sarapamon

ቅዱስ ሰራባሞን የኒቅዩስ ሊቀ ጳጳስ – ሕይወቱና ተጋድሎው

ነሐሴ 30 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሓላፊ

sarapamonቤተ ክርስቲያን በዓላውያን ነገሥታት አሰቃቂ ስደት በደረሰባት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕት ዓመታት ውስጥ ከተነሱት የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል አንዱ የሆነውና ለዛሬው የተጋድሎውን ዜና በአጭሩ የምንመለከተው ሰማዕት ቅዱስ ሰራባሞን ዘኒቅዩስ ነው። አባቱ አብርሃም ይባላል፤ አያቱ የቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ አጎት ሲሆን የተወለደው በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ነው። ሲወለድ ወላጆቹ “ስምዖን” ብለው ስም አወጡለት፤ “ሰራባሞን” የጵጵስና ስሙ ነው። የዐረብኛ እና የግዕዝ መጻሕፍት “ሰራባሞን” ሲሉት፣ የቅብጥና እንግሊዝኛ ምንጮች ደግሞ “ሰራፓሞን” ብለው ይጠሩታል።

በተወለደበት በኢየሩሳሌም ሳለ ክርስቲያን መሆን አጥብቆ ይፈልግ ነበር። እመቤታችን በራእይ ተገልጻ ወገኖቹ አይሁድ እንዳይገድሉት ወደ ግብፅ ሄዶ እንዲጠመቅና አገልግሎቱንም በዚያ እንዲፈጽም ስለነገረችው ቤተሰቦቹን ጥሎ መነነ። ግብፅ ሲደርስ እመቤታችን የእስክንድርያ 16ኛ ፓትርያርክ የነበረውን አቡነ ቴዎናስን (282-300) ባዘዘችው መሠረት አስተምሮ አጠመቀው። የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜያት፣ የነቢያትንና ሐዋርያትን መጻሕፍት ተማረ፣ የአግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳን እና የበልኪሮስን ድርሳናት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠና።

ከዚያም ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ በሆነ እልሐብጡን በተባለ በአባ ሳዊሮስ ገዳም ውስጥ መነኮሰ። ከዘመናት በኋላ በተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ዘመን (300-311) የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ሲያርፍ በእርሱ ምትክ የኒቅዮስ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን መራ፤ ከገድሉ እንደምናነበው ወደ ተመደበበት ሀገረ ስብከት ሲገባ የተደረገለት አቀባበል የደመቀ ከመሆኑ የተነሣ ጌታ በሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ታጅቦ ሲገባ እንደተደረገለት የሚመስል ነበረ። በቅዱስ ሰራባሞን አገልግሎት በኒቅዮስና በአጎራባች ከተሞች የነበሩ ጣዖታት ተሰባብረው ወድቀዋል፤ በእጁ በርካታ ገቢረ ተአምራት ተደርገዋል፤ በመስቀሉ አጋንንትን አባሯል።

ይህ ቅዱስ አባት ስለ ወንጌል ብዙ መከራን ተቀብሏል፤ ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን ብዙ ዘለፋ ደርሶበታል። አርዮስ፣ ሰባልዮስ እና ሚሊጦስ በእርሱ ዘመን የነበሩ መናፍቃን ናቸው። የአርዮስ ዋና ክህደት “ወልድ (ክርስቶስ) ፍጡር ነው” የሚል ሲሆን ሚሊጦስ ደግሞ “ከማርያም የተወለደው ክርስቶስ በምትሐት ነው እንጂ በእውነት አይደለም” የሚል ነበር። ሰባልዮስ “እግዚአብሔር አንድ ገጽ ነው” ብሎ የሚያስተምር ሲሆን፤ ሰራባሞን ሁሉንም ተከራክሮ ረቷቸዋል።

በዚህ የተነሣ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። አርዮስና ሚሊጦስ የሚያስተምረውን ባለመቀበላቸው በክፋታቸው ጸንተው ብዙዎችን እያሳቱ፣ በትዕቢታቸውም ልባቸውን እያኮሩ ቢያገኛቸው በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ የአርዮስና ሚሊጦስን አንገታቸውን በመሐረብ ይዞ “እናንተ አባታችሁን ዲያብሎስን በክህደት የምትመስሉ እስከ መቼ ድረስ ነው በዚህ ክህደታችሁ ሰውን የምታጠፉ?” ብሎ ገስጿቸዋል (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 130-137)። አርዮስ ከክሕደቱ የማይመለስ ከሆነ አንጀቱ ተበጣጥሶ እንደሚሞት፣ ሚሊጦስም ካልተመለሰ ሥጋውን በቁሙ ዕፄያት እንደሚበሉት ትንቢት ተናግሮባቸዋል። እምቢ በማለታቸው በሁለቱም ላይ ይኸው ተፈጽሞባቸዋል።

ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅልጥያኖስ (284-305) የሚያፈርሳትን ቤተ ክርስቲያን ሰረባሞን ሲሰራ፣ ጣዖት የሚያመልኩትንም ሰዎች በክርስቶስ ስም ሲያሳምናቸው ንጉሡ እና መኳንንቱ ስጋት ጨመረባቸው። ሰራባሞን እንዲታሰር እና ስለ ክርስቶስ ፈጽሞ እንዳያስተምር በእስክንድርያው ገዢ አውጣኪያኖስ፡ ኮሞስ፡ ትዕዛዝ ተሰጠ።

ሰራባሞን ግን ከአቋሙ አልተናወጸም። ስለዚህ እስር ቤቱን አንዴ በታሕታይ ግብጽ አንዴ ደግሞ በላዕላይ ግብጽ በበረሃው ሁሉ በማፈራረቅ አሰቃዩት። እርሱ ግን ስቃዩንና ዛቻውን ከምንም ሳይቆጥር በእስር ቤት ውስጥም ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን አሳምኗል። የላዕላይ ግብፅ ገዢ የነበረው አርያኖስ (ከከሐዲው አርዮስ የተለየ እና የሀገረ እንጽና ገዢ የነበረ) ብዙ ካሠቃየው በኋላ በኒቅዩስ ከተማ ወደብ አቅራቢያ አንገቱን እንዲቆርጡት ትዕዛዝ ሰጠ። የሚጓዙበት መርከብ ግን አልንቀሳቀስም አለ። ቅዱስ ሰራባሞንን ከመርከቡ ሲያወርዱት በሰላም ሄዱ። በዚህ ሁኔታ እያለ እንኳን ወንጌልን መስበክና ትንቢት መናገርን አልተወም።

ይህ በእርሱ ላይ የሞት ውሳኔ የሰጠበት አርያኖስ በኋላ ዲዮቅልጥያኖስን ክዶ ክርስቲያን እንደሚሆን በመጨረሻም ሰማዕትነትን ተቀብሎ እንደሚሞት፣ እንዲሁም የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ጴጥሮስም በሰማዕትነት እንደሚሞትና “ተፍጻሜተ ሰማዕት” እንደሚሆን እንዲህ ብሎ ተንብዮአል፥ “ወበከመ፡ ጴጥሮስ፡ ቀዳማየ፡ እምሐዋርያት፡ ከማሁ፡ አንተኒ፡ ትከውን፡ ተፍጻሜተ፡ ሰማዕት። ናሁ፡ አቅደምኩ፡ ነጊሮተከ፡ ዘይከውን፡ በጊዜሁ።” (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል 158)። እንደ ትንቢቱም ሁሉም ተፈጽሟል። በመጨረሻም ከሀገረ ስብከቱ ኒቅዩስ በስተደቡብ በምትገኘው ቦታ ወስደው ኅዳር 28 ቀን (በቅብጥ አቆጣጠር ሐቱር 28 ቀን) አንገቱን በሰይፍ ቀሉት።

ደቀመዛሙርቱ አስከሬኑን በመንገድ ላይ እንዳልባሌ ነገር ተጥሎ ሲያዩት በመረረ ሐዘን ተውጠው እያለቀሱ “እረኛችን ሆይ ለማን ታስጠብቀናለህ? አባታችን ሆይ እንግዲህ ማን ይሰበስበናል? አውሬ ከቦናል፣ በወንጌል ኮትኩተህ ያሳደግከው ተክልህን ከእንግዲህ ማን ይንከባከበው?” እያሉ መሪር እንባን ያነቡ ነበር። ከብዙ ለቅሶ በኋላ አስከሬኑን ወስደው በኒቅዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር አሳረፉት (ገድለ ሰራባሞን፣ ቅጠል166)።

ከገድሉ እንደምናነበው ሰራባሞን ባደረገው ተጋድሎና በጽንአቱ በርካታ የክብር ስሞችና ቅጽሎች ተሠጥተውታል። ዋና ዋናዎቹም፥ “ብፁዕ ወቅዱስ ሰማዕት”፣ “ለባሴ መንፈስ”፣ “ለባሴ፡ አምላክ”፣ “ዓምደ ቤተ ክርስቲያን”፣ “ሐረገ ወይን”፣ “ሐዲስ ዳንኤል”፣ “ላዕከ መንፈስ ቅዱስ”፣ “ሙሴ ሐዲስ”፣ “ጳውሎስ ዳግመ”፣ “ዮሐንስ ሐዲስ”፣ “መስተጋድል ዐቢይ” የሚሉት ናቸው።

በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በስሙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ታንጸዋል፣ ገድል ተጽፎለታል፣ በስንክሳርም ይዘከራል። ገድሉ እና የሰማዕትነቱ ዜና በቅብጥ እና ዐረብኛ ቋንቋ የተጻፈና የተተረጎመ ሲሆን ሁሉም ግን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ አልተገኘም። የቅብጡ ቅጂ በHyvernat, (ገጽ. 304-31) የታተመ ሲሆን የዐረብኛው ደግሞ (Kairo 27 በሚል ዝርዝር) በKraf (1934:12) ካታሎግ ተሠርቶለታል። በቅርቡ ደግሞ Youssef (2013: 263-280) የሚባል ተመራማሪ “ሰራባሞንን የሚመለከቱ የቤተ ክርስቲያን ምንባባት” ብሎ ጥናታዊ ጽሑፍ አውጥቷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያነ የቅዱስ ሰራባሞን ዜና ሕይወት እና ተጋድሎ እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን እምብዛም ጎልቶ የሚታወቅ ባይሆንም በሕዳር 28 ስንክሳር ይታወሳል። ከዚህም በላይ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገድሉ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በአቡነ መርሐ ክርስቶስ ዘመን (1408-1497) ተተርጉሞ ይገኛል። ይህም ገድል አሁን ከሚገኙት የቅብጥና ዐረብኛ ቅጂዎች ይልቅ የተሟላ እና ይዘቱም ሰፊ ነው። ይህ ገድል በ1970ዎቹ ውስጥ (EMML 6533) በሚል መለያ ማይክሮ ፊልም ተነስቷል።

ብራናው አጠቃላይ 168 ቅጠል ያለው ሲሆን ከመጀመሪያ እስከ 118 ድረስ የሐዋርያው ጳውሎስ ገድል፣ ከቅጠል 119-167 ድረስ ደግሞ የሰማዕቱ ሰራባሞንን ገድል ይዟል። የሰራባሞን ገድሉ አራት ክፍሎችን ይዟል፤ እነዚህም፥ 1) ድርሳን (ከቅጠል 119-131)፣ 2) ገድል (ከቅጠል135-142)፣ 3) ተአምር (ከቅጠል 132-149)፣ 4) ስምዕ (ከቅጠል 150-167) የሚሉ ናቸው። ይህም ስለ ሰራባሞን የሚጠናውን ጥናት ይበልጥ የተሟላ የሚያደርግና በተለይ ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ለዜና አበው እና ለነገረ ቅዱሳን የጥናት መስክ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። ከስንክሳሩና ከገድሉ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ሰራባሞን የተዘጋጁ ልዩ ልዩ አርኬዎች (Chaîne ቁ. 48 እና Wein፣ Athiop. 19 [በN.Rhodokanakis አማካይነት ካታሎግ የተሠራላቸው])፣ እንዲሁም ሁለት የተለያዩ መልክአት (Chaîne ቁ. 158 እና 325) ተዘጋጅተዋል። በኢትዮጵያው የገድል ቅጅ ላይ እስካሁን የተደረገ ጥናት የለም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ መነሻ ጥናት አድርጎ ገድሉንም እየተረጎመ ይገኛል።

ይህን ጽሑፍ የምንደመድመው በቪየና የሚገኘው ብራና (Vienna ms f.62v-63r) ስለ ቅዱስ ሰራባሞን ከሚያመሰግነው አርኬ ውስጥ አንዱን በማንበብ ይሆናል፤

ለከ፡ ስነ፡ ሰረባሞን፡ ዘኤፍራታ፤

ነጺሮሙ፡ ጥቀ፡ ለሕሊናሁ፡ ጥብዓታ፤

ከመ፡ ይከውን፡ ሰማዕት፡ ውስተ፡ ዓውደ፡ ግሩም፡ ሐተታ፤

ገደፈ፡ አብ፡ እጓሎ፡ ወእም፡ ወለታ፤

ወሐማትኒ፡ ሐደገት፡ መርዓታ።

የሰማዕቱ ሰራባሞን በረከት ይድረሰን!!!

ስምዓት

  • መጽሐፈ ስንክሳር – በግዕዝና በአማርኛ (ከመስከረም እስከ የካቲት)፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 1994 ዓ.ም.

  • ገድለ ጳውሎስ ወሰራባሞን – (EMML 6533)- ደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኝ፣ በ15ኛው መ/ክ/ዘ/ የተጻፈ ብራና (እስካሁን አልታተመም)።

  • Amsalu Tefera, 2013, “Gädlä Särabamon: the case of the Ethiopic version”, a paper read on a workshop titled “EMML@40: The Life and Legacy of the Ethiopian manuscript microfilm Library” organized by Hill Museum & Manuscript Library, Saint John’s University, Collegeville, MN, USA, July 25-26, 2013.

  • Budge, Wallis, 1928, The Book of the Saints of the Ethiopian Church: a translation of the Ethiopic Synaxarium መጽሐፈ፡ ስንክሳር፡ made from the manuscripts Oriental 660 and 661 in the British Museum, vol. I, Cambridge at the University Press.

  • Chaîne, M., 1912, “Catalogue des manuscrits Ethiopiens de la collection Antoine d’Abbadie”, Paris.

  • Chaîne, M., 1913, “Répertoire de salam et Melke’e contenus dans les manuscrits éthiopiens des bibliotheques d’Europe” in Revue de L’Orient Chrétien, , deuxieme Serie, Tome viii, no. 2

  • Colin, G. 1988, “Le Synaxaire Éthiopien mois de Ḫedār” in Patrologia Orientalis, Tome 44, fascicule3, no. 99)

  • Coptic Synaxarium, reading on Hatour 28, – retrieved online –http://popekirillos.net/EN/books/COPTSYNX.pdf, accessed on May 14, 2012.

  • Hayvernat, Henry, Les Actes des martyrs del’Égypte, retrieved online from http://www.archive.org.detailes/lesactesdesmarty01hyve – accessed on November 6, 2012.

  • Kraf, George, 1934, Catalogue de manuscrits Arabes Chrétiens conserves au Caire, studi e testi 63, Città del Vaticano Biblioteca Apostolica Vaticana

  • Rhodokanakis, N. 1906, Die Äthiopischen Handscriften der K. K. Hofbibliothek zu Wein, Wein Athiop. 19.

  • Youssef, 2013, “Liturgical Texts Relating to Sarapamon of Nikiu”, Peeters Online Journal, pp. 263-280.

ማቴዎስ ወንጌል

ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.

ምዕራፍ 7 ካለፈው የቀጠለ

ሠ. ሰፊ ደጅ የተባለች ባለጸጋን መጽውት ድኃን ጹም ማለት ነው፡፡

ሰፊ ደጅ የተባለች ፈቃደ ሥጋ ናት ወደ ሰፊው ደጅ የሚገቡ ብዙዎች ወደ ጠባቧ ደጅ የሚገቡ ደግሞ ጥቂቶች መሆናቸው ጌታን አያስቀናውም፡፡ ምክንያቱም ጥቂት ዕንቁ ያለው ደግሞ ብዙ ወርቅ ባለው፤ ጥቂት ወርቅ ያለው ብዙ ብር ባለው፤ ጥቂት ብር ያለው ብዙ ብረት ባለው፤ ጥቂት ብረት ያለው ብዙ ሸክላ ባለው አይቀናም፡፡

6. ስለ ሐሰተኞች ነቢያት

የበግ ለምድ ለብሰው ይመጣሉ የተባሉት ነጣቂ ተኩላዎች መንፈሳውያን መስለው የሚመጡ ሥጋውያን፤ ሃይማኖታውያን መስለው የሚመጡ መናፍቃን ናቸው፡፡ ጌታችን “በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ናቸው፡፡” ማለቱ ቢመረምሯቸው ሰውን ከመንጋው/ ከማኅበረ ምእመናን/ መካከል እየነጠቁ ወደ ገሃነም የሚያወርዱ መሆናቸውን ሲያጠይቅ ነው፡፡ እነዚህም ወይንና በለስ የማይገኝባቸው እሾሆችና ኩርንችቶች በመሆናቸው ከፍሬያቸው እንደሚታወቁ ተናግሯል፡፡ ይህም “ሥራቸውን አንሠራም ትምህርታቸውን ግን ብንማር ምን ዕዳ ይሆናል? ትሉኝ እንደሆነ ከመናፍቅ መምህር ሃይማኖት፣ ከሐሰተኛ መምህር እውነተኛ ትምህርት ቃል አይገኝም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ወይን ወይንን ኮሶ ደግሞ ኮሶን ያፈራል እንጂ ወይን ኮሶን፣ ኮሶ ደግሞ ወይንን አያፈራም፡፡ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ተቆርጦ ወደ እሳት እንዲጣል መናፍቃንንም ሥላሴ በገሃነም እሳት ፍዳ ያጸኑባቸዋል፡፡

ጌታችን ከዚህ አያይዞ “ሁሉ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ይሉሃል፤ ታዲያ ወደ መንግሥትህ የሚገባውንና የማይገባውን በምን እናውቃለን? ትሉኝ እንደሆነ የሰማይ አባቴን ፈቃድ የሠራ ይገባል እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፡፡ በዚያን ጊዜም ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” ብሏል፡፡ ትንቢት መናገርማ በለዓምም ትንቢት ተናግሯል፡፡ ዘኁ.20፡4፣17፡፡ አጋንንትን ለማውጣት ደቂቀ አስቄዋ አጋንንትን አውጥተዋል የሐዋ.19፡14፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለእነዚህ ሰዎች ሲናገር “እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኰለኞች ሠራተኞች ናቸውና፡፡

 

ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና፡፡ እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጸድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል፡፡” ሲል አስጠንቅቋል 2ኛ ቆሮ.11፡13-15፡፡ በኦሪቱም “በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ እንደነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም እርሱም ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍቡጸምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደሆነ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስሙ” ተብሏል ዘዳ.13፡1-3፡፡

7. በዓለት ላይ ስለተመሠረተውና በአሸዋ ላይ ስለተሠራው ቤት፡፡

ጌታችን በዚህ በመጨረሻው አንቀጽ ላይ ቃሉን ሰምቶ እንደ ቃሉ የሚኖረውን ልባም ሰው በዓለት ላይ በተመሠረተ ቤት መስሎታል፡፡ በዓለት ላይ የተመሠረተውም ቤት ዝናብ ወርዶ በጐርፍ፣ ነፋስ ነፍሶ በነፋስ ተገፈቶ አልወደቀም ብሏል፡-

ዓለት ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወልድ ዋሕድ ብለው ለሚታመንበት ሁሉ መንፈሳዊ መጠን የሚገኝበትና መንፈሳዊ መሠረት የሚቆምበት ዓለት ነው 1ኛ.ቆሮ.10፡4፡፡ ለማያምኑት ግን የማሰናከያ ዓለት ተብሎአል ኢሳ.8፡14፣ 1ኛ.ጴጥ.2፡8፡፡ ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስንም ዓለት ነህ ብሎታል ማቴ.16፡16-18፡፡ ዝናም ነፋስ የባለ መከራ ነው፡፡

ከምሳሌው የምንረዳው ዋነኛው ምሥጢር እንደሚከተለው ነው፡፡

  1. ሃይማኖትን በበጎ ልቡና ይዘው እንደ ቃሉ የሚኖሩ ሰዎች ዓላውያን መኳንንት መከራ ቢያጸኑባቸው፣ ቤተሰቦቻቸውም ንጉሥ የወደደውን ዘመን የወለደውን ይዛችሁ ኑሩ ብለው ቢገፋፏቸው ምንም ይሁን ምን በክህደት አይወድቁም፡፡ እነዚህ ሃይማኖታቸውንና ምግባራቸውን እንደ ኢዮብ ባለ ሰውነት ይዘው የሚኖሩ ሰዎች የልጅ ሞት፣ የሀብት ውድመት እና የአልጋ ቁራኛ የሚያደርግ ደዌ ቢያጋጥማቸውም በምስጋና ይኖራሉ እንጂ ሃይማኖታቸውን አይለውጡም፡፡

  2. ሃይማኖትን በበጎ ልቡና ይዘው እንደቃሉ የሚኖሩ ሰዎች በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን ስለሚኖሩ አጋንንት በጎ አስመስለው ገፋፍተው ከክፉ ወጥመድ አይጥሏቸውም፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች አጋንንት በአሳብ ይዋጓቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ እንጦንስ እንደ መቃርስ ንጽሕ ጠብቀን ከሴት ርቀን እንኖራለን የሚል አሳብ ሲመጣባቸው ቸኩለው አይወስኑም፡፡ ፈጥነው ለመምህረ ንስሐቸው ይነግራሉ፡፡ እነርሱም ቆዩ ይሏቸዋል፡፡ ደግሞም እንደ እንጦንስ እንደ መቃርስ ንጽሕ ጠብቀን ከሴት ርቀን መኖር አይቻለንም፤ እንደ ኢዮብ እንደ አብርሃም በሕግ ጸንተን እንኖራለን የሚል አሳብም ሲመጣባቸው ለመምህረ ንስሐቸው ይነግሩታል፡፡ እርሱም የሰይጣን ፆር እንደሆነ ዐውቆ ቆዩ ይላቸዋል፡፡ በመጨረሻም አጋንንት ሁሉም አይሆንልንም አሰኝተው ሃይማኖቱን ለማስለቀቅ ይገፋፏቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመሥርተው ስለሚኖሩ አይወድቁም፡፡

ጌታችን ቃሉን ሰምቶ እንደቃሉ የማይኖረውን ሰው ደግሞ በአሸዋ ላይ በተሠራ ቤት መስሎታል፡፡ ይህንንም ቤት ጐርፍ ነፋስ በገፉት ጊዜ አወዳደቁ የከፋ ሆኗል፡፡ እነዚህም ሃይማኖታቸውን በበጎ ልቡና ያልያዙ ሰዎች ናቸው፡፡ እንደ ቃሉ ይኖሩ መከራውን ተሰቅቀውና በወሬ ተፈትነው በክህደት ይወድቃሉ፡፡ ለጊዜው በጌታ ዐፀደ ወይን በቤተ ክርስቲያን ቢበቅሉም ፀሐይ ሲወጣ ግን ይጠወልጋሉ ማቴ.13፡5-6፣20፡፡

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አስተምህሮ ከፈጸመ በኋላ ሕዝቡ ትምህርቱን አደነቁ፡፡ ምክንያቱም እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበረ፡፡ ይህም ማለት ንጉሥ እንዲህ ይላችኋል እንደሚሉ ሹማምንት ያይደለ እኔስ እላችኋለሁ እያለ አስተምሯቸዋልና ነው፡፡

“ከመዝ ይቤ እግዚአብሔር” እንደሚሉ ዐበይት ነቢያት ያይደለ ሠራዔ ሕግ እንደ መሆኑ እኔስ አላችኋለሁ እያለ አስተምሯቸዋል፡፡ “ከመዝ ይቤ ሙሴ፤ ከመዝ ይቤ ሳሙኤል፣” እንደሚሉ ደቂቀ ነቢያት ያይደለ ፈጻሜ ሕግ እንደመሆኑ አስተምሯቸዋል፡፡

“ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም፡፡” እንዳላቸው ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያይደለ እንደ ጌትነቱ በርኅራኄ አስተምሯቸዋል፡፡ ከወርቁ የጠራውን፣ ከግምጃ ያማረውን፣ ከላሙ የሰባውን እንደሚሉ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያይደለ የቸርነቱን ሥራ እየሠራ አስተምሯቸዋል፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ሰኔ 1989 ዓ.ም.

dn tolosa 2

የ2006 ዓ.ም. የግቢ ጉባኤያት ፍሬዎች ዋንጫና ሜዳልያቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን አስረከቡ

ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም

እንዳለ ደምስስ

  • ለኔ ይህ ዋንጫ ትልቁ ሀብቴ ነው፤ ሰው ሀብቱ ባለበት ልቡ ይኖራልና ዋንጫውን ሳስብ ማኅበሬን አስባለሁ፤ ተግቼም እንዳገለግል ያደርገኛል፡፡ የማልተካውን ሀብቴ ለማይተካው የማኅበሬ አገልግሎት መሥጠት ለኔ ታላቅ ደስታ ነው፡፡ /ዲያቆን ቶሎሳ ታዬ/

dn tolosa 2ማኅበረ ቅዱሳን በ2006 ዓ.ም. ከዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ግቢ ጉባኤያት በርካታ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ቆይታቸው ያስመዘገቡት ውጤት ከፍተኛ በመሆኑም በርካቶች የተሸለሙትን ዋንጫና ሜዳልያ በሥጦታ ለማኅበሩ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ተመራቂዎች መካከል በወሎ ዩኒቨርስቲ ደሴ ካምፓስ በእንስሳት ሳይንስ ትምህርት የተመረቀው ዲያቆን ቶሎሳ ታዬ አንዱ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታው የግቢ ጉባኤው ሰብሳቢ የነበረ ሲሆን፤ በርካታ ውጣ ውረዶችን ተቋቁሞ 4 ነጥብ እና 18A+ በማምጣት የዩኒቨርስቲው አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ዋንጫና ሜዳልያ ለመሸለም በቅቷል፡፡

የተሸለመውን ዋንጫ በማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት ለማኅበሩ ሲያስረክብ፤ ሜዳልያውን ደግሞ ከሕፃንነት ጀምሮ ሲያገለግልበት ለነበረው ለምእራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት በለስ ወረዳ ዳቡስ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲሰጥለት በጉባኤው ላይ ለተገኘው የወረዳ ማእከሉ ተወካይ እንዲያደርስለት አስረክቧል፡፡dn tolosa 3

ዲያቆን ቶሎሳ ዋንጫና ሜዳልያውን ካበረከተ በኋላ ባስተላለፈው መልእክት “ወሎ ዩኒቨርስቲ ስገባ ማኅበሩ ባዘጋጀው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል መርሐ ግብር ላይ ተገኝቼ የጉባኤ ቃና ጋዜጣን ገዝቼ ዶክተር እንግዳ በጅማ ዩኒቨርስቲ ሲመረቁ ያገኙትን ሜዳልያ ለማኅበሩ እንደሰጡ አነበብኩ፡፡ ወዲያውኑ እኔም ለዚህ ክብር እግዚአብሔር ቢያበቃኝ ያገኘሁትን ሽልማት ለማኅበሩ ለመሥጠት ቃል ገባሁ፡፡ እግዚአብሔርም ምኞቴን አሳካልኝ፡፡ ለኔ ይህ ዋንጫ ትልቁ ሀብቴ ነው፤ ሰው ሀብቱ ባለበት ልቡ ይኖራልና ዋንጫውን ሳስብ ማኅበሬን አስባለሁ፤ ተግቼም እንዳገለግል ያደርገኛል፡፡ የማልተካውንና በሕይወቴ አንድ ጊዜ ብቻ የማገኘውን ሀብቴ ለማይተካው የማኅበሬ አገልግሎት መሥጠት ለኔ ታላቅ ደስታ ነው” ብሏል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተገኙት ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ ዋንጫውንና ሜዳልያውን ከዲያቆን ቶሎሳ በመረከብ ለማኅበሩ ሰብሳቢና ለወረዳ ማእከሉ ከሠጡ በኋላ የተሰማቸውንdn tolosa 4 ደስታ ሲገልጹ “ይህ ውጤት በሀገራችን በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ታሪክ በጥቂቶች ብቻ ሊመዘገብ የሚችል ከፍተኛ ውጤት ነው፡፡ ካስመዘገበው ውጤት ይልቅ ደግሞ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ በሕይወቱ አንድ ጊዜ ብቻ ሊገጥመው የሚችለውን እድል ውድ ሥጦታ ለማኅበሩ መሥጠቱ አስደንቆኛል፡፡ ብዙዎቻችንንም ያስተማረ ነው፡፡ ወደፊትም በሕይወቱ የተሳካ ጊዜ አሳልፎ ለሌሎች አርአያ እንዲሆን እመኛለሁ” ብለዋል፡፡

የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ሰሙ ሥጦታውን ከተቀበሉ በኋላ የተሰማቸውን ሲገልጹም “ይህ ሥጦታ ጠቅላላ ጉባኤውንና ማኅበራችንን ወክዬ ነው የተቀበልኩት፡፡ እኛም ይህንን ታሪክና ሀብት ለመጠበቅ፤ አገልግሎቱንም ለማገዝ አብሮንም በአገልግሎት እንዲዘልቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ አደራውንም ተቀብለናል” ብለዋል፡፡

የደሴ ማእከል የማኅበረ ቅዱሳን ጸሐፊ ዲያቆን ሰሎሞን ወልዴ በሠጠው ምሥክርነትም ዲያቆን ቶሎሳ የግቢ ጉባኤው ሰብሳቢ ሆኖ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መሠብሠቢያ አዳራሽ በማሠራት፤ በአቅራቢያው ቤተ ክርስቲያን በማሳነጽና በመምራት፤ የሥራ አስፈጻሚና በዩኒቨርስቲው የሚካሔዱ አገልግሎቶችን በማስተባበር ተጠምዶ ስለሚውል ለዚህ ክብር ይበቃል የሚል ግምት አልነበረንም፡፡ ሆኖም ለግቢ ጉባኤውና ማኅበሩ ለሚያከናወነው አገልግሎት አርአያ እንዲሆን ስናበረታታው ቆይተናል፡፡ እግዚአብሔር መልካም ነገር አደረገልን፡፡ በወረዳ ማእከላችን ከሚገኙ 8 ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውሰጥ ከተዘጋጁት ሜዳልያዎች ሰባቱን የወሰዱት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ናቸው ብሏል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ በደሴ ካምፓስ በትምህርትና እቅድ አስተዳደር ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው አሰፋ አደፍርስ፤ በደብረ ታቦርdn tolosa 5 ማእከል የፈቃደ እግዚእ ኮሌጅ ተመራቂዎቹ ዘውዴ ደሴና ከፍያለው ስመኝ ለማኅበሩ ማእከላት ሜዳልያቸውን አስረክበዋል፡፡ እንዲሁም ከሐረር የሜንሽን አግሮ ቴክኒካል ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ሰብሳቢ የሆነው ቃል ኪዳን ዓለሙ ሜዳልያውን በማእከሉ በኩል ለኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን እንዲሰጥለት አበርክቷል፡፡

guba 2006 24 1

ማኅበረ ቅዱሳን 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሔደ

ነሐሴ 27 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

guba 2006 24  1የማኅበረ ቅዱሳን 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2006 ዓ.ም. በማኅበሩ ሕንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ የሀገር ውስጥና የውጭ ማእከላት፤ የወረዳ ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ተወካዮች፤ የማኅበሩ ሥራ አመራርና ሥራ አሥፈፃሚ አባላት፤ የማኅበሩ ልዩ ልዩ ክፍል ተጠሪዎች፤ ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት አካሄደ፡፡

guba 2006 24  2የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፈዎች ከነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ የጸሎት፤ የመርሐ ግብር ትውውቅና ማስገንዘቢያ በጠቅላላ ጉባኤው አዘጋጅ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ በዶክተር ዳኝነት ይመኑ ቀርቧል፡፡ የእጽበተ እግር መርሐ ግብርም ተከናውኗል፡፡

ነሐሴ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ጉባኤው በጸሎተ ወንጌል ተጀምሮ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክትና የማኅበሩ የሁለት ዓመታት የዕቅድ ክንውን ዘገባ በማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ ቀርቧል፡፡ በቀረበው ዘገባም የስብከተ ወንጌል guba 2006 24  3አገልግሎት ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማትን በማጠናከር ረገድ፤ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማጠናከር ከአህጉረ ስብከቶች ጋር እየተሠሩ ስለሚገኙ በርካታ ተግባራት ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያትን በማጠናከር ረገድ፤ የማኅበሩን ተቋማዊ አቅም ለማሳደግ እየተሠሩና በመሠራት ላይ የሚገኙ ሥራዎች፤ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሔዎችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የ2005 ዓ.ም. የማኅበሩ የሒሳብ ሪፖርት በማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፤ እንዲሁም የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት በአቶ የሺዋስ ማሞ የቀረቡ ሲሆን፤ የ2004 ዓ.ም. እና የ2005 ዓ.ም. የሁለቱን ዓመታት የኦዲት ሪፖርት ዓለም አቀፍ እውቅና ባለው የውጭ ኦዲተር በማስመርመር በድርጅቱ ሓላፊ የኦዲት ሪፖርቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቧል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት በማካሔድ አጽድቋቸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ከ1996 ዓ.ም. በማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ ጸድቆ ሲሠራበት የቆየው የማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅትና የምርጫ ሥነ ሥርዓት መመሪያ በአሁኑ ወቅት ማኅበሩ ከደረሰበት የእድገት ደረጃና የአገልግሎት ስፋት አንጻር ሊጣጣም ባለመቻሉ መመሪያውን ማሻሻል በማስፈለጉ በሥራ አመራር ጉባኤው የተሰየመው ኮሚቴ የጥናቱን ረቂቅ ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርቧል፡፡ በቀረበው የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅትና የምርጫ ሥነ ሥርዓት መመሪያ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ በተሳታፊዎች ውይይት ተካሒዶበት ለማሻሻያ የሚጠቅሙ በርካታ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡ አጥኚ ኮሚቴውም የቀረቡለትን ገንቢ ሃሳቦች በማካተት ለመደበኛ ሥራ አመራር ጉባኤ እንዲያቀርብ፤ ሥራ አመራር ጉባኤውም የቀረበለትን ማሻሻያውን መርምሮ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጠቅላላ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡

guba 2006 24  5ጠቅላላ ጉባኤው በሁለተኛ ቀን ውሎው ብፁዕ አቡነ ሰላማ የምሥራቅ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ የተገኙ ሲሆን፤ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ያሰባሰባችሁ እግዚአብሔር ነው፤ በእናንተ ኃይል አልተሰባሰባችሁም፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር አስነስቷችኋልና በጉዟችሁ ፈተና ሊገጥማችሁ ይችላል፡፡ ፈተና ደግሞ ያለ ነው፤ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ ከሚወድህ ይልቅ የሚጠላህ ይጠቅምሃል እንዲሉ አባቶቻችን ካልተፈተኑ ክብር አይገኝም፡፡ በአገልግሎታችሁ እንደጸናችሁ ሳትበሳጩ ልትጓዙ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ማኅበሩን ይባርክ” ብለዋል፡፡

በቀጣይነትም ጠቅላላ ጉባኤው የግቢ ጉባኤያት የእድገትና ውጤታማነት መርሐ ግብር ስልታዊ አቅጣጫና እቅድ በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት /ከ2007 – 2017/፤ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን ስልታዊ እቅድ አጋማሽ ዘመን ግምገማ በሚሉ ሁለት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡

የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት እድገትና ውጤታማነት ስልታዊ አቅጣጫና እቅድ ለሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ በቀረበው ጥናት ላይ ተሳታፊዎችን በ23 ቡድን በመከፋፈል ውይይት ተደርጓል፡፡ በቡድን ውይይቱ የተነሱ በርካታ ነጥቦችን በግብአትነት በመያዝ በዋናነት በተያዙ የጥናቱ ክፍሎች ተከፋፍለዋል፡፡ በዚህም መሠረት የተነደፉት ግቦች፤ ዓላማዎች፤ ስልቶችና ተግባራት ስልታዊ እቅዱን ከማሳካት አንጻር፤ የግቢ ጉባኤያትን ስልታዊ እቅድ ከማስፈጸም አንጻር መዋቅራዊ አደረጃጀቱ ምን መምሠል እንዳለበት፤ በቀረበው ሰነድ ላይ የተጠቀሰው ገንዘብ ማግኛ ስልትና ምንጭ ተገቢ መሆኑን መመልከት፤ የግቢ ጉባኤያት ሁኔታ በአገልግሎት ክፍሎች በዋና ጉዳይነት አካቶ መሥራት በሚሉት ነጥቦች ሥር ለይቶ በመያዝ ለመደበኛ ሥራ አመራር ጉባኤ ለውሳኔ በማቅረብ፤ ሥራ አመራር ጉባኤው የቀረበለትን ሠነድ መርምሮ በማጽደቅ ተግባራዊ እንዲሆን ጠቅላላ ጉባኤው ወስኗል፡፡

guba 2006 24  4የማኅበረ ቅዱሳን ስልታዊ እቅድ አጋማሽ ዘመን ግምገማ በማስመልከት ከጥር 2005 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2006 ዓ.ም. የተከናወኑትን ሥራዎች ተገምግመው ሓላፊነት በወሰደው አጥኒ ቡድን ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርበዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም ውይይት በማድረግ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት ቀጣይ አፈጻጸማችን ምን መምሰል እንደሚገባው ለማሳየት ቢሞከር፤ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከስትራቴጂክ እቅዱ አንጻር አስታርቆ ማስኬድ፤ የክብደት አሥራር ሥርዓቱን ግልጽ ማድረግ፤ ግምገማው ከስልታዊ እቅዱ ጋር በደንብ ቢታይ የሚሉና ሌሎችም ጠቃሚ ነጥቦች ከተካተቱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ የጥናት ቡድኑ ከጠቅላላ ጉባኤው በተሰጡት ሃሳቦች መሠረት የግምገማውን ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመደበኛ ሥራ አመራር ጉባኤ እንዲያቀርብ፤ ሥራ አመራር ጉባኤውም አጽድቆ በሚመለከታቸው አካላት ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲያስተላልፍ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ማጠቃለያ ላይም የዝግጅቱ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዳኝነት ይመኑ ለጉባኤው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ድርጅቶችንና በጎ አድራጊ ምእመናንን በዝርዝር በመጥቀስ በጠቅላላ ጉባኤው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ጉባኤው እሰኪጠናቀቅ ድረስ ላሳዩት አርአያነት ላለው ሥነ ምግባር የተላበሰ ታዛዥነትና ተሳትፎ አመስግነዋል፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያም ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ለሦስት ቀናት በትዕግስት፤ በታዛዥነትና በንቁ ተሳታፊነት ለአገልግሎት ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን በማምንጨት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ከ650 በላይ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡