ጾመ ሐዋርያት

በተክለሐዋርያት

ጾመ ሐዋርያት በወርኃ ሰኔ ስለሚጾም በምእመናን ዘንድ የሰኔ ጾም በመባል ይታወቃል፤ ከሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማትም አንዱ ነው፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለስብከተ ወንጌል ከመሰማራታቸው በፊት የጾሙት ጾም ነው፡፡

ይህም ጾም ከበዓለ ኀምሳ በኋላ የሚጾም ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን ቅዱሳን ሐዋርያት በጸሎት ይተጉ ወደ ነበረበት ቤት በመሄድ ደቀመዛሙርቱን ይዟቸው ከቤት በመውጣት መንገድ ጀመረ፡፡ እርሱ ከፊት እየመራቸው እነርሱ እየተከተሉት ወደ ረጅሙና በረጃጅም ዛፎች ወደ ተሞላው ደብረ ዘይት ተራራ ይዟቸው ወጣ፡፡ ይህንንም እየነገራቸው ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ፤ከፍ አለ፡፡ ነጭ የሆነች ብሩህ ደመናም አምላካችንን ተቀበለችው፡፡ከዓይናቸውም እየራቀ፤ከእይታቸው በርቀት ሳይሆን በርኅቀት ተሰወረባቸው፡፡ሐዋርያትም ኢየሱስ ክርስቶስን በጣም ይወዱት ስለነበር ሲለያቸው አዝነው አተኩረው ሰማዩን ለረጅም ሰዓት ተመለከቱ፡፡ ድንገትም ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ቅዱሳን መላእክት በአጠገባቸው ቆመው ታዩአቸው፡፡መላእክትም ሐዋርያትን እንዲህ አሏቸው፤ ‹‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን  ቆማችኋል፡፡ ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል›› አሏቸው፤ (ሐዋ. ፩፥፰-፲፩)፡፡ ሐዋርያትም የመላእክትን ማረጋጊያ ቃል ከሰሙ በኋላ  በኢየሩሳሌም ወደ ምትገኘው ቤተ መቅደስ በመሄድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነገራቸው እስኪፈጸም ድረስ ቀን ከሌሊት በአንድነት ሆነው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከመካከላቸው አድርገው በጾምና በጸሎት እየተጉ ቆዩ፡፡

የጾመ ሐዋርያት የጊዜ ቀመር ሥሌት በዓለ ጰራቅሊጦስ እንደ ገባ ባለው የመጀመሪያው ሰኞ ይውላል፡፡ ጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ደቀ መዛሙርቱን ይህን ጾም እንደሚጾሙት እንዲህ ተናግሮ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው። ‹‹እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ እንጾማለን፥ ደቀ መዛሙርትህስ ለምን አይጾሙም? አሉት›› (ማቴ.፱፥፲፬)።  ደቀ መዛሙርቱ ይህንን በጠየቁት ጊዜ ጌታችን እንዲህ ብሎ መልሶላቸው ነበር፡፡‹‹ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው  ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ አይችሉም፤ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ያንጊዜም ይጾማሉ›› (ማቴ.፱፥፲፭)፡፡

እኔ ሳለሁ አይጾሙም ማለቱ እርሱ ካልሞተና ካላረገ፤ መንፈስ ቅዱስም ካልተሰጣቸው በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነት ጾመው ድል መንሳት ስለማይቻላቸው ነው፡፡ ይህን ጾም የምንጾመው ሐዋርያት ጾመው ጸልየው ድል ያደረጉትን ዓለም እኛም የምናሸንፍበት ኃይል እንዲሰጠን ፈጣሪያችንን አምላከ ሐዋርያት ተለመነን እያልን ለመማጸን ነው፡፡

ይህን ጾም እንደ ሌሎቹ አጽዋማት ሁሉ እያንዳንዱ ምእመን ሊጾመው የሚገባ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን አብዛኛው ምእመን ‹‹የቄስ ጾም›› ነው በማለት ከጾሙ ሽሽት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሥርዓተ ቤተክርስትያንን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ መስተካከል ይገባዋል፡፡

ሐዋርያትን አብነት በማድረግ ጾመን በረከትን ልናተርፍ ይገባናል፡፡

የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት

የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት

የቅዱሳን ሐዋርያት በረከት

የጻድቃን የሰማዕታት ጸሎት እና ምልጃ አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

አሜን፡፡

‹‹እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቆያለሁ›› (፩ኛቆሮ.፲፮፥፰)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የቤተክርስቲያን የልደት ቀን ብሎ የጠራው ቀን በዓለ ኃምሳ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ እንደሚከበር ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ምስክር ነው፡፡በዓለ ኃምሳ፤ በዓለ ጰራቅሊጦስ፤ በዓለ ጰንጠቆስጤ እየተባለም ይጠራል፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተነገረም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለቅዱሳን ሐዋርያት፤ ለሰብአ አርድእትና ለቅዱሳት አንስት ጸጋውን ያደለበት፤ ምሥጢራትን የገለጠበት፤ መንፈሳዊ ጥብዓትን (ጥንካሬን) የሰጠበት፤ ታላቅ ቀን ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ዓለምን የሞላችው ወደ ሁሉ የደረሰችው በዚህ ቀን ከመንፈስ ቅዱስ በተቀበለችው ጸጋ ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደመሠከረው መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላት ኖሮ የቤተክርስቲያን ሕልውና ከስሞኖ ቀጭጮ ይቀር ነበርና ነው፡፡

ይህች ቀን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩኤል አንደበት ‹‹ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞ በዚያም ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎች ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፡፡›› በማለት የተናገረው ትንቢታዊ ኃይለ ቃል ፍጻሜውን ያገኘበት ዕለት ናት፡፡ ይህች ቀን ቅድመ ሥጋዌ በነቢዩ አንደበት ይህን የተናገረ አምላክ በፍጹም ተዋሕዶ በሥጋ ማርያም ተገልጦ ለአባቶቻችን ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጠው የተስፋ ቃል የተፈጸመባት ዕለት ናት፡፡ (ኢዩ.፪፥፳፰፤የሐዋ.፪፥፲፯)

በዓለ ኃምሳ፤ በዓለ ጰራቅሊጦስ፤ በዓለ ጰንጠቆስጤ እየተባለ የሚጠራ እንደመሆኑ መጠን ይህ ወቅት የነገረ መንፈስ ቅዱስ ትምህርት በስፋት የሚሰበክበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህም በመነሣት እግዚአብሔር የፈቀደልንንና የገለጠልንን ያህል ስለ መንፈስ ቅዱስ በነገረ መለኮት ትምህርት  መማር እንችላለን፡፡ በዚህ ትምህርት ውስጥም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማንነት እርሱ በገለጠላቸው መጠን አምልተው አስፍተው ያስተምራሉ፡፡

በመንፈስ ቅዱስ ላይ የተነሡ የክሕደትና የኑፋቄ ትምህርቶችንም ይመረምራሉ፤ ለሚነሡ የክሕደት ትምህርቶችም ኦርቶዶክሳዊ ምላሽን ይሰጣሉ፤ የክሕደቱ አመንጪ መናፍቃንንም ማንነትና የክሕደት ምክንያቶቻቸውን ይገልጣሉ፡፡

መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን የሚያድለው እርሱም የሚገኘው አንድነትና መተባበር ባለበት ሥፍራ ነው፡፡ በዕለተ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ጸጋውን ያደላቸው በአንድነትና በእምነት ተሰብስበው በነበሩበት ሁኔታ እንደነበር መጽሐፍ ሲነግረን «በዓለ ኃምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ›› ይለናል፡፡ (የሐዋ.፪፥፩-፪) እኛም የአባቶቻችን ልጆች በመሆናችን እርሱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አናምናለን፡፡

 

መንፈስ ቅዱስ

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ብዙዎች የተለያየ ግንዛቤ አላቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደ ረቂቅ ኃይል ይመለከቱታል፡፡ ሌሎች ደግሞ  እግዚአብሔር ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ የገለጠውና ማንነት የሌለው ኃይል እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሆነ ያውጃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም  አእምሮ ያለው ማንነት፤ ስሜትና ፈቃድ ያለው መለኮታዊ አካል እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ «እኔ እግዚአብሔር በምልበት ጊዜ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለቴ ነው» ብሎ እንደተናገረው እግዚአብሔር የሚለው ስም የሥላሴ መጠሪያ ነው፡፡ የአብ የወልድ እስትንፋሳቸው የሆነ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ ጋር በዕሪና በፍጹም መተካከል ያለ ነውና እግዚአብሔር መሆኑን እንመሠክራለን፡፡ ይኽውም የቅዱሳን ነቢያት ሐዋርያትና መምህራን ትምህርት ምስክር ነው፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ ንጉሡ በራእዩ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ እንዳየው፤ ሱራፌልም በሁለት ክንፎቻቸው ፊታቸውን፤ በሁለት ክንፎቻቸው እግሮቻቸውን እየሸፈኑ፤ በሁለት ክንፎቻቸውም ከጽንፍ ጽንፍ እየበረሩና አንዱም ለአንዱ «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ በቸርነትህ ተሞልታለች» እያሉ እንደሚያመሰግኑት ነግሮናል፡፡ ሊቃውንቱ ሱራፌል ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ያመሰገኑበትን ምሥጢር ሲያብራሩ፤ ቅዱስ የሚለው ቃል አለመለወጡ፤ ሦስቱ አካላት በባሕርይ፤ በህልውና፤ በሥልጣን፤ በአገዛዝና በመሳሰለው አንድ መሆናቸው ሳይለወጥ ሦስት መሆኑ የእግዚአብሔርን የአካል ሦስትነት የሚገልጥ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡(ኢሳ.፮፥፩-፱) ይህ የሊቃውንቱ ትምህርት እውነተኛ መሆኑ ማስረጃው ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ቅዱስ መነጽር እንደተመለከተው በሐዲስ ኪዳንም የራእይ አባት (አቡቀለምሲስ) የተባለው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም በእግዚአብሔር ዙፋን መካከል ያሉ የሰው፤ የአንበሳ፤ የላምና የንሥርን ፊት ይመስላሉ፡፡ እነርሱም ኪሩቤል ቃሉ ሳይለወጥ «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ፤ የነበረና ያለ፤ የሚመጣውም፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ» እያሉ ቀንና ሌሊት ያለ ዕረፍት እንደሚያመሰግኑ መናገሩ ነው፡፡ (ራእ.፬፥፰)

ዳግመኛም ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ ፮ ቁጥር ፱ ላይ «የጌታንም ድምጽ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?» ሲል ሰማሁ ይላል፡፡ ተናጋሪው ጌታ እግዚአብሔር ማንን እልካለሁ? ማለቱ ባሕርያዊ አንድነቱን ማንስ ይሄድልናል? ብሎም ሦስትነቱን ገልጧል፡፡ ነቢዩ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ብሎ እግዚአብሔር ለተናገረው ነገር ‹‹እኔን ላከኝ›› ካለው በኋላ በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ተቀምጦ የተገለጠለት እግዚአብሔር ‹‹ሂድና ይህን ሕዝብ መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱም፤ በላቸው አለኝ›› በማለት ተናገረ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉና ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር መሆኑን በግልጥ መስክረዋል፡፡(ዮሐ.፲፪፥፴፱-፵፩፤የሐዋ.፳፰፥፳፭-፳፯) ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ኃይለ ቃል ብቻ ሳይሆን በኦሪት፤ በነቢያት፤ በጸጋና በረድኤት አድሮባቸው ሕዝቡን ሲመክር፤ሲያስተምርና ሲገሥጽ የነበረ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ደጋግሞ አስተምሯል፡፡ ይኽው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በፍጹም የማይመረመር፤ የማይታወቅ፤ የእግዚአብሔር ጥልቅ ባሕርይ የሚታወቀው፤ በራሱ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ የመንፈስ ቅዱስን ነገር በስፋት እንዳስተማረ እንረዳለን፡፡(፩ቆሮ.፪፥፲፩፤ዕብ.፫፥፯)

መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር የመሆኑ እውነታ  በብዙ ቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ በግልጽ ተነግሮአል፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናንያ ለምን እንደዋሸ ሲጠይቀው  ‹‹ሐናንያ ሆይ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን ስለምን በልብህ ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥከውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህንን ነገር በልብህ ስለምን አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው›› ይለናል፡፡ እንግዲህ ከዚህ ኃይለ ቃል ሐናንያ እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን እንዳልዋሸ፤ ይህ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሆነ በግልጽ እንረዳለን(የሐዋ.ሥራ ፭፥፫-፬)፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ «አቤቱ  ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፤ አንተ በዚያ አለህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፤ በዚያ አለህ።» በማለት ተናግሯል፡፡ ይህ ደግሞ በሰማይ በምድርም፤ በጠፈርም በጥልቁም ምሉዕ ሆኖ መገኘት የእግዚአብሔር መለኮታዊ ባሕርዩ ስለሆነ መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ሥፍራ የሚገኝ ፍጹም ምሉዕ አምላክ መሆኑን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ይነግረናል (መዝ. ፻፴፱፥፯-፰)፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእርግጥ መለኮታዊ ማንነት እንደሆነ ማወቅ እንችላለን፤ ምክንያቱም አዕምሮ፤ ስሜቶችና ፈቃድ አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያስባል፤ያውቃልም (፩ኛ ቆሮ. ፪፥፲)፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሊያዝን ይችላል፡፡  (ኤፌ. ፬፥፴) መንፈስ ለእኛ ይማልድልናል (ሮሜ ፰፥፳፮-፳፯)፡፡ እንደ ፈቃዱ ውሳኔዎችን ያደርጋል፡፡ (፩ኛ ቆሮ.፲፪፥፯-፲፩) መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ጻድቁ ኢዮብም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፤ ሁሉን የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ›› እንደዚሁም ‹‹በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ›› በማለት ደጋግሞ መናገሩ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ መሆኑን ያስረዳል፡፡እነዚህ ኃይለ ቃላት የሚያስረዱን መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ፤ ሁሉን ቻይና የአምላክ (የአብ የወልድ) እስትንፋሳቸው መሆኑን ነው፡፡

እግዚአብሔር አካላዊም ነው፡፡ ነገር ግን እንደፍጡራን አካል በሰው ልጅ ልቡና የሚመረመር  አይደለም፡፡ (ኢዮ.፲፩፥፯፤፩ቆሮ.፪፥፲-፲፭፤ሮሜ ፲፩፥፴፫) ወንጌላዊው ዮሐንስም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አካል ረቂቅ መሆኑን ሲያስተምር «እግዚአብሔር መንፈስ ነው» ብሎናል፡፡ (ዮሐ. ፬፥፳፬) እግዚአብሔር መንፈስ መባሉም አካል የሌለው ማለት ሳይሆን አካሉ የማይመረመር የማይዳሰስ የማይጨበጥ የማይታይ መሆኑን ለመገለጽ ሲሆን መንፈስ ቅዱስም መንፈስ መባሉም አካላዊና አካሉም ረቂቅ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ቃለ ሰብእ እንደ ቃለ መላእክት ዝርው ያይደለ፤ የአብ የመንፈስ ቅዱስ አካላዊ ቃል እንደሚባል ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ (ዮሐ.፩፥፩-፫) ስለዚህም ሁሉን የሚችል የአምላክ እስትንፋስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ የአብ የወልድ አካላዊ እስትንፋሳቻው ነው፡፡ አካላዊ በመሆኑም ከአብና ከወልድ ጋር በክብር ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ለነቢዩ ኢሳይያስ ተገልጧል፡፡(ኢሳ.፮፥፩-፱፤የሐዋ. ፳፰፥፳)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክቱ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ በመሆኑ የአካል ክፍል በሆነው አንደበቱ እየተናገረ እንዲህ ሲል መስክሯል ‹‹መንፈስ ግን በግልጥ በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንት ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል (ይናገራል)››፡፡ (፩ጢሞ.፬፥፩) መንፈስ ቅዱስ መምከር ብቻ ሳይሆን ለሐዋርያትም ስለ አገልግሎታቸው መመሪያን ይሰጣቸው እንደነበርም ‹‹እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ›› በማለት ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ መንፈስ ቅዱስ አካላዊነት ይናገራሉ፡፡ (የሐዋ.፲፫፥፪) በሰማይ ድል ስለነሱ ቅዱሳን‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ለጌታ የሚሞቱ ብፁዓን ናቸው›› ተብሎ በተነገረ ጊዜም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የእኛን አካል የፈጠረ አካላዊ ነውና ‹‹አዎን ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸውም ይከተላቸዋል›› ብሎ እንደነገረው ባለራእዩ ቅዱስ ዮሐንስ  አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ (ራእ.፲፬፥፲፫) ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዕርገቱ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ወደ እነርሱ እንደሚመጣና ሁሉን እንደሚያስተምራቸው፤ምሥጢራትንም እንደሚገልጥላቸው፤ተአምራት የሚያደርጉበትን ጸጋና ሥልጣንም እንደሚሰጣቸውና መከራን ሁሉ እንዲችሉ ኃይልን እንደሚያስታጥቃቸው በሚገባ አስተምሯቸዋል፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፳፮)

አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና መንፈስ ቅዱስ የሚሠርጸው ከአብ ብቻ እንደሆነ ‹‹ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለእኔ ይመሰክራል›› በማለት ለቅዱሳን ሐዋርያት አስቀድሞ ነግሮአቸዋል፡፡ (ዮሐ.፲፭፥፳፮) መንፈስ ቅዱስ ከአብ ጋር ወልድን ለድኅነተ ዓለም እንደላከም ተብሎ ተጽፏል ‹‹አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል›› እንዳለ ፊተኛና ኋለኛ አልፋና ዖሜጋ፤ መጀመሪያውና መጨረሻው የሆነ እግዚአብሔር ወልድም ከዕርገቱ በኋላ በደልን ለማንጻት ምሥጢራትን ለመግለጽ በመንፈሳዊ ሐሴት ኃጢአትን ለማስተሥረይ ከአብ ጋር ሆኖ የባሕርይ ሕይወቱ የሆነ መንፈስ ቅዱስን ልኮታል፡፡ (ኢሳ.፵፰፥፲፪-፲፮፤ራእ.፩፥፰፤፳፪፥፲፫) ሃይማኖታቸው የቀናች ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ሊቃውንትም በጉባዔ ኒቅያ መቶ ሃምሳው ሊቃውንት በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ጌታችን በወንጌል ያስተማረውን ትምህርት መሠረት አድርገው በጸሎተ ሃይማኖት ‹‹ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ ዘሠረጸ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት፤በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን እርሱም ጌታ ሕይወትን የሚሰጥ ከአብ የሠረጸ ከአብና ከወልድ ጋር በአንድነት እንሰግድለታለን እናመሰግነዋለን፤ እርሱም በነቢያት አድሮ የተናገረ ነው›› ብለው አውጀዋል፡፡

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ባለበት ሥፍራ ሁሉ አርነት አለ፡፡‹‹የጌታ መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ›› ተብሎ እንደተጻፈ፤ አርነቱም ከዲያብሎስ አገዛዝ፤ ከሰይጣናዊ አሠራር፤ ከኃጢአትና ከሥጋ ፈቃድ ሁሉ ነው፡፡ (፪ቆሮ. ፫፥፲፯፤ገላ. ፭፤፲፱) ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በወረደላቸው ጊዜ አልጮኹም፤ ተንቀጥቅጠው አልወደቁም፤ የነበሩበትን አካባቢ በጩኽት አላወኩም፤ የእግዚአብሔር የሆኑትን አልተሳደቡም፡፡ የተገለጠላቸውና የተናገሯቸው ቋንቋዎችም፤ በወቅቱ ከመላው ዓለም የመጡ ሰዎች ይናገሩባቸው የነበሩ ቋንቋዎች (ልሳናት) ናቸው፡፡ቅዱሳን ሐዋርያት ከመንፈስ ቅዱስ በተገለጠላቸው የተለያዩ ቋንቋዎች ዓለም ክርስቶስን በማመን፤ ጽድቅን በመከተል፤ የሰውን ዘር በሙሉ እንደራሱ እንዲወድ፤ ለኔ የሚያስፈልገኝ ለሌላውም ያስፈልገዋል እንዲል አስተማሩት፡፡መንፈስ ቅዱስ ባለበት ሥፍራ ከልዩነት አንድነት፤ ከእኔነት ይልቅ ለእኛ ማለት፤ ከመገፋፋት መደጋገፍ፤ ከመበታተን መሰባሰብ፤ ከትዕቢትና ከዕብሪት ትሕትና ጎልቶ ይታያል፡፡ስለዚህም በቅዱሳት መጻሕፍት ‹‹መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን›› እንደዚሁም ደግሞ ‹‹በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ›› ተብሎ እንደተነገረ፤ የምንጓዝበትን መንገድና አስተሳሰባችንን ከዚህ አንጻር ልንመረምር ይገባናል፡፡ (ሰቆ.ኤር. ፫፥፵፤፪ቆሮ.፲፫፥፭)

የጸጋ ሁሉ ባለቤት፤ ፈጣሪ ፍጡራን፤ አምጻኤ ዓለማት፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በቸርነቱ ለክብርና ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃን፤ አሜን!!!

ለ፲፰ ቀናት የቆየው የ፳፻፲፩ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ውሳኔዎችን አሳለፈ

በሕይወት ሳልለው

 ከግንቦት ፲፬ እስከ ሰኔ ፫ ፳፻፲፩ ዓ.ም ድረስ የተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የ፳፻፲ እና ፳፻፲፩ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳላፉን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመግለጫቸው አስታወቁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በመንቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ኃላፊነቷን ለመወጣት የሚያስችል ውሳኔ መወሰኑን ይፋ አድርገዋል፡፡ ለተቃጠሉት አብያተ  ክርስቲያናት መልሶ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰቡን ፤ ምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃትና በሀገር ደረጃ ሰላም፤ፍቅርና አንድነት እንዳይኖር የሚያግዱ ችግሮችን ማውገዙንና ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን ቅዱስ ፓትርያርኩ ገልጸዋል፡፡ «በውጭ ሀገር የሚገኙ አህጉረ ስብከቶችን የቤተ ክርስቲያንን በማጠናከር መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ማስፋፋት እንዲቻል ቃለ ዓዋዲው ከየሀገራቱ መንግሥታት ሕግ ጋር የተጣጣመ ደንብ ሆኖ እንዲዘጋጅና ለጥቅምት ፳፻፲፪ ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል» ብለዋል፡፡

በተለይም ከቀናት በፊት ቅዱስ ሲኖዶሱ ስላወገዘው የግብረ ሰዶማውያን እንቅስቃሴም ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳስበዋል፡፡ «የሀገራችንን የቱሪስት መስሕብነት ምክንያት በማድረግ ዜጎች በቅድስናና በፈሪሀ እግዚአብሔር ተከብረው የሚታወቁባትን የሀገራችንን ታሪክ የሚቀይር፤ የዜጎችን መልካም ሥነ ምግባር የሚለውጥ፤ ሕገ ተፈጥሮንና የተቀደሰውን ሥርዓተ ጋብቻን የሚያበላሽ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የተወገዘ ግብረ-ሰዶምን በሀገራችን ለማስፋፋት፤ በዚህም የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ቅድስና የሚጎዳ ሕገ-ወጥ ተግባር ለመፈጸም መቀመጫውን በአሜሪካን ሀገር ያደረገው የግብረ-ሰዶማዊያን አስጎብኚ ድርጅትን በመቃወም ወደ ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዳይገባ፤ቅዱሳት መካናትንም እንዳይጎበኝ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው አውግዟል»

እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ምልአተ ጉባኤው በውይይቱ ላይ  ፲፭ ዋና ዋና ጉዳዮች ያነሳ ሲሆን በእያንዳንዳቸው ላይ ጥናት በማካሄድና ችግሮቹን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሚል ባለሞያዎችንም እንደመደበ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በየሦስት ዓመቱ የሚመረጡ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊን የጠቅላይ ቤ ክርስቲያን ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት፤ ሊቀጳጳስ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ እና ብፁዕ አቡነ ያሬድ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ መሰየሙን አሳውቋል፡፡

በመጨረሻም ከ፳፬ ዓመት በኋላ የቤተ ክርስቲያኗ ታላላቅና ሁለት መለስተኛ ሕንጻዎች በአቤቱታ መመለሳቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ግንቦት ፳፱ ቀን መቀበላቸውን ሊቀ ካህናት ኀይለ ስላሴ ዘማርያም ገልጸው ሰኔ ፫ ቀን ርክክቡ በፊርማ ጸድቋል፡፡

 

 

 

 

የአበገደ ፊደላት ትርጉም

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

የአበገደ ፊደላት የየራሳቸው መጠሪያ ስም እና ትርጉም አላቸው፡፡ በመጀመሪያ ፊደላቱን ከዚያም መጠሪያቸውን፤ ማለትም የሚወከሉበትና ትርጉማቸውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡-

አ ፡- አልፍ፤ አሌፍ ብሂል አብ ፈጣሬ ኵሉ ዓለም፤ አ፤ አልፍ፤ አሌፍ ማለት ዓለምን

          ሁሉ የፈጠረ አብ ማለት ነው፡፡

በ፡- ቤት ፡- ቤት ብሂል ባዕል እግዚአብሔር፤ በ፤ ቤት፤ ማለት ባለጸጋ እግዚአብሔር

         ማለት ነው፡፡

ገ፡- ጋሜል፡- ጋሜል ብሂል ግሩም እግዚአብሔር፤ ገ፤ ጋሜል ማለት የሚያስፈራ እግዚአብሔር

          ማለት ነው፡፡

ደ፡- ዳሌጥ፡- ዳሌጥ ብሂል ድልው እግዚአብሔር፤ ደ፤ ዳሌጥ ማለት «ዝግጁ የሆነ»         እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡

ሀ፡- ሄ ፡- ሄ ብሂል ህልው እግዚአብሔር፤ ሀ፤ ሄ ማለት እግዚአብሔር ህልው ዘለዓለማዊ ነው ማለት ነው፡፡

ወ፡- ዋው፡- ዋው ብሂል ዋሕድ እግዚአብሔር፤ ወ፤ ዋው ማለት እግዚአብሔር አንድ ነው

         ማለት ነው፡፡

ዘ፡- ዛይ፡- ዛይ ብሂል ዝኩር እግዚአብሔር፤ ዘ፤ ዛይ ማለት እግዚአብሔር አሳቢ ነው

        ማለት ነው፡፡

ሐ፡- ሔት፡- ሔት ብሂል ሕያው እግዚአብሔር ፤ሐ፤ ሔት ማለት ሕያው፤ ዘለዓለማዊ

          እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡

ጠ፡- ጤት፡- ጤት ብሂል ጠቢብ እግዚአብሔር፤ ጠ፣ ጤት ማለት ጠቢብ፤ ጥበበኛ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡

የ፡- ዮድ፡- ዮድ ብሂል የማነ እግዚአብሔር፣እደ እግዚአብሔር፤ የ፤ ዮድ ማለት የእግዚአብሔር

        ቀኝ ፤ የእግዚአብሔር እጅ ማለት ነው፡፡

ከ፡- ካፍ፡- ካፍ ብሂል ከሃሊ እግዚአብሔር፤ ከ፤ ካፍ ማለት ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር

        ማለት ነው፡፡

ለ፡- ላሜድ፡- ላሜድ ብሂል ልዑል እግዚአብሔር፤ ለ፤ ላሜድ ማለት እግዚአብሔር ታላቅ ነው

     ማለት ነው፡፡

መ፡- ሜም፡- ሜም ብሂል ምዑዝ እግዚአብሔር፤ መ፤ ሜም ማለት ጣፋጭ እግዚአብሔር

      ማለት ነው፡፡

ነ፡- ኖን፡- ኖን ብሂል ንጉሥ እግዚአብሔር፤ ነ፤ ኖን ማለት እግዚአብሔር ንጉሥ ነው ማለት ነው፡፡

ሠ፡- ሣምኬት፡- ሣምኬት ብሂል ሰፋኒ እግዚአብሔር፤ ሠ፤ ሣምኬት ማለት ገዥ  እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡

ዐ፡- ዔ፡- ዔ ብሂል ዐቢይ እግዚአብሔር፤ ዐ፤ ዔ ማለት እግዚአብሔር ታላቅ ነው ማለት ነው፡፡

ፈ፡- ፌ ፡- ፌ ብሂል ፍቁር እግዚአብሔር፤ ፈ፤ ፌ ማለት እግዚአብሔር የሚወደድ ነው ማለት ነው፡፡

ጸ፡- ጻዴ፡- ጻዴ ብሂል ጻድቅ እግዚአብሔር፤ ጸ፤ ጻዴ ማለት እግዚአብሔር እውነተኛ ነው ማለት ነው፡፡

ቀ፡- ቆፍ፡- ቆፍ ብሂል ቅሩብ እግዚአብሔር ፤ ቀ፤ ቆፍ ማለት እግዚአብሔር ቅርብ ነው

        ማለት ነው፡፡

ረ፡- ሬስ ፡- ሬስ ብሂል ርኡስ እግዚአብሔር፤ ረ፤ ሬስ ማለት እግዚአብሔር አለቃ ነው

        ማለት ነው፡፡

ሰ፡- ሳን፡- ሳን ብሂል ስቡሕ እግዚአብሔር፤ ሰ፤ ሳን ማለት እግዚአብሔር ምስጉን ነው

        ማለት ነው፡፡

ተ፡- ታው፡- ታው ብሂል ትጉህ እግዚአብሔር፤ ተ፤ ታው ማለት እግዚአብሔር ትጉህ ነው ማለት ነው፡፡

ኀ የሐ፤ እና ፀ የጸ ድርቦች ተደርገው የግእዝ ፊደል በቊጥር ፳፪ እንደሆኑ የሚገልጹ ሊቃውንት አሉ፡፡ ለምሳሌ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ኀ የሐ እና ፀ የጸ ድርቦች እንደሆኑ ሁለቱ ፊደላት ፐ እና ጰ ደግሞ ከጊዜ በኋላ እንደተጨመሩ ይገልጻሉ፡፡ የተጨመሩበትንም ምክንያት ሲያስረዱ ሁለቱ ፊደላት በጽርእ፣ በቅብጥና በሮማይስጥ ያሉ ፊደሎች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ  መጻሕፍት ደግሞ የተተረጎሙት ከእነዚህ ነውና መጻሕፍቱ ከተተረጎሙበት ቋንቋ ጋር ለማስማማት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ፊደላት ነገረ እግዚአብሔርን እንደሚያስረዱ በሀለሐመ እንዲሁም በአበገደ አስረድተናል፡፡ የጥንቱ የግእዝ ፊደል የአበገደ እንደሆነ በአለፈውም ገልጸናል፡፡ ይህ የአበገደ የፊደል ቊጥር ፳፪ ነው ይህም የ፳፪ቱ ሥነ ፍጥረት ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ ፊደል የዕውቀት ሁሉ መሠረት፤ የጥበብ ምንጭ ነውና ምርምራችንን ከፊደል እንድንጀምር ከሚል እሳቤ ይህን አቅርበናል፡፡

ማስታወሻ፡- ኀ የሐ፣ ፀ የጸ ድርቦች ናቸው ስለተባለ ግን የትርጉም ልዩነት አያመጡም ወይም ተመሳሳይ ድምፆች ( ዘረ ድምፆች) ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ሠረቀ፡- ወጣ፤ ተወለደ፤ ሰረቀ፡- ሰረቀ፤ በንጉሡ «ሠ» እና በእሳቱ «ሰ» ሲጻፍ የትርጉም ልዩነት እንደሚያመጣ ሁሉ ኀ እና ፀም የትርጉም ልዩነት ያመጣሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ፈፀመ በፀሐዩ “ፀ” ሲጻፍ  አሰረ፤ ለጎመ፤ የሚል ትርጉም ሲሰጥ፤ ፈጸመ በጸሎቱ «ጸ» ሲጻፍ ደግሞ ጨረሰ የሚል ትርጉም  ይሰጣል፡፡ እንዲሁም ነስሐ በሐመሩ «ሐ» ሲጻፍ ተጸጸተ፣ ተመለሰ የሚል ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን ነስኀ በብዙኃን «ኀ» ሲጻፍ ደግሞ ሸተተ፤ ከረፋ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ ስለዚህ በቋንቋ ሥርዓት አንድ ድምፅ የፍች (የትርጉም) ለውጥ ካመጣ ሞክሼ ወይም ዘረ ድምፅ ሊባል አይችልም፡፡ በመሆኑም ራሳቸውን የቻሉ የግእዝ ድምፆች እንደሆኑ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ፡- ሐመር ፳፮ኛ ዓመት ቁጥር ፲

ክፉን በጋራ እናርቅ

 መጋቤ ምሥጢር ስንታየሁ አባተ

ኢትዮጵያ ሥነ ፈለክንና ሥነ ከዋክብትን፤ በአንድ አምላክ የማምለክን ፅንሰ ሐሳብ ያበረከተች ሀገር ናት:: በእነዚህ ሁሉ ዘመናት እጅግ ሰፊና ጥልቅ የእምነት የባህል የፍልስፍና አስተምህሮዎችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ስታስተላልፍ ቆይታለች:: ይህ ማለት ደግሞ ዜጎቿ ከጥንት ጀምሮ የራሳቸው የሆነ ጠንካራ የሥነ ጾታ የትዳር የቤተሰብ አስተምህሮ አላቸው:: አንድ ወንድ በአንዲት ሴት፤ አንዲት ሴት በአንድ ወንድ ጸንተው የሚኖሬባት ሀገር ናት፡፡ ተፈጥሯቸው ከሰው እጅግ ባነሱና አእምሮ በሌላቸው በእንስሳት ዘንድ እንኳን የማይታሰብ የተመሳሳይ ጾታ ርኩስነትን የሚጸየፉ መሆናቸውም የዜጎቻችን የማይለወጥ እምነት ነው:: ይህን እምነት በሕዝቡ ልቡና በማሥረፅ ደግሞ ግንባር ቀደም መሪዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ናቸው:: እነዚህ መሪዎች የሚያስተምሩባቸው የተቀደሱና የእግዚአብሔር በረከት መቀበያ መካናት ገዳማት አድባራት አሏቸው:: እነዚህን ሕዝቡ ከራሱ በላይ የሚሳሳላቸውን፤ ከአምላክ በረከት የሚያገኙባቸውን፤ በጫማው እንኳን የማይረግጣቸውን፤ አቧራውን በእምነት ዘግኖ በመቀባትና በውኃ በጥብጦ በመጠጣት ፈውስ የሚያገኝባቸውን የተቀደሱ ቦታዎች ከመጥፎና ከረከሰ ሥራቸው የተነሣ የሚጸየፋቸው «ሰዎች» በጉብኝት ስም የከበረውን ሲያረክሱበት ማየት የሚችል ተፈጥሯዊ ሰብእና ሊኖረው አይችልም::

በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ ከተፈጠሩ በኋላ እግዚአብሔር በማይከበርበት፤ ከክፉ ምኞታቸው የተነሣ ለርኩስ መንፈስ የተሰጡትን ግብረ ሰዶማውያንን ቀርቶ ሌላውን መፍራት አባቶቻችን አላስተማሩንም:: እኛ የፈራነው ግርማ አልባ አካላቸውን ሳይሆን ከእግዚአብሔር መንፈስ በተራቆተ ሕይወታቸው የሌላ በሆነ መንፈሳቸው ተመልተዋልና ምድራችንን እንዳያጎሰቁሉ ነው:: ከዚህም በተጨማሪ «የራሳችንን አስተሳሰብ በማንም ላይ ለመጫን አይደለም» የሚለው የቶቶ የግብረ ሰዶማውያን አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት የዳን ዌር አባባል አሳማኝ አይደለም:: «የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው የሚያስፈራው ነገር ያለ አይመስለኝም:: የማንንም ሃይማኖት ልንጋፋም ሆነ የራሳችንን አስተሳሰብ በሰዎች ላይ ለመጫን አይደለም ወደ ኢትዮጵያ የምንሄደው:: እንዲያውም ባህሉን ለማየትና ለመረዳት እንዲሁም ለማድነቅ ነው የምንፈልገው» የሚል መግለጫ ሰጥተዋል::

ነገር ግን ተቃራኒ አስተሳሰብን ወደ ሌላው ለማሥረፅ እኮ የግድ ማስተማር፤ መወያየት ወይም መከራከር አያስፈልግም::ማንኛውም ትምህርትና ልምድ የሚቀሰመው በማትና በመስማት ነው:: ስለሆነም ይህንን መጥፎ ተግባር ይዘው ወደ ሀገራችን እንዳይመጡ በእግዚአብሔር ስም እናሳስባለን::

ዳን ዌር በንግግራቸው «ባህሉን ለማየትና ለማድነቅ» ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ መወሰናቸውን ገልጸዋል:: የኢትዮጵያ ባህል የኢትዮጵያውያን የእምነት ተቋማት አስተምህሮ ውጤቶች ናቸው:: ባህሎቻችን የተቀረፁትና መልክ የያዙት በሃይማኖታዊ አስተምህሮዎቻችን ነው:: በዚያ ላይ እንጎበኛቸዋለን ብለው ያቀዷቸው ቦታዎች የእምነት ማእከላት እንጂ የባህል መገለጫዎች አይደሉም:: ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፤ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም፤ አክሱም ጽዮን ማርያም፤ ጎንደር ዐርባ አራቱ ታቦታት ወይስ የጣና ሐይቅ ገዳማት፤ የትኞቹ ናቸው የባህል መዳረሻዎች?

ኢትዮጵያ መመኪያዋ ጉልበቷና ተስፋዋ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን፤ ሀገራችን ያለፉትን እጅግ መራራና ዘግናኝ ጦርነቶችን የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት ተቋቁማ ያሳለፈችው  እግዚአብሔር ክንድ፤ ተስፋና መመኪያ ሆኗት እንጂ በምዕራባውያኑ ርዳታ አይደለም:: መሪዎቻችን በሁሉ ታናሽ ስትሆኑ በታላቋ ኢትዮጵያ ላይ በክቡር ዜጎቿም ላይ መሪ አድርጎ ያስቀመጣችሁን እግዚአብሔርን አስቡት:: የሃይማኖት አባቶችም በዚህ ጉዳይ ግንባር ቀደም መሪ ሆናችሁ እነዚህ ግለሰቦች ወደ ሀገራችን እንዳይገቡ ማሳሰብ አለባችሁ::

ኢትዮጵያውያን በታሪካችን ሌላውን ወረን አናውቅም:: በትዕቢት ሀገራችንን፤ እምነታችንን፤ ባህላችንንና ትውልዳችንን ሊወር የመጣውን ደግሞ እጅ ነሥተን መመለስ እንችልበታለን:: በመሆኑም ጊዜው ደርሶ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ ሁላችንም ከመግባታችን በፊት ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ማእከላዊው መንግሥት በሥልጣን ላይ ያላችሁ ኃላፊዎች በየእምነታችን ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሲኖዶስ ያለን የእምነት አባቶች ክፉውን በጋራ ለማራቅ እንመካከር:: በየአድባራቱና በየገዳማቱ ያለን ሁላችንም ኢትዮጵያ ተስፋዋና ኃይሏ እግዚአብሔር ስለሆነ ራሳችንን በንስሓ አንጽተን እንጸልይ::

 

ዕርገተ ሥጋ፤ርደተ ቃል

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

የቃልን ከልዕልና ወደ ትሕትና መምጣት፤ የሥጋን ከትሕትና ወደ ልዕልና መውጣት ስናስብ እጅግ ያስደንቀናል! የመጀመሪያው የሰው ልጆች አባት ከክብር ወደ ሓሳር መምጣት ፍጥረትን ሁሉ ያስገረመ ጉዳይ ነበር፤ የሁለተኛው አባታችን ከልዕልና ወደ ትሕትና መምጣት ዳግም አስገረመን፤ ሁለቱም ይሆናሉ ብለን ያልጠበቅናቸው ክሥተቶች ናቸውና።

የእግዚአብሔርን ፍቅር እስኪ ተመልከቱት! አዳምን በልጅነት አከበረው፤ ይህ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ነው፤ ሙት የነበረውን ባሕረ የሰብእ ምድራዊት ሕይወቱን በሰማያዊ የልዕልና ሕይወት ለወጠለት። ይህንንም ሲያደርግ የበለጠ ተስፋ በማድረግ ነው እንጅ እንዲያው ያለ ምክንያት አልነበረም፤ ወይሁቦ እግዚአብሔር አምላክ መንበረ ዳዊት አቡሁ ወይነግሥ ለቤተ ያዕቆብ ለዓለም፤ እግዚአብሔር አምላክም የዳዊትን የአባቱን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ለዘለዓለም ይነግሣል››፡፡ ይህ የመጨረሻውን የተስፋ ምሥጢር የያዘ ቃል ነው፤(መጨረሻነቱ ለሕገ ተሰብኦ ነው እንጅ ለዘለዓለሙ እንዳልሆነ ግልጽ ነው)።

ከመሬት ዐፈር ያበጀው ምድራዊ ፍጡር አዳም፤ በተረገመባት ዕለት ‹‹ኦ! አዳም መሬት አንተ ወትገብእ ውስተ መሬት፤ አዳም ሆይ! አንተ መሬት ነህ ወደ መሬትነትህ ትመለሳለህ ›› ብሎ ነገረው፡፡ በዚህም የሥጋውን ፈቃድ ትቶ በነፍሱ ፈቃድ ይኖር ነበር፤ ይህ ለነፍሱ የተሰጠው ቃል ኪዳን ነው፤ ሥጋ የራሷን ፈቃድ ትታ በነፍስ ፈቃድ ትሄዳለች፤ ነፍስ ደግሞ ያላትን ሰማያዊ ጸጋዋን ከሥጋዋ አዋሕዳ ትኖራለች።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም መጥቶ የጠፋውን የሰው ልጅ ክብር መለሰ፤ ሳይገባቸው የነገሡትንም ቀጣቸው፤ያለ አግባብ የተዋረዱትን ከፍ ከፍ ሊያደርጋቸውም ፍጹም ሰው ሆኗል። ከተሾሙትና ከሊቃውንቱ መካከል የተሾመ ሐዋርያ ልትነግሩኝ ትችላላችሁ? ራሳቸውን ጻድቃን ብለው ከሚጠሩት መካከል የተገኘበትን ልታሳዩኝ ትችላላችሁ? እንዲያው ከአሕዛብ የመረጠ፤ ከኃጥአን ጋር የበላ የጠጣ አይደለምን? እንዲያውም ስለእርሱ በመጽሐፍ ‹‹ባለጠጎችን ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው፤ የተራቡትን በቸርነቱ አጠገባቸው፤የተዋረዱትን ከፍ ከፍ አደረጋቸው›› ተብሎለታል፤ ሉቃ.፩፥፶፩-፶፬፡፡ ጌታም የመጣበትም ምክንያት ለተዋረደው ሥጋችን ዋጋን መስጠት ነውና ወደ ተዋረዱት መካከል ገብቶ ታየ፡፡ መንግሥቱን በቄሣር ሳይሆን በዚህ ዓለም ገዥ በዲያብሎስ ለተነጠቀው ሰው መንግሥቱን የሚመልስ ስለሆነ ነው፤ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም የዳዊትን የአባቱን ዙፋን ይሰጠዋል›› የተባለው ያውም ለጊዜው ያይደለ ለዘለዓለሙ እንዲነግሥ መንግሥትን ስለመለሰለት ነው፡፡

ወደዚህ ዓለም የመጣበትን መንገድ ምሥጢር ማንም ሊያውቅ አይቻለውም፤ ማንም በማይመረምረው ምሥጢር ነበርና፤ ሲያርግ ግን ዐይን ሁሉ እየተመለከተው ነበር፡፡ ጠላት ወደ ሰዎች የገባው ተሰውሮ እንጅ ተገልጦ አልነበረም፤ በኋላ በደረሰብን መከራ እስክናውቀው ድረስ አዳምና ሔዋን ከሕይወት ወደ ሞት  መግባቱን መች አወቁትና! ድል ከነሣቸው በኋላ ግን ነግሦ ለዘመናት ኖረ፡፡ ጌታ የተወለደበትን ዘመኑን አስቡት፤ ከዳዊት ቤት ነጋሢ የታጣባት፤ የይሁዳው አንበሳ የዳዊት ዘር ለባርነት ተላልፎ የተሰጠበት ዘመን ነበር፤ መጽሐፍ እንደተናገረው በአንድ ወቅት ከምድር ዳርቻ የተሰበሰቡ ሰዎች ያደንቁት የነበረ ነጋሢ የነበረበት የዳዊት ቤተ መንግሥት ዛሬ ምንም ተተኪ ንጉሥ ታጥቶ ለሌላ ንጉሥ ለሮማዊ ቄሣር ተላልፎ ሲሰጥ ተመልከቱ፤ ሮማውያን በመንግሥት ሳይደራጁ ገና እስራኤላውያን እስከ ዓለም ዳርቻ የወጣ ዜና የነበረው መንግሥት ነበራቸው፤ማቴ.፲፪፥፵፪፡፡

በያዕቆብ ላይ ለዘለዓለሙ እንዲነግሥ የተነገረለት የዳዊት ልጅ ማለቂያ በሌለው መንግሥት ይነግሥ ዘንድ ዳግመኛ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ የቃል ርደት (መውረድ)፤ የሥጋ ዕርገት ሥጋን በዚህ ዓለም ብቻ ያነገሠው አይደለም፤ በመላአክት ዓለምም እንዲነግሥ ሥልጣንን ሰጥቶታል፡፡ ሁሉን ከሚያስገዛለት በቀር ሁሉን እንዲገዛ ሥልጣን ተሰጥቶታልና፤ በማቴዎስ ወንጌል ፳፰፥፳ ላይም ‹‹ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ›› ተብሏል፡፡  በቆሮንቶስ ፲፭፥፳፯ እና በሌሎች መጻሕፍት ስለእርሱ ሲናገር በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ ዳግመኛ ይመጣል ብሎ መናገሩ በሕያዋኑ በመላእክት፤ የሰው ልጆች ላይ ነግሦ እንዲኖር መሆኑን ያሳያል፡፡

ጌታችን ክርስቶስም በሥውር ወደዚህ ዓለም መጥቶ ጠላትን ድል ስለነሳው እየተዘመረለትና ቅዱሳን ሐዋርያት ትኩር ብለው እያዩት ወደ ሰማይ ዐረገ፤ የሐዋርያት ሥራ ፩፥፲ ላይም ትኩር ብለው ወደ ሰማይ እየተመለከቱ የነበሩ መሆናቸውን ተጽፏል። አርባኛው ቀን በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እያነጋገራቸው ከኢየሩሳሌም ውጭ ቢታንያ ወደተባለው ሥፍራ ወሰዳቸው፤ እጁን አንሥቶ እየባረካቸው ዐረገ፤ እነርሱም ትኩር ብለው እየተመለከቱት ሳሉ ደመና ከዐይናቸው ሰውራ ተቀበለችው፤ሥራ ፩፥፱-፲፬፡፡

እንግዲህ እነርሱ ከዓለም የወጡት ከዚያ በፊት የነበረው ሕይወታቸው መውጣት መግባት፤ መውደቅ መነሣት የበዛበት ስለነበረ፤ ይህንንም በመረዳት የዓለም ፍቅር ስቦ እንደማያስቀረው በመገንዘብ፤ ከክርስቶስ ሞትና ዕርገት በኋላ ወደ ሕይወት እንጅ ወደ ሞት የሚያደርስ ፍቅር እንደሌለ በማወቅ ነበር። ስለዚህ ልቡናቸው የሞትን አድማስ ተሻግሮ የሰማያትን ዳርቻ ተመራምሮ ወደ ክርስቶስ ዙፋን በማየት ክርስቶስ ዙፋን ላይ ሲቀመጥ ከዙፋኑ ፊት ቆሞ ዘወትር ለማመስገን ትኩር ብለው ተመለከቱ።

ከዚህ በኋላ ለሐዋርያት በምድር ላይ ሰማያዊውን ኑሮ እያሰቡ የሚኖሩ እንደሆነ ተገንዝበው ትኩር ብለው በመመልከት እዝነ ልቦናቸውን ከክርስቶስ ጋር አሳርገዋል፤ ፩ኛ ቆሮ.፪፥፲፮፤ እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ የእግዚአብሔርን ምሥጢር፤ የመንግሥተ ሰማያትን ነገር እንደምን ማወቅ ይቻላል?

አንድ ቀን ዮሐንስ ሐጺር የመነኮሳቱን የእጅ ሥራ ሽጦ እንዲመጣ ታዞ ወደ ገበያ ወጣ፤ ከገበያው መካከል እንደ ተቀመጠ ልቡን ወደ ሰማይ የሚነጥቅ ምሥጢር መጣበትና ያን እያደነቀ ሳለ ገዥ መጥቶ ዋጋ ንገረኝ ይለዋል፤ እሱ ግን ልቡናው በምድር ላይ አልነበረምና ለገዥው አልመለሰለትም፡፡ ሕሊና ሲያርግ እንዲህ ነው! እጅህ ላይ ያለውን ቁሳዊ ነገር ሳይሆን በሰማይ ያለውን መንፈሳዊ ሀብት እንድትሻ ያደርግሃል፤ ከገበያ መካከል ቆሞ የዓለምን ጫጫታ ሳይሰሙ በመላእክት ዜማ ነፍስን መማረክ አይገርምም!

ዓለም የያዝከውን እስክታገኝ አጠገብህ ናት፤ የያዝከውን ከሸጥህላት ግን ካጠገብህ አታገኛትም። ወዳንተ ስትመጣም ገዥ ሆና ትቀርባለች፤ ልብህን ካልሰጠሀት ለምትጠይቅህም መልስ ካልሰጠሀት እሷ ላንተ ገዥ አይደለችም፤ እንዳትገዛ ከፈለክ እንደ ንሥር ሽቅብ ወጥተህ አቆልቁለህ የምትመለከት አትሁን! አንዳንዶቹ አየሩን እየከፈሉ ጠፈሩን ሰንጥቀው የመላአክትን ከተማ አልፈው ከሄዱ በኋላ አቆልቁለው መመልከት ይጀምራሉ፤ ከምድር የወደቀች ቁራጭ ሥጋ ያዩ እንደሆነ ወርደው ይቀራሉ።

መቼም ቢሆን ካለ ክርስቶስ ዓለምን ማሸነፍ አይቻልም፤ ክርስቶስ በመጽሐፍ እንደተነገረው  እዝነ ልባቸውን ማርኮ ወደ ሰማይ ዐረገ ‹‹ዐረገ ውስተ አርያም ጼዊወከ ጼዋ፤ምርኮን ማርከህ ወደ ሰማይ ወጣህ›› መዝ. ፷፯፥፲፰፡፡ ለብዙ ኃያላን ያልተሳካላቸው የሰውን እዝነ ልቦና መማረክ ነው። ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ሰውን መማረክ የቻሉ ብዙ ኃያላን መንግሥታት አሉ፤ ሰውን መማረክና የሰውን እዝነ ልቦና መማረክ ግን እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሰውን ለመማረክ ጀብደኛ መሆንና የሰውን ልብ መማረክ እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡ የሰውን ልብ መማረክ በፍቅር ስለሆነ የሕይወት ልምድ ይጠይቃል፤ የሰውን ደም እያፈሰሱ ሳይሆን ስለሰው የራስን ደም እያፈሰሱ፤ ራስን ዝቅ አድርጎ ለሌሎች ክብር መስጠት በሚታገሉት ትግል ነው አንጅ ዙፋን ላይ ሆኖ በሚዋጉት ጦርነት ልብ አይማረክም።

እኛም ዘወትር ዕርገትን በእዝነ ልቦናችን ትኩር ብለን የምንመለከት ከሆነ ዓለምን እናሸንፋታለን፤ ካልሆነ ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ባሕሩ እንሰጥማለን። ቅዱስ ጴጥሮስ የሰመጠው ባሕሩን ሲመለከት ነው፤ ጌታ ሆይ እባክህን አድነኝ፤ እየሰመጥኩ ነው ያለው፤የማቴ. ፲፬፥፳፮-፴፡፡ ስለዚህ እኛም እይታችንን ከቀራንዮ ካነሣን ዓለም ታሰጥመናለች፤ ሁል ጊዜ በእዝነ ልቦናችን ክርስቶስን ስንመለከት መንፈሳችን ታርጋለች፤ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ብሎም ለራሳችን ሰላምና ፍቅርን ይስጠን፤አሜን።

«ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች»መዝ፤ ፷፯፥፴፩

በሕይወት ሳልለው 

ሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስትናን ከተቀበሉት ቀደምት ሀገሮች አንዷ ናት፤ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር፤ ፷፯፥፴፩ ላይ «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» ብሏል፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ኢትዮጵያዊት ሴት ባገባበት ዘመን ኢትዮጵያ በሕገ ልቡና አምልኮተ እግዚአብሔርን ትፈጽም ነበር፤ የብሉይ ኪዳን እምነትና የሕገ ኦሪት ሥርዓት ደግሞ በንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት መጀመሩን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ይህም የሆነው ንግሥተ ሳባ ስለ ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብና አገዛዝ ለማወቅ እጅግ ትመኝ ስለነበር ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ በተማረችው ትምህርተ ኦሪት ነው፡፡

በዚያን ዘመን ታምሪን የተባለ ጎበዝ የነጋዴዎች አለቃና የንግሥት ሳባ አገልጋይ ነበር፤ ብልህና አስተዋይ ስለነበር ወደ ኢየሩሳሌም በተጓዘበት ወቅት የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብና አገዛዝ አደነቀ፡፡ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ሲመለስ ስለንጉሡ ለኢትዮጵያዋ ንግሥት ይነግራት ነበር፤ እርሷም ይህንን በሰማች ጊዜ በዓይኗ ለማየት፤ ጥበቡንም በጆሮዋ ለመስማት ተመኘች፡፡ ለሕዝቦቿም እንዲህ አለቻቸው «ወገኖቼ!፤ ነገሬን አድምጡኝ፤ እኔ ጥበብ እሻለሁ፤ልቤም እውቀትን ትፈልጋለች፤ በጥበብም ፍቅር ተነድፌአለሁ፤ በጥበብ ገመዶችም ተይዣለሁ፤» (ክብረ ነገሥት ፳፬)፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ሀገሩ ሂዳ ጥበብን ለመመርመር እንደምትሻ ለአገልጋይዋ ነገረችው፤ ታምሪንም ምኞቷን ያሳካ ዘንድ ጉዞዋን አመቻቸላት፤ሕዝቦቿም ንግሥታቸውን ወደ ጠቢቡ ሀገር ሸኟት፡፡

ለስድስት ወር ከተጓዘች በኋላ ኢየሩሳሌም ደረሰች፤ ስለእርሷ ከነጋዴው ታምሪን የሰማው ንጉሥ ሰሎሞን በክብር ተቀበላት፤ «የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ስም፤የእግዚአብሔርን ስም በሰማች ጊዜ ሰሎሞንን በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች፤» ቀዳማዊ ነገሥት ፲፥፩-፲፫፡፡ ስለ ጥበብ የሚያውቀውን ሁሉ ነገራት፤አስተማራትም፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለዚያን ጊዜ ትውልደ አይሁድን ሲወቅሳቸው እንዲህ ብሏቸዋል፤ «በፍርድ ቀን ንግሥተ አዜብ ትነሳለች፡፡ ይህችንም የቃሌን ትምህርት ያልሰሙትን እነዚያን ትውልዶች ትዋቀሳቸዋለች፤ ትፋረዳቸዋለች፤ ታሸንፋቸዋለችም፡፡የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና»(ክብረ ነገሥት ፳፩)፤ንግሥተ አዜብ ያላትም የኢትዮጵያን ንግሥት ነው፡፡

ከዚያ በኋላ ንጉሡ ከእርሷ ዘር ሊያገኝ ወደደ፤ለስድስት ዓመት በእርሱ ግዛት ተቀመጠች፡፡ ንግሥተ ሳባም ፀነሰች፤ ሆኖም ወደ ሀገሯ የመመለሻ ጊዜ ሲደርስ ንጉሡን «እሄድ ዘንድ ተወኝ» አለችው፤ ንጉሡም እንድታስታውሰው ብሎ የጣት ቀለበቱን ከእጁ አውልቆ ሰጣት፤ በብዙ ግርማም ሸኛት፤(ክብረ ነገሥት ፴‐፴፩)፡፡

ከዘጠኝ ወርና አምስት ቀናት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ላይ በነበረችበት ወቅት ዲሰሪያ ውስጥ ባላ በተባለ ከተማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሀገሯ ስትደርስ ከንጉሡ ሰሎሞን የተማረችውን ጥበብ እንዲሁም የተቀበለችውን የኦሪት እምነት ለሕዝቦቿ አስተማረች፤ ግዛቷንም በሕገ እግዚአብሔር እንዲመራ አደረገች፡፡

ልጇም ምኒልክ ፲፪ ዓመት በሞላው ጊዜ አባቱን እንድታሳየው ለእናቱ ደጋግሞ ይጠይቃት ጀመር፤ንግሥተ ሳባም የልጇን ጭንቀት ለማቅለል አባቱም እናቱም እርሷ እንደሆነች ልታሳምነው ሞከረች፡፡ እድሜው ፳፪ በደረሰ ጊዜ ምኒልክ አባቱን ለማየት ወደ እስራኤል እንደሚሄድ ነገራት፤ ከነጋዴው ታምሪን ጋርም ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ፡፡

የልጁን ወደ ሀገሩ መምጣት የሰማው ንጉሥ ሰለሞን እጅጉን በመደሰቱ በክብር ተቀበለው፤  ግርማ ሞገሱና መልኩ አባቱን ይመስል ነበር፤ ሲያገኘውም ልጁ መሆኑን አምኖ እንዲቀበል ለምልክት ብላ እናቱ የሰጠችውን ቀለበት አሳየው፡፡ ንጉሡ ግን መልካቸው መመሳሰሉ ብቻ በቂ ማስረጃ መሆኑን በፍቅር አስረዳው፤ አቅፎም ሳመው፡፡

ነገር ግን ምኒልክ የእናቱ ናፍቆት ነበረበት፤ ለአባቱም ወደ ሀገሩ መመለስ እንደሚፈልግ በነገረው ጊዜ ንጉሡ እጅግ አዘነ፡፡ ሐሳቡን ለማስለወጥ ብዙም ጣረ፤ በእርሱ ተተክቶ እንዲነግሥ ጠየቀው፤ ልጁ ግን ሊስማማ አልቻለም፡፡ በመሆኑም ንጉሥ ሰሎሞን መኳንቱን አማክሮ በስመ ዳዊት መርቆና ባርኮ ወደ ሀገሩ ላከው፤ ወደ ኢትዮጵያም በተመለሰ ጊዜ በአባቱ አገዛዝ ሥርዓት ቀዳማዊ ምኒልክ  ተብሎ ነገሠ፤ ሕገ ኦሪትም በሀገራችን በይፋ ታወጀ፡፡