የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት (ሰሙነ ሕማማት)

ካለፈው የቀጠለ…

ሚያዚያ ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ‹‹ሁሉ ተፈጸመ› አለ፡፡ ያን ጊዜም   ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ፡፡ አይሁድም ቀጣዩ ቀን ሰንበት ነውና እኒህ ሰዎች እንደተሰቀሉ አይደሩ ብለው ጭን ጭናቸውን ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ጠየቁት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ ጭፍሮቹም የሁለቱን ወንበዴዎች ጭናቸውን ሰብረው አወረዷቸው፡፡ ወደ ጌታችንም ሲቀርቡ ፈጽሞ ሞቶ አገኙት፤ በዚህም ‹‹ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንቱንም አትስበሩ›› ተብሎ የተነገረው ምሳሌያዊ ትንቢት ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ ጭኑን ሳይሰብሩት ቀሩ፡፡ (ዘፀ.፲፪፥፵፮)

ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ‹‹ወአሐዱ እምሐራ ረገዞ ገቦሁ በኲናት፤ ከጭፍሮቹም አንዱ ቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው›› እንዲል፤ ከወታደሮቹ አንዱ የሆነው ለንጊኖስ የጌታችንን ጎን ቢወጋው ትኩስ ደምና ቀዝቃዛ ውኃ ፈሷል፡፡ ለንጊኖስ አንድ ዓይኑ የጠፋ ሰው ሲሆን ጌታችን በተሰቀለበት ጊዜ ወደጫካ ሸሽቶ ርቆ ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ በዚህ ሰው ሞት አልተባበርም በማለት ነው፡፡ በኋላ አመሻሽ ላይ የአይሁድ አለቆች ሲመለሱ ከመንገድ አገኘቱ ስለምን ከመሢሁ ሞት አልተባበርክም አሉት፤ እርሱም ምንም ስላላገኘሁበት አላቸው፤ በኋላ እንደሕጋቸው እንደሚቀጡት ቢነግሩት እየሮጠ ሔዶ፤ የጌታችንን ጎን ሲወጋው ደሙ በዓይኑ ላይ ፈሰሰ፤ ያን ጊዜም ዓይኑ በራለት፡፡ ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደም እንደ ቅርጽ በመሆን በሁለት ወገን ደምና ውኃ ሆኖ ነው፡፡ ከጌታችንም የፈሰሰውን ትኩስ ደም መላእክት በጽዋ ብርሃን ቀድተው በምድር ላይ ረጩት፤ ይህ መሠረት ሆኖ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታነጸው እግዚአብሔር ባወቀ ደሙ የነጠበበት ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው፤ ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔር በደሙ የዋጃትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን›› በማለት የቅድስት ቤተክርስቲያንን ክብር የሚመሰክረው፡፡ ዛሬም ምእመናን የልጅነት ጥምቀትን ስንጠመቅ ውኃውን ካህኑ ሲባርከው በዕለተ ዐርብ ከጌታችን ጎን ወደ ፈሰሰው ማየ ገቦነት (የጎን ውኃ) ይቀየራል፡፡ በዚህ ላይም ስንመለከት የጌታችን ሞት የሚደንቅና የሚገርም ነው፡፡  (ዮሐ.፲፱፥፳፣ ሐዋ.፳፥፳፰)

የጌታችን ሥጋ ወደ መቃብር መውረዱ

ጌታችን የተቀበረበት ሥፍራ ለተሰቀለበት ቦታ አቅራቢያ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ሲመሽ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ወደ ጲላጦስ ሄደው የጌታን ሥጋ አውርደው ይቀብሩ ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ ከዚያም ከመስቀል አውርደው  ዮሴፍ ለራሱ ብሎ ባሳነጸው በአዲስ መቃብር ለመቅበር በኀዘንና በልቅሶ በአዲስ በፍታ ሲገንዙትም የጌታችን ዓይኖች ተገለጡ፤ ‹‹እንደፍጡር ዝም ብላችሁ ትገንዙኛላችሁን? በሉ እንዲህ እያላችሁ ገንዙኝ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ… እያላችሁ ገንዙኝ›› አላቸው፤ እነርሱም እንዳለቸው አደረጉ፡፡ ትልቅ ድንጋይም አምጥተው በመቃብሩ ላይ  ገጠሙት፡፡ የአይሁድ አለቆች ግን ‹‹ክርስቶስ እነሣለሁ ብሏል፤ ስለዚህ ሐዋርያት ሰርቀው ተነሥቷል እንዳይሉን መቃብሩን እናስጠብቅ›› ብለው ጠባቂዎችን ቀጠሩለት፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፳፯)

የጌታችን ዓይኖች ሞቶ ሳለ ስለምን ተገለጡ?

ጌታችንን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሲገንዙት ዐይኖቹ ተከፍተው ተናግሯል፡፡ እንዴት ነፍስ ተለይታ ዓይኖቹ ተከፈቱ? እንዴትስ ተናገረ? ብንል የጌታችን ሞት የነፍስ ከሥጋ መለየት እንጂ የመለኮት መለየት አይደለም፡፡ ዓይኖቹም የተከፈቱት በሞተ ጊዜ መለኮት ከሥጋ እንዳልተለየ ለማጠየቅ ነው፡፡ መለኮት ከነፍስም ባለመለየቱ ነፍሱ ወደሲኦል ሄዳ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፡፡ ሌላው ሙስና መቃብርን ማጥፋቱንና በትንሣኤ ዘጉባኤ ለሥጋችን ትንሣኤ እንዳለው ሲያስረዳን ነው፡፡ ሠልጥኖብን የነበረው ሙስና መቃብር (በስብሶ መቅረት) ጌታችን በሞቱ አጠፋልን፡፡

የሲኦል መበርበር

‹‹ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ጻድቅህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አልተወውም›› እንዳለ ጌታችንም ነፍሱን በገዛ ሥልጣኑ ከሥጋው ከለየ በኋላ ሥጋው ወደ መቃብር ወረደ፤ ነፍሱ ደግሞ ወደ ሲኦል ሄዳ የሲኦልን በር ሰብሮ ገባ፤ አጋንንትና ሠራዊቱ ሸሹ፡፡ አዳም ጌታን ባየው ጊዜ በሲኦል የነበሩትን  ነፍሳት ‹‹ተንሥኡ ለጸሎት፤ ለጸሎት ተነሡ›› አላቸው፤ እነርሱም እግዚኦ ተሠሃለነ፤ አቤቱ ይቅር በለን›› አሉ፤ ጌታም ‹‹ሰላም ለኵልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን›› አላቸው እነርሱም ‹‹ምስለ መንፈስከ፤ ከመንፈስህ ጋራ›› አሉ፡፡ ይህም ዛሬ በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ ዲያቆኑ የአዳም፤ ካህኑ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ (መዝ.፲፭፥፲)

ጌታችን በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወርዶ በመቃብር ያሉትን ሙታን አስነሣ፤ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ገብቶ በዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ሁሉ ነፃ አወጣ፡፡ ያን ጊዜ መቃብራት ተከፈቱ፤ ከእግረ መስቀሉ ሥር የነበሩ ሙታን ተነሡ፡፡ ሲኦልን የሚጠብቁ የአጋንንት አለቆች ጌታችንን ባዩ ጊዜ ተሸበሩ፤ ሠራዊተ አጋንንትም ተንቀጠቀጡ፡፡ ሲኦልንም ጥለው ሸሹ፤ ደጆችዋም ተሰበሩ፡፡ ፍዳና መርገምን አጠፋልን፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው ‹‹ሲኦል ተነዋወጠች፤ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፤ ምድርን ያለጊዜዋ እንዳታልፍ አጸናት፤ ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፤ ከኅልፈት ጠበቃት፤ በእርሷ ያለውንም ሁሉ ጠበቀ›› በማለት ተግዘው የነበሩትን የወገኖቹን ሁሉ ከሲኦል እንዳወጣ ተናገር፡፡ (ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ)

፮. ቀዳም ሥዑር

የማትጾመዋ ቅዳሜ (ቀዳም ሥዑር) ስለምትጾም ወይም በጾም ስለተሻረች እንጂ  በዓል መሻርን የሚመለከት አይደለም፡፡ በቀዳም ሥዑር ሌሊት ነገረ ሕማማቱን የሚዘክረው መላው ሥርዓተ ማኅሌቱ ‹‹ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ፤ የሕይወትን ጌታ ግን ሰቀሉት›› በሚለው ሥርዓተ ዜማ ይጠናቀቃል፡፡ ከዚያም ገብረ ሰላም በመስቀሉ እየተባለ እየተዘመረ ቄጠማውም ቤተ መቅደሱን ዞሮ በካህናቱ ተባርኮ ለምእመናን ይታደላል፡፡ የቄጠማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ሲሆን ምድር በማየ አይኅ (በጥፋት ውኃ) በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቄጠማ ይዛ በመመለስ ነውና፡፡

ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጎደለ፣ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ፤ ታወጀ፤ በማለት ካህናቱ ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ምእመናን ሁሉ በየዓመቱ ሰሙነ ሕማማትን ራስን ከፈቃደ ሥጋ ከልክለው በቅድስት ቤተክርስቲያን በሚካሄደው ሥርዓተ ሕማማቱ ላይ  በመሳተፍ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት ይሰነብታሉ፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ከበረከተ ሕማሙ ያሳትፈን፤ አሜን፡፡