gundagundi 02

ማኅበረ ቅዱሳን በትግራይ ሦስት ገዳማት የተገበራቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ

•ለፕሮጅክቶቹ ማስፈጸሚያ ከ3 ሚሊዮን 180 ሺሕ ብር በላይ ወጪ ሆኗል፡፡ 

ኅዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

gundagundi 02ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አማካይነት በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም፤ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ጽምባላ ወረዳ በአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ፤ በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳማት ያከናወናቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ፡፡

 

በተለያዩ ጊዜያት ተጀምረው የነበሩት እነዚህ ፕሮጅክቶች ከኅዳር 3/2007 ዓ.ም. – ኅዳር 8/2007 ዓ.ም. ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ፕሮጀክቶችን አስመርቆ ለየገዳማቱ አስረክቧል፡፡ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ፅብላ ወረዳ ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም የተመረቀው የአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ አንድነት ገዳም በ630 ሺሕ ብር የተሠራ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሲሆን፤ 150 ሺሕ ሊትር መያዝ ይችላል፡፡ ይህ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በገዳሙ ውስጥ ተገንብቶ በመጠናቀቁ ማኅበረ መነኮሳቱ የመጠጥ ውኃ ፍለጋ በቀን ከ4-5 ሰዓት በመጓዝ የሚባክንባቸውን የአገልግሎትና የጸሎት ጊዜያቸውን እንደሚያስቀርላቸው የገዳሙ አባቶች ተናግረዋል፡፡

abune tomas zehayda 02 1ገዳሙ ያለበትን ችግር በማጥናት የውኃ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ መንገዱ በጣም አስቸጋሪና ከ3-4 ሰዓት በእግር የሚያስኬድ በመሆኑ አባቶች በሸክም፤ እንዲሁም ግመሎችን በመጠቀም የግንባታ ቁሳቁስ በማመላለስ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተችሏል፡፡

ገዳሙ ጥንታዊና ገዳማዊ ቀኖና እና ሥርዓት ተጠብቆ የሚገኝበት ሲሆን፤ በርካታ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በማፍራትም ይታወቃል፡፡

gundagundi 03በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ደግሞ ለደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም የተገነባው ሁለገብ ሕንፃ ነው፡፡ ሁለገብ ሕንፃው በአዲግራት ከተማ የተገነባ ሲሆን፤ ለተለያየ አገልግሎት በማከራየት ገቢ ማስገኘት የሚችል ነው፡፡ ሕንፃው በብር 2,326,717.87 /ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሃያ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ ዐሥራ ሰባት ብር ከ87 ሣንቲም/ ተገንብቶ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡

ሕንፃው በ416.49 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ማኅበሩ የሠራው የምድሩን ወለል ብቻ ነው፡፡ መሠረቱ ባለ ሁለት ወለል ሕንፃን መሸከም እንዲችል ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ ቀሪውን የግንባታ ሥራ ገዳሙ ባቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ይገነባል፡፡

ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ቀድሞ በርካታ መነኮሳት የነበሩባት ቢሆንም በደርግ መንግሥት የነበራት ሰፊ ይዞታ በመነጠቋ የመነኮሳቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በችግር ምክንያት እየተመናመነ ሄዶ ሁለት መነኮሳት ብቻ ቀርተው ነበር፡፡ እነሱም በገዳሟ ውስጥ የሚገኙትን ንዋያተ ቅድሳትና በሌሎች ገዳማት የማይገኙ ቅዱሳት የብራና መጻሕፍትን ለማን ጥለን እንሔዳለን በማለት ችግሩን ተቋቁመው ዛሬ ድረስ ለመዝለቅ ችለዋል፡፡

ወደ ገዳሟ ለመድረስ መንገዱ አስቸጋሪና መኪና የማይገባ በመሆኑ የአንድ ቀን ሙሉ የእግር መንገድ መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ለመመለስም እንዲሁ የአንድ ቀን የእግር ጉዞ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
ገዳሟ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላት ሲሆን፤ የሁለገብ ሕንፃው መገንባት ችግሩን እንደሚቀርፍ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የመነኮሳቱ ቁጥር ከሁለት ወደ ሰባት ከፍ ለማለት ችሏል፡፡

dibo 02በተጨማሪም በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ማኅበሩ በብር 225,343.65 /ሁለት መቶ ሃያ አምስት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ሦስት ብር ከ65 ሣንቲም/ ተግባራዊ ያደረገውን የሽመና ውጤቶችን መሥሪያ አዳራሽ ሠርቶ በማጠናቀቅ፤ የሽመና ቁሳቁስ በማሟላት፤ እንዲሁም የልብስ ሥፌት መኪናዎችን ገዝቶ በማቅረብ ርክክብ ተደርጓል፡፡

የሽመና ፕሮጀክቱ ታሳቢ ያደረገው በገዳሟ ውስጥ ለሚገኙት መነኮሳይያት ሲሆን፤ መነኮሳይያቱ ቁጥራቸው ከፍ ያለ በመሆኑ የሽመና ውጤቶችን ማምረት ያስችላቸዋል፡፡

ደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ጥንታዊ ከሚባሉ ገዳማት መካከል የምትመደብ ስትሆን በውስጧም ጥንታዊ ሥዕላትን ጠብቃ ለትውልድ በማቆየት ትታወቃለች፡፡ ለትኅርምት እና ለጽሞና የምትመረጥም ገዳም ናት፡፡

ማኅበሩ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍሉ አማካይነት ለበርካታ ገዳማትና አድባራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግበር ገዳማት የልማት ሥራዎችን በመሥራት ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ ሲሆን፤ ሌሎች በጅምር ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል፡፡

 

 

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቀባበል ተደረገላቸው

 መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ 

ህዳር 09 ቀን 2007 ዓ.ም.

በ2007 ዓ.ም የጥቅምት ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ሥራ ለመጀመር ከሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች፣ ከአጥቢያ ገዳማትና አድባራት ሓላፊዎች፣ ጸሐፊዎችና ምእመናን ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡

 

ብጹዕነታቸው የሥራ መጀመሪያቸው ለሆነው የትውውቅ መርሐ ግብር ወደ ሀገረ ስብከታቸው ሲሔዱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት  ለጉባኤው ታዳሚዎች ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› በሚለው ቃለ ወንጌል የቅድስና ሥራ መሥራት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የፍቼ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስም ‹‹ለሁለት ጌታ፤ ለገንዘብና ለእግዚአብሔር መገዛት አንችልም፡፡ ለገንዘብ ስንገዛ የኖርንበትን ዘመን ትተን እስቲ ለእግዚአብሔር እንገዛ›› በማለት አባታዊ መልእክታቸውን ለጉባኤው ታዳሚ አስተላልፈዋል፡፡

 

አዲሱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስም  የሀገረ ስብከቱን ሠራተኞችንና ሌሎች የአጥቢያ ባለጉዳዮችን በጽ/ቤታቸው ብቻ እንደሚያስተናግዱ ገልጸዋል፡፡

 

                    ለብፁዕነታቸው መልካም የሥራ ዘመን እንመኛለን፡፡

 

 

jinka tim02 2

ከ2004- 2007 ዓ.ም. በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት 16,630 አዳዲስ አማንያን ተጠመቁ

 ኅዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

jinka tim02 2የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር ከ2004- 2007 ዓ.ም. 16,630 አዳዲስ አማንያንን በማስተማር መጠመቃቸውን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡

ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቅዳሴ ቤቱ ሲመረቅም በሀገረ ስብከቱ እና በማኅበረ ቅዱሳን አማካይነት የቀረቡትን 1350 አዳዲስ አማንያን በቅዱስነታቸው እና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተጠምቀው የሥላሴ ልጅነትን አግኝተዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት ቃለ ምእዳን “ይህ ቀን የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የተፈጸመበት ቀን ነው፡፡ የመድኀኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን ገንዘባችሁን፤ እውቀታችሁንና ጉልበታችሁን አስተባብራችሁ የሠራችሁበትና 1350 አዲስ ክርስቲያኖች የተጨመሩበት ቀን ስለሆነ ለቤተ ክርስቲናችን ታላቅ የደስታ ቀን ነው” ብለዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉኀን ወንድወሰን ገ/ሥላሴ የዕለቱን መርሐ ግብር ሲያስተዋውቁ ከ2004-2007 ዓ.ም. ድረስ ሀገረ ስብከቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል ጋር በመተባበር 16,630 አዳዲስ አማንያንን በማስተማር እንዲጠመቁ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑም ከታቀደለት ጊዜ በፊት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

jinka tim02 1የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጀማል ዑመር /ዐምደ ሚካኤል/ ባቀረቡት ሪፖርት የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ሥራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እገዛ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያኑን ዲዛይን በተመለከተም ሲገልጹ “የወንጌል አርበኞች የሆኑት የማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል አባላት የቤተ ክርስቲያኑን ዲዛይን በነጻ በመሥራት እገዛ አድርገዋል” ብለዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

jebera 01

የጀበራ ማርያም አንድነት ገዳምን ዳግም ለማቋቋም ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

jebera 01በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በደምቢያ ወረዳ በጣና ሐይቅ ውስጥ በ1335 ዓ.ም. ተገድማ የነበረችው የጀበራ ማርያም አንድነት ገዳም ከፈረሰች ከበርካታ ዘመናት በኋላ ዳግም ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገዳሙን መልሶ ለማቋቋም በማስተባበር ላይ የሚገኙት አባ ዘወንጌል ገለጹ፡፡

አባ ዘወንጌል ከ23 ዓመታት በፊት በዚሁ ገዳም ውስጥ በጸሎት ከሚተጉ አባቶች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን፤ ወደ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም በመሄድ በአገልግሎት ሲተጉ ቆይተዋል፡፡ በ2005 ዓ.ም. “የአባቶቼ ርስት እንዴት ቆይታ ይሆን?” በማለት አባቶችን ለመጎብኘት ወደ ቦታው ሲያቀኑ ቤተ ክርስቲያኗ ፈርሳ፤ አባቶችና እናቶች በርካቶቹ አርፈው፤ ገሚሶቹ ተሰደው ሁለት አባቶች ብቻ በእርግና ምክንያት የሚጦራቸው አጥተው በችግር ውስጥ እንዳሉ ይደርሳሉ፡፡

በሁኔታው የተደናገጡት አባ ዘወንጌል ከጣና ሐይቅ ማዶ ያሉትን ነዋሪዎች በመቀስቀስ፤ በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር ገዳሟን እንደገና ጥንት ወደነበችበት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ኮሚቴ በማዋቀር ከበጎ አድራጊ ምእመናን በተገኘ ድጋፍም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኗን በማስገንባት ላይ ሲሆኑ፤ በገዳሟ ውስጥም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ15 በላይ መናንያን ተሰባስበውባት በጸሎትና በአገልግሎት በመፋጠን ገዳሟን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

jebera 02በስድስት ወራት ውስጥ የተጀመረው ግንባታም በመፋጠን ላይ ሲሆን፤ ሠርቶ ለማጠናቀቅም በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ የጣሪያ ቆርቆሮ፤ የበር፤ የመስኮት፤ የቤተ መቅደስ፤ የማጠናቀቂያ ሥራዎችና ሌሎችም ስለሚቀሩት በባለሙያዎች ተጠንቶ 1.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያስፈልገውና ይህንን ለማሟላት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በችግር ውስጥ እንደሚገኝ አባ ዘወንጌል ገልጸዋል፡፡ በጎ አድራጊ ምእመናንም ገዳሟ ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በ14ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት አባ በረከተ አልፋ በተባሉ አባት ተገድማ እንደ ነበረች የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱ የገለጹት አባ ዘወንጌል፤ ገዳሟ በርካታ መናንያንን ስታስተናግድ የኖረች በመሆኗ በገዳማዊ ሕይወታቸውና በትሩፋታቸው ከልዑል እግዚአብሔር በረከትን ያገኙ አባቶችና እናቶች የኖሩባትና ጸሎት ሲያደርሱ የእጆቻቸው ጣቶች እንደ ፋና ያበሩ ስለነበር የአካባበቢው ነዋሪዎች “እጀበራዎች” እያሉ ይጠሯቸው ስለነበር ገዳሟ “ጀበራ” የሚለውን ስያሜ ማግኘቷን ይናገራሉ፡፡

ገዳሟ በድርቡሽ ወረራ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የጣና ገዳማት መካከል አንዷ ስትሆን ገዳማውያኑም በመሰደዳቸው እስከ 1956 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ ፈርሳ ቆይታለች፡፡ በ1956 ዓ.ም መምህር ካሳ ፈንታ በተባሉ አባት ዳግም ተመሥርታ ብትቆይም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በማረፋቸው ገዳሟን የሚንከባከብ በመጥፋቱ ገዳማውያኑም ወደ ተለያዩ ገዳማት ተበተኑ፡፡ ተሠርታ የነበረቸው መቃኞም በምስጥ ተበልታ ፈረሰች::

sami.02.07

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጸሎተ ምኅላ ተጀመረ

ጥቅምት 11 ቀን 2007ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ ጥቅምት 11ቀን 2007ዓ.ም. ከቀኑ ዐሥር ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎተ ምኅላ ተጀመረ፡፡

 

       sami.02.07

የጥቅምት 2007 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  ከጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የሚካሔድ ሲሆን በዚህ ጉበኤ ሐዋርያት  እኛና መንፈስ ቅዱስ   ወስነናል እያሉ ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ውሳኔ ይወስኑ እንደነበር፤ የሐዋርያት አምላክና መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ ረድቷቸው፣ በርደተ መንፈስ ቅዱስ ወቅት   ከሐዋርያት ያልተለየች እመቤታችን  ሳትለያቸው  ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ውሳኔዎችን ያስተላልፋሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡

sami01

ቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትሥርዓተ ጸሎትና ፍትሐት ተፈጸመላቸው

ጥቅምት 10 ቀን 2007 ዓ.ም.

ይብረሁ ይጥና

  • የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖትርያርክ የመታሰቢያ ሐውልትም ተመርቋል፡፡

sami01ከአጸደ ሥጋ ዓለም በሞት ተለይተው በአጸደ ነፍስ የሚገኙ ቅዱሳን ፓትርያኮችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ተደረገላቸው፡፡ ሥርዓተ ጸሎተ ፍትሐቱ በተለይ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳትን እንዲሁም ቤተክርስቲያንን አገልግለው ያለፉ አበው የታሰቡበትና በረከታቸው በአጸደ ሥጋ ላለነው እንዲደርስ ጸሎት የተደረገበት ነው፡፡

 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዕለቱ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “አባቶቻችን ርእሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን አደራ ጠብቀው በሚችሉት አቅም ሊሠሩት የሚገባውን ሁሉ ሠርተው አልፈዋል፡፡ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀውና ሃይማኖትን አጽንተው በማቆየት ለእኛ አስተላልፈዋል” ብለዋል፡፡

 

sami04ቅዱስነታቸው አያይዘውም “እናትና አባትህን አክብር የሚለውን የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በዚህ ቦታ ተገኝተናል በመንፈስ ወልደውና በምግባር አሳድገው ለዚህ ስላበቁን እነሱን ማክበርና ማስታወስ ግዴታችን ነው፡፡ ስለሆነም ይህ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ የሚመሰገን ነው፡፡” በማለት ቀደምት የቤተክርስቲያን አበውን መዘከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ “ሰው በዚህ ዓለም ይሞታል፤ የማይሞተው ግን የሠራው ሥራ ነው፤ ለሰው ሐውልቱ ሥራው ነው ስለሆነም ዛሬ የዘከርናቸው እንደነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ቴዎፍሎስ፣ ተክለ ሃይማኖትና ጳውሎስ ስማቸው ሕያው ነው፡፡ ብለዋል፡፡

 

sami03በዚሁ እለት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የመታሰቢያ ሐውልት ተመርቋል፡፡ የመታሰቢያ ሐውልቱ የተሠራው በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያና ትዕዛዝ ሲሆን፤ ወጭውን ደግሞ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሸፈኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አስታውቀዋል፡፡ 

 

ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ስለ ሐውልቱ መሠራት ሲገልጹ “የቅዱስ አባታችን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐውልት በዚህ ቦታ የተተከለው ለመታሰቢያነት እንጂ ሐውልታቸው በሕይወተ ሥጋ ሳሉ በመላው ኢትዮጵያ የሠሩት ሥራ ነው፡፡

 

በዚህም ዘለዓለም ሲታሰብ ይኖራል፡፡ ሰው በታላቅነቱና በሠራው ሥራ ሲታወስ ይኖራል፤ እኒህ ታላቅ አባትም በዚህ ስፍራ የቆመው ሐውልት ለመታሰቢያነት እንጂ ሐውልታቸው በሔዱበት ቦታ ሁሉ የሠሩት ሥራ ነው፡፡ ” ብለዋል፡፡

 

በዕለቱ የቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሥርዐተ ጸሎተ ፍትሐትና የመታሰቢያ ሐውልት ምርቃት መርሐ ግብር ቅዱስ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ኤልሳ የሰሜን ጐንደር ሊቀ ጳጳስ ትምህርት ፣ የመርካቶ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳንም፤ ቅዱሳን ፓትርያኮችና ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚታሰቡበትን እለት በየዓመቱ እንደሚያደርገው ሁሉ “ዝክረ አበው” በማለት በጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የእራት ግብዣ አድርጓል፡፡ 

33 9 2007 01

የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ባለ 21 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

 ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

33 9 2007 01 የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማጠቃለያ መርሐ ግብር የተጀመረው ከረፋዱ 2፡46 ነበር፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርክ አቡነ ማትያስ ጉባኤውን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ ከምንጊዜውም በላይ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት፣ መጠበቅ እንደሚገባ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

33.02.2007.02በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሦስት ቀናት በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት እንዲደረግ ጋብዘዋል፡፡ ሆኖም ግን ቅዱስ ፓትርያርኩ በጉባኤው መክፈቻ ዕለት ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ ብቻ ሰፊና ጠንካራ ውይይቶች ተደርጓል፡፡

የጉባኤው ማጠቃለያ በመጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር ቃለ ጉባኤ ተነቦ ባለ 21 ነጥብ የአቋም መግለጫ ተነቧል፡፡ ከቃለ ጉባኤው ንባብ ለመረዳትም እንደተቻለው ማኅበረ ቅዱሳን በበጀት ዓመቱ በበርካታ ሀገረ ስብከቶች በከፍተኛ ደረጃ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መደገፉ ተወስቷል፡፡

33.2007.03በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ በልማት፣ ዓመታዊ ገቢ በስብከተ ወንጌል፣ በመልካም አስተዳደር የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸውን ሀገረ ስብከቶች ደረጃ በማውጣት  ሽልማት ተበርክቶለቸዋል፡፡ሽልማቶቹም የሕዳሴው ግድብ ቦንድ ግዢ፣ መጻሕፍት፣ የቃለ ዓዋዲ መጽሐፍ ተሸልመዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ለ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ቃለ ምእዳንና መመሪያ በመስጠት ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

33 8 2007

የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን ሪፖርት አደመጠ፡፡

ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

  • የማኅበረ ቅዱሳን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በየሀገረ ስብከቶቹ በሪፖርት ቀርቧል፡፡

ሦስተኛ ቀኑን የጠናቀቀው የ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችና ሪፖርት አድምጦ አጠናቋል፡፡

33 8 2007ሪፖርት አቅራቢ ሥራ አስኪያጆችና የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በ2006 ዓ.ም የሥራ ዘመን ክንውን ሪፖርታቸውን የጉባኤው ታዳሚዎች ሲያቀርቡ የሪፖርቱ ይዘት ጉባኤውን በሐሴት እንዲሞላ፣ አንገት እንዲደፋና የዕንባ ዘለላ እንዲወርድ ያደረገ ነበር፡፡

ጉባኤው በሐሴት የተሞላባቸው ሪፖርቶች በርካታ ሀገረ ስብከቶች በልማት ሥራዎች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸው፡፡

ዘመናዊ የመልካም አስተዳደርና ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር ግንዛቤ አየጨመረ መምጣቱ፡፡

በጠረፋማ አካባቢ የሚገኙ ሀገረ ስብከቶች የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት በማጠናከር በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜጎችን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን እንዲቀላቀሉ ያደረጉ መሆናቸው፡፡

የቅርስና ንዋያተ ቅዱሳት አያያዝን በተመለከተ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ የቅርስና ንዋያተ ቅድሳት አያያዝና አጠባበቅ የተሻለ መሆኑ የተዘገበ ሲሆን አንዳንድ ሀገረ ስብከቶችም የተዘረፉ ቅርሶችን በማስመለስ ቅርሶቹ በክብር እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡

33 8 2007 3ዓመታዊ ገቢ ማሳደግን በተመለከተ በርካታ ሀገረ ስብከቶች ካለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት ማሳየት መዘገቡ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ለነዚህ አገልግሎቶች ስኬታነት የማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበርና በሥልጠና፣ በስብከተ ወንጌል፣ በሕንፃ ዲዛይን በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤት ድጋፍ ወዘተ የተደረገው ድጋፍ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በተለይ በተደረገ ሥልጠና አንዳንድ ሀገረ ስብከቶች የሀገረ ስብከቶች ዓመታዊ ገቢያቸው የሥራ ተነሳሽነታቸው መጨመሩም በሪፖርቱ ተወስቷል፡፡

ጉባኤውን ያሳዘነና ያስለቀሰ ለቀጣዩ የአገልግሎት ዘመን በትጋት ለመሥራት ቁጭት የፈጠረው

  • የቤተ ክርስቲያን አባላት ቁጥር መቀነስ

  • የተሐድሶ እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ረቅቆ የቤተ ክርስቲያኒቷን መዋቅር በመጠቀም ሥርዓተ አምልኮዋን ቀኖና ሥርዓቷን ለማጥፋት የሚደረገው ቅሰጣና ሁከት መፍጠር፡፡

  • የቤተ ክርስቲያኒቱ አንዳንድ አገልጋዮች በንብረትና ቅርስ ዘረፋ ላይ ተሰማርተው መገኘት፡፡

  • የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች በሙስና ተግባር ላር ተሰማርተው በመገኘታቸው የቤተ ክርስቲያንን መልካም ስም ያጎደፈ፣ ምእመናንን አንገት ያስደፋና ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲወጡ ምክንያት እንደነበር ተወስቷል፡፡

33 8 2007  2ጥቅምት 6 ቀን 2007 ዓ.ም እና ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ትምህርተ ወንጌል በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርተ ወንጌል የጉባኤው ታዳሚ ስለ እናት ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ እንዲያስብ፣ እንዲሠራ፣ እንዲተጋ ያሳሰበ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስም በተለይ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ስውር ተልዕኮ ተረድቶ ቤተ ክርስቲያኒቷን እንዲጠብቅ የሚያሳስብ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ጥቅምት 9 ቀን የጠዋት ውሎ በቀረቡት ሪፓርቶች ላይ ውይይት ተደርጎ የአቋም መግለጫ ከቀረበ በኋላ የሽልማትና የምሥጋና መርሐ ግብራት ከተከናወነ በኋላ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምእዳንና መመሪያ የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ይጠናቀቃል፡፡

 

 

ማኅበረ ቅዱሳን የጠራው የ”አጋርነት መግለጫ” መርሐ ግብር የለም!

ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

እሑድ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 2007 ዓ.ም ማኅበረ ቅዱሳን እየደረሰበት ያለውን ክስ በመቃወም ለማኅበሩ ያለንን አጋርነት እንግለጽ በሚል ባልታወቁ አካላት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተጠራውን መርሐ ግብር አስመልክቶ፤ ማኅበሩ መርሐ ግብሩ እንዲደረግ ጥሪ ያላቀረበ መኾኑንና ስለጠራውም አካል ምንም ዓይነት ዕውቀት እንደሌለው የማኅበሩን ሕዝብ ግንኙነት በመጥቀስ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ማኅበሩ የሰጠውን አጭር መግለጫ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

 

ሰሞኑን በማኅበራችን ላይ የሚሰነዘሩ ክሶችና ስም የማጥፋት ቅስቀሳዎች እንዳሉ የሚሸሸግ አይደለም፡፡ በመሠረቱ ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ፈቃድ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ታቅፎ አገልግሎቱን በይፋ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያየ ዓላማ ካላቸው አካላት እንደማኅበር ያልተሰጠው መጥፎ ስም፣ የአገልግሎት ጉዞውም ያልተቀባው ጥላሸት የለም፡፡ ይሁን እንጂ በሚያጋጥመው ፈተና ሁሉ ከመዳከም ይልቅ ብርታትን እያገኘ፣ በእግዚአብሔር ኃይል፣በአበው ጸሎትና ምክር የአገልግሎት አድማሱን ከጊዜ ወደጊዜ እያሰፋ በመሄድ ማንም በጎ ኅሊና ያለው ሁሉ ሊመሰክረው የሚችል መጠነ ሰፊ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፤ ዛሬም በመስጠት ላይ ይገኛል፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነገም አገልግሎቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ስለኾነም ማኅበሩ ሰሞኑን የሚሰሙትን ክሶች ከወትሮው የተለዩ አድርጎ ሳይመለከት እነዚህን ተቋቁሞ በሚያልፍበት መንገድ ላይ እየሠራ፣ ስለቀጣይ አገልግሎቱም እየመከረ ይገኛል፡፡

 

በዚህም መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ባለፉት ቀናት በማኅበሩ ላይ የተሰነዘሩበትን የሐሰት ክሶች አጣርቶ በአገልግሎት ጉዞው ላይ ያጋጠሙትን ወቅታዊ ችግሮች እንዲፈታለት በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ ለጥያቄውም ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ከሚጀምረው መደበኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መልስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም አባላቱን ሰብስቦ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል በአንድነት ያቆመ አምላክ ለማኅበሩ ከሳሾች ልቡና እንዲሰጥ እግዚአብሔር ቤተክርስያንንና የማኅበሩን አገልግሎት ከአጽራረ ቤተክርስቲያን እንዲጠብቅ እንደማኅበር አብዝቶ በመጸለይ ላይ ይገኛል፡፡

 

የማኅበሩ ወቅታዊ እንቅስቃሴና ዐቋም ይህ ኾኖ ሳለ፤ እሑድ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚደረገው ዓመታዊ ዝክረ አበው የጸሎት መርሐ ግብር ላይ «ታላቅ አገር አቀፍ የማኅበረ ቅዱሳን አጋርነት መርሐ ግብር» ባልታወቁ አካላት እንደተጠራ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን በማኅበራችን ላይ እየተሰነዘሩ ባሉ መሠረተ ቢስ ክሶች ማኅበራችን ያዘነ ቢኾንም፤ ጉዳዩን አስመልክቶ አባቶች በተቀደሰ ጉባኤያቸው ተወያይተው መፍትሔ ይሰጡ ዘንድ በልጅነት ትሕትና አቤቱታ ከማቅረብ ያለፈ የተጠቀሰውን ጉባኤ እንዳልጠራና ስለጠራው አካል ማንነትም ምንም ዓይነት ዕውቀት እንደሌለው በአክብሮት ይገልጻል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ማኅበረ ቅዱሳን

 

ማኅበረ ቅዱሳን የጠራው ሰልፍ እንደሌለ አስታወቀ

ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም.

በተለያዩና ባልታወቁ አካላት ለማኅበሩ አጋርነት ለማሳየት በመጪው እሑድ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰልፍ ለማድረግ በማኅበራዊ ሚዲያው የሚሽከረከረውን አስመልክቶ ከአባላቱ ለቀረበለት ጥያቄ የሚያውቀው ነገር እንደሌለና ማኅበሩም ምንም ዓይነት ጥሪም እንዳላካሔደ የማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አስታወቀ፡፡

ማኅበሩ በአገልግሎቱ ሂደት ላይ ፈተናዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች እያጋጠሙት እንደሆነ ባይሸሽግም ችግሮቹን ለመፍታት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በአድራሻና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በግልባጭ አመልክቶ ውሳኔውን መጪው ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሚጀምረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እየተጠባበቀ ከመሆኑ በቀር ምንም ዓይነት ጉባኤም ሆነ ሰልፍ አለመጥራቱን አስታውቋል፡፡

ማኅበሩ ገጽታውን ለማበላሸት ሆን ብለው በሐሰት ስሙን የሚያጠፉትን ግለሰቦች በሕግ እንደሚጠይቅ ማሳወቁም የሚታወስ ነው፡፡