ማቴዎስ ወንጌል

ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.

ምዕራፍ 7 ካለፈው የቀጠለ

ሠ. ሰፊ ደጅ የተባለች ባለጸጋን መጽውት ድኃን ጹም ማለት ነው፡፡

ሰፊ ደጅ የተባለች ፈቃደ ሥጋ ናት ወደ ሰፊው ደጅ የሚገቡ ብዙዎች ወደ ጠባቧ ደጅ የሚገቡ ደግሞ ጥቂቶች መሆናቸው ጌታን አያስቀናውም፡፡ ምክንያቱም ጥቂት ዕንቁ ያለው ደግሞ ብዙ ወርቅ ባለው፤ ጥቂት ወርቅ ያለው ብዙ ብር ባለው፤ ጥቂት ብር ያለው ብዙ ብረት ባለው፤ ጥቂት ብረት ያለው ብዙ ሸክላ ባለው አይቀናም፡፡

6. ስለ ሐሰተኞች ነቢያት

የበግ ለምድ ለብሰው ይመጣሉ የተባሉት ነጣቂ ተኩላዎች መንፈሳውያን መስለው የሚመጡ ሥጋውያን፤ ሃይማኖታውያን መስለው የሚመጡ መናፍቃን ናቸው፡፡ ጌታችን “በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ናቸው፡፡” ማለቱ ቢመረምሯቸው ሰውን ከመንጋው/ ከማኅበረ ምእመናን/ መካከል እየነጠቁ ወደ ገሃነም የሚያወርዱ መሆናቸውን ሲያጠይቅ ነው፡፡ እነዚህም ወይንና በለስ የማይገኝባቸው እሾሆችና ኩርንችቶች በመሆናቸው ከፍሬያቸው እንደሚታወቁ ተናግሯል፡፡ ይህም “ሥራቸውን አንሠራም ትምህርታቸውን ግን ብንማር ምን ዕዳ ይሆናል? ትሉኝ እንደሆነ ከመናፍቅ መምህር ሃይማኖት፣ ከሐሰተኛ መምህር እውነተኛ ትምህርት ቃል አይገኝም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ወይን ወይንን ኮሶ ደግሞ ኮሶን ያፈራል እንጂ ወይን ኮሶን፣ ኮሶ ደግሞ ወይንን አያፈራም፡፡ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ተቆርጦ ወደ እሳት እንዲጣል መናፍቃንንም ሥላሴ በገሃነም እሳት ፍዳ ያጸኑባቸዋል፡፡

ጌታችን ከዚህ አያይዞ “ሁሉ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ይሉሃል፤ ታዲያ ወደ መንግሥትህ የሚገባውንና የማይገባውን በምን እናውቃለን? ትሉኝ እንደሆነ የሰማይ አባቴን ፈቃድ የሠራ ይገባል እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፡፡ በዚያን ጊዜም ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” ብሏል፡፡ ትንቢት መናገርማ በለዓምም ትንቢት ተናግሯል፡፡ ዘኁ.20፡4፣17፡፡ አጋንንትን ለማውጣት ደቂቀ አስቄዋ አጋንንትን አውጥተዋል የሐዋ.19፡14፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለእነዚህ ሰዎች ሲናገር “እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኰለኞች ሠራተኞች ናቸውና፡፡

 

ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና፡፡ እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጸድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል፡፡” ሲል አስጠንቅቋል 2ኛ ቆሮ.11፡13-15፡፡ በኦሪቱም “በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ እንደነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም እርሱም ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍቡጸምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደሆነ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስሙ” ተብሏል ዘዳ.13፡1-3፡፡

7. በዓለት ላይ ስለተመሠረተውና በአሸዋ ላይ ስለተሠራው ቤት፡፡

ጌታችን በዚህ በመጨረሻው አንቀጽ ላይ ቃሉን ሰምቶ እንደ ቃሉ የሚኖረውን ልባም ሰው በዓለት ላይ በተመሠረተ ቤት መስሎታል፡፡ በዓለት ላይ የተመሠረተውም ቤት ዝናብ ወርዶ በጐርፍ፣ ነፋስ ነፍሶ በነፋስ ተገፈቶ አልወደቀም ብሏል፡-

ዓለት ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወልድ ዋሕድ ብለው ለሚታመንበት ሁሉ መንፈሳዊ መጠን የሚገኝበትና መንፈሳዊ መሠረት የሚቆምበት ዓለት ነው 1ኛ.ቆሮ.10፡4፡፡ ለማያምኑት ግን የማሰናከያ ዓለት ተብሎአል ኢሳ.8፡14፣ 1ኛ.ጴጥ.2፡8፡፡ ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስንም ዓለት ነህ ብሎታል ማቴ.16፡16-18፡፡ ዝናም ነፋስ የባለ መከራ ነው፡፡

ከምሳሌው የምንረዳው ዋነኛው ምሥጢር እንደሚከተለው ነው፡፡

  1. ሃይማኖትን በበጎ ልቡና ይዘው እንደ ቃሉ የሚኖሩ ሰዎች ዓላውያን መኳንንት መከራ ቢያጸኑባቸው፣ ቤተሰቦቻቸውም ንጉሥ የወደደውን ዘመን የወለደውን ይዛችሁ ኑሩ ብለው ቢገፋፏቸው ምንም ይሁን ምን በክህደት አይወድቁም፡፡ እነዚህ ሃይማኖታቸውንና ምግባራቸውን እንደ ኢዮብ ባለ ሰውነት ይዘው የሚኖሩ ሰዎች የልጅ ሞት፣ የሀብት ውድመት እና የአልጋ ቁራኛ የሚያደርግ ደዌ ቢያጋጥማቸውም በምስጋና ይኖራሉ እንጂ ሃይማኖታቸውን አይለውጡም፡፡

  2. ሃይማኖትን በበጎ ልቡና ይዘው እንደቃሉ የሚኖሩ ሰዎች በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን ስለሚኖሩ አጋንንት በጎ አስመስለው ገፋፍተው ከክፉ ወጥመድ አይጥሏቸውም፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች አጋንንት በአሳብ ይዋጓቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ እንጦንስ እንደ መቃርስ ንጽሕ ጠብቀን ከሴት ርቀን እንኖራለን የሚል አሳብ ሲመጣባቸው ቸኩለው አይወስኑም፡፡ ፈጥነው ለመምህረ ንስሐቸው ይነግራሉ፡፡ እነርሱም ቆዩ ይሏቸዋል፡፡ ደግሞም እንደ እንጦንስ እንደ መቃርስ ንጽሕ ጠብቀን ከሴት ርቀን መኖር አይቻለንም፤ እንደ ኢዮብ እንደ አብርሃም በሕግ ጸንተን እንኖራለን የሚል አሳብም ሲመጣባቸው ለመምህረ ንስሐቸው ይነግሩታል፡፡ እርሱም የሰይጣን ፆር እንደሆነ ዐውቆ ቆዩ ይላቸዋል፡፡ በመጨረሻም አጋንንት ሁሉም አይሆንልንም አሰኝተው ሃይማኖቱን ለማስለቀቅ ይገፋፏቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመሥርተው ስለሚኖሩ አይወድቁም፡፡

ጌታችን ቃሉን ሰምቶ እንደቃሉ የማይኖረውን ሰው ደግሞ በአሸዋ ላይ በተሠራ ቤት መስሎታል፡፡ ይህንንም ቤት ጐርፍ ነፋስ በገፉት ጊዜ አወዳደቁ የከፋ ሆኗል፡፡ እነዚህም ሃይማኖታቸውን በበጎ ልቡና ያልያዙ ሰዎች ናቸው፡፡ እንደ ቃሉ ይኖሩ መከራውን ተሰቅቀውና በወሬ ተፈትነው በክህደት ይወድቃሉ፡፡ ለጊዜው በጌታ ዐፀደ ወይን በቤተ ክርስቲያን ቢበቅሉም ፀሐይ ሲወጣ ግን ይጠወልጋሉ ማቴ.13፡5-6፣20፡፡

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አስተምህሮ ከፈጸመ በኋላ ሕዝቡ ትምህርቱን አደነቁ፡፡ ምክንያቱም እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበረ፡፡ ይህም ማለት ንጉሥ እንዲህ ይላችኋል እንደሚሉ ሹማምንት ያይደለ እኔስ እላችኋለሁ እያለ አስተምሯቸዋልና ነው፡፡

“ከመዝ ይቤ እግዚአብሔር” እንደሚሉ ዐበይት ነቢያት ያይደለ ሠራዔ ሕግ እንደ መሆኑ እኔስ አላችኋለሁ እያለ አስተምሯቸዋል፡፡ “ከመዝ ይቤ ሙሴ፤ ከመዝ ይቤ ሳሙኤል፣” እንደሚሉ ደቂቀ ነቢያት ያይደለ ፈጻሜ ሕግ እንደመሆኑ አስተምሯቸዋል፡፡

“ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም፡፡” እንዳላቸው ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያይደለ እንደ ጌትነቱ በርኅራኄ አስተምሯቸዋል፡፡ ከወርቁ የጠራውን፣ ከግምጃ ያማረውን፣ ከላሙ የሰባውን እንደሚሉ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያይደለ የቸርነቱን ሥራ እየሠራ አስተምሯቸዋል፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ሰኔ 1989 ዓ.ም.