“ቄስ” ገዳሙ ደምሳሽ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተለዩ

ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም

በዲ/ን ፍቃዱ ዓለሙ

በኑፋቄ ትምህርታቸው ምእመናንን ሲቀስጡና የማኅበረ ካህናቱንና ምእመናኑን አንድነት ሲጎዱ የቆዩት “ቄስ” ገዳሙ ደምሳሽ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ከቅስናና ከቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት እንዲሁም ከማንኛውም ክህነታዊ አገልግሎትና ትምህርተ ወንጌል ከመስጠት ታገዱ፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ ሰኔ 18 ቀን 2006 ዓ.ም ውሳኔውን ያስተላለፈው ግለሰቡ ግልጽ ባልኾነ ሁኔታ የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ኾነው ከመቀመጣቸው በፊት ወደ ፕሮቴስታንት የእምነት ተቋም ሔደው በቆዩባቸው ጊዜያት ጽፈው ያሳተሟቸው መጻሕፍት ይዘት በሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር ካደረገ በኋላ መኾኑ በመግለጫው ታትቷል፡፡

 

በተጨማሪም ግልጽ ባልኾነ ሁኔታ ተመልሰዋል ተብሎ በሀገረ ጀርመን ካሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በኾነው ቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሾሙም በኋላ በልዩ ልዩ የጀርመን ግዛቶች እየተዘዋወሩ ሲያስተምሩ የነበረውን ፀረ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በመቃወም በየጊዜው ከምእመናንና ካህናት የተላኩትን አቤቱታዎች እንደመረመረ መግለጫው ያብራራል፡፡

 

በሊቃውንት ጉባኤው ምርመራ መሠረት ጽሑፎቻቸው ግለሰቡ “የቤተ ክርስቲያናችንን የአብነት ትምህርት በውል ያልተማሩና ምሥጢራትን ያልተረዱ መኾናቸውን” የሚያሳዩ ከመኾናቸው በላይ የተሳሳቱና ኦርቶዶክሳዊ ያልኾኑ የኑፋቄ አስተምህሮዎችን የያዙ ናቸው፡፡ በመኾኑም እነዚህ መጻሕፍት በማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እንዳይሠራጩና ለማስተማሪያነትም እንዳይቀርቡ ታዝዟል፡፡ ይህ በቅዱስ ሲኖዶስ ተላልፎ ለደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የተላከው ውሳኔ መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም በፍራክፈርት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ ሰብሳቢነት በተደረገ አጠቃላይ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች ስብሰባ በውሳኔው የተለዩት ግለሰብም ባሉበት በንባብ መሰማቱን፤ በዚህም ወቅት ግለሰቡ ጉባኤውን ረግጠው መውጣታቸውን መግለጫው ያትታል፡፡ 

 

እኒህ ሰው በሀገረ ጀርመን ሲፈጠሯቸው የነበሩ ችግሮችን አስመልክቶ ከቦታው በሚደርሱን መረጃዎች በመመሥረት በኅትመቶቻችን ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ዝርዝር በሚቀጥለው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ እናቀርባለን፡፡

 

33 Sebeka Gubae

33ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሊካሄድ ነው፡፡

ጥቅምት 4 ቀን 2007 ዓ.ም.

 በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 33ኛው መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 5-8 ቀን 2007 ዓም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ይካሄዳል፡፡

33 Sebeka Gubaeበመንፈሳዊ ጉባኤው ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ተመድበው ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ የሚገኙ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የየሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

sewasew 1

ማኅበረ ቅዱሳን ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ 90 ሺሕ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

sewasew 1

ማኅበረ ቅዱሳን ለአንጋፋውና የሊቃውንት መፍለቂያ ለሆነው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ 90 ሺሕ ብር የሚያወጡ ኮምፒዩተሮች፤ ፕሪንተሮችና መጻሕፍት ጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለኮሌጁ ደቀመዛሙርት አገልግሎት እንዲውል ድጋፍ አደረገ፡፡

ማኅበሩ ከኮሌጁ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት የኮሌጁን ደቀመዛሙርት እውቀት ለማሳደግ የሚያስችሉ ግምታቸው 90 ሺሕ ብር የሚደርሱ 12 ኮምፒተሮች፤ 2 ፕሪንተሮች፤ እንዲሁም ማኅበረ ቅዱሳን በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ያሳተማቸውን 184 መጻሕፍት በኮሌጁ አዳራሽ ርክክብ አድርጓል፡፡

በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊና የኮሌጁ ዋና ዲን ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ማኅበሩ ያደረገውን ድጋፍ አስመልከቶ ሲገልጹ “ኮሌጁ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ያፈራ ነው፡፡ ዛሬም sewasew 2በማፍራት ላይ ቢገኝም በርካታ ችግሮች አሉበት፡፤ በዚህም መሠረት ደቀዛሙርቱ ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር ለማገናኘትና ከኢንተርኔት አጠቃቀም አንጻር ያለባቸውን ክፍተት ለመፍታት ለማኅበረ ቅዱሳን ባቀረብነው ጥያቄ መሠረት የኮምፒዩተሮችና የመጻሕፍት ድጋፍ በማድረጉ በመላው የኮሌጁ ማኅበረሰብና ደቀመዛሙርት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ማኅበሩ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ እሰየሠጠ ካለው አገልግሎት አንጻር ወደፊት ተጨማሪ ድጋፎችንም እንደሚያደርግልን ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ በበኩላቸው ኮምፒዩተሮችና መጻሕፍቱን ካስረከቡ በኋላ እንደገለጹት “ማኅበሩ ከኮሌጁ በተጠየቀው መሠረት ማድረግ ከሚችለው ውስጥ ትንሹን ነው ያደረገው፡፡ ወደፊትም ኮሌጁ በሚያስፈልገው፤ ማኅበሩ ደግሞ በሚችለው መጠን ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል፡፡

በኮሌጁ ውስጥ ከሚገኙት ሊቃውንት መካከል መምህር ሃይማኖት ኃይለ ማርያም ማኅበሩ ባደረገው ድጋፍ በሰጡት አስተያየት “የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ማድረግ መልካም ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመሆናቸው የቤተ ክርስቲያንን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ነው የሰጡት፡፡ ሌሎችም ማኅበሩን አርአያ አድርገው ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል” በማለት ገልጸዋል፡፡

በኮሌጁ መምህራን የተዘጋጁ መጻሕፍትም ለማኅበረ ቅዱሳን ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲውሉ በመምህራኑ አቅራቢነት፤ በኮሌጁ ዲን አማካይነት ለማኅበረ ቅዱሳን ተበርክቷል፡:

  

jima 2007 3

የጅማ ሀገረ ስብከት ሁለገብ ዘመናዊ ሕንፃ ተመረቀ

መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

jima 2007 3የጅማ ሀገረ ስብከት ያስገነባው ባለ 5 ፎቅ ሁለገብ ዘመናዊ ሕንፃ መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅዱስ ፓትርያርኩና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ተመረቀ፡፡

jima 2007ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎችና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ክፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን የጅማ ሀገረ ስብከት ከሃያ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ አራት ሺሕ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን ባለ አምስት ፎቅ ዘመናዊ ሁለገብ ሕንፃ ባርከው ሲመርቁ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ይህ ሁለገብ ዘመናዊ ሕንፃ በጣም የሚያስደንቅና ለቤተ ክርስቲያናችን ተጨማሪ ሀብት መሆን የቻለ ነው፡፡ ለሌሎች ሀገረ ስብከቶችም ታላቅ ምሳሌና በአርአያነቱም ተጠቃሽ የሚሆን ነው” ብለዋል፡፡

የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ባቀረቡት ሪፖርትም በጅማ ሀገረ ስብከት 308 አብያተ ክርስቲያናት እንደሚገኙና፤ የዚህ ሕንፃ መገንባት ዋነኛ ዓላማ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አብያተ ክርስቲያናት በካህናትና በበጀት እጥረት jima 2007 2ምክንያት የተቸገሩ በመሆናቸው ሕንፃው ተከራይቶ በሚያስገኘው ገቢ እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት በመደገፍ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ለማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ዝርዝሩን እንደደረሰልን እናቀርባለን፡፡

 

meskel 001

በመስቀል በዓል መጨመር ወይም መቀነስ የሌለበት የትኛው ነው?

 መስከረም 20 ቀን 2006 ዓ.ም.

በዲ/ን ፍቃዱ ዓለሙ

meskel 001የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ታሪካዊት እንደ መሆኗ፣ ሁሉም ሃይማታዊ በዓላት ከመንፈሳዊ ባህላዊ ሥርዓቶች ጋር ተሣሥረው እንዲከበሩ መሠረት ናት፡፡ ለዚህ ነው ከሀገራዊና ከሃይማታዊ በዓላት ጋር ተያይዘው የሚከናወኑት መንፈሳዊና ባሕላዊ ሥርዓቶች ምንጫቸው/መነሻቸው/ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ናት የምንለው፡፡ ቀድሞም በኦሪቱ በኋላም በሐዲሱ ሕግጋት ጸንታ የቆየች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ ተዟዙራ አስተምራለች፡፡ ለመስቀሉም ሆነ ለሌሎች ሃይማታዊ በዓላት መነሻቸው የቀደሙት አባቶቻችን ከ4ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የዘሩት የወንጌል ዘር ነው፡፡

ለዕንቁጣጣሽ (ዐዲስ ዓመት)፣ ለልደት፣ ለጥምቀት እና ለፋሲካ በዓላት ብቻ ሳይሆን ለመስቀል በዓልም ባህላዊ መሠረቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የመስቀል በዓልን የተመለከትን እንደሆነ በሰሜኑ፣ በደቡቡ፣ በምሥራቁ፣ የሀገራችን ክፍሎች የሚከናወኑት ማናቸውም ባህላዊ ሥርዓቶች መሠረታቸው ፍጹም ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ይህም ከላይ እንደተገለጠው የቀድሞ አባቶቻችን በዐራቱም የኢትዮጵያ መዓዝናት እየተዘዋወሩ ወንጌልን የመስበካቸው ውጤት ነው፡፡

የመስቀል በዓል በማይታዩ ወይም በማይዳሰሱ ቅርሶች በዓለም አቀፍ ቅርስነት በዩኔስኮ ከተመዘገበ እነሆ አንድ ዓመት ሞላው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመሆን ይህን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ በዓል በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ስታስመዘግብ ከዚህ በፊት በበዓሉ ላይ ሲከናወኑ የነበሩ ሃይማታዊና መንፈሳዊ ባህላዊ ሥርዓቶችን አካታ ነው፡፡ የቀነሰችው ወይም የጨመረችው አንዳችም ምዕራባዊ ባዕድ ነገር የለም፡፡

meskel 002በዓሉን ስናከብርም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በማጉላት ሊሆን ይገባል፡፡ በስመ ዓለማቀፋዊነት ከሃይማኖታዊና ከባህላዊ ሥርዓቶች ውጭ ያሉትን እንደ ርችት መተኮስ፣ ጭፈራና ጩኸት ያሉ ሰርጎ ገብ ድርጊቶችን ወይም ልማዶችን መተው ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ድርጊቶች የበዓሉን ሃይማኖታዊ ይዘት ከመሸርሸራቸው ባለፈ የሀገራችንንም መልካም ገጽታ ስለሚያጎድፉ ነው፡፡

ባዕድ ልማዶችን ከመከላከል አንጻር ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ብዙ ይጠበቃል፡፡ በበዓሉ ቀን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ሀገራችን የሚጎርፉ ቱሪስቶች /ጎብኝዎች/ የኛ የሆነውን ሥርዓት እንጂ እነርሱ የሰለቻቸውን ለማየት አይመጡምና ነው፡፡ ስለዚህ በዓሉን አስመልክቶ በሚቀርቡ ትርኢቶች ላይ የውጭው ዓለም የባሕል ተፅዕኖ እንዳያድርብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡meskel 003

ይልቁንስ በብዙ ምእመናን ዘንድ የሚዘወተሩ ለምሳሌ የደመራውን አመድ በትእምርተ መስቀል አምሳል ግንባር ላይ መቀባት፣ ትርኳሹን ወደ ቤት መውሰድ፣ በዕለቱ ከወዳጅ ከዘመድ ጋር መሰባሰብን የመሳሰሉ ከእናት አባቶቻችን የወረስናቸው መንፈሳዊ ድርጊቶች ሊበረታቱና ሊቀጥሉ ይገባል፡፡

ለወደፊትም የበዓሉን ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ይዘት ሊያዳክሙ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይከሰቱ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የምንኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች እና ምእመናን እንደ ባለቤት በጋራ በመሆን ለመስቀል በዓል ሥርዓት መጠበቅ የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባናል፡፡ ባሕላዊው የበዓል አከባበር ሥርዓት ለሃይማታዊው የበዓል አከባበር ሥርዓት መገለጫ ነው እንጅ የሚጨመር ወይም የሚቀነስ ሥርዓት አይኖረውም፡፡