ውኃ የሌለባቸው ምንጮች
ውኃ ከምንጭ ተገኝቶ እየፈሰሰ የፍጥረትን ጥማት ያረካል፡፡ በውኃ ሰው ሕይወቱን ያለመልማል፤ እንስሳትና አራዊትም እንዲሁ፡፡ ዕፅዋትና አዝርዕትም ያለ ውኃ አይለመልሙም፤ አይበቅሉምም፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ የአገባቡ መምህራን በውኃ ምንጭ ተመስለዋል፡፡ ከምንጭ ንጹሕ ውኃ ተገኝቶ ፍጥረትን እንደሚያረሰርስ ከመምህራንም አንደበት በውኃ የሚመስል ቃለ እግዚአብሔር እየፈሰሰ የሰው ልጆችን በጽድቅ እንዲኖኑ ያደርጋል፡፡ ምእመናን ውኃ ቃለ እግዚአብሔር ከሚገኝባቸው እውነተኞች መምህራን እግር ሥር ተገኝቶ በመማር ከድርቀት ኃጢአት ወደ ልምላሜ ጽድቅ ይመጣሉ፤ የመንፈስ ፍሬንም ያፈራሉ፡፡