ሞክሼ ፊደላት

 

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

ሞክሼ ማለት ተመሳሳይ ስያሜ ኖሮት ተመሳሳይ ትርጉም ሲያስተላልፍ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአንድ ቋንቋ ውስጥ ሁለት የተለያዩ ምልክቶች በአንድ ድምፅ እየተጠሩ የትርጉም ለውጥ የማያመጡ ከሆነ ሞክሼ (ዘረ ድምፅ) ተብለው ይጠራሉ፡፡ ዘረ ድምፅ የሚባለው አንድ ድምፅ ከሌላ ድምፅ ጋር በተመሳሳይ ስያሜ እየተጠራ ነገር ግን የፍች ለውጥ የማያመጣ ከሆነ አንዱ ለሌላኛው ዘረ ድምፅ ይባላል፡፡ ለምሳሌ በአማርኛ ቋምቋ በድምፅ ቁጥር ውስጥ የሚጠናው “ህ” ሲሆን ሌሎች በተመሳሳይ ስያሜ የሚጠሩ “ሕ” እና “ኅ” አሉ እነዚህ በአማርኛ ቋንቋ ዘረ ደምፅ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ምክንያቱም የፍች ለውጥ ስለማያመጡ ነው፡፡

የቋንቋ ምሁራን የግእዝ ሞክሼ ፊደላትን በተመለከተ የተለያየ አመለካከት አላቸው፡፡

የሞክሼነትን ሁኔታ ከላይ በገለጽነው መሠረት አንድ ድምፅ በቅርጽ፣ በድምፅ፣ የሚለይ ከሆነና የፍች ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ዘረ ድምፅ ሊባል አይችልም፡፡ በግእዝ ቋንቋ ሞክሼ ፊደል የለም የሚሉት ምሁራን ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ ምክንያቱም በግእዝ ቋንቋ ተመሳሳይ ድምፅ፣ ተመሳሳይ ፍች፣ ተመሳሳይ ቅርጽ ያለው ድምፅ (ፊደል) ስለሌለ ነው፡፡ ይህ ሲባል ሀ፣ ሐ እና ኀ፣ ሰ እና ሠ፣ ጸ እና ፀ በተመሳሳይ ድምፅ ይጠሩ የለም የሚል ጥያቄ ቢነሳ ከጊዜ በኋላ ድምፀታቸውን አጥተው ነው እንጂ ተመሳሳይ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም የሚፈጠሩበት ቦታ ( መካነ ፍጥረት)፣ ድምፆቹ ሲፈጠሩ በመካነ ፍጥረታቸው በሚያሳዩት ባሕርያት (ባሕርየ ፍጥረት)፣ እና የንዝረት ሁኔታ ማለትም በነዛሪነትና ኢ ነዛሪነት የተለያዩ እንደነበሩ ልብ ማለት ይገባል፡፡

ይህን ሐሳብ በአጽንዖት ከሚያስረዱን ምሁራን መካከል አንዱ መምህር ዘርዐ ዳዊት አድሐና እንደገለጹት ሐሳባቸውን እንደሚከተለው እንጥቀስ “በልሳነ ግእዝ ውስጥ ፊደል የሌለው ድምፅ፣ ድምፅ የሌለው ፊደል የለም፡፡ ወይም የተዳበለ ሞክሼ ፊደልና ድምፅ የለም፡፡  እያንዳንዱ ፊደለ ግእዝ የየራሱ ድምፅ አለው፡፡ ይሁን እንጂ “የሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ አ፣ ዐ፣ ሠ፣ ሰ፣ ጸ፣ ፀ ፊደላት ድምፃቸው ተዘንግቷል፡፡” ይሉንና የታሪክ ምሁራን ከሆኑት መካከል አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስን (፲፱፻፵፰) መጽሔተ ጥበብ ስለ ግእዝና አማርኛ ቋንቋ ታሪክ በሚል የጻፉትን በመጥቀስ የእነዚህ ፊደላት ድምፆች እስከ ፲፭፻፴ ዓ.ም ድረስ ማለትም እስከ ዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት ድረስ የእነዚህ ፊደላት ድምፅ ተለይቶ ሲነገር እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ (ልሳናተ ሴም ገጽ፲፭)፡፡

በመሆኑም ዛሬ ላይ ድምፀታቸውን አጥተው በተመሳሳይ ድምፅ እየተጠሩ ስለሆነ ሞክሼ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ተመሳሳይ ድምፅ ስላላቸው ሞክሼ ግን ሊባሉ አይችሉም፡፡ ሞክሼ ፊደላት (ድምፅ) የምናገኘው በአማርኛ ቋንቋ እንጂ በግእዝ አይደለም፡፡ አማርኛ የድምፅ ሥርዓቱን ከግእዝ ሲዋስ በመካነ ፍጥረትና በባሕርየ ፍጥረት የተለያዩ ሆነው የየራሳቸው ንጥረ ድምፆች የነበሩትን፣ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ድምፀታቸውን ያጡትን ድምፆች ከነጠፋ ድምፃቸው ተውሷቸዋል፡፡ የፍች ሥርዓታቸውንም ትቶ እንዲሁ ከንጥረ ድምፆቹ ጋር በዘረ ድምፅነት እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡

ከላይ እንደገለጽነው በግእዝ ቋንቋ ድምፀታቸውን ቢያጡም ማለትም መካነ ፍጥረታቸው፣ ባሕርየ ፍጥረታቸው፣ የንዝረት ሁኔታቸውን አጥተው በተመሳሳይ ድምፅ ቢጠሩም የፍች ለውጥ ያመጣሉ፡፡ በቋንቋ ጥናት ደግሞ የፍች ለውጥ ካመጣ ሞክሼ (ዘረ ድምፅ) አይባልም፡፡ ስለዚህ ከላይ በተገለጸው አገባብ ከሆነ በግእዝ ቋንቋ ሞክሼ ድምፅ የለም የሚለውን ሐሳብ እንድናጸና እንገደዳለን፡፡

ነገር ግን በተመሳሳይ ድምፀት በመጠራታቸው ሰዎች በጽሑፍ ሥርዓት ላይ አንዱን በአንዱ ቦታ እያቀያየሩ ይጽፏቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ስሕተቶች ይፈጠራሉ፡፡ በርከት ያሉ ምሳሌዎችን እያነሳን ስሕተቶችንም ለማሳየት እንሞክራለን፡፡

ቃል               ፍች/ትርጉም

በርሀ            ብርሃን ሆነ

በርሐ            በራ ሆነ

ሠረቀ            ወጣ፣ ተወለደ

ሰረቀ             ሰረቀ

ኀለየ             አሰበ

ሐለየ             ዘፈነ

ኀመየ            አሰረ፣ ቀፈደ

ሐመየ            አማ

ሀደመ            አንቀላፋ

ሐደመ            አወጋ፣ ተረተ

ፈፀመ            ዘጋ፣ አሰረ

ፈጸመ            ጨረሰ

ከላይ የተዘረዘሩት በትክክለኛው አጻጻፍ የተቀመጡት ሲሆኑ የፊደላቱ መቀያየር ሊሰጠን የሚችለው ፍች እኛ ልናስተላልፈው ከፈለግነው የተገለበጠ ይሆናል፡፡

ለምሳሌ ሠረቀ በሥጋ እምድንግል ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ፣ ወአድኃነነ በሚለው ላይ ሰረቀ በሥጋ እምድንግል ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ ወአድኃነነ ብለን ብንጽፍ የምናገኘው ፍች፣ ከድንግል ያለ ወንድ ዘር በሥጋ ተወልደና አዳነን የሚለውን ሳይሆን፤ ከድንግል ያለ ወንድ ዘር በሥጋ ሰረቀና አዳንን የሚለውን ይሆናል፡፡ ከድንግል ያለ ወንድ ዘር መወለዱን ሳይሆን ሌብነትን የሚገልጽ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ይህንንስ አይሁድም አላሉት የተባለውን ነገር ይፈጠርብናል፡፡ የአንዲት ፊደል መለወጥ ይህን ያህል ስሕተት ትፈጥርብናለች፡፡

ሌላም ምሳሌ እናንሳ፡፡  ፈፀመ፣ ነጨ፣ አሰረ በሚለው ቦታ ፈጸመ የሚለውን “ጸ” ለመጠቀም ብንፈልግ የሚሰጠን ፍች እኛ ካሰብነው የተለየ ይሆናል፡፡ በምሳሌ ቢቀመጥ “ኦ ባዕል ሶበ ታከይድ እክለከ ኢትፍፅሞ አፉሁ ለብዕራይከ፤ እህልህን በምታበራይበት ጊዜ በሬውን አፉን አትሰረው፣ ለሚሠራ ደሞዙ ይገባዋልና” (፩ጢሞ.፭፣፲፰) በሚለው ቦታ ኢትፍጽሞ አፉሁ የሚለውን ብንጠቀም የምናገኘው ፍች ባለጸጋ ሆይ እህልህን በምታበራይበት ጊዜ የበሬህን አፉን አታፍነው የሚለውን ሳይሆን የበሬህን አፉን አትጨርሰው የሚለውን ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ የግእዝ ቋንቋ ፊደላት እያንዳንዳቸው ሀልዎተ እግዚአብሔርን የሚያስረዱ፣ ሥርዓተ አምልኮን የሚያሳውቁ፣ የየራሳቸው ጥልቅ መልእክትን የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ እንዲሁም ፊደላቱ መግባት በሌለባቸው ቦታ ሲገቡም የሚፈጠረው ስሕተት የዚያን ያህል እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ስለሆነም የፊደላቱን ትርጉም ጠንቅቀን አውቀን በየራሳቸው ቦታ እንድንጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ይገልጽልን ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡ ይቆየን

የመናፍቃን ቅሠጣ በቤተክርስቲያን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊት ነች፡፡ አስተምህሮዋና መሠረተ እምነቷ ከአማናዊው መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘ በመሆኑ አማናዊትና ርትዕት ናት፡፡ ከቤተክርስቲያን ታሪክ በቀጥታ መረዳት እንደሚቻለው ቤተክርስቲያኗ «ወርቃማ» ተብለው የሚጠሩ ዘመናትን ያሳለፈች ስትሆን በዚያው መጠን እጅግ ፈታኝ የሆኑ የመከራ ጊዜያትንም አሳልፋለች፤አሁንም እያሳለፈች ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የራሱን እምነት በሰላም ማራመድ ሲገባው  በተቃራኒው ፀረ ኦርቶዶክስ ዘመቻ  በሁለት ግንባር በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡

የፀረ ክርስትናው ቡድን ውድመትና የሐሳውያን መናፍስት የቅሠጣ ዘመቻ፤በሰባክያነ ወንጌል እጥረትና በአባቶች ቸልተኝነት አብያተ ክርስቲያን እየተዘጉ ናቸው፤ምእመናንንም በነጣቂ ተኲላዎች እየተበሉ ነው፡፡ ለውጡን ተከትሎ የሚነሣ ፀረ ክርስትና ቡድን  በሚወስደው ኢ-ክርስቲያናዊ እርምጃ  ምክንያት የአምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ የሆኑት አብያተ ክርስቲያን ሲደፈሩና ሲወድሙ፤ በአገልጋዮቿ ካህናትና በተከታዮቿ ምእመናንም ላይ እስከ ኅልፈተ ሕይወት ጉዳት ሲደርስ፤ሌላ አቅም ባይኖራትም የተከታይ አቅም እያላት «ዝም በሉ የእኔን እግር ነው የሚበላው» እንደተባለው ዐይነት ነገር የደረሰባትን ጉዳትና ችግር ሁሉ በትዕግሥት፤በአርምሞና በጽሞና  ማሳለፍ ይቻላል (ዜና ቤተክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ፤ ጥቅምት እና ኅዳር ፳፻፲፩ ዓ.ም.)

እነዚህ ፈታኝ ወቅቶች ኢትዮጵያዊያን ሕዝባዊ ጠባይን የተላበሰ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተሉ ከማድረጉም በላይ የተለያዩ እምነቶች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ መንገድን አመቻችተዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗም ከውስጥና ከውጭ በተነሱባት ፈተናዎች ምክንያት «ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው» (ማቴ.፳፥፲፱ ) «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ» (ማር.፲፮፥፲፭)  «አባቴ እንደላከኝ እናንተንም እልካችኋለሁ» (ዮሐ.፳፥፳፩) ተብሎ በወንጌል የታዘዘውን ለዓለም ለማዳረስ በምታደርገው አገልግሎት ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንቅፋት ሆነውባት አገልግሎቷን በሚፈለገው መጠን መፈጸም እንዳትችል አድርጓታል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር ምክንያት በማድረግ የተለያዩ እምነቶች አብዛኛውን የገጠርና ጠረፋማ ኀብረተሰብ የተሳሳተ አስተምህሮን በማስተማርና በጥቅም በመደለል ፍጹም ከቤተክርስቲያኗ ሲያርቁት መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህም በቂ ማስረጃ የሚሆኑን ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት የተካሄዱት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤቶች ምስክሮች ናቸው፡፡

ይህ የሌሎች ቤተ እምነት ተጽኖ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በቂ አለመሆንና የምእመናን የግንዛቤ ማነስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ለሦስት ተከታታይ ወቅቶች በተካሄደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት ቊጥራቸው እየቀነስ መጥቷል፡፡ ይህም በአኃዝ ሲሰላ (በ፲፱፻፸፮ ዓ.ም፤60.02% በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም፤ 50.6% እና በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም፤43.5%) ይሆናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአጽራረ ቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ የሚገታና ምእመናንን በቤተክርስቲያን እንዲጸኑ ሊያደርግ የሚችል ሥራ መሥራት ካልተቻለ አሁንም ብዙ ምእመናንን ከቤተክርስቲያን  በረት ይልቅ ወደ ሌሎች ቤተ እምነቶች የመኮብለል እድላቸውን ሊያሰፋው እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያናችን የጀርባ አጥንት ነውና የግራኝ አሕመድ ጊዜ እንደገና እንዳያገረሽ፤ቤተክርስቲያናችን ዘመቻ ፊልጶስን ልታውጅ ይገባታል፡፡

ምንጭ፡ዐውደ ርእይ፤ ስለ ወንጌል እተጋለሁ! መጽሔት ከሰኔ ፲፬ እስከ ፲፮/፳፻፲፩ ዓ.ም.

 

የዐዋጅ አጽዋማት

በተክለሐዋርያት

የዐዋጅ አጽዋማት በቤተክርስቲያን ለምእመናን ሁሉ አሳውቆ በአንድነት የሚጾም ጾም ነው፤ በሰባትም ይከፈላል፤ እነርሱም የነቢያት  ጾም፤ ጾመ ገሃድ ወይም ጋድ፤ ጾመ ነነዌ፤ የዐብይ ጾም፤ጾመ ድኅነት፤ የሐዋርያት ጾም እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡ በጾም ወቅት ከአንድ ምእመን የሚጠበቁ ምግባራት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ. ዕለት ዕለት አብዝቶ መጸለይ

በጾም ወቅት ልናዘወትራቸው ከሚገቡን ምግባራት መካከል ጸሎት አንዱ ነው፤ በጸሎት ያልታገዘ ጾም ከንቱ ነው፤ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን በጾም ወቅትና ከጾም ወቅት ውጪ በጸሎት ትጉ መሆን ክርስቲያናዊ ግዴታው ነው፡፡ ጸሎት ከፈጣሪ የምንገኛኝበት ክርስቲያናዊ ምግባር ነው፡፡ ጸሎት ወደ ፈተና እንዳንገባ የሚረዳን የጽድቅ መሥመር ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን በጠራሁት ጊዜ ጽድቄን ሰማኝ ጭንቀቴንም አራቀልኝ ይቅር አለኝ ጸሎቴንም ሰማኝ››(መዝ.፬፥፩)

ለ. ከዝሙት መከልከል

ዝሙት ነፍስና ሥጋን ይጎዳል፤ በሰማይም በምድርም ከፍተኛ ቅጣትና ሥቃይን ያመጣል፡፡ ሴሰኝነት መልካም ስምን ያጠፋል፤ ክብርን ያሳጣል፤ ኅሊናን ይበጠብጣል፤ ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ከእግዚአብሔር አንድነት የሚለይ መሆኑ ነው፡፡ ሴሰኞችና አመንዝራዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ይደረግባቸዋል፡፡ ነቢዩ ‹‹ወንዶችም ደግሞ ከአመንዝሮች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰሰኑ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁ በአመነዘሩ ጊዜ አልቀጣኋቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ከአመንዝራ ጋር ይቀላቀላል፡፡ (ሆሴ.፬፥፲፬)

ሐ. የስሜት ሕዋሳትን ማስገዛት

በጾም ወቅት ሁሉንም የስሜት ሕዋሳቶችን መግዛት መቻል አለብን፡፡ የስሜት ሕዋሳትን መግዛት ካልቻልን በምኞትና በፍትወት ገመድ እየጎተቱ ወደ ኃጢአት ይወስዱናል፡፡ ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ይጹም ዓይን (ዓይን ይጹም) ፤ ይጹም ልሳን(አንደበት ይጹም)፤ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ሕሱም (ጆሮም ክፉን ከመስማት ይጹም)፤ በማለት ያስተማረን ዓይን የሚያየውን ጆሮም የሚሰማውን አንደበትም የሚናገረውን ክፉ ነገር አእምሮ ወደ ሐሳብ በመቀየር ወደ ኃጢአት ሊያመራን ይችላል፡፡ በመሆኑም በጾማችን ወይም በክርስትናችን ዓይናችንን ክፉ ነገርን ከማየት አንደበታችንን ክፉን ከመናገር ጆሮአችንንም ክፉን ከመስማት ልንከለክል ይገባናል፡፡ ‹‹ኃጢአትን ወደ መውደድ አንተን ከሚስቡህ ከማየት ከመስማት ተጠበቅ›› (ማር ይስሐቅ)፡፡ ዓለሙንና በዓለም ያለውን አትውደዱ ዓለሙን የሚወድ ግን የአብ ፍቅር በእርሱ የለም በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለገንዘብም መመካት ከዓለም እንጂ ከአብ አይደለም፡፡ (፩ዮሐ.፪፥፲፭‐፲፮)

መ. ቅዱሳት መጻሕፍትን መመርመር ፤ መመልከት

ቅዱሳት መጻሕፍት የሰው ልጅ የፈጣሪውን የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት ይማርባቸው ዘንድ የተሰጡትና ከአለማወቅ ወደ ማወቅ ከሞትም ወደ ሕይወት የሚወስዱት የሚያደርሱት ከፈጣሪው ጋርም እንዴት መኖር እንደሚገባው የሚያስተምሩት የቅድስናው መሠረቶች የክርስትና ሕይወት መመሪያዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል ‹‹መጻሕፍትን ካለማወቃችሁ የተነሣ ትስታላችሁ›› በማለት ያስተማረን ቅዱሳት መጻሕፍት እንዴት መጾም እንዳለብን በጾማችን ወቅት ምን ምን ተግባራትን ማድረግ እንዳለብንና እንደሌለብንም ጭምር ያስተምሩናል በጾም የተጠቀሙ የቅዱሳን አባቶቻችንንም ታሪክ እየነገሩን እኛም እንድንጾም ያደርጉናል፡፡

በመሆኑም ኦርቶዶክሳውያን  ምእመናን በጾም ወቅት እነዚህን ቅዱሳት መጻሕፍትን አብዝቶ በማንበብ ወደ ቅድስና ሕይወት የሚወስዱ የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዛትን መረዳትና መፈፀም ተገቢ ነው፡፡

ሠ. ምጽዋትን ማዘውተር

ምጽዋት ማለት መስጠት፤መለገስ ማለት ነው፡፡ ይህም ከጾም ጋር ከሚተባበሩ ክርስቲያናዊ ምግባራት አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን ይህንም ላደርግ ደግሞ ተጋሁ›› በማለት እንዳስተማረን ምጽዋት ለምእመናን ትጋት ናት፡፡ (ገላ.፪፥፲)

ምጽዋት መስጠት ከገንዘብ ከዕውቀት ከንብረት…ላይ ለእግዚአብሔር ቤት መለገስ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ “ብፁዓን መሐርያን የሚምሩ ብፁዓን” ናቸው ያለውን ሊቃውንት ለምጽዋት ሰጥተው ሲተረጉሙት በሦስት መንገድ ያስቀምጡታል፡፡ እነዚህም፡-

.ምሕረት ሥጋዊ፡ ይህ የሚያስረዳው ለሥጋ የሚኾን ነገርን መለገስን ሲኾን
. ምሕረት መንፈሳዊ፡ በምክር በትምህርት ሥነ ልቡናን የሚያንጽ (የሚያበረታታ) ማድረግን ነው፡፡

. ምሕረት ነፍሳዊ፡ ደግሞ «መጥወተ ርእስ» ወይም ራስን እስከ መስጠት መድረስን ነው፡፡ (ማቴ.፭፥፯ትርጓሜ ወንጌል)

ምጽዋት ካለን ነገር ላይ ማካፈልን ያመለክታል፡፡ ለፍጹምነትም የሚያበቃ ምግባር መኾኑ የተመሰከረለት ነው፡፡ «ፍጹም እንድትኾን ለድኻ ስጥ» እንዲል (ማቴ.፲፱፥፳፩) እንደዚሁም «የሚሰጥ ብፁዕ ነው» የሚለው ኃይለ ቃል የሚያስረዳን ይህንኑ ነው፡፡ (ሐዋ.፳፥፴፭) በዕለተ ምጽአትም ከሕይወት ቃል አንዱ በምጽዋት የሚገኝ መኾኑ እሙን ነው፡፡ (ማቴ.፳፭፥፴፭) ምጽዋት በልብስ በገንዘብ እንጀራ በመቁረስ የመሳሰሉትን ለደኃ በመስጠት ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች ማካፈል ነው፡፡ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ምእመናን ሀብታቸውን ለደኃ ያካፍሉ ነበር፡፡ (ሐዋ.፬፥፴፪፣፮፥፩) እንደዚሁም ዕውቀትን ማካፈል ምክር መለገስ ከምጽዋት የሚቈጠር ሲኾን ለእግዚአብሔር ቤትም በገንዘብ በጉልበትና በስጦታችን ማገልገል የምጽዋትን ዋጋ ያስገኛል (ዘዳ. ፲፭፥፲፩‐፲፭፤ኢሳ.፶፰፥፯፤፯፤ምሳ.፫፥፳፯፤ሮሜ.፲፪፥፰) እንግዲህ በጾማችን ለኃጢአታችን ሥርየትን፤ ምሕረትና ይቅርታን የምናገኝባቸውን የሥጋና የነፍስ በረከትንም የምንታደልባቸውን እነዚህን ክርስቲያናዊ ምግባራት በሕይወታችን አዘውትረን ልንፈጽማቸው ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

 

የዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና

የተከበራችሁ አንባብያን በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታና በየአካባቢው እና በየክልሉ በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ  ክፍል አንድ፤ክፍል ሁለት እና ክፍል ሦስት ጽሑፍ ማቅረባችን ይታወቃል፡፡ክፍል አራትን እነሆ ብለናል፡፡

አሁን እየተፈጸመ ያለውም አስቀድሞ ሲፈጸም ለኖረው ቀጣይ ይመስላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ውድመት፤ ዜና ቤተ ክርስቲያን፡- የግራኝ አህመድ ዘመን ተመልሶ እንዳይመጣ እንዲህ በማለት አሳስቧል፡፡ «አሁን በቅርቡ ባሳለፍነው በ፳፻፲ ዓ.ም መገባደጃ ላይ አገር የሆነችውን ወይም ሁለንተናዊ ጠቀሜታዋና ትሩፋቷ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታ የሆነችውን አንጋፋዋን ቤተ ክርስቲያን ከሌላው ነጠሎ ለመምታትና የተከታዮቿን የምዕመናንን አሻራ ከገጸ ምድር ለማጥፋት ወይም አሳምኖ የራሱ ተከታዮች ለማድረግ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ባለው የሱማሌ ክልል ፀረ ክርስትና ቡድን በፈጸመው ጥቃት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያንን በሙሉ አውድሟቸዋል፤ ሀብታቸውን፣ ንብረታቸውንና ቅርሶቻቸውንም ዘርፏቸዋል፤ አገልጋዮቿንም እንደ ካህኑ ዘካርያስ በየቤተ መቅደሳቸው ውስጥ አርዷቸዋል»፡፡ ይህ የሚያሳየው በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥፋት ጊዜያዊ ጥቃትና ተራ ጥፋት አለመሆኑን ነው፡፡ በ፳፻፱ ዓ.ም በለገጣፎ የሚገኘውን የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የንግሥ በዓል በሚያከብሩበት ወቅት የከተማው ማዘጋጃ ቤት የላካቸው አፍራሽ ግብረ ኃይል ሰኔ ፴ ቀን በግሬደር አፍርሶታል፡፡ ሰላምን ማስፈን፣ ዜጎቹን በእኩል አይን ማየት የማገባው የሕዝብ አስተዳደር አካል ይህን ማድረጉ የሚያስገርም ነበር፡፡ በያዝነው ዓመትም በዚያው አካባቢ ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጋዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲጠለሉ ቤተ ክርስቲያን ለምን ለችግረኞች መጠጊያ ሆነች የሚሉ ወገኖች ካህናትን ማስፈራራታቸው በመገናኛ ብዙኃን ተገልጧል፡፡

«መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በሂደቡ አቦቴ ወረዳ ኤጄሬ ከተማ የመጥምቀ መለኮት ትዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያንን ቁልፍ ሰብረው በመግባት ታቦቱንና ንዋያተ ቅድሳቱን ዘርፈው ንዋያተ ቅዱሳቱን ሹንቁራ በሚባለው ተራራ ላይ አቃጥለውታል፡፡ መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በዚሁ ወረዳ የሚገኘውን የአድዓ ቅዱስ በዓለወልድ ቤተ ክርስቲያን ቀን ላይ በእሳት አቃጥለውት ንዋያተ ቅዱሳቱ ሲቃጠል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በምእመናን ርብርብ ተርፏል»፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሁሉ መከራ መካከል ሳትጠፋ የምትኖር ቢሆንም፣ አብረውን የሚኖሩ ወገኖቻችን እንዲህ ዓይነት የጭካኔ ተግባር የሚያሳዝንም የሚያስገርምም ነው፡፡

 ለ. የቤተ ክርስቲያን ይዞታ መነጠቅና ደን መቃጠል፣ ቤተ ክርስቲያን የዓደባባይ በዓላትን የምታከብርባቸው የመስቀል ደመራና የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎቿ ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ይዞታዋን እየነጠቁ ለባለሀብቶች መስጠት፣ ለሌለ እምነት ተቋም ማሸጋገር የተለመደ ሆኗል፡፡ በጎንደር፣ በባሕርዳር፣ በአርባምንጭ፣ እና በሌሎችም ለጥምቀተ ባሕር የሚሆኑ ቦታዎች ለባለሀብቶች ተሰጥተው በተፈጠረ ብጥብጥ ብዙ ሰው ሞቷል፤ ብዙዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ የአየር ጤና ኪዳነ ምሕረት የጥምቀተ ባሕር ማክበሪያ ቦታ በወቅቱ የከተማዋ ከንቲባ በነበረው ግለሰብ ትእዛዝ ለሌላ ቤተ ዕምነት ተሰጥቷል፡፡ መንግሥት በሰጣቸው ሥልጣን እምነታቸውን የሚያስፋፉ፣ በተገኘው አጋጣሚ የቤተ ክርስቲያን የነበረውን ቦታ ሁሉ ለራሳቸው በማድረግ እንቅልፍ የሌላቸው ምእመናን ይዞታቸውን ለማስመለስ ሲነሡ ለእስር የሚዳርጉ፤ በጥይትና በዱላ እንዲደበደቡ የሚያደርጉ ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡

 «የካቲት ፳፻፭ ዓ.ም በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊበን ዝቋላ ወረዳ አዱላላ ከተማ በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም መንሥኤው ያልታወቀ እሳት ተነሥቶ በከባድ የነፋስ ኃይል እየተገዛ ወደ ገዳሙ እንዳይስፋፋ ተሰግቶ ነበር፡፡ ገዳሙ ከዚህ በፊትም መጋቢት ፲ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም በደረሰው የእሳት ቃጠሎ አርዘሊባኖስ፣ የሐበሻ ጥድ እና መሰል ሀገር በቀል ዛፎች ወድመዋል፡፡ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም በተቀሰቀሰ ቃጠሎ ገዳሙ ጉዳት ደርሶበታል፡፡» ቃጠሎውን የፈጸመው ባይታወቅም የእኛ ጥያቄ የሀገር ሀብት የሆነው ደን ሲወድም የቤተ ክርስቲያን በመባል ብቻ ትኩረት ሳይሰጠው መቅረቱ ተገቢ አለመሆኑን ለመግለጽም ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ስለሆነ ብቻ ትኲረት ሳይሰጠው መቅረቱ ተገቢ አለመሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በአንድ አካባቢ በቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር ሲፈጠር በወቅቱ መረጃው እንዳይወጣ ይደረግ የነበረው ጫና ቀላል አልነበረም፡፡

ምእመናን የተናገሩትን፣ መነኮሳት የተሰማቸውን አካቶ ዜና ለመሥራት የነበረው ችግር ቀላል አልነበረም፡፡ ሀገራችን ዘመናዊ የእሳት ማጥፊያ እንደሌላት ይታወቃል፡፡ በሚችሉት መርዳት፣ በአሳብ መደገፍ፣ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በምንችለው ሁሉ ተረባርበን እናጠፋለን፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያንና የሀገር ሀብት የሆነው ቋሚ ቅርስ ለጉዳት ሲጋለጥ ሃይማኖት ዘርና ቀለም ሳንለይ ችላ አላልንም በማለት የባለቤትነት ስሜት እንዳን ሁላችንም ማሳወቅ ይኖርብናል፡፡ ይህ ጉዳት በታላቁና በጥንታዊው የአሰቦት ደብረ ወገግ ሥላሴ ገዳምም ተፈጽሟል፡፡ የገዳሙን ደን አክራሪዎች ባስነሡት እሳት መቃጠሉ በወቅቱ ተዘግቧል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ፣ ችግር ሲፈጠር ከክርስቲያኖቹ ያላነሰ ልባቸው የሚያዝን፣ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ የሌላ ከክርስትና ውጪ ያሉ ዕምነት ተከታዮት እንዳሉ አንክድም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማየት የማይፈልጉ በሐሰት መረጃ የተሞሉ ጥፋት አድራሾችም እንደዚሁ፡፡ እየተፈጸመ ያለው ጥፋት በንፁህ ኅሊና መለስ ብለን ማየት ካልቻልን፣ ትኩረት አለመስጠታችንና ጆሮ ዳባ ለበስ ማለታችን የበለጠ ጥፋት ያስከትላል፡፡

ከታሪክ ምሁራን፣ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከመገናኛ ብዙኀንና ከመንግሥት አካላት ስለ ቤተ ክርስቲያን በስሕተት ሲዘራ የኖረውን ታሪክ ማስተካከልና ትክክለኛውን መረጃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለምን ገዳማት በዙ፣ ለምን ቱሪስቶችን የሚስቡት የክርስቲያኖች የተጋድሎ ውጤቶች ሆኑ የሚሉ ወገኖች በቅናት ታሪክ ለመቀየር እየሠሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምሁራን ለሚጻፉ የሐሰት ጽሑፎች መልስ መስጠት፣ የመረጃቸውን ፍሬ ቢስነት ማጋለጥ ይኖርባቸዋል፡፡ እንደፈለጋቸው ሲሳደቡ ቤተ ክርስቲያን ከዛሬ ነገ ይታረማሉ በማለት በትዕግሥተ ስላለፈችው፡፡ ስታልፈው በጥሞና የራስን ምግባር ማየት ይገባል እንጂ በጥፋት ላይ ጥፋት መፈፀም ሰብዓዊነት አይደለም፡፡ ይህ መሰተካከል ይኖርበታል፡፡ የራሳቸው እምነት ተከታይ ሆነው ሚዛናዊ ጽሑፍ ያቀረቡትን የሚያጣጥሉ፣ ምንጭ የሌለው የጥላቻ ጽሑፍ የሚጽፉትን ታላቅ ነገር እንዳገኙ ሁሉ እየጠቀሱ ሲያሞካሹ ሕሊናቸውን እይቆጠቁጠውም፡፡ ኦርቶዶክሳውያንም ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ምሁራንም ምርቱን ከገለባው፣ እውነቱን ከሐሰት በመለየት ለአንባብያን ማድረስ አለባቸው፡፡

በየጊዜው እነዚህ ጥፋቶች ተፈፀሙ ስንል፣ በጥፋቱ ላይ የተሠማሩ ሰዎች ወደ ኅሊናቸው እንዲመለሱ እንጂ እሳትን በእሳት አጥፉ ለማለት አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ በዚህ አምሳ ዓመት የተፈጸመው በዓላማ መሆኑን የሚያሳየው በአንድ ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን ርከን ላይ የነበሩ ሰው «ሥልጣኑን ከአማራና ከኦርቶዶክስ አርቀነዋል» በማለት ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም የተመረጡ ሰሞን መናገራቸው ማሳያ ነው፡፡ እንደዚያ ማለት መብታቸው ቢሆንም፣ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ሆኖ ለሀገር ባለውለታ የሆነችን፣ ቅርሶቿ በዓለም የምርምር መድረክ ግንባር ቀደም ሚና የምትጫወትን ቤተ ክርስቲያን ማጥፋት ወይም አጥፊዎች ሲያወድሟት ቆሞ ማየት ተገቢ ነው ብለን አናምንም፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ሰዎችና አካላት ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ብለው ሲሠሩ ኦርቶዶክሳውያን እና የሚያመዛዝኑ ወገኖች ደግሞ ቢችሉ በመገሠጽና በማረም ቢይችሉ የጥፋት ተባባሪ ባለመሆን የቤተ ክርስቲያን እና የሀገር ሀብት እንዳይጠፋ ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በህዝብ አስተዳደር ላይ የሚገኙ አካላትም በታሪክ ላለመጠየቅ ከሕሊና ፍርድም ነፃ ለመሆን ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል ምእመናን ሲሳደዱና ሲገደሉ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ የራሳቸው በሆነ ስሜት ውስጥ ሆነው የሚነጐዱ ሰዎች ለከፋና ዕውነታውን ከመቀበል ይልቅ፣ ለበለጠ ነገር በእልክ መሔድን የሚመረጡ ስለሆነ ‹‹ጨርሰን ባንበገር›› ቢቀር?

 ማንኛውም የዕምነት ተቋም ተከታዮች ሲሞቱ የሚያሳርፍበት ቦታ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ጠይቆ ማግኘት መብቱ ቢሆንም፤ በሲዳሣ ሀገረ ስብከት የወንዶ ገነት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን የቀብር ቦታ ፕሮቴስታንቶች ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ወስደው የራሳቸው የቀብር ቦታ አድርገውታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይዞታዋን ለማስመለስ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ተከራክራ ይዞታዋ ቢወሰንላትም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የሚያስተገብር በመጥፋቱ ጉዳዩ ወደ ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተሸጋግሮ ይገኛል፡፡ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ ሲጠየቅ በጎ ምላሽ አለመገኘቱ የልማት ቦታም በሊዝ ካልሆነ ማግኘት አለመቻሉ ተገልጧል፡፡»ክርስቲያኖችም ከስሜታዊነት ወጥተን በማስተዋል እንመላለስ፡፡ አካባቢያችንንም እንጠበቀ፣ ለመንግሥት አካላትም ትክክለኛውን መረጃ እናድርስ፡፡ የሚፈጸሙ ጥፋቶች እንዲቆሙ ድምፃችንን እናሰማ ጥፋቶችንም መዝግበን እንያዝ፡፡

ይቆየን

ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከሰኔ ፩-፲፭ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም

‹‹ጾም የነፍስን ቊስል ትፈውሳለች›› (ቅዱስ ያሬድ)  

                                                                                              በብዙአየሁ ጀምበሬ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሚከናወኑ ዓበይት ክርስቲያናዊ ምግባራት መካከል ጾም አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ጾም ‹‹ጾመ››  ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ተከለከለ፤ተወ፤ታቀበ፤ታረመ ማለት ነው፡፡ በሱርስትና በዕብራይስጥ ቋንቋዎች ‹‹ጻም›› ሲባል በአረብኛ ቋንቋ ደግሞ ‹‹ጻመ›› በመባል ይታወቃል፡፡ (ጾም እና ምጽዋት ገጽ ፰)

የቤተ ክርስቲያናችን የሕግና የሥርዓት መጽሐፍ የሆነው ፍትሐ ነገሥት ደግሞ በአንቀጽ ፲፭ ላይ ‹‹ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ፤ ጾምስ በታወቀው ዕለት፤በታወቀው ሰዓት ከምግብ መከልከል ነው›› በማለት ጾምን በዚህ መልኩ ይተረጕመዋል፡፡

እንግዲህ በሃይማኖታዊ ትርጉሙ ጾም ማለት ራስን ከእህል፤ከውኃ ብሎም አምላካችን እግዚአብሔር ከሚጠላቸው እኩይ ምግባራት ሁሉ ራስን በመከልከል የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ በማስገዛት መቆየት ማለት ነው፡፡‹በዚያም ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም፤ በጽላቱም ዐሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ።›› (ዘፀ.፴፬፥፳፰) ሁለቱን የድንጋይ ጽላት፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃል ኪዳን ጽላት፥ እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ፥ በተራራው ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ተቀምጬ ነበር እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም›› ተብሎ እንደተጻፈ። (ዘዳ.፱፥፱)

ከዚህም ባሻገር ጾም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅባት በማጣት ከሳ›› በማለት እንደናገረው በዚህ የጾም ወቅት ከጥሉላት መባልዕት ወይም የእንስሳት ተዋጽኦ የሚባሉትን ማለትም እንደ ሥጋ፤ወተት፤ዕንቁላል፤ዐይብ፤ ቅቤ ወዘተ ከመሳሰሉት ቅባትነት ካላቸው ምግቦችና ከሚያሰክሩ መጠጦች ራስን መከልከል መከልከል ያስፈልጋል፡፡ (መዝ ፻፰፥፳፬)

ነቢዩ ዳንኤልም በትንቢት መጽሐፉ ስለ መባልዕት ጥሉላት እንዲህ ብሏል‹‹በዚያም ወራት እኔም ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ፡፡ ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፤ሥጋና የወይን ጠጅም በአፌ አልገባም››(ዳን.፲፥፪-፫) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፤‹‹ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣናል፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና፡፡›› ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ ወንጌል ሥጋን የሚያደልበውን መብልን እንደማትሰብክና በመብል ብቻ ልባችንን ማጽናት እንደሌለብን ገልጿል (ዕብ. ፲፫፥፱)

የክርስትናችን መሠረት ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ መብልና መጠጥ ከንቱነት እንዲህ በማለት አስተምሮናል፡፡ ‹‹ራሳችሁን ጠብቁ፤ በመብልና በመጠጥ፤በመቀማጠልና የዓለምን ኑሮ በማሰብ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ያቺ ቀንም በድንገት ትደርስባችኋለች፡፡››(ሉቃ.፳፩፥፴፬)

የሰው ልጅ አብዝቶ በበላና በጠጣ ጊዜ ከአእምሮው በመውጣት እኩይ ተግባራትን ሊፈጽም ይችላል፡፡ ጥጋብና ስካር የኅሊናን አቅል በማሳጣት ለኃጢአት ይዳርጋሉ፡፡ ‹‹በቀን እንደሚሆን በጽድቅ ሥራ እንመላለስ፤በዘፈንና በስካር፤በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤በክርክርና በቅናት አይሁን››(ሮሜ ፲፫፥፲፫)  ስካር ከእግዚአብሔር መንግሥት ያርቃል ‹‹ምቀኝነት፤መግደል፤ስካር፤ዘፋኝነት፤ይህንም የሚመስል ነው፡፡አስቀድሜም እንደ ነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡›› (ገላ.፭፥፳፩) ስካር የሰው አዕምሮን ያጠፋል፡፡(ሆሴ.፬፥፲፩)

ከማንኛውም ክፉ ነገሮች ሁሉ መጠበቅ፤ራስን መግዛት እና መቈጣጠር፤ በንስሓና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ፤ እርሱንም ደጅ መጥናትና ለኃጢአታችን ሥርየትን መለምን ማለት ነው፡፡ ይህንንም ስናደርግ ነቢዩ ዳንኤል ‹‹ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ።›› በማለት እንደተናገረው አምላካችን እግዚአብሔር የሚወደውን የተቀደሰውን ጾም በመጾም ለነፍሳችን መልካም ዋጋን እናገኝ ዘንድ ከሥጋዊ ምቾትና ቅንጦት በመራቅና ራሳችንን ዝቅ በማድረግ ልንጾም ይገባል፡፡(ዳን.፱፥፫)

እንግዲህ ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎ አንዱ ነው፤ ለሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት መንፈሳዊ ስንቅ ነው፡፡ ‹‹ጾም ቊስለ ነፍስን የምትፈውስ፤ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፤ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ፤ከእግዚአብሔር ጸጋን የምታሰጥ፤የወንጌል ሥራ መጀመሪያ፤የጽሙዳን ክብራቸው፤የደናግል የንጽሕና ጌጣቸው፤ የዕንባ መፍለቂያዋ፤ አርምሞን (ዝምታን) የምታስተምር፤ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፤ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡››(ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፬ ምዕ. ፮)

እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በአምሳሉና በአርአያው ከፈጠረው በኋላ ከማእከለ ምድር (ኤልዳ) ወደ ኤዶም ገነት በመውሰድ ክፉውንና መልካሙን የሚለይበት አስተዋይ ኅሊና ባለቤት አድርጎ አኖረው፡፡ (ኩፋሌ ፬፥፱) በዚህም መሠረት የሰው ልጅ ‹‹ከዚህ አትብላ›› በሚል አምላካዊ ቃል ጾም ኆኅተ ጽድቅ የጽድቅ በር ሆና የተሰጠች የመጀመሪያቱ ሕግ ናት፡፡ ጾም ከምግባረ ሃይማኖት ዋነኛው ነው፤ይህም ለአንድ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የማይለየው ምግባር ነው፡፡ ጾም የሰው ልጅ ለአምላኩ ለልዑል እግዚአብሔር ያለውን ፍቅር የሚገልጥበት፤መንፈሳዊ ተጋድሎዎችን የሚያከናውንበት፤ስለራሱና ስለወገኖቹ ኃጢአት የሚያዝንበት፤ የሚያለቅስበትና ወደ ንስሓ የሚመለስበት ታላቅ ሥርዓት ነው፡፡

የጾም አስፈላጊነት በክርስትና ሕይወት እጅግ የጎላ ነው፡፡ በመሆኑም በጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛትና ከሥጋዊ ከንቱ ኃጢአት ለመራቅ ይረዳናል፡፡ ሥጋ በምግብ ሲደነድን ለፍትወትና ለተለያዩ ሥጋዊ ኃጢአቶች ቅርብ ይሆናል፡፡ የሥጋ ፍላጎት በቀዘቀዘ ቊጥር ነፍስ ትለመልማለች፤ ለአምላክ ሕግና ትእዛዛት ሁሉ ተገዢ ትሆናለች፡፡ ማኅሌታዊ ቅዱስ ያሬድ  ስለ ጾም እንዲህ ብሏል፤‹‹ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ፤ ወታጸምም ኵሎ ፍትወታተ ዘሥጋ ፤ ትሜህሮሙ ጽሙና ለወራዙት፤ ጾም የነፍስን ቊስል ትፈውሳለች፤የሥጋን ፍትወታት ሁሉ ታጠፋለች፤ ለወጣቶችም ትሕትናን ታስተምራለች፡፡››

ለክርስቲያን የነፍስን ሥራ መሥራት  ከእግዚአብሔር ጋር መተባባርና አንድ ወገን እንደመሆን ያለ ምግባር ነው፡፡‹‹አሁንም ወንድሞቻችን በዚህ በሥጋችን ሳለን ፈቃደ ሥጋችንን ልንሠራ አይገባንም፡፡ ፈቃደ ሥጋቸውን የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ በወዲሁ አለን ሲሉ በወዲያው ምውታን ናቸውና፡፡ ፈቃደ ሥጋችሁንስ በፈቃደ ነፍሳችሁ ድል ከነሣችሁት ለዘለዓለሙ ሕያዋን ትሆናላችሁ፡፡ ፈቃደ ነፍስን የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡›› (ሮሜ ፰፥፲፪-፲፬) እንዲል፡፡

ጾም የኃጢአት ሥርየትን ለማግኘትና ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ይረዳል፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ወደ እርሱ በጾምና በጸሎት እንድንመለስ በነቢያት አድሮ አሥተምሮናል፡፡ ‹‹በፍጹም ልባችሁ፤በጾምም፤በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፡፡››(ኢዩ.፪፥፲፪)

ጾም በጸጸት መንፈስ ሆነን በንጹሕ ልባችን ወደ ልዑል እግዚአብሔር በንስሓ እንድንመለስ ይረዳናል፡፡ ‹‹ወሀበነ ጾመ ለንስሓ በዘይሰረይ ኃጢአት፤ ኃጢአት የሚሠረይበትን ይቅር የሚባልበትን ጾምን ሰጠን›› ጾም በደልን አምኖና ጥፋትን ተቀብሎ በፍጹም ትሕትና ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ በድያለሁ ማረኝ ይቅር በለኝ በማለት የንስሓ ዕንባን በማንባት ከእግዚአብሔር ምሕረትን የምናገኝበት ምግባር ነው፡፡

በመጽሐፍ «የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፤ አለቀሱም፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ በዚያም ቀን እስከ ማታ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትንና የደኅንነት መሥዋዕትን አቀረቡ›› እንደዚሁም ፤«ወደ መሴፋ ተሰበሰቡ፤ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት በምድር ላይ አፈሰሱ፤ በዚያም ቀን ጾሙ፤ በዚያም፤ በእግዚአብሔር ፊት በድለናል አሉ፤ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በመሴፋ ፈረደ›› (መሳ.፳፥፳፮፤፩ኛሳሙ.፯፥፮)

በቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ ጾም መሠረት ጾምን የፈቃድ ጾም (የግል ጾም) እና የዐዋጅ ጾም (የሕግ ጾም) በማለት በሁለት ከፍለን የምንመለከታቸው ሲሆን የግል ጾም የምንለው ምእመናን ለንስሓ በግል የሚጾሙትን የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም ምእመናን በምክረ ካህናት ወይም ከንስሓ አባታቸው ጋር በመመካከርና ቀኖናን በመቀበል የሚጾሙት ጾም ሲሆን አንዱ ሲጾም ሌላው ማወቅ የለበትም፡፡ የዐዋጅ አጽዋማት የምንላቸው ደግሞ ዕድሜያቸው ሰባት ዓመት ከሞላቸው ሕፃናት ጀምሮ መላው ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በኅብረት በግልጽ የሚጾሟቸው አጽዋማት ናቸው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና

 

የተከበራችሁ አንባብያን በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታና በየአካባቢው እና በየክልሉ በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ክፍል አንድና ሁለትን  ጽሑፍ ማቅረባችን ይታወቃል፡ ፡ከፍል ሦስት እነሆ ብለናል፡፡

ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የተነሡ አካላት ለጥፋታቸው የሚጠቅሱትን የፈጠራ ታሪክ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ልደት እስከ አሁን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በመጠኑ አሳይተናል፡፡ የገጠማትን ፈተና፣ ሊወጓት የመጡትን ያለዘበችበትን መንፈሳዊ ጥበብ ባለፈው ዝግጅት አቅርበናል፡፡ በተለይ ከ፲፱፻፹፫ ዓ.ም ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋትና የመንግሥት አካላትን ምላሽ ፍርድ ቤትን ጨምሮ ማቅረብ ጀምረናል፡፡ ባለፈው የጀመርነውን ቤተ ክርስቲያንን የማቃጠል ጥፋት መረጃዎችን በመጨመር ወደ ቀጣዩ እናልፋለን፡፡

በየቦታው ቤተ ክርስቲያን ትቃጠላለች፡፡ መቃጠሉ በዓላማ መሆኑ የሚታወቀው አሻራው እንዳይገኝ ወዲያውኑ የሌላ ዕምነት ቤት፣ የሌላ ዕምነት ቤት አዳራሽና ሌላም እንዲሠራበት መደረጉ ነው፡፡ «በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያኖች ተቃጥለው ወደ መስጊድነት የተቀየሩ መሆናቸውን የአካባቢው ምዕመናን ይህ እኮ ቤተ ክርስቲያን የነበረበት ነው» እያሉ ቦታውን የሚያመለክቱት በቁጭት ነው፡፡ የሚፈጸመው ጥፋት የራስን ዓላማ ለማሳካት የሌላውን መብት መጋፋት ትክክለኛ ተደርጐ ሲፈጸም እየታየ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ዓላማን ማሳካት አንድ ነገር ነው፡፡ የሌላውን መብት እየተጋፉ ዓላማን ማሳካት ግን ተገቢነት የሌለው ነው፡፡ የሌላውን ተደራጅቶ ማጥፋት በጥንታዊት ማሌ፣ በሴኔጋል፣ በጥንታዊት ግብፅና ሜርዋ፣ በርበሮችና አክራሪዎች ነባር የሥልጣኔ አሻራዎችን ማጥፋታቸውን አስታውሰን ነቅተን እንድንጠብቅ ያደርገናል፡፡ ነባሮቹና ተረጋግተው በመኖር ላይ የሚገኙ ሙስሊሞች በዕምነታቸው ስም ተገቢ ያልሆኑ ተግባራትን የሚፈፅሙ ወገኖቻቸውን ማስታገስ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥትም ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጐ ሳይመለከት ሌሎችን የሚያስተምር ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡

በዚህ ሀገር እስላሙም፣ ክርስቲያኑም፣ ፕሮቴስታንቱም የመኖር መብት አለው፡፡ አንዱ ገፊ ሌላው ተገፊ፣ አንዱ ባለ አገር ሌላው አገር የሌለው መምሰል የለበትም፡፡ ይህ ሃይማኖት የእነ እገሌ ነው ያንተ ሃይማኖት ይህ ነው ማለትም ፖለቲካ እንጂ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ሃይማኖት የሚሰበከው የሃይማኖት ትምህርት ባላቸው ወገኖች እንጂ፣ የፖለቲካ ዓላማ ባላቸው  የጥፋት ኃይሎች አይደለም፡፡ የምናመልከውን በሚመርጡልን ወገኖች ሃይማኖተኛ መሆን የለብንም፡፡ ሰሞኑን በሊሙ ኮሳ በዕምነታቸው ሽፋን አክራሪነትን የሚያራምዱ ሰዎችና ቡድኖች ክርስቲያኖችን ከማጥፋት አልፈው ‹‹ክርስትና የአማራ ነው የኦሮሞ ክርስቲያን የለውም›› በማለት ይቀሰቅሱ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ የኦሮሞ ክርስቲያን እንዳይኖር ከክርስትና ውጪ ሌሎች የኦሮሞ ሃይማኖት እንዲኖር የፈቀደው ማን ነው? አክራሪነት ሥሩ የት ሆኖ ነው የኦሮሞ ሃይማኖት መስሎ የሚሰበከው፡፡ ይህ አብረን እንዳንኖር የሚያደርግ ተባብሮ ለማጥፋት የተደረገ ሴራ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ የሚያምነው ሃይማኖት መምረጥ ያለበት ራሱ ምእመኑ እንጂ በኋላቸው ፖለቲካ አንግበው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ወገኖች መሆን የለባቸውም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ይህን የሚለው ሰላም የሚገኘው ሰላማውያንን በመግፋት ባለመሆኑ የበለጠ ጥፋት እንዳይፈጠር ነው፡፡ ይህ የእኔ ነው አትድረሱብኝ ማለትና ነባር ገዳማት ያለባቸውን ሁሉ ይጥፉ ማለት ሰላም አያመጣም፡፡

በጀጁ ወረዳ አቦምሳ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ፣ አቡሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አብሸራ መድኃኔዓለም በጉና ወረዳ አንድሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ተራም ቅዱስ ገብርኤልና መሶ ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ በእሳት ሲወድሙ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ፈርሰው፣ ጽላቱን ጨምሮ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸው ከዓመታት በፊት ተዘግቧል፡፡ ይህን የምናቀርበው መንግሥት ባለበት ሀገር እንዲህ ዓይነት ጥፋት መፈጸሙን በማሳሰብ ዳግም እንዳይፈጸም እንዲከላከል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የተመሠረተች ዘለዓለማዊት እንደሆነች ብናምንም በጥፋታችን እግዚአብሔር እንዳይቀጣን፣ ከኃጢዓት እንድንርቅ፣ እንደ ዘመነ ሰማዕታት አጥፊዎችን የሚማርክ ክርስትና የሚነበብ ክርስትና እንዲኖረን ጭምር ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን በሰማይ አለች፣ በምድርም ትኖራለች፣ በገሀድ የሚኖሩትና የተሰወሩት አንደነት መሆኗን እየመሰከርን እኛ ግን በስንፍናችን እንዳንቀጣ መንቃት ይኖርብናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደማትጠፋ መረዳትና በእምነት መጽናት ይኖርብናል፡፡ ዲያብሎስ ዓላማየን ያሳኩልኛል ያላቸውን አካላት ጦር እያስመዘዘ፣ ገጀራ እያስጨበጠ፣ እሳት እያስለኮሰ፣ ቃታ እያሳበ ጥፋታቸውን ጽድቅ አስመስሎ እያሳያቸው በማጥፋት ለመርካት ቢፈልጉም ደስታን እንደማያገኟት መረዳት ይገባል፡፡ ከአጥፊዎች ወገንም የዲያብሎስን ሽንገላ አልፈው የእግዚአብሔር ጥሪ ደርሷቸው የሚመጡ እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ «ሰውን ብትታገለው ያሸንፍሀል ወይም ታሸንፈዋለህ፤ ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች፤ ተሸንፋ ግን አታውቅም፡፡ ዲያብሎስ ቤተ ክርስቲያንን ለመውጋት ዝናሩን አራገፈ፤ ቀስቱንም ጨረሰ፤ ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጐዳትም» በማለት ያስተማረውን ክርስቲያኖች በተግባር ተፈጽሞ፣ ያዩት ነው፡፡ ይህንን እያመንንም ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠልና ምእመናን ቦታችሁ አይደለም ተብለው ሀብት ያፈሩበትን፣ ወልደው ከብደው የኖሩበትን ቦታ ሲለቁ ችግሩ እየተባባሰ ሔዶ ልንቋቋመው ከማንችልበት ደረጃ እንዳይደርስ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብ የዋሆች በመሆን ማሰብ አለብን፡፡ የግል ፍላጐታቸውንና ዓላማቸውን ለማስፈጸም ሀገራችንን በተፅዕኖአቸው ሥር ማድረግ የሚናፍቁ ወገኖች እርስ በርስ ስንፋጅ ዓላማቸውን እንዳያስፈጽሙብን፣ መሬታችንን እንጂ እኛን ስለማይፈልጉ የሩቅ ተመልካች ሆነው ሰንጫረስ ቆመው አይተው ሀገራችንን እንዳይወሰዱብን ጭምር ነው፡፡

በሥልጣኔ ሰበብ፣ በሉላዊነት ስም እየተፈጸመ ያለውን ድሀ ሀገሮችን የማዳከምና በጠንካራው የመዋጥ መጥፎ አካሔድ እንዳይደርስብን ዘመኑን የሚዋጅ ተግባር መፈጸም ግድ ይላል፡፡ በጦርነት አልሳካ ያላቸውን በማዘናጋትና በተናጥል በሚፈጽሙት ጥፋት ከእስከ አሁኑ የበለጠ እንዳንጐዳ እየተፈጸመ ያለውን እኩይ ተግባር መረዳት ይገባል፡፡ በሌሎች ሀገራት ከተፈጸሙ የሀገርን ቅርስ አጥፍቶ በአዲስ የመተካት ድርጊት ልንማርበት ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሚያቃጥሉ፣ ምእመናንን የሚያሳድዱ፣ ይዞታዋን የሚቀሙ ወገኖች በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያንንና ሀገራቸውን የሚያስጠላ ትምህርት ሲጋቱ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህም የምዕራባውያን አድናቂዎች፣ የራሳቸውን ግን አናናቂዎች ሆነዋል፡፡ የጻፏቸውን የጥላቻ መጻሕፍት እየጠቀሱ ቤተ ክርስቲያንን ሲያብጠለጥሏት ኖረዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ሥልጣን ሲይዙም ቤተ ክርስቲያንን ለሀገሪቱ ኋላ መቅረት አስተዋጽኦ ያደረገች አስመስለው ከመሳል አልፈው በክርስቲያኖች ላይም ጥላቻና ጥርጣሬ አሳድረዋል፡፡ ይህን ጉዳይ ዮሐንስ አድገህ የተባሉ ተመሪማሪ «ከዚያ በኋላ (ከንጉሡ ቀጠሎ) የመጣው መንግሥትም ዓላማዊነት (secularism) በሚል ከንቱ ፍልስፍና ተጀቡኖ ለሃይማኖት ቦታ የማይሰጥ፣ ይልቁንም ቤተ ክርስቲያኒቱን የነገሥታት መጨቆኛ መሣሪያ እንደነበረች አድርጐ በመሳል በሕዝብ ዘንድ ያላትን ተቀባይነት ለመቀነስ ይሞክር ነበር» ብለዋል፡፡

ይቆየን

ምንጭ ፤ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከሰኔ!  ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም

 

“ስለ ወንጌል እተጋለሁ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ተከፈተ

                                                                                                                በእንዳለ ደምስስ

በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን “ስለ ወንጌል እተጋለሁ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የማኅበሩ አባላትና ምእመናን በተገኙበት ሰኔ ፲፬ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ስድስት ኪሎ በሚገኘው የስብሰባ ማእከል ተከፈተ፡፡

ዐውደ ርእዩ ከሰኔ ፲፬ – ፲፮ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ኬንያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የአውስትራልያና የኒውዚላንድ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጸሎተ ወንጌል በማድረስ በይፋ ከፍተውታል፡፡

በዐውደ ርእዩ ክፍል አንድ “ቅዱስ ወንጌል ለሁሉ” በሚል የቀረበ ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያን ማን ናት?የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ዓላማ፣ ወንጌል ማስፋፋት ነው፣ የወንጌል መስፋፋት መገለጫዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ተዳሰውበታል፡፡

የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በተለይም የግብጽ፣የሕንድና የሩሲያ ተሞክሮ በክፍል ሁለት ቀርቧል፡፡አማኞቻቸውን ማጽናት መቻላቸው፣ ከተከላካይት አልፈው የተሻለ ተቋማዊ አቅም መፍጠር መቻላቸው ዛሬ ለደረሱበት አስተዋጽኦ ማድረጉ እንደ ተሞክሮ መታየት እንደሚገባው ተገልጿል፡፡እንደ ምሳሌም በመገናኝ ብዙኃን  ደረጃ ግብጽ ፲፬ የቴሌቪዥን፣ ፲፻፬፻ ድረ ገጾች፣በሕንድ ፰፣በሩሲያ ፭፻ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ዘርፍ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት ያሳየ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ከኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ አንጻር ከእኛ ምን ይጠበቃል? በሚለው ትእይንት የተጀመሩት የቴሌቪዥንና የድረ ገጽ አገልግሎቶችን ማጠናከርና ማስፋፋት፣ በስብከተ ወንጌል ላይ የሚሠሩ አካላትን ማጠናከር፣ የአስኳላ ትምህርት ቤቶችን በስፋት መከፈትና ትውልድን ማነጽ፣እንዲሁም ሌሎች በስብከተ ወንጌል ዙሪያ የተቀናጀ አገልግሎት ለማበርከት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በትዕይንቱ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

“ቤተ ክርስቲያን በመጪው ዘመን ምን መሆን አለባት” የሚለው ትዕይንት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት የሚያስችሉ መልካም ዕድሎችን፣ ፈተናዎች እንዲሁም መፍትሔ ሰጭ ጉዳዮችን የዳሰሰ ነበር፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በጠረፋማ አካባቢዎች የሚያካሔደውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተመለከተም በደቡብ ኦሞ፣ የቤንች ማጂ እና የመተከል አህጉረ ስብከት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች እንደምሳሌ ቀርበዋል፡፡ ከአንድ መቶ ሰባ ሺሕ በላይ አዳዲስ አማንያንን ማስጠመቅ እንደተቻለም ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የአውስትራሊያ እና የኒውዚላንድ አህጉረ ስብክት ሊቀ ጳጳስ ዐውደ ርእዩን ከተመለከቱ በኋላ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክትም “ወንጌል የሚለው ሐሳብ ሰውን ማዳን ነው፡፡ አባላት መሰብሰብ፣ ማብዛት ማለት አይደለም፡፡የሰውን ልብ ማግኘት፣ የእግዚአብሔርንና የሰውን ልብ ማያያዝ፣ በሌላ መልኩ ማዳን ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ስለ ዐውደ ርእዩ ብጹዓን አባቶች አስተያየታቸውን በጹሑፍ ሲያስቀምጡ

ብፁዕነታቸው ኦርቶዶክሳዊነት ላይ በማተኮር “ኦርቶዶክሳዊነት ዝም ብሎ በአንድ ጊዜ የሚጠፋ ወይም በአንድ ጊዜ የተገኘ ነገር አይደለም፡፡ ክርስትና ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስካለንበት ጊዜ ድረስ በመንፈሳዊ  ሐረገ ትውልድ ተያይዞ የመጣ ዕንቊ የሆነ ነገር ነው፡፡ ይህንን ትውልዱ መቀበል ከቻለ ዓለምን ማዳን ይችላል፡፡” ብለዋል፡፡

ዐውደ ርእዩ እሰከ ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፣በየዕለቱ ትምህርተ ወንጌል፣ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ ዶክመንተሪ ፊልሞች ይቀርባሉ፡፡

ዕረፍት ያጣች ነፍስ!

በሕይወት ሳልለው

እግዚአብሔር አምላካችን በአርአያውና በአምሳሉ ሲፈጥረን በክብር ነውና ከአለመኖር ወደ መኖር ያመጣንም በእስትንፋሱ ነበር፡፡ «እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ»፤ (ዘፍ ፪፥፯)፤

አባታችን አዳም ባደረገው ስሕተት ከገነት ተባሮ ወደ ምድር ከወረደ በኋላ ኑሮው የከፋ ነበር፤ ብዙም ተፈትኗል፤ ገነት ሳለ ደስታን እንጂ መከራን አላወቀም፤ ነገር ግን እዚህ ምድር ላይ በፍርሃትና በጭንቀት ይኖር ነበር፡፡ ከልብሰ ብርሃንም ተራቆተ፤ ተበረደ፤ የበለስ ቅጠል ቆርጦም ለበሰ፤ በመከራውም ጊዜ የፈጣሪውን ትእዛዝ በመተላለፉ የሠራውን ኃጢአቱን በማሰብ ያለማቋረጥ ያለቅስ ነበር፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላም በተገባለት ቃልኪዳን መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እስኪያድነው ድረስ በምድር ብዙ ተሠቃይቷል፡፡

ሰው ድኅነትን የሚያገኘው በክርስትና ሕይወቱ ውስጥ ለእምነትና ለሃይማኖቱ መሥዋዕትነት በመክፈል፤ ዘወትር በክርስቲያናዊ ሥርዓት፤ በምስጋናና በሕገ እግዚአብሔር ሲኖር ነው፡፡ ነገር ግን ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ በኃጢአት ማዕበል ውስጥ ተዘፍቃለች፤ መከራ፤ ሥቃይ፤ ችግር፤ እንዲሁም ጦርነት በየሀገሩ በዝቷል፡፡ ትንቢቱም እንደሚገልጸው «ሕዝብ በሕዝብ ላይ፤ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ፤ በየሀገሩም ረኃብ፤ ቸነፈርም፤ የምድር መናወጥም ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡ ያንጊዜም ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ ያን ጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ» (ማቴ. ፳፬፥፯-፲)፡፡

በዚህች ምድር ላይ ስንኖር ልንፈተን እንችላለን፤ በዕለት ክንዋኔያችን ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ ሊገጥመን ይችላል፡፡ ከጥንት ጀምሮ አእምሮአችንን ለመቆጣጠርና ትዕግስትን አስጨርሶ ተስፋ ለማስቆረጥ የሚፈታተነን ጠላት ዲያብሎስ የማሳቻ መንገዱ ብዙ ነውና በእምነት ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሰው ለውድቀትና ለጥፋት የቀረበ ይሆናል፤ ዕረፍትን የሚሻ ሰው ግን በተስፋ ውስጥ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሔ እንዳለው፤ ለእያንዳንዱ ለተቆለፈ መዝጊያ አንድ ወይም ብዙ ቁልፎች እንዳሉትና ለእያንዳንዱ ውድቀትም መነሻ እንዳለው ይታወቃል::

ሰላምና ፍቅር ከእኛ ሲርቅ ማንነታችንን መጥላት፤ የእኛ ያልሆነውን ባዕድ ጠባይ መቀበል እንጀምራለን፤ ነፍስ ግን ሁሌም ፈጣሪዋን ትፈልጋለች፤ እናም ትጨነቃለች፡፡

ዛሬም ያለው ትውልድ ከነፍሱ ይልቅ ለምድራዊ ሕይወቱ ይለፋል፤ ነገር ግን ከንቱ ልፋት ነው፡፡ «ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ነፋስንም እንደመከተል ነው»መጽሐፈ መክብብ ፩፥፲፬፡፡የሰው ልጅ ኅሊናውን ሳይክድ ለእምነቱ ተገዝቶ ሲኖር ወደ ፈጣሪው መቅረብ ይቻለዋል፤ ሁል ጊዜም አምላኩን ሲያስብ፤ በተስፋም ሲኖር፤ ወደ ክብር ቦታው እንደሚመለስ በማመን በጎ ሥራን አዘውትሮ ይተገብራል፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ሰው ፈጣሪውን ያስባል፤ ይፈራል፤ ያከብራል እንዲሁም በሕጉ ይመራል፤ ከራሱም አልፎ ለሌሎች ጥሩ ማድረግን ይመኛል፤ ያደርጋልም፡፡

እርግጥ ነው ጠባያችን እንደመልካችን ይለያያል፤ እግዚአብሔር አምላካችን በቃሉ «ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሉአት» እንዳለው (ዘፍ. ፩፥፮)፤ በዓለማችን በቢሊዮን የምንቆጠር ሰዎች አለን፡፡ እናም ተከባብሮ የመኖር ውዴታና ግዴታ የእኛ ቢሆንም ኃላፊነትን ከመወጣት ይልቅ ክፋት፤ ተንኮል፤ በደል፤ ጥላቻ፤ ግድያ ከዛም አልፎ  ባዕድ አምላኪም በዝቷል፡፡ ፈውስና በረከት ማጣት፤ በምሬትና በሰቆቃ ውስጥ ለመኖር መንስኤው የኃጢአት መብዛት ነው፤ ክፉውም ሆነ ደጉ የሥራችን ውጤት ነው፡፡

በዚህ ምድር ስንኖር ሥጋችንንም ዋጋ በማሳጣት ለነፍሳችን ልንኖርላት እንደሚገባ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል አስተምሮናል፤ «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ፤ ነፍሱንም ቢያጣ፤ ለሰው ምን ይረባዋል? ሰውስ ለነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር?» (ማቴ. ፲፮፥፳፮)፡፡

ሰላም ፍቅር ማጣት

የባዶነት ስሜት

ማንነትን መጥላት

በምሬት አንደበት

ክፉ ነገር ማውጣት

ርኩሰት በኃጢአት

ነፃነትን መሻት

  ነፍስ ስታጣ ዕረፍት

የተጨነቀች ዕለት

«እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ፤» (ማቴ.፲፩፥፳፰) ይለናልና ፈጣሪያችንን አብዝተን እንለምነው፤ እንጸልይ እንጹም፤ ዕረፍት ያጣች ነፍሳችንን እናሳርፋት፡፡

በዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና

የተከበራችሁ አንባብያን በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታና በየአካባቢው እና በየክልሉ በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ክፍል አንድን  ማቅረባችን ይታወቃል ክፍል ሁለትን እነሆ ብለናል፡፡

ምዕራባውያንና የእነሱ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን ሁሉ ፈጽመዋል፡፡ የአሳባቸው አቀንቃኝ ኢትዮጵያዊ “ፈረንጆችንም” አግኝተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም ሊቃውንቷንም ለመተቸት ያለ ስማቸው ስም ያለ ግብራቸው ግብር በመስጠት ጥላቻውን በመግለጽ አልሜዳ የተባለ ሚሲዮናዊ የፈጠራ ታሪክ ጽፏል፡፡ የእሱን ጥላቻ እየጠቀሱ ቤተ ክርስቲያንን የሚተቹት የግብር ልጆቹ ናቸው፡፡ የእሱን ጥፋት ዳንኤል ክብረት «አልሜዳ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አምርሮ የሚጠላ ኋላ ቀርና በኑፋቄ የተሞላች አድርጎ የሚፈርጅ ኢየሱሳዊ /ሚስዮናዊ/ ነበር፡፡ በጽሑፎቹ ላይ ይህን ነው ሲያንጸባርቅ የኖረው፡፡ ከዚህ ጠባዩ አንጻርም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ቢተች የሚጠበቅ እንጂ የሚገርም አይደለም» (ዳንኤል፣ ፳፻፲፩፣፫‐፬) በማለት ገልጦታል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ሆነ ተሐድሶአውያን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን የሚተቹት የእሱን አሳብ እየጠቀሱ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን መንቀፍና ያለ ግብራቸው ግብር መስጠት ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ይጠቅመናል ብለው ያስባሉ፡፡ ለኋለኞቹ የቤተ ክርስቲያን ተችዎች ጀማሪና ፊታውራሪያቸው አልሜዳ ነው፡፡ የውጭ ጸሐፊዎች የኢትዮጵያውያንን አእምሮ በመበረዝ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትችት እንዲያዘንቡ ምክንያት መሆናቸውን ከአልሜዳ ጽሑፍ መረዳት ይቻላል፡፡ ለመነሻ ያህል ይህን ካቀረብን በየዘርፉ የደረሱትን ችግሮች እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

ሀ. የቤተ ክርስቲያን መቃጠል፡- በየዘመናቱ፣ በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት በአክራሪ ሙስሊሞች፣ በግለኝነት በታወሩ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችና በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠሉ ቆይተዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት የግል ጥላቻና የተለየ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እንጂ ሁሉም የሌሎች እምነቶች ተከታዮች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል አብረው የሚያዝኑና የሚያለቅሱ፣ ክርስቲያኖች ሲሳደዱና መከራ ሲደርስባቸው በቤታቸው የሚሸሽጉ ብሎም አብረው መከራ የሚቀበሉ፣ ክርስቲያኖች ኃይላቸውን እያሰባሰቡ አቅማቸውን እያጠናከሩ መልሰው ለመገንባት ሲደክሙ ከገንዘብ እስከ አሳብ ድጋፍ የሚያደርጉ የሌላ እምነት ተከታዮች አሁንም በየቦታው መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ በዘመናችንም ክርስቲያኖች በጥብዐት መከራውን ተቋቁመው ክርስትና በሞት፣ በስድት፣ በእሳትና በመከራ የማይፈታ መሆኑን አስመስክረዋል፡፡ በዚሁ አንጻር ግን በመገናኛ ብዙኃን በተለያዩ ቦታዎች የሚቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያናት ያልታወቁ ግለሰቦች ያቃጠሏቸው እንደሆነ ቢነገርም ታስቦበት፣ ተጠንቶ፣ ምን ለማግኘትና ምን መልስ ለመስጠት አስቀድሞ እየታሰበ ቃጠሎው መፈጸሙን የሚጠቁሙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ፲፱፻፺፫ዓ.ም ሚያዝያ ፲፪ ቀን በአርሲ ሀገረ ስብከት ኮፈሌ ወረዳ ጉች ቀበሌ ገበሬ ማኅበር የሚገኘው የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በአክራሪ እስላሞች ለመቃጠል የቻለው ከተማ ላይ ሊያደርሱት የነበረው አደጋ በመከላከያ ሠሪዊትና በፖሊስ ስለተደናቀፈባቸው ነው፡፡ ገጠር በመግባት የክርስቲያኖችን ቤት እየመረጡ ማቃጠላቸው የታቀደና የተደራጀ ጥቃት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሃይማኖታዊ ትንኮሳ ከትላንት እስከ ዛሬ መቀጠሉ ታስቦበት እየተሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በአንድ በኩል አጥፊዎች ልብ እንዲገዙ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ከትላንት እስከ ዛሬ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በመረዳት ለእምነት ቤቶችና ለክርስቲያኖች ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግ ሊያነቁ፣ ምእመናንም ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ እንዲደራጁና አዲስ ነገር ሲገጥማቸው ለፍትሕ አካላት እንዲያቀርቡ ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡ ክርስቲያኖች የሚማሩት ከመከራ፣ ቅድስናቸው የሚገለጠው በፈተና መሆኑ የተጻፈ፣ ክርስቲያኖች በተግባር ፈጽመው ያሳዩት ሕይወት ነው፡፡

በጅማ ሀገረ ስብከት ከመስከረም ፲፮ እስከ ጥቅምት ፬ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም ጨጉ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቦሬ ቅዱስ ገብርኤልና በሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናት በአክራሪ እስላሞች ተቃጥለዋል፡፡ ንዋያተ ቅድሳት ተዘርፈዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጅማ፣ በምዕራብ በወለጋና በኢሉባቡር ከ፲፫ በላይ አብያተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ተዘርፈዋል፡፡ ኅዳር ፮ ቀን ፲፱፻፺፰ዓ.ም በአርሲ ሀገረ ስብከት በኮፈሌ ወረዳ የምትገኘው የአይሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፀረ ክርስትና አቋም ባለው ቡድን ተቃጥላለች፡፡ አገልጋይ ካህናት በቤተ መቅደስ ውስጥ ታርደዋል፣ አሥር ክርስቲያኖች በገጀራ ተገድለው፣ አብያተ ክርስቲያናትና የክርስቲያኖች መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ብዙ ንብረት ወድሟል፤ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው በሀገራችን ሰላም እንዳይሰፍን ሆን ብለው ግጭት የሚፈጥሩ አካላት መኖራቸውን ነው፡፡

በወቅቱ አጥፊዎችን ሊያስተምር የሚችል እርምጃ መወሰድ ሲገባ ጉዳዩ ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆን ከመንግሥት አካላት ተጽዕኖ ይደረግ ነበር፡፡ አጥፊዎችን ማስታገስ ሲገባ ጉዳት የደረሰባቸው ክርስቲያኖች ጉዳታቸውን እንዳይናገሩ መከልከል ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ሲፈጸም መፈጸም በሕግም በሞራልም የሚያስወቅስ ነው፡፡ ይህ በምንም ዓይነት መንገድ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ለአጥፊዎች ከለላ መስጠትን እንጂ ለፍትሕ መቆምን አያሳይም፡፡ አጥፊዎች ሲያጠፋና ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ ዝም ብሎ ማየት ትዕግሥትን ሳይሆን የጥፋት ተባባሪ መሆንን የሚያሳይ ነው፡፡

በወቅቱ የመንግሥት አካላትን ያሳስብ የነበረው የገደሉትንና አደጋ ያደረሱትን አካላት ለመያዝ ሳይሆን አደጋው በተፈጸመበት ወቅት ከቦታው ተገኝተው የዘገቡትን አካላት ለመያዝ ነበር፡፡ ይህ ተግባር አሁንም ስለቀጠለ ቤተ ክስስቲያን እየተገፋች ድምፅ የሚያሰማላት አካል እያጣች ነው፡፡ አጥፊዎች ለስንት ሺህ ዘመናት የኖረ የሀገር ሀብት ሲያወድሙ እንደ ቀልድ እየታለፈ መሆኑ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በየካቲት ወር መጨረሻና በመጋቢት ወር መጀመሪያ በድሬደዋ ከተማ አጠገብ የሚገኘውን ደን በመመንጠር የቤተ ክርስቲያንን መሬት በመከፋፈል ላይ ሳሉ ሕግ አስከባሪ አካላት ቢደርሱም አልታዘዝንም በማለት ቆመው ሲመለከቱ አጥፊዎች ከቦታው እንዲሸሹ ሲያደርጉ እንደነበር የዐይን እማኞች ገልጠዋል፡፡ በሊሙ ኮሳ ወረዳ በያዝነው ዓመት በተፈጸመው ጥፋት ከወረዳ አመራር ጀምሮ ሥልጣን ላይ የሚገኙ ወገኖች ጥፋቱን ያደረሱት አካላት በእምነት ስለሚመስሏቸው ወደ ሕግ ለማቅረብ አለመቻላቸውን ወረዳ ቤተ ክህነቱ ለሀገረ ስብከቱ የጻፈው የድረሱልኝ ደብዳቤ ያስረዳል፡፡ ምክንያት ተፈልጐ የሚያዙትና ካለ ፍርድ እስር ቤት እንዲቆዩ የሚደረጉትም ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ይህም ክርስቲያኖች እንዲሞቱ የተፈረደባቸው፣ ለሚደረስባቸው  አደጋ ሁሉ ከለላ የሌላቸው መሆኑን ሲያመለክት አጥፊዎች ደግሞ ሽፋን የሚሰጣቸው ይመስላል፡፡ ይህንም በሐረር ከተማ ጥር ፲፩ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ.ም ለጥምቀት በዓል በወጡ ምእመናን ላይ ለጁምአ ስግደት በአንድ መስጊድ ተሰብስበው የነበሩ ሙስሊሞች በፈጸሙት ትንኮሳ ግጭት ተፈጥሮ የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በፖሊስ ቊጥጥር ሥር የዋሉት ፲፮ ምእመናን ያለ ምንም ውሳኔ ከስድስት ወራት በላይ መቆየታቸው ማሳያ ነው፡፡ ግጭቱን ማን እንደጀመረው? ዓላማው ምን እንደነበር? አጣርቶ አስቸኳይ ውሳኔ መስጠት፣ አጥፊም በጥፋቱ እንዳይቀጥል ማስተማር ሲገባ ክርስቲያኖችን መርጦ ማሰር መፍትሔ አይሆንም፡፡ ወንጀል የፈጸመ ሰው አይያዝ ባይባልም ክርስቲያኖች ብቻ ተይዘው የሚታሰሩበት፣ ቢታሰሩም ቶሎ ለፍርድ የማይቀርቡበት ምክንያት ሌላ ዓላማ ያለ ያስመስላል፡፡

በአጥፊዎች ላይ ውሳኔ ቢሰጥበትም ቤተ ክርስቲያንን ላቃጠሉ፣ ንዋያተ ቅድሳትን ለዘረፉ አካላት የሚሰጠው ፍርድ አንድ በግ ከሰረቀ ሌባ ጋር ልዩነት የሌለው በነፃ ከማሰናበት ያልተሻለ መሆኑ ለክርስቲያኖችና ለቤተ ክርስቲያን ትኩረት መነፈጉን የሚያሳይ ነው፡፡ መረዳት የሚገባው ቤተ ክርስቲያንን አቃጥለው፣ ቅርሱን አውድመው እስከሚጨርሱ ዝም ከተባለ “ኢትዮጵያን የጎብኝዎች መዳረሻ እናደርጋለን” የሚለው አሳብ የሕልም እንጀራ መሆኑን ነው፡፡ የሚነገረው ቃልም ተፈጻሚነት ሳይኖረው ክርስቲያኖችን በማይሆን ነገር ለማዘናጋት የሚፈጸም መሆኑን የሚያሰገነዝብ ነው፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያን ላይ የተነሡት አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ብቻቸውን ሳይሆኑ በጀርባቸው ሌላ አይዞህ ባይ እንዳላቸው የሚያመለክት ነው፡፡ የክርስቲያኖችና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ትኩረት እንዳይሰጠው፣ በመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዳያገኝና ሽፋን የሚያገኘውም ዘግይቶ መሆኑ ሌላ ችግር ይዞ እንዳይመጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የሚሰጠው አስተያየት እውነት የሚመስለው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጽሙት እንዲሸፈን መደረጉ ነው፡፡

 በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሜኤሶን ወረዳ በሚገኘው የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አቡነ ሳሙኤል ገዳም የካቲት ፳ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ለከብት ዘረፋ ወደ ገዳሙ ክልል የገቡ የኢሳ ጎሳ አባላትን ለመከላከል የተደረገውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ ሰደድ እሳት ተቀሰቀሰ፡፡ በወቀቱ የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ከ፳፻፩ ዓ.ም በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነበር፡፡ ከአሥራ አምስት ዓመት በፊት ተቀስቅሶ ለ፲፭ ቀናት የቆየው ሰደድ እሳት ከ፲፩ ሺህ ሄክታር በላይ ደን አውድሟል፡፡ እሳቱ በቊጥጥር ሥር የዋለው ከዋናው የገዳሙ ግቢ ለመድረስ ፭፻ ሜትር ያህል ሲቀረው ነበር፡፡ በወቅቱ ከ፴፰ ያላነሱ ከሰል አክሳዮች ለሰደድ እሳቱ መነሣት ምክንያት ናቸው በሚል ተጠርጥረው በቊጥጥር ሥር ቢውሉም ወዲያው በዋስ ተለቀዋል፡፡ ክስ ይመሥረትባቸው አይመሥረትባቸውም የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ማስተካከያ የሚሰጥ አለመኖሩን ያሳያል፡፡

ይቆየን!

ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከግንቦት ፲፮-፴ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም

በዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና

በተለያዩ መድረኮች ቤተ ክርስቲያን ከእምነት ውጭ የሆኑትን ለማሰቃየት የክፉ አድራጊዎች ጠበቃ የሆነች የሚያስመስሉ ጽሑፎች ይቀርባሉ፡፡ ድብቅ ዓላማ ያላቸው ወገኖች ቤተ ክርስቲያንንና ክርስቲያኖችን ለማጥፋት ሰበብ በመፈለግ ጥፋተኛ እያስመሰሉ ያቀርባሉ፡፡ በመሠረቱ ይህ አስተሳሰብ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው ታሪክ በመሰነድ፣ ትውልድ በምግባር ኮትኩታ ያቆየች ባለውለታ፣ ቅርሶቿ ለሀገር ልዩ መታወቂያ ጐብኝዎችን ማርኮ የሚያመጣ ሆኖ ሳለ ያለ ስሟ ስም መስጠቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከእውነት የራቀ ሐሳብ ይዘው ጥፋተኛ ሳትሆን፤ ጥፋተኛ ስለሆነችና ከአጥፊዎች ስለተባበረች መጥፋት ይገባታል እንበቀላት የሚለው ነው፡፡ እነዚህ ለማጥፋት ምክንያት ፈላጊ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን እያቃጠሉና ምእመናንን እየገደሉ ለምን ሲባሉ ጥፋተኛ ስለሆነች ይላሉ፡፡ መቼ፣ የት፣ በማን፣ እነማንን ተብለው ሲየጠቁ መልስ የላቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠልና ምእመናንን መግደል የእምነቱ ተከታዮች ራሳቸውን ወደ መከላከል ከዚያም ወደ መጉዳት ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ መረዳት ይገባል፡፡ ለተፈጸመው ጥፋት አጸፋውን ቤተ ክርስቲያን ብትመልስ በሀገር ላይ ሊከሠት የሚችለውን ጥፋት አስቀድሞ መረዳትም ይጠቅማል፡፡ ጥናትን ሽፋን አድርጎ ለአጥፊዎች ዱላ የሚያቀብሉ አካላትም ከድርጊታቸው መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት አጥፊዎችን ለሕግ ከማቅረብ በተጨማሪ ለክርስቲያኖችና ለቤተ ክርስቲያን ከለላ መስጠት ይኖርበታል፡፡ አጥፊዎችም ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የመዘዙት ሰይፍ ወደ ራሳቸው እንዳይዞር እና የእርስ በእርስ መጠፋፋት ሊያስከትል እንደሚችል ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በሃይማኖትና በዘር ምክንያት የተቀሰቀሰ ግጭት መብረጃ እንደሌለው በየሀገራቱ የተፈጸሙትን ጥፋቶች ማየት ይገባል፡፡ ታሪክ መጥቀስ ብቻውን የዕውቀት ባለቤት አያደርግም ከታሪክ መማር እንጂ፡፡

ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ወዲህ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውንና ከዛሬ ነገ እርምት ይወስድበታል በማለት በትዕግሥት ስትጠብቅ መኖሯን ከመግለጻችን በፊት ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማያት ስታዘጋጅ፣ በፍቅር ስባ፣ በትምህርት አለዝባ በእምነትም በምግባርም እንዲስተካከሉ በማድረግ ነው፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ሀገራችን ብቸኛ የራሷ ፊደል ያላት፣ ዘመን ተሻግሮ ከዘመናችን የደረሰ ቅርስ አበርክታ ሀገራችን በመላው ዓለም እንድትታወቅ ያደረች ባለውለታ ናት፡፡ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ኢትዮጵያውያን የቅኝ ግዛት ቀንበርን ሰብረው ጥለው፣ የነጭን ትምክተኛነት አስተንፍሰው ልጆቻቸው ቀና ብለን እንድንሔድ የመሪነቱን ሚና የተጫወተች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በውጭ ሀገራት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተጽፈው እምነት፣ ዕውቀት፣ ሥነ ምግባር የሚያስተምሩ መጻሕፍት ኢትዮጵያዊ በሆነ ብሂል ተተርጒመው ትውልድ እንዲማርባቸው፣ ሊቃውንቶቿ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በአውሮፓ የኢትዮጵያን ባህል፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ በማስተዋወቅ የአምባሳደርነት ሚና እንዲጫወቱ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህን የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ‹‹የኢትዮጵያ ምሁራን መነኮሳት በኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ክልል ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ውጭ በመሔድ በታሪክ ሊታወስና ሊጠና የሚገባ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ አካባቢ በሱዳንና በግብፅ፣ በየመንና በኢየሩሳሌም፣ በአውሮፓ በመሔድ እነሱም እየተማሩ፣ የውጭውንም ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋና ታሪክ፣ ሃይማኖትና ባህል እንዲያውቅና እንዲፅፍ አድርገዋል›› (አክሊሉ፤፹፩) በማለት ገልጠውታል፡፡

እውነተኞቹ ተመራማሪዎች ያለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን ማሰብ እንደሚከብድ በምርምራቸው አረጋግጠው እውነቱን ከሐሰት፣ ብስሉን ከጥሬ፣ የሚጠቅመውን ከሚጐዳው፣ የተፈጸመውን ካልተፈጸመው ለይተው ከጥንካሬያችን እንድንማር ከስሕተታችን እንድንጠበቅ ያደረጋሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማዳከም ዓላማችንን ያሳካልናል ብለው የሚያስቡ ወገኖች ደግሞ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ፈልገው ቅስማቸው ተሰብሮ እንዲመለስ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ስለተረዱ ስሟን ለማጥፋት፣ ታሪኳን ለመበከል የጻፉትን አሉባልታ እውነት አድርገው በመውሰድ ታሪክ ሲያበላሹ፣ በተቀመጡበት የኃላፊነት ቦታ ጥፋት ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ ሰውን በሰውነቱ እኩል ማገልገል ሲገባቸው በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በጎጥ፣ በቡድንና በባህል በመከፋፈል ሥልጣንን ለክፉ ተግባር ይጠቀማሉ፡፡ ሕዝብን ለማገልገል የተሰጣቸውን ሥልጣን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን የማሳደድ ተልእኮ ይፈጽማሉ፡፡ ሀገር ሰላም ካልሆነችና ዜጎቿ በሰላም ወጥተው ካለገቡ አጥፊዎችም ችግር እንደሚገጥማቸው አልተረዱትም፡፡

በካናዳ፣ በቫቲካን፣ በጀርመንና በሌሎችም ሀገሮች የኢትዮጵያ ጥናት ተቋማት እንዲከፈቱ፣ ተመርምሮ የማያልቅ ዕውቀት የያዙት የብራና መጻሕፍት ለዓለም እንዲተዋወቁ ያደረጉት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምራ «ሑሩ ወመሀሩ» ብላ ያሰማራቻቸው ሊቃውንት ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም ሀገራችን እንግዳ ተቀባይ የሆነችውና ዓለም ፊቱን ያዞረባቸውን የመሐመድ ተከታዮች ሳይቀር መጠጊያ እንድትሆን ያደረጋት ቤተ ክርስቲያን በእምነት ኮትኩታ፣ በምግባር አንፃ ያስተማረቻቸው እነ ንጉሥ አርማህ ርኅሩኆች ብቻ ሳይሆኑ አስጠጉኝ ብሎ የመጣባቸውን አሳልፈው ለመስጠት ሰብአዊነት የተለያቸው ስላልነበሩ ጭምር ነው፡፡

ወርቅ ላበደረ ጠጠር፣ እህል ላበደረ አፈር እንዲሉ ይህን ውሉ ውለታ ለዋለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው መልስ ነው፡፡ የደረሱበት መረጃ ካለ ማስረጃን መሠረት አድርጎ እውነት ማሳወቅ አንድ ነገር ነው፣ ሐሰትን እውነት እያስመሰሉ ማቅረብና ሰውን ለብጥብጥ መጋበዝ ግን ጤነኛ አእምሮ ያለው፣ በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው የሚፈጽመው አይደለም፡፡ በየጊዜው ቤተ ክርስቲያንን የሚያቃጥሉት፣ ክርስቲያኖችን የሚገድሉት፣ ንብረታቸውን የሚቀሙትና የሚያሳድዱት ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መንግሥት እርምት ይወስዳል ቢባልም ምንም ነገር እንዳልተፈጸመ እየታለፈ፣ የማዘናጊያና የማረሳሻ ተግባር እየተፈጸመ ነው፡፡

ከምዕራባውያን የተኮረጀው ሥርዐተ ትምህርት ባልነበረበት ዘመን የሀገራቸው አምባሳደር የነበሩ፣ የውጭ ዲፕሎማት ሲመጣ አስተርጓሚ ሆነው ሲያገለግሉ የኖሩ ሊቃውንትን ያፈራችን ቤተ ክርስቲያን ከዋለችበት ላለማሳደር፣ ካደረችበት ላለማዋል እየተፈጸመ ያለው ግፍ መቆም አለበት፡፡ የሊቃውንቱን አስተዋጽኦ አክሊሉ ሀብቴ ‹‹ሆኖም እዚያ (ኢየሩሳሌም) የተደራጀው የመነኮሳት ማኅበር ኢትዮጵያን በመወከል ወደ ኢጣሊያም፣ ወደ አርመንም፣ ወደ ቊስጥንጥንያም፣ በመሔድ ግንኙነት ፈጥሮ እንደነበርና ምን አልባትም ከአርመኖች ጋር በነበረው የቅርብ ግንኙነት አርመኖች ፊደላቸውን ሊቀረፁ የቻሉት ከኢትዮጵያ ፊደል እንደሆነም ይነገራል፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም በሚመላለሱበት ዘመን እግረ መንገዳቸውንም ከሱዳንና ከግብፅ ክርስቲያኖች ጋር የቅርብ ግንኙነት መፍጠራቸው ይታመናል፡፡ የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ምሁራን መነኮሳት ፈር ቀዳጅ አስተዋጽኦ እንዲሁ መጠናት የሚገባው ነው›› (አክሊሉ፣ ፷፪) በማለት ገልጠውታል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ሰው አክባሪ፣ ሀገር ወዳድ፣ የሥራ ፍቅር ያላቸው፣ የራሳቸውን የማያስነኩ፣ የሌላውን የማይፈልጉ አድርጋ ስታሳድጋቸው ጠብ አጫሪነትን፣ በጉልበታቸው የሚመኩ መሆንን እንዲጸየፉ በማድረግ ነው፡፡ ጠላታቸውን በጽናትና በትዕግሥት እንዲቋቋሙ፣ ሀገርና ሃይማኖት ሊያጠፋ የመጣውን የጥፋት ኃይል እንዳያሸንፍ ያደረገች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህ ድርጊቷ ያበሳጫቸው ምዕራባውያን በዘመናዊ ትምህርት ሰበብ በየሴሚናሪዎቻቸውና ኮሌጆቻቸው አስተምረው የላኳቸው ወገኖቻችን ነባሩን የኢትዮጵያ ሃይማኖትና፣ የክርስቲያኖች ተጋድሎ የሚያናንቅ፣ መልኩ የእኛ ቢሆንም የነጭ ጉዳይ አስፈጻሚ ሀገሪቱን ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት የባለቤትነት ስሜት የሚያድርበት እንዳይሆን አእምሮውን ለውጠው ሲልኩት ኖረዋል፡፡ በመመረቂያ ጽሑፍ ሰበብ ቤተ ክርስቲያንን ያለ ስሟ ስም፣ ያለ ግብሯ ግብር እየሰጡ የዘመናችን ተመራማሪ ነን ባዮች የግብር አባት ሆኑ፡፡ በዚህ ተግባራቸውም ትውልዱ በሰላም ውሎ እንዳይገባ እንቅልፍ ላጡ ወገኖች መንገድ መሪ የጥፋት ተባባሪ ሆነው አልፈዋል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሠየሙ አካላት በተለያዩ የኅትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያወርዱትን የስድብ ዶፍ መመልከት ይቻላል፡፡ በአካል መግዛት ያልተቻላቸውን ኢትዮጵያውያንን በአእምሮ ለመግዛት መሰሎቻችንንና በሥጋ የሚዛመዱንን አእምሮ እየለወጡ የሚልኩልንንና እነሱም አልፎ ሒያጅ መንገደኞችና ለቤተ ክርስቲያን ጥላቻ ያደረባቸውን ወገኖች እየጠየቁ የጻፉትን አሉባልታ በትክክለኛ ማስረጃ በመሞገት፣ የዕውቀታቸውን ግልብነት፣ የመረጃቸውን ተራነት፣ የትነታኔያቸውን አመክንዮ አልባነት ማሳየት ይኖርብናል፡፡ አጥፊዎች ታጥቀው ሲዘምቱብን ዝም ብሎ ማየት እሳት መቃጠሉን የሰማ የዋህ እኔስ ሣር ውስጥ ተደብቄያለሁ በማለት የመለሰውን የሚያስታውስ ይሆናል፡፡

ቱሪስቶች ሊጐበኙ የሚመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ገዳማት፣ አድባራት፣ ሥዕላት፣ የብራና መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት እንዲሁም ክርስቲያን ነገሥታት የገነቧቸውን አብያተ ክርስቲያናት፣ ሐውልቶችና አብያተ መንግሥታት ለመጎብኘት ነው፡፡ ይህን አስተዋጽኦ ያደረገችልን ቤተ ክርስቲያን መደገፍና መጠበቅ ሲገባ ስትጠቃ ዝም ብሎ ማየት ማሯን እንጂ ንቧን አልፈልግም እንደ ማለት ይቈጠራል፡፡ ለጥፋት የተሰለፉ ወገኖች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ አደጋ ሲያደርሱ የግለሰቦች ጉዳይ እየመሰለ ይቀርባል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ይነገራል፡፡ በሌሎች እምነቶች ላይ የሚፈጸመው ወይም ራሳቸው ፈጽመው ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል የተባለውን ለሚፈጽሙት ግን ከመገናኛ ብዙኃን ጀምሮ የሚሰጠው ሽፋን የሚገርም ነው፡፡ ይህም ክርስቲያኖች ሲገደሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ መረጃው በቶሎ እንዳይነገር ከተቻለም ተዳፍኖ እንዲቀር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን እንድንጠረጥር የሚያደርግ ነው፡፡ ለምሳሌ በቡኖ በደሌ የተፈጸመውን ሰቆቃ በሥልጣን ላይ የተቀመጡ አካላት ወንጀሉን የፈጸሙት አካላት በእምነት ስለሚመስሏቸው ለማዳፈን ሞክረዋል፡፡ በሰሜን ሸዋና በኬሚሴ በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው ጥፋት በመገናኛ ብዙኃን የተነገረው ጥፋቱ ከተፈጸመ ከአራት ቀናት በኋላ መሆኑን ኢትዮጲስ ጋዜጣ በሚያዝያ ፮ ዕትሙ አስነብቧል፡፡ በበሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አካባቢው አብያተ ክርስቲያን ተቃጥለውና ምእመናን ተገድለው አጥፊዎችን መያዝ ሲገባ መረጃው ያላቸውን ክርስቲያኖች ለመያዝ ይደረግ የነበረው ወከባ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ይቆየን!

ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከግንቦት ፲፮-፴ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም