መፃጒዕ /ለሕፃናት/

መጋቢት1/2004 ዓ.ም.

በቴዎድሮስ አሸቱ

እንደምን ሰነበታችሁ? ልጆች ደህና ናችሁ? መልካም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አሁን የአብይ ጾም አራተኛው ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን ይህ ሳምንት መፃጒዕ ይባላል፡፡ በዚህ ሳንምንት በቤተ ክርስቲያን የሚቀርቡ ምስጋናዎች ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጋችውን ድንቅ ድንቅ ተአምራት /ህሙም መፈወሱን፤ ሙት ማስነሣቱን/ የሚያዘክሩ ናቸው፡፡

መፃጒዕ ማለት ልጆች ድውይ፣ ሕመምተኛ ማለት ነው፡፡ በኢየሩሳሌም አንዲት ቤተሳይዳ ተብላ የምትጠራ የመጠመቂያ ቦታ ነበረች፡፡ ይህቺ የመጠመቂያ ቦታ ጠዋት ጠዋት የእግዚአብሔር መልአክ በክንፉ ያማታታል፣ ያናውጣታል፡፡ በዚህ ሰዓት ወዲያውኑ ገብቶ የተጠመቀ ካለበት በሽታ ሁሉ ይድናል፤ ይፈወሳል፡፡

በዚህች የመጠመቂያ ቦታ 38 ዓመት ሙሉ የተኛ በሽተኛ ነበር ከአልጋው መነሣት ስለማይችል መልአኩ ውኃውን ሲያማታው ቀድሞ መግባትና መጠመቅ አልቻለም ከዕለታት አንድ ቀን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ሲያልፍ ይህንን መፃጒዕ /ድውይ/ አየውና “ልትድን ትወዳለህን?” አለው ያም መፃጒዕ “ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ሌላው ቀድሞኝ እየገባ ይፈወሳል፡፡ “አለው ጌታችንም ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ አለው ያም መፃጒዕ ዳነና 38 ዓመት ሙሉ ተኝቶባት የነበረችውን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤቱ ሔደ ዮሐ.5፥1-9

በሉ ልጆች በሚቀጥለው ሳምንት ስለተከታዩ የአብይ ጾም ሳምንት ይዤላችሁ እመጣለሁ እስከዚያው መልካም የጾም ሳምንት ደህና ሰንብቱ፡፡