ማኅበረ ቅዱሳን በ2006 ዓ.ም ከ13,948,984.71 በላይ ወጪ በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ደገፈ

ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

በ33ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ባቀረቡት ሪፖርትና በዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት 6ኛ ዓመት ቁጥር 10 ጥቅምት 2007 ዓ.ም ላይ በተገለጸው ሪፖርት ውስጥ የማኅበረ ቅዱሳን የ2006 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ከነጻ ሞያ አገልግሎት ውጭ ከ13,948.984.7 /አሥራ ሦስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ዐርባ ስምንት ሺሕ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ዐራት ብር/ በላይ ወጪ በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት መደገፉ ተገልጿል፡፡

ዋና ዋና ድጋፍ ያደረገባቸው ሀገረ ስብከቶች

ማኅበረ ቅዱሳን በበጀት ዓመቱ ለደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ ለምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት፣ ለደብረ ከዋክብት ጉንዳጉንዶ ገዳም፣ ለሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ አቡነ ቶማስ ገዳም ለውኃ ታንከር፣ ለዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ለምዕመናን መቀመጫ ወንበር ለመግዛት ብር 8,139,847.36 /ስምንት ሚሊዮን አንድ መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ሺሕ ስምንት መቶ ዐርባ ሰባ ብር ከሠላሳ ዘጠኝ ሣንቲም ወጪ በማድረግ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ደግፏል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ አህጉረ ስብከት ለሚገነቡ የአብነት ት/ቤቶችና የካህናት ማሠልጠኛዎች እንዲሁም ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች ድጎማና አህጉረ ስብከት ለሚያካሒዷቸው ሥልጠናዎች መደጎሚያ፣ ለምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ግንባታ ብር 11,034,334.00/ አሥራ አንድ ሚሊየን ሠላሳ ዐራት ሺሕ ሦስት መቶ ሠላሳ አራት ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ማኅበሩ በሙያ ደረጃ ለ35 አብያተ ክርስቲያናት የዲዛይን ሥራ ከተለያዩ አህጉረ ስብከት ለመጡ 15 የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች የነጻ የሕግ ምክር አገልግሎት የሰጠ ሲሆን ከተለያዩ አህጉረ ስብከት ለተጠየቀ 10 የልማት ሥራዎች ፕሮጀክት ጥናት በነጻ ተጠንቶ ለጠያቂዎቹ ተሰጥቷል፡፡ በኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ አውታሮች አማካኝነት በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ሰፊ ትምህርት የሰጠ ሲሆን 671,000.00 /ስድስት መቶ ሰባ አንድ ሺሕ/ ሐመርና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በበጀት ዓመቱ አሰራጭቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች በድረ ገጽ ትምህርታዊ ዝግጅቶች እንዲተላለፉ አድርጓል፡፡

ማኅበሩ በበጀት ዓመቱ በ341 የመንግሥትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኙ 200,000 /ሁለት መቶ ሺሕ/ ኦርቶዶክሳዊ ተማሪዎች ተከታታይ ኮርስ ሰጥቷቸዋል፡፡ በ2006 በጀት ዓመትም 14,847,657.82 /አሥራ አራት ሚሊዮን ስምንት መቶ አርባ ሰባ ሺሕ ስድስት መቶ ሃምሳ ሰባ ብር ከሰማንያ አራት ብር ከሰባ አንድ ሣንቲም ወጪ በማድረግ 848,675.11/ ስምንት መቶ አርባ ስምንት ሺሕ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ብር ከአሥራ አንድ ሣንቲም/ በልዩነት ተመዝግቧል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን

 • የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ሁለገብ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት በብር 4,599,645.00 /አራት ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺሕ ስድስት መቶ ዐርባ አምስት ብር/ ወጪ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡

 • የደብረ ካስዋ ጉንዳጉንዶ ገዳም ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ዓዲግራት ከተላ ላይ በብር 2,614,431.36 /ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ አሥራ ዐራት ሺሕ ዐራት መቶ ሠላሳ አንድ ብር ከሰላሣ ስድስት ሣንቲም/ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡

 • ሰሜን ምዕራብ ትግራይ /ሽሬ/ አቡነ ቶማስ ገዳም 150 ሺሕ ሊትር ውኃ መያዝ የሚችል ውኃ ታንከር በብር 672,822.00 /ስድስት መቶ ሰባ ሁለት ሺሕ ስምንት መቶ ሃያ ሁለት ብር/ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

 • ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን 64 ተማሪዎችን መቀበልና ማስተናገድ የሚችል የአብነት ትምህርት መማሪያ እና ማደሪያ ከነሙሉ መገልገያው በብር 2,950,380.00 /ሁለት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ሺሕ ሦስት መቶ ሰማንያ ብር/ ተሠርቶ እና ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

 • በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት አርባ ምንጭ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን 100 ተማሪዎችን መቀበልና እና መያዝ የሚችል ማሰልጠኛ በብር 1,666,378.00 /አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ሺሕ ሦስት መቶ ሰባ ስምንት ብር/ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

 • ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በጎንደር በዓታ የአቋቋም ትምህርት ቤት በብር 5,981,132.00 /አምስት ሚሊዮን ብር/ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

 • በተለያዩ አህጉረ ስብከት 160 የአብነት ት/ቤቶች ለሚገኙ 171 የአብነት መምህራን እና 993 የአብነት ተማሪዎች ከ1,800,000.00 /አንድ ሚሊየን ስምንት መቶ ሺሕ ብር/ በላይ ወጪ ለማዳን ድጎማ ተደርጓል፡፡

 • ከተለያዩ አህጉረ ስብከት ለተጠየቁ የ35 አብያተ ክርስቲያናት የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ዲዛይን ሥራ በነጻ በመሥራት አብያተ ክርስቲያናቱ ሊያወጡ የነበረው ብር 840,000.00 /ስምንት መቶ ዐርባ ሺሕ ብር/ ወጪን ለማዳን ተችሏል፡፡

 • ሀገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ አህጉረ ስብከት ከ150 በላይ የሕዝብ ጉባኤያት እና በሰሜን አሜሪካ 5 የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት ተደርጎ በርካታ ምእመናን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲያገኙ ሆኗል፡፡

 • ከሚመለከታቸው አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ፈቃድና ከየአህጉረ ስብከት ጋር በመተባበር ለ10 ቀናት የቆየ ሐዋርያዊ ጉዞ ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ /አፋር፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ድሬዳዋ እና ሶማሌ አህጉረ ስብከት/ ተደርጓል፡፡

 • ስብከተ ወንጌል ያልተስፋፋባቸውን ጠረፋማ አካባቢዎች በመለየት እና ፕሮጀክት በመቅረጽ ስብከተ ወንጌል የማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን በተሰጠው አገልግሎት ከአህጉረ ስብከት ጋር በመተባበር 4396 ምእመናን ተጠምቀው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ለመሆን በቅተዋል፡፡

 • በሀገሪቱ ባሉት የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ላሉ ኦርቶዶክሳዊያን ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ትውፊትና ነገረ ሃይማኖት ለማወቅ የሚያስችላቸውንና በሥራ ሲሠማሩ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል መነሻ የሚሆናቸውን ትምህርት በካሪኩለም በማካተት ተከታታይነት ያለው የኮርስ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል፡፡