ዕርገተ ሥጋ፤ርደተ ቃል

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

የቃልን ከልዕልና ወደ ትሕትና መምጣት፤ የሥጋን ከትሕትና ወደ ልዕልና መውጣት ስናስብ እጅግ ያስደንቀናል! የመጀመሪያው የሰው ልጆች አባት ከክብር ወደ ሓሳር መምጣት ፍጥረትን ሁሉ ያስገረመ ጉዳይ ነበር፤ የሁለተኛው አባታችን ከልዕልና ወደ ትሕትና መምጣት ዳግም አስገረመን፤ ሁለቱም ይሆናሉ ብለን ያልጠበቅናቸው ክሥተቶች ናቸውና።

የእግዚአብሔርን ፍቅር እስኪ ተመልከቱት! አዳምን በልጅነት አከበረው፤ ይህ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ነው፤ ሙት የነበረውን ባሕረ የሰብእ ምድራዊት ሕይወቱን በሰማያዊ የልዕልና ሕይወት ለወጠለት። ይህንንም ሲያደርግ የበለጠ ተስፋ በማድረግ ነው እንጅ እንዲያው ያለ ምክንያት አልነበረም፤ ወይሁቦ እግዚአብሔር አምላክ መንበረ ዳዊት አቡሁ ወይነግሥ ለቤተ ያዕቆብ ለዓለም፤ እግዚአብሔር አምላክም የዳዊትን የአባቱን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ለዘለዓለም ይነግሣል››፡፡ ይህ የመጨረሻውን የተስፋ ምሥጢር የያዘ ቃል ነው፤(መጨረሻነቱ ለሕገ ተሰብኦ ነው እንጅ ለዘለዓለሙ እንዳልሆነ ግልጽ ነው)።

ከመሬት ዐፈር ያበጀው ምድራዊ ፍጡር አዳም፤ በተረገመባት ዕለት ‹‹ኦ! አዳም መሬት አንተ ወትገብእ ውስተ መሬት፤ አዳም ሆይ! አንተ መሬት ነህ ወደ መሬትነትህ ትመለሳለህ ›› ብሎ ነገረው፡፡ በዚህም የሥጋውን ፈቃድ ትቶ በነፍሱ ፈቃድ ይኖር ነበር፤ ይህ ለነፍሱ የተሰጠው ቃል ኪዳን ነው፤ ሥጋ የራሷን ፈቃድ ትታ በነፍስ ፈቃድ ትሄዳለች፤ ነፍስ ደግሞ ያላትን ሰማያዊ ጸጋዋን ከሥጋዋ አዋሕዳ ትኖራለች።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም መጥቶ የጠፋውን የሰው ልጅ ክብር መለሰ፤ ሳይገባቸው የነገሡትንም ቀጣቸው፤ያለ አግባብ የተዋረዱትን ከፍ ከፍ ሊያደርጋቸውም ፍጹም ሰው ሆኗል። ከተሾሙትና ከሊቃውንቱ መካከል የተሾመ ሐዋርያ ልትነግሩኝ ትችላላችሁ? ራሳቸውን ጻድቃን ብለው ከሚጠሩት መካከል የተገኘበትን ልታሳዩኝ ትችላላችሁ? እንዲያው ከአሕዛብ የመረጠ፤ ከኃጥአን ጋር የበላ የጠጣ አይደለምን? እንዲያውም ስለእርሱ በመጽሐፍ ‹‹ባለጠጎችን ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው፤ የተራቡትን በቸርነቱ አጠገባቸው፤የተዋረዱትን ከፍ ከፍ አደረጋቸው›› ተብሎለታል፤ ሉቃ.፩፥፶፩-፶፬፡፡ ጌታም የመጣበትም ምክንያት ለተዋረደው ሥጋችን ዋጋን መስጠት ነውና ወደ ተዋረዱት መካከል ገብቶ ታየ፡፡ መንግሥቱን በቄሣር ሳይሆን በዚህ ዓለም ገዥ በዲያብሎስ ለተነጠቀው ሰው መንግሥቱን የሚመልስ ስለሆነ ነው፤ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም የዳዊትን የአባቱን ዙፋን ይሰጠዋል›› የተባለው ያውም ለጊዜው ያይደለ ለዘለዓለሙ እንዲነግሥ መንግሥትን ስለመለሰለት ነው፡፡

ወደዚህ ዓለም የመጣበትን መንገድ ምሥጢር ማንም ሊያውቅ አይቻለውም፤ ማንም በማይመረምረው ምሥጢር ነበርና፤ ሲያርግ ግን ዐይን ሁሉ እየተመለከተው ነበር፡፡ ጠላት ወደ ሰዎች የገባው ተሰውሮ እንጅ ተገልጦ አልነበረም፤ በኋላ በደረሰብን መከራ እስክናውቀው ድረስ አዳምና ሔዋን ከሕይወት ወደ ሞት  መግባቱን መች አወቁትና! ድል ከነሣቸው በኋላ ግን ነግሦ ለዘመናት ኖረ፡፡ ጌታ የተወለደበትን ዘመኑን አስቡት፤ ከዳዊት ቤት ነጋሢ የታጣባት፤ የይሁዳው አንበሳ የዳዊት ዘር ለባርነት ተላልፎ የተሰጠበት ዘመን ነበር፤ መጽሐፍ እንደተናገረው በአንድ ወቅት ከምድር ዳርቻ የተሰበሰቡ ሰዎች ያደንቁት የነበረ ነጋሢ የነበረበት የዳዊት ቤተ መንግሥት ዛሬ ምንም ተተኪ ንጉሥ ታጥቶ ለሌላ ንጉሥ ለሮማዊ ቄሣር ተላልፎ ሲሰጥ ተመልከቱ፤ ሮማውያን በመንግሥት ሳይደራጁ ገና እስራኤላውያን እስከ ዓለም ዳርቻ የወጣ ዜና የነበረው መንግሥት ነበራቸው፤ማቴ.፲፪፥፵፪፡፡

በያዕቆብ ላይ ለዘለዓለሙ እንዲነግሥ የተነገረለት የዳዊት ልጅ ማለቂያ በሌለው መንግሥት ይነግሥ ዘንድ ዳግመኛ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ የቃል ርደት (መውረድ)፤ የሥጋ ዕርገት ሥጋን በዚህ ዓለም ብቻ ያነገሠው አይደለም፤ በመላአክት ዓለምም እንዲነግሥ ሥልጣንን ሰጥቶታል፡፡ ሁሉን ከሚያስገዛለት በቀር ሁሉን እንዲገዛ ሥልጣን ተሰጥቶታልና፤ በማቴዎስ ወንጌል ፳፰፥፳ ላይም ‹‹ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ›› ተብሏል፡፡  በቆሮንቶስ ፲፭፥፳፯ እና በሌሎች መጻሕፍት ስለእርሱ ሲናገር በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ ዳግመኛ ይመጣል ብሎ መናገሩ በሕያዋኑ በመላእክት፤ የሰው ልጆች ላይ ነግሦ እንዲኖር መሆኑን ያሳያል፡፡

ጌታችን ክርስቶስም በሥውር ወደዚህ ዓለም መጥቶ ጠላትን ድል ስለነሳው እየተዘመረለትና ቅዱሳን ሐዋርያት ትኩር ብለው እያዩት ወደ ሰማይ ዐረገ፤ የሐዋርያት ሥራ ፩፥፲ ላይም ትኩር ብለው ወደ ሰማይ እየተመለከቱ የነበሩ መሆናቸውን ተጽፏል። አርባኛው ቀን በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እያነጋገራቸው ከኢየሩሳሌም ውጭ ቢታንያ ወደተባለው ሥፍራ ወሰዳቸው፤ እጁን አንሥቶ እየባረካቸው ዐረገ፤ እነርሱም ትኩር ብለው እየተመለከቱት ሳሉ ደመና ከዐይናቸው ሰውራ ተቀበለችው፤ሥራ ፩፥፱-፲፬፡፡

እንግዲህ እነርሱ ከዓለም የወጡት ከዚያ በፊት የነበረው ሕይወታቸው መውጣት መግባት፤ መውደቅ መነሣት የበዛበት ስለነበረ፤ ይህንንም በመረዳት የዓለም ፍቅር ስቦ እንደማያስቀረው በመገንዘብ፤ ከክርስቶስ ሞትና ዕርገት በኋላ ወደ ሕይወት እንጅ ወደ ሞት የሚያደርስ ፍቅር እንደሌለ በማወቅ ነበር። ስለዚህ ልቡናቸው የሞትን አድማስ ተሻግሮ የሰማያትን ዳርቻ ተመራምሮ ወደ ክርስቶስ ዙፋን በማየት ክርስቶስ ዙፋን ላይ ሲቀመጥ ከዙፋኑ ፊት ቆሞ ዘወትር ለማመስገን ትኩር ብለው ተመለከቱ።

ከዚህ በኋላ ለሐዋርያት በምድር ላይ ሰማያዊውን ኑሮ እያሰቡ የሚኖሩ እንደሆነ ተገንዝበው ትኩር ብለው በመመልከት እዝነ ልቦናቸውን ከክርስቶስ ጋር አሳርገዋል፤ ፩ኛ ቆሮ.፪፥፲፮፤ እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ የእግዚአብሔርን ምሥጢር፤ የመንግሥተ ሰማያትን ነገር እንደምን ማወቅ ይቻላል?

አንድ ቀን ዮሐንስ ሐጺር የመነኮሳቱን የእጅ ሥራ ሽጦ እንዲመጣ ታዞ ወደ ገበያ ወጣ፤ ከገበያው መካከል እንደ ተቀመጠ ልቡን ወደ ሰማይ የሚነጥቅ ምሥጢር መጣበትና ያን እያደነቀ ሳለ ገዥ መጥቶ ዋጋ ንገረኝ ይለዋል፤ እሱ ግን ልቡናው በምድር ላይ አልነበረምና ለገዥው አልመለሰለትም፡፡ ሕሊና ሲያርግ እንዲህ ነው! እጅህ ላይ ያለውን ቁሳዊ ነገር ሳይሆን በሰማይ ያለውን መንፈሳዊ ሀብት እንድትሻ ያደርግሃል፤ ከገበያ መካከል ቆሞ የዓለምን ጫጫታ ሳይሰሙ በመላእክት ዜማ ነፍስን መማረክ አይገርምም!

ዓለም የያዝከውን እስክታገኝ አጠገብህ ናት፤ የያዝከውን ከሸጥህላት ግን ካጠገብህ አታገኛትም። ወዳንተ ስትመጣም ገዥ ሆና ትቀርባለች፤ ልብህን ካልሰጠሀት ለምትጠይቅህም መልስ ካልሰጠሀት እሷ ላንተ ገዥ አይደለችም፤ እንዳትገዛ ከፈለክ እንደ ንሥር ሽቅብ ወጥተህ አቆልቁለህ የምትመለከት አትሁን! አንዳንዶቹ አየሩን እየከፈሉ ጠፈሩን ሰንጥቀው የመላአክትን ከተማ አልፈው ከሄዱ በኋላ አቆልቁለው መመልከት ይጀምራሉ፤ ከምድር የወደቀች ቁራጭ ሥጋ ያዩ እንደሆነ ወርደው ይቀራሉ።

መቼም ቢሆን ካለ ክርስቶስ ዓለምን ማሸነፍ አይቻልም፤ ክርስቶስ በመጽሐፍ እንደተነገረው  እዝነ ልባቸውን ማርኮ ወደ ሰማይ ዐረገ ‹‹ዐረገ ውስተ አርያም ጼዊወከ ጼዋ፤ምርኮን ማርከህ ወደ ሰማይ ወጣህ›› መዝ. ፷፯፥፲፰፡፡ ለብዙ ኃያላን ያልተሳካላቸው የሰውን እዝነ ልቦና መማረክ ነው። ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ሰውን መማረክ የቻሉ ብዙ ኃያላን መንግሥታት አሉ፤ ሰውን መማረክና የሰውን እዝነ ልቦና መማረክ ግን እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሰውን ለመማረክ ጀብደኛ መሆንና የሰውን ልብ መማረክ እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡ የሰውን ልብ መማረክ በፍቅር ስለሆነ የሕይወት ልምድ ይጠይቃል፤ የሰውን ደም እያፈሰሱ ሳይሆን ስለሰው የራስን ደም እያፈሰሱ፤ ራስን ዝቅ አድርጎ ለሌሎች ክብር መስጠት በሚታገሉት ትግል ነው አንጅ ዙፋን ላይ ሆኖ በሚዋጉት ጦርነት ልብ አይማረክም።

እኛም ዘወትር ዕርገትን በእዝነ ልቦናችን ትኩር ብለን የምንመለከት ከሆነ ዓለምን እናሸንፋታለን፤ ካልሆነ ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ባሕሩ እንሰጥማለን። ቅዱስ ጴጥሮስ የሰመጠው ባሕሩን ሲመለከት ነው፤ ጌታ ሆይ እባክህን አድነኝ፤ እየሰመጥኩ ነው ያለው፤የማቴ. ፲፬፥፳፮-፴፡፡ ስለዚህ እኛም እይታችንን ከቀራንዮ ካነሣን ዓለም ታሰጥመናለች፤ ሁል ጊዜ በእዝነ ልቦናችን ክርስቶስን ስንመለከት መንፈሳችን ታርጋለች፤ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ብሎም ለራሳችን ሰላምና ፍቅርን ይስጠን፤አሜን።