ዘመነ አስተርእዮ

 ጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም.

 

ር/ደብር ብርሃኑ አካል

አስተርእዮ ቃሉ የግእዝ ቃል ሲሆን መታየት መገለጥ ማለት ነው፡፡ ገሐድ የሚለው ቃልም በጾምነቱ ሌላ ትንታኔ ሲኖረው ትርጉሙ ያው መገለጥ ማለት ነው፡፡ በግሪክ ኤጲፋኒ ይሉታል፡፡ የኛም ሊቃውንት ቀጥታ በመውሰድ ኤጲፋኒያ እያሉ በዜማ መጻሕፍቶቻቸው ይጠሩታል፡፡ ትርጉሙም ከላይ ከጠቀስናቸው ጋር አንድ ነው፡፡

አስተርአየ የተባለው ግሥ ራሱን ችሎ ሳይለወጥ በአምስቱ አዕማድ የሚፈታ ብቸኛ ግሥ ነው፡፡ ይህም ማለት፡- አስተርአየ፤ ታየ፤ ተያየ፤ አሳየ፤ አስተያየ፤ አየ ተብሎ ይፈታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዘመነ አስተርእዮ ሲያጥር ከጥር 11 ቀን እስከ ጥር 30 ቀን ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት 20 ቀናት ይሆናሉ፡፡ ሲረዝም ደግሞ ከጥር 11 ቀን እስከ መጋቢት 3 ቀን ይሆናል፡፡ ይህም 53 ቀናት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

 

ጌታን ለሐዋርያት ህፅበተ እግር ያደረገበት ቀንም ከጸሎተ ሐሙስ እስከ ጰራቅሊጦስ ቢቆጠር 53 ቀናት ስለሚሆኑ የእነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ዮሐንስ በጥምቀት ዕለት ለልዕልና /ጌታ ሰውን ምን ያህል እንዳከበረው/ ለማሳየት እጁን ከጌታ ራስ በላይ ከፍ እንዳደረገ ጌታም ለትህትና እጁን ከሐዋርያት እግር በታች ዝቅ አድርጎ እግራቸውን አጥቧቸዋልና ነው፡፡ ጥምቀት የህጽበት አምሳል ሲሆን፤ /ህጽበት/ መታጠብ በንባብ አንድ ሆኖ ሁለት ምሥጢራት አሉት፡፡

አንደኛ፤- ምእመናን የእንግዳ እግር እንዲያጥቡ ትምህርት ማስተማሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ለሐዋርያት ጥምቀት ነው፡፡

በጸሎተ ሐሙስ ቢጠመቁም መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት የጰራቅሊጦስ ነውና ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፤ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያን ስለ ቅዱሳን ሐዋርያት ጥምቀት እንደጠየቀውና ጥምቀታቸው ህጽበተ እግር መሆኑን እንደመለሰለት፡፡

 

በሌላ በኩል ከዘመነ ልደት እስከ ጥምቀት ተወልደ፤ ተሰገወ /ሰው ሆነ/ ይባላል እንጂ አስተርአየ አይባልም፡፡ ከጥምቀት በኋላ ግን አብሮ ተባብሮ ተጠምቀ፤ ተወለደ፤ ተሰገወ አስተርአየ ይባላል፡፡ ከጥምቀት በፊት አስተርእዮ ለመባሉ በሦስት ነገሮች ነው፡፡

 

አንደኛ፡- የማይታየው ረቂቅ አምላክ በበረት ተወልዶ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ ቢታይና እንደ ሕፃን ሲያለቅስ ቢሰማም ሰው ሁሉ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው ሙሉ ሰው ይሆናል እንደሚባለው፤ አምላክ ነኝ ብሎ በአንድ ቀን ሳያድግ በጥቂቱ ማደጉንና ስደት እንደ ውርደት ሆኖ እንዳይቆጠር ለሰዎች ጀምሮ ለመስጠት፤ ሄሮድስም ሊገድለው ይፈልገው ስለነበር የሚሰደድበት እንጂ የሚታይበት ስላልነበረ ነው፡፡

 

ሁለተኛ፡- ሰው በተፈጥሮም ሆነ በትምህርት አዋቂ ቢሆን ለሚመለከተው ሥራና ደረጃ እስከ ተወሰነ ጊዜ ይህ ሕፃን ለእንዲህ ያለ ማዕረግ ይሆናል አይባልም፡፡ ተንከባክባችሁ አሳድጉት ይባላል እንጂ፤ አዋቂ ነው አይባልም፡፡ ያውቃል ተብሎም ለትልቅ ደረጃ አይበቃም፡፡ በየትኛውም ሓላፊነት ላይ አይሰጥም ራሱን በመግዛት ይጠበቃል እንጂ፡፡ እንዲሁም ጌታ የመንፈሳዊ እና የሥጋዊ ባለሥልጣን ቢሆንም ፍፁም ሰው ሆኗልና የሰውን ሥርዓት ከኃጢአት በቀር ለመፈጸም በበሕቀ ልሕቀ ይላል፡፡ አምላክ ነኝና ሁሉን በዕለቱ ልፈጽም ሳይል በየጥቂቱ ማደጉን እናያለን፡፡ በዚህም የተነሣ ሰው ሁሉ 30 ዓመት ሲሆነው ሕግጋትን እንዲወክል እንዲወስን እስከ 30 ዓመት መታገሡ ስለዚሁ ነው፡፡ ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን ሰው ቢመቸው ይወፍራል፤ ቢከፋው ይከሳል እንጂ ቁመት አይጨምርም አይቀንስም፡፡ ስለዚህ ጌታ ሙሉ ሰው የ30 ዓመት አዕምሮው የተስተካከለለት ሰው /ጎልማሳ ሆኖ በመታየቱ ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል፡፡

 

ሦስተኛው፤- በ30 ዓመት እሱ ሊጠመቅበት ሳይሆን የመጀመሪያ መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት መሠረት የሆኑ ጥምቀትንና ጾምን ሰርቶ በመሳየትና መመሪያ አድርጎ በመስጠት አምስት ገበያ ያህል ሰው የቃሉን ትምህርት ለመስማት፤ የእጁን ተአምራት ለማየት፤ እሱ ሙሉ ሰው ሆኖ ተገልጾ ትምህርት፤ ተአምራት የሚያደርግበት ሥራዬ ብሎ የመጣበት መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት የተፈጸመበት ዘመን ነው፡፡

 

የታየውም ብቻ አይደለም፤ አብ ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ ሲል መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል ረቂቁ የታየበት የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ምሥጢር የተገለጠበት ስለሆነ ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል፡፡

 

በዚህ ምክንያትም ሌሎች በዓሎችም ይጠሩበታል፡፡ ለምሳሌ ድንግል ማርያም ጥር 21 ቀን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይቶ በደመና ተነጥቃ ወደ ገነት በመግባት ለጻድቃን ሰዎችና ለመላእክት በሰማይና በምድር የተሰጣት ጸጋና ክብር የተገለጸበት ዕለት ስለሆነ በዓሉ አስተርእዮ ማርያም ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በዚህ ቃል ሐሳባቸውን ያስተባብራሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ አምላክ በሥጋ ከድንግል መወለዱን በዚህ አካለ መጠን ለዓለም መገለጡን አስተርእዮ ብሎ ሲናገር፤ አባ ጽጌ ብርሃን ደግሞ በማኅሌተ ጽጌ “የትንቢት አበባ እግዚአብሔር እኛን ሥጋ የሆነውን የአንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደተገለጠ ለእኛም እንዲታወቅ ድንግል ሆይ የወገናችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለማርያም በሰማይ ፍጹም በደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግናለን” ብሏል፡፡ ዳዊትም እንዲህ አለ “በከመ ሰማዕና ከማሁ ርኢነ” መዝ. 47፡6 ፡፡ በነቢያት ይወለዳል ሲባል የሰማነው በበረት ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው እንዲሁም በዮርዳኖስ ሲጠመቅ አየነው፡፡

 

የቤተ መጻሕፍቱን የመረጃ ክምችት በዘመናዊ ለማሳደግ ማእከሉ ጥሪ አቀረበ

ጥር 20 ቀን 2006 ዓ.ም.  

በእንዳለ ደምስስ

“ስትመጣ ….መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ ” 2ኛ ጢሞ4፡13

የማኅበረ ቅዱሳንን ቤተ መጻሕፍት የመረጃ ክምችት ለማሣደግና በዘመናዊ መልኩ ለማደራጀት የ3ኛ ዙር ልዩ የመጻሕፍትና ቤተ መጻሕፍቱን የሚገለግሉ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብ መርሐ ግብር ማዘጋጀቱን የማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማእከል ገለጸ፡፡ ከጥር 2 እስከ ጥር 30/ 2006 ዓ.ም የሚቆየው የመጻሕፍትና የቁሳቁስ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ እና በማኅበሩ የንዋያተ ቅዱሳት መሸጫ ሱቆች ከጧቱ 3፡00 እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ይካሔዳል፡፡

በዚሁ መሠረት ቤተ መጻሕፍቱን ለሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ለተመራማሪዎች፤ ነገ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለሚረከቡ ወጣቶችና ተማሪዎች ትልቅ እገዛ ማድረግ የሚችል በመሆኑ፤ መጻሕፍትን በመለገስ በሥጋም በነፍስም ተጠቃሚ የሚሆን ትውልድ ለመፍጠር የበኩልዎን ድርሻ ይወጡ ዘንድ ተጋብዘዋል፡፡

ቤተ መጻሕፍቱ ከ1996ዓ.ም – 1999 ዓ.ም በጎ ሐሳብ ባላቸዉ አገልጋዮች በለገሱት መጻሕፍት፤ በትንሽ ኮንቴነር ውስጥ ለማኅበሩ አገልጋዮች ብቻ የውሰት አገልግሎት በመስጠት የተቋቋመ ሲሆን፤ የመረጃ ሀብቶቹ ከ500 የማይበልጡ ነበሩ፤ ተገልጋዮችም ውስን ነበሩ፡፡

 

ከ2000 ዓ.ም-2003 ዓ.ም ቤተ መጻሕፍቱ በዲ.ዲ.ሲ. /Dewey Decimal Classification/ ሕግ መሠረት በዕውቀት ዘርፍ ተለይተው እንዲደራጁ በማድረግ ግንባታው ባልተጠናቀቀ የማኅበሩ ሕንፃ ውስጥ የንባብ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የመረጃ ሀብት ክምችቱም በዓይነትና በብዛት ጨምሮ 3000 በማድረስ፤ ጥናታዊ ጽሑፎች ተሰብስበዉ ለአገልግሎት ዉለዋል፡፡

 

በዚህ ወቅት ብዙ መጻሕፍትን በስጦታ ለመሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ከ 400 በላይ መጻሕፍትን አበርክተዋል፡፡ ከ2004 ዓ.ም – 2006 ዓ.ም ባሉት ዓመታትም፤ የመረጃ ሀብቶች ለአያያዝና ለአጠቃቀም በሚያመች ሁኔታ በማደራጀት በምቹ የአገልግሎት ክፍል ውስጥ የንባብ እና የውሰት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ክምችቱም 5000 የታተመ ቅጅ፤ 5000 ያልታተመ ቅጂ ላይ ደርሷል፡፡ አገልግሎቱ በኮምፒውተር የታገዘ በማድረግ በመካነ ድር እና በሶፍትዌር አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በቀን በአማካይ ከ50 ለሚበልጡ ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል፤ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ፖሊሲ እና መመሪያም ተዘጋጅቷል፡፡

 

ከ2007 ዓ.ም – 2009 ዓ.ም ድረስ ክምችቱ ወደ 40,000 /አርባ ሺሕ/ በማሳደግ በሶፍትዌር የታገዘና ቀልጣፋ የE-Library፤ የኢንተርኔት እና የዲጂታል አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ተደርጎ እንዲደራጅ የታቀደ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለጥናትና ምርምር የሚሆን ማዕከላዊ የመረጃ ተቋም ይሆናል፡፡

 

ምእመናን ሙያዊ አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ የመረጃ ምንጮችን (መጻሕፍት፣መጽሔት፣ ጋዜጦች) እና የቤተ መጻሕፍት መገልገያዎችን (ኮምፒዉተር፣ ስካነር፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን፣ ሲዲ፣ ወንበር እና ጠረጴዛ) በመለገስ፤ የቤተ መጻሕፍቱን ደረጃ በማሳደግ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል አቅማቸው የፈቀደውን ልገሳ እንዲያደርጉ የማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማእከል ጥሪ አቅርቧል፡፡

 

የሆሳዕና ቡሻና በዐታ ለማርያም ገዳም ተቃጠለ

 ጥር 13 ቀን 2006 ዓም.                            

በእንዳለ ደምስስ

በሐድያና ስልጢ ሀገረ ስብከት ጎረጎራ ወረዳ ውቅሮ ፋለታ ቀበሌ የደብረ ምጥማቅ ቡሻና በዓታ ለማርያም ገዳም ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የከተራ ዕለት መነሻው ባልተወቀ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መቃጠሉን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ቢኒያም መንቻሮ ገለጹ፡፡bushana

 

ሥራ አስኪያጁ በሰጡን መረጃም የከተራ ዕለት የበዐታ ለማርያም ታቦት ወደ ጥምቀተ ባሕር ከወረደ በኋላ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ መቃጠሉን ገልጸው ቤተ ክርስቲያኑ ንዋያተ ቅዱሳቱን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል ብለዋል፡፡

 

በካዝና ውሰጥ የነበረው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽላት ካዝናው በእሳቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመለብለቡ ምክንያት መክፈት እንዳልተቻለና መቃጠልና አለመቃጠሉን እንዳልተረጋገጠ ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ፤ ጉዳዩን ለፖሊስ በማሳወቅ የቃጠሎውን መንስኤ ለማጥራት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

 

የቡሻና በዐታ ለማርያም ገዳም ከዚህ በፊት ሥዕለ አድኅኖ በዛፎች ላይ ታይቶበት በነበረ ቦታ መቃኞ ተሰርቶለት ሐምሌ 2001 ዓ.ም. ቅዳሴ ቤቱ እንደተከበረ ይታወቃል፡፡

 

ትልቁ በገና

ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም.                                                                                                                                                        

እንዳለ ደምስስ

የማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ክፍል አባላትና የአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል በበገና ድርደራ የሠለጠኑ 250 ወጣቶችን የከተራ በዓልን ለማክበር የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳምን በዝማሬ አጅበው ወደ ጃንሜዳ 06Begenaሰልፋቸውን ይዘው በገናቸውን እየደረደሩ ይጓዛሉ፡፡ አሰላለፋቸውና ብዛታቸው እንዲሁም ጸዓዳ አለባበሳቸው ለዓይን ይማርካሉ፤ እንደ ምንጭ ውኃ ኮለል እያለ የሚፈሰው ዝማሬ ነፍስን ያለመልማል፡፡ ምእመናን በትኩትና በተመስጦ፤ ጎብኚዎች ባዩት ነገር በመገረም የፎቶ ግራፍና የቪዲዮ ካሜራቸውን አነጣጥረው የቻሉትን ያህል ያነሳሉ፡፡

 

በመካከላቸው አንድ በገና ከሁሉም ቁመት በላይ ረዝሞ ይታያል፡፡ ሰልፉ ቆም ሲል ጠጋ ብዬ ተመለከትኩት፡፡ ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ትልቅ በገና አይቼ እንደማላውቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በገናውን የያዙት ልጆች መገረሜን አስተውለው “ይህ በገና በዓለማችን ከሚገኙ በገናዎች ትልቁ ነው፡፡ በገና እግዚአብሔርን ለማመስገን የምትጠቀመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን ብቻ ናት፡፡ እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥም ይህንን በገና በትልቅነቱ የሚስተካከለው የለም” አሉኝ፡፡ በገናውን እንደ ሕፃን ልጅ በፍቅር እንደሚያሻሽ አባት ዳሰስኩት፡፡

 

በገናው ሁለት ሜትር ከሃያ ሳንቲ ሜትር ይረዝማል፡፡ አሥር አውታሮች ሲኖሩት እያንዳንዱ አውታር በስምንት በጎች አንጀት የተሠራ ነው፡፡ አሥሩ አውታሮች በአጠቃላይ በ80 በጎች አንጀት ተዘጋጅተዋል፡፡ ከላይ ያለው ብርኩማ ስልሳ ሳንቲ ሜትር ይረዝማል፡፡ በተጨማሪም በገናውን ለማዘጋጀት የአንድ ትልቅ በሬ ቆዳ ፈጅቷል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን በየዓመቱ በጥምቀት በዓል ላይ ለታቦታት ክብር ሲባል፤ እንዲሁም ሊጠፋ ተቀርቦ የነበረውን የቤተ ክርስቲያናችን ቅርስ ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስና ለትውልድ ለማስተላለፍ በአቡነ ጎርጎርዮስ ሥልጠና ማእከል ወጣቶችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡

 

ለጥምቀት በዓል በክብር የወጡት ታቦታት በክብር ተመልሰዋል

 ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ለጥምቀት በዓል ከመንበራቸው በክብር የወጡት ታቦታት ወደመጡበት አብያተ ክርስቲያናት በእልልታና በዝማሬ ታጅበው ተመልሰዋል፡፡ከሌሊቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ 06Epiphany17ተክለ ሃይማኖት ፤ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዩልዮስ፤ ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የመንግሥት ተወካዮች ጋር በመሆን በጃንሜዳ ጥምቀተ ባሕር ተገኝተዋል፡፡

 06Epiphany21

በቅዱስነታቸው መሪነት የጸሎተ ወንጌል ሥርዓት በማድረስ በዐራቱም ማእዘናት፤ ከዐራቱም የወንጌል ክፍሎች ዕለቱን በማስመልከት ምንባባት ተነበዋል፡፡ ቀጥሎም ቅዱስነታቸው ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሆነው ጸበሉን ባርከው  ለምእመናን ረጭተዋል፡፡

 

የጥምቀት ሥነሥርዓቱ ቀጥሎም የወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሰንበት ትምህርት ቤቱ መዘምራን ዕለቱን በማስመልከት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡06Epiphany22የሕንድ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዩልዮስ ባስላለፉት መልእክት “የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እኅትማማቾችና የቀረበ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡  በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ታሪክና ትውፊት ያላት በመሆኗ የጥምቀት በዓልን በደመቀና ማራኪ በሆነ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት የምታከብር ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን ናት” ብለዋል፡፡

 

 

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በመጨረሻ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ይቀድስ፤ ያጣነውን ልጅነት ይመልስልን ዘንድ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ሰላሙንም አደለን፡፡ ይህንንም ጠብቀን መኖር ይገባናል” ብለዋል፡፡

 

በመጨረሻም በትናንትናው ዕለት በክብር ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር የወረዱት ታቦታት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ምአመናን ታጅበው ወደየመጡበት በክብር ተመልሰዋል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ታቦታት ግን በነገው እለት የሚመለሱ በመሆኑ በዚያው ይገኛሉ፡፡

 

የጥምቀት በዓል አከባበር በጃን ሜዳ

 ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም

የከተራ በዓል ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም. በጃሜዳ ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ የዋለ ሲሆን፤ ምሽቱን ደግሞ በስብከተ ወንጌልና በዝማሬ ቀጥሎ በሥርዓተ ቅዳሴ ተፈጽሟል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የጥምቀተ ባሕር ቦታዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የከተራ በዓል በድምቀት ተከብሯል፡፡

ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሌሊቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች እየተካሔዱ ሲሆን፤ ጃን ሜዳ የሚካሔደው ሥነሥርዓት ቅዱስነታቸውና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በጸሎተ ወንጌል ተጀምሮ የጥምቀት መርሐ ግብሩ ይቀጥላል፡፡ የእለቱ ተረኛ የሆነው የወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ዝማሬ የበዓሉ አካል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

 

የከተራ በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት ተከበረ

 

 

ጥር10 ቀን 2006                                                                                                                      ዳንኤል  አለሙ  ደብረ ታቦር ማእከል

በደብረ ታቦር ከተማ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሰት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ማኅበራት እንዲሁም ሕዝበ ክርስቲያኑ ከሰባት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት የመጡ ታቦታትን አጅበው በአጅባር ባሕረ ጥምቀት በድምቀት ተከበረ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቱ ታባታቱን በቃለ እግዚአብሔርና በቅዱስ ያሬድ ዜማ፤ ከሰ/ትቤት መዘምራንና ምእመናን ጋር በምስጋናና በእልልታ በማጀብ በዓሉን አድምቀውታል፡፡

የከተራ በዓል መንፈሳዊ ይዘት በተሞላበት ሁኔታ በነጫጭ አልባሳት በደመቁ ምእመናን እና ምእመናት ተከብሮ ሲውል፤ ለከተማው ህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባጃጆች በባንዲራ እና ምስጢረ ጥምቀቱን በሚገልፁ ጥቅሶች ተውበው የተለየ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡ በተጨማሪ ታሪካዊ እና ለታላቁ ደብር ለደብረ ታቦር ኢየሱስ በወጣቶች የተሰራ ሰረገላ በዓሉን ካደመቁት ትእይንቶች መካከል አንዱ ነበር፡፡

ደብረ ታቦር ለሀገሪቱ ሊቃውንት መፍለቂያ በመሆን በምሳሌነት የሚጠሩ ካህናት እንደተለመደው ሁሉ የሚማርክ ጣዕመ ዝማሬአቸውና በአባቶችሽ ፈንታ ልጆችሽ ተተኩልሽ እንዳለ ነብዩ ከሊቃውንቱ እግር ሥር ቁጭ ብለው የተማሩ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ የደብረ ታቦር ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤትም ለበዓሉ አከባበር የሚሆን የድምጽ ማጉያ በመስጠት እንዲሁም ከደብረ ታቦር ወረዳ ቤተ ክህነትና ማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር የሀገሪቱን ባሕልና እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን አድርገዋል፡፡

የከተራ መርሐ ግብሩ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የ4ቱ ጉባኤ መምህር የሆኑት የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ትምህርት፤ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ እርሳቸውም በዓለ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው አበይት በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ታቦቱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው የሚያድሩበት ምክንያት እግዚአብሔር ወልድ በፈለገ ዮርዳኖስ መጠመቁ ምሳሌ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በጥምቀቱም የሰው ልጅ ኃጢዓት የተደመሰሰበት፤ ከኃጢዓት ባርነት የወጣበት መሆኑን ገልጸው ምእመናን ዳግመኛ ወደ ኃጢዓት ባርነት እንዳይመለሱ መትጋ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ የጥምቀትን በዓልን ስናከብር ድኅንነት ነፍስን የምናገኝበት ከኃጢዓት ጸድተን የዘላለም ሕይወት የምንወርስበት በመሆኑ በሰላምና በፍቅር እንድናከብረው አበክረው አሳስበዋል፡፡

በዓለ ጥምቀቱ የሚከበርበት አጅባር ሜዳ አራት የታቦታት መግቢያ በሮች ያሉት ሲሆን ለብዙ ዘመናት ቅድስት ቤተክርስቲያን እየተገለገለችበት ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ በሀገረ ስብከቱና በወረዳ ቤተ ክህነቱ ፈቃድና እውቅና የተቋቋመ ኮሚቴ ቢኖርም የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ አለመኖሩ፤ በህዝቡ ዘንድ ስጋት የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ስለሆነም የሀገር እና ቤተክርስቲያን ሀብት በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ተሰጥቶት የይዞታ ማረጋገጫ ሊኖረው እንደሚገባ አባቶች እና የአካባቢው ምእመናን ገልጸዋል፡፡

 

የከተራ በዓል በጃንሜዳ በድምቀት ተከበረ

  ጥር 10/2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ 

የከተራ በዓል በጃን ሜዳ ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራንና ምእመናን እንዲሁም የተለያዩ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮችችና ሀገር ጎብኚዎች በተገኙበት በድምቀት ተከበረ፡፡06Epiphany19

06Epiphany20ከአሥራ አንድ ታቦታት በላይ ከየአብያተ

ክርስቲያናት በክብር በመውጣት በዝማሬና በእልልታ እንደታጀቡ ወደ ጃንሜዳ አምርተዋል፡፡ የእለቱ ተረኛ አዘጋጅ የሆነው የደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት፤ በፍስሐ ወበሰላም” በማለት እለቱን06Epiphany18 በማስመልከት ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡ የደብሩ ፍቁረ እግዚእ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላትም “በሰላም አስተርዐየ፡ አስተርዐየ ወልደ አምላክ፤ ወተወልደ በሀገረ ዳዊት ተወልደ፤ በዮርዳኖስ ተጠምቀ ከመይቤ ዘወነ” እያሉ ዝማሬ በማቅረብ በዓሉን አድምቀውታል፡፡

06Epiphany15

ስለበዓሉ አከባበር ከሰሜን አሜሪካ የመጣችው ሀገር ጎብኚ በዓሉን አስመልከተን ላቀረብንላት ጥያቄ ስትመልስ “ከዚህ በፊት ለአንድ ጊዜ የመስቀልን በዓል አከባበር ተመልክቼ ነበር፡፡ እሰከዛሬም ከምደነቅባቸው ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ የጥምቀት በዓላችሁ ደግሞ የተለየ ነው፡፡ ልታከብሩትና ልትኮሩበት ይገባችኋል” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

06Abune Mathias

 

በመጨረሻም ቅዱስነታቸው በሰጡት ቃለ ምእዳን “ጌታን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ መጣ፡፡ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመናት በላያችን ተጭኖ የነበረውን መርገመ ነፍስ መርገመ ሥጋን አስወግዶ በረከተ ነፍስ በረከተ ሥጋን ለማደል በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡ ኃጢዓታችንንም አስወገደ፡፡ ከዲያብሎስ ቁራኝነትም አላቀቀን፡፡ ወደ ወገኖቹ መጣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፡፡ ነገር ግን ለተቀበሉት የእግዚአብሔር ልጅ መባልን ሰጣቸው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን የተጠራነው በጥምቀት ነው” ብለዋል፡፡ 

 

የከተራ በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው

ጥር 10/2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የከተራ በዓል በመላው ኢትዮጵያ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ታቦታት በብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት፤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በሰንበት ትምህርት ቤተ መዘምራንና ምእመናን ታጅበው ወደ ጥምምቀት ባሕር በማምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ፤ የቅዱስ በዓለ ወልድ፤ የታዕካ ነገሥት በዐታ ለማርያም፤ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም፤ የመንበረ መንግሥት ቅዱሰ ገብርኤል ታቦታት በአንድነት በመሆን ወደ ጃን ሜዳ በማምራት ላይ ይገኛሉ የሌሎቹም አድባራትና ገዳማት ታቦታት ወደ ጃን ሜዳ በመቃረብ ላይ ናቸው፡፡

06Epiphany1    06Epiphany2   06Epiphany3

 

 06Epiphany4

ዝግጅት ለጥምቀት በዓል

 

IMG 0062የጥምቀት በዓል በኢትጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ የጥምቀት በዓልን በአደባባይ በማክበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብቸኛዋ ቤተክርስቲያን  ስትሆን ከተለያዩ ዓለማት የበዓሉ ታዳሚ ለመሆን የእምነቱ ተከታዮችና ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ወደ ጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች ይሄዳሉ፡፡ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ለታቦታቱ ማረፊያና ለበዓሉ ማክበሪያ የተለያዩ ዝግጅቶች ይከናወናሉ፡፡
 ካህናትና ምእመናን  ለበዓሉ የሚስማማ ልብስ በመልበስ ታቦታቱን በማጀብ  ከከተራ ጀምሮ በዝማሬና በእልልታ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡
ሰሞኑንም በሀገራችን የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎችና ታቦታቱ የሚጓዙበት መንገዶች ሲጸዱና ሲያሸበርቁ ሰንብተዋል፡፡ ጥቂት ቦታዎችን ለመጎብኘት ሞክረናል፡፡

አዲስ አበባ
በአዲስ አበባ ከተማ 46 የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች አሉ፡፡ ወደነዚህ ቦታዎች የሚወስዱ መንገዶች ሁሉ እየጸዱ በኢትዮጵያ ባንዲራ፣ በዘንባባና በቄጤማ እያሸበረቁ ይገኛሉ፡፡
በአራዳና በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቶች ያገኘነው መረጃ እንደሚገልጸው፡-
1.    በጃንሜዳ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ከአስራ አንድ ባላይ ታቦታት የሚያድሩ ሲሆን እነሱም መንበረ ፓትርያርክ ቅ/ቅ/ማርያም ገዳም፣ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም፣ መ/ፀ/ቅ/ሥላሴ፣ መ/መ/ቅ/ገብርኤል፣ ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ፣ ቀጨኔ ደ/ሰ መድኃኔዓለም፣ መንበረ ልዑል ቅ/ማርቆስ፣ ወ/ነጎድጓድ ቅ/ዮሐንስ ፣ገነተ ኢየሱስ፣ መ/ህ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ አንቀጸ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ሲሆን የ2006 ዓ.ም በዓል መንፈሳዊ አገልግሎት አቅራቢ ተረኛ የወ/ነጎድጓድ ቅ/ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

IMG 0034IMG 0045

2.    ወረዳ 13 ቀበሌ 16 ቀበና ሼል አካባቢ ቀበና መድኃኔዓለምና ቀበና ኪዳነምሕረት
3.    በጉለሌ እንጦጦ ተራራ  መ/ፀ ር/አድባራት ቅ/ማርያም እና እንጦጦ ደ/ኃ/ቅ/ራጉኤል
4.    ሽሮ ሜዳ አካባቢ
መንበረ ስብሐት ቅ/ሥላሴ፣ ሐመረ ኖህ ቅ/ኪዳነ ምሕረት
5.    ወረዳ 11 ቀ. 27 ቁስቋም አካባቢ መ/ንግሥት ቁስቋም ማርያም
6.    አዲሱ ገበያ በላይ ዘለቀ መንገድ አካባቢ ደ/ሲና እግዚአብሔር አብ፣ መንበረ ክብር ቅ/ሚካኤል እና አቡነ ተክለሃይማኖት
7.    ጉለሌ አምባ ቅ/ኪዳነ ምሕረትና ድልበር መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን
8.   ወረዳ 11 ቀበሌ 20 ፡-ገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፤ የረር ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ቦሌ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን
9.   ወረዳ 17 ቀበለሌ 24 /ለምለም ሜዳ/፡-ደብረ ምጽላል እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን፤
10.  ወረዳ 17 ቀበሌ 2 ወንድራይድ ት/ቤት አካባቢ፡- 7 አብያተ ክርሰቲያናት
11.  ወረዳ 28፡- ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም፤ አቡነ አረጋዊ፤ ቅዱስ ኡራኤል
12.  ወረዳ 16/17 ቀበሌ 1፡- ደብረ እንቁ ልደታ ለማርያም፤
13.  ሎቄ ገበሬ ማኅበር፡- ሎቄ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
14.  ወረዳ 17 ገበሬ ማኅበር፡- ቦሌ ቡልቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስ
15.  ወረዳ 28 ገበሬ ማኅበር ቀበሌ 14/15 ሲኤም ሲ፡- ሰሚት ኪዳነ ምሕረት፤ ቀሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤  ወጂ መድኀኔዓለም
16.  ቦሌ 14 /15፡- መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል፤ የረር ቅዱስ ገብርኤል፤ የረር ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ
17.  ወረዳ 28 ገበሬ ማኅበር፡-  ደብረ ኢያሪኮ እግዚአብሔር አብ
18.  ራስ ኃይሉ ሜዳ/ መድኀኔዓለም ትምህርት ቤት አካባቢ፡- ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል፤ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል፤ ጽርሐ አርያም ሩፋኤል፤ ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጼጥሮስ ወጳውሎስ፤ ጠሮ ሥላሴ
19.  ትንሹ አቃቂ ወንዝ/ ገዳመ ኢየሱስ/፡- ቀራንዮ መድኀኔዓለም፤ ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል፤ ቅዱስ ጳውሎስ፤ ገዳመ ኢየሱስ፤ ደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ፤ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፤ ፊሊዶር አቡነ ተክለ ሃማኖት
20.  አስኮ ጫማ ፋብሪካ / ሳንሱሲ አካባቢ፡- አስኮ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል፤ ኩርፎ ቅዱስ ጊዮርጊስ
21.  ወረዳ 25 ቀበሌ 25 አካባቢ፡- ደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ገብረ ክርስቶስ፤ ደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ አውጉስታ ቅድስት ማርያም፤ ዳግማዊት ጸድቃኔ ማርያም፤
22.  ወረዳ 24 ቀበሌ 15፡- አየር ጤና ኪዳነ ምሕረት፤ ጀሞ ሥላሴ፤ ደብረ ራማ ቅዱስ ገብርኤል
23.  ቃሌ 15 ቀበሌ፡- ቃሉ ተራራ አቡነ ሃብተ ማርያም፤ ፍኖተ ሎዛ ቅድስት ማርያም
24.  አያት ቤተ ሥራዎች ድርጅት፡- መሪ አቡ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፡- መሪ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፤ ቅዱስ ሩፋኤል፤ መሪ ቅድስት ሥላሴ
25.  ወረዳ 28 ገበሮ ማኅበር፡- ኢያሪኮ እግዚአብሔር አብ
26.  ቤተል ኳስ ሜዳ፡- ደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል፤ አንፎ ቅዱስ ኡራኤል
27.  ወረዳ 18 ቀበሌ 26፡- ቅዱስ እስጢፋኖስ፤ ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ
28.  ወረዳ 16 ቀበሌ 11 ኳስ ሜዳ፡- ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል፤ የካ ቅዱስ ሚካኤል
29.  አድዋ ፓርክ፡-ቦሌ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም

IMG 0056

ከአዲስ አበባ ወጪ የሚገኙ አኅጉረ ስብከት በከፊል
  የበዓለ ጥምቀት ዝግጅት በጎንደር – ፋሲለደስ፡-
ቀሃ ኢየሱስ፤ ዮሐንስ መጥምቅ፤ አባ ጃሌ ተክለ ሃማኖት፤ እልፍኝ ቀዱስ ጊዮርጊስ፤ ፊት ሚካኤል፤ አጣጣሚ ሚካኤል፤ መንበረ መንግሥት መድኀኔዓለም
ፋሲለድስ መዋኛ ፡- 8 ታቦታት
ልደታ ለማርያም
በዓታ ለማርያም
   አቡነ ሐራ – ሩፋኤልን ዞሮ ይገባል
በጎንደር ዙሪያ በሚገኙ 13 ቀበሌዎች፤ 13 ክፍለ ከተማዎችና የገጠር ቀበሌዎች

በሐዋሳ  የበዓለ ጥምቀት ዝግጅት
ፒያሳ ሔቁ አካባቢ፡- ደብረ ምጥማቅ መድኃኔዓለም
ቅዱስ ገብርኤል
ቅድስት ሥላሴ
ፋኑኤል
በዓለ ወልድ
ዳቶ ኪዳነ ምሕረት
ሐዋሳ መግቢ በይርጋለም ሞኖፖል አካባቢ፡- ደብረ ምጥማቅ መድኃኔዓለም፤ አቡነ ተክለ ሃማኖት፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የበዓለ ጥምቀት ዝግጅት በሚዛን ተፈሪ
በሚዛን ተፈሪ ከተማ በሚዛንና አማን ክፍለ ከተማ ለሚከበረው  በዓል ከከተራው  ጀምሮ የከተማዋን ዋና መንገድ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ  የማስዋብ ስራ በከተማው የእምነቱ ተከታይ ወጣቶች ተሰርቷል:: በከተማው የዘንድሮው የበዓሉን ዝግጅት ተረኛ የሆኑት የአቡነ ተክለሀይማኖት የእናቶች አንድነት ገዳምና የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን ለታቦታት ማደርያና እንዲሁም ለስርኣተ ማኅሌቱና ቅዳሴው የሚከናወንበት ድንኳን በሰበካ ጉባኤያት አስተባባሪነት፣ በወጣት ሰንበት ተማሪዎች ፣ በሚዛን መዕከል አባላት፣ በሚዛን ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችና በአካባቢው የሚገኙ የእምነቱ ተከታይ ወጣቶች ተባባሪነት የጥምቀተ ባህር ማክበርያ ቦታ ጽዳት ከተደረገ በኋላ ድንኳንና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማቅረብ በዓሉን ለማድመቅ ተዘጋጅተዋል::
በዓሉ የሚከበረው በሁለት የጥምቀተ ባህር ስፍራዎች ኮሶኮልና አማን ጥምቀተ ባህር ናቸው፡፡  በሚዛን ክፍለ ከተማ ከሾርሹ በዓለ ወልድ አንድ ታቦት፣ ከሚዛን ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ሁለት ታቦታት፣ ከሚዛን ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሁለት ታቦታት፣ ከሚዛን ማረሚያ ቤት ቅዱስ ሚካኤል  አንድ ታቦት በተለምዶ ኮሶኮል ወደሚባለው ጥምቀተ ባህር ጉዟቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ፣ በአማን ክፍለ ከተማ ደግሞ ከደብረ መድኀኒት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ታቦታት፣ ከቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አንድ ታቦት፣ ከደብረ ሰላም ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ሁለት ታቦታት፣ ከዛሚቃ አባ ሳሙኤል ገዳም አንድ ታቦት፣ ከቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ታቦት ፣ ከመንበረ ንግስት ቅድስት ቁስቋም ቤተ ክርስቲያን አንድ ታቦት ወደ አማን ጥምቀተ ባህር እንደሚዎጡና በአጠቃላይ ቁጥራቸው አስራ አራት የሚሆኑ ታቦታት ወደ ሁለቱ ጥምቀተ ባህር እንደሚያመሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ::
ወጣቶች እንደተለመደው ዘንድሮም ሕዝቡ በግፍያ እንዳይጎዳና መጨናነቅ እንዳይፈጠር ታቦታት በሚያልፉበት መንገድ ላይ ምንጣፍ እየተሸከሙ በማንጠፍ ባለፉት ጊዜያት ያሳዩት የነበረው አገልግሎት ዘንድሮም ለቤተ ክርስቲያናቸውና ለእምነታቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር ለማሳየት ተዘጋጅተዋል፡፡ /ከሚዛን ማዕከል ሚድያ ክፍል/

የጥምቀት በዓል ዝግጅት በወልድያ
በወልድያ ከተማ የጥምቀት በዓል ከዋዜማው ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በድምቀት እንደሚከበር ተገለፀ፡፡
የሰሜን ወሎ ሃገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ኃላፊና የወልድያ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ኃይል ስጦታው ሞላ የበዓሉን አከባበር አስመልክተው በሰጡት መረጃ በከተማው ውስጥ ያሉ አድባራትና በዙሪያው የገጠር አብያተ ክርስቲያናት የከተራ በዓሉን በወልድያ ታቦት ማደሪያ በአንድ ላይ ያከብራሉ፡፡
በከተማውና በዙሪያው ያሉ የ10 አብያተ ክርስቲያናት 15 ታቦታት ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ ወደ ታቦት ማደሪያው እንደሚንቀሳቀሱና ምዕመናንም በሰዓቱ ተገኝተው የሚከብሩ ሲሆን፤ ምዕመናን በዓሉን በሰላምና በፍቅር እንዲሁም ጧሪ የሌላችውን አረጋዊያንና አሳዳጊ የሌላቸው ህፃናትን በመርዳት እንድያከብሩ ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
ከባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ በበዓላት አከባበር ወጣቱ እያሳየው ያለው ተሳትፎና ሥነ-ስርዓት እጅግ የሚያስደስት በመሆኑ በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚጠበቅ ሲሆን፤
ታቦታቱ ጉዞ የሚያደርጉበትን ጎዳናዎች በማፅዳት፣ ሠንደቅ ዓላማዎችን በመስቀል፣ ምንጣፍ በማንጠፍና ቄጤማ በመጎዝጎዝ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር ሰ/ት/ቤቶች፣ ማኅበራትና ወጣቶች ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በዕለቱ መዝሙር፣ ዕለቱን የተመለከተ ስብከተ ወንጌልና ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች ከተካሄዱ በኋላ 11፡30 ላይ ታቦታቱ ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ ይገባሉ፡፡ በዚሁ የዋዜማ በዓሉ ፍፃሜ ይሆናል፡፡ /ወልድያ ማዕከል  ሚድያ ክፍል/