መንፈስ ቅዱስ

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ብዙዎች የተለያየ ግንዛቤ አላቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደ ረቂቅ ኃይል ይመለከቱታል፡፡ ሌሎች ደግሞ  እግዚአብሔር ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ የገለጠውና ማንነት የሌለው ኃይል እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሆነ ያውጃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም  አእምሮ ያለው ማንነት፤ ስሜትና ፈቃድ ያለው መለኮታዊ አካል እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ «እኔ እግዚአብሔር በምልበት ጊዜ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለቴ ነው» ብሎ እንደተናገረው እግዚአብሔር የሚለው ስም የሥላሴ መጠሪያ ነው፡፡ የአብ የወልድ እስትንፋሳቸው የሆነ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ ጋር በዕሪና በፍጹም መተካከል ያለ ነውና እግዚአብሔር መሆኑን እንመሠክራለን፡፡ ይኽውም የቅዱሳን ነቢያት ሐዋርያትና መምህራን ትምህርት ምስክር ነው፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ ንጉሡ በራእዩ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ እንዳየው፤ ሱራፌልም በሁለት ክንፎቻቸው ፊታቸውን፤ በሁለት ክንፎቻቸው እግሮቻቸውን እየሸፈኑ፤ በሁለት ክንፎቻቸውም ከጽንፍ ጽንፍ እየበረሩና አንዱም ለአንዱ «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ በቸርነትህ ተሞልታለች» እያሉ እንደሚያመሰግኑት ነግሮናል፡፡ ሊቃውንቱ ሱራፌል ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ያመሰገኑበትን ምሥጢር ሲያብራሩ፤ ቅዱስ የሚለው ቃል አለመለወጡ፤ ሦስቱ አካላት በባሕርይ፤ በህልውና፤ በሥልጣን፤ በአገዛዝና በመሳሰለው አንድ መሆናቸው ሳይለወጥ ሦስት መሆኑ የእግዚአብሔርን የአካል ሦስትነት የሚገልጥ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡(ኢሳ.፮፥፩-፱) ይህ የሊቃውንቱ ትምህርት እውነተኛ መሆኑ ማስረጃው ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ቅዱስ መነጽር እንደተመለከተው በሐዲስ ኪዳንም የራእይ አባት (አቡቀለምሲስ) የተባለው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም በእግዚአብሔር ዙፋን መካከል ያሉ የሰው፤ የአንበሳ፤ የላምና የንሥርን ፊት ይመስላሉ፡፡ እነርሱም ኪሩቤል ቃሉ ሳይለወጥ «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ፤ የነበረና ያለ፤ የሚመጣውም፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ» እያሉ ቀንና ሌሊት ያለ ዕረፍት እንደሚያመሰግኑ መናገሩ ነው፡፡ (ራእ.፬፥፰)

ዳግመኛም ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ ፮ ቁጥር ፱ ላይ «የጌታንም ድምጽ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?» ሲል ሰማሁ ይላል፡፡ ተናጋሪው ጌታ እግዚአብሔር ማንን እልካለሁ? ማለቱ ባሕርያዊ አንድነቱን ማንስ ይሄድልናል? ብሎም ሦስትነቱን ገልጧል፡፡ ነቢዩ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ብሎ እግዚአብሔር ለተናገረው ነገር ‹‹እኔን ላከኝ›› ካለው በኋላ በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ተቀምጦ የተገለጠለት እግዚአብሔር ‹‹ሂድና ይህን ሕዝብ መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱም፤ በላቸው አለኝ›› በማለት ተናገረ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉና ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር መሆኑን በግልጥ መስክረዋል፡፡(ዮሐ.፲፪፥፴፱-፵፩፤የሐዋ.፳፰፥፳፭-፳፯) ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ኃይለ ቃል ብቻ ሳይሆን በኦሪት፤ በነቢያት፤ በጸጋና በረድኤት አድሮባቸው ሕዝቡን ሲመክር፤ሲያስተምርና ሲገሥጽ የነበረ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ደጋግሞ አስተምሯል፡፡ ይኽው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በፍጹም የማይመረመር፤ የማይታወቅ፤ የእግዚአብሔር ጥልቅ ባሕርይ የሚታወቀው፤ በራሱ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ የመንፈስ ቅዱስን ነገር በስፋት እንዳስተማረ እንረዳለን፡፡(፩ቆሮ.፪፥፲፩፤ዕብ.፫፥፯)

መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር የመሆኑ እውነታ  በብዙ ቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ በግልጽ ተነግሮአል፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናንያ ለምን እንደዋሸ ሲጠይቀው  ‹‹ሐናንያ ሆይ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን ስለምን በልብህ ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥከውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህንን ነገር በልብህ ስለምን አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው›› ይለናል፡፡ እንግዲህ ከዚህ ኃይለ ቃል ሐናንያ እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን እንዳልዋሸ፤ ይህ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሆነ በግልጽ እንረዳለን(የሐዋ.ሥራ ፭፥፫-፬)፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ «አቤቱ  ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፤ አንተ በዚያ አለህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፤ በዚያ አለህ።» በማለት ተናግሯል፡፡ ይህ ደግሞ በሰማይ በምድርም፤ በጠፈርም በጥልቁም ምሉዕ ሆኖ መገኘት የእግዚአብሔር መለኮታዊ ባሕርዩ ስለሆነ መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ሥፍራ የሚገኝ ፍጹም ምሉዕ አምላክ መሆኑን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ይነግረናል (መዝ. ፻፴፱፥፯-፰)፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእርግጥ መለኮታዊ ማንነት እንደሆነ ማወቅ እንችላለን፤ ምክንያቱም አዕምሮ፤ ስሜቶችና ፈቃድ አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያስባል፤ያውቃልም (፩ኛ ቆሮ. ፪፥፲)፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሊያዝን ይችላል፡፡  (ኤፌ. ፬፥፴) መንፈስ ለእኛ ይማልድልናል (ሮሜ ፰፥፳፮-፳፯)፡፡ እንደ ፈቃዱ ውሳኔዎችን ያደርጋል፡፡ (፩ኛ ቆሮ.፲፪፥፯-፲፩) መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ጻድቁ ኢዮብም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፤ ሁሉን የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ›› እንደዚሁም ‹‹በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ›› በማለት ደጋግሞ መናገሩ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ መሆኑን ያስረዳል፡፡እነዚህ ኃይለ ቃላት የሚያስረዱን መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ፤ ሁሉን ቻይና የአምላክ (የአብ የወልድ) እስትንፋሳቸው መሆኑን ነው፡፡

እግዚአብሔር አካላዊም ነው፡፡ ነገር ግን እንደፍጡራን አካል በሰው ልጅ ልቡና የሚመረመር  አይደለም፡፡ (ኢዮ.፲፩፥፯፤፩ቆሮ.፪፥፲-፲፭፤ሮሜ ፲፩፥፴፫) ወንጌላዊው ዮሐንስም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አካል ረቂቅ መሆኑን ሲያስተምር «እግዚአብሔር መንፈስ ነው» ብሎናል፡፡ (ዮሐ. ፬፥፳፬) እግዚአብሔር መንፈስ መባሉም አካል የሌለው ማለት ሳይሆን አካሉ የማይመረመር የማይዳሰስ የማይጨበጥ የማይታይ መሆኑን ለመገለጽ ሲሆን መንፈስ ቅዱስም መንፈስ መባሉም አካላዊና አካሉም ረቂቅ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ቃለ ሰብእ እንደ ቃለ መላእክት ዝርው ያይደለ፤ የአብ የመንፈስ ቅዱስ አካላዊ ቃል እንደሚባል ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ (ዮሐ.፩፥፩-፫) ስለዚህም ሁሉን የሚችል የአምላክ እስትንፋስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ የአብ የወልድ አካላዊ እስትንፋሳቻው ነው፡፡ አካላዊ በመሆኑም ከአብና ከወልድ ጋር በክብር ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ለነቢዩ ኢሳይያስ ተገልጧል፡፡(ኢሳ.፮፥፩-፱፤የሐዋ. ፳፰፥፳)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክቱ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ በመሆኑ የአካል ክፍል በሆነው አንደበቱ እየተናገረ እንዲህ ሲል መስክሯል ‹‹መንፈስ ግን በግልጥ በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንት ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል (ይናገራል)››፡፡ (፩ጢሞ.፬፥፩) መንፈስ ቅዱስ መምከር ብቻ ሳይሆን ለሐዋርያትም ስለ አገልግሎታቸው መመሪያን ይሰጣቸው እንደነበርም ‹‹እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ›› በማለት ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ መንፈስ ቅዱስ አካላዊነት ይናገራሉ፡፡ (የሐዋ.፲፫፥፪) በሰማይ ድል ስለነሱ ቅዱሳን‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ለጌታ የሚሞቱ ብፁዓን ናቸው›› ተብሎ በተነገረ ጊዜም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የእኛን አካል የፈጠረ አካላዊ ነውና ‹‹አዎን ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸውም ይከተላቸዋል›› ብሎ እንደነገረው ባለራእዩ ቅዱስ ዮሐንስ  አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ (ራእ.፲፬፥፲፫) ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዕርገቱ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ወደ እነርሱ እንደሚመጣና ሁሉን እንደሚያስተምራቸው፤ምሥጢራትንም እንደሚገልጥላቸው፤ተአምራት የሚያደርጉበትን ጸጋና ሥልጣንም እንደሚሰጣቸውና መከራን ሁሉ እንዲችሉ ኃይልን እንደሚያስታጥቃቸው በሚገባ አስተምሯቸዋል፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፳፮)

አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና መንፈስ ቅዱስ የሚሠርጸው ከአብ ብቻ እንደሆነ ‹‹ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለእኔ ይመሰክራል›› በማለት ለቅዱሳን ሐዋርያት አስቀድሞ ነግሮአቸዋል፡፡ (ዮሐ.፲፭፥፳፮) መንፈስ ቅዱስ ከአብ ጋር ወልድን ለድኅነተ ዓለም እንደላከም ተብሎ ተጽፏል ‹‹አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል›› እንዳለ ፊተኛና ኋለኛ አልፋና ዖሜጋ፤ መጀመሪያውና መጨረሻው የሆነ እግዚአብሔር ወልድም ከዕርገቱ በኋላ በደልን ለማንጻት ምሥጢራትን ለመግለጽ በመንፈሳዊ ሐሴት ኃጢአትን ለማስተሥረይ ከአብ ጋር ሆኖ የባሕርይ ሕይወቱ የሆነ መንፈስ ቅዱስን ልኮታል፡፡ (ኢሳ.፵፰፥፲፪-፲፮፤ራእ.፩፥፰፤፳፪፥፲፫) ሃይማኖታቸው የቀናች ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ሊቃውንትም በጉባዔ ኒቅያ መቶ ሃምሳው ሊቃውንት በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ጌታችን በወንጌል ያስተማረውን ትምህርት መሠረት አድርገው በጸሎተ ሃይማኖት ‹‹ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ ዘሠረጸ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት፤በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን እርሱም ጌታ ሕይወትን የሚሰጥ ከአብ የሠረጸ ከአብና ከወልድ ጋር በአንድነት እንሰግድለታለን እናመሰግነዋለን፤ እርሱም በነቢያት አድሮ የተናገረ ነው›› ብለው አውጀዋል፡፡

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ባለበት ሥፍራ ሁሉ አርነት አለ፡፡‹‹የጌታ መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ›› ተብሎ እንደተጻፈ፤ አርነቱም ከዲያብሎስ አገዛዝ፤ ከሰይጣናዊ አሠራር፤ ከኃጢአትና ከሥጋ ፈቃድ ሁሉ ነው፡፡ (፪ቆሮ. ፫፥፲፯፤ገላ. ፭፤፲፱) ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በወረደላቸው ጊዜ አልጮኹም፤ ተንቀጥቅጠው አልወደቁም፤ የነበሩበትን አካባቢ በጩኽት አላወኩም፤ የእግዚአብሔር የሆኑትን አልተሳደቡም፡፡ የተገለጠላቸውና የተናገሯቸው ቋንቋዎችም፤ በወቅቱ ከመላው ዓለም የመጡ ሰዎች ይናገሩባቸው የነበሩ ቋንቋዎች (ልሳናት) ናቸው፡፡ቅዱሳን ሐዋርያት ከመንፈስ ቅዱስ በተገለጠላቸው የተለያዩ ቋንቋዎች ዓለም ክርስቶስን በማመን፤ ጽድቅን በመከተል፤ የሰውን ዘር በሙሉ እንደራሱ እንዲወድ፤ ለኔ የሚያስፈልገኝ ለሌላውም ያስፈልገዋል እንዲል አስተማሩት፡፡መንፈስ ቅዱስ ባለበት ሥፍራ ከልዩነት አንድነት፤ ከእኔነት ይልቅ ለእኛ ማለት፤ ከመገፋፋት መደጋገፍ፤ ከመበታተን መሰባሰብ፤ ከትዕቢትና ከዕብሪት ትሕትና ጎልቶ ይታያል፡፡ስለዚህም በቅዱሳት መጻሕፍት ‹‹መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን›› እንደዚሁም ደግሞ ‹‹በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ›› ተብሎ እንደተነገረ፤ የምንጓዝበትን መንገድና አስተሳሰባችንን ከዚህ አንጻር ልንመረምር ይገባናል፡፡ (ሰቆ.ኤር. ፫፥፵፤፪ቆሮ.፲፫፥፭)

የጸጋ ሁሉ ባለቤት፤ ፈጣሪ ፍጡራን፤ አምጻኤ ዓለማት፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በቸርነቱ ለክብርና ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃን፤ አሜን!!!