እንደ ገብር ኄር ታማኝ አገልጋዮች እንኹን

በአያሌው ዘኢየሱስ 

መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፱ .

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ ትምህርቱን ቃል በቃል ወይም በሰምና ወርቅ ወይም በምሳሌ አስተምሮአቸዋል፡፡ ሲያስተምርም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የተለያዩ ምሳሌዎችን በማቅረብና ምሥጢሩን በማስረዳት ነበር፡፡ ስለዚህም ቃሉን ለገበሬዎች በዘርና በእንክርዳድ፤ እንደዚሁም በሰናፍጭ ቅንጣት፤ ለእናቶች በእርሾ፤ ለነጋዴዎች በመዝገብና በዕንቍ፤ ለዓሣ አጥማጆች በመረብ፤ ወዘተ. እየሰመሰለ ያስተምራቸው ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በዐሥሩ ቆነጃጅት፤ በሰርግ ቤት፤ በበግና በፍየል፤ ወዘተ. እየመሰለ ስለ መንግሥቱ በስፋት አስተምሯል፡፡ ጌታ ትምህርቱን በምሳሌ ያስተምር የነበረው አስቀድሞ፡- «አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ተምሳሌት እናገራለሁ፤» ተብሎ በነቢዩ ዳዊት እንደ ተነገረ (መዝ.፸፯፥፪)፣ ቃሉን የሚሰሙት ዅሉ ትምህርቱ ሳይገባቸው እየተጠራጠሩ ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱና ምሥጢሩ ግልጽ እንዲኾንላቸው ለማድረግ ነበር፡፡

በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት በቤተ ክርስቲያን የሚቀርበው ንባብ፣ ስብከትና መዝሙር የሚያስረዳን ምሥጢርም ስለ አንድ በጎ እና ታማኝ አገልጋይ በምሳሌ የተነገረውን ትምህርት ነው፡፡ በዚህ የወንጌል ንባብ ውስጥ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ሰዎች እንደ ሥራቸው መጠን እንደሚዳኙ በምሳሌ አስተምሯል፡፡ በዚህ ምሳሌ አንድ ጌታ ለሦስት አገልጋዮቹ ለአንዱ አምስት፤ ለአንዱ ሁለት እና ለሌላው ደግሞ አንድ መክሊት ከሰጣቸው በኋላ ነግዱና አትርፉ በማለት እርሱ ወደ ሌላ አገር መሔዱ ተገልጦአል፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው የመጀመሪያው አገልጋይ በተሰጠው አምስት መክሊት ቆላ ወርዶ፣ ደጋ ወጥቶ ከነገደ በኋላ አምስት ተጨማሪ መክሊቶችን በማትረፍ ዐሥር መክሊት አኖረ፡፡ ሁለተኛውም በተሰጡት አምስት መክሊቶች ከነገደ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አስቀመጠ፡፡ ሦስተኛው ግን እንደ ሁለቱ አገልጋዮች ሳይወጣና ሳይወርድ፣ ሳይደክምና ሳያተርፍ በአቅሙ መጠን በተሰጠው አንድ መክሊት ሥራ ሳይሠራ መክሊቱን በጉድጓድ ቀበረው፡፡

ይህ ዅሉ ከኾነ በኋላ ለእነዚህ ሦስት ባሪያዎች በመጠን የተለያዩ መክሊቶችን ሰጥቶ ወደ ሩቅ አገር ሔዶ የነበረው ጌታቸው ወደ እነርሱ ተመልሶ መጣ፡፡ ከዚያም እያንዳንዳቸውን በየተራ እየጠራ በተሰጧቸው መክሊቶች ምን እንደ ሠሩ ጠየቃቸው፤ ተቆጣጠራቸው፡፡ በዚህ መሠረት አምስት መክሊቶችን የተቀበለው የመጀመሪያው አገልጋይ በጌታው ፊት ቀርቦ በተሰጡት አምስት መክሊቶች አምስት በማትረፍ ዐሥር መክሊቶችን ለጌታው አስረከበ፡፡ ሁለተኛውም እንዲሁ ሌሎች ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አራት መክሊቶች ለጌታው አስረከበ፡፡ በዚህ ጊዜ የእነዚህ ሁለት አገልጋዮች ጌታ በእነርሱ ደስ በመሰኘቱ፡- ‹‹አንተ መልካም፣ በጎ እና ታማኝ ባርያ! በጥቂቱ ታምሃልና በብዙ ስለምሾምህ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› በማለት ሁለቱንም ወደ መንግሥቱ አስገባቸው፡፡

የተሰጠውን አንድ መክሊት ምንም ሥራ ሳይሠራና ሳያተርፍበት ጉድጓድ ውስጥ የቀበረው ሦስተኛው አገልጋይ ግን፡- ‹‹ጌታ ሆይ፣ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መኾንህን ስለማውቅና ስለ ፈራሁ መክሊትህን ጉድጓድ ቆፍሬ በመቅበር አቆይቼልሃለሁና እነሆ ተረከበኝ!›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተቆጥቶ፡- ‹‹አንተ ክፉና ሐኬተኛ ባርያ! በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ሰው መኾኔን ካወቅህ ገንዘቤን ለሚነግዱበት ወይም ለሚለውጡ ሰዎች በመስጠት እንዲያተርፉበት ማድረግና ተመልሼ ስመጣ ከነትርፉ ከእነርሱ መቀበል እችል ነበር፡፡ አንተ ይህን ሳታደርግ ጭራሹኑ በድፍረት እነዚህን በእውነት ላይ ያልተመሠረቱ ክፉ ቃላትን ስለ ተናገርህ ቅጣት ይገባሃል!›› ሲል መለሰለት፡፡ ከዚያም፡– ‹‹ያለውን መክሊት ውሰዱና ዐሥር መክሊት ላተረፈው ጨምሩለት፤ላለው ይሰጠዋል፤ ይበዛለትማል፡፡ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ ስለዚህ የማይጠቅመውን ባሪያ ወደ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ ውጪ አውጡት!›› ብሎ ለወታደሮቹ አሳልፎ ሰጠው፡፡

በዚህ የወንጌል ቃል «ወደ ሌላ አገር የሚሔድ ሰው» ተብሎ የተጠቀሰው ባለጠጋ ቅን ፈራጅ የኾነው የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት አገልጋዮች የሚወክሉት ምእመናንን ወይም እኛን ነው፡፡ መክሊት የተባለው ደግሞ በጎ የሚያሰኘው መልካም ሥራ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሪያዎች ወይም አገልጋዮች ምግባርን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረው በያዙ ጻድቃን ይመሰላሉ፤ መክሊቱን ጉድጓድ በመቆፈር የቀበረው ክፉና ሐኬተኛ አገልጋይ ደግሞ ምግባርና ሃይማኖት የሌላቸው ኃጥአን ምሳሌ ነው፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በመካከላችን ተገኝቶ ወንጌለ መንግሥቱን ከሰበከልን በኋላ ለእያንዳንዳችን አንድ፣ ሁለትና አምስት መክሊቶችን በመስጠት ‹‹ለፍርድ እስከምመጣ ደረስ ነግዳችሁና አትርፋችሁ ጠብቁኝ›› ብሎን በዕርገቱ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ  ሔዷል፡፡ ዅላችንም ከእግዚአብሔር የተለያዩ መክሊቶችን ተቀብለናል፤ እንድንነግድባቸውና እንድናተርፍባቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ ቃሉን ባስተማረበት መልእክቱ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፤ ለአንዱም በዚያው መንፈስ ዕውቀትን መናገር ይሰጠዋል፡፡ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፤ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፤ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፤ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፤ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፤ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል፡፡ ይህን ዅሉ ግን ያ፣ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል፤» (፩ኛ ቆሮ.፲፪፥፰-፲፩)፡፡

እግዚአብሔር ለልጆቹ የሰጣቸው መክሊት ብዙ ነው፤ ለአንዱ የመስበክ፣ ለሌላው የማስተማር፣ ለሌላው የመቀደስ፣ ለሌላው የመዘመርመ ለሌላው የመባረክ፣ ለሌላው የማገልገል፣ ወዘተ. መክሊቶችን ወይም ልዩ ልዩ ጸጋን ሰጥቶአል፡፡ አንድ ሰው የሚሰጠው አንድ መክሊት ብቻ አይደለም፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ መክሊቶች ሊሰጡት ይችላል፡፡ በፍርድ ቀን ዅሉም ሰው የሚፈረድበትም በተሰጠው መክሊት ትርፍ መሠረት ነው፡፡ በተቀበለው መክሊት የሚያተርፍ ሰው በፍርድ ቀን በኢየሱስ ክርስቶስ፡- ‹‹መልካም፤ አንተ በጎ፣ ታማኝም ባርያ! በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙም እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› የሚል ቃል ይሰማል፡፡ መክሊቱን መሬት ቆፍሮ የሚቀብር አገልጋይ ግን በውጪ ባለው ጨለማ ውስጥ ተጥሎ በዚያ በልቅሶና ጥርስ በማፋጨት እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ዅሉም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተለያዩ ስጦታዎችን ወይም መክሊቶችን ተቀብሏል፡፡ ይኹን እንጂ ዅሉም መክሊቱን ቆፍሮ ስለ ቀበረ ለእግዚአብሔር ምንም ሊያተርፍ አልቻለም፡፡ በወንጌል ላይ የተጠቀሰው ክፉና ሐኬተኛ አገልጋይ የተሰጠውን መክሊት ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠራበት ወይም ሳይነግድበት ወይም ሳያተርፍበት በመሬት ውስጥ ቆፍሮ በማስቀመጡና ጌታው ሲመጣ ያለ ትርፍ በማስረከቡ በዚህ ዘመን ከምንገኝ ሰዎች እጅጉን ይሻላል፡፡ ምክንያቱም እኛ መክሊቶቻችንን ጠብቀን በማቆየት ለእግዚአብሔር ማስረከብ እንኳ አልቻልንምና፡፡ ዛሬ መክሊት የተቀበለ ዅሉ መክሊቱን ቀብሯል ወይም ጥሏል ለማለት ያስደፍራል፡፡ አንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ በተሰጠው የመቀደስ መክሊት መቀደስ ሲገባው የሚዘፍን ከኾነ መክሊቱን ጥሏል፡፡

አንድ የመዘመር መክሊት የተሰጠው አገልጋይ ለእግዚአብሔር መዘመር ሲገባው የሚዘፍን ወይም ሰዎችን የሚያማ ወይም የሚሳደብ ከኾነ መክሊቱን ጥሏል፡፡ ትክክለኛውን የወንጌል ትምህርት እንዲያስተምርና ሰዎችን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲያስገባ የማስተማር መክሊት ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለ ሰባኬ ወንጌል የኑፋቄ ትምህርት በማስተማር የዋሃንን ወደ ሲኦል የሚመራ ከኾነ መክሊቱን ጥሎታል ወይም አጥፍቶታል እንጂ አልቀበረውም፡፡ በተሰጠው የመባረክ መክሊት ወይም ሥልጣን ምእመናንን መባረክና ኃጢአታቸውን መናዘዝ ሲገባው ለጥንቆላ ሥራ ተቀምጦ እፈርዳለሁ የሚል ከኾነ መክሊት የተባለ ክህነቱን አቃሎአታል፤ አጥፍቷታል እንጂ አልቀበራትም፡፡ በእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ላይ ወንጌልን መናገር ሲገባው ተራ ወሬ ወይም ፖለቲካ የሚደሰኩር ከኾነ ይህ ሰው መክሊቱን ጥሏል፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ፡፡ ለዚህ ነው በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች መክሊቱን ከቀበረው ሰው ያነስን፤ ክፉዎች እና ሐኬተኞች ነን የምንለው፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በወንጌል እንደ ተነገረለት ለጻድቃን ሊፈርድላቸውና በኃጥአን ሊፈርድባቸው ዳግመኛ ወደ ምድር ይመጣል፡፡ ከፍርዱ በፊት ዅላችንንም በሰጠን መክሊቶች መጠን ይቆጣጠረናል፡፡ ስለዚህም አንድ መክሊት የተሰጠን ሁለትና ከዚያ በላይ፤ ሁለት የተሰጠን ሁለት ወይም ከዚያ በላይ፤ አምስት የተቀበልነውም አምስትና ከዚያም የሚበልጡ መክሊቶችን ማትረፍ ይጠበቅብናል፡፡ ለመኾኑ በተሰጠን መክሊት እኛ ያተረፍነው ምንድር ነው? በዕርቅ ፋንታ ጠብን የምናባብስ ከኾንን በመክሊታችን ሰዎችን አጉድለናል እንጂ ማትረፍ አልቻልንም፡፡ በመመረቅ ፋንታ የምንራገም ከኾንን መክሊታችንን ጥለናል፡፡ በመጸለይ ፋንታ ለመደባደብ የምንጋበዝ ከኾነም የተሰጠንን መክሊት አጥፍተናል፡፡ የገብር ኄርን ሰንበት ዛሬ ስናከብር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ እያንዳንዳችንን፡- ‹‹ታተርፉበት ዘንድ የሰጠኋችሁን መክሊት እስከነትርፉ አስረክቡኝ!› ቢለን ምንድር ነው የምናስረክበው? ለጥያቄው የምንሰጠውስ ምላሽ ምን የሚል ይኾን?

በወንጌል የተጠቀሰው ያ፣ ሰነፍ አገልጋይ መክሊቱን መቅበሩ ሳያንሰው ለጌታው የሰጠው ክፉ መልስ ለከፍተኛ ቅጣት ዳርጎታል፡፡ ለጌታው፡- «ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መኾንህን አውቃለሁ፤» የሚል ምላሽ ነበር የሰጠው፡፡ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ከዚህ ሰው ጋር የሚመሳሰል ጠባይ አላቸው፤ እነርሱ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምንም ነገር ሳያውቁ የእግዚአብሔርን ጠባይና ዕውቀት በእነርሱ የዕውቀት ሚዛን ለመመዘን ይሞክራሉና፡፡ አንድ ክርስቲያን በጠና ሕመም ሲታመም ወይም ከልጆቹ አንዱ በሞት ሲለይበት ወይም ንብረቱ በእሳት ቃጠሎ ሲወድም ይህን አደጋ ያደረሰበት እግዚአብሔር እንደ ኾነ አድርጎ በማሰብ የማይገቡ ቃላትን በእግዚአብሔር ላይ የሚሰነዝሩ ሰዎች አሉ፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች በእግዚአብሔር ህልውና ላይ በመምጣት «እግዚአብሔር ቢኖር ኖሮ ይህ ሕመም ወይም አደጋ በእኔ ላይ አይደርስም ነበር፤» ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ «እግዚአብሔር እንደዚህ የጨከነብኝ ምን አድርጌው ነው እያሉ እግዚአብሔርን እንደ ሐኬተኛው አገልጋይ ጨካኝ አምላክ የሚያደርጉት ሰዎችም አሉ፡፡

የጻድቁ የኢዮብ ሚስት በእግዚአብሔር ላይ በልቧ ስትሰነዝራቸው የነበሩ ቃላትን ይደግማቸው ዘንድ «እግዚአብሔርን ስደበውና ሙት» በማለት በእርሱ ላይ ልታነሣሣው ሞክራ ነበር፡፡ ነገር ግን «የለም» ወይም «ጨካኝ ነው» ብሎ በድፍረት እግዚአብሔርን መናገር ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨለማ የሚያስገባ ክፉ ቃል መኾኑን እናስተውል፡፡ በመሠረቱ ሊነቀፍ ወይም ሊወገዝ ወይም ሊኮነን የሚገባው ሰይጣን እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቸር፣ ርኅሩኅ፣ ታጋሽ፣ ይቅር ባይ፣ መዓቱ የራቀ፤ ምሕረቱ የበዛ አምላክ ነው፡፡ እርሱ በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ያልዘራነውን የጽድቅ ፍሬ እንድንዘራና እንድናጭድ፤ ያልበተንነውንም መልካም ዘር በመበተን በፍርድ ቀን ምርቱን እንድንሰበስብ የሚፈልግ ጌታ ነው፡፡ እኛ ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ በማፍራት የእነዚህ ፍሬዎችን ምርት በመሰብሰብ ሰማያዊ መንግሥቱን እንድንወርስ ይፈልጋል፡፡ እርሱ ለሚያምኑትና ለሚታመኑት ዅሉ ታማኝ ነው፤ የሚያምኑትን የሚክድ ጨካኝ ፈጣሪ አይደለም፡፡ ካልዘራበት የሚያጭድና ካልበተነበት የሚሰበስብ ሰው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፤ ጨካኝ፣ ከሀዲና የማይታመንም ሰው ነው፡፡

ዛሬ እግዚአብሔር በጎ እና ታማኝ አገልጋይ አጥቶአል፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታመን አገልጋይ አጥታለች፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፡- «ዅሉ ዐመፁ፤ በአንድነትም ረከሱ፡፡ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ፤» (መዝ ፲፫፥፫) ተብሎ የተነገረው ለዚህ ዘመን አገልጋዮች ነው፡፡ የሰው ልጅ ለእግዚአብሔርና ለቤተ ክርስቲያን ታማኝ አገልጋይ ሊኾን አልቻለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በቃሉ የሚገኝ ሰው ለማግኘት ተቸግራለች፡፡ በጥቂቱ ታምኖ በብዙ ላይ ሊሾም የሚችል ሰው ስለ ጠፋ ቤተ ክርስቲያን ‹‹የሰው ያለህ!›› እያለች ነው፡፡ ለምእመናን መዳንና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት የሚተጉ አገልጋዮች ቍጥር እየቀነሰ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አገልጋዮችን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሾማቸውና የሚሾማቸው ግን ራሳቸውን፣ ቤተ ክርስቲያንንና መንጋውን ከጥፋት እንዲጠብቁ ነበር (ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡ ሕዝቡን ለመጠበቅ ተሹሞ የሚያጠፋ ጠባቂ ዕድል ፈንታውና ዕጣ ተርታው ትሉ በማያንቀላፋበትና እሳቱ በማይጠፋበት ዘላለማዊ ሲኦል ውስጥ ነው፡፡ ይህን የሚያደርግ አገልጋይ ቅጣቱ ዘላለማዊ መኾኑን ከወዲሁ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡

አምላካችን በዳግም ምጽአቱ እስከሚገለጥ ድረስ መንጋውን በመመገብ፣ ውኃ በማጠጣትና በማሳረፍ ፋንታ ለራሱ ብቻ የሚበላና የሚጠግብ፤ የሚጠጣና የሚሰክር፤ የሚያርፍና የሚዝናና ከኾነ እግዚአብሔር ዕድሉን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ባለበት ጨለማ ውስጥ ያደርግበታል (ማቴ. ፳፬፥፵፭-፶፩)፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በተለያያ መልኩ የሚዘርፍና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን አገልጋይም ኾነ ተገልጋይ ከዚህ ጠባዩ ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡  የቤተ ክርስቲያን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለው ለዚህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በጥፊ የተመታው፤ ርኩስ ምራቅ የተተፋበት፤ የእሾኽ አክሊል የተቀዳጀው፤ በአጠቃላይ የተንገላታውና የሞተው ለዚህች ቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ነው፡፡ ስለ ኾነም ካህናትም ምእመናንም በጎ እና ታማኝ አገልጋዮች ልንኾን ይገባናል፡፡

የአምላካችን የእግዚአብሔር አብ ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይኹን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡