jinka 01

በጂንካ ማእከል አበረታች ሐዋርያዊ አገልግሎት እየተከናወነ ነው

መስከረም 6 ቀን 2007 ዓ.ም.

jinka 01በደቡብ ኦሞ ጂንካ ሀገረ ስብከት በማኅበረ ቅዱሳን የጂንካ ማእከል እየታየ ያለው ሐዋርያዊ አገልግሎት አበረታች መሆኑን የማእከሉ ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ጌታቸው አስታወቁ፡፡

ከነሐሴ 29 ቀን እስከ ጳጉሜን 4 ቀን2006 ዓ.ም ዐሥር አባላት ያሉት የማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር የልኡካን ቡድን በጂንካ ማእከል በመገኘት በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ተወያይቷል፡፡ ልኡካን ድኑ በጂንካ ማእከል ድጋፍ የሚደረግላቸውን በሣልማ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ የአብነት ተማሪዎችንና በሸጲ ገይላ የሚገኘውን የ“ስብከት ኬላ” ጎብኝቷል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የጂንካ ማእከል ሰበሳቢ አቶ ዘለዓለም ጌታቸው የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት ማእከሉ በአካባቢው ቋንቋ ወንጌልን የሚያስተምሩ አገልጋዮችን ለማፍራት ሥልጠናዎችን ሠጥቷል፣ በአካባቢው የሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ደግፏል፣ አብያተ ክርስቲያናት ባልታነጹባቸው ገጠር ቀበሌዎች የ“ስብከት ኬላዎችን” በማቋቋም ትምህርተ ወንጌል ሠጥቷል፣ ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት የንዋያተ ቅዱሳት ድጋፍ አድርጓል፣ ለአብያተ ክርስቲያናት የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ የልማት ሥራዎችን ሠርቷል ሲሉ በመረጃዎች አስደግፈው ለልኡክ ቡድኑ የሠሯቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ማእከሉ ከሀገረ ስብከት፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ከመንፈሳውያን ማኅበራት ጋር በመተባበር ወደ ገጠሩ ክፍል ሐዋርያዊ ጉዞ እንደሚያደርግ የተናገሩት አቶ ዘለዓለም በዚህም አበረታች ለውጥ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለስብከተ ወንጌል ከቦታ ቦታ ስንዘዋወር “አስተምሩን፣ አጥምቁን፣ አስከሬናችን የእንሰት ማሳ ውስጥ ከሚቀበር ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶልን በተቀደሰ መሬት ላይ እንዲቀበር አድርጉ” በማለት ጥያቄ የሚያቀርቡ ኢአማንያን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት የማእከሉ የትምህርት ክፍል ተጠሪ ዲያቆን ፈቃዱ ብዙአየሁ ማእከሉ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ እና የቁሳቁሶች ችግር ስላለበት ፍላጎታቸውን ሙሉ በሙሉ ማሟላት አለመቻሉንም አስረድተዋል፡፡

በጂንካ ማእከል ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን የሚናገረው ዲ/ን ሀብታሙ ግዛው ዓይኑን፣ እግሩንና ኩላሊቱን ታማማ ሲሆን ሥራ ሠርቶ ራሱን መደገፍ አልተቻለውም፡፡ ነገር ግን ለወንጌል አገልግሎት ካለው ከፍተኛ ፍቅር የተነሣ በአካባቢው እየተዘዋወረ በቋንቋ በሚያስተምርበት ወቅት ማእከሉ ከጎኑ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በሠልማ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን 55 የአካባቢው ተወላጅ ልጆችን ሰብስበው የአብነት ትምህርት በማስተማር ላይ የሚገኙት ቄስ ብርሃኑ “ከቤተሰብ ርቄ ስኖር የዓይኔ ማረፊያዎች ተማሪዎቼ ናቸው” ብለዋል፡፡ አያይዘውም ተማሪዎች በቃለ እግዚአብሔር ታንጸው ለክህነት አገልግሎት እንዲበቁ የጂንካ ማእከል በቅርበት እየደገፋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጂንካ ማእከል ለሠልማ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ለተማሪዎች ማደሪያ ቤት የሚውል 25 ቆርቆሮ እና የጸሎት መጻሕፍት ድጋፍ ማድረጉን አቶ ዘለዓለም ጠቁመው፣ በቀጣይም ለካህናት 40 ቆርቆሮ የሚፈጅ የመኖሪያ ቤት ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር አስተባባሪ መጋቤ ሐዲስ አዲስ አለማየሁ እና የገቢ አሰባሳቢና የቅስቀሳ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ታደሰ ጌታሁን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ወንጌልን ማስተማር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ዓለም የላካቸው ወንጌልን እንዲሰብኩ ነው፡፡ የጂንካ ማእከልም የሐዋርያትን ፍኖት ተከትሎ እየሠራ ያለው ተግባር አበረታች ነው ብለዋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር አማካኝነት ለጂንካ ማእከል ከበጎ አድራጊ ምእመናን በ2006 ዓ.ም. የተገኘ አንድ ሞተር ሳይክል፤ በተጨማሪም ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉ ጀነሬተር፣ አምስት ድምፅ ማጉያ፣ አምስት ቴፕ፣ አልባሳትና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን መጋቤ ሐዲስ አዲስ ተናግረዋል፡፡

ቀሲስ ታደሰ ለዚህ የተቀደሰ አገልግሎት መሳካት ድጋፍ ያደረጉ በጎ አድራጊ ምእመናን እና በማኅበረ ቅዱሳን የጂንካ ማእከልን አመስግነው ተጠማቅያኑን በእምነት ለማጽናትና ተጨማሪ ኢአማንያንን ለማስጠመቅ ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ምእመናን በአካባቢው ቋንቋ ለሚያስተምሩ ቋሚ መምህራን በጀት እና ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር የሚውሉ ልዩ ልዩ ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 
የጂንካ ማእከል በ1989 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት 88 አባላት አሉት፡፡