የዐቢይ ጾም ስብከት (ክፍል 4)

የካቲት 29/2004 ዓ.ም.

በአያሌው ዘኢየሱስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሰው ሁሉ በሥጋም ሆነ በነፍስ ታሞ ነበር፡፡ እርሱ ወደዚህ ዓለም የመጣው የሰው ልጆች ሁሉ አባትና መድኀኒት ስለሆነና ከዚህ በሽታቸው ሊያድናቸው ነው፡፡ ይህ ስለሆነ ወደ እኛ ከመጣ በኋላ ስለ መጣበት ዓላማ እንዲህ በማለት ተናገረን፡-   «. . . ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፤ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ፤ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል. . .» ሉቃ 4፥17-19፡፡ ይህ በመሆኑም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድረ እስራኤል ተዘዋውሮ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ አድኗቸዋል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ይህን ሁኔታ የገለጸው እንዲህ በማለት ነው፡- «. . . የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር፡፡ ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ፤ አጋንንት ያደሩባቸውን፤ በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፤ ፈወሳቸውም፡፡» ማቴ 4፥23-24፡፡

ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን እያደረገ በምድረ እስራኤል ሲዞር ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ለ38 ዓመታት ያህል በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ በአልጋው ላይ ተኝቶ የነበረውን በሽተኛ ሰው ኢየሩሳሌም ውስጥ በምትገኘውና ቤተ ሳይዳ በምትባለው የመጠመቂያ ቦታ ያገኘው፡፡ በዚህች የጸበል ቦታ ላይ ተኝቶ ድኅነቱን ለማግኘት ይጠባበቅ የነበረው ይህ ሰው ብቻ አልነበረም፤ሌሎችም በተለያዩ በሽታዎች የተያያዙ ብዛት ያላቸው በሽተኞች ጭምር እንጂ፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ሁኔታ የገለጸው እንዲህ በማለት ነው፡- «. . . በሽተኞችና ዕውሮች፣ አንካሶችም፣ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡» ዮሐ 5፥3፡፡ እነዚህ ሁሉ በሽተኞች በዚያች አምስት መተላለፊያ ባሏት የመጠመቂያ ቦታ ላይ ተኝተው ይጠባበቁ የነበረው  የጌታ መልአክ ወርዶ ጠበሉን ሲያናውጠው ቀድሞ ወደ ውኃው የሚገባ ስለሚድን ነበር፡፡ መልአኩ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጠው ሊፈወስ የሚችለው አንድ በሽተኛ ብቻ ነበር፡፡ መልአኩ ቤተ ሳይዳ ተብላ የምትጠራውን ጸበል ሲያናውጣት ይህን በሽተኛ ሰው ወደ ጸበሉ ቦታ ተሸክሞ የሚያደርሰው ሰው ስላልነበረው ፈውስን ሊያገኝ አልቻለም ነበር፡፡ እርሱ  ለ38 ዓመታት ያህል በመጠመቂያዋ አጠገብ ሊተኛ የቻለው ምንም ዓይነት ሰው ወይም ዘመድ ወይም ወገን ስላልነበረው ነው፡፡

መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች የመጠመቂያ ቦታ የመጣው በተለይ ይህን ሰው ለመፈወስ ነው፡፡ ምክንያቱም ወንጌላዊው ዮሐንስ «ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ. . .» (ዮሐ 5፥7) ብሎ የጻፈልን ለ38 ዓመታት ያህል  መተኛቱን አውቆ ሊያድነው መምጣቱን ከአነጋገሩ ስለ ተረዳ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ምድራውያን ሀኪሞች፡- እንዴት ያደርግሃል? ከጀመረህ ስንት ጊዜ ይሆንሃል? ልትታመም የቻልኸው በምን ምክንያት ይመስልሃል? ሳይል በአምላክነቱ ሁሉንም ነገር ያውቅ ስለ ነበር «ልትድን ትወዳለህን?» በማለት ፈቃደኛነቱን ከጠየቀው በኋላ «ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ. . .» በማለት በቃሉ ስለ ፈወሰው አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ሊሔድ ችሏል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ከነበረበት በሽታ ጤናማ ሊሆን ያልቻለበትን ምክንያት ሲናገር «ጌታ ሆይ፡- ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ነገር ግን እኔ ልመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል. . .» (ዮሐ 5፥7) ነበር ያለው፡፡

ዛሬም ቢሆን «ሰው የለኝም» የሚለው ቃል የብዙ ሰዎች ምክንያት ነው፡፡ ለምን ትምህርትህን አልቀጠልህም ተብሎ የሚጠየቅ ሰው እንድማር የሚረዳኝ ሰው የለኝም ይላል፡፡ ለምን ሥራ አልጀመርሽም የምትባል ሴት ልጅ ሥራ የሚያስገባኝ ሰው የለኝም ትላለች፡፡ ልትድኑ ያልቻላችሁት ለምንድር ነው ተብለው የሚጠየቁ ሰዎችም የምንታከምበት ገንዘብ የሚሰጠን ሰው የለንም ይላሉ፡፡ ብዙ ሰዎች በብዙ ቦታዎች ላይ አጥብቀው የሚሹት ወይም የሚፈልጉት የሰዎችን መኖር ወይም እርዳታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እኛ አጥብቀን ልንሻው የሚያስፈልገን ነገር የእግዚአብሔርን እርዳታና ማዳን መሆን አለበት፡፡ የምንበላው ምግብ፣ የምንጠጣው መጠጥ፣ የምንለብሰው ልብስ፣ የምንጠለልበት መጠለያ፣ የምንማርበትና የምንታከምበት ገንዘብና የምንፈልገውን ሥራ መሥራት የምንችልበትን መንገድ ሊያድሉን የሚችሉት ሰዎች ናቸው ብለን ስለ ወሰንን ሁሉን ሊሰጥ ከሚችለው ከእግዚአብሔር ላይ ዓይኖቻችንን አንሥተናል፡፡ የሚያበላ፣ የሚያጠጣ፣ የሚያለብስ፣ መጠለያ የሚሰጥ፣ ሥራን የሚባርክ፣ የሚፈውስ፣ የሚያበለጽግ፣ የሚያኖር እግዚአብሔር መሆኑን አስረግጠን ስላላመንንና መታመኛችንን ሁሉ በሰዎች ላይ ስላደረግን ልንድን አልቻልንም፡፡ ይህ በሽተኛ ሰው እድናለሁ ብሎ የተኛው የእግዚአብሔርን እርዳታ አገኛለሁ ብሎ ሳይሆን የአንድን ጎልማሳ ሰው ፈርጣማ ክንድ ስለ ነበር ሊድን አልቻለም፡፡ እርሱ የዳነው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያድነው እንደሚችል ባመነ ጊዜ ነበር፡፡ ለመዳንና ሌሎች ያጣናቸውን ነገሮች ለማግኘት በእግዚአብሔር ማመን ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ማመን ከዚያም መዳን!

እግዚአብሔር ያለው ሰው ሁሉም ነገር አለው፤ እግዚአብሔር የሌለው ሰው ግን ሁሉም ነገር ያለው ይመስለዋል እንጂ ምንም ነገር የለውም፡፡ የተማረ ቢመስልም አልተማረም፤ሥራ ያለው ይምሰለው እንጂ ሥራ የለውም፤ጤና ያለው ይምሰለው እንጂ ጤና የለውም፤ ሀብት ያለው ይምሰለው እንጂ ድሃ ነው፤ የለበሰ ይምሰለው እንጂ እርቃኑን ነው፤ እግዚአብሔርን ሳያምኑ የሚገኝ ትምህርት፣ ሥራ፣ ጤና፣ ልብስ፣  ሀብት. . . ወዘተ በከንቱ የሚጠፉ ናቸውና፡፡ ላጣው ነገር ሁሉ እንደ መፍትሔ አድርጎ ሰውን የሚያቀርብና  መፍትሔ ሲያጣ ሰው ስለሌለኝ ነው በማለት ምክንያት የሚቀርብ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ደካማ ወይም ባዶ መሆኑን ይህ ሁኔታ ያረጋግጥልናል፡፡

መፃጒዕ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር በማድረግ ከሰው የሚበልጥ መሆኑን ቢያውቅ ኖሮ እንዲህ አይልም ነበር፡፡ ብዙ ሰዎችም ከሰዎች ይልቅ የሚያምኑ እግዚአብሔርን ቢሆኑ ኖሮ ችግር ላይ አይወድቁም ነበር፡፡ ሰው በሰው ከሚታመን ይልቅ በእግዚአብሔር ቢታመን የሚሻል መሆኑን ነቢዩ ዳዊት ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- «ለእኔስ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው፤» መዝ 72፥28፡፡ ብዙዎች ግን መታመኛቸውን ወደ ሰው ስላደረጉ ወደ እግዚአብሔር ሊቀርቡ አልቻሉም፡፡ በእግዚአብሔር አምኖ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመቅረብ ጠበል ከመጠመቅ፣ በእምነት ከመታሸትና ቅብዓ ቅዱስ ከመቀባትና በመስቀል ከመዳሰስ ይልቅ በሰዎች አምኖ ወደ ጠንቋዩ፣ ወደ ቃልቻው፣ ወደ ዛር ጎታቹ በመቅረብ እርሱ አድርጉ የሚላቸውን ነገሮች ማድረግን የሚሻል መፍትሔ አድርገው ተቀብለውታል፡፡

በእግዚአብሔር አምናለሁ ማለት ብቻም ድኅነትን ወይም ያጡትን ነገር አያስገኝም፤ለመዳን ያመኑትን ነገር በሥራ መግለጽ ያስፈልጋልና፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲሁ በአፋቸው ብቻ በእግዚአብሔር እናምናለን በማለት ቢናገሩም እምነታቸውን በሥራ ለመግለጽ ስላልቻሉ ሊድኑ አልቻሉም፡፡ በዚህ ጊዜ ጉድለቱ ከእነርሱ አለማመን እንደ መጣ አድርገው ስለማይቀበሉ እግዚአብሔርን ሲያማርሩ እንመለከታለን፡፡ ሰው ግን የሚድነው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር ነው፡፡ አባታችን አብርሃም በእምነት የጸደቀ ሰው ቢሆንም ይህን እምነቱን በሥራ አስረግጦ የገለጸው እግዚአብሔር አድርግ ወይም ሥራ ያለውን ነገር ስለ ሠራ ነው፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር አምኜያለሁ ብሎ በኀጢአት ከተሞላው ከከለዳውያን አገር ከዑር ለመውጣት ፈቃደኛ ባይሆን ኖሮ እግዚአብሔር የገባለትን ቃል ኪዳን በሙሉ ሊያገኝ አይችልም ነበር፡፡ ማመን፤ ካመኑ በኋላ ያመኑበትን ነገር በሥራ መግለጽ የክርስትና ዐቢይ መርሆ ነው፡፡ ይህ ስለሆነም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንዲህ በማለት የተናገረው፡- «ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡» ያዕ 2፥26፡፡

ሥራና እምነት የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ እምነት ያለ ሥራ፤ ሥራም ያለ እምነት ዋጋ ወይም ድኅነት ሊያሰጡ አይችሉም ማለት ነው፡፡ የሰው ሥጋ ሞተ የሚባለው ነፍሱ ስትለየው ነው፤ የሰው እምነት ምውት ነው የምንለውም ሥራ ሲለየው ነው፡፡ ለማመንማ አጋንንትም እግዚአብሔርን ያምኑታል በፊቱም ይንቀጠቀጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እምነታቸውን በሥራ ሊገልጹት ስላልቻሉ ወይም ስላልፈቀዱ ሊድኑ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ታሞ ለረዥም ጊዜ በአልጋ ላይ የተኛ ሰው እግዚአብሔርን አምናለሁ እያለ ይህ እምነቱን በሥራ መግለጽ የማይችል ከሆነ የእርሱ እምነት ከአጋንንት እምነት ጋር የሚመሳሰል ስለሆነ ድኖ የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ መሔድ አልቻለም፡፡ ይህ ሰው እምነቱን እግዚአብሔር በሚከብርባቸው ሥራዎች ሳያስደግፍ እርሱ የማይከብርባቸውን ሥራዎች የሚሠራ ከሆነ ሊድን አይችልም፤ሥራዎቹ ይበልጥ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣሉት ሥራዎች ናቸውና፡፡ አንድ ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ልብስና ምግብ ላጡ ሰዎች እምነቱን ምግብና ልብስ በመስጠት ወይም በሥራ በመግለጽ ሊታደጋቸው ይገባዋል እንጂ ያለ ምንም ዓይነት በጎ ሥራ ሳያደርግላቸው «በደኅና ሒዱ፤ እሳት ሙቁ፤ ጥገቡም» ቢላቸውና ለሰውነታቸው የሚያስፈልጋቸውን ምግብና ልብስ ባይሰጣቸው (ያዕ 2፥14-16) የእርሱ እምነት በሥራ ስላልተገለጸ እምነቱ የክርስቲያን እምነት ሳይሆን የአጋንንት እምነት ነው ማለት ነው፡፡

ሰው በእግዚአብሔር መታመኑን ትቶ በሰው የሚታመን ከሆነና የታመነበትን ሰው አንድ ቀን እንደ መፃጉዕ ከአጠገቡ ሲያጣው ወይም ልብስ፣ ምግብና ጤና ሊያድለው ሲያቅተው ወይም ያለ ልብስና ያለ ምግብ እሳት ሙቅ እና ጥገብ ሲለው ለ38 ዓመታት ያህል በደዌ ዳኛ እና በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ሊቆይ ይችላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በበሽታው ወይም በቁስሎቹ ምክንያት ከፍተኛ ሥቃይ የደረሰበት ሰው ጻድቁ ኢዮብ ነው፡፡ ኢዮብ ሥጋውን በገል እስከሚፍቅ ድረስ ነው የተሰቃየው፡፡ ይሁን እንጂ እምነትን ከሥራ ጋር አስተባብሮ የያዘ ሰው ስለ ነበር እግዚአብሔር አምላክ ፈውሶታል፤ያጣውንም ነገር ሁለት እጥፍ አድርጎ መልሶለታል፡፡ ስለሆነም ሰው ከበሽታው ሊፈወስና ያጣው ነገር ሁለት እጥፍ ሆኖ እንዲመለስለት ከፈለገ ፍጹም በእግዚአብሔር ማመንና የጽድቅ ሥራዎችን መሥራት ይገባዋል፡፡ መፃጉዕ ለእነዚህ ሁሉ ዘመናት በአልጋው ላይ ሊተኛ የቻለው በኀጢአቱ ምክንያት መሆኑን የወንጌሉ ቃል እንዲህ በማለት ገልጦታል፡- «ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፡- እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደፊት ኀጢአት አትሥራ አለው፡፡» ዮሐ 5፡14፡፡ ሕመም በኢዮብ ላይ እንደ ተገለጠው ለፈተና ሊገለጥ እንደሚችል ሁሉ በመፃጒዕ ላይም ለኀጢአት ተገልጦአል፡፡ በዘውሩ ተወልደ ላይ የእግዚአብሔር ክብር እንዲገለጥበት እንደ ተገለጠውም ሊገለጥ ይችላል፡፡ በመሆኑም በመፃጉዕ ላይ የተገለጠው ደዌ በሠራው ኀጢአት አማካይነት የመጣ ስለሆነ ጌታ «ከዚህ የበለጠ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኀጢአት አትሥራ፡፡» (ዮሐ 5፡14) በማለት አስጠንቅቆታል፡፡

ዛሬም ቢሆን ሰው ሁሉ በኀጢአት ደዌ ተይዟል፡፡ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጠብ፣ ክርክር፣ ውሸት፣ ስርቆት፣ ስድብ፣ ዋልጌነት፣. . . ወዘተ በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚዘወተሩ የኀጢአት ዓይነቶች ናቸው፡፡ የለበስነው ሥጋ ድካምና ኀጢአት የሚስማማው ሥጋ ስለሆነ ሁላችንም በአንዱ ወይም በሌላው የኀጢአት ዓይነት እንሰነካከላለን፡፡ ሁሉም ሰው ኀጢአተኛ ሰው መሆኑን ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በአንደኛ መልእክቱ ውስጥ እንዲህ በማለት ገልጾታል፡- «ኀጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም፡፡» 1ኛ ዮሐ 1፥8፡፡ ሁሉም ሰው ኀጢአተኛ ከሆነ ደግሞ ድኅነትን ወይም ፈውስን ለማግኘት «አቤቱ፡- እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ፡፡ ከበደሌም ፈጽሞ እጠበኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፤ ኀጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና፡፡» (መዝ 50፡1-3) እያለ በየጊዜው ንስሓ በመግባት ምሕረት የሚያድለውን ጌታ መለመን አለበት፡፡ እንደ መፃጒዕ ስለ ሠራው ሥራ ሳይፀፀት «ሰው የለኝም» እያለ በስሞታ የሚቆይ ሰው ድኅነትን ሊያገኝ አይችልም፡፡ ዘወትር እንደ ቅዱስ ዳዊት ኀጢአቱን በዓይኖቹ ፊት የሚመለከት ሰው በሠራው ኀጢአት ዘወትር እየተፀፀት ዕንባዎቹን በመኝታው ላይ ያፈስሳል፡፡

ዛሬ ግን ብዙ ሰዎች ኀጢአት መሥራታቸው ከቶውኑ ትዝ ስለማይላቸው በንስሓ ሊመለሱ አልቻሉም፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ዕድሚያቸውን የሚያሳልፉት በኀጢአት አልጋ ላይ ተንጋልለው ነው፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድመን ከተኛንበት የኀጢአት አልጋችን ላይ በመነሣት ይህንኑ አልጋችንን ተሸክመን እንድንሔድ በመናገር የሚገድል ኀጢአችንን በመከራው፣ በሞቱና በትንሣኤው ቢያጠፋልንም ተመልሰን እዚያው አልጋችን ላይ በኀጢአት ተጠልፈን ወድቀናል፡፡ ከአሁን በኋላ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኀጢአት ወድቀው በንስሓ ለመመለስ ላልቻሉት ኀጢአተኞች ለሁለተኛ ጊዜ «አልጋህን ተሸክመህ ሒድ» ለማለት በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት አይገለጥም፡- «የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡» (ማቴ 25፡30) በማለት ሊፈርድበት እንጂ፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤አሜን፡፡

ይቆየን፡፡

በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡