‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ›› (ዘፀ. ፮፥፪)
እግዚአብሔር አምላካችን ሰማይና ምድርን፣ መላእክትን፣ ሰውን እንዲሁም ፍጥረታትን በሙሉ የፈጠረ አምላክ ነው፡፡ ለፍጥረታቱም ህልውናውን እንደብቃታቸው ይገልጻል፤ በጥንተ ተፈጥሮ እግዚአብሔር አምላክ መላእክትን ለባውያን (አዋቂዎች) አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ በሰጣቸው ዕውቀት ተመራምረው ፈጣሪያቸውን ያመልኩት ዘንድ እንዲሁም ከባሕርዩ ፍጹም ርቀት የተነሣ በመካከላቸው ሳለ ተሰወረባቸው፡፡ መላእክትም ተፈጥሮአቸውንና ፈጣሪያቸውን መመርመር ጀመሩ፤ አንዱም ለአንዱ ‹‹አንተ ምንድን ነህ? ከየትስ መጣህ?›› ይባባሉ፣ እርስ በርሳቸውም እየተያዩ በተፈጥሮአቸው ይደነቁ ነበር፡፡ በኋላም ‹‹ማን ፈጠረን? ከየትስ መጣን?›› የሚለው የማኅበረ መላእክት ጥያቄ መበርታቱን የተረዳው ሳጥናኤል ሹመቱ ከሁሉ በላይ ነበርና አሻቅቦ ቢያይ ‹እኔ ነኝ ባይ› ድምጽ አጣ፤ ዝቅ ብሎም ቢያዳምጥ ከእርሱ በክብር ያነሱ መላእክት ይመራመራሉ፤ ‹ለምን እኔ ፈጠርኳችሁ ብዬ ፈጣሪነትን በእጄ አላስገባም› ብሎ አሰበ፤ ከዚያም ‹እኔ ፈጣሪያችሁ ነኝ› በማለት ተናገረ፡፡…