ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከትናንት እስከ ዛሬ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥቅምት ፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ግብረ ኖሎት

በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ምሳ ተመግቧል፡፡ የተዘጋጀው የምግብ ማዕድ ካበቃ በኋላም ቅዱስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጠርቶ ‹‹ትወደኛለህን?›› እያለ ጠይቆታል፡፡ እንደሚወደው ምላሽ መስጠቱን ተከትሎም ‹‹በጎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ፤ ግልገሎቼን ጠብቅ፤›› በማለት አዝዞታል (ዮሐ. ፳፩፥፩-፲፯)፡፡

ይህ ምሥጢር ለጊዜው ጌታችን ሐዋርያትን፣ ሰብዐ አርድእትንና ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስትን በአጠቃላይ መቶ ሃያውን ቤተሰብእ እንዲጠብቅና እንዲከባከብ ለቅዱስ ጴጥሮስ ሓላፊነት መስጠቱን ያመላክታል፡፡ ለፍጻሜው የቤተ ክርስቲያን አባቶች (ጳጳሳት) መምህራንን፣ ካህናትን እና ሕዝበ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ፣ እንዲያስተዳድሩ በእግዚአብሔር መሾማቸውን የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ መምህራንና ካህናትም በየመዓርጋቸው ወጣንያን፣ ማእከላውያን እና ፍጹማን ምእመናንን የመጠበቅ፣ የማስተማር፣ የመከታተል ሓላፊነት እንዳለባቸው ከዚህ ትምህርት እንገነዘባለን፡፡ ይኸውም ሐዋርያዊ ግብረ ኖሎት (ሐዋርያዊ የእረኝነት አገልግሎት) ነው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ

ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጣቸውን አምላካዊ ትእዛዝ እና የኖላዊነት ሥልጣን (ሥልጣነ ክህነት) መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የኖላዊነት ተልእኮውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ተልእኮዉን ለማከናወን የሚያስችሉ ሕግጋትን ለማውጣት፣ መመሪያዎችንም ለማጽደቅ በዓመት ሁለት ጊዜ መንፈሳዊ ጉባኤ ያደርጋል፡፡ የመጀመሪያው ጉባኤ ጥቅምት ፲፪ ቀን (በቅዱስ ማቴዎስ ክብረ በዓል)፤ ሁለተኛው ደግሞ በዓለ ትንሣኤ በዋለ በሃያ አምስተኛው ቀን (በርክበ ካህናት) ይካሔዳል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ብቻ በሚሳተፉበት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አባቶቻችን በጋራ በመሰባሰብ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቀላጠፈ አገልግሎት፣ ለምእመናን በሃይማኖት መጽናትና መንፈሳዊ ዕድገት የሚበጁ መመሪያዎችንና ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ፡፡

አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ

ከቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በተጨማሪ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ያሉ መንፈሳውያን ሰበካ ጉባኤያትም ቃለ ዓዋዲውንና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን መነሻ በማድረግ በየጊዜው ጉባኤ በማድረግ ለሐዋርያዊ ተልእኮው መዳረስ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት የሚበጁ የጋራ አቋም መግለጫዎችንና ደንቦችን ያወጣሉ፡፡ ከእነዚህ ጉባኤያት መካከልም የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

በየዓመቱ በጥቅምት ወር በሚካሔደው በዚህ ጉባኤ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚጠቅሙ፣ ለመንፈሳዊ አስተዳደሯም የሚበጁ መሠረታዊ ጉዳዮች ይነሣሉ፤ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ይወጡና በአባቶች ተመዝነው አስፈላጊነታቸው ከታመነበት ይጸድቃሉ፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ አህጉረ ስብከት፣ የድርጅቶችና የመንፈሳዊ ኮሌጆች እንደዚሁም የማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎት ሪፖርቶች በዚህ ጉባኤ ይቀርባሉ፡፡ በሪፖርቶቹ ላይም ውይይትና የልምድ ልውውጥ ይደረግና የላቀ ውጤት ያስመዘገቡት ይሸለማሉ፤ ይበረታታሉ፡፡ ዝቅተኛ የአገልግሎት ፍሬ ይዘው የመጡ ደግሞ ከጉባኤው ልምድ ቀስመው አገልግሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ይመከራሉ፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አመሠራረት ታሪክ በአጭሩ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በእጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሰብሳቢነት፣ በፀባቴ ጥዑመ ልሳን ጸሐፊነት፣ በሰባ ሁለት የአድባራት አስተዳዳሪዎችና አገልጋይ ካህናት አባልነት የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የሚወስን መንፈሳዊ ጉባኤ መስከረም ፰ ቀን ፲፱፻፲፰ ዓ.ም ተቋቁሞ እንደነበር፤ ከዚያም በ፲፱፻፶፱ ዓ.ም መንግሥት ያወጣው የመሬት ግብር ዓዋጅ በቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር በማምጣቱ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ተቋማት ለማዋቀር በዓዋጅ ቍጥር ፵፰/፶፱ እና ፹፫/፷፭ ሕጋዊ ፈቃድ እንደተሰጣት፤ በዚህ ሥልጣን መሠረትም ቤተ ክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ቃል ተመርታ፣ በሀብቶቿ በምእመናን ተጠቅማ፣ ከመንግሥት ጥገኝነት ነጻ ኾና፣ ራሷን ችላ መተዳደር እንደጀመረች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ሰማዕቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ፓትርያርክ ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ምእመናንን የሚያሳትፍ የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ደንብ (ቃለ ዓዋዲ) አዘጋጅተው በ፲፱፻፷፭ ዓ.ም የሰበካ ጉባኤ አስተዳደርን አቋቁመዋል፡፡ ወጣቶችን ጭምር የሚያሳትፈው ይህ ቃለ ዓዋዲም አገልጋይ ካህናት የወር ደመወዝ እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባሻገር በካህናትና በምእመናን መካከል ያለው ኅብረት እንዲጠናከርም አድርጓል፡፡ ስለዚህም ስለሰበካ ጉባኤ መቋቋም ሲነገር ወጥነት ያለው መንፈሳዊ የአስተዳደር መዋቅር እንዲዘረጋ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አብረው ይዘከራሉ፡፡

ቅዱስነታቸው የጀመሩት ይኼው መዋቅራዊ አሠራር እና ያፋጠኑት ሐዋርያዊ አገልግሎትም በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን ይበልጥ ተስፋፍቷል፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ኾነው ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ የሰበካ ጉባኤን በማጠናከር ረገድ ያደረጉት ብርቱ ጥረትም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በዚህ መልኩ እየተጠናከረ የመጣው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በማሳደግ፣ አስተዳደሯንም በማቀላጠፍ ዓመታትን አልፎ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ቅዱስ ሲኖዶስ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የወቅቱንና የዘመኑን አካሔድ በሚዋጅ መልኩ ቃለ ዓዋዲው ተሻሽሎ ሊታተም ዝግጅት ላይ ነው፡፡

የታሪኩ ምንጮች፡-

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ አክሱም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ፳፻፯ ዓ.ም፣ ገጽ 168 – 169፡፡
  • ዝክረ ነገር ዘመልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪኹን፣ ማኅበረ ቅዱሳን፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፱ ዓ.ም፤ ገጽ 140 – 141፡፡
  • ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት፣ የመጀመሪያው ልዩ ዕትም፤ አዲስ አበባ፣ የካቲት ወር 2001 ዓ.ም፤ ገጽ 14 – 15፡፡

የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ እና ተግባር

በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ ፭ ላይ እንደተገለጸው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲኾን ማድረግ፤ የቤተ ክርስቲያንን አገልጋዮች በሐዋርያዊ ተግባር ማደራጀትና ችሎታቸውንና ኑሯቸውን ማሻሻል፤ ምእመናንን ማብዛትና በመንፈሳዊ ዕውቀት ጐልምሰው፣ በምግባር በሃይማኖት ጸንተው በክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ፤ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ማሻሻልና በማናቸውም ጉዳይ ራሳቸውን ማስቻል ነው፡፡

ይህን መንፈሳዊ ዓላማ ለማስፈጸም የተዋቀረው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤም የእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፤ ከየመንበረ ጵጵስናው የተወከሉ ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ሓላፊዎች ጋር በአንድነት ተሰባስበው የሚመሠርቱት ጉባኤ ሲኾን፣ በዓመት አንድ ጊዜ የሚሰበሰብ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንዳለውና ይህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ስብሰባ እንደኾነ በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ ፵፮ ላይ ተደንግጓል፡፡

በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ ፵፯ ላይ በተቀመጠው ድንጋጌ መሠረት በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ዓመታዊ ጉባኤው ላይ ፓትርያርኩ ርእሰ መንበር፤ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ምክትል ሊቀ መንበር፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አባላት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አባልና ጸሐፊ፤ የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው አስተዳደር ጉባኤ (ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) አባል፤ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች አባላት፤ ከየአህጉረ ስብከት መንፈሳውያን አስተዳደር ጉባኤያት የተወከሉ ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አባላት፤ በውጭ አገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች አባላት ኾነው የሚሳተፉበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ነው፡፡

የአህጉረ ስብከትን ሪፖርቶችና ዕቅዶች ከሰማ በኋላ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ እና ተመካክሮ ውሳኔ ማሳለፍ፤ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማጠናከር ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤቶች፣ የካህናት፣ የሰባክያንና የሰንበት ት/ቤት መምህራን ማሠልጠኛዎች እንደዚሁም የልማትና በጎ አድራጎት ተቋማት በሀገረ ስብከት እና በማእከል ደረጃ እንዲቋቋሙና እንዲደራጁ ማድረግ፤ የአጠቃላዩን አስተዳደር ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ (ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) መምረጥ በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ ፵፰ የተዘረዘሩ የጉባኤው ሥልጣንና ተግባራት ናቸው፡፡ በዚሁ አንቀጽ እንደተጠቀሰው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ተሳትፎ በጉባኤው

ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተመሠረተ ሕጋዊ ማኅበር እንደመኾኑ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አመራርና አስፈጻሚ አባላቱን እየወከለ በአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ ስብከተ ወንልን በማስፋፋት፣ አዳዲስ ምእመናንን በማስጠመቅ፤ ለገዳማትና አብነት ትቤቶች ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ፤ ለአባቶች የስብከተ ወንጌልና ከአስተዳደር ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን በመስጠት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስፋፋት ያከናወናቸው ዐበይት ተግባራቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ከአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ጋር ተካተው ሲቀርቡ መቆየታቸውም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ለአብነትም በጠረፋማ አካባቢዎች ስብከተ ወንጌልን በማዳረስ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከስድሳ ዘጠኝ ሺሕ ለሚበልጡ አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን ማሰጠቱ፤ ለአብነት መምህራን እና ደቀ መዛሙርት ወርኃዊ የገንዘብ እና አስቸኳይ የቀለብ ድጋፍ ማድረጉ፤ የአብነትና ዘመናዊ ት/ቤቶችን፣ የመጠጥ ውኃና ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት ማስገንባቱ፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኙ ከሁለት መቶ ሺሕ በላይ የሚኾኑ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ትምህርተ ወንጌል ማስተማሩና ዐርባ አምስት ሺሕ ያኽሉን ማስመረቁ፤ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ከሰባት መቶ ዐሥር ሺሕ በላይ ልዩ ልዩ የመዝሙር ቅጂዎችንና የኅትመት ውጤቶችን እንደዚሁም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሐመር መጽሔቶችንና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጦችን ማሠራጨቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት ተካቶ በ፴፭ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ የሰበካ ጉባኤ ላይ መቅረቡ የሚታወስ ነው (ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት፣ ጥቅምት ወር ፳፻፱ ዓ.ም፤ ገጽ 75)፡፡

በመንፈሳዊ አገልግሎት ዋጋ የሚከፍል እግዚአብሔር ነውና ‹‹ይኽን ሠርተናል፤ ይኽን ፈጽመናል›› ብሎ ስለሠሩት ተግባር መናገርም ሌላ አካል እንዲናገር መሻትም ተገቢ አይደለም፡፡ ኾኖም ግን ለቍጥጥር፣ ለዕቅድና ለክንውን ያመች ዘንድ የአገልግሎት ሪፖርት ማቅረብ አንዱ የሥራ አፈጻጸም አካል ነው፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ልዩ ልዩ መምሪያዎች፣ ድርጅቶችና መንፈሳዊ ኮሌጆች እንደዚሁም የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት በአጠቃላይ ጉባኤው በሪፖርት መልክ የሚቀርበውም ከዚህ አኳያ ነው፡፡ የማኅበሩ አገልግሎት የየአህጉረ ስብከት ሪፖርት አካል ኾኖ መቅረቡ ማኅበረ ቅዱሳን አባላቱንና በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር በሚቻለው አቅም ዅሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ የመደገፍ ዓላማ እንዳለው ያመላክታል፡፡ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች ጋር በመመካከር የልጅነት ተግባሩን በመወጣት ላይ እንደሚገኝም ያስረዳል፡፡ ማኅበሩ፣ በ፳፻፱ ዓ.ም የአገልግሎት ዘመንም በተመሳሳይ መልኩ በርካታ መንፈሳውያን ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ለወደፊትም እግዚአብሔር እስከፈቀደለት ጊዜ ድረስ አገልግሎቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

፴፮ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ

ለቤተ ክርስቲያን ዅለንተናዊ አገልግሎት አስፈላጊ የኾነው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ካሁን ቀደም ይደረግ እንደነበረው ዂሉ፣ በዘንድሮው ዓመትም ከጥቅምት ፮ – ፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለሠላሳ ስድስተኛ ጊዜ ይካሔዳል፡፡ በዚህ ጉባኤ ሪፖርት ከማቅረብና መግለጫዎችን ከማውጣት ባለፈ ለቤተ ከርስቲያን አገልግሎት መፋጠን የሚተጉ አባቶች፣ እናቶችና ወንድሞች ይበረታታሉ፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት ማኅበራትና የበጎ አድራጎት ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ ድጋፍ ያገኛሉ የሚል እምነት አለን፡፡

በአንጻሩ ደግሞ በኑፋቄ፣ ገንዘብ በመመዝበር፣ ሕገ ወጥ አሠራርን በማስፈንና በሌላም ልዩ ልዩ በደል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚፈታተኑና መንፈሳውያን አባቶችን የሚያስነቅፉ አንዳንድ ግለሰቦች ተመክረውና ተገሥፀው ከስሕተታቸው እንዲመለሱ ይደረጋሉ፤ እንቢ ካሉ ደግሞ አስፈላጊውን ቅጣት ይቀበላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በአንዳንድ አገልጋዮች ዘንድ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ አሠራር እና በፍቅረ ንዋይ መታለልን ተከትሎ የሚመጣውን፣ ለብዙዎች መሰናክል የሚኾነውን አእምሯዊ ጥፋት፣ መንፈሳዊ ዝለትና አስተዳደራዊ ግድፈት ለመግታትም የዘንድሮው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የማያዳግም ውሳኔ እንደሚያሳልፍ፤ ውሳኔውንም በቅዱስ ሲኖዶስ አጸድቆ ተግባራዊ እንደሚያደርግ እንጠብቃለን፡፡

ማጠቃለያ

‹‹ለመንጋው ምሳሌ ኹኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፡፡ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ፤›› (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፫-፬) ተብሎ እንደተጻፈው ግብረ ኖሎት (የመንፈሳውያን እረኞች ተግባር) ለምድራዊ ጥቅም እና ዝና በመጨነቅ ሳይኾን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን ዋጋ በማሰብ በበግ የሚመሰሉ ምእመናን በአጋንንት ተኩላዎች እንዳይነጠቁ፣ በለምለሟ መስክ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየተሰባሰቡ ምግበ ሥጋ ምግበ ነፍስ የኾነውን ቃለ እግዚአብሔር እንዲመገቡ፣ ሰማያዊ ሕይወት የሚያስገኘውን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንዲቀበሉ በማድረግ በዐቢይነት ወደ ዘለዓለማዊ ማረፊያቸው ገነት (መንግሥተ ሰማያት) እንዲገቡ የድኅነት መንገዱን ማመቻቸት ነው፡፡

ስለኾነም ቅዱስ ሉቃስ ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ዅሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤›› (ሐዋ. ፳፥፳፰) በማለት እንዳስተማረው እረኞቻችን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሳያስጨንቁ በሥርዓትና በጥንቃቄ በጎች ምእመናንን መምራት፤ እኛ ምእመናኑም ከአባቶች ጋር የምንወርሰውን የእግዚአብሔር መንግሥት ተስፋ በማድረግ እረኞቻችንን ማክበር፣ ትእዛዛቸውንም መፈጸም ይጠበቅብናል፡፡ ከዚሁ ዂሉ ጋርም እያንዳንዳችን፣ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የመጨረሻው ወሳኝ አካል በኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡ ውሳኔዎችን እና በአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው የሚዘጋጁ ድንጋጌዎችን ተቀብለን የመፈጸምና የማስፈጸም ክርስቲያናዊ ግዴታ እንዳለብን አንርሳ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዘመነ ጽጌ  

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም 

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ በአገራችን በኢትዮጵያ የወቅቶች ሥርዓተ ዑደት መሠረት ከመስከረም ፳፮ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ፺ ቀናትን የሚያጠቃልለው ጊዜ ‹ዘመነ መጸው› ይባላል፡፡ ‹መጸው› ማለት ‹ወርኀ ነፋስ› (የነፋስ ወቅት) ማለት ሲኾን ይኸውም ‹መጸወ ባጀ፤ መጽለወ ጠወለገ› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ዘመነ መጸው ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ የሚብት (የሚገባ) የልምላሜ፣ አበባ፣ የፍሬ ወቅት ነው፡፡ በውስጡም አምስት ንዑሳን ክፍሎችን የሚያካትት ሲኾን እነዚህም፡- ዘመነ ጽጌ፣ ዘመነ አስተምህሮ፣ ዘመነ ስብከት፣ ዘመነ ብርሃን እና ዘመነ ኖላዊ ናቸው (ያሬድና ዜማው፣ ገጽ ፵፰-፵፱)፡፡

ከአምስቱ የዘመነ መጸው ክፍሎች መካከልም የመጀመሪያው ክፍል ‹ዘመነ ጽጌ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያሉትን ፵ ቀናት ያጠቃልላል፡፡ ‹ጽጌ› ቃሉ ‹ጸገየ አበበ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም አባባ ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ጽጌ› ደግሞ ‹የአበባ ወቅት፣ የአበባ ጊዜ፣ የአበባ ዘመን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ዕፀዋት በአበባ የሚያጌጡበት፣ ምድር በአበቦች ኅብረ ቀለማት የምታሸበርቅበት፣ ወንዞች ንጹሕ የሚኾኑበት፣ ጥሩ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት፣ እኛም የሰው ልጆች ‹‹አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት፤ አቤቱ ምድርን በአበቦች ውበት አስጌጥሃት›› እያልን የዘመናት አስገኚ እና ባለቤት የኾነውን ልዑል እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት፤ ከዚህም ባሻገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር ከገሊላ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዷን የምናስብበት ወቅት ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ የዘመኑ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ ጌታችንን ለማስገደል አሰበ፡፡ ጌታችንም በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብጽ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታን ያገኘሁ መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ የሁለት ዓመት ከዚያ በታች የኾኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በሰይፍ አስጨርሷል፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን የጌታችን እና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኀ ግንቦት ነው፡፡ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባ፣ የፍሬ ወቅት በመኾኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ ከመስከረም እስከ ኅዳር ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በስፋት ተገልጧል፡፡ በተለይ በአባ ጽጌ ድንግል ድርሰት በማኅሌተ ጽጌ በጥልቀት ተመሥጥሯል፡፡

በአጠቃላይ በዘመነ ጽጌ በማኅሌትና በቅዳሴ ጊዜ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚሰጡ ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታት ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን በጥልቅ ትምህርተ ሃይማኖት የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም ነው፡፡ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፡፡

በተአምረ ማርያም እና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም እናቱን እመቤታችንን የዘለፏትን ትዕማንና ኮቲባ የሚባሉ ሴቶችን ከሰውነት ወደ ውሻነት መቀየሩ፤ ውኃ በጠማቸው ጊዜ ውኃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንንም ውኃ ክፉዎች እንዳይጠጡት ማምረሩ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ኾኖ እንዲቆይ ማዘዙ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ ሰይፉን በተአምራት እንደ ቀድሞው ማደሱ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን በአምላክነቱ ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር በተሰደደች ጊዜ የደረሰባትን መከራ በማስታወስ ዘመነ ጽጌን በፈቃዳቸው የሚጾሙ ካህናትና ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡ ኾኖም ግን የጽጌ ጾም የፈቃድ ጾም እንጂ ከሰባቱ አጽዋማት ጋር የሚመደብ ስላልኾነ ጽጌን የማይጾሙ አባቶች ካህናትንና ምእመናንን ልንነቅፋቸው አይገባም፡፡ የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በሄሮድስ እጅ በግፍ የተሠዉ ሕፃናት በረከት አይለየን፡፡ አምላካችን በአበባ የሚመሰለው ሰውነታችን የጽድቅ ፍሬን ሳያፈራ እና ንስሐ ሳንገባ በሞት እንዳንወሰድ መልካም ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ብዙኃን ማርያም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን ከሚዘከሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላት መካከል መስከረም ፳፩ ቀን የሚውለው በዓል ብዙኃን ማርያም በመባል ይታወቃል፡፡ በዓሉ በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ይከበራል፤ የመጀመሪያው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ከሩቅም ከቅርብም የተሰባበሰቡት ቀን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት መኾኑ ነው፡፡ ሁለቱንም ታሪኮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፤

በ፫፻፳፭ ዓ.ም አርዮስ የሚባል መናፍቅ የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም በሚል ክህደት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል ኾነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አርዮስ ክህደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ የአርዮስ ክህደትም በሊቃውንቱ መካከል መለያየትን ፈጠረ፡፡ ጊዜው ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ‹‹አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!›› የሚል ዐዋጅ የነገረበት ወቅት ነበርና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአርዮስ ክህደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሔድ በየአገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡

በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ኒቅያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያትም ጳጳሱን ከማኅበረ ካህናቱ፤ ንጉሡን ከሠራዊቱ ጋር አጠቃላ ለመያዝ የምትችል ሰፊና ምቹ ቦታ ከመኾኗ ባሻገር ለኹሉም አማካይ ሥፍራ ስለነበረች ነው፡፡ በጉባኤው ከተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከልም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ፣ ለምጽ ያነጹ፣ አንካሳ ያረቱ፣ የዕውራንን ዓይን ያበሩ ድውያንን የፈወሱ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ተአምር ያደረጉ፤ እንደዚሁም ስለ ርትዕት ሃይማኖታቸው በመጋደል ዓይናቸው የፈረጠ፣ እጃቸው የተቈረጠ አበው ይገኙበታል፡፡

ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡

፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎች ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት ብዙኃን ማርያም እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡ እነዚህ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው (ዘፍ. ፲፬፥፲፬)፡፡

በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤

ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው ‹‹የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በአገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል›› አሏቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር ‹‹የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ›› የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ ‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› ብለው አሳውጀው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡

ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡

መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› ይላቸው ነበር፡፡ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ም የጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡

ከዚህ በኋላ ንጉሡ ‹‹መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!›› ብለው ዐዋጅ አስነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የክርስቶስ የመስቀሉ ኃይል፣ የአባቶቻችን ሊቃውንትና ነገሥታት በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ / አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ .ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ ፫፻፶፬፫፻፶፮፡፡

የሕንዱ ፓትርያርክ የመስቀል በዓልን በአዲስ አበባ አከበሩ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፲፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ካልዕ የመስቀል ደመራ በዓልን በአዲስ አበባ ከተማ በመስቀል ዐደባባይ አከበሩ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ካልዕ

ቅዱስነታቸው በዓለ መስቀልን በአዲስ አበባ ያከበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያቀረቡላቸውን መንፈሳዊ ግብዣ ተቀብለው ነው፡፡

ፓትርያርኩ በዕለቱ በሰጡት ቃለ ምዕዳን ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በቀረበላቸው መንፈሳዊ ጥሪ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረጋቸውና በዓለ መስቀልን በአዲስ አበባ ከተማ በማክበራቸው መላው የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን እንደተባረኩ፣ በዚህም ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

መስቀልን ማክበር ማለት ራስን መፈለግና የመስቀሉን ክብር ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት እንደኾነ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ኢትዮጵያውያን ምእመናን በመንፈሳዊ ሥርዓት ብቻ ሳይኾን በሕይወታቸው ጭምር የመስቀሉን ክብር እንደሚገልጹት መስክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር ሥርዓት በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በቅርስነት በመመዝገቡ መደሰታቸውንም ተናግረዋል፡፡

መላው ሕዝበ ክርስቲያን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን ወደፈጸመበት መስቀል ሊመለከት እንደሚገባው ያስረዱት ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ማጠቃለያም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ለመላው ምእመናን አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡

በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተመሠረተችው የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ስትኾን፣ በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሰባክያነ ወንጌልና ካህናት እንደዚሁም ወደሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን እንዳሏትና ሠላሳ በሚኾኑ አህጉረ ስብከቷ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በመወጣት ላይ እንደምትገኝ ታሪኳ ያስረዳል፡፡

በ፳፻፲ ዓ.ም የሚከበረውን በዓለ መስቀል በማስመልከት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተዘጋጀው ልዩ ዕትም መጽሔት በገጽ 12 – 13 እንደተጠቀሰው፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ካልዕ በሕንድ ምሥራቅና ማላንካራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ቶማስ መንበረ ፓትርያርክ ሰባተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማርቶማ ዲዲሞስ ቀዳማዊን በመተካት ከስምንት ዓመታት በፊት ስምንተኛው ፓትርያርክ ኾነው ተሹመዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር

በዘመነ ፓትርያርክነታቸውም ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ በኦሪየንታል አኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ሃይማኖታዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ከፍ ያለ መንፈሳዊ ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡

ቅዱስነታቸው መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ወደኢትዮጵያ በመጡ ጊዜም ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መንፈሳዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ፓትርያርኩ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም በዓለ መስቀልን ከማክበራቸው በተጨማሪ የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን፣ ደብረ ሊባኖስን፣ ሰበታ ቤተ ደናግል የሴት መነኮሳይያት ገዳምን እና ሌሎችም ቅዱሳት መካናትን እንደሚጎበኙ፤ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ሃይማኖታዊ ግንኙነት በሚመለከትም የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረሙ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከፓትርያርኩ የጉብኝት ዜና ስንወጣ የመስቀል ደመራ በዓል በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በመንፈሳዊ ሥርዓት ተከብሯል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል ዐደባባይ በዓሉ ሲከበርም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የየመምሪያ ሓላፊዎች፤ የገዳማት፣ አድባራት አስተዳዳሪዎች እና አገልጋይ ካህናት፤ የየሰንበት ት/ቤቶች እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፤ የኢፊድሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአጠቃላይ በመቶ ሺሕ የሚቈጠር ሕዝብ በሥርዓቱ ታድሟል፡፡

በዕለቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡

በቃለ ምዕዳናቸውም የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ጥሪያቸውን አክብረው ወደኢትዮጵያ በመምጣት በዓሉን በጋራ በማክበራቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ ‹‹የመስቀል በዓል በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት የሚከበረው መስቀሉ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን የፈጸመበት በመኾኑ ነው›› በማለት በዓሉ የሚከበርበትን ምክንያት አስገንዝበዋል፡፡

አያይዘውም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን እንደሰጠን ዂሉ፣ እኛ ኢትዮጵያውያንም አገራዊ አንድነታችንንና ወንድማማችነታችንን በመጠበቅ በመካከላችን ፍቅርንና ሰላምን ማስፈን፤ ዕድገታችንንም ማስቀጠል እንደሚገባን ቅዱስነታቸው አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ከዚሁ ዂሉ ጋርም በቅርቡ በኦሮምያ እና ሱማሌ የኢትዮጵያ ክልሎች በተነሣው ግጭት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ወገኖች ዕረፍትን፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን፤ ጉዳት ለደረሰባቸውና ሕክምና ላይ ለሚገኙት ደግሞ ፈውስን እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተመኝተዋል፡፡

በዕለቱ መንግሥትን ወክለው መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ደሪባ ኩማ በበኩላቸው ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው ማለት አንዳቸው በአንዳቸው አስተዳደር ጣልቃ አይገቡም ማለት እንጂ ለአገር ሰላም በሚጠቅሙ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ አይመክሩም ማለት እንዳልኾነ አስታውሰዋል፡፡

የመስቀል በዓል አከባበር ሥርዓት በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በቅርስነት መመዝገቡ ለቱሪዝም ዕድገት ከሚኖረው አገራዊ ፋይዳ ባሻገር የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ጸሎተ ቡራኬ ተደርጎ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ እና በዶክተር ሙላቱ ተሾመ የመስቀል ደመራው ከተለኮሰ በኋላ የበዓሉ አከባበር ሥርዓት በሰላም ተፈጽሟል፡፡

የምስል ወድምፅ ዝግጅቱ ተመርቆ በነጻ ተሠራጨ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በተሐድሶ መናፍቃን መሠረታዊ ስሕተት እና ወቅታዊ እንቅስቃሴያቸው ዙሪያ ያዘጋጀው የምስል ወድምፅ ዝግጅት መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም  ተመርቆ ለምእመናን በነጻ ተሠራጨ፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ ማስተባበሪያ በተሰናዳው በዚህ የምስል ወድምፅ ዝግጅት፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ እሸቱ ዓለማየሁ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር እና ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ትምህርታዊ ማብራሪያ በመስጠት፣ ዲያቆን ምትኩ አበራ ደግሞ በማወያየት ተሳትፈውበታል፡፡

በምስል ወድምፅ ዝግጅቱ የተሳተፉ መምህራነ ወንጌል

የአምስት ሰዓታት ጊዜን የሚወስደው ዝግጅቱ፣ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሚጠሩ መናፍቃን ለሚያነሧቸው የማደናገሪያ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ የተሰጠበት ሲኾን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ራሱንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃን ወረራ ለመጠበቅ ይችል ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ለምእመናን በነጻ እንዲሠራጭ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

ዝግጅቱ ለአንድ ዓመት ያህል እንደ ተደከመበት፤ በከፍተኛ ጥራት እንደ ተዘጋጀ እና ብዙ ገንዘብ ወጪ እንደ ተደረገበትም ከማስተባበሪያው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዕለቱ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ፣ የግብጽ እና የሰሜን ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት የበላይ ሓላፊ፤ አባቶች ቀሳውስት እና ወንድሞች ዲያቆናት፤ ሰባክያነ ወንጌል እና ዘማርያን፤ የሰንበት ት/ቤት እና የመንፈሳውያን ማኅበራት አባላት በአጠቃላይ ከሁለት ሺሕ አምስት መቶ በላይ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይም በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቃለ ምዕዳን ተሰጥቷል፡፡ በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ሒደቶችን የሚያስቃኝ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡ በዋና ጸሐፊው አቶ ውብእሸት ኦቶሮ አማካይነት የማኅበረ ቅዱሳን መልእክት ተላልፏል፡፡ በዋናው ማእከል መዘምራን በአማርኛ ቋንቋ፤ ከሰንዳፋ በመጡ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ደግሞ በአፋን ኦሮሞ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በዕለቱ በሰጡት ቃለ ምዕዳን ሕዝበ ክርስቲያኑን ለመንፈሳዊ ጉባኤ ላሰባሰበ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ካቀረቡ በኋላ በአዲስ ዓመት አዲስ ሐሳብ በማቅረብ የተሐድሶ ኑፋቄን ትምህርት ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ለምእመናን ያሠራጨውን ማኅበረ ቅዱሳንን፣ በዝግጅቱ የተሳተፉ አባላትን እንደዚሁም በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ ምእመናንን አመስግነዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ፈተናዎችን እንዳሳለፈች ያወሱት ብፁዕነታቸው ምእመናን ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን አጽንቶ የመጠበቅ ድርሻ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ሃይማኖትን መጠበቅም ለአገር ሰላምና ጸጥታ፣ ለሕዝብ አንድነትና ፍቅር ዘብ መቆም ማለት መኾኑን አስረድተዋል፡፡

ራሱን ያዘጋጀ ወታደር ጠላቱን በቀላሉ ድል ለማድረግ እንደሚቻለው የጠቀሱት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ‹‹ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና ቃለ እግዚአብሔርን በመማር ለመናፍቃን ምላሽ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ኹኑ›› በማለት ለምእመናን አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ባቀረቡት የፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ሒደቶችን የሚያስቃኝ አጠር ያለ የዳሰሳ ጥናት፣ በተለይ ከ፲፱፻፺ ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ እንቅስቃሴያቸውን በሦስት ክፍለ ጊዜ በመመደብ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሚጠሩ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱትን ጫና ማስረጃዎችን በመጥቀስ አሳይተዋል፡፡

እንደ ዲያቆን ያረጋል ማብራሪያ በ፲፱፻፺ ዓ.ም አራት የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ መነኮሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው መለየታቸው ለፀረ ተሐድሶው ተግባር ምቹ አጋጣሚ ቢኖረውም በአንጻሩ ግን ኦርቶዶክሳውያኑ ተሐድሶ መናፍቃን የሉም ብለን እንድንዘናጋ፤ መናፍቃኑ ደግሞ ውግዘትን በመፍራት የኑፋቄ ትምህርታቸውን በስውር እንዲያስፋፉ ምክንያት ኾኗል፡፡ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቀሰሴም በየጊዜው እየዘመነ በመምጣቱ አሁን ፈታኝ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

አያይዘውም ችግሮች ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት የመካላከል ባህላችን ዝቅተኛ መኾን፣ የተሐድሶ ኑፋቄን ጉዳይ ከግለሰቦች ቅራኔ እንደ መነጨ አድርጎ መውሰድና ጉዳዩን በሽምግልና ለመፍታት መሞከር፣ የገንዘብ ዓቅም ማነስ፣ በሚታይ ጊዜያዊ ውጤት መርካት፣ የሰው ኃይል እጥረት፣ መሰላቸትና መዘናጋት ሐዋርያዊ ተልእኮው በሥርዓት እንዳይዳረስና የመናፍቃን ትምህርት በቀላሉ እንዲዛመት የሚያደርጉ ውስንነቶች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ መናፍቃኑ በሚያነሧቸው ጥያቄዎች አእምሮው እንዲጠመድና መምህራነ ቤተ ክርስቲያንም ለመናፍቃን ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ጊዜያቸውን እንዲያጠፉ መደረጋቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮው መቀዛቀዝ ምክንያት መኾኑን አመላክተው ምእመናን ከተሐድሶ ኑፋቄ ትምህርት ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያንን ተግተው መጠበቅ እንዳለባቸው ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ አሳስበዋል፡፡

‹‹ምን እናድርግ?›› በሚለው የዳሰሳ ጥናታቸው ማጠቃለያም የተሐድሶ እንቅስቃሴን ለመከላከል በዐቢይነት የትምህርተ ሃይማኖት ዕውቀትን ማሳደግ እንደሚገባ፤ ለዚህም የሥልጠና መርሐ ግብሮችን፣ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶችን እና የቪሲዲ ዝግጅቶችን መጠቀም ምቹ መንገድ እንደሚጠርግ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ጠቁመዋል፡፡

በመናፍቃን ተታለው የተወሰዱ ምእመናንን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ እና በሚሊዮን የሚቈጠሩ ወገኖችን በማስተማር የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ማድረግ ማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ ነድፎ ከሚያከናውናቸው ዐበይት ተግባራቱ መካከል መኾናቸውን የጠቀሱት ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ውብእሸት ኦቶሮ ናቸው፡፡

የምስል ወድምፅ ዝግጅቱን ለምእመናን በነጻ ለማዳረስ መወሰኑ ማኅበረ ቅዱሳን ሕዝበ ክርስቲያኑ በሃይማኖቱ ጸንቶ እንዲኖር ለማበረታታት እና የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲፋጠን ለማድረግ የሚተጋ ማኅበር ለመኾኑ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል – ዋና ጸሐፊው፡፡ ከዚህ የበለጠ ብዙ ሥራ ከማኅበሩና ከምእመናን እንደሚጠበቅም አስታውሰዋል፡፡

በሁለት ቋንቋዎች ብቻ የሚግባቡና በቍጥር ከዐሥር ሚሊዮን የማይበልጡ ምእመናን የሚገኙባት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከስምንት በላይ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዳሏት ያወሱት አቶ ውብእሸት፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎችን የሚጠቀሙና ወደ አምሳ ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን ባለቤት ለኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ ብቻ በቂ አለመኾኑን ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም ይህን ጉዳይ የተገነዘበው ማኅበረ ቅዱሳን፣ የአየር ሰዓት በመከራየት በአሌፍ የቴሌቭዥን ጣቢያ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ በማስታወስ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን መርሐ ግብሩን አጠናክሮ ለመቀጠል ያመች ዘንድ በገንዘብም፣ በቁሳቁስም፣ በሐሳብም ምእመናን ድጋፍ እንዲያደርጉ ዋና ጸሐፊው ጠይቀል፡፡

ከዚሁ ዂሉ ጋርም ማኅበረ ቅዱሳን ሰባክያነ ወንጌልን በማሠልጠን፣ አዳዲስ አማንያንን በማስጠመቅ፣ በጠረፋማ አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነጽ እና በመሳሉት ዘርፎች ፕሮጀክት ቀርፆ ለስብከተ ወንጌል መዳረስ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በሚችሉት መንገድ ዂሉ በመደገፍ እና ከማኅበሩ ጎን በመቆም ምእመናን የሚጠበቅባቸውን ክርስቲያናዊ ድርሻ እንዲወጡ አቶ ውብእሸት ኦቶሮ በማኅበረ ቅዱሳን ስም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በመልእክታቸው ማጠቃለያም ትምህርተ ወንጌልን በማዳረስ፤ የግንዛቤ ማዳበሪያ መርሐ ግብራትን በማዘጋጀትና ሥልጠና በመስጠት፤ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎትና ለሥልጠና መስጫ የሚውል ገንዘብ በመለገስ፤ የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችን በማጋለጥ በአጠቃላይ በልዩ ልዩ መንገድ ሱታፌ በማድረግ ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ እንዲስፋፋ፣ የተሐድሶ ኑፋቄ ትምህርት ደግሞ እንዲዳከም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰባክያነ ወንጌል እና በጎ አድራጊ ምእመናን በተጨማሪም ማኅበሩ ያስተላለፈውን ጥሪ ተቀብለው በድምፅ ወምስል ዝግጅቱ ምረቃ ላይ ለተገኙ ወገኖች ዅሉ ዋና ጸሐፊው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም መንፈሳዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም የምስል ወድምፅ ዝግጅቱ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቡራኬ ተመርቆ በቍጥር አንድ ሺሕ በሚኾኑ በባለ ፲፮ ጊጋ ባይት ፍላሽ ዲስኮች ለምእመናን የታደለ ሲኾን፣ በዕለቱ ያልተገኙ ምእመናን ከማኅበሩ ሕንጻ ድረስ በአካል በመምጣት ዝግጅቱን በፍላሽ እንዲወስዱ፤ በጎ አድራጊ ምእመናን ፍላሽ ዲስኮችን ገዝተው በማበርከት ለትምህርቱ መዳረስ ትብብር እንዲያደርጉ፤ ዝግጅቱ የደረሳቸው ወገኖችም እያባዙ ቤተ ክርስቲያንን ለሚወዱም ኾነ ለማይወዱ ወገኖች እንዲያዳርሱ፤ ዝግጅቱ ያልደረሳቸው ደግሞ ትምህርቱ በማኅበሩ ቴሌቭዥን ሲተላለፍ፣ በዩቲዩብ ሲለቀቅና በሲዲ ሲሠራጭ እንዲከታተሉ በማስተባበሪያው በኩል ማሳሰቢያ ከተሰጠ በኋላ በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳን እና ጸሎተ ቡራኬ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

ከምረቃ መርሐ ግብሩ በኋላ ስለ ዝግጅቱ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው ምእመናን፣ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ፈተና የኾነውን የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ለመከላከል ይቻል ዘንድ ብዙ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ያዘጋጀውን የምስል ወድምፅ ዝግጅት ለምእመናን በነጻ ማዳረሱ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለመደገፍ የሚተጋ የቍርጥ ቀን ልጅ መኾኑን እንደሚያስረዳ መስክረዋል፡፡ ከማኅበሩ ጋር በመኾን የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በሚቻላቸው ዓቅም ዅሉ የማኅበሩን አገልግሎት ለመደገፍም ቃል ገብተዋል፡፡

ከዚህ በተለየ ደግሞ የማኅበሩ አዳራሽ እና በምድር ቤቱ ወለል ላይ የተዘጋጁ ድንኳኖች ሞልተው በርካታ ምእመናን ቆመው መርሐ ግብሩን መከታተላቸውን፤ ከፊሉም መግቢያ አጥተው በመርሐ ግብሩ ለመሳተፍ አለመቻላቸውን ያስተዋሉ አንዳንድ በጎ አድራጊ ምእመናን በመንፈሳዊ ቍጭት ተነሣሥው ‹‹ብዙ ሕዝብ ማስተናገድ የሚችል ሰፊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ መገንባት አለብን›› እየተባባሉ ሲነጋገሩ ተሰምቷል፡፡

ዘመነ ክረምት – የመጨረሻ ክፍል

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በክፍል ስምንት ዝግጅታችን ስድስተኛውን የክረምት ንዑስ ክፍል (ዘመነ ፍሬን) በሚመለከት ወቅታዊ ትምህርት ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዛሬው የመጨረሻ ክፍል ዝግጅታችን ደግሞ ሰባተኛውን ክፍለ ክረምት (ፀአተ ክረምትን ወይም ዘመነ መስቀልን) የሚመለከት ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን እንድትከታተሉ መንፈሳዊ ግብዣችንን አስቀድመናል፡፡ መልካም የንባብ ጊዜ ይኹንላችሁ!

፯. ፀአተ ክረምት (ዘመነ መስቀል)

ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ሰባተኛው የክረምት ክፍለ ጊዜ ፀአተ ክረምት ወይም ዘመነ መስቀል በመባል የሚታወቅ ሲኾን ይኸውም የክረምት መውጣት እና በአተ መጸው (የመጸው መግባት) የሚሰበክበት ወቅት ነው፡፡ የፀአተ ክረምት መጨረሻ የሚኾነውም መስከረም ፳፭ ቀን ነው፡፡ ‹ፀአተ ክረምት› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረት ‹የክረምት መውጣት› የሚል ትርጕም አለው፡፡ የክረምት መውጣት ሲባል ለዘመነ ክረምት የተሰጠው ጊዜ በዘመነ መጸው መተካቱን ለማመልከት እንጂ ክረምት ተመልሶ አይመጣም ለማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት እስከሚያበቃበት እስከ ኅልፈተ ዓለም ድረስ የወቅቶች መፈራረቅም አብሮ ይቀጥላልና፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህንን የወቅቶች መፈራረቅ ለመግለጽ ነው ‹‹መግባት፣ መውጣት›› እያሉ በክፍል በክፍል የሚያስቀምጧቸው፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹እስመ ናሁ ክረምት ኀለፈ ወዝናም ገብአ ድኅሬሁ ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ ጊዜ ገሚድ በጽሐ ቃለ ማዕነቅ ተሰምዐ በምድርነ በለስ አውጽአ ሠርጸ አውያን ጸገዩ ወወሀቡ መዓዛ፤ እነሆ ክረምት ዐለፈ፤ ዝናቡም ዐልፎ ሔደ፡፡ አበባ በምድር ላይ ታየ፤ የመከርም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ፤ ወይኖችም አበቡ፤ መዓዛቸውንም ሰጡ፤›› (መኃ. ፪፥፲፩-፲፫) በማለት እንደ ተናገረው አሁን የክረምቱ ጊዜ አብቅቶ ሌላ ወቅት ዘመነ መጸው ተተክቷል፡፡ መጭው ዘመን የተስፋ፣ የንስሐና የጽድቅ ወቅት እንዲኾንልን እግዚአብሔርን ከፊት ለፊታችን ማስቀደም ይኖርብናል፡፡ እርሱ ከቀደመ መሰናክሎቹን ለማለፍ፣ ፈተናዎችንም ለመወጣት ምቹ ኹኔታዎችን እናገኛለንና፡፡ ክረምቱ አልፎ መጸው ሲተካ ምድር ባገኘችው ዝናም አማካይነት የበቀሉ ዕፀዋት በአበባና በፍሬ ይደምቃሉ፡፡ ምእመናንም በተማርነው ቃለ እግዚአብሔር ለውጥ በማምጣት እንደ ዕፀዋት በመንፈሳዊ ሕይወታችን አፍርተን ክርስቲያናዊ ፍሬ ማስገኘት ይኖርብናል፡፡ በዚህ ፍሬያችን ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እንችላለንና፡፡

አንድ ክፍለ ጊዜ (ወቅት) ሲያልፍ ሌላ ክፍለ ጊዜ ይተካል፡፡ ‹‹ሲሞት ሲተካ፣ ሲፈጭ ሲቦካ›› እንደሚባለው የሰው ልጅ ሕይወትም እንደዚሁ ነው፡፡ አንደኛው ሲሞት ሌላኛው ይወለዳል፤ አንደኛው ሲወለድ ሌላኛው ይሞታል፡፡ ወቅቶችም የጊዜ ዑደት መንገዶች እንደ መኾናቸው ለሰው ልጅ ምቾት እንጂ ለራሳቸው ጥቅም የተዘጋጁ ሕያዋን ፍጥረታት አይደሉም፡፡ በመኾኑም ራሳቸውን እየደጋገሙ ይመላለሳሉ፤ የሰው ልጅ ግን አምሳሉን ይተካል እንጂ ራሱ ዳግመኛ ተመልሶ አይመጣም፡፡ እንግዲህ ክርስቶስ ለፍርድ ሲመጣ እንዳናፍር ዳግም በማናገኛት በዚህች ምድራዊ ሕይወታችን የማያልፍ ክርስቲያናዊ ምግባር ሠርተን ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡ ከሞት በኋላ ዘለዓለማዊ ፍርድ እንጂ ንስሐ የለምና፡፡

መንፈሳዊ ዓላማችን ይሳካልን ዘንድም እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው፡፡ እንደዚህ እያልን፤ ‹‹ድኅረ ኀለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም፤ ዘአርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም፤ አፈወ ሃይማኖት ነዓልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም፤ አትግሀነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም፤ ለጽብስት ንህብ ወነአስ ቃህም፡፡›› ትርጕሙም፡- ‹‹ክረምት ካለፈ፣ ዝናምም ወደ ቦታው ከተመለሰ በኋላ የዱር አበቦችን ያሳየህ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ! የሃይማኖት ሽቱን እናስገኝና የሚጣፍጥ የምግባር ፍሬን እናፈራ ዘንድ ተወዳጅ እንደ ኾነው የታታሪዋ ንብና የብልሃተኛዋ ገብረ ጕንዳን ትጋት እኛንም ለምስጋናህ አትጋን›› ማለት ነው (መጽሐፈ ስንክሳር፣ የመስከረም ፳፭ ቀን አርኬ)፡፡

በተጨማሪም በዚህ ወቅት (ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ቀን ድረስ ባለው ክፍለ ክረምት) ነገረ መስቀሉን የሚመለከት ትምህርት በቤተ ክርስቲያናችን በሰፊው ይነገራል፡፡ ማለትም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል በፈቃዱ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስለ መሞቱ፣ በሞቱም ዓለምን ስለ ማዳኑ፣ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰሰበት ዕፀ መስቅሉ የተቀደሰ ስለ መኾኑ ከሌሎች ጊዜያት በላይ በስፋት የሚነገረውና ትምህርት የሚሰጠው በዚህ ወቅት ነው፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም በአይሁድ ቅናት በጎልጎታ ለ፫፻ ዓመታት ያህል ተቀብሮ የቆየው የጌታችን ዕፀ መስቀልን ለማውጣት በንግሥት ዕሌኒ አማካይነት ቍፋሮ መጀመሩ፣ መስቀሉ ከወጣ በኋላም በዐፄ ዳዊትና በልጃቸው በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጥረት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ደብረ ከርቤ መቀመጡ የሚዘከረው በእነዚህ ዐሥር የፀአተ ክረምት ዕለታት ውስጥ ነው፡፡ እኛ ምእመናን ይህንን የመስቀሉን ነገር በልቡናችን ይዘን በክርስትናችን ምክንያት የሚገጥመንን ልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና በትዕግሥት ማሳለፍ ይጠበቅብናል፡፡

ማጠቃለያ

ትምህርታችንን ለማጠቃለል ያህል ዘመነ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት፤ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን (ምግብን) ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይ እና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት የውኃ ባሕርይ ይሠለጥናል፤ ውኃ አፈርን ያጥባል፤ እሳትን ያጠፋል፡፡ ኾኖም ግን ውኃ በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህን ምሥጢር ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተው ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፡፡ በክረምት ወቅት ገበሬው ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን ወቅት የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

ዘመነ ክረምት ዕፀዋቱ በስብሰው ከበቀሉ፣ ካበቡና ካፈሩ በኋላ የሚጠቅሙት በሪቅ፣ በጎተራ እንደሚሰበሰቡ፤ እንክርዳዶቹ ደግሞ በእሳት እንደሚቃጠሉ ዅሉ እኛም ተወልደን፣ አድገን፣ ዘራችንን ተክተን እንደምንኖር፤ ዕድሜያችን ሲያበቃም እንደምንሞት፤ ሞተንም እንደምንነሣና መልካም ሥራ ከሠራን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደምንገባ፤ በኀጢአት ከኖርን ደግሞ በገሃነመ እሳት እንደምንጣል የምንማርበት ወቅት ነው፡፡ በመኾኑም ሰይጣን በሚያዘንበው የኀጢአት ማዕበል እንዳንወሰድና በኋላም በጥልቁ የእሳት ባሕር እንዳንጣል ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁልንን የቃለ እግዚአብሔር ዘር በእርሻ ልቡናችን በመዝራት (በመጻፍ) እንደየዓቅማችን አብበን፣ ያማረ ፍሬ አፍርተን መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ይህንን እንድናደርግም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና የቅዱሳኑ ዅሉ ተራዳኢነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ተአምረ ማርያም በጼዴንያ

በዝግጅት ክፍሉ

መስከረም ፲ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን ከሚዘከሩ በዓላት መካከል የእመቤታችን በዓል አንደኛው ሲኾን ይኸውም ጼዴንያ በምትባል አገር ከሥዕሏ ተአምር የተደረገበት ዕለት ነው፡፡ በተአምረ ማርያም እና በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበው ቅዱስ ሉቃስ ከሣላት ሥጋ የለበሰች ከምትመስል የእመቤታችን የሥዕል ሠሌዳ ቅባት ይንጠፈጠፍ ነበር፡፡ ከዚህች የእመቤታችን ሥዕል የተገለጠው ተአምርና ታሪክም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የምትወድና በሚቻላትም ዂሉ የምታገለግላት፣ ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች አንዲት ማርታ የምትባል ሴት ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አባ ቴዎድሮስ የሚባሉ መነኵሴ ከእርሷ ዘንድ በእንግድነት አድረው በማግሥቱ ከቤቷ ሲወጡ ማርታ የሚሔዱበትን አገር በጠየቀቻቸው ጊዜ  እርሳቸውም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው ቅዱሳት መካናትን እንደሚሳለሙ ነገሯት፡፡ ማርታም ከእርሷ ገንዘብ ወስደው የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተው ይዘውላት እንዲመጡ ለመነቻቸው፡፡ መነኵሴውም በራሳቸው ገንዘብ ሥዕሉን ገዝተው እንደሚያመጡላት ቃል ገቡላት፡፡ አባ ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌም ደርሰው ቅዱሳት መካናትን ከተሳለሙ በኋላ ሥዕሏን ሳይገዙ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ ያን ጊዜም ‹‹ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ?›› የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰምተው ወደ ገበያ ተመልሰው መልኳ ያማረና የተወደደ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል ገዝተው በሐርና በንጹሕ ልብስ ጠቅልለው ይዘው እየተጓዙ ሳሉ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ደረሱ፡፡ በዚያም ወንበዴዎች ተነሡባቸውና ከእነርሱ ሊሸሹ ሲሉ ‹‹መንገድህን ሒድ›› የሚል ቃል ከሥዕሏ ወጣ፤ መነኵሴውም መንገዳቸውን በሰላም ተጓዙ፡፡ ሁለተኛም አንበሳ ሊበላቸው በተነሣባቸው ጊዜ ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረላቸው፡፡

አባ ቴዎድሮስ ይህን ዂሉ ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜም ያቺን ሥዕል ለማርታ ከመስጠት ይልቅ ወደ አገራቸው ሊወስዷት ወደዱ፡፡ በመርከብ ተሳፍረው በሌላ አቅጣጫ ሲሔዱም ታላቅ ነፋስ ተነሥቶ ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያ ወሰዳቸው፡፡ ከመርከብም ወርደው ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ደረሱ፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን ለማርታ አልገለጡላትም፤ እርሷም አላወቀቻቸውም ነበር፡፡ በማግሥቱም ተሠውረው ወደ አገራቸው ሊሔዱ ሲሉ የቅፅሩ ደጃፍ ጠፍቶባቸው ሲፈልጉ ዋሉ፡፡ በመሸባቸው ጊዜም ወደ ማደሪያቸው ተመለሱ፡፡ ማታ ማታ በሩን ያዩታል፤ ነግቶ መሔድን ሲሹ ግን የበሩ መንገድ ይሠወርባቸዋል፡፡ እንዲህም ኾነው እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቆዩ፡፡ ማርታም ‹‹አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን? ስትቅበዘበዝ አይሃለሁና ምን ኾነህ ነው?›› ሰትል ጠየቀቻችው፡፡ እርሳቸውም ከእመቤታችን ሥዕል የተደረገውን ተአምር እና ሥዕሏን ይዘው ለመጥፋት ያደረጉትን ጥረት ዂሉ ነግረው፣ ራሳቸውን ገልጠው ሥዕሏን ሰጧት፡፡ እርሷም የእመቤታችንን ሥዕል ተቀብላ የተጠቀለለችበትን ልብስ በፈታችው ጊዜ ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋ ብዛት የተነሣም የአባ ቴዎድሮስን እጃቸውንና እግራቸውን ሳመች፡፡

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር አኖረቻት፡፡ ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት፡፡ በቀንና በሌሊትም የሚያበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች፤ ከመቅረዞች ውጭም የሐር መጋረጃን ጋረደች፡፡ ከሥዕሊቱ በታችም እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች፡፡ እኒያ መነኰስም እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገሉ ኖሩ፡፡ የአገሩ ሊቀ ጳጳስም የእመቤታችን ሥዕል ሥጋ የለበሰች ኹና ባገኙና ተአምሯንም በተመለከቱ ጊዜ ከዚህ አምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ፡፡ ከሥዕሏ ከሚንጠባጠበው ቅባት ቀድተው ለበረከት ሲካፈሉም ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ መላ፡፡ ሥዕሊቱን ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜም ንውጽውጽታ ኾኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ፡፡ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያች አገር (በጼዴንያ) ትገኛለች፡፡

‹‹እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፷፯፥፴፭) እግዚአብሔር አምላካችን በልዩ ልዩ መንገድ ለሰው ልጅ ተአምራቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ከዓለት ላይ ውኃ እያፈለቀ ሕዝቡን ያጠጣል፡፡ እንደዚሁም ቅዱሳን ሐዋርያት በቃላቸውም፣ በልብሳቸውም፣ በጥላቸውም ሙታንን በማስነሣት፤ ሕሙማንን በመፈወስ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው፤ ቅዱስ ጳውሎስም በልብሱ ቅዳጅ ያደርጓቸው የነበሩ ተአምራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከግዑዝ ዓለት ውስጥ ውኃ የሚያፈልቅ አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፤ ከነፍሷ ነፍስ ተዋሕዶ ካከበራት ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዝ እንዲፈስ ቢያደርግ ምን ይሳነዋል? ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጣቸው ጸጋ በልብሳቸውና በሰውነታቸው ጥላ ተአምራትን ማድረግ እንደ ተቻላቸው ዂሉ አምላክን በማኅፀኗ የተሸከመችው ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያምም በሥዕሏ ወዝ ብዙ ሕሙማንን መፈወስ ይቻላታል፡፡ ከቅዱሳን ልብስና ጥላ የእርሷ ሥዕል ይከብራልና፡፡ ስለዚህም ነው በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት የሚከበረው፡፡

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፤ የልጇ፣ የወዳጇ የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡