sami.02.07

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጸሎተ ምኅላ ተጀመረ

ጥቅምት 11 ቀን 2007ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ ጥቅምት 11ቀን 2007ዓ.ም. ከቀኑ ዐሥር ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎተ ምኅላ ተጀመረ፡፡

 

       sami.02.07

የጥቅምት 2007 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  ከጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የሚካሔድ ሲሆን በዚህ ጉበኤ ሐዋርያት  እኛና መንፈስ ቅዱስ   ወስነናል እያሉ ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ውሳኔ ይወስኑ እንደነበር፤ የሐዋርያት አምላክና መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ ረድቷቸው፣ በርደተ መንፈስ ቅዱስ ወቅት   ከሐዋርያት ያልተለየች እመቤታችን  ሳትለያቸው  ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ውሳኔዎችን ያስተላልፋሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡

sami01

ቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትሥርዓተ ጸሎትና ፍትሐት ተፈጸመላቸው

ጥቅምት 10 ቀን 2007 ዓ.ም.

ይብረሁ ይጥና

  • የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖትርያርክ የመታሰቢያ ሐውልትም ተመርቋል፡፡

sami01ከአጸደ ሥጋ ዓለም በሞት ተለይተው በአጸደ ነፍስ የሚገኙ ቅዱሳን ፓትርያኮችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ተደረገላቸው፡፡ ሥርዓተ ጸሎተ ፍትሐቱ በተለይ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳትን እንዲሁም ቤተክርስቲያንን አገልግለው ያለፉ አበው የታሰቡበትና በረከታቸው በአጸደ ሥጋ ላለነው እንዲደርስ ጸሎት የተደረገበት ነው፡፡

 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዕለቱ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “አባቶቻችን ርእሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን አደራ ጠብቀው በሚችሉት አቅም ሊሠሩት የሚገባውን ሁሉ ሠርተው አልፈዋል፡፡ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀውና ሃይማኖትን አጽንተው በማቆየት ለእኛ አስተላልፈዋል” ብለዋል፡፡

 

sami04ቅዱስነታቸው አያይዘውም “እናትና አባትህን አክብር የሚለውን የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በዚህ ቦታ ተገኝተናል በመንፈስ ወልደውና በምግባር አሳድገው ለዚህ ስላበቁን እነሱን ማክበርና ማስታወስ ግዴታችን ነው፡፡ ስለሆነም ይህ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ የሚመሰገን ነው፡፡” በማለት ቀደምት የቤተክርስቲያን አበውን መዘከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ “ሰው በዚህ ዓለም ይሞታል፤ የማይሞተው ግን የሠራው ሥራ ነው፤ ለሰው ሐውልቱ ሥራው ነው ስለሆነም ዛሬ የዘከርናቸው እንደነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ቴዎፍሎስ፣ ተክለ ሃይማኖትና ጳውሎስ ስማቸው ሕያው ነው፡፡ ብለዋል፡፡

 

sami03በዚሁ እለት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የመታሰቢያ ሐውልት ተመርቋል፡፡ የመታሰቢያ ሐውልቱ የተሠራው በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያና ትዕዛዝ ሲሆን፤ ወጭውን ደግሞ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሸፈኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አስታውቀዋል፡፡ 

 

ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ስለ ሐውልቱ መሠራት ሲገልጹ “የቅዱስ አባታችን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐውልት በዚህ ቦታ የተተከለው ለመታሰቢያነት እንጂ ሐውልታቸው በሕይወተ ሥጋ ሳሉ በመላው ኢትዮጵያ የሠሩት ሥራ ነው፡፡

 

በዚህም ዘለዓለም ሲታሰብ ይኖራል፡፡ ሰው በታላቅነቱና በሠራው ሥራ ሲታወስ ይኖራል፤ እኒህ ታላቅ አባትም በዚህ ስፍራ የቆመው ሐውልት ለመታሰቢያነት እንጂ ሐውልታቸው በሔዱበት ቦታ ሁሉ የሠሩት ሥራ ነው፡፡ ” ብለዋል፡፡

 

በዕለቱ የቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሥርዐተ ጸሎተ ፍትሐትና የመታሰቢያ ሐውልት ምርቃት መርሐ ግብር ቅዱስ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ኤልሳ የሰሜን ጐንደር ሊቀ ጳጳስ ትምህርት ፣ የመርካቶ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳንም፤ ቅዱሳን ፓትርያኮችና ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚታሰቡበትን እለት በየዓመቱ እንደሚያደርገው ሁሉ “ዝክረ አበው” በማለት በጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የእራት ግብዣ አድርጓል፡፡ 

33 9 2007 01

የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ባለ 21 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

 ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

33 9 2007 01 የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማጠቃለያ መርሐ ግብር የተጀመረው ከረፋዱ 2፡46 ነበር፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርክ አቡነ ማትያስ ጉባኤውን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ ከምንጊዜውም በላይ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት፣ መጠበቅ እንደሚገባ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

33.02.2007.02በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሦስት ቀናት በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት እንዲደረግ ጋብዘዋል፡፡ ሆኖም ግን ቅዱስ ፓትርያርኩ በጉባኤው መክፈቻ ዕለት ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ ብቻ ሰፊና ጠንካራ ውይይቶች ተደርጓል፡፡

የጉባኤው ማጠቃለያ በመጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር ቃለ ጉባኤ ተነቦ ባለ 21 ነጥብ የአቋም መግለጫ ተነቧል፡፡ ከቃለ ጉባኤው ንባብ ለመረዳትም እንደተቻለው ማኅበረ ቅዱሳን በበጀት ዓመቱ በበርካታ ሀገረ ስብከቶች በከፍተኛ ደረጃ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መደገፉ ተወስቷል፡፡

33.2007.03በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ በልማት፣ ዓመታዊ ገቢ በስብከተ ወንጌል፣ በመልካም አስተዳደር የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸውን ሀገረ ስብከቶች ደረጃ በማውጣት  ሽልማት ተበርክቶለቸዋል፡፡ሽልማቶቹም የሕዳሴው ግድብ ቦንድ ግዢ፣ መጻሕፍት፣ የቃለ ዓዋዲ መጽሐፍ ተሸልመዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ለ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ቃለ ምእዳንና መመሪያ በመስጠት ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

33 8 2007

የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን ሪፖርት አደመጠ፡፡

ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

  • የማኅበረ ቅዱሳን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በየሀገረ ስብከቶቹ በሪፖርት ቀርቧል፡፡

ሦስተኛ ቀኑን የጠናቀቀው የ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችና ሪፖርት አድምጦ አጠናቋል፡፡

33 8 2007ሪፖርት አቅራቢ ሥራ አስኪያጆችና የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በ2006 ዓ.ም የሥራ ዘመን ክንውን ሪፖርታቸውን የጉባኤው ታዳሚዎች ሲያቀርቡ የሪፖርቱ ይዘት ጉባኤውን በሐሴት እንዲሞላ፣ አንገት እንዲደፋና የዕንባ ዘለላ እንዲወርድ ያደረገ ነበር፡፡

ጉባኤው በሐሴት የተሞላባቸው ሪፖርቶች በርካታ ሀገረ ስብከቶች በልማት ሥራዎች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸው፡፡

ዘመናዊ የመልካም አስተዳደርና ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር ግንዛቤ አየጨመረ መምጣቱ፡፡

በጠረፋማ አካባቢ የሚገኙ ሀገረ ስብከቶች የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት በማጠናከር በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜጎችን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን እንዲቀላቀሉ ያደረጉ መሆናቸው፡፡

የቅርስና ንዋያተ ቅዱሳት አያያዝን በተመለከተ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ የቅርስና ንዋያተ ቅድሳት አያያዝና አጠባበቅ የተሻለ መሆኑ የተዘገበ ሲሆን አንዳንድ ሀገረ ስብከቶችም የተዘረፉ ቅርሶችን በማስመለስ ቅርሶቹ በክብር እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡

33 8 2007 3ዓመታዊ ገቢ ማሳደግን በተመለከተ በርካታ ሀገረ ስብከቶች ካለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት ማሳየት መዘገቡ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ለነዚህ አገልግሎቶች ስኬታነት የማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበርና በሥልጠና፣ በስብከተ ወንጌል፣ በሕንፃ ዲዛይን በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤት ድጋፍ ወዘተ የተደረገው ድጋፍ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በተለይ በተደረገ ሥልጠና አንዳንድ ሀገረ ስብከቶች የሀገረ ስብከቶች ዓመታዊ ገቢያቸው የሥራ ተነሳሽነታቸው መጨመሩም በሪፖርቱ ተወስቷል፡፡

ጉባኤውን ያሳዘነና ያስለቀሰ ለቀጣዩ የአገልግሎት ዘመን በትጋት ለመሥራት ቁጭት የፈጠረው

  • የቤተ ክርስቲያን አባላት ቁጥር መቀነስ

  • የተሐድሶ እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ረቅቆ የቤተ ክርስቲያኒቷን መዋቅር በመጠቀም ሥርዓተ አምልኮዋን ቀኖና ሥርዓቷን ለማጥፋት የሚደረገው ቅሰጣና ሁከት መፍጠር፡፡

  • የቤተ ክርስቲያኒቱ አንዳንድ አገልጋዮች በንብረትና ቅርስ ዘረፋ ላይ ተሰማርተው መገኘት፡፡

  • የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች በሙስና ተግባር ላር ተሰማርተው በመገኘታቸው የቤተ ክርስቲያንን መልካም ስም ያጎደፈ፣ ምእመናንን አንገት ያስደፋና ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲወጡ ምክንያት እንደነበር ተወስቷል፡፡

33 8 2007  2ጥቅምት 6 ቀን 2007 ዓ.ም እና ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ትምህርተ ወንጌል በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርተ ወንጌል የጉባኤው ታዳሚ ስለ እናት ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ እንዲያስብ፣ እንዲሠራ፣ እንዲተጋ ያሳሰበ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስም በተለይ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ስውር ተልዕኮ ተረድቶ ቤተ ክርስቲያኒቷን እንዲጠብቅ የሚያሳስብ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ጥቅምት 9 ቀን የጠዋት ውሎ በቀረቡት ሪፓርቶች ላይ ውይይት ተደርጎ የአቋም መግለጫ ከቀረበ በኋላ የሽልማትና የምሥጋና መርሐ ግብራት ከተከናወነ በኋላ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምእዳንና መመሪያ የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ይጠናቀቃል፡፡

 

 

ማኅበረ ቅዱሳን የጠራው የ”አጋርነት መግለጫ” መርሐ ግብር የለም!

ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

እሑድ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 2007 ዓ.ም ማኅበረ ቅዱሳን እየደረሰበት ያለውን ክስ በመቃወም ለማኅበሩ ያለንን አጋርነት እንግለጽ በሚል ባልታወቁ አካላት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተጠራውን መርሐ ግብር አስመልክቶ፤ ማኅበሩ መርሐ ግብሩ እንዲደረግ ጥሪ ያላቀረበ መኾኑንና ስለጠራውም አካል ምንም ዓይነት ዕውቀት እንደሌለው የማኅበሩን ሕዝብ ግንኙነት በመጥቀስ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ማኅበሩ የሰጠውን አጭር መግለጫ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

 

ሰሞኑን በማኅበራችን ላይ የሚሰነዘሩ ክሶችና ስም የማጥፋት ቅስቀሳዎች እንዳሉ የሚሸሸግ አይደለም፡፡ በመሠረቱ ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ፈቃድ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ታቅፎ አገልግሎቱን በይፋ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያየ ዓላማ ካላቸው አካላት እንደማኅበር ያልተሰጠው መጥፎ ስም፣ የአገልግሎት ጉዞውም ያልተቀባው ጥላሸት የለም፡፡ ይሁን እንጂ በሚያጋጥመው ፈተና ሁሉ ከመዳከም ይልቅ ብርታትን እያገኘ፣ በእግዚአብሔር ኃይል፣በአበው ጸሎትና ምክር የአገልግሎት አድማሱን ከጊዜ ወደጊዜ እያሰፋ በመሄድ ማንም በጎ ኅሊና ያለው ሁሉ ሊመሰክረው የሚችል መጠነ ሰፊ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፤ ዛሬም በመስጠት ላይ ይገኛል፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነገም አገልግሎቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ስለኾነም ማኅበሩ ሰሞኑን የሚሰሙትን ክሶች ከወትሮው የተለዩ አድርጎ ሳይመለከት እነዚህን ተቋቁሞ በሚያልፍበት መንገድ ላይ እየሠራ፣ ስለቀጣይ አገልግሎቱም እየመከረ ይገኛል፡፡

 

በዚህም መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ባለፉት ቀናት በማኅበሩ ላይ የተሰነዘሩበትን የሐሰት ክሶች አጣርቶ በአገልግሎት ጉዞው ላይ ያጋጠሙትን ወቅታዊ ችግሮች እንዲፈታለት በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ ለጥያቄውም ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ከሚጀምረው መደበኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መልስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም አባላቱን ሰብስቦ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል በአንድነት ያቆመ አምላክ ለማኅበሩ ከሳሾች ልቡና እንዲሰጥ እግዚአብሔር ቤተክርስያንንና የማኅበሩን አገልግሎት ከአጽራረ ቤተክርስቲያን እንዲጠብቅ እንደማኅበር አብዝቶ በመጸለይ ላይ ይገኛል፡፡

 

የማኅበሩ ወቅታዊ እንቅስቃሴና ዐቋም ይህ ኾኖ ሳለ፤ እሑድ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚደረገው ዓመታዊ ዝክረ አበው የጸሎት መርሐ ግብር ላይ «ታላቅ አገር አቀፍ የማኅበረ ቅዱሳን አጋርነት መርሐ ግብር» ባልታወቁ አካላት እንደተጠራ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን በማኅበራችን ላይ እየተሰነዘሩ ባሉ መሠረተ ቢስ ክሶች ማኅበራችን ያዘነ ቢኾንም፤ ጉዳዩን አስመልክቶ አባቶች በተቀደሰ ጉባኤያቸው ተወያይተው መፍትሔ ይሰጡ ዘንድ በልጅነት ትሕትና አቤቱታ ከማቅረብ ያለፈ የተጠቀሰውን ጉባኤ እንዳልጠራና ስለጠራው አካል ማንነትም ምንም ዓይነት ዕውቀት እንደሌለው በአክብሮት ይገልጻል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ማኅበረ ቅዱሳን

 

ማኅበረ ቅዱሳን የጠራው ሰልፍ እንደሌለ አስታወቀ

ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም.

በተለያዩና ባልታወቁ አካላት ለማኅበሩ አጋርነት ለማሳየት በመጪው እሑድ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰልፍ ለማድረግ በማኅበራዊ ሚዲያው የሚሽከረከረውን አስመልክቶ ከአባላቱ ለቀረበለት ጥያቄ የሚያውቀው ነገር እንደሌለና ማኅበሩም ምንም ዓይነት ጥሪም እንዳላካሔደ የማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አስታወቀ፡፡

ማኅበሩ በአገልግሎቱ ሂደት ላይ ፈተናዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች እያጋጠሙት እንደሆነ ባይሸሽግም ችግሮቹን ለመፍታት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በአድራሻና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በግልባጭ አመልክቶ ውሳኔውን መጪው ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሚጀምረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እየተጠባበቀ ከመሆኑ በቀር ምንም ዓይነት ጉባኤም ሆነ ሰልፍ አለመጥራቱን አስታውቋል፡፡

ማኅበሩ ገጽታውን ለማበላሸት ሆን ብለው በሐሰት ስሙን የሚያጠፉትን ግለሰቦች በሕግ እንደሚጠይቅ ማሳወቁም የሚታወስ ነው፡፡

 

33 2007 3

33ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሦስተኛ ቀን ውሎ

ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

የ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን የ2006 ዓ.ም. የሥራ ክንውን ሪፖርት አደመጠ፡፡

33 2007 3ሦስተኛ ቀኑን የያዘው ይህ ጉባኤ በሀገረ ስብከቶች አማካኝነት የቀረበውን ሪፖርቶች ያደመጠ ሲሆን በአብዛኛው የሀገረ ስብከቶች ሪፖርት ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን የሚያደርገውን ሁለገብ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን በሪፖርቶቹ የቀረቡ ሲሆን የጉባኤው ታዳሚም አድናቆቱን በጭብጨባ ገልጿል፡፡

በመርሐ ግብሩ መሠረት በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት ሊደረግ የነበረ ቢሆንም በጊዜ መጣበብ ምክንያት በተያዘው መርሐ ግብር ያልተካሔደ ሲሆን በጉባኤው ማጠቃለያ ዕለት ነገ ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ውይይቱ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

33 2nd 2 1

33ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው እንደቀጠለ ነው፡፡

ጥቅምት 6 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 5 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም የተጀመረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቀጥሏል፡፡ በጥቅምት 5 ቀን የከሰዓት ውሎና ጥቅምት 6 ቀን ጠዋት 24 አህጉረ ስብከቶች ሪፓርቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡

ከቀረቡት ሪፓርቶች በዋናነት ትኩረት የሳቡት

  • ለልማት ሥራ ትኩረት መሰጠቱ

  • አዳዲስ አማንያንን ማጥመቃቸው (ከእናት ቤተ ክርስቲያን የወጡትን የከፋ ቦንጋ ሀገረ ስብከት ብቻ ሪፓርት ቢያደርግም)

  • የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴን መጠናከር

  • ሕገ ወጥ ሰባኪያንን እና አጥማቅያንን መቆጣጠር

  • ክህነት የማይገባቸው አላግባብ ክህነት መቀበል ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተግዳሮት መሆን

  • የቅርስና ንብረት ዘረፋ

  • በየሀገረ ስብከቶቹ ሪፓርት ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን እየሰጠ ያለው መንፈሳዊ አገልግሎት ከተነሱት ዋና ዋና የሥራ ፍሬዎች ናቸው፡፡

ከቀረቡት ሪፓርቶች መካከል ማሳሰቢያ የተሰጠባቸው

33 2nd 2 1ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት፡-

“…መስቀል በዓል አከባበር በዮኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንደተመዘገበ ሁሉ የመስቀሉ ማኅደር የሆነችው ግሸን ደብረ ከርቤም በዮኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንድትመዘገብ ጥረት እንዲደረግ፣…”

 

 

33 2nd 2 2ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት፡-

“…የክርስቲያን ተደላ ደስታ በመንግሥተ ሰማይ ነው፤ ለሥጋ ተድላ ሲባል ያለ አግባብ ሥልጣነ ክህነት መቀበልና የቤተ ክርስቲያንን ሀብት መመዝበር አምላካዊ ፍርድን ይጠብቃል…”

ማኅበረ ቅዱሳን በ2006 ዓ.ም ከ13,948,984.71 በላይ ወጪ በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ደገፈ

ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

በ33ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ባቀረቡት ሪፖርትና በዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት 6ኛ ዓመት ቁጥር 10 ጥቅምት 2007 ዓ.ም ላይ በተገለጸው ሪፖርት ውስጥ የማኅበረ ቅዱሳን የ2006 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ከነጻ ሞያ አገልግሎት ውጭ ከ13,948.984.7 /አሥራ ሦስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ዐርባ ስምንት ሺሕ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ዐራት ብር/ በላይ ወጪ በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት መደገፉ ተገልጿል፡፡

ዋና ዋና ድጋፍ ያደረገባቸው ሀገረ ስብከቶች

ማኅበረ ቅዱሳን በበጀት ዓመቱ ለደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ ለምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት፣ ለደብረ ከዋክብት ጉንዳጉንዶ ገዳም፣ ለሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ አቡነ ቶማስ ገዳም ለውኃ ታንከር፣ ለዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ለምዕመናን መቀመጫ ወንበር ለመግዛት ብር 8,139,847.36 /ስምንት ሚሊዮን አንድ መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ሺሕ ስምንት መቶ ዐርባ ሰባ ብር ከሠላሳ ዘጠኝ ሣንቲም ወጪ በማድረግ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ደግፏል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ አህጉረ ስብከት ለሚገነቡ የአብነት ት/ቤቶችና የካህናት ማሠልጠኛዎች እንዲሁም ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች ድጎማና አህጉረ ስብከት ለሚያካሒዷቸው ሥልጠናዎች መደጎሚያ፣ ለምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ግንባታ ብር 11,034,334.00/ አሥራ አንድ ሚሊየን ሠላሳ ዐራት ሺሕ ሦስት መቶ ሠላሳ አራት ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ማኅበሩ በሙያ ደረጃ ለ35 አብያተ ክርስቲያናት የዲዛይን ሥራ ከተለያዩ አህጉረ ስብከት ለመጡ 15 የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች የነጻ የሕግ ምክር አገልግሎት የሰጠ ሲሆን ከተለያዩ አህጉረ ስብከት ለተጠየቀ 10 የልማት ሥራዎች ፕሮጀክት ጥናት በነጻ ተጠንቶ ለጠያቂዎቹ ተሰጥቷል፡፡ በኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ አውታሮች አማካኝነት በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ሰፊ ትምህርት የሰጠ ሲሆን 671,000.00 /ስድስት መቶ ሰባ አንድ ሺሕ/ ሐመርና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በበጀት ዓመቱ አሰራጭቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች በድረ ገጽ ትምህርታዊ ዝግጅቶች እንዲተላለፉ አድርጓል፡፡

ማኅበሩ በበጀት ዓመቱ በ341 የመንግሥትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኙ 200,000 /ሁለት መቶ ሺሕ/ ኦርቶዶክሳዊ ተማሪዎች ተከታታይ ኮርስ ሰጥቷቸዋል፡፡ በ2006 በጀት ዓመትም 14,847,657.82 /አሥራ አራት ሚሊዮን ስምንት መቶ አርባ ሰባ ሺሕ ስድስት መቶ ሃምሳ ሰባ ብር ከሰማንያ አራት ብር ከሰባ አንድ ሣንቲም ወጪ በማድረግ 848,675.11/ ስምንት መቶ አርባ ስምንት ሺሕ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ብር ከአሥራ አንድ ሣንቲም/ በልዩነት ተመዝግቧል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን

  • የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ሁለገብ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት በብር 4,599,645.00 /አራት ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺሕ ስድስት መቶ ዐርባ አምስት ብር/ ወጪ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡

  • የደብረ ካስዋ ጉንዳጉንዶ ገዳም ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ዓዲግራት ከተላ ላይ በብር 2,614,431.36 /ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ አሥራ ዐራት ሺሕ ዐራት መቶ ሠላሳ አንድ ብር ከሰላሣ ስድስት ሣንቲም/ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡

  • ሰሜን ምዕራብ ትግራይ /ሽሬ/ አቡነ ቶማስ ገዳም 150 ሺሕ ሊትር ውኃ መያዝ የሚችል ውኃ ታንከር በብር 672,822.00 /ስድስት መቶ ሰባ ሁለት ሺሕ ስምንት መቶ ሃያ ሁለት ብር/ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

  • ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን 64 ተማሪዎችን መቀበልና ማስተናገድ የሚችል የአብነት ትምህርት መማሪያ እና ማደሪያ ከነሙሉ መገልገያው በብር 2,950,380.00 /ሁለት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ሺሕ ሦስት መቶ ሰማንያ ብር/ ተሠርቶ እና ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

  • በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት አርባ ምንጭ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን 100 ተማሪዎችን መቀበልና እና መያዝ የሚችል ማሰልጠኛ በብር 1,666,378.00 /አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ሺሕ ሦስት መቶ ሰባ ስምንት ብር/ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

  • ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በጎንደር በዓታ የአቋቋም ትምህርት ቤት በብር 5,981,132.00 /አምስት ሚሊዮን ብር/ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

  • በተለያዩ አህጉረ ስብከት 160 የአብነት ት/ቤቶች ለሚገኙ 171 የአብነት መምህራን እና 993 የአብነት ተማሪዎች ከ1,800,000.00 /አንድ ሚሊየን ስምንት መቶ ሺሕ ብር/ በላይ ወጪ ለማዳን ድጎማ ተደርጓል፡፡

  • ከተለያዩ አህጉረ ስብከት ለተጠየቁ የ35 አብያተ ክርስቲያናት የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ዲዛይን ሥራ በነጻ በመሥራት አብያተ ክርስቲያናቱ ሊያወጡ የነበረው ብር 840,000.00 /ስምንት መቶ ዐርባ ሺሕ ብር/ ወጪን ለማዳን ተችሏል፡፡

  • ሀገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ አህጉረ ስብከት ከ150 በላይ የሕዝብ ጉባኤያት እና በሰሜን አሜሪካ 5 የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት ተደርጎ በርካታ ምእመናን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲያገኙ ሆኗል፡፡

  • ከሚመለከታቸው አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ፈቃድና ከየአህጉረ ስብከት ጋር በመተባበር ለ10 ቀናት የቆየ ሐዋርያዊ ጉዞ ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ /አፋር፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ድሬዳዋ እና ሶማሌ አህጉረ ስብከት/ ተደርጓል፡፡

  • ስብከተ ወንጌል ያልተስፋፋባቸውን ጠረፋማ አካባቢዎች በመለየት እና ፕሮጀክት በመቅረጽ ስብከተ ወንጌል የማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን በተሰጠው አገልግሎት ከአህጉረ ስብከት ጋር በመተባበር 4396 ምእመናን ተጠምቀው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ለመሆን በቅተዋል፡፡

  • በሀገሪቱ ባሉት የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ላሉ ኦርቶዶክሳዊያን ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ትውፊትና ነገረ ሃይማኖት ለማወቅ የሚያስችላቸውንና በሥራ ሲሠማሩ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል መነሻ የሚሆናቸውን ትምህርት በካሪኩለም በማካተት ተከታታይነት ያለው የኮርስ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል፡፡

33 2007 3

33ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተጀመረ

ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

33 2007 3በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ 33ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በስብከተ ወንጌል አዳራሽ የተጀመረው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መሪነት ጸሎተ ኪዳን ተደርሶ “ወንድምህ ቢበድልህ ምከረው፣ ይቅር በለው” የሚለው የማቴ.18፡15 ከተነበበ በኋላ ነው፡፡

ከጸሎተ ቡራኬው በመቀጠል የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጣዕመ ዝማሬ አሰምተዋል፡፡

33 2007 2ከዝማሬው በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የመምሪያ ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ከሀገር ቤትና ከሀገር ውጭ ለመጡት የ33ኛው መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ከአስተላለፉ በኋላ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቡነ ማቴዎስ ጋባዥነት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የጉባኤውን መከፈት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ትኩረት ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል፡-

  • በቤተ ክርስቲያን ስላለው የመልካም አስተዳደር እጦት

  • የምእመናን ቁጥር መቀነስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን

  • የሕገወጥ የሰው ልጆች ዝውውር

  • በአፍሪካ ስለተከሰው በሽታ አሳሳቢነትና አደገኛነት

  • በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚገኙ ማኅበራት አስመልክቶ ለጉባኤው ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከቅዱስ ፓትርያርኩ መግለጫ በመቀጠል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ለ33ኛው የሰበካ33 2007 1 መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የ2006 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ሪፓርት አቅርበዋል፡፡

 

ለ4 ቀናት በሚቆየው ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኝ ሀገረ ስብከቶች ሪፓርታቸውን አቅርበው ከጨረሱ በኋላ በቀረቡት ሪፓርቶች መነሻነት ውይይት ይደረጋል፡፡

እንደ መርሐ ግብሩ መሠረት በጉባኤው መጨረሻ ቀን ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. የጋራ መግለጫ ተነቦ የሽልማትና የምስጋና መርሐ ግብር ከተከናወነ በኋላ በቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቃለ ምእዳንና መመሪያ ተሰጥቶ፣ የእራት ግብዣ ከተደረገ በኋላ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ይጠናቀቃል፡፡

33 2007 4እሑድ ጠዋት ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአጸደ ነፍስ ለሚገኙ ቅዱሳን ፓትርያርኮችና ሊቃነ ጳጳሳት የመታሰቢያ ጸሎተ ፍትሐትና ቅዳሴ ይከናወናል፡፡

በዕለቱ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ የፓትርያርኮችና ሊቃነ ጳጳሳት መታሰቢያ “ዝክረ አበው” በሚል ርእስ በማኅበረ ቅዱሳን የመታሰቢያ እራት ይደረጋል፡፡ከጥቅምት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ይካሔዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡