ እናቴ እያለቀሰች ወደ እግዚአብሔር ከመጮኽ ሌላ ምርጫ አልነበራትም፡፡ አዝላኝ ትውላለች፤ ከጀርባዋ አታወርደኝም ነበር፡፡ በሀገራችን ታቦቱ ሰሚ የሆነ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡ እዚያ ይዘሽው ሔደሽ ለምን አታስጠምቂውም፤ ከዳነልሽ የታቦቱ አገልጋይ ይሆናል ተብላ ወሰደችኝ፡፡ ወዲያውኑ አንደኛው ዓይኔ በራልኝ፡፡ ሌላኛው ግን በድንግዝግዝ ነበር የሚያይልኝ፡፡ እናቴም በተደረገላት ተዓምራት በመደሰት ከከብቶቿ መካከል አንዱን ወይፈን ወስዳ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስዕለቷን ሰጠች፡፡ ብዙም ሳይቆይ ኩፍኝ ያዘኝና በድንግዝግዝ የነበረው አንዱ ዓይኔ ሙሉ ለሙሉ ጠፋ፡፡ አንዱ ብቻ ቀረ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡– የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አጀማመርዎ እንዴት ነበር?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- ለቤተ ክርስቲያን የተለየ ፍቅር በውስጤ ያደረው ገና በሕፃንነቴ ነው፤ ወደ ትምህርቱም አደላሁ፡፡ የተማርኩት ብዙ ቦታ ነው፡፡ ዙር አምባ ቅዱስ ያሬድ ካስተማረበት ቦታ ጀምሮ ከብዙ መምህራንም እውቀት ቀስሜአለሁ፡፡ ከየኔታ ክፍሌና ከየኔታ ተካልኝ ጽጌ ምዕራፍ፤ ድጓ፤ ጾመ ድጓ፤ ዝማሬ መዋዕስት ተምሬአለሁ፤ አቋቋምም ከእነሱ ሞካክሬአለሁ፡፡ ለአቋቋም ልዩ ፍቅር ነበረኝ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡– አቋቋምን ከማን ተማሩ?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- አቋቋም የነፍሴ ምግብ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ከዜማ ይልቅ ወደ አቋቋም አዘነበልኩ፡፡ ደብረ ታቦር መልአከ ገነት ጥሩነህ ዘንድ አምስት ሆነን አቋቋም ለመማር ገባን፡፡ እሳቸው በየቦታው የሚያገኟቸውን የአቋቋም አይነቶችን ተምረዋል፡፡ የጎንደር ቀለም ግን እዚያ አይቆምም፡፡ እኔም ሁሉንም ለመማር ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ ነገር ግን ሲያስተምሩን የጎንደርን የታች ቤትንና የተክሌን አደበላለቁብን፡፡ ለምን እንዲህ ይሆናል ብዬ አምስት ዓመት ከእሳቸው ጋር ከቆየሁበት ጥዬ በመውጣት አለቃ መንገሻ ዘንድ ሔድኩ፡፡

አለቃ መንገሻ ዘንድ ለሁለት ወራት ደጅ ስጠና ቆየሁ፡፡ ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ አስጠርተውኝ ከየት እንደመጣሁ፤ የት እንደተማርኩ ጠይቀውኝ ሁሉንም ነገርኳቸው፡፡ በመጨረሻም ፈቅደውልኝ የአቋቋም ትምህርቴን ቀጠልኩ፡፡ በተለይም የላይ ቤት፤ የተክሌ አቋቀቋም ላይ ትኩረት ሰጥቼ ተማርኩ፡፡ ከአለቃ መንገሻ ዘንድ ለአስራ ሰባት ዓመታት ተቀምጫለሁ፡፡ ዝማሬ መዋስዕት፤ ድጓ፤ ጾመ ድጓንና ሌሎችንም ለተማሪዎች አስተምር ነበር፡፡ ቅኔ ከሦስት ሊቃውንት ነው የተማርኩት፡፡ ከአለቃ ብሩ፤ ከአለቃ መጽሔትና የአቋቋም ተማሪዬ ከነበረው ሊቀ ጠበብት ወልደ ሰንበት ተምሬአለሁ፡፡እኔ አቋቋም እያስተማርኩት እሱ ደግሞ ቅኔ አስተምሮኝ ተመረቅሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ወንበር ዘርግተው ማስተማሩን እንዴት ጀመሩ?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- መምህሬ አለቃ መንገሻ ከአዲስ አበባ ከሚገኘው በዓታ ለማርያም እንዲመጡ ጥሪ ተደርጎላቸው ስለነበር አብረን እንድንሔድ ቢጠይቁኝም እምቢ በማለት ጸናሁ፡፡ የሚቀረኝን ትምህርት ለመማር ስለፈለግሁ ዙር አምባ ወፋሻ ኪዳነ ምሕረት የእድሜ ባለጸጋ ከነበሩት አባት ዘንድ ሃያ አምስት ሆነን ለመሔድ ተስማምተን መልእክት ሰደድንላቸው፡፡ እሳቸውም ጥያቄአችንን ተቀበሉን፡፡

አለቃ መንገሻ በድምጼ በጣም ይገረሙ ስለነበር ጨጨሆ ላይ ብታዜም ዋድላ ደላንታ ይሰማል ይሉኝ ስለነበር “መድፉ”፤ “ወልደ ነጎድጓድ” በማለት ይጠሩኛል፡፡ በአቋሜ እንደጸናሁ ስለተረዱም “ልጄ አብረን ብንሆን መልካም ነበር፤ ይቅናህ” በማለት ግንባሬን ስመው አሰናበቱኝ፡፡ ዙር አምባ ኪዳነ ምሕረት የተወሰነ ጊዜ ከቆየሁ በኋላ በደብረ ታቦር አጋጥ ኪዳነ ምሕረት ወንበር ዘርግቼ አቋቋም ማስተማር ጀመርኩ፡፡

ደብረ ታቦር እያለሁ ዐሥራ ሦስት የሚደርሱ አብያተ ክርስቲያናት መምህር ስላልነበራቸው እየተዟዟርኩ አገልግያለሁ፡፡ ነገር ግን ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ያንን አካባቢ ተውኩና ጋይንት ልዳ ጊዮርጊስ ለማስተማር ወረድኩ፡፡ እልም ያለ በረሃ ነው፡፡ ጥቂት እያስተማርኩ ቆይቼ ተማሪዎቹ በረሃውን መቋቋም እየተሳናቸው ጥለውኝ ሔዱ፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ባለመቻሌ በ1941 ዓ.ም. ወደ ዳውንት ሔድኩ፡፡ ዳውንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እስከ 1945 ዓ.ም. ተማሪዎችን ሰብስቤ ወንበር በመዘርጋት አቋቋም፤ ዝማሬ መዋስዕት፤ ድጓ፤ ጾመ ድጓ ማስተማሬን ቀጠልኩ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ ጋር እንዴት ተገናኛችሁ?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡– በ1943 ዓ.ም. ተከስተ ብርሃን /ተከስተ ብርሃን የሚለው ስያሜ አለቃ ወልደ ሰንበት ያወጡላቸው ስም ነው፡፡ መምህራን ተማሪዎቻቸውን በምግባራቸውና በትምህርት አቀባበላቸው ተነስተው ስም ማውጣት የተለመደ ነው፡፡/ ዳውንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከማስተምርበት መጣ፡፡ ታዲያ እርሱና የአሁኑ ዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አበምኔት አባ ሐረገ ወይን ጸናጽሉ ቢቀላቸውም ዘንጉ ይከብዳቸው ነበር፡፡ ተከስተ ብርሃን የሚለውን ስያሜ ያወጣሁለት በወቅቱ በነበረው የትምህርት አቀባበል ፍጥነቱንና ኃይለኛነቱን ተመልክቼ ነው፡፡በትምህርት እርሱ ዘንድ ቀልድ የለም፡፡ ተማሪዎቼ ሲያለምጡ የሚገስጻቸው እርሱ ነበር፡፡

ተከስተ ብርሃን ለትምህርትና ለሥራ ልዩ ፍቅር ነበረው፡፡ ፈቀደ /መቂ የደብረ አለቃ ሆኖ ነበር አሁን ግን አርፏል/ ከሚባል ተማሪ ጋር ሆነው “ተማሪው በትርፍ ጊዜው እየተንጫጫ ለምን ያስቸግራል፤ ለምን እርሻ አናርስም፤ በማለት ሃሳብ አቅርበው ዶማና መጥረቢያ ፈልገው ተማሪውን ሰብስበው ጫካውን እየመነጠሩ በበሬ አረሱት፡፡ ምሥር ዘርተውበት ሃምሳ ቁምጣ አስገብተዋል፡፡

በተጨማሪ ከቤተ ክርስቲያኑ በላይ በኩል ዳገታማ ሥፍራ ላይ ተማሪውን አስቆፍረው ገብስ ዘሩበት፡፡ “እባካችሁ ተማሪውን በሥራ እያማረራችሁ አታፈናቅሉብኝ” እላቸዋለሁ፡፡ እነሱ ግን ሦስት ኩንታል ገብስ አምርተው አስገቡ፡፡ ከትምህርታቸው በተጓዳኝ ጥጥ ገዝተው እያመጡ ለአካባቢው ሴቶች እያስፈተሉ ጋቢና ኩታ ያሰሩ ነበር፡፡ ተዉ ብላቸውም አሸነፉኝ፡፡ ተማሪ ሥራ ሲፈታ ስለማይወዱ ነበር ይህንን የሚያደርጉት፡፡

በተለይ ተከስተ ብርሃን ተማሪዎቹን ስለሚገስጽ ተማሪዎቹ “ይኼ ጥቁር ፈጀን እኮ” እያሉ ስሞታ ያቀርባሉ፡፡ እኔም ጠባዩን ስላወቅሁት “አንድ ስህተት አግኝቶባችሁ ይሆናል እንጂ ያለ ምክንያት አይቆጣችሁም” እያልኩ ፊት አልሰጣቸውም ነበር፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- እርስዎ ምን አይነት መምህር ነበሩ?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- እኔም ኃይለኛ ነበርኩ፡፡ ተማሪዎቼ ሲያጠፉ በኃይል ነበር የምገርፋቸው፡፡ አስቸጋሪ ተማሪ ካጋጠመኝም አባርራለሁ፡፡ ይህን የማደርገው ለእውቀት ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረኝ የእኔን አርአያነት እንዲከተሉ ለማድረግ እንጂ በክፋት አልነበረም እርምጃውን የምወስደው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ለተማሪውና ለእርስዎ ድርጎ ከየት ያገኙ ነበር?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ለተማሪዎች አቡጀዲና ለቀለብ የሚሆን ገንዘብ ይልኩልኛል፡፡ “የኢትዮጵያ መድፏና መትረየሷ ጸሎት ነው” በማለት በጸሎት እንድንበረታ መልእክት ይሰዱልኛል፡፡ እኔም በታማኝነት የቻልኩትን ሁሉ አደርግ ነበር፡፡ በተጨማሪም ዋድላ ደላንታ ላይ የተሰጠኝ እስከ ሠላሳ ጥማድ የሚያሳርስ የእርሻ መሬት ነበረኝ፤ የተመረተውን አስመጥቼ ለተማሪዎቼ ቀለብ አደርገው ነበር፡፡ ተማሪዎቼም የለመኑትን ያመጣሉ፤ በዚህ ሁኔታ ችግራችንን እንወጣ ነበር፡፡
ስምዐ ጽድቅ ፡- ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እርስዎ ዘንድ ለምን ያህል ጊዜ ቆይተዋል?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡– ተከስተ ብርሃን ለሁለት ዓመታት አቋቋም ካስተማርኩት በኋላ ነው የተለያየነው፡፡ ከዚያ በኋላ የት እንዳለ ሳላውቅ በደርግ ዘመን ጵጵስና መሾማቸውን ሰማሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ስለ ቤተሰብዎ ጥቂት ቢያጫውቱን

አለቃ ወልደ ሰንበት፡– በ1947 ዓ.ም. ነው ትዳር የመሠረትኩት፡፡ ስምንት ልጆችን ወልጃለሁ፡፡ አራቱ አርፈዋል፡፡ የልጅ ልጆችም አሉኝ፡፡ አንዱ የልጅ ልጄ ደሴ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅኔ ቤት ገብቶ እየተማረ ነው፡፡ ለአባቱ ያሉኝን መጻሕፍት ልስደድለት እለዋለሁ፡፡ እሱ ደግሞ ቆይ ይደርሳል እያለኝ ነው፡፡ አያቴ ገብረ ተክሌ የታወቁ የድጓ መምህር ነበሩ፤ እኔም የእሳቸውን ፈለግ ተከትያለሁ፡፡ በተራዬ እኔን የሚተካ ከልጅ ልጆቼ መካከል በመገኘቱ ተደስቻለሁ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ሓላፊነት ይሸከም ዘንድ ተገኘልኝ፡፡ እግዚአብሔር መጨረሻውን ያሳምርለት፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- አዲስ አበባ እንዴት መጡ?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- ባለቤቴም አረፈች፡፡ እመነኩሳለሁ ብዬ ደብረ ሊባኖስ ገብቼ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስላልነበር አልተሳካልኝም፡፡ ሔኖክ የሚባል አቋቋም ያስተማርኩት ልጅ ደብረ ሊባኖስ አግኝቶኝ በ1971 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ወስዶ በመሪ ጌትነት እንዳገለግል አደረገ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በዚሁ ቤተ ክርስቲያን እያገለገልኩ ቆይቻለሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡– በቅርብ የሚረዳዎት ሰው አለ?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- የመጨረሻዋ ልጄ ከእኔው ጋር ናት፤ እግዚአብሔር እሷን አጠገቤ አኖረልኝ፡፡ እኔም ሰውም እየመረቅናት ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡– ካስተማሯቸው ተማሪዎችዎ ማንን ያስታውሳሉ?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል /የቀድሞው/ ዝዋይ የነበሩት፤ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ /አሁን የወልዲያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በርካታ የደብር አለቃ የሆኑ ሊቃውንትን አፍርቻለሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡– የሚያስተላልፉት መልእክት ካለዎት?

አለቃ ወልደ ሰንበት፡- እኔ የጋን ውስጥ መብራት ሆኜ ነው የኖርኩት፡፡ ተደብቄ ነው ያለሁት፡፡ ቅንነት መልካም ነገር ነው፤ ለሰው ልጅ እጅግ ያስፈልጉታል፤ ኖሬበታለሁም፡፡ ዕድሜና የሰው ፍቅር ሰጥቶኛል፤ ለእናንተም ይስጣችሁ፡፡ ከተደበቅሁበት አስታውሳችሁኛልና አምላከ ጎርጎርዮስ የማኅበሩን አገልግሎት ይባርክ፡፡ አሜን፡፡