አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2

የካቲት 29/2004 ዓ.ም.

በመ/ር ምሥጢረሥላሴ ማናየ

ይህ ከላይ ያነሣነው ርዕስ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት መጾሙን ያስተምረናል፡፡
በዚህ ኀይለ ቃል ሁለት ታላላቅ ቁም ነገሮችን ቃላትን እንመለከታለን

 

  1. አርባ መአልትና አርባ ሌሊት
  2. ጾም የሚሉት ናቸው፡፡

በቅድሚያ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት የሚለውን ከእነ ምስጢሩ እንመለከተዋለን፡፡ ቀጥለን ደግሞ ጌታችንስ ለምን አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ? የሚለውን እንመለከታለን እግዚአብሔር አይነልቡናችንን ይክፈትልን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የፈጠረውን የሰው ልጆችን አባት አዳምን፣ በልጅነት አክብሮ ገነት ያስገባው በፈጠረው በአርባ ቀኑ ነው፡፡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለአዳም” አዳምን የፈጠረ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው እያሉ እያመሰገኑ መላእክት ወደገነት አስገብተውታል /ቀሌ.4፥/

“ወላምድኅረ ተፈጸመ ለአዳም ፵ መዋዕል በምድር ኀበ ተፈጥረ አባዕናሁ ውስተ ገነተ ኤዶም ኩፋ.9፥12 ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ወደገነት አስገባነው፡፡ ሔዋንንም በሁለት አርባ ማለትም በሰማኒያ ቀኑዋ ወደገነት አስገቧት ኩፋ.4፥12

በተጨማሪም አዳም ትእዛዘ እግዚአብሔር ካፈረሰ በኋላ ዲያብሎስ በአቋራጭ መጥቶ አስወጣው እንጂ ሱባኤ የገባው ለአርባ ቀናት ነበር፡፡ ይህን አርባ ቀን የሰው ልጆች ከስህተት በኋላ በቀንም ሆነ በዓመት ለጾም፣ ለሱባኤ፣ ከዚያ አልፎ ለመቅጫነት አግልሏል፡፡

በኦሪት ዘፍጥረት እንደምናነበው የሰው ልጅ በንፍር ውኃ የተቀጣው አርባ መአልትና ሌሊት ነበር፡፡ “አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናም አዘንማለሁና የፈጠርሁትንም ፍጥረት በምድር ላይ አጠፋለሁና ዘፍ.7፥12 “የሰማይ መስኮቶች ተከፈቱ ዝናቡም አርባ መአልትና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ” ዘፍ.7፥12

በዚህ ዐይነት አርባ ቀን እግዚአብሔር ሰውን እንደቀጣበት እናያለን፡፡ መቅጣት ብቻ ሳይሆን በዚህ የአርባ መአልትና የአርባ ሌሊት ዝናም ምድርን ከበዛባት ርኲሰት አጥቧታል፡፡ ምክንያቱም የጥምቀት ምሳሌ ነውና፡፡ ማየ አይህ /የጥፋት ውኃ/ የጥምቀት ምሳሌ ለመሆኑ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡” 2ጴጥ.3፥20ና21

አሁንም ከዚሁ ሳንርቅ የመርከቧ መስኮቶች የተከፈቱት በአርባ ቀን መሆኑን ይገልጻል፡፡ “ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ” ዘፍ.8፥6 መርከቧ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ እስራኤል ወደ ምድረ ርስት ያደረጉት ጉዞ አርባ ዓመት እንደፈጀ ተጽፏል፡፡ ይህም መንገድ ደግሞ የአርባ ቀን መንገድ ነበር በእግዚአብሔር ቁጣ ወደ አርባ ዓመታት ተለወጠ እንጂ፡፡ “በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ ዓመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ” ዕብ.3፥7-19 ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎታል፡፡

እስራኤል አርባ ዘመን መና ከደመና እየወረደላቸው ተመግበዋል፣ ውኃ ከአለት እየፈለቀላቸው ጠጥተዋል፡፡ ሲያምጹም ተቀጥተዋል፡፡ ሙሴ ወንድሞቹን እስራኤልን ለመጎብኘት የመጣው በአርባ ዓመት ነበር “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ የሥራቸውን መከራ ተመለከተ” ዘፀ.3፥11 ሐዋ.7፥23 የተሰደደውም በዚሁ እድሜው ነው፡፡ በምድያም በግ በመጠበቅ አርባ ዘመን ኖሯል እንደገና እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ እንዲያወጣ እግዚአብሔር የላከው በአርባ ዘመን ነበር፡፡ “አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ ታየው፡፡ ዘፀ.3፥30

ይህም ብቻ አይደለም ሙሴ ለዚህ አገልግሎት በተመረጠበት ጊዜ በሲና ተራራ አርባ ቀንና ሌሊት ጾሟል “ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ቆየ” ዘፀ.24፥19 ዝም ብሎ ሥራ ፈትቶ አይደለም የቆየው እየሠራ ነው ሥራውም ጾም ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ሙሴን በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው በዚያም አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበር አልበላም አልጠጣም” ዘፀ.34፥27 እየጾመ ነበር ማለት ነው በዚህ ጾሙ ሙሴ የቃል ኪዳኑን ጽላቶች ተቀብሎበታል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ከንቱ ሳይሆን ዋጋ ያለው እንደሆነ ነው፡፡ የኤልያስ ጉዞ አርባ ቀን አርባ ሌሊት እንደነበረ ተጽፏል፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና የምትሔድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው ተነሥቶም በላ ጠጣ በዚያም ምግብ ኀይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሔደ” 1ነገ.19፥4-8

ሕዝቅኤል አርባ ቀን ጾሞ 600 ሙታን አስነሥቷል፡፡ እዝራ ሱቱኤል አርባ ቀን ጾሞ የጠፋ መጻሕፍትን መልሷል አብረው የነበሩ አምስት ሰዎች ቀን ቀን ይጽፋሉ ማታ ማታ ጥቂት እህል ውኃ ይቀምሱ ነበር እዝ.ሱቱ.13፥23-25 ጌታችን በተወለደ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል ሉቃ.2፥22 ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2 በተነሣ በአርባኛው ቀን ወደሰማይ አረገ ሐዋ.11፥10 ሰው በተጸነሰ በአርባ ቀኑ ተስዕሎተ መልክዕ ይፈጸምለታል፡፡ “በአርባ ቀን ትሾመዋለህ” እንዲል ቅዱስ አትናቴዎስ ወንድ በተወለደ በአርባ ቀኑ ሴትም በ80 ሁለት አርባ ክርስትና ይነሣል፡፡ ሰው በአረፈ በአርባ ቀኑ ጸሎተ ፍትሐት ይደርስለታል፡፡  ሰው በአርባ ቀን ጸሎት ተክሊል ይደርስለታል ፍት.ነገ. እን.24 ገጽ 322

አርባ ቀን ይህን ያህል ምስጢር ያለው ቀኑ ነው ጌታችን ለምን? አርባ ቀን ጾመ ስንል ከላይ ያየናቸው አበው ነቢያት ብዙውን ጊዜ የጾሙት አርባ ቀን ነው፡፡ ቢቀንስ አጎደለ ከፍ ቢያደርግ አበዛ ብለው አይሁድ የነቢያትን ሕግ አፈረሰ በማለት ትምህርቱ አንቀበልም ባሉ ነበርና ይህን ምክንያት ለመንሳት አርባ መአልትና ሌሊት ጾመ፡፡ እስራአል 40 ዓመት ተጉዘው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ እናንተም 40 ቀን ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ሲለን ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የጥፋት ውኃ በምድር አርባ ቀንና ሌሊት ዘነመ ምድር ነጻች ሰው አርባ ቀንና ሌሊት ቢጾም ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳል ሲለን ነው፡፡ ጾም ለርስት ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃ ከኀጢአት የሚያነጻ እንደሆነ ሊያስተምረን በኦሪት በተጾመው ቁጥር ጾሞ ሥርዓትን ሰጠቶናል፡፡

ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ፍት.አን.15 “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ መብል መጠጥ የኀጢአት መሠረት ነው በመብል ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ላይ መጣ “ይችን ዕፀ በለስ ብትበሉ ሞትን ትሞታላችሁ” ዘፍ.2፥17

መብል መጠጥ ከልክ ሲያልፍ ከተዘወተረም ከእግዚአብሔር ይለያል፤ “ያዕቆብ በላ ጠገበ ወፈረ ገዘፈ ደነደነ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ” ዘዳ.32፥15-17 “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም” ሮሜ.14፥16፣ 1ቆሮ.8፥8-13 “ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና ማቴ.5፥6 ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ “ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት መዝ.68፥10 ጾም በነቢያት የተመሠረተ በክርስቶስ የጸና በሐዋርያትም የተሰበከና የተረጋገጠ ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረን ይህን ጾም ከምግብ ለመከልከል ጋር ጸሎትን፥ ስግደትን፥ ምጽዋትንና የንስሐ ዕንባን ጨምረን እንጹመው፡፡ ጌታችንና ነቢያት፣ ሐዋርያት የተውልን መንፈሳዊ መሣሪያ ነውና፡፡

መዋዕለ ጾሙን በሰላመ ያስፈጽመን