የግቢ ጉባኤያት ተተኪ ሰባኪያነ ወንጌል ተመረቁ

 መስከረም 12 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በአምስት የማኅበረ ቅዱሳን ማስተባበሪያ ማእከላት አስተባባሪነት በስድስት የሥልጠና ቦታዎች ለአንድ ወር ሲሰጣቸው የነበረውን የደረጃ ሁለት ሥልጠና በማጠናቀቅ 357 የግቢ ጉባኤያት ተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ተመረቁ፡፡

በአማርኛ ቋንቋ በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና የካህናት ማሠልጠኛ 70፤ በሐዋሳ ደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን 45፤ በጅማ ፍኖተ ብርሃን የካህናት ማሠልጠኛ 42፤ በማይጨው የካህናት ማሠልጠኛ 34፤ በባሕር ዳር ሰላም አርጊው ቅድስት ማርያም 83 ሠልጣኞች የሠለጠኑ ሲሆን፤ በኦሮምኛ ቋንቋ በአሰላ ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ 83 የግቢ ጉባኤያት ተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ሥልጠና ወስደው ተመርቀዋል፡፡

በሐዋሳ ደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በተሠጠው ሥልጠና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በማይጨው የካህናት ማሠልጠኛ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡባዊ እና ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ሥልጠና በመሥጠት ተሳትፈዋል፡፡ እንዲሁም በቂ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው መምህራን ሥልጠናው መሰጠቱን፤ ሲመረቁም በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተባርከው የምሥክር ወረቀት መቀበላቸውን ከየሀገረ ስብከቱ ማእከላት የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በሐዋሳ ጳጉሜን 2 ቀን 2006 ዓ.ም በደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ አማካይነት ከግቢ ጉባኤያት ለተወጣጡት 45 ተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ ለተመራቂዎቹ የምሥክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት ”ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ እንደ እናንተ አይነት አገልጋዮች ያስፈልጓታል፡፡ የተሰጣችሁ ሓላፊነትም ታላቅ ነው“ ብለዋል፡፡

በቀንና በማታ ሲሰጥ የቆየው የክፍል ውስጥ ሥልጠና ነገረ ሃይማኖት፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፤ ትምህርተ ክርስትና እና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፤ ነገረ ቅዱሳን፤ ሐዋርያዊ ተልእኮ፤ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮችን ከመፍታት አንጻር የሰባክያነ ወንጌል ድርሻና ያሬዳዊ መዝሙር ያካተተ ነበር፡፡ በተጨማሪም የተግባር ላይ ሥልጠናና የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም. በተካሄዱት የ6ዙር ሥልጠናዎች 2301 በአማርኛ፤ 453 በኦሮምኛ ቋንቋዎች በድምሩ 2754 ተተኪ የግቢ ጉባኤያት መምህራንን ማፍራት መቻሉን በማኅበረ ቅዱሳን በትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌልና የሥልጠና ማስተባበሪያ ክፍል ገልጿል፡:

St.Mary

ጼዴንያ ማርያም

መስከረም 9 ቀን 2007 ዓ.ም.

St.Mary“ሰላም ለሥዕልኪ እንተ ሠዓላ በእዱ፡፡ ሉቃስ ጠቢብ እምወንጌላውያን አሐዱ፡፡ አመ ተቀብዑ ማርያም እምሐፈ ሥዕልኪ ቅብዐ ናርዱ፡፡ በሕማም እኩይ እለ ደወዩ ወውሕዱ፡፡ ፅዑራነ ዓለም ጥዕዩ ወጥቀ ፈድፈዱ፡፡” አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥር በዚች ቀን ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገለጠ፡፡

ይቺንም ሥዕል የሣላት ወንጌላዊ ሉቃስ ነው፡፡ ወደ ጼዴንያ አገርም የመጣችበት ምክንያት አንዲት ስሟ ማርታ የሚባል መበለት ሴት ነበረችና ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ናት አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያምንም እጅግ ትወዳት ነበር፡፡ በሚቻላትም ሁሉ ታገለግላታለች፡፡

በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኲሴ ከእርሷ ዘንድ እንግድነት አደረ በመልካም አቀባበልም ተቀበለችው በማግሥቱም ስትሸኘው አባት ሆይ የምትሔደው ወዴት ነው አለችው፡፡ እርሱም በከበሩ ቦታዎች ውስጥ ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም እሔዳለሁ አላት እርሷም ከአኔ ገንዘብ ወስደህ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ግዛልኝና በመመለሻህ ጊዜ አምጣልኝ አለችው፡፡ እርሱም በራሴ ገንዘብ ገዝቼ አመጣልሻለሁ አላት፡፡

ከዚህም በኋላ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከቅዱሳት መካናት ተባረከና ሥዕሏን ሳይገዛ ወደ ጐዳናው ተመለሰ፡፡ ያን ጊዜም ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰማ ወደ ገበያም ተመልሶ ላሕይዋና መልኳ ያማረና የተወደደ የሆነ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ገዛት በሐርና በንጹሕ ልብስም ጠቀለላት፡፡

በጐዳናውም እየተጓዘ ሳለ ከማያስፈራ ዱር ውስጥ ወንበደዎች ተነሡበት ሊሸሽም ወደደ ከዚያቺም ሥዕል መንገድህን ሒድ የሚል ቃል ወጣ የተከተለውም ሳይኖር መንገዱን ተጓዘ፡፡ ሁለተኛም ነጥቆ ሊበላው አንበሳ ተነሣበት ያን ጊዜም ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረው፡፡

አባ ቴዎድሮስም ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምር በአየ ጊዜ ያቺን ሥዕል ወደ አገሩ ሊወስዳት ወደደ ግዛልኝ ላለችው መበለት ይሰጣት ዘንድ አልፈለገም፡፡ ከዚህም በኋላ በመርከብ ተሳፍሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ ታላቅ ነፋስ ተነሣበት ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያም ወሰደው ከመርከብም ወርዶ ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ሔደ ማንነቱንም አልገለጣላትም እርሷም አላወቀችውም፡፡

በማግሥቱም ተሰውሮ ወጥቶ ወደ አገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የቅጽሩን ደጃፍ አጥቶ ሲያጥመሰምስ ዋለ በመሸ ጊዜም ወደ ማደሪያው ተመለሰ፡፡ ያቺም መበለት በአየችው ጊዜ ታደንቃለች እንዲህም ሁኖ እስከ ሦስት ቀን ኖረ በመሸ ጊዜ በሩን ያየዋል ነግቶ መሔድን ሲሻ የበሩ መንገድ ይሠወረዋል፡፡ ያቺም መበለት ያዝ አድርጋ አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን ስትቅበዘበዝ አይሀለሁና ምን ሁነህ ነው አለችው፡፡

ከዚህም በኋላ ከዚያች ሥዕል የሆነውን ሁሉ ነገራት ራሱንም ገለጠላት፡፡ ያቺንም ሥዕል ሰጣት ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ፈታች ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኲሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች፡፡

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት በቀንና በሌሊትም የሚበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች ከመቅረዞም ውጭ የሐር መጋረጃን ጋረደች፡፡ ከሥዕሊቱ በታችም ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች ያም መነኰስ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ፡፡

የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ፡፡ በሠሌዳዋም ውስጥ በአዩዋት ጊዜ ሥጋ የለበሰች ሁና አገኙዋት ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ ከዚያም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ ይመላል፡፡

ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሁኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች፡፡ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእናቱ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡

  • ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ከመስከረም እስከ የካቲት

 

gedamate11

ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማትና በአብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ እያከናወናቸው የሚገኙ ውጤታማ ተግባራት

መስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

gedamate11በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ገዳማት ከተረጅነት ወጥተው በራስ አገዝ የገቢ ምንጭ እንዲተዳደሩና አንድነታቸውና ገዳማዊ ሥርዓታቸው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገሩ፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት ሥርዓትና ትውፊት ሳይበረዝ፤ ተተኪ ሊቃውንትንና አገልጋዮችን ለማፍራት ትልቅ ድርሻ ያላቸው አብነት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር፤ ባልተቋቋመባቸውም አካባቢዎች የማቋቋም ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ዋና ክፍሉ የገዳማትንና አብነት ትምህርት ቤቶችን ችግር ለመፍታት ከሰሜን አሜሪካና ከአውሮፓ ማእከላት፤ ከማኅበራት፤ በዋና ክፍሉና በማእከላት አስተባባሪነት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የማኅበሩን አገልግሎት ከሚያግዙ ምእመናን በተደረገ ድጋፍ የገዳማትንና አብነት ትምህርት ቤቶችን ችግር ለመቅረፍ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ወደፊትም በቅዱሳት መካናት በየዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከዋና ክፍሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

በ2005 ዓ.ም. እና በ2006 ዓ.ም. በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ በልማትና በአቅም ማሳደግ ረገድ ራሳቸውን ችለው መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የተከናወኑትን ተግባራት ዋና ክፍሉ ካደረሰን መረጃ ጥቂቶቹን እናቀርባለን፡፡

የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች፡-

gedamat12በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የላይ ቤት የመጻሕፍት ትርጓሜ ሐተታ ስልት የሚሰጥበትና ማስመስከሪያ የሆነው የሞጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ ቤተ ጉባኤ 64 ተማሪዎችን እንዲሁም 2 መምህራንን ማስተናገድ የሚችል ባለ አንድ ፎቅ የመማሪያ፣ የማደሪያ፣ የቤተ መጻሕፍት ክፍሎች ያሉት ሕንፃ ከነ ሙሉ መገልገያው ተሠርቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

በምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ለደብረ ካስዋ ጉንዳጉንዶ ቅድስት ማርያም ገዳም የገቢ ማስገኛ ይውል ዘንድ በዓዲግራት ከተማ ላይ ባለ ሁለት ፎቅ የሚከራይ ሕንፃ ፕሮጀክት አጥንቶ የምድር ወለሉን በማጠናቀቅ ቀጣይ የግንባታ ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል፡:

 
gedamat13በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡

 

በሰሜን ምዕራብ ትግራይ /ሽሬ/ ሀገረ ስብከት በአስገደ ጽብላ የአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ አንድነት ገዳም 150 ሺህ ሊትር ውኃ መያዝ የሚችል የውኃ ማጠራቀሚያ /ታንከር/ ተሠርቶ ለአገልግለሎት ተዘጋጅቷል፡፡

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ዘመናዊ የወተት ላም እርባታ ፕሮጀክት ከገዳሙ ጋር በወጪ መጋራት ተጠናቆ ርክክብ ተደርጓል፡፡

በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት የዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም የሽመና ቤት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡: በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የደብረ ዘመዳ ቅድስት ማርያም ወአቡነ በርተሎሜዎስ አንድነት ገዳም የጎርፍ መቀልበሻ ግድብ ሥራ ተጠናቆ ገዳሙን ከጎርፍ ጥቃት ለመታደግ ተችሏል፡፡

gedamat14በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የበዴሳ መካነ ሰላም ቅድስት ማርያም የወተት ላም እርባታ፤ በአፋር ሀገረ ስብከት አዋሽ አርባ ቅዱስ ሚካኤል የመስኖ ልማት ፤ በሽሬ ሀገረ ስብከት ማይ ወይኒ ግዝግዝያ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የወፍጮ ተከላ፤ በከምባታ ሐዲያና ጠምባሮ ሀገረ ስብከት ዱራሜ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የበግ ማድለብ፤ ፤ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት አስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የወፍጮ ተከላ፤ ፕሮጀክቶች በወጪ መጋራት መርሐ ግብር ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ደብረ ከርቤ ጥንታዊ ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን የጊዜያዊ የጣሪያ ማልበስ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ደብረ ፀሐይ ዋንጣ ቅድስት ማርያም የንብ ልማት ፕሮጀክት ተጠናቆ ርክክብ ተደርጓል፡፡

በምእራብ ወለጋ ቂልጡ ካራ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም እና በሆሣዕና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነባር አዳሪ ትምህርት ቤቶችን የመቀበል አቅም ለማሳደግ የማስፋፊያና የማጠናከሪያ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

 

በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች፡-

በሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት የደብረ ኃይል ወደብረ ጥበባት በዓታ ለማርያም የአቋቋም ምስክር ጉባኤ ቤት ለ120 ተማሪዎች ማደሪያ፣ መማሪያና ቤተ መጽሐፍ ያለው ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ እየተገነባ ሲሆን፤ ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቋል፡፡

gedamat16በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት የደብረ ባሕርይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ወአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ባለ 3 ፎቅ ሁለገብ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ከምሥራቁ የሀገራችን ክፍሎች ተተኪ አገልጋዮችን ለማፍራት በሐረር ከተማ በደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ገዳም ባለ አንድ ፎቅ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት በአርባ ምንጭ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም ለተማሪዎች ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጠት የሚችል አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ እየተሠራ ይገኛል፤ ሥራውም በቀጣይ ጥቂት ወራት ይጠናቀቃል፡፡

የ100 ገዳማት የመረጃ ጥንቅር የምጣኔ ሀብት አመላካች መሠረታዊ መረጃ / Economical maping & profiling / የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

 

የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎች፡-

ገዳማት በራሳቸው ተነሳሽነት በልማት ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ ከ70 ገዳማት ለተውጣጡ የገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች ስለ ሀብት ምንነትና አጠቃቀም፣ ስለ ፕሮጀክት አጠናን፤ እንዲሁም ስለ ሒሳብ መዝገብ አያያዝ የአንድ ሳምንት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በዚህም ጠንካራ ገዳማዊ ሥርዓት የሚመሠረትበትንና የገዳማት እርስ በእርስ ግንኙነት የሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

የአብነቱንና የዘመናዊዉን ትምህርት አቀናጅቶ መስጠት በሚያስችለው የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ነጻ የትምህርትና ሥልጠና እድል መርሐ ግብር የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት 569 ተማሪዎችን በማሳተፍ በአራት አብነት ትምህርት ቤቶች ተጀምሯል፡፡

በ10 አብነት ትምህርት ቤቶች እና በ4 ገዳማት ለሚገኙ አባቶችና እናቶች ባለሙያዎችን በማስተባበር ሕክምና እንዲሁም የጤና፤ የግልና የአካባቢ ንጽሕና ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

ለ120 የአብነት መምህራንና ተማሪዎች ልዩ ልዩ የአስተዳደርና የሥራ ፈጠራ ክህሎት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

የተጠናቀቁ ጥናቶች፡-

በምዕራባዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በሁመራ የአብነት ትምህርት ቤት እና የካህናት ማሠልጠኛ ለመሥራት የሚያስችል ጥናት ተጠናቋል፡፡

በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት በጂንካ አንቀጸ ብፁዓን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የአብነት ትምህርት ቤቱን የቅበላ አቅም ለማሳደግ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡

በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ለዙር አባ ጽርሐ አርያም አቡነ አረጋዊ ገዳም የዝማሬ መዋስዕት ማስመስከሪያ ጉባኤ ቤት የትምህርት መስጫ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ጥናት ተደርጎ የእቃ አቅርቦት በመደረግ ላይ ነው፡፡

በባሕርዳር ከተማ የግእዝና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ሁለገብ የአብነት መምህራን፣ ተማሪዎችና መነኮሳት የሥልጠናና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለመመሥረት የሚቻልበትን ሁኔታ ጥናት ተደርጓል፡፡ በጥናቱ መሠረትም አንድ ብሎክ ሕንፃ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ግንባታው ተጀምሯል፡፡

ልዩ ልዩ ድጋፎች፡-

በ162 የአብነት ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ለ182 መምህራንና ለ1,069 ተማሪዎች ወርሃዊ የገንዘብ ድጎማ ተደርጓል፡፡

ጤና ሀብት ነው በሚል መሪ ቃል 20 ሺሕ ለሚሆኑ የአብነት ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የግልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ የግል ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ተሰራጭተዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት በደብረ ሊባኖስ ገዳም፤ በምዕራፈ ቅዱሳን በልበሊት ኢየሱስ አንድነት ገዳምና በፍቼ ደብረ ሲና ዓራተ ማርያም ገዳም ለሚገኙ አብነት መምህራንና ተማሪዎች፤ እንዲሁም ለገዳማቱ ማኅበረሰብ ልዩ ልዩ የጤና ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ ለ80 የአብነት መምህራን የመነጽር እና የመድኃኒት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ለ275 ቅዱሳት መካናት የእጣን፤ የጧፍ፤ የዘቢብ እና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

jinka 01

በጂንካ ማእከል አበረታች ሐዋርያዊ አገልግሎት እየተከናወነ ነው

መስከረም 6 ቀን 2007 ዓ.ም.

jinka 01በደቡብ ኦሞ ጂንካ ሀገረ ስብከት በማኅበረ ቅዱሳን የጂንካ ማእከል እየታየ ያለው ሐዋርያዊ አገልግሎት አበረታች መሆኑን የማእከሉ ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ጌታቸው አስታወቁ፡፡

ከነሐሴ 29 ቀን እስከ ጳጉሜን 4 ቀን2006 ዓ.ም ዐሥር አባላት ያሉት የማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር የልኡካን ቡድን በጂንካ ማእከል በመገኘት በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ተወያይቷል፡፡ ልኡካን ድኑ በጂንካ ማእከል ድጋፍ የሚደረግላቸውን በሣልማ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ የአብነት ተማሪዎችንና በሸጲ ገይላ የሚገኘውን የ“ስብከት ኬላ” ጎብኝቷል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የጂንካ ማእከል ሰበሳቢ አቶ ዘለዓለም ጌታቸው የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት ማእከሉ በአካባቢው ቋንቋ ወንጌልን የሚያስተምሩ አገልጋዮችን ለማፍራት ሥልጠናዎችን ሠጥቷል፣ በአካባቢው የሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ደግፏል፣ አብያተ ክርስቲያናት ባልታነጹባቸው ገጠር ቀበሌዎች የ“ስብከት ኬላዎችን” በማቋቋም ትምህርተ ወንጌል ሠጥቷል፣ ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት የንዋያተ ቅዱሳት ድጋፍ አድርጓል፣ ለአብያተ ክርስቲያናት የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ የልማት ሥራዎችን ሠርቷል ሲሉ በመረጃዎች አስደግፈው ለልኡክ ቡድኑ የሠሯቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ማእከሉ ከሀገረ ስብከት፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ከመንፈሳውያን ማኅበራት ጋር በመተባበር ወደ ገጠሩ ክፍል ሐዋርያዊ ጉዞ እንደሚያደርግ የተናገሩት አቶ ዘለዓለም በዚህም አበረታች ለውጥ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለስብከተ ወንጌል ከቦታ ቦታ ስንዘዋወር “አስተምሩን፣ አጥምቁን፣ አስከሬናችን የእንሰት ማሳ ውስጥ ከሚቀበር ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶልን በተቀደሰ መሬት ላይ እንዲቀበር አድርጉ” በማለት ጥያቄ የሚያቀርቡ ኢአማንያን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት የማእከሉ የትምህርት ክፍል ተጠሪ ዲያቆን ፈቃዱ ብዙአየሁ ማእከሉ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ እና የቁሳቁሶች ችግር ስላለበት ፍላጎታቸውን ሙሉ በሙሉ ማሟላት አለመቻሉንም አስረድተዋል፡፡

በጂንካ ማእከል ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን የሚናገረው ዲ/ን ሀብታሙ ግዛው ዓይኑን፣ እግሩንና ኩላሊቱን ታማማ ሲሆን ሥራ ሠርቶ ራሱን መደገፍ አልተቻለውም፡፡ ነገር ግን ለወንጌል አገልግሎት ካለው ከፍተኛ ፍቅር የተነሣ በአካባቢው እየተዘዋወረ በቋንቋ በሚያስተምርበት ወቅት ማእከሉ ከጎኑ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በሠልማ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን 55 የአካባቢው ተወላጅ ልጆችን ሰብስበው የአብነት ትምህርት በማስተማር ላይ የሚገኙት ቄስ ብርሃኑ “ከቤተሰብ ርቄ ስኖር የዓይኔ ማረፊያዎች ተማሪዎቼ ናቸው” ብለዋል፡፡ አያይዘውም ተማሪዎች በቃለ እግዚአብሔር ታንጸው ለክህነት አገልግሎት እንዲበቁ የጂንካ ማእከል በቅርበት እየደገፋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጂንካ ማእከል ለሠልማ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ለተማሪዎች ማደሪያ ቤት የሚውል 25 ቆርቆሮ እና የጸሎት መጻሕፍት ድጋፍ ማድረጉን አቶ ዘለዓለም ጠቁመው፣ በቀጣይም ለካህናት 40 ቆርቆሮ የሚፈጅ የመኖሪያ ቤት ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር አስተባባሪ መጋቤ ሐዲስ አዲስ አለማየሁ እና የገቢ አሰባሳቢና የቅስቀሳ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ታደሰ ጌታሁን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ወንጌልን ማስተማር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ዓለም የላካቸው ወንጌልን እንዲሰብኩ ነው፡፡ የጂንካ ማእከልም የሐዋርያትን ፍኖት ተከትሎ እየሠራ ያለው ተግባር አበረታች ነው ብለዋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር አማካኝነት ለጂንካ ማእከል ከበጎ አድራጊ ምእመናን በ2006 ዓ.ም. የተገኘ አንድ ሞተር ሳይክል፤ በተጨማሪም ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉ ጀነሬተር፣ አምስት ድምፅ ማጉያ፣ አምስት ቴፕ፣ አልባሳትና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን መጋቤ ሐዲስ አዲስ ተናግረዋል፡፡

ቀሲስ ታደሰ ለዚህ የተቀደሰ አገልግሎት መሳካት ድጋፍ ያደረጉ በጎ አድራጊ ምእመናን እና በማኅበረ ቅዱሳን የጂንካ ማእከልን አመስግነው ተጠማቅያኑን በእምነት ለማጽናትና ተጨማሪ ኢአማንያንን ለማስጠመቅ ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ምእመናን በአካባቢው ቋንቋ ለሚያስተምሩ ቋሚ መምህራን በጀት እና ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር የሚውሉ ልዩ ልዩ ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 
የጂንካ ማእከል በ1989 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት 88 አባላት አሉት፡፡

 

memebers 001

የሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ 14ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

መስከረም 2 ቀን 2006 ዓ.ም.

ከሰሜን አሜሪካ ማእከል

memebers 001በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ 14ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን በአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ እና በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ወአቡነ አረጋዊ አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶች አዘጋጅነት ከነሐሴ 23 – 25/2006 ዓ/ም (August 29 – 31/2014) አካሄደ።

በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የመጡ የሰንበት ት/ቤት አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች አርብ ነሐሴ 23 ረፋዱ ላይ አትላንታ የገቡ ሲሆን፣ ምሽት ላይ የጉባኤው መክፈቻ የጸሎት መርሐ ግብር በመካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ቤ/ክ ተከናውኗል። የደብሩ አስተዳዳሪ መላከ ሕይወት ቀሲስ እርገተ ቃል እና የአዘጋጆቹ ሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ለጉባኤው ተጋብዘው የተገኙት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ የእለቱን ትምህርት አስተምረዋል። በመቀጠል የአንድነት ጉባኤው ሰብሳቢ ዲ/ን ኄኖክ ተዘራ ስለ ቀጣይ ሁለት ቀናት የጉባኤው መርሐ ግብር አጠቃላይ ገለጻ ሰጥተው የእለቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል።

ቅዳሜ ነሐሴ 24 ጠዋት መርሐ ግብሩ በጸሎት ከተጀመረ በኋላ ለጉባኤው ከሜኒያፖሊስ ፣ ሜኒሶታ ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ተጋብዘው የተገኙት መምህር ቀሲስ ስንታየሁ ወጣቶችን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚያነቃ እና የሚያንጽ ትምህርተ ወንጌል አስተላልፈዋል፡፡

 

በመቀጠልም የአንድነት ጉባኤው ሥራ አመራር እና የሦስት ክፍለ ግዛቶች የ2006 ዓ/ም የሥራ እንቅስቃሴ ጠቅላላ ሪፖርት እና ውይይት ተካሂዷል። ከቀረቡት ሪፖርቶች መካከል አንድነት ጉባኤው ከሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት እና ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ጋር ያለው የጠነከረ ግንኙነት ወደፊት አንድነት ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ አገልግሎቱን እንዲያካሂድ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ያመለክታል።

 

በኢትዮጵያ ጎንደር ቤዛዊት ማርያም እና ደብረ ዘይት ደብረ መጽሔት ቅ/ኪዳነ ምሕረት ሰንበት ት/ቤቶች በ2006 ዓ/ም ያደረገው የ$8000.00 (ስምንት ሺህ ዶላር) እርዳታabune fan 01 አባላቱ የበለጠ ለአገልግሎት እንዲተጉ መነሳሳትን ፈጥሯል። በመቀጠልም ከሰባቱ የአንድነት ጉባኤው ክፍለ ግዛት መካከል በሰሜን ምዕራብ ክፍለ ግዛት ትምህርታዊ ጉባኤ ላይ ከቀረቡ ዝግጅቶች መካከል “የምንፈልገውን ወይስ የሚያስፈልገንን” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የምልከታ ጽሑፍ በዲ/ን ዳዊት ብርሃኑ አማካይነት ቀርቧል።

ከሰዓት በኋላ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ጥልቅ ምሥጢር ያለው ትምህርተ ወንጌል ካስተላለፉ በኋላ በዲሲ እና አካባቢው የሚገኙ “መስማት የተሳናቸው” ወንድሞች እና እህቶች በአይነቱ ልዩ የሆነ ዝግጅት አቅርበዋል። የቀረበው ዝግጅት መስማት የተሳናቸው ወገኖች ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ስላላቸው ትጋት፣ ከምእመናን እና ከቤተ ክርስቲያን አካላት ሊደረግላቸው ስለሚገባ ድጋፍ እና የወደፊት እቅዳቸውን የሚገልጽ ነበር።

 

የአንድነት ጉባኤው የ2007 ዓ ም በጀት ዓመት ዕቅድ እና ውይይት ከተካሄደ በኋላ “በክርስትና የሚገኝ ተስፋ” በሚል ርዕስ መላከ ሰላም ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል። ጥናታዊ ጽሑፉ ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈችውን ፈተናዎች፣ በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ሁኔታ፣ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ያለፉበት እና አሁን ያሉባቸው ፈታናዎች፣ እንዲሁም በዚህ ሁሉ ፈተና መካከል ስላለ ክርስቲያናዊ ተስፋ የዳሰሰ ነበር። ከጥናታዊ ጽሑፉ በኋላ የሲያትል ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ የፍኖተ ሰላም ሰንበት ት/ቤት አባላት ልዩ ያሬዳዊ ጣዕመ ዜማ አቅርበዋል።

 

አብዛኛው የአንድነት ጉባኤው አባላት የተሳተፉበትና ሰፊ ውይይት የተካሄደበት የአንድነት ጉባኤው ሥልታዊ ዕቅድ (ከ2008 – 2012) መነሻ ሃሳብ በዲ/ን ብዙአየሁ ልመንህ ቀርቦ አባላቱ ለረጅም ሰዓታት በስድስት መሪ ነጥቦች ላይ ውይይት አካሂደዋል። ከአባላቱ የተሰበሰቡትን ሃሳቦች አጠቃሎ የያዘ የ4 ዓመት ሥልታዊ እቅድ በሚቀጥለው ዓመት (በ15ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ) እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

 

ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ የአንድነት ጉባኤው ሥራ አመራር አባላት አስመራጭ ኮሚቴ ከተመረጠ በኃላ ከ13ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ጀምሮ በጉጉት የሚጠበቀው በሰንበት ት/ቤቶች መካከል ከፍተኛ መንፈሳዊ ፉክክር የሚታይበት በአንድነት ጉባኤው የ14 ዓመት የጉዞ ሂደት ላይ ያተኮረ፣ ስለደንቡ ፣ መመሪያው እና ልዩ ልዩ ታሪኮች ዙሪያ የተዘጋጀ የጥያቄ እና መልስ ውድድር በቤካ መገርሳ መሪነት ተከናውኖ የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎት ተጠናቋል።

እሁድ ጠዋት የአንድነት ጉባኤው አባላት አትላንታ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ቅዳሴ ከተሳተፉ በኋላ የከሰዓቱ መርሐ ግብር አዘጋጆቹ ሰንበት ት/ቤቶች ለዓመታዊ ጉባኤው በሚገባ እንደተዘጋጁበት በሚያሳይ የምሳ መስተንግዶ ተጀምሯል። በማስከተልም “ቤተ ክርስቲያን እና ቴክኖሎጂ” በሚል ርዕስ አሁን ያለው የቴክኖሎጂ ምጥቀት እና ቤተ ክርስቲያናችን ልትጠቀምባቸው ስለሚገባ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሰፊ ጥናታዊ ዝግጅት በዲ/ን ዮሴፍ አዱኛ ቀርቧል። ዝግጅቱ የቴክኖሎጂን ጥቅም እና ጉዳት፣ በአንድነት ጉባኤው እስካሁን የተሰሩ እና ሊተገበሩ ስለሚገቡ ሥራዎች በስፋት ተገልጿል። የወደፊቱንም ሥራ ሊያግዙ የሚችሉ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር የተገናኘ ሙያ ያላቸው ሰባት የአንድነት ጉባኤው አባላትም ተመርጠዋል። ዲ/ን ዮሴፍ አዱኛ የ debelo.org የአብነት ትምህርት ቤት ድረ-ገጽ አዘጋጅ ናቸው።

ከጥናታዊ ዝግጅቱ በኋላ የቀጣይ ሁለት ዓመታት የአንድነት ጉባኤው ሥራ አመራር አባላት ምርጫ ተካሂዶ የአትላንታ እና አካባቢው ሰ/ት/ቤት አባላት የመድረክ መዝሙር አቅርበዋል። በመቀጠልም ከማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል እና ከማኅበረ ባለ ወልድ በሰሜን አሜሪካ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ቀርቧል፡፡

 

abune fanuel 02ከዓመታዊ የሀገረ ስብከት ስብሰባ ቆይታ በኋላ በዓመታዊ ጉባኤው ላይ ለመገኘት ቅዳሜ ምሽት አትላንታ የገቡት የዲሲ እና ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከአትላንታ ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ የተክለ ሃይማኖት በዓለ ንግስ በኋላ አትላንታ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ጋር በመሆን እሁድ ከሰዓት በኋላ በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል። ብፅዕነታቸው ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ለተመረጡት የሥራ አመራር አባላት ጸሎት ካደረጉ በኋላ ቃለ ቡራኬ አስተላልፈዋል። አንድነት ጉባኤው አገልግሎቱን አጠናከሮ መቀጠል እንደሚገባው፣ ወጣቱ ወደፊት ብዙ አገልግሎት እንደሚጠብቀው እና ሁል ጊዜ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ እንደሚገባው አባታዊ ምክርና ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል።

 

በ2006 ዓ/ም ለአንድነት ጉባኤው አገልግሎት መሳካት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ እና በበዓሉ ላይ ለሚቀርቡ ዝግጅቶች ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን ላበረከቱ አባቶች፣ ሰንበት ት/ቤቶች፣ ወንድሞች፣ እና እህቶች የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ከብፅዕነታቸው እንዲቀበሉ ተደርጓል።

 

የእለቱን የማጠቃለያ መርሐ ግብር ታሪካዊ ካደረጉት ዝግጅቶች አንዱ የሆነው በኢትዮጵያውያን ሰዓሊያን የተሳለ የቅዱስ ያሬድ ስዕል በአንድነት ጉባኤው ልማት ክፍል አማካይነት ለጨረታ ቀርቦ ለጉባኤው የመጡ ሰ/ት/ቤቶች ከፍተኛ ፉክክር አድርገውበታል፡፡ በመጨረሻም መስማት የተሳናቸው ወንድሞች እና እህቶች አሸንፈዋል።

 

all memebersበዕለቱም በአብርሃም ሰሞሎን እና በቤዛ ኃይሉ የተዘጋጁ መንፈሳዊ ግጥሞች የዝግጅቱ አካላት ነበሩ። ዲ/ን ዳዊት ፋንታዬ፣ ጋሻው ታደሰ እና ሲሳይ ደንቦባ የሁለቱን ቀናት መርሐ ግብር በመምራት ዓመታዊ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አድርገዋል። በጉባኤው በተገኙ ዘማርያን እና አጠቃላይ አባላት በአንድነት በመሆን መዝሙር ከተዘመረ በኋላ የዓመታዊ ጉባኤው መርሐ ግብር በጸሎት ተፈጽሟል።

 

ሰኞ እለት አትላንታ የነበሩ ወንድሞች እና እህቶች በአትላንታ ሊጎበኙ የሚችሉ ታሪካዊ ቦታዎችን ሲጎበኙ አርፍደው ወደ ምሽት ላይ በመካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ በተዘጋጀው ልዩ የእራት እና አዝናኝ የውይይት መርሐ ግብር ላይ አምሽተዋል።

የመካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ እና የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ወነቡነ አረጋዊ ቤ/ክ ሰንበት ት/ቤት ካህናት፣ ሰበካ ጉባኤ እና ሰንበት ት/ቤት አባላት መስተንግዷቸው፣ ፍቅራቸው እና ለጉባኤው መሳካት ያደረጉት ልዩ ጥረት ፍጹም ከልብ የማይጠፋና ዘወትር በጉባኤው ተሳታፊዎች ሲታሰብ የሚኖር ነው።

እግዚአብሔር ቢፈቅድ 15ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በዳላስ ቴክሳስ ፣ 16ኛው ጉባኤ ደግሞ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

 

የ2007 አጽዋማትና በዓላት

ጳጉሜን 5 ቀን 2006 ዓ.ም.

  • መስከረም 1 ሐሙስ፣

  • ነነዌ ጥር 25፣

  • ዓብይ ጾም የካቲት 9፣

  • ደብረ ዘይት መጋቢት 6፣

  • ሆሣዕና መጋቢት 27፣

  • ስቅለት ሚያዚያ 2፣

  • ትንሣኤ ሚያዚያ 4፣

  • ርክበ ካህናት ያዚያ 28፣

  • ዕርገት ግንቦት 13፣

  • ጰራቅሊጦስ ግንቦት 23፣

  • ጾመ ሐዋርያት ግንቦት 24፣

  • ምሕላ ድኅነት ግንቦት 26፣

dscf7869

ቅዱስ ፓትርያርኩ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

ጳጉሜን 4 ቀን 2006 ዓ.ም.

 dscf7869ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለ2007 ዓ.ም. አዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡

የመግለጫውን ሙሉ ቃል አቅርበነዋል፡፡

02 2006jpg 1 02 2006jpg 202 2006jpg 3

 

atena 2006 2

ሀገር ዓቀፍ ዐውደ ጥናት ተካሔደ

ጳጉሜን 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የተዘጋጀው 6ኛው ሀገር ዓቀፍ ዐውደ ጥናት ጳጉሜን 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በማኅበሩ ሕንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሔደ፡፡

atena 2006  2ለአንድ ቀን በተዘጋጀው ዐውደ ጥናት 6 በምርምር ማእከሉ የተመረጡ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቄት ወረዳ የደብረ ገነት ናዙኝ ማርያምና የአቡነ አሮን መንክራዊ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ፤ ኪነ ሕንፃ፤ ተንቀሳቃሽ ቅርስና ያሉበት ሁኔታ በሚል ርዕስ በዲያቆን ፀጋዬ እባበይ በዲላ ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂ መምህር የመጀመሪያውን ጥናት አቅርበዋል፡፡

የደብረ ገነት ናዙኝ ማርያምና የአቡነ አሮን መንክራዊ ገዳማት የተረሱ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት መሆናቸውን የገለጹት ጥናት አቅራቢው፤ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ በከፍተኛ ጉዳት በአደጋ ውስጥ እንደሚገኙና በጥናት ላይ የተደገፈ ጥገና እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

ናዙኝ ማርያም ሁለተኛው የኢትዮጵያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ሙሴ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንዳነጿት አብራርተው፤ ቤተ ክርስቲያኗ ለአክሱማውያን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መሠረት፤ አለበለዚያም ለኋለኞቹ ድልድይ እንደሆነች በጥናታቸው ዳስሰዋል፡፡በመቄት ወረዳ ብቻ ከ19 በላይ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ሲገኙ 13ቱ በአቡነ ሙሴ፤ ሁለቱ ደግሞ በአቡነ አሮን እንደታነጹ ገልጸዋል፡፡

atena 2006  1ሁለተኛው ጥናት ሥነ ምኅዳርን ያማከለ የአካባቢ ጥበቃ እቅድ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ደን የሥነ ምኅዳር አገልግሎት ለማሳደግ በሚል ርዕስ በመስፍን ሳህሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥናት ተማሪ የቀረበ ሲሆን፤ የደብረ ሊባኖስን ገዳም ደን የሥነ ምኅዳር አገልግሎት ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንደሚገባቸው በጥናት አቅራቢው ተገልጿል፡፡ ቀድሞ የነበረው ተፈጥሯዊ ደን መመናመን፣ በተለያዩ ምክንያቶች መሬቱ እየተራቆተ መምጣቱ፤ የአፈሩ መሸርሸር፣ ለጐርፍ አደጋ ገዳሙ መጋለጡንና የአካባቢው የአየር ጸባይ መለዋወጥ ገዳሙን ለከፍተኛ አደጋ እንዳጋለጠው ጠቅሰዋል፡፡

በዲያቆን ሔኖክ ሐይሉ /MA/ ከማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የቀረበው 3ኛው ጥናት የተቀናጀ ሃይማኖታዊ እና የምክክር /counseling/ መርህ የካህናትን የማማከር ክሂል በማሳደግ ረገድ ያለው ውጤታማነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንጻር በሚል ርዕስ ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ቢጋር አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡

የንስሐ አባቶች ከንስሐ ልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ዘመኑን የዋጀ ዘመናዊ የሥነ ልቦና የማማከር አገልግሎት ሥልጠና ቢወስዱ ውጤታማ የቤተ ክርስቢተያንን አገልግሎት ለመተግበር እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል፡፡ የንስሃ ልጆቻቸው ኃጢአታቸውን ተናዝዘው፤ ንስሃ ገብተው፣ ቀኖናቸውን ተቀብለው ወደ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የመቅረብ ሂደት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጓደኝነት፤ በትዳር፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ለሚገጥማቸው መሰናክል የንስሐ አባቶች የሥነ ልቦና የማማከር አገልግሎት ላይ እውቀት ኖሯቸው ከልጆቻቸው ምክክር ቢያደርጉ አገልግሎቱን የተሟላ ሊያደርገው እንደሚችል በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

በሦስቱም ጥናቶች ላይ ከተጋባዥ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምሁራንና ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ከሰዓት በኋላ በቀጠለው ዐውደ ጥናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብራና መጻሕፍት ይዞታቸው፤ ያካተቷቸው ምሥጢራትና ከባሕር ማዶ ስለሚገኙት መጻሕፍት በሚል ርእስ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህር ጥናታቻውን አቅርበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩ አስደናቂ የብራና መጻሕፍት መካከል ቀዳሚዎቹ የዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊቃውንት ለምስክርነት የሚጠቀሙባቸው ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ የብሉይ፤ የሐዲስ ኪዳን፣ የጸዋትወ ዜማ፣ የጸሎትና የምስጋና መጻሕፍት፣ መጻሕፍተ ሊቃውንት እና የሃይማኖት መጻሕፍት፣ መጻሕፍተ መነኮሳትና ሌሎችም መጻሕፍት በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር ወጥተው በውጭ ሀገራት እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ዓለማት ያሉ ተመራማሪዎች እነዚህ ሁሉ ጥበባት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዳሉ በማወቃቸው መጻሕፍቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሀገራችን እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ እንደ ምሳሌም ጀምስ ብሩስ /ከ1768-1773/ መጽሐፈ ሔኖክን እና በርካታ መጻሕፍትን ይዘው እንደወጡ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡

በዚህም መሠረት በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት 1082፣ በእንግሊዝ 850፣ በጀርመን 734፣ በጣሊያን 550 ወዘተ የብራና መጻሕፍት እንደሚገኙ በጥናታቸው አካትተዋል፡፡

በዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሓላፊ የቀረበው ጥናት የአማርኛ ሥርዓተ ጽሕፈት በቤተ ክህነት ሊቃውንት እይታ በሚል ርዕስ ሲሆን፤ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የፊደላት ምንጫቸው ከፈጣሪ የተገኘ፣ ለሄኖስ በሰማይ ሰሌዳ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸና፤ የግዕዝ ፊደላት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሥራ ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡ አማርኛን በተመለከተም ከግዕዙ የወሰዳቸው 26 አናባቢዎች እንዳሉ ሆነው፤ በኋላ 7 ከዚያም /ቨ/ን በመጨመር 34 እናት ፊደላት /consonants/፤ እንዲሁም 4 ደቃልው /labioverals/ /ኰ፣ጐ፣ቈ፣ኈ/ ፊደሎች አሉት:: 20 ፍንድቅ ፊደላትን /ሏ፣ ሟ፣ ሷ፣ ሯ…./ በመጨመር የአገልግሎት አድማሱን ማስፋቱን በጥናታቸው ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም መሠረት 278 ድምጽ ወካይ ፊደላት /characters/ አሉት፡፡

atena 2006  3ከፊደላት ጋር የሚከሰቱ ችግሮችን አስመልክቶም በአማርኛ ፊደል ገበታ ላይ ተመሳሳይ ድምጽ ያላቸው ስለሚገኙ፤ በአጻጻፍ ረገድ በርካታ ልዩነቶች መኖራቸው፤ ራብዕ ድምጸት ያላቸው ከግእዙ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ፊደላት መኖራቸው፤ ሳድስና ሳልስን እያቀያየሩ መጠቀም፣ ደቃልውና ፍንድቅ ፈደላትን በዝርዝር የመጠቀም ዝንባሌ፣ በመሠረታዊ ቃሉ ላይ የሌለውን ቃል መጨመር፣ የአናባቢዎች ቅጥል አለመለየት ችግሩን ይበልጥ እንዳሰፋው ጠቁመዋል፡፡

ይህ ችግር በምሁራን ዘንድ ሞክሼ ቃላት ይቀነሱ፤ አይቀነሱ የሚለው ሐሳብ ዛሬም ድረስ እያከራከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አማራጮችንም በተመለከተ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ በ1973 ዓ.ም. ተመሳሳይ ድምጽ ያላቸው ፊደሎች ከገበታው ላይ ተቀንሰው በአንድ ፊደል ብቻ ይወከሉ የሚል ሲሆን፣ የቤተ ክህነት ሊቃውንት አቋም ደግሞ ፊደላት የፈጣሪን ቸርነት የሚገልጹ እና ከእሱ የተገኙ ስለሆኑ ሁሉም ጠንቅቆ ሊጽፋቸው ይገባል እንጂ በፍጹም ሊቀነሱ አይገባም፡፡ ፊደላቱ በሙሉ መንፈሳዊ፣ ተፈጥሯዊና ሙያዊ ትርጓሜ ስላላቸው ያንን ያጣሉ በማለት ይገልጻሉ፡፡

አማርኛ እንዴት ሥርዓተ ጽሕፈቱን ይጠብቅ የሚለውን እንደመፍትሔ ሲያቀርቡም የአማርኛ ሥርዓተ ጽሕፈት መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን እየተጠቀምንበት የሚገኘውን የግዕዙን ሥርዓተ ሰዋሰውና የትውስት ቃላት እንዳሉ መጠበቅ ሲቻል ነው ብለዋል፡፡

የአማርኛ ፊደል የሚጽፍ ሁሉ ፊደላቱን እንዲጠነቀቅ ማስተማር፣ በባለሙያ የተሠናዱ የሥርወ ቃላት መዝገበ ቃላት እና የሰዋሰው መጻሕፍትን ማዘጋጀት፣ ያሉት ፊደላት እስካሁን ድረስ ሲጻፉ ኖረዋል በዚህም እጅግ በርካታ መጻሕፍትና የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች ተመርተዋል፣ አገልግሎትም እየሰጡ ስለሚገኙ የፊደላቱ መብዛትና መመሳሰል አሳሳቢ እንዳልሆነና ሥርዓተ ጽሕፈቱን ከቅድመ ትምህርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ወጥነት ባለው መንገድ ማስተማር ወዘተ.. እንደመፍትሔ አቅርበዋል፡፡

የመጨረሻው ጥናት ክርስቲያናዊ ጾም በሰው ልጅ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ጾም ከተለያዩ ሃይማኖቶች አንጻር በሚል በዲያቆን ታደሰ አለሙ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ FDS እና የሥነ ምግብ የዶክትሬት ተማሪ ቀርቧል፡፡ በቀረቡ ጥናቶች ላይ በርካታ ሐሳቦችን በማንሳት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ 

 

በመጨረሻም የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከሉ ከቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትና ከተመራማሪ ምሁራን የሚቀርቡለትን ጥናቶች ጠቃሚነታቸውን መርምሮ ለውይይት ማቅረቡን እንደሚቀጥል፤ አቅሙ ያላቸው ተመራማሪዎች ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ምርምሮችንና ጥናቶችን እንዲያቀርቡ ማእከሉ እንደሚያበረታታ የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር አባተ መኩሪያው ገልጸዋል፡፡ 

የንባብ ምልክቶች

ነሐሴ 30 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ደሴ ቀለብ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ መምህር

  • የማንሳት ምልክት

  • የመጣል ምልክት

  • የማጥበቅ ምልክት

አንዳንድ የግእዝ ግሶች የሚጠብቅ ድምፅ ሲኖራቸው ግማሾቹ የላቸውም፡፡

ምሳሌ፣ ቀተለ — ገደለ፣ ቀደሰ — አመሰገነ

ትውውቅ

ሰላም ለከ አኁየ                     ወ ሰላም ለከ

(ሰላም ላንተ ይሁን ወንድሜ)       (ሰላም ላንተም ወንድሜ)

መኑ ስምከ እኁየ                    ወልደ ገብርኤል ውእቱ ስምየ

(ስምህ ማን ነው ወንድሜ)         (ስሜ ወልደ ገብርኤል ነው)

ወመኑ ስመ አቡከ                  ገ/ ማርያም ውእቱ ስመ አቡየ

(ያባትህ ስም ማን ነው)            (ያባቴ ስም ገ/ማርያም ነው)

እስፍንቱ አዝማኒከ                  እሥራ ወአሐዱ

(ዕድሜህ ስንት ነው)               (ሀያ አንድ)

እም አይቴ መጻእከ                      እም ጎጃም

(ከየት መጣህ)                        (ከጎጃም)

ግብር እፎ ውእቱ                      ሚመ ኢይብል

(ሥራ እንዴት ነው)                  (ምንም አይል)

እስኩ ነዓ ነሑር ኀበ ቤተ እግዚአብሔር    ትፍስሕትየ ውእቱ

እስኪ ና ወደ ቤተክርስቲያን እንሂድ       (ደስታዬ ነው)

ሕይወት እፎ ውእቱ                      ሠናይ ውእቱ

(ሕይወት እንዴት ነው)                  (ጥሩ ነው)

እሉ አብያፂከ ውእቶሙ                    እወ

(እነዚህ ጓደኞችህ ናቸው)                (አዎ)

አይቲ ብሔሮሙ                          (ዝ እም ሲዳሞ ወዝኩሰ እም ወሎ)

(የት ነው ሀገራቸው)                     (ይህ ከሲዳሞ ነው ያ ደግሞ ከወሎ)

ትትሜህርኑ ትምህርተ ዘመነዌ              እወ እትሜሀር አነ ትምህርተ ዘመነዌ

(የዘመናዊ ትምህርት ትማራለህ)            (አዎ የዘመናዊ ትምህርት እማራለሁ)

አይቴ ውእቱ ቤተ ትምህርትከ               6 ኪሎ ውእቱ ቤተ ትምህርትየ

(ትምህርት ቤትህ የት ነው)                (6 ኪሎ ነው ትምህርት ቤቴ)

ስፍነ አመተ በጻሕከ                        ሣልሳ ዓመተ በጻሕኩ

(ስንተኛ ዓመት ደረስክ)                    (3 ዓመት ሆኖኛል)

ተአምርኑ ትምህርተ ሃይማኖትከ ወ ሀገርከ      ምንት ውእቱ ትምህርተ ሀገርየ

(የሀይማኖትህ እና የሀገርህን ትምህርት ታውቃለህ)     (የሀገሬ ትምህርት ምንድን ነው)

ንባብ፣ ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ግእዝ፣ ቅኔ ይትበሀሉ       ለእሉሰ አኣምሮሙ ቀዲሙ

(ንባብ፣ ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ይባላሉ)                 እነሱን ቀድሞ አውቃቸዋለሁ

በል እግዚእ የሀብከ ጽንአቶ ወይክስት ለከ           አሜን

(በል ጌታ ፅናትን ይስጥህ ይግለፅልህም)           (ይሁን ይደረግልኝ)

 

ግሥ አርዕስት (Root Verbs)

 

የግሥ አርዕስት ማለት ለሌሎች ግሶች መሠረት በመሆን የሚከተሏቸው ግሶች የእነርሱን የአወራረድ ባህሪ የሚከተሉ እና በአቀማመጣቸው የሚመስሏቸው ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ግልፅ የሚሆኑት በዝርዝር ሥንመለከታቸው በመሆኑ በመጀመሪያ ግር ሊለን አይገባም፡፡ የሆነው ሆኖ ለግስ ርባታ መሠረት መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ የታወቁት የግስ አርዕስታት ስምንት ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸውም የየራሳቸው ሠራዊት አላቸው፡፡

1. ቀተለ    2. ቀደሰ    3. ገብረ    4. አእመረ   5. ባረከ   6. ሤመ    7. ብህለ         8. ቆመ
6.1 እርባ ግስ (Tense and Nouns formation, including Adjectives)

በመጀመሪያ ግን አንድ በአንድ የስምንቱን ግሶች ቀለማት ብዛትና ዓይነት አንባቢው ማስተዋል ይገባዋል፡፡

  1. ቀተለ ፍፁም ሁሉም ግእዝ ሆኖ የላላ

  2. ቀደሰ ፍፁም ግእዝ ሆኖ የጠበቀ

  3. ገብረ ግእዝ ሳድስ ግዕዝ ሆኖ የላላ

  4. አእመረ ግእዝ ሳድስ ግዕዝ ሆኖ የላላ

  5. ባረከ ራብዕ ግዕዝ ግዕዝ ሆኖ የላላ

  6. ሤመ ኀምስ ግእዝ ሆኖ የላላ

  7. ብህለ ሳድስ ሳድስ ግዕዝ ሆኖ የላላ

  8. ቆመ ሳብዕ ግእዝ ሆኖ የላላ

ማንኛውም የቀዳማይ አንቀፅ ግስ ሁሉ ተነሽ መሆኑን በሥርዓተ ንባብ ላይ አይተናል፡፡

1. ቀተለ —- ገደለ ( past tense – ሐላፊ) / ቀዳማይ አንቀፅ/

ይቀትል — ይገድላል (future- ካልአይ— ትንቢት ወይም Present Tense – ያሁን ጊዜ)

ይቅትል —- ይገድል ዘንድ / ዘንድ አንቀፅ/

  • ቀቲል / ቀቲሎት/ — መግደል/ to kill ( infinitive) ንዑስ አንቀፅ/

ቀታሊ — የገደለ / ቅጽል –Adjective

ቀታልያን— የገደሉ /ወንዶች/ / ቅጽል ሲበዛ/

ቀታሊተ — የገደለች / ለሴት ቅጽል ሲሆን

ቀታልያት — የገደሉ / ለብዙ ሴቶች ቅጽል ሲሆን/

ቅቱል —- የተገደለ / ቅጽል — Adjective/

ቀታሊ —-ገዳይ / ስም ሲሆን/

ቀትል — ውጊያ / ጥሬ ዘር/

ቅትለት — አገዳደል / ሳቢዘር/

በ ቀተለ ምሳሌ እንሰራና ሌሎችን እንዴት እንዳሚወርዱ ካየን በኋላ ሌሎችን በራሳችን መሥራት እንችላለን፡፡

ምሳሌ፡-

አነ ቀተልኩ — እኔ ገደልኩ

አነ እቀትል — እኔ እገድላለሁ

አነ እቅትል— እገድል ዘንድ/ ዘንድ አንቀፅ/

አነ እቅትል — ልግደል / ትዕዛዝ/

አንተ ቀተልከ — አንተ ገደልክ አንቲ ቀተልኪ—- ገደልሽ

አንተ ትቀትል — አንተ ትገድላለህ አንቲ ትቀትሊ— ትገድያለሽ

አንተ ቅትል—– አንተ ግደል አንቲ ትቅትሊ —- ትገድይ ዘንድ

ንህነ ቀተልነ — ገደልን አንቲ ቅትሊ — ግደዬ

ንህነ ንቀትል — እንገድላለን አንትን ቀተልክን — ገደላችሁ /ሴ/

ንህነ ንቅትል — እንገድል ዘንድ አንትን ትቀትል —- ትገድላላችሁ / ሴ/

ንህነ ንቅትል — እንግደል አንትን ትቅትል—- ትገድሉ ዘንድ /ሴ/

አንትሙ ቀተልክሙ —ገደላችሁ /ወ/ አንትን ቅትል —- ግደሉ /ሴ/

አንትሙ ትቀትሉ —-ትገድላላችሁ/ወ/ ውእቶሙ ቀተሉ — ገደሉ /ወ/

አንትሙ ትቅትሉ —ትገድሉ ዘንድ/ወ/ ውእቶሙ ይቀትሉ —-ይገድላሉ/ወ/

አንትሙ ቅትሉ —- ግደሉ/ወ/ ውእቶሙ ይቅትሉ — ይገዳሉ ዘንድ/ወ/

ውእቱ ቀተለ — ገደለ ውእቶሙ ይቅትሉ —- ይግደሉ/ወ/

ውእቱ ይቀትል —– ይገድላል ይእቲ ቀተለት —- ገደለች

ውእቱ ይቀትል —- ይገድል ዘንድ ይእቲ ትቀትል — ትገድላለች

ውእቱ ይቅትል —- ይግደል ይእቲ ትቅትል — ትግድል ዘንድ /ሴ/

ውእቶን ቀተላ — ገደሉ /ሴ/ ይእቲ ትቅትል— ትግደል

ውእቶን ይቅትላ —- ይገድላሉ /ሴ/

ውእቶን ይቅትላ — ይገድሉ ዘንድ /ሴ/

ውእቶን ይቅትላ — ይግደሉ /ሴ/

ማስታወሻ፣ ሀ. የትንቢት( future) እና የአሁን ጊዜ( Present) በግእዝ

አንድ ዓይነት የግሥ አወራረድ / አገባብ/ አላቸው፡፡

ለ. ዘንድ አንቀጽና ትዕዛዝ አንቀጽም እንዲሁ አንድ ዓይነት ናቸው፡፡

ሐ. የእግዝ ግሶች ርባታቸውን የሚጀምሩት በቀዳማይ አንቀጽ (past) ነው፡፡

ቀተለን የሚመስሉ ግሶች ነበረ፣ ወረደ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ነገር ግን አወራረዳቸው ከቀተለ ሊለዩ ስለሚችሉ ማስተዋል ያስፈልጋል ፡፡

ምሳሌ ወረደ፣ ይወርድ፣ ይረድ

sarapamon

ቅዱስ ሰራባሞን የኒቅዩስ ሊቀ ጳጳስ – ሕይወቱና ተጋድሎው

ነሐሴ 30 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሓላፊ

sarapamonቤተ ክርስቲያን በዓላውያን ነገሥታት አሰቃቂ ስደት በደረሰባት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕት ዓመታት ውስጥ ከተነሱት የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል አንዱ የሆነውና ለዛሬው የተጋድሎውን ዜና በአጭሩ የምንመለከተው ሰማዕት ቅዱስ ሰራባሞን ዘኒቅዩስ ነው። አባቱ አብርሃም ይባላል፤ አያቱ የቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ አጎት ሲሆን የተወለደው በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ነው። ሲወለድ ወላጆቹ “ስምዖን” ብለው ስም አወጡለት፤ “ሰራባሞን” የጵጵስና ስሙ ነው። የዐረብኛ እና የግዕዝ መጻሕፍት “ሰራባሞን” ሲሉት፣ የቅብጥና እንግሊዝኛ ምንጮች ደግሞ “ሰራፓሞን” ብለው ይጠሩታል።

በተወለደበት በኢየሩሳሌም ሳለ ክርስቲያን መሆን አጥብቆ ይፈልግ ነበር። እመቤታችን በራእይ ተገልጻ ወገኖቹ አይሁድ እንዳይገድሉት ወደ ግብፅ ሄዶ እንዲጠመቅና አገልግሎቱንም በዚያ እንዲፈጽም ስለነገረችው ቤተሰቦቹን ጥሎ መነነ። ግብፅ ሲደርስ እመቤታችን የእስክንድርያ 16ኛ ፓትርያርክ የነበረውን አቡነ ቴዎናስን (282-300) ባዘዘችው መሠረት አስተምሮ አጠመቀው። የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜያት፣ የነቢያትንና ሐዋርያትን መጻሕፍት ተማረ፣ የአግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳን እና የበልኪሮስን ድርሳናት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠና።

ከዚያም ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ በሆነ እልሐብጡን በተባለ በአባ ሳዊሮስ ገዳም ውስጥ መነኮሰ። ከዘመናት በኋላ በተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ዘመን (300-311) የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ሲያርፍ በእርሱ ምትክ የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን መራ፤ ከገድሉ እንደምናነበው ወደ ተመደበበት ሀገረ ስብከት ሲገባ የተደረገለት አቀባበል የደመቀ ከመሆኑ የተነሣ ጌታ በሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ታጅቦ ሲገባ እንደተደረገለት የሚመስል ነበረ። በቅዱስ ሰራባሞን አገልግሎት በኒቅዮስና በአጎራባች ከተሞች የነበሩ ጣዖታት ተሰባብረው ወድቀዋል፤ በእጁ በርካታ ገቢረ ተአምራት ተደርገዋል፤ በመስቀሉ አጋንንትን አባሯል።

ይህ ቅዱስ አባት ስለ ወንጌል ብዙ መከራን ተቀብሏል፤ ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን ብዙ ዘለፋ ደርሶበታል። አርዮስ፣ ሰባልዮስ እና ሚሊጦስ በእርሱ ዘመን የነበሩ መናፍቃን ናቸው። የአርዮስ ዋና ክህደት “ወልድ (ክርስቶስ) ፍጡር ነው” የሚል ሲሆን ሚሊጦስ ደግሞ “ከማርያም የተወለደው ክርስቶስ በምትሐት ነው እንጂ በእውነት አይደለም” የሚል ነበር። ሰባልዮስ “እግዚአብሔር አንድ ገጽ ነው” ብሎ የሚያስተምር ሲሆን፤ ሰራባሞን ሁሉንም ተከራክሮ ረቷቸዋል።

በዚህ የተነሣ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። አርዮስና ሚሊጦስ የሚያስተምረውን ባለመቀበላቸው በክፋታቸው ጸንተው ብዙዎችን እያሳቱ፣ በትዕቢታቸውም ልባቸውን እያኮሩ ቢያገኛቸው በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ የአርዮስና ሚሊጦስን አንገታቸውን በመሐረብ ይዞ “እናንተ አባታችሁን ዲያብሎስን በክህደት የምትመስሉ እስከ መቼ ድረስ ነው በዚህ ክህደታችሁ ሰውን የምታጠፉ?” ብሎ ገስጿቸዋል (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 130-137)። አርዮስ ከክሕደቱ የማይመለስ ከሆነ አንጀቱ ተበጣጥሶ እንደሚሞት፣ ሚሊጦስም ካልተመለሰ ሥጋውን በቁሙ ዕፄያት እንደሚበሉት ትንቢት ተናግሮባቸዋል። እምቢ በማለታቸው በሁለቱም ላይ ይኸው ተፈጽሞባቸዋል።

ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅልጥያኖስ (284-305) የሚያፈርሳትን ቤተ ክርስቲያን ሰረባሞን ሲሰራ፣ ጣዖት የሚያመልኩትንም ሰዎች በክርስቶስ ስም ሲያሳምናቸው ንጉሡ እና መኳንንቱ ስጋት ጨመረባቸው። ሰራባሞን እንዲታሰር እና ስለ ክርስቶስ ፈጽሞ እንዳያስተምር በእስክንድርያው ገዢ አውጣኪያኖስ፡ ኮሞስ፡ ትዕዛዝ ተሰጠ።

ሰራባሞን ግን ከአቋሙ አልተናወጸም። ስለዚህ እስር ቤቱን አንዴ በታሕታይ ግብጽ አንዴ ደግሞ በላዕላይ ግብጽ በበረሃው ሁሉ በማፈራረቅ አሰቃዩት። እርሱ ግን ስቃዩንና ዛቻውን ከምንም ሳይቆጥር በእስር ቤት ውስጥም ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን አሳምኗል። የላዕላይ ግብፅ ገዢ የነበረው አርያኖስ (ከከሐዲው አርዮስ የተለየ እና የሀገረ እንጽና ገዢ የነበረ) ብዙ ካሠቃየው በኋላ በኒቅዩስ ከተማ ወደብ አቅራቢያ አንገቱን እንዲቆርጡት ትዕዛዝ ሰጠ። የሚጓዙበት መርከብ ግን አልንቀሳቀስም አለ። ቅዱስ ሰራባሞንን ከመርከቡ ሲያወርዱት በሰላም ሄዱ። በዚህ ሁኔታ እያለ እንኳን ወንጌልን መስበክና ትንቢት መናገርን አልተወም።

ይህ በእርሱ ላይ የሞት ውሳኔ የሰጠበት አርያኖስ በኋላ ዲዮቅልጥያኖስን ክዶ ክርስቲያን እንደሚሆን በመጨረሻም ሰማዕትነትን ተቀብሎ እንደሚሞት፣ እንዲሁም የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ጴጥሮስም በሰማዕትነት እንደሚሞትና “ተፍጻሜተ ሰማዕት” እንደሚሆን እንዲህ ብሎ ተንብዮአል፥ “ወበከመ፡ ጴጥሮስ፡ ቀዳማየ፡ እምሐዋርያት፡ ከማሁ፡ አንተኒ፡ ትከውን፡ ተፍጻሜተ፡ ሰማዕት። ናሁ፡ አቅደምኩ፡ ነጊሮተከ፡ ዘይከውን፡ በጊዜሁ።” (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 158)። እንደ ትንቢቱም ሁሉም ተፈጽሟል። በመጨረሻም ከሀገረ ስብከቱ ኒቅዩስ በስተደቡብ በምትገኘው ቦታ ወስደው ኅዳር 28 ቀን (በቅብጥ አቆጣጠር ሐቱር 28 ቀን) አንገቱን በሰይፍ ቀሉት።

ደቀመዛሙርቱ አስከሬኑን በመንገድ ላይ እንዳልባሌ ነገር ተጥሎ ሲያዩት በመረረ ሐዘን ተውጠው እያለቀሱ “እረኛችን ሆይ ለማን ታስጠብቀናለህ? አባታችን ሆይ እንግዲህ ማን ይሰበስበናል? አውሬ ከቦናል፣ በወንጌል ኮትኩተህ ያሳደግከው ተክልህን ከእንግዲህ ማን ይንከባከበው?” እያሉ መሪር እንባን ያነቡ ነበር። ከብዙ ለቅሶ በኋላ አስከሬኑን ወስደው በኒቅዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር አሳረፉት (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል166)።

ከገድሉ እንደምናነበው ሰራባሞን ባደረገው ተጋድሎና በጽንአቱ በርካታ የክብር ስሞችና ቅጽሎች ተሠጥተውታል። ዋና ዋናዎቹም፥ “ብፁዕ ወቅዱስ ሰማዕት”፣ “ለባሴ መንፈስ”፣ “ለባሴ፡ አምላክ”፣ “ዓምደ ቤተ ክርስቲያን”፣ “ሐረገ ወይን”፣ “ሐዲስ ዳንኤል”፣ “ላዕከ መንፈስ ቅዱስ”፣ “ሙሴ ሐዲስ”፣ “ጳውሎስ ዳግመ”፣ “ዮሐንስ ሐዲስ”፣ “መስተጋድል ዐቢይ” የሚሉት ናቸው።

በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በስሙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ታንጸዋል፣ ገድል ተጽፎለታል፣ በስንክሳርም ይዘከራል። ገድሉ እና የሰማዕትነቱ ዜና በቅብጥ እና ዐረብኛ ቋንቋ የተጻፈና የተተረጎመ ሲሆን ሁሉም ግን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ አልተገኘም። የቅብጡ ቅጂ በHyvernat, (ገጽ. 304-31) የታተመ ሲሆን የዐረብኛው ደግሞ (Kairo 27 በሚል ዝርዝር) በKraf (1934:12) ካታሎግ ተሠርቶለታል። በቅርቡ ደግሞ Youssef (2013: 263-280) የሚባል ተመራማሪ “ሰራባሞንን የሚመለከቱ የቤተ ክርስቲያን ምንባባት” ብሎ ጥናታዊ ጽሑፍ አውጥቷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያነ የቅዱስ ሰራባሞን ዜና ሕይወት እና ተጋድሎ እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን እምብዛም ጎልቶ የሚታወቅ ባይሆንም በሕዳር 28 ስንክሳር ይታወሳል። ከዚህም በላይ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገድሉ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በአቡነ መርሐ ክርስቶስ ዘመን (1408-1497) ተተርጉሞ ይገኛል። ይህም ገድል አሁን ከሚገኙት የቅብጥና ዐረብኛ ቅጂዎች ይልቅ የተሟላ እና ይዘቱም ሰፊ ነው። ይህ ገድል በ1970ዎቹ ውስጥ (EMML 6533) በሚል መለያ ማይክሮ ፊልም ተነስቷል።

ብራናው አጠቃላይ 168 ቅጠል ያለው ሲሆን ከመጀመሪያ እስከ 118 ድረስ የሐዋርያው ጳውሎስ ገድል፣ ከቅጠል 119-167 ድረስ ደግሞ የሰማዕቱ ሰራባሞንን ገድል ይዟል። የሰራባሞን ገድሉ አራት ክፍሎችን ይዟል፤ እነዚህም፥ 1) ድርሳን (ከቅጠል 119-131)፣ 2) ገድል (ከቅጠል135-142)፣ 3) ተአምር (ከቅጠል 132-149)፣ 4) ስምዕ (ከቅጠል 150-167) የሚሉ ናቸው። ይህም ስለ ሰራባሞን የሚጠናውን ጥናት ይበልጥ የተሟላ የሚያደርግና በተለይ ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ለዜና አበው እና ለነገረ ቅዱሳን የጥናት መስክ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። ከስንክሳሩና ከገድሉ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ሰራባሞን የተዘጋጁ ልዩ ልዩ አርኬዎች (Chaîne ቁ. 48 እና Wein፣ Athiop. 19 [በN.Rhodokanakis አማካይነት ካታሎግ የተሠራላቸው])፣ እንዲሁም ሁለት የተለያዩ መልክአት (Chaîne ቁ. 158 እና 325) ተዘጋጅተዋል። በኢትዮጵያው የገድል ቅጅ ላይ እስካሁን የተደረገ ጥናት የለም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ መነሻ ጥናት አድርጎ ገድሉንም እየተረጎመ ይገኛል።

ይህን ጽሑፍ የምንደመድመው በቪየና የሚገኘው ብራና (Vienna ms f.62v-63r) ስለ ቅዱስ ሰራባሞን ከሚያመሰግነው አርኬ ውስጥ አንዱን በማንበብ ይሆናል፤

ለከ፡ ስነ፡ ሰረባሞን፡ ዘኤፍራታ፤

ነጺሮሙ፡ ጥቀ፡ ለሕሊናሁ፡ ጥብዓታ፤

ከመ፡ ይከውን፡ ሰማዕት፡ ውስተ፡ ዓውደ፡ ግሩም፡ ሐተታ፤

ገደፈ፡ አብ፡ እጓሎ፡ ወእም፡ ወለታ፤

ወሐማትኒ፡ ሐደገት፡ መርዓታ።

የሰማዕቱ ሰራባሞን በረከት ይድረሰን!!!

ስምዓት

  • መጽሐፈ ስንክሳር – በግዕዝና በአማርኛ (ከመስከረም እስከ የካቲት)፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 1994 ዓ.ም.

  • ገድለ ጳውሎስ ወሰራባሞን – (EMML 6533)- ደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኝ፣ በ15ኛው መ/ክ/ዘ/ የተጻፈ ብራና (እስካሁን አልታተመም)።

  • Amsalu Tefera, 2013, “Gädlä Särabamon: the case of the Ethiopic version”, a paper read on a workshop titled “EMML@40: The Life and Legacy of the Ethiopian manuscript microfilm Library” organized by Hill Museum & Manuscript Library, Saint John’s University, Collegeville, MN, USA, July 25-26, 2013.

  • Budge, Wallis, 1928, The Book of the Saints of the Ethiopian Church: a translation of the Ethiopic Synaxarium መጽሐፈ፡ ስንክሳር፡ made from the manuscripts Oriental 660 and 661 in the British Museum, vol. I, Cambridge at the University Press.

  • Chaîne, M., 1912, “Catalogue des manuscrits Ethiopiens de la collection Antoine d’Abbadie”, Paris.

  • Chaîne, M., 1913, “Répertoire de salam et Melke’e contenus dans les manuscrits éthiopiens des bibliotheques d’Europe” in Revue de L’Orient Chrétien, , deuxieme Serie, Tome viii, no. 2

  • Colin, G. 1988, “Le Synaxaire Éthiopien mois de Ḫedār” in Patrologia Orientalis, Tome 44, fascicule3, no. 99)

  • Coptic Synaxarium, reading on Hatour 28, – retrieved online –http://popekirillos.net/EN/books/COPTSYNX.pdf, accessed on May 14, 2012.

  • Hayvernat, Henry, Les Actes des martyrs del’Égypte, retrieved online from http://www.archive.org.detailes/lesactesdesmarty01hyve – accessed on November 6, 2012.

  • Kraf, George, 1934, Catalogue de manuscrits Arabes Chrétiens conserves au Caire, studi e testi 63, Città del Vaticano Biblioteca Apostolica Vaticana

  • Rhodokanakis, N. 1906, Die Äthiopischen Handscriften der K. K. Hofbibliothek zu Wein, Wein Athiop. 19.

  • Youssef, 2013, “Liturgical Texts Relating to Sarapamon of Nikiu”, Peeters Online Journal, pp. 263-280.