መሠልጠን ማለት ግን ምን ማለት ነው?!

በዲ/ን ቴዎድሮስ በየነ

 

ሥልጣኔ ሲተነተን አንድ ገጽታ፣ አንድ መልክ፣ አንድ ወጥ ሳይሆን ብዙ መልኮች፣ ብዙ ገጽታዎች እንዳሉት ማጤን ይገባል፡፡ ሥልጣኔ የሰው ልጅ አካባቢውን ለኑሮ እንዲስማማው፣ እንዲመቸው ለማድረግና ለሕይወቱ የተመቻቸ ሥፍራ ለማድረግ የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ቀስ በቀስ የተከሰተ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ሥልጣኔ ጥንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ለወደፊትም የሚኖር የሰው ልጅ የተፈጥሮ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሆኖም ግን ስለ ሥልጣኔ ብይን ሲሰጥ፣ ስለ መግለጫው ሲነገር፣ ስለ ጥቅሙ ሲዘመር፣ ስለ ግቡ /መዳረሻው/ ሲታተት፤ ሥልጣኔ ከቁሳዊ ነገር መሟላትና ከሥጋዊ ድሎትና ምቾት ጋር ብቻ ሲያያዝ ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ይመስላል የሥልጣኔን ክስተት በዓይን በሚታዩ፣ አብረቅራቂና ሜካኒካዊ በሆኑ ነገሮች ብቻ እንድናይ ከታች ጀምሮ በትምህርት ቤት እንድንማረው የሆነው፡፡ በሚዲያ ዘወትር እንድንሰማው የተደረገው፡፡ከበደ ሚካኤል ስለ ሥልጣኔ ምንነት ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፡፡

 

“ሰዎች ራሳቸውን ለማረምና ኑሯቸውን ለማሻሻል ሲሉ በሥጋና በመንፈስ ያፈሩት ከመጀመሪያ ጀምሮ አሁን ድረስ የተከማቸው የሥራ ፍሬ ሥልጣኔ ይባላል፡፡”

በእኚህ ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ የሥልጣኔ ምንነት ገለጻ ውስጥ በዚህ ዘመን ሚዛን ላይ ያልወጡ ታላላቅ ቁምነገሮችን አምቆ ይዟል፡፡ ከነዚህም ውስጥ “በሥጋና በመንፈስ” በማለት ለሰው ልጅ የህላዌው መሠረት፣ የደስታው ምንጭ ሥጋዊ ፣/ቁሳዊ/ ነገር ብቻ እንዳልሆነ አስምረውበታል፡፡ መንፈሳዊም ፍሬም ሥልጣኔ እንደሆነ፡፡ ሥልጣኔ ከመጀመሪያ ጀምሮ አሁን ድረስ የተከማቸ የሥራ ፍሬ ነው ሲሉም፤ ሥልጣኔ የዛሬ ሦስት መቶ ወይም አራት መቶ ዓመት ክስተት ብቻ አይደለም ማለታቸው ነው፡፡

ዘመናዊ ሥልጣኔን ከምዕራባውያን ሥልጣኔ ጋር ብቻ አያይዞ የሥልጣኔ መልክና ገጽታ በምዕራባውያን መስታወት ብቻ የሚታይ እንዳልሆነም የጸሐፊው እይታ ያሳያል ፡፡

 

ዛሬ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሥልጣኔ ማለት ምዕራባዊ መስሎ መቅረብ፣ የምዕራብ ቋንቋን መናገር፣ የምዕራባውያንን የአኗኗር ዘይቤ መያዝ ይመስላል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያውያን ሠርግ ሲዘፈን እንደነበረው “የእኛ ሙሽራ ኩሪባቸው በእንግሊዝ አናግሪአቸው” የምዕራብ ቋንቋ መናገር የኩራት ምልክት፣ የሥልጣኔ ምልክት ነበር፡፡ ይህ ግን ስህተት እንደሆነ ኤቪሊንዎ የተባለ አንድ ምዕራባዊ ጸሐፊ ኢትዮጵያ ኋላቀር ነች እያሉ የሚተቹትን በነቀፈበት ጽሑፉ እንዲህ ይላል፡-

“የአንድን ኅብረተሰብ ትልቅነት የምትገምተው አውሮፓን ስላልመሰለ ወይም የ”ሰለጠኑ” አገራትን ስላልመሰለ ሳይሆን በራሱ እምነትና የእሴት ስልት ውስጥ የተቃረነ ነገር ሲሠራ ነው፡፡”

የዚህ መጣጥፍ ዐቢይ ጭብጥ ሥልጣኔ ከራስ እሴት አለመቃረን ነው የሚል ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ትውፊታችን፣ ባህላችንና ታሪካችን የኢትዮጵያውያን እሴቶች ምንነትን ይነግሩናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዛሬ እዚህ ላይ የምናየው ስለ ከበረው የዳኝነት /ፍትሕ/ ሥርዓት እሴታችን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ረዥም ዘመን ታሪካችን የዳኝነት ሥርዓት የተከበረ ነው፡፡ ፈረንጆች “the rule of law /ሕጋዊ ሥርዓት/” የሚሉትን የኢትዮጵያ ሕዝብ “የሕግ አምላክ” ይለዋል፡፡

በቆየው የኢትዮጵያ ባሕል አንድ ሰው ከመንገድ ላይ ባላጋራውን ካየ “በሕግ አምላክ ቁም” በማለት ብቻ ባላጋራውን አስቁሞ የነጠላዎቻቸውን ጫፍ ቋጥረው /ተቆራኝተው/ ያለ ፖሊስ አጀብ ወደ መረጡት ዳኛ ዘንድ ሄደው ፍርዳቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡

“በቆረጡት በትር ቢመቱ፤ በመረጡት ዳኛ ቢረቱ፤ የእግዜር ግቡ ከብቱ፡፡” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በቀድሞ ዘመን “የተበደለ ከነጋሽ፤ የተጠማ ከፈሳሽ” ብለው፤ የተጠማ ውሃን እንደሚሻ ሁሉ የተበደለም ጉዳቱን ለንጉሡ አሰምቶ ትክክለኛ ፍርድ እንደሚያገኝ ያምኑ ነበር፡፡ በዚህም ምኞትና ሐሳቡን የፈጸሙ የመንፈስ ልዕልና ደረጃቸውን ያሳዩ ፈታሔ ጽድቅ /እውነተኛ ዳኞች/ በታሪኩ አይቷል፡፡ አጼ ዘርአያዕቆብ /15ኛው መቶ ክ/ዘ/፤ ልጃቸው የደሀ ልጅ ገድሎ በዳኞቻቸው ዘንድ በቀላል ፍርድ ስለ ተለቀቀ ይግባኙን ንጉሡ ወስደው የሞት በቃ ፈርደው እንዳስገደሉት ይታወቃል፡፡ ይህ ምንም ርትዕ ቢሆን፤ ከአብራክ በተከፈለ ልጅ ላይ ሞትን መፍረድ ሐቀኝነት ነው፡፡ በሌላ ዘመንና ቦታም ይህ ተመሳሳይ ታሪክ በትግራዩ ራስ ልዑል ሚካኤል ስሑል /18ኛው መ/ክ/ ተፈጽሟል፡፡ ሁለቱም ከግል ጥቅማቸው በተቃራኒ ቆመዋል፡፡ ይህ ነው ኢትዮጵያዊው መልካም እሴት፡፡ ሁለቱም መሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ሲጓደል በብርቱ እንደሚያዝን፤ ምንም የተወሰደው ሀብት ዋጋው ያነሰ ቢሆን በዳኝነት መዛባት እጅግ አድርጎ እንደሚቆጭ ያውቃሉ፡፡ “በፍርድ ከሄደችው በቅሎዬ፤ ያለ ፍርድ የሄዳችው ጭብጦዬ ታሳዝነኛለች” የሚል ጽኑ የፍትሕ ጥማት እምነቱ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ እነርሱም የርትዕ ፍርድ ታላቅነት አሳዩት፡፡

ስለዚህም የአንድ ሥልጡን ማኅበረሰብ አንዱ መገለጫው ይህን ከመሰለ ባሕላዊ እሴቱ ጋር አለመጋጨቱ፤ አለመቃረኑ ነው፡፡ ስለ ሥልጣኔ ስናወራ ለሥጋ እርካታ መገለጫ የሆነችውን የአብረቅራቂ ቁስ ሙሌትን ብቻ ይዘን መጓዝ የለብንም፡፡ የከበሩ የባሕልና የታሪክ እሴቶቻችንም የሥልጣኔ ማነጸሪያዎች ናቸው፡፡ የሰው ልጅን ማንነትና ፍላጎት በቁሳዊ ነገር ብቻ መመዘንም፤ ሰውን ከሰውነት ደረጃ ማውረድ ነው፡፡ በዚህ መተማመን ከተደረሰ አንድ ሥልጡን ማኅበረሰብ ለመገንባት በምናደርገው ጉዞ ውስጥ ሥልጣኔን በግንጥል ጌጧ ሳይሆን በሙሉ ክብሯ እንረዳታለን ማለት ነው፡፡

ዛሬ ጊዜና ታሪክ በሰጡን ኃላፊነት ላይ ያለን ሁሉ “ደሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ” የማንል ከሆነ፤ ከግል ጥቅም ይልቅ ለብዙኃኑ ጥቅም ካልቆምን? የሰው እንባ እሳት ነው ያቃጥላል ካላልን? ከራሳችን የእምነትና የእሴት ስሌት በተቃራኒ ስለቆምን በእውነት አልሰለጠንም፡፡

ውድ አንባቢዎች አፄ ዘርአያዕቆብና ራስ ልዑል ሚካኤል ስሑል በልባቸው ካለው የእምነትና የእሴት ስሌት በተቃራኒ ያልቆሙበት ምክንያት /ሠልጥነው የታዩበት ምሥጢር/ የሚከተሉት አራቱ ይመስሉኛል፡፡

1. እግዚአብሔር አለ፤ እሱ ይፈርዳል፤ በምንሰጠው ፍርድ እሱ ይመለከታል ብለው ማመናቸው፡፡

2.  ሕሊና አለ፤ እሱን ማምለጥ አይቻልምና ብለው ለሕሊናቸው በመገዛታቸው፡፡

3. ታሪክ አለ፤ ታሪክ ይፋረደናል፤ የምንሠራውን ነገር ለታሪክ ትተነው የምንሄድ ነን፤ ከታሪክ ማምለጥ አንችልም ብለው በጽናት መቆማቸውና፣

4.  ሕዝብ አለ፤ የተደረገውን ስለሚያውቅ ይመለከተናል፡፡ ይታዘበናል፡፡ ከእነዚህ ነገሮች ማምለጥ አንችልም ብለው በመንፈሳዊ ወኔ መቆማቸው ነው፡፡

ስለ እውነተኛ ዳኝነት ከቱባ ባሕላችን ውስጥ መዘን ስናጠና የምናገኘው የትልልቆቹን መሪዎች፣ የከበሩት አበውና፣ የሚደነቁት እመው ያልተዛባ ፍርድ ክዋኔ ምሥጢሩ፤ በምንሠራው ሥራ፤ በምንሰጠው ፍርድ እግዚአብሔር፣ ሕሊና፣ ታሪክና ሕዝብ አለ ብለው ማመናቸው ነው፡፡ ከሰፈር የዕቁብ ዳኝነት እስከ ሀገር ማስተዳደር፤ ከማኅበር ሙሴነት እስከ ቤተ ክርስቲያን መምራት የቻለ ሰው በሚያስተላልፈው ውሳኔና በሚሰጠው ፍርድ ውስጥ ከላይ ያየናቸውን አራቱን የባሕላችንን እሴቶች በልቡናው ጽላት ቀርጾ በእነርሱ መመራት ካልቻለ፡፡ ፍትሕ ትጨነግፋለች፡፡ እውነት ከምድሩ ትጠፋለች፡፡ ፍቅር ጓዟን ጠቅልላ ትበናለች፡፡ ክህደት ታብባለች፡፡ ማስመሰል ትነግሳለች፡፡ ውሸት ትወፍራለች፡፡ ሥልጣኔ ቅዥት ትሆናለች፡፡

ይቆየን…..