ጾመ ሐዋርያት

በተክለሐዋርያት

ጾመ ሐዋርያት በወርኃ ሰኔ ስለሚጾም በምእመናን ዘንድ የሰኔ ጾም በመባል ይታወቃል፤ ከሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማትም አንዱ ነው፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለስብከተ ወንጌል ከመሰማራታቸው በፊት የጾሙት ጾም ነው፡፡

ይህም ጾም ከበዓለ ኀምሳ በኋላ የሚጾም ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን ቅዱሳን ሐዋርያት በጸሎት ይተጉ ወደ ነበረበት ቤት በመሄድ ደቀመዛሙርቱን ይዟቸው ከቤት በመውጣት መንገድ ጀመረ፡፡ እርሱ ከፊት እየመራቸው እነርሱ እየተከተሉት ወደ ረጅሙና በረጃጅም ዛፎች ወደ ተሞላው ደብረ ዘይት ተራራ ይዟቸው ወጣ፡፡ ይህንንም እየነገራቸው ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ፤ከፍ አለ፡፡ ነጭ የሆነች ብሩህ ደመናም አምላካችንን ተቀበለችው፡፡ከዓይናቸውም እየራቀ፤ከእይታቸው በርቀት ሳይሆን በርኅቀት ተሰወረባቸው፡፡ሐዋርያትም ኢየሱስ ክርስቶስን በጣም ይወዱት ስለነበር ሲለያቸው አዝነው አተኩረው ሰማዩን ለረጅም ሰዓት ተመለከቱ፡፡ ድንገትም ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ቅዱሳን መላእክት በአጠገባቸው ቆመው ታዩአቸው፡፡መላእክትም ሐዋርያትን እንዲህ አሏቸው፤ ‹‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን  ቆማችኋል፡፡ ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል›› አሏቸው፤ (ሐዋ. ፩፥፰-፲፩)፡፡ ሐዋርያትም የመላእክትን ማረጋጊያ ቃል ከሰሙ በኋላ  በኢየሩሳሌም ወደ ምትገኘው ቤተ መቅደስ በመሄድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነገራቸው እስኪፈጸም ድረስ ቀን ከሌሊት በአንድነት ሆነው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከመካከላቸው አድርገው በጾምና በጸሎት እየተጉ ቆዩ፡፡

የጾመ ሐዋርያት የጊዜ ቀመር ሥሌት በዓለ ጰራቅሊጦስ እንደ ገባ ባለው የመጀመሪያው ሰኞ ይውላል፡፡ ጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ደቀ መዛሙርቱን ይህን ጾም እንደሚጾሙት እንዲህ ተናግሮ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው። ‹‹እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ እንጾማለን፥ ደቀ መዛሙርትህስ ለምን አይጾሙም? አሉት›› (ማቴ.፱፥፲፬)።  ደቀ መዛሙርቱ ይህንን በጠየቁት ጊዜ ጌታችን እንዲህ ብሎ መልሶላቸው ነበር፡፡‹‹ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው  ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ አይችሉም፤ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ያንጊዜም ይጾማሉ›› (ማቴ.፱፥፲፭)፡፡

እኔ ሳለሁ አይጾሙም ማለቱ እርሱ ካልሞተና ካላረገ፤ መንፈስ ቅዱስም ካልተሰጣቸው በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነት ጾመው ድል መንሳት ስለማይቻላቸው ነው፡፡ ይህን ጾም የምንጾመው ሐዋርያት ጾመው ጸልየው ድል ያደረጉትን ዓለም እኛም የምናሸንፍበት ኃይል እንዲሰጠን ፈጣሪያችንን አምላከ ሐዋርያት ተለመነን እያልን ለመማጸን ነው፡፡

ይህን ጾም እንደ ሌሎቹ አጽዋማት ሁሉ እያንዳንዱ ምእመን ሊጾመው የሚገባ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን አብዛኛው ምእመን ‹‹የቄስ ጾም›› ነው በማለት ከጾሙ ሽሽት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሥርዓተ ቤተክርስትያንን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ መስተካከል ይገባዋል፡፡

ሐዋርያትን አብነት በማድረግ ጾመን በረከትን ልናተርፍ ይገባናል፡፡

የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት

የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት

የቅዱሳን ሐዋርያት በረከት

የጻድቃን የሰማዕታት ጸሎት እና ምልጃ አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

አሜን፡፡