በዲያቆን አባተ አሰፋ
መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛው ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ‹ገብር ኄር› የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ትርጕሙም ‹በጎ አገልጋይ› ማለት ሲኾን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ነው (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴)፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የኾነው ይህ የወንጌል ክፍል በርካታ መልእክትታን በውስጡ ይዟል፡፡ በቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ሓላፊነት ላይ የሚገኙ ሰዎች ትኩረት ሰጡባቸው የሚገቡ ነጥቦችን ይጠቁማል፡፡ ይህን ለመረዳት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመርያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና ነጥቦችን መመርመር ጠቃሚ ነው፤
በዚህ ምሳሌያዊው ታሪክ አንድ ጌታ አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደ ሰጣቸው ተጠቅሷል፡፡ ከታሪኩ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ እንዲያተርፉበት ገንዘቡን ለአገልጋዮቹ ሰጥቷቸዋል፡፡ ሰውዬው ማትረፍ በመፈለጉ ብቻም ገንዘቡን ያለ አግባብ አልበተነም፡፡ ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ እንደየችሎታቸው መጠን እንዲሠሩበት አከፋፈላቸው እንጂ፡፡
ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደ ኾነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ሓላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት ይችላል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ሓላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት፣ ሁለት፣ አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡ የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለን ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የባለ መክሊቱን ቅንነት እናስተውላለን፡፡
ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ አትርፉበት ብሎ መክሊቱን ሰጥቷቸው በሔደበት አገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደ ሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ተመልሷል፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደ ሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የኾነ መክሊትን በመስጠት እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናስተውለው ከአእምሯቸው በላይ ሳይኾን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደ ሰጣቸው ነው፡፡
ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት፣ እንደዚሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፈው ከጌታቸው ፊት እንደ ቆሙ፤ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታ ቦታ እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው አገልጋይ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት ምድርን ቆፍሮ እንደ ቀበረ፤ ከዚህም አልፎ ‹‹ምን አደረግህባት?›› ተብሎ ሲጠየቅ የዐመፅ ንግግር እንደ ተናገረ፤ በዚህ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው እንረዳለን፡፡ በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችን፣ ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጠል እንመልከታቸው፤
የአገልጋዮቹ ጌታ
ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመኾኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን አለው፡፡ ባለ መታዘዙ ምክንያት በክፉው አገልጋይ ላይ የፈረደበትን ፍርድ (ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት፣ በውጪ ወዳለ ጨለማ አውጡት የሚለው) የጌታው ሙሉ ሥልጣን ያሳያል፡፡ ይህ ጌታ ፍርዱ በእውነት ላይ የተመረኮዘ መኾኑንም በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት ሁለቱ አገልጋዮቹ ከሰጣቸውን ክብር መረዳት ይቻላል፡፡
በጎ እና ታማኝ አገልጋዮች
በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እነዚህ አገልጋዮች በጎ ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ቍጥር ያለው መክሊት በመቀበላቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ብዛት ሳይኾን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡
ክፉና ሰነፍ አገልጋይ
አንድ መክሊት የተቀበለውን አገልጋይ ከሁለቱ አገልጋዮች ያሳነሰውም ከአንድ በላይ መክሊት አለመቀበሉ ሳይኾን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ አገልጋይ ሦስት መሠረታዊ ስሕተት ፈጽሟል፤
የጌታውን ትእዛዝ በቸልተኝነት መመልከቱ የመጀመርያው ስሕተቱ ነው፡፡ ጌታው ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ እንደ አቅማቸው መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትእዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡
ሁለተኛው ስሕተቱ ጌታው መክሊቱን በተቆጣጠረው ጊዜ የዐመፅ ቃል መናገሩ ነው፡፡ ጌታው ከሔደበት ቦታ ተመልሶ በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ይህን አገልጋይ ሲጠይቀው፡- «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ኾንህ አውቃለሁ፡፡ ስለ ፈራሁም ሔድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤» ሲል ነበር የመለሰለት፡፡ ይህ ምላሽ ከዐመፃ ባሻገር የሐሰት ቃልም አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድ ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢኾን ኖሮ ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደ ነበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ ይገባዋል፤ በትኗልና መሰብሰብም መብቱ ነው፡፡
ሦስተኛው ስሕተቱ ደግሞ ዕድሉን ለሌሎች አለመስጠቱ ሲኾን፣ ይህ አገልጋይ በተሰጠው መክሊት ነግዶ ማትረፍ ቢሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች መስጠት ሲገባው መክሊቱን ቆፍሮ ቀብሮታል፡፡ ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና ሲቀበል ከጌታው የተቀበለው ትእዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ እርሱ መውጣት መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ በውስጡ የተቀረፀው የዐመፅ መንፈስ ለመኾኑ ለጌታው የሰጠው ረብ የሌለው ምላሽ ማስረጃችን ነው፡፡
የአገልጋዮቹ ጌታ የእግዚአብሔር ምሳሌ እንደ ኾነ፤ ሦስቱ አገልጋዮች ደግሞ በተለያየ ደረጃ ያሉ ምእመናንን እንደሚወክሉ የቤተ ክርስቲያን መተርጕማን ያስተምራሉ፡፡ ከተጠቀሰው ታሪክ ከምንማራቸው ቁም ነገሮች መካከልም ሁለቱን እንመልከታለን፤
ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ጸጋ እንዳለ እንረዳበታለን
እግዚአብሔር አምላካችን እያንዳንዳችን በሃይማኖታችን ፍሬ እንድናፈራ ይፈልጋል፡፡ ፍሬ ማፍራት የምንችልበትን ኃይልና ጸጋ ደግሞ እርሱ ይሰጠናል፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበልናቸው ስጦታዎች በቍጥር እጅግ ብዙ ቢኾኑም በዓይነታቸው ግን በሁለት መክፈል እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ዳግመኛ በመወለድ ምሥጢር ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋና ከልጅነት ጋር በተያያዘ የሚሰጠን ስጦታ ነው (ዮሐ.፫፥፫)፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደየአቅማችን ለመንፈሳዊ አገልግሎታችን ማስፈጸሚያ ይኾነን ዘንድ የሚሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ለምሳሌ ትንቢት መናገር፣ በልዩ ልዩ ልሳናት መናገር፣ አጋንንትን ማስወጣት፣ ወዘተ. የመሳሰሉት ጸጋዎች (ስጦታዎች) ከዚህኛው ዓይነት ስጦታ የሚመደቡ ናቸው (፩ኛቆሮ.፲፪፥፬)፡፡
በመጀመሪያውም ይኹን በሁለተኛው ዓይነት ስጦታ በእኛ በተቀባዮች ዘንድ ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ ዳግመኛ በመወለድ ምሥጢር (በጥምቀት የሥላሴን ልጅ መኾን) ስላገኘው የልጅነት ጸጋ የሚያስብና በዚህም የሚደሰት ክርስቲያን ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ለዓመት በዓላት (ለመስቀል ደመራ፣ ለጥምቀት፣ ለፋሲካ፣ ወዘተ) ካልኾነ በስተቀር ክርስትናችን ትዝ የማይለን ክርስቲያኖች ጥቂቶች አይደለንም፡፡ እንደዚሁም ዘመዶቻችን ወይም ራሳችን ከዚህ ዓለም በሞት ስንለይ ካልኾነ በስተቀር በሕይወት ዘመናችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ የማንደርስ ብዙዎች ነን፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ የልጅነትን ጸጋ በመስጠቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም ልጆች የተባልነው፡፡
እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውኃ የፈሰሰውም በጦር ከተወጋው ከጌታች ጎን ነው (ዮሐ.፲፱፥፳፬)፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይኼንን ዅሉ ምሥጢር ሲያመለክት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፤›› በማለት ያደንቃል (፩ኛ ዮሐ.፫፥፩)፡፡ እኛ ልጆቹ እንኾን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅሩ ባሻገር ልጆቹ በመኾናችን መንግሥቱን እንድንወርስ መፍቀዱም ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከኾናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፤›› በማለት የሚነግረንም ይህንኑ ተስፋ ነው (ገላ.፬፥፯)፡፡
ትልቁ ችግር ተጠማቂው ሰው ይህን የልጅነት ክብር አለመረዳቱ ነው፡፡ የልጅነቴን ክብር ተረድቻለሁ እያለ የሚያወራውም ቢኾን የልጅነቱን መክሊት በልቡናው ውስጥ ቀብሮ አንድም ፍሬ ሳያፈራ ስለ ማንነቱ ለማውራት ቃላት ሲመርጥ ጊዜውን ያባክናል፡፡ አብዛኞቻችን ክርስቲያን የክርስትና እምነት ደጋፊዎች እንጂ ተከታዮች አይደለንም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነት ሊገለጥ የሚገባው ግን በምናሳየው የደጋፊነት (የቲፎዞነት) ስሜት አይደለም፡፡ ደጋፊነት የሚያስፈልገው በጊዜ እና በቦታ ለተወሰነ ያውም ኃላፊ ለኾነ ድርጊት ነው፡፡ ክርስትና ግን በማንኛውም ቦታና ጊዜ ልንኖርበት የሚገባ ዘለዓለማዊ የሕይወት መስመር ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መኾኑን በሚገባ መረዳት ያስፈልገናል፡፡ በዚህ መክሊታችንም የታዘዝናቸውን ምግባራት ፈጽመን የሚጠበቅብንን ፍሬ ማፍራት አለብን፡፡ ካለዚያ መክሊቱን እንደ ቀበረው ሰው መኾናችን ነው፡፡
እያንዳንዱ ስጦታ እንደሚያስጠይቅ እንገነዘብበታለን
እግዚአብሔር ያለ አንድ ዓላማ በሓላፊነት ለሰዎች ስጦታን አልሰጠም፤ አይሰጥምም፡፡ ማንም ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሰው የተሰጠው ስጦታ ለዓላማ ነውና ጥያቄ አለበት፡፡ ጠያቂው ደግሞ የስጦታው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ መንጋውን እንዲጠብቁለት ልዩ ልዩ የአገልግሎት ሰጦታዎችን እግዚአብሔር የሰጣቸው አሉ (ዮሐ. ፳፩፥፲፭፤ ገላ. ፩፥፲፭-፲፮)፡፡ ኾኖም ግን የተሰጣቸው ሓላፊነት የሚያስጨንቃቸው፤ ከልባቸው በትሕትና የሚተጉ ክርስቲያኖች የመኖራቸውን ያህል የሚያገለግሉበትን ስጦታ ከእግዚአብሔር መቀበላቸውን፣ ጸጋቸው የሚያስጠይቃቸው መኾኑን የዘነጉና መንገዳቸውን የሳቱም በርካታ ናቸው፡፡
በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል እንደ ድልድይ ኾነው ያገለግሉበት ዘንድ በተሰጣቸው ሥልጣን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር የሚፈጽሙ አገልጋዮች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑን ወደ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ የነሱ ደጋፊ፣ ስለ ክብራቸው ተሟጋች እንዲኾን፤ እርስበርስ ጎራ እንዲፈጥርና ‹‹የጳውሎስ ነኝ፤ የአጵሎስ ነኝ›› በሚል ከንቱና የማይጠቅም ሐሳብ እንዲከፋፈል የሚያደርጉ ሰባኪዎችም አይታጡም፡፡ በአጠቃላይ ዅላችንም በተሰጠን መክሊት ባለቤቱ ከፊቱ አቁሞ ስለሚጠይቀን ከገብር ኄር ታሪክ በጎ አገልጋይነትን ተምረን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን፣ እንደየአቅማችን መልካም ፍሬን ማፍራት ይጠበቅብናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡