“አባታችን ሆይ” ክፍል አንድ

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

መግቢያ

አንባቢያን ሆይ ይህ ጽሑፍ የትርጉም ሥራ ሲሆን ትምህርቱም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስን ወንጌል ሲተረጉም ከጻፈው ላይ የተወሰደ ነው፡፡ የዚህ ቅዱስ አባት ሥራዎች ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ ታላቁ ጸሐፊ /The great author/ ተብሎ ነው በሥነ መለኮት ምሁራን የሚታወቀው፡፡ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን የጸሎት ሥርዐት ይህ ቅዱስ እንዴት አድርጎ ድንቅ በሚባል መልኩ እንደተረጎመው ትመለከቱ ዘንድ እነሆ ብለናል፡፡


ግብዞችን አትምሰሉአቸው

ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባና መዝጊያህንም ዘግተህ በሥውር ላለው አባትህ ጸልይ በሥውር የሚያይህ አባትህ በግልጽ ይከፍልሃል፡፡” /ማቴ.6÷1-6/

በዚህ ቦታ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ግብዞች ማለቱ አግባብነት ነበረው፡፡ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሐር ቤት ለጸሎት በሚመጡበት ጊዜ የሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ሲሉ ከሥርዓት የወጣ አለባበስን ይለብሱ ነበር እንጂ ለጸሎት ተስማሚ የሆነውን የትሕትና አለባበስን አይለብሱም ነበርና ነው፡፡

ለጸሎት ወደ አምላኩ የሚቀርብ ሰው ሌሎች ጉዳዮቹን ሁሉ ወደ ኋላ ትቶና ከሰው ዘንድም ምስጋናንና ክብርን ሳይሻ ጸሎቱን ተቀብሎ ወደሚፈጽምለት አምላኩ ብቻ ትኩረቱን ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ይህን መፈጸም ትተህ ዐይኖችህን የትም የምታንከራትት ከሆነ ከእግዚአብሐር ቤት በባዶ እጅህ ምንም ሳታገኝ እንድትመለስ ዕወቅ፡፡ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ ዋጋ ማግኘትና ማጣት በእጅህ የተሰጠ የአንተ እድል ፈንታህ ነው፡፡ ስለዚህ ከንቱ ውዳሴን የሚሹ ሰዎች ከእኔ ዘንድ አንዳች አያገኙም አላለም፡፡ ነገር ግን “ዋጋቸውን ተቀብለዋል” አለ፡፡

በእርግጥ ከእግዚአብሐር ዘንድ ሳይሆን እነርሱን ከመሰሉ ሰዎች ምስጋናና አድናቆትን አግኝተው ይሆናል፡፡ ይህ ለእነርሱ ዋጋቸው ነው፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሐር ዘንድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለጸሎታቸው ብድራትን የጠበቁት ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰዎች ነውና፡፡ ነገር ግን በዚህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ማንኛውንም እንደ ፈቃዱ ልመናና ጸሎት ብናቀርብ ልመናችንን ሊሰማን ጸሎታችንን ሊቀበል ቃል ኪዳን መግባቱም እናስተውላለን፡፡ ጌታችን ጻፎችና ፈሪሳውያን ለጸሎታቸው የመረጡት ሥፍራ ለከንቱ ውዳሴ የሚያጋልጥ መሆኑን ካስረዳ በኋላ እኛ ስንጸልይ ምን ማድረግ እንዳለብን አስተምሮናል፡፡
እንዲህም አለን “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በሥውር ላለው አባትህ ጸልይ፡፡” ምንድን ነው ታዲያ? እንዲህ ሲለን በቤተ ክርስቲያን ጸሎትን አታድርጉ ሲለን ነውን? አይደለም ነገር ግን እንዲህ ማለቱ በየትኛውም ቦታ ሆነን ጸሎትን ብናደርግ በፍጹም ተመስጦ ሆነን ማቅረብ እንዳለብን ሲያሳስብ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በየትም ቦታ ማንኛውንም መልካም ሥራ ብንፈጽም ሁልጊዜም በማስተዋል ሆነን ብንፈጽማቸው የእርሱ ፈቃድ ነውና፡፡ ምንም እንኳን አንተ የእልፍኝህን በር ዘግተህ ብትጸልይ ይህን በማድረግህ ከሰው ዘንድ ምስጋናን ሽተህ ከሆነ የእልፍኝህን በር ዘግተህ በመጸለይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች ዋጋን አገኛለሁ ብለህ አትጠብቅ፡፡

ይህንን ግልጽ ለማድረግም “ለሰው ትታዩ ዘንድ” የሚለውን ቃል ጨመረበት፡፡ ስለዚህም አንተን የእልፍኝህን ደጅ ዘግተህ ትጸልይ ዘንድ ማዘዙ ልቡናህን ሰብስበህ ትጸልይ ዘንድ ነው እንጂ በርህን ዘግተህ መጸለይ ዋጋ ያሰጥሃል እያለህ አይደለም፡፡ የእግዚአብሐር ፈቃድ የቤትህን ደጅ ዘግተህ ትጸልይ ዘንድ ሳይሆን የልብህን ደጆች በመዝጋት ትጸልይ ዘንድ ነው፡፡

ማንኛውንም የትሩፋት ሥራዎችን ስትሠራ ከከንቱ ውዳሴ ነፃ መሆን መልካም ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ስትጸልይ ራስህን ከከንቱ ውዳሴ መጠበቅ ይገባሃል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በጸሎታችን ሰዓት የምንቅበዘበዝና የምንባክን ከሆነና ከልባችን የማንጸልይ ከሆነ ለዚህ ክፉ ለሆነ በሽታ ማለትም ለከንቱ ውዳሴ እንጋለጣለን፡፡ እኛ በተመስጦ ሕሊናችንን ሰብስበን ካልሆነ የምንጸልየው እንዴት ጸሎታችንን እግዚአብሔር እንደሚሰማን እርግጠኛ እንሆናለን?

እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ምዕመናን ከሥርዓት የወጣ ጩኸት በማሰማትና ያልተገባ ጠባይን በማሳየት የሌላውን ሰላም የሚያውኩ ከዚህም ባለፈ ራሳቸውን ለከንቱ ውዳሴ የሚያጋልጡ አሉ፡፡ በገበያ ቦታ እንኳ አንድ የእኔ ቢጤ ባልተገባ ጠባይ እና ለመስማት በማይመች ጩኸት ለአንዱ ባለጸጋ ልመና ቢያቀርብ ፈጥኖ ከፊቱ እንዲያባርረው በትሕትና በመሆን ቢለምነው ግን የባለጸጋውን ሆድ አባብቶ ያለውን እንዲሰጠው እንደሚያደርገው አትመለከትምን?

እኛም ስንጸልይ በማይገባና ፈር በለቀቀ ከሥርዐት በወጣ መልኩ አብዝተን በመጮኽ ሊሆን አይገባም፡፡ ነገር ግን በውጭ የምናሰማው አንዳች ጩኸት ሳይኖር ለከንቱ ውዳሴ ከሚያጋልጡ ያልተገቡ ጠባያት ርቀን አጠገባችን ያሉትን ሰዎች  ሳናውክ በፍጹም ትሕትና በውስጣዊ ማንነታችን ማለትም በነፍሳችን ወደ እግዚአብሐር ልንጮኽና ልመናችንን ልናቀርብ ይገባል፡፡

እንዲህ ስንል ሰው ከደረሰበት ታላቅ ኅዘን የተነሣ አምርሮ ሊጮኽ አይችልም ማለታችን ግን አይደለም፡፡ ቢሆንም አንድ ሰው ምንም እንኳ እጅግ ያዘነና የተከዘ ቢሆንም ይህን ታላቅ ኅዘን በነፍሱ ወደ እግዚአብሔር በመጮኽ ሊገልጸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሙሴ ወደ እግዚአብሐር አምላኩ በነፍሱ አብዝቶ ቃተተ ጮኸም፤ ጩኸቱም ከእግዚአብሐር ዘንድ ተሰማች፤ በዚህም ምክንያት እግዚአብሐር ሙሴን “ለምን ትጮኽብኛለህ” አለው፡፡ /ዘጸአ.14÷15/ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና ከከንፈሩዋ የወጣ አንዳችን ድምፅ ሳይኖር በነፍሷ ግን የልቧን ኅዘን ወደ እግዚአብሐር ታመለክት ነበር፡፡ ልመናዋንም እግዚአብሐር ተቀበላት የልቧንም መሻት ሁሉ ፈጸመላት፡፡ አቤል እንኳን በሞቱና በደሙ ከእግዚአብሐር አምላክ ዘንድ ከመለከት ድምፅ ይልቅ ጠርታ የምትሰማ ጩኸትን ወደ እግዚአብሐር ጮኾ ነበር፡፡ /ዘፍ.4÷10/

ነቢዩ ኢዩኤልም በእግዚአብሔርም ፊት የልባችንን ኅዘን ለመግለጽ ልብሳችንን ሳይሆን ልበችንን ለጸሎት ልናዋርድ እንዲገባን ሲያስረዳ “ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ” /ኢዩ.2÷13/ ብሎናል፡፡

መዝሙረኛውም “አቤቱ አንተን ከጥልቅ ጠራሁ” /መዝ.129፥1/ ብሏል፡፡ ከልባችን ጥግ ከጥልቁ የሚወጣው ጩኸታችን ድንቅ የሆነ ምላሽን ይዞልን ይመጣል፡፡ በምድራዊው ቤተ መንግሥት ትንሽ የሆነ ኮሽታ ወይንም ሹክሹክታ የግቢውን ጸጥታ ምን ያህል እንደሚያውከው አትመለከትምን? እንዴት ታዲያ ምድራዊ ባልሆነው እጅግም አስፈሪ በሆነው ሰማያዊው ቤተ መንግሥት ስትገባ የበለጠ ፀጥታን ገንዘብህ ማድረግ ይጠበቅብህ ይህን!!

አንተ አሁን በምስጋና ከትጉሃን መላእክት ጋር ተቆጥረሃል፡፡ ከሊቃነ መላእክት ጋርም ማኅበርተኛ ሆነሃል፡፡ ከሱራፌል ጋር ዝማሬን ለእግዚአብሐር ለማቅረብ ታድመሃል፡፡ በሰማያት ያሉ መላእክት ሁሉ በመልካም ሥርዓት በመሆን ለእግዚአብሔር ይገዛሉ፡፡ እርሱንም በመፍራት ሆነው ድንቅ የሆነ ዝማሬአቸውንና ቅዳሴአቸውን ለፍጥረት ሁሉ ገዢ ለሆነው አምላክ ያለማቋረጥ ያቀርባሉ፡፡

አንተም ከእነርሱ ጋር እግዚአብሐርን በማመስገን ስሙን በመቀደስ እነርሱን ትመስሏቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋርም በጥምቀት ማኅበርተኛ ሆነሃል፡፡ ስለዚህም በምትጸልይበት ጊዜ ለሰዎች ትታይ ዘንድ አትጸልይ ነገር ግን ወደ እግዚአብሐር ጸልይ፡፡ እርሱ በሁሉ ቦታ ይገኛልና እይታን ከፈለግህ በሁሉ ቦታ ያለ እርሱ ከሰው ይልቅ ያስተውልሃል፡፡ እርሱ በልብህ የታሰበውን እንኳ ያውቃል፡፡

በሥውር የሚያይህ አባትህ በግልጥ ይከፍልሃል፡፡” እንዲህ ሲል /Shall freely give thee “but shall reward thee”/  በነጻ ይሰጣሀል አላለም ነገር ግን እንደሚገባ ሆነህ በመጸለይህ ምክንያት በብድራት በግልጽ ይከፍልሃል ማለት ነው፡፡ አዎን እርሱ በአንተ ዘንድ እንደ ተበዳሪ ሆኖ ታየ፡፡ በዚህም አንተን ምን ያህል እንደወደደህና እንዳከበረህ አስተውል፡፡ እርሱ የማይታይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን እንዲሁ እኛም ስንጸልይ በሥውር ላለው አባት ብለን እንጂ ከሰው ምስጋናን ለመቀበል ሽተን ሊሆን አይገባውም፡፡

በጸሎታችሁ አሕዛብን አትምሰሉአቸው

በመቀጠል ጸሎታችንን አንዴት ማቅረብ እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደነርሱ በከንቱ አትድከሙ” /ማቴ.6÷7/ አለ፡፡
ትመለከታለህ! አስቀድሞ ስለምጽዋት ሲያስተምር ወደ ከንቱ ውዳሴ የሚካተቱንን ነገሮች በማውጣት ከእነርሱ እንድንጠበቅ አዝዞን ነበር፡፡ ከእነዚህም ሌላ ግን ጨምሮ አላስተማረንም ወይንም ከድካማችን ካገኘነው እንጂ በአመፃ ካገኘነው ገንዘብ እንዳንመጸውት አስተማረን እንጂ ምጽዋቱ መቼ መፈጸም እንዳለበት ጊዜውን ለይቶ አላስተማረንም፡፡ ምክንያቱም “ስለጽድቅ የሚራቡ ብፁዓን ናቸው” በማለት ምጽዋታችን ምን መምሰል እንዳለበት አስቀድሞ አስተምሮ ነበርና ነው፡፡

ጸሎትን በተመለከተ ግን ደግሞ ደጋግሞ ነበር ያስተማረው፡፡ አስቀድሞ ጻፎችና ፈሪሳውያንን እንደወቀሳቸው ሁሉ “በከንቱ አትድከሙ” በማለት አሕዛብን ወቀሳቸው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ ወገኖችንም አሳፈራቸው፡፡ጌታችን በትምህርቱ የምንሳብባቸውንና እኛም ልንፈጽማቸው የምንጓጓላቸውን ነገሮች ጎጂነት ነቅሶ በማውጣት ደጋግሞ አስተምሮናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ሰዎች ስንባል በውጫዊ ገጽታቸው አምረውና አሽብርቀው በሚታዩ ነገሮች በቀላሉ ስለምንሳብ በውጭ ሲታዩ ጻድቃን የሚመስሉን ግብዞች መስሎ መመላለስን ስለምንመርጥ ነው፡፡

“በከንቱ አትድገሙ” በማለት እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ የዘቀጠ አስተሳሰብ እንዳላቸው ገለጠ፡፡ እኛ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሥልጣንን፣ ክብርን፣ የጠላት ነፍስን ባለጸግነትን እንዲሁም ሌላም እኛን የማይመለከቱን ነገሮችን በጸሎት ብንጠይቅ በከንቱ እንደመድገም ይቆጠርብናል፡፡

ስለዚህም “አትምሰሏቸው ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና” አለን፡፡ እዚህ ላይ ጌታችን እንዲህ ሲል ጸሎታችሁን አታርዝሙት ማለቱ አይደለም የጌታችን ዋናው የትምህርቱ ትኩረት ጊዜን በተመለከተ አይደለም ነገር ግን አስቀድመን እንዳስቀመጥነው የማይገቡ ጸሎታትን በማድረግ በከንቱ መድከም አብዝተንና አርዝመን የምንጸልየውን ጸሎት ነው፡፡

የሚገባ ጸሎት ከሆነ ደጋግመን መጸለይ እንዲገባ “በጸሎት ጽኑ” ተብለን ታዘናል፡፡ በኤፌ.6÷18 ላይም በጸሎት መጽናት እንዳለብን ተቀምጦልናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም የጎደለውን ልንሞላ ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እንጸልያለን” /1ኛተሰሎ.3÷9-10/ በማለት በተግባር እየፈጸመ እንደነበር እናስተውላለን፡፡

ጌታችን ከጨካኙ ዳኛ ዘንድ ፍርድ ተጓደለብኝ በማለት በተደጋጋሚ ደጅ የጠናችውን መበለት ምሳሌ በማድረግ /ሉቃ.18÷1/ እንግዳ ስለመጣበት እንጀራ በእኩለ ሌሊት ከወዳጁ ይለምን ዘንድ የሄደውን ሰው ትጋት በማውሳትና ያም ወዳጁ የተጠየቀውን የሰጠበት ምክንያት ስናስተውል ስለወዳጅነቱ ሳይሆን ስለንዝነዛው ብዛት እንደሆነ አብራርቶ ገልጾልናል፡፡ በዚህም ያለማቋረጥ መጸለይ እንደሚገባ አስትምሮናል፡፡ በእርግጥ አጭር ስንኞችን ደጋግሞና አርዝሞ መጸለይ ይገባል አንልም ይህም እንደማይገባ ሲያስረዳ “በጸሎታቸው ብዛት የሚሰሙ ይመስላቸዋልና እነርሱን አትምሰሉአቸው” ብሎናልና፡፡

“ባትለምኑትም አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃል” ይላልና እርሱ የሚያስፈልገንን ካወቀ የእኛ መጸለይ ለምን አስፈለገ? ብሎ የሚጠይቅ ከእኛ መካከል አይጠፋም፡፡ አምላክን እንዲህ አድርግ ብለን አናዘውም ነገር ግን ከእርሱ ጋር የፍቃድ አንድነት ይኖረን ዘንድ ስለሚገባን ነው፡፡ /እግዚአብሔር ያለፈቃዳችን አንዳች ነገር ሊያደርግብን አይፈቅድም እርሱ ፈቃዳችንን ይጠይቃል/ ከዚህም በተጨማሪ ከእርሱም ጋር በጸሎት በምንመሠርተው የጠበቀ ግንኙነት ተጠቃሚዎች እንድንሆንና እንዲሆን የገዛ ኃጢአታችንን ዘወትር በማሰብ በትሕትና እንመላለስ ዘንድ ነው፡፡

“እናም ስትጸልዩ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር”/ማቴ.6÷9/

ይቀጥላል…

ቅዱስ እሰጢፋኖስ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ

ቀን ጥቅምት 17/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ሽመል መርጊያ

 

(የሐዋ.6፡8-ም.7፡53)

መግቢያ

በሐዋርያት ስብከት ቤተ ክርስቲያን ስትስፋፋ በትምህርታቸውና በተዐምራታቸው ተስበው ወደ ክርስትና እምነት የተመለሱ ከአይሁድና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች መሬታቸውንና ጥሪታቸውን በመሸጥ  ያላቸውን ሀብት አንድነት በማድረግ በኢየሩሳሌም የአንድነት ኑሮን ይኖሩ ነበር፡፡ በሕብረትም የሐዋርያት ትምህርትን በመስማትና  በጸሎት ይተጉ እንዲሁም ማዕድን በመባረክ በጋራ ይመገቡ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም “አንድ ልብና አንዲትነፈስ አላቸው በማለት (የሐዋ.4፡32) ስለአንድነታቸው ፍጹምነት ይነግረናል፡፡

 

ነገር ግን በቁጥር እየበዙ ሲመጡ በመካከላቸው በማዕድ ምክንያት ልዩነት ተፈጠረ፡፡ ከይሁዲነት ወደ ክርስትና የተመለሱ ክርስቲያኖች በምግብ ክፍፍል ወቅት ከግሪክ የመጡትን ይጸየፉዋቸው፣ በተለይ ባልቴቶቻቸውን ቸል ይሉባቸው ስለነበር በማኅበሩ መካከል አለመስማማት ተፈጠረ፡፡ ይህም በሐዋርያት ዘንድ ተሰማ፡፡

 

ሐዋርያትም “የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም”የሐዋ.6፡2) በማለት ማዕዱንና በውስጥ ያለውን አገልግሎት ያስተናብሩ ዘንድ ሰባት ሰዎች እንዲመረጡ የክርስቲያኑን ኅብረት ጠየቁ፡፡ ምዕመናኑም በአሳቡ ደስ ተሰኝተው መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ክርስቲያኖችን መረጡ፡፡ ሐዋርያትም እጆቻቸውን ጭነው ረድእ ይሆኑአቸው ዘንድ ዲያቆናት አድርገው ሾሙአቸው፡፡

 

ከእነዚህም ዲያቆናት መካከል በቅድስና ሕይወቱ ለክርስቲያኖች ዓብነት የሆነው ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ይገኝበታል፡፡ እስጢፋኖስ የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “አክሊል” ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ግእዝ በኋላም ወደ አማርኛ የመለሱት አባቶች በቀጥታ የግሪኩን እስጢፋኖስ የሚለውን ቃል ተጠቅመዋል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ምንም እንኳ ስሙ የግሪክ ስም ይሁን እንጂ በትውልዱ አይሁዳዊ ነው፡፡ ወላጆቹ ይህንን ስም ሊሰጡት የቻሉት በፍልስጤም ጠረፋማ ከተሞች ይኖሩ ስለነበር የግርክ ባሕልና ቋንቋ ተጽእኖ አድሮባቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡

 

ቅዱስ እስጢፋኖስ በሐዋርያት ጥበቃ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ከአምላክ ዘንድ ባገኘው የማስተማርና የፈውስ ሀብት ያገለግል ነበር፡፡ በእርሱም ታላላቅ ተኣምራት ይፈጸሙ ነበር፡፡ ስለዚህም ሕዝቡ ከፊት ይልቅ እጅግ እየበዛና በትምህርት እየጠነከረ መጣ፡፡ አይሁድም ይህን ተመልክተው በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ በቅናትና በጠላትነት ተነሡበት፡፡ ነገር ግን ከመንፈስ ቅዱስ ባገኘው ጥበብና ኃይል እነርሱን በቃልም በድርጊትም ይቃወማቸው ነበርና ሊረቱት አልተቻላቸውም፡፡ ስለዚህም እግዚአብርሔርን፣ ሙሴ ሲሳደብ ሰምተነዋል፣. ሙሴ የሠራልንን ሥርዐት ይለውጣል፣ በዚህ ቤተ መቅደስና በሕጉ ላይ የስድብን ቃል ይናገራል፣ ይህንንም ቤተ መቅደስ የናዝሬቱ ኢየሱስ አፍርሱ ብሎአል እያለ ያስተምራል አያሉ፣ ሕዝቡን፣ ሽማግሌዎችንና ጸሐፍትን በማናደድ ይዘው ከሸንጎ ፊት አቆሙት፡፡

 

ቅዱስ እስጢፋኖስን በሸንጎ ፊት ባቆሙት ጊዜም ፊቱ ልክ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ በርቶ ነበር፡፡ እርሱም ለተከሰሰበት ነጥብ መልስ ሰጠ፡፡ ከአብርሃም እስከ ክርስቶስ ለእነርሱ የተሰጣቸውን በረከት በመቃወማቸው ከተስፋ ቃል እርቀው እንደተወገዱ ገለጠላቸው፡፡ ክርስቶስንም ባለመቀበላቸው ወቀሳቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በቁጣ ተነሣስተው ከከተማ ውጭ በመውሰድ በድንጋይ ወግረው ገደሉት፡፡

 

ቅዱስ እስጢፋኖስ አይሁድ በድንጋይ እየወገሩት ሳለ ሰማያት ተከፍተው ክርስቶስን በአብ ቀኝ ቆሞ ተመለከተ፡፡ ይህንን ራእይ የክርስቶስን ትንሣኤን ለማይቀበሉት አይሁድ አሰምቶ ተናገረ፤ እነርሱ ከፊት ይልቅ በእርሱ ጨከኑ በድንጋይም ወገሩት፡፡ ነገር ግን ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታውን ክርስቶስን መስሎ ነበርና ልክ እንደ መምህሩ ክርስቶስ “አቤቱ ይህን ኀጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኾ  ነፍሱን ሰጠ፡፡ በቤተክርስቲያንም ታሪክ ስለክርስቶስ መስክሮ ሰማዕትነትን የተቀበለ የመጀመሪያው ዲያቆን ሆኖአል፡፡

 

በደማስቆ መንገድ ላይ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ ሳውል በኋላም ቅዱስ ጳውሎስ ተብሎ ስያሜ የተሰጠው ሐዋርያ  ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ በሚወግሩበት ወቅት በእርሱ ሞት ተስማምቶና ድንጋይን በእስጢፋኖስ ላይ ያነሡትን የአይሁድ ልብስ ይጠብቅ የነበረ ብላቴና ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ከሆነ በኋላ የእስጢፋኖስን ቤተሰቦች አጥምቆአቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ድንቅ ነው፡፡  ቅድስት ቤተክርስቲያናችንም ይህን ቅዱስ የመታሰቢያ ቀን በመስጠት  ጥቅምት 17 የድቁና ማዕረግን በአነብሮተ ዕድ በሐዋርያት የተቀበለበትን፥  ጥር 1 ደግሞ ዕረፍቱን ታስባለች፡፡

 

ከዚህ በመቀጠል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሐዋርያት ሥራን በተረጎመበት በ15ኛው ድርሳኑ የሐዋ.6.8-ም.7፡53  ያለውን መሠረት አድርጎ የሰጠውን ትምህርት እንመለከታለን፡፡

 

ድርሳን 15 የሐዋርያት ሥራ ትርጓሜ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት

 

ከሰባቱ ዲያቆናት መካከል አንዱ ብቻ የክብሩን አክሊል እንደደፋ ትመለከታለህን? ምንም እንኳ ለሁሉም የተሰጠው ሥልጣን አንድ ዓይነት ቢሆንም ታላቅ የሆነን ጸጋን ለራሱ እንዴት ገንዘቡ እንዳደረገ አስተውል፡፡ አንድም ተአምር ወይም ድንቅ ሳያደርግ በዛን ዘመን እንዴት በምዕመናኑ ዘንድ ታዋቂ እንደሆነ ተመልከት፡፡ ነገር ግን ሕዝቡን ወደ መምራት አልመጣም፡፡ ይህ የሚያሳየን በጥምቀት የምናገኘው ጸጋ ብቻውን ሕዝቡን ለመምራት በቂ እንዳልሆነ ነው፡፡ ምንዕመኑን ለማገልገል የሚነሣ ሰው አስቀድሞ ከጸጋው ጋር ሥልጣኑም ሊኖረው ይገባዋል፡፡ ምንም እንኳ በጥምቀት መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን ብንሆንም  የእግዚአብሔርን መንጋ ለማገልገል ሌላ አጋዥ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡ ከዚህም የምንረዳው ይህንኑ ነው፡፡

 

“የነጻ ወጪዎች ከተባለችው ምኩራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእሲያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር”(ቁ.9) “ተነሥተው” የሚለው ቃል የሚያሳየው የእነርሱ ቁጣ ነው፡፡ እኛ በዚህ ብዙ ሆነን እንደተሰባሰብነው እንዲሁ የእስጢፋኖስ ጉባኤም  ነበር፡፡ በዚህ ቦታ የአይሁድን ሌላ ሴራ እናስተውላለን፡፡ ገማልያል በሐዋርያት ላይ ስህተትን እንዳይፈላልጉ ቢያስጠነቅቃቸውም በዚህ ቦታ ዘዴያቸውን ቀይረው እንደገና  በሐዋርያት ላይ በጠላትነት መነሣታችን በዚህ ቦታ ላይ እናስተውላለን፡፡

 

እናም “የነጻ ወጪዎች ከተባለችው ምኩራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእሲያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፡፡ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡ በዚያን ጊዜ፡-በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ፡፡”(ቁ.9-12)አለን፡፡ በዚህ እነዚህ ወገኖች  “በሙሴና በእግዚብሔር ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” ብለው በቅዱስ አስጢፋኖስ ላይ መነሣታቸውን እናስተውላለን፡፡ እንዲህም ማድረጋቸው ከእርሱ ስህተትን ለማግኘት እንዲመቻቸው ሊያናገሩት ስለፈለጉ ነበር፡፡

 

እርሱ ግን ከፊት ይልቅ በግልጥ ስለክርስቶስ ሰበከላቸው፡፡ በሚሰብክበትም ወቅት የእግዚአብሔርን ሕግ መሠረት አድርጎ ነበረ ወይም ሕጉን እየጠቀሰ ነበር የሰበከው፡፡ እርሱ በግልጥ በመስበኩ ምክንያትም እርሱን ለመወንጀል ሲባል የሐሰት ምስክሮችን ማሰባሰባቸውን ከንቱ አደረገባቸው፡፡ወደ ምኩራቡ የመጡት አይሁዳውያን አመጣጣቸው ከተለያየ ቦታ ነበር፡፡ እንደ አመጣጣቸውም የተለየዩ ምኩራቦችም የነበራቸው ይመስላሉ፡፡ አንዳንዶች ግን  ምልልሱ አሰልችቶአቸው መኖሪያቸውን በዚያው በኢየሩሳሌም አድርገው የሚኖሩም ናቸው፡፡ ምኩራቡዋም የነጻ ወጪዎች ምኩራብ መባሉዋ ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ የሆነች ምኩራብ በመሆኑዋ ነበር፡፡ በዚህች ምኩራብ ብዙ የውጭ ሀገር ሰዎች ከትመውባት ይኖሩ ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህች ከተማ ሕጉ የሚነበብባት ምኩራብ ይህቺ  ነበረች፡፡

 

“እስጢፋኖስን ተከራከሩት” አለ ወንጌላዊው፤ ተወዳጆች ሆይ በዚህ ኃይለ ቃል አይሁድ  ቅዱስ እስጢፋኖስን በግልጽ አስተማሪነቱ አይገባህም እያሉ ሳይሆን ይከራከሩት የነበሩት እኔ መምህር ልባል አይገባኝም እንዲል ነበር ጫና ይፈጥሩበት የነበሩት፡፡ በእርሱ የሚፈጸሙ ተአምራቶች በእርሱ ላይ በክፋት እንዲነሣሡበት ምክንያት ሆኖአቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ጋር በቃል ወደ መሟገት ሲመጡ አሳፍሮ ይመልሳቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ሐሰተኛ ምስክሮችን ወደማሰባሰብ ተመለሱ፡፡

 

ነገር ግን “እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡” ተብሎ እንደተጻፈው  ለክርክራቸው ምላሽ ስላሳጣቸው ይህ ምክንያት ሆኖአቸው በቁጣ በመነሣሣት እርሱን ለመግደል አልሞከሩም፡፡ ነገር ግን ሐዋርያትን በመተው በእርሱ ላይ ብቻ ውንጀላዎችን በማቅረብ በዚህ መንገድ በሐዋርያትና በተከታዮቻቸው ላይ ሽብርን በመዝራት ጉባኤውን መበታተንን ነበር ዓላማቸው፡፡

 

ስለዚህም ሲከሱት “እንዲህ ብሎ ተናገረ” አላሉትም ነገር ግን  “ሕዝቡንና ሽማግሌዎችም ጻፎችም ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና፡- ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰ ስፍራ  በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም”(ቁ.12-13) በማለት ነበር የከሰሱት፡፡” “የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም” ሲሉም እንዲህ ማወክ የእለት ከእለት ተግባሩ አድርጎታል ሲሉ ነው፡፡

 

“ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዐት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ፡፡”(ቁ.14)ሲሉም ክርስቶስን ሊነቅፉት ሽተው የናዝሬቱ ማለታቸውን እናስተውላለን ፡፡ እነዚህ ወገኖች “ቤተመቅደስን የምታፈርስ በሦስትም ቀን የምትሠራው ራስህን አድን”(ማቴ.27፡40) በማለት በክርስቶስ ላይ ሲሳለቁ የነበሩ ወገኖች ናቸው፡፡እነዚህ ወገኖች ምንም እንኳ አገራቸውን ጥለው የሚኖሩ ቢሆኑም ለሙሴና ለቤተመቅደሱ ያላቸው ክብር የተለየ ነበር፡፡ የእነርሱ ክስ ሁለት ገጽታ ነበረው፡፡ እርሱ ሥርዐቱን የሚለውጠው ከሆነ በእርሱ ምትክ ሌላ ሥርዐት ይተካልና ብለው ስለሰጉ ነበር፡፡ ለውጡ እንዴት ከቀደመው የተሻለና ከዕንቊ ይልቅ የከበሩ ጸጋዎች የሞሉት እንደሆነ አስተውል፡፡

 

“በሸንጎ የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት ፡፡”(ቁ.15) በቤተክርስቲያን አነስተኛ ማዕረግ ላይ ላለው ክርስቲያን እንኳ የፊት መልክ እንደ ፀሐይ አብርቶ መታየት የተለመደ መሆኑን ነው ከዚህ ምንባብ  የምናስተውለው፡፡ አንድ የምጠይቀው ጥያቄ አለኝ ይህ ዲያቆን ከሐዋርያት የሚያንስበት ነገ አለውን? ተአምራት ከመፈጸም አልተቆጠበም፣ በድፍረት ነበር ሲያስተምር የነበረው፡፡ መጽሐፉም “በሸንጎ የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት” ይልና “እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት”ይላል (ዘጸአ.34፡30) ይህ የእርሱ ጸጋ ነው፤ ይህ የሙሴ ክብር ነው፤ እርሱ የሚናገረውን ሁሉ በመታዘዝ ይፈጽሙት ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ይህን ክብር ሰጥቶት ነበር፡፡ አዎን ዛሬም በሚወዱአቸውም በሚጠሉአቸውም ፊት አስገራሚና አስደናቂ  መንፈሳዊ ብርሃንን ከፊታቸው የሚፈልቅላቸው ቅዱሳን አሉ፡፡

 

በዚህ ቦታ የቅዱስ እስጢፋኖስን ቃል መስማት ለምን እንዳስፈለገ አስቀድሞ ተገልጦአል፡፡ ስለዚህም ከዚህ በመቀጠል “ሊቀ ካህናቱም ይህ ነገር እንዲህ ነውን አለ? (የሐዋ.7፡1) እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ውስጥ አንዳች ታላቅ ተንኮል እንዳለ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ እስጢፋኖስ መልሱን ታላቅ በሆነ ብስለት ጀመረ “ወንድሞችና አባቶች  ሆይ ስሙ የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው፡፡” አለ፡፡(ቁ.2-3) በዚህ መልሱ የእነርሱን ተንኮል ነቅሎ አጠፋው፡፡ በዚህም ስለምን ቤተመቅደሱ  ከእንግዲህ ምንም እንደማይጠቅም ገለጠላቸው፡፡ ሥርዐታቸውም ከእነርሱ ግምት ውጪ ምንም ጥቅም እንደሌለው በተዘዋዋሪ አስረዳቸው፡፡ እንዲሁም ስብከቱን ምንም የማስቆም ኃይሉ እንደሌላቸውና ደካማ በሆነው አካል ተጠቅሞ እግዚአብሔር ብርቱ የሆነውን ኃይሉን እንደሚገልጥ አሳየበት፡፡

 

ይህ የመግቢያ ንግግሩ ማግ ጠቅላላ የንግግሩን ይዘት እንዴት እንዲታታው አስተውል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ እነዚህ ወገኖች እንዴት ታላቅ ደስታና ታላላቅ በረከቶችን ያመጡላቸውን አስካሁንም እየተቃረኑዋቸው እንደመጡ፣ አሁንም ድል ሊነሡት የማይችሉትን አምላክ እየተፈታተኑ እንደሆኑ መግለጡንም ልብ እንላለን፡፡

 

“የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና ከዚህ  ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው “ አለው፡፡ በዚያን ዘመን ቤተመቅደስ፣ መሥዋዕትም አልነበረም ነገር ግን የእግዚአብሔር ራእይ ብቻ ለአብርሃም የተገለጠለት ነበር፡፡ የእርሱም ቅድመ አያቶቹ ፋርሶች እንደነበሩ እርሱም በተቀመጠባትም ምድር እንግዳ ሆኖ እንደኖረ ያስረዳቸው፡፡በንግግሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ እስጢፋኖስ “ የክብር አምላክ” ማለቱ መልካም ነበር፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለሰዎች ከሰጠው ክብር ውጪ እንዳደረጋቸው አስረዳቸው፡፡ “የክብር አምላክ” ሲል   “አብርሃምን ያከበረው አምላክ እኛም ይህን ክብር በእምነት እንድናገኝ  አበቃን” ሲላቸው ነው፡፡

 

ቅዱስ እስጢፋኖስ ከሥጋዊ ሥርዐትና ለቦታ ከሚሰጡት ክብር አውጥቶ እንዴት በውስጣቸው ጥያቄን እንደፈጠረባቸው አስተውል፡፡ “የክብር አምላክ” አለ እንዲህ ሲል እርሱ ከእኛ ዘንድ፣ ከመቅደሱም ለእርሱ የሚቀርበው ክብር፣ ክብሩን እንደማይጨምርለት፣ ይልቁኑ እርሱ ራሱ የክብራቸው ምንጭ እንደሆነ ለማሳየት በመፈለጉ ነበር እንዲህ ያላቸው፡፡ በተጨማሪም  ሴራ ሠርታችሁ እኔን ለዚህ ሸንጎ በማቅረባችሁ እግዚአብሔርን ያከበራችሁት እንዳይመስላችሁም እያላቸው ነበር፡፡

 

“ከዘመዶችህ” አለ፡፡ ስለምን የአብርሃም አባት ታራ ከካራን ወጣ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ተናገረ? (ዘፍ.11፡1) ከዚህ የምንማረው ለአብርሃም በተገለጠለት ራእይ መሠረት የአብርሃምም አባት ከካራን ወጥቶ ከንዓን መግባቱን ነው፡፡ በዚህ ቦታ ደግሞ አብርሃምን  “ከዚህ  ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድርና አለው”  በአብርሃም ታላቅ መታዘዝ  የእነርሱን አለመታዘዝ በመግለጥ  የአብርሃም ልጆች ለመባል ምንም እንደማይበቁ ገለጠላቸው፡፡  “ከዘመዶችህ” በማለት ለእግዚአብሔር የማይመቹ ክፉዎች፣ ክፋታቸውንም ሊታገሥ ካልቻላቸው ትውልድ እንደሆኑ፣  አብርሃምም በዚያ ቢቆይ  ከክፋታቸው የተነሣ መልካም ፍሬን ሊያፈራ እንደማይችል ሲገልጥለት ነው፡፡

 

“በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ፡፡ ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩበት ወደዚች አገር አወጣው፡፡ በዚህችም የእግር መረገጫ  ጫማ ስንኳ የሚያህል ርስት አልሰጠውም ”(ቁ.4) እንዲህ በማለቱ በአእምሮአቸው ርስታችን ናት ብለው ከሚመኩባት አውጥቶ እንደሰደዳቸው እናስተውላለን፡፡ ሰጠው ቢላቸው ኖሮ ፍርዱ በእነርሱ ላይ ሳይሆን በእርሱ ላይ ይወድቅ ነበር፡፡ ስለዚህም ዘመዶቹንና ሀገሩን ጥሎ ከወጣ በኋላ ወደዚህ መጣ አላቸው፡፡  ከዛስ በኋላ ከንዓንን ለአብርሃም ርስት አድርጎ አልሰጠውምን? ሰጥቶታል ነገር ግን ይህ የሌላይቱ ርስት ጥላ ነበር፡፡

 

ቅዱስ እስጢፋኖስ ትምህርቱን “ርስት አልሰጠውም” ብቻ ብሎ ለማጠናቀቅ አልፈለገም “ነገር ግን ልጅ ሳይኖረው ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ ሰጠው፡፡” (ቁ.5) አለ፡፡ ከዚህ በመቀጠል የማይቻለው ሁሉ ለእርሱ የሚቻለው እግዚአብሔር ምን እንዳደረገ ገለጠላቸው፡፡ ከሩቁ አገር የሆነ ሰው እነሆ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፡- አንተን የከንዓን አገር ገዢ አደርግሃለሁ፡፡ ነገር ግን ስለ እርሱ የተነገረውን መልሰን እንመርምረው፡፡ ተወዳጆች ሆይ እጠይቃኋለሁ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ የጸጋው ብርሃን የታየው በምን ምክንያት ነው? ጸሐፊው ስለእርሱ ማንነት አስቀድሞ ሲጽፍ “ጸጋና ኃይል የተሞላ”(የሐዋ.6፡8)በማለት ማረጋገጫውን ሰጥቶአል፡፡

 

ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መገለጥን ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል ለአንዱ ጥበብን መናገር ይሰጠዋልና፣ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፣ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፣ ለአንዱ የመፈወስ ስጦታን …” (1ቆሮ.12፡8፣9)እንዲል አንድ ሰው የመፈወስ ጸጋ ያይደለ ሌላ ጸጋ ሊሰጠው ይችላል፡፡ “በሸንጎ የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት፡፡”(ቁ.15) ብሎ መናገሩ እንደእኔ ለቅዱስ እስጢፋኖስ  በመንፈስ ቅዱስ የተሰጠውን “ጸጋና ኃይሉን” ይመስለኛል፡፡ ልክ በርናባስን “ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና፡፡” (የሐዋ.11፡24) እንደተባለው ዓይነት ማለቴ ነው፡፡ እውነተኞችና ንጹሐን ሰዎች ከምንም ነገር በላይ ሰዎች ይድኑ ዘንድ ይፈልጋሉ ፡፡ ይህ ጸጋም እጅግ ታላቅ የሆነ ጸጋ ነው፡፡

 

“በዚያን ጊዜ፡- በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ፡፡”(ቁ.11) አለ፡፡ አስቅድመው ሐዋርያትን ሲከሷቸው ትንሣኤውን ይሰብካሉ ሕዝቡን ወደ ራሳቸው ስበዋል ብለው ነበር፡፡ በዚህ ግን ሕመማቸውን ከእነርሱ ላይ ባራቀላቸው ቅዱስ ላይ ክሳቸውን ያቀረቡት፡፡ (ቁ.4፡ 2) እነዚህ ወገኖች በተደረገላቸው ፈውስ የተነሣ ምስጋናን ሊያቀርቡ  እንጂ እርሱ ላይ በጠላትነት እንዲነሡ የሚያበቃቸው አልነበረም፡፡ እንዴት ታላቅ እብደት ነው! በዚህ ቦታ በሥራ የረታቸውን  በቃላቸው ሊረቱትን ሲሟገቱት እናስተውላለን፡፡ በክርስቶስ ላይ የፈጸሙትን በቅዱስ እስጢፋኖስም ላይ የደገሙት በቃል ብቻ ጉልበታቸውን ማሳየት ነው፡፡

 

እነዚህ ወገኖች ምንም ወንጀል ሳያገኙባቸው ያለምንም መረጃ ምንም የሚከሱበት ነጥብ ሳይኖራቸው ክርስቲያኖችን ሲይዙዋቸው አያፍሩም፡፡ እነርሱ ላይ ምስክር ኖሮት እነርሱን ወደ ፍርድ ወንበር የሚያመጣቸው እንዳልነበር አስተውሉ፡፡ ከሆነ ግን እነርሱ ተከራክረው ይረቱዋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሐሰተኛ ምስክሮችን በእነርሱ ላይ ያስነሡባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሥራቸው ሕገወጥ እንዳይመስልባቸው ነበር፡፡ እነዚህ ወገኖች ክርስቶስን ሕግን ሽፋን አድርገው የሰቀሉት ወገኖች ናቸው፡፡

 

ቢሆንም የሐዋርያትን እንዲሁም የቅዱስ እስጢፋኖስን ስብከት ሰውን  እንዴት እየለወጠ እንደነበር አስተዋላችሁን? በዚህም ምክንያት ነው እነርሱ ላይ በቁጣ ከመነሣት አልፈው በድንጋይ እስከመውገር ደደረሱት፡፡ አሁንም እንዲሁ ናቸው፡፡ እንዲህም በሚፈጽሙበት ወቅት አንዱ ወዳጁን ወደ አንድ ቦታ ወስዶ አንደሚደረገው ዓይነት በየግላቸው የሚያደርጉት ዱለታ አይደለም፡፡ ነገር ግን  ከየአቅጣጫው ተሰባስበው ነበር ሴራቸውን ይጠነስሱ ይነበሩት፡፡ በሴራቸው ጠላቶቻቸውን ሳይቀር ያሳትፉ ምስክር ይሆኑላቸው ዘንድ ያግባቡ ነበር፡፡ ይህን ያህልም ደክመው የእስጢፋኖስን ጥበብ መቃወም አልተቻላቸውም፡፡(ቁ.10)

 

ከኢየሩሳሌም ብቻ ያሉት አይደሉም እርሱን ለመቃወም የተሰለፉት ነገር ግን ከሌሎችም አገራት የመጡትም ጭምር  ነበሩ፡፡ እኒህ ወገኖች “በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል”አሉ (ቁ.11) እናንተ በድርጊታችሁ እፍረትን የማታውቁ አይሁድ ሆይ የእናንተ ድርጊት በራሱ እግዚአብሔርን እንደመሳደብ አይቆጠርምን? ስለዚህ ክፉ ተግባራችሁ ዞር ብላችሁ አታስቡምን?

 

እነዚህ ወገኖች በዚህም ቦታ ሙሴን ማንሣታቸው የእግዚአብሔር ነገር ለእነርሱ እንደተራ ነገር ተደርጎ ስለሚቆጠር ነው፡፡“… ይህ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንደሆነ አናውቅምና”(የሐዋ.7፡40)ያሉት እነዚህ ወገኖች፣ የሙሴ ወዳጆች መስለው በመታየት በየትኛውም ሙግታቸው ላይ የሙሴን ስም መላልሰው ያነሡ ነበር፡፡

 

“ሕዝቡንና ሽማግሌዎችን ጻፎችንም አናደዱ”(ቁ.12) ይላል፡፡ በዚያ ዘመን የነበረው ሕዝቡ በቀላሉ የሚታለል ሕዝብ ነበር፡፡ አስቡት እስቲ እንዴት ወደዚህ ድንቅ ማዕረግ የደረሰ ሰው እግዚአብሔርን ሊሳደብ ይችላል? እግዚአብሔርን የሚሳደብ ኃጢአተኛ ቢሆን ኖሮ እንዴት በሕዝቡ ፊት እንዲህ ዓይነት ድንቃድንቅ ተአምራትን ሊያደርግ ይችላል? ነገር ግን አላዋቂና ሥርዐት አልበኛ ሕዝብ ለእነርሱ ክፉ ፈቃድ መፈጸም እንደ ደጀን ሆናቸው፡፡ “በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” (ቁ.11) እና “ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራና በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም”(ቁ.13) እንዲሁም “ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዐት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋል”(ቁ.14) ብለው ነበር ቀሊል ልብ ያለውን ሕዝብ በእርሱ ላይ የቀሰቀሱበት፡፡ በዚህ ቦታ ሙሴ ያስተላለፈልንን ሥርዐት አሉ እንጂ እግዚአብሔር የሠጠንን ሥርዐት አላሉም፡፡ በጭፍን ጥላቻም በእርሱ ላይ ተነሣሥተው የእነርሱን ክፋት በእርሱ ላይ በመለጠፍ ሥርዐት አልበኛ ብለው ከሰሱት፡፡

 

ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚሳደብ አንድም ሰብዕና የሌለው ሰው መሆኑን እንዲገለጥ “በሸንጎ የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት” ይህ ቅዱስ በሸንጎው ፊት እንዲህ ብለው ሲያሳጡት እንኳ ርጋታን ተላብሶ ነበር ክሱን ያደምጥ የነበረው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ አጥፊ ላይ እውነተኛ ምስክሮች ምስክርነታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ዓይነት ተአምር እንደተከሰተ ጽፎልን አናገኝም፡፡ ነገር ግን በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮች ሐሰተኞች ስለመሆናቸው እግዚአብሔር ያሳይ ዘንድ   ፊቱ እንደመልአክ ፊት እንዲበራ አደረገው፡፡

 

እኚህ አይሁድ ሐዋርያትን ስለ ክርስቶስ ዳግም እንዳይሰብኩ ከለከሉ  እንጂ ሐሰተኞች ምስክሮች አቁመው አልከሰሷቸውም ነበር፡፡ ይህን ቅዱስ ግን ሐሰተኛ ምስክሮችን አቁመው በሸንጎ ፊት ከሰሱት፡፡ ስለዚህም በሁሉ ፊት የእርሱ ጻድቅነት ይሟገታቸው ዘንድ ከፊቱ ብርሃን መንጭቶ ሲያበራ ታያቸው፡፡ ይህም ሽማግሌዎችንም ሳይቀር አስደንቁዋቸው ነበር፡፡

 

እርሱም  እንዲህ አለ፡-“ወንድሞችና አባቶች ሆይ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየው” አለ፡፡(ም.7፡4) በዚህ ንግግሩ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ከርሰታቸው፣ ከግርዘት፣ ከመሥዋዕት፣ ከቤተመቅደሱ በፊት እንዲኖር፣ ከእነርሱ በጎነት የተነሣ ግርዘትና ሕግ ለእነርሱ እንዳልተሰጣቸው ነገር ግን ምድሪቱ በአብርሃም መታዘዝ ምክንያት እንደተሰጠቻቸው እንዲገነዘቡ አድርጎአቸዋል፡፡ እንዲሁም መገረዛቸው ብቻውን የተስፋውን ቃል ለመቀበል እንደማያበቃቸው  አመለከታቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ለአማናዊው ሥርዐት ይህ ጥላ እንደሆነ እንዲሁም እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀው አገርና ርስት ለመግባት ሲባል  አገርንና ርስትን ጥሎ በእርሱ ትእዛዝ መውጣት ሕግን ማፍረስ እንዳልሆነ ሲያስረዳ “በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ”(ቁ.4)እንዳለ ማስተዋል እንችላለን፡፡

ይቀጥላል……

 

ኢይብቁል ብክሙ መሪር ሥርው /መራራ ሥር አይብቀልባችሁ/ /ዕብ.12፡15/

ዘገብርኤሏ


የአብርሃም ልጆች ነን የሚሉ ነገር ግን የአብርሃምን ሥራ የማይሠሩና የነቢዩ ዳዊት ልጆች ነን የሚሉ የእርሱን ፈለግ የማይከተሉ ዕብራውያንን ቅዱ ጳዉሎስ «መራራ ሥር አይብቀልባችሁ» ሲል መከራቸው፡፡ ዕብራውያን በእግዚአብሔር እናምናለን፤ የእሱ ልጆች ነን እያሉ ይመጻደቁ ስለነበሩ መልካም ሥራ በመሥራት ወደ እግዚአብሔር እንዳይቀርቡ የከለከላቸውን መራራውን ሥር እንዲያስወግዱ አሳሰባቸው፡፡ ሁሉን የሚያይና የሚያውቅ አምላከ ሰማይ ወምድር ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ውጫቸውን ያሳመሩ ነገር ግን ውስጣቸውን በኃጢአት ያሳደፉትንና በመራራ ሥር የተመሰለው ኃጢአት በውስጣቸው የበቀለባቸውን ጸሐፍትና ፈሪሳውያንን ሲገስጽ «እናንተ ግብዞች ጻፎች፤ ፈሪሳዉያን በውስጡ ቅድሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ ወዮላችሁ፡፡» ብሏቸል፡፡ /ማቴ.23፡25/

ኃጢአትን በሐልዮ ጸንሶ በነቢብ መውለድ፣ በነቢብ ወልዶም በገቢር ማሳደግ መራራ ሥር ነው፡፡ /ማቴ.24፡16/ ይህም ማለት ኃጢአትን ማሰብ አስቦም ሥራ ላይ ማዋል በአጠቃላይ በኃጢአት መውደቅ በሰው ልቡና ውስጥ የሚበቅል መራራ ሥር ነው፡፡ በዚህም «ሐሞትና እሬትም የሚያበቅል ሥር አይሁንባችሁ» /ዘዳ.18፡19/ የተባለውም የሰው ልጅ በመራራ ሥር፣ በሐሞትና በእሬት የተመሰለውን ኃጢአት ከሕይወቱ ካላራቀ መራራ ገሀነመ ዕሳት እጣ ፈንታው ይሆናል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ሐሳቦች በሙሉ መራራ ሥር የተባለው ኃጢአት መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ስለሆነም እስኪ በሕይወታችን ውስጥ ሊነቀሉ የሚገባቸው ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚለዩንን መራራ ሥሮች በዝርዝር እንመልከት፡፡

1.ዝሙት

ዝሙት አእምሮን የሚያጐድል፣ ሰላምን የሚነሣ፣ ጤንነትን የሚያሳጣ፣ ሕይወትን የሚያበላሽ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን የሚያሳጣ /የሚገፍፍ/ በሰው ልቦና ውስጥ የሚበቅልና መነቀል ያለበት መራራ ሥር ነው፡፡ ብዙ ታላላቅ አባቶች ክብራቸውን ያጡት በዝሙት እንደሆነ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ፡- እስራኤላዊያን ከሞአብ ልጆች ጋር በማመንዘራቸው ብኤልፌጐር የሚባል ጣዖት እንዲያመልኩ አደረጓቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔርን በማስቆጣታቸው 24 ሺሕ ሕዝብ በአንድ ቀን ተቀስፏል፡፡ /ዘፍ.22፡37፣ ዘኁ.27፡1/ «ኃጢአትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል» እንደተባለው፡፡ /ምሳ.22፡1ዐ/
ዝሙት፣ ሴሰኝነትና አመንዝራነት ቅድስናን ከሚያሳጡ ታላላቅ ኃጢአቶች ውስጥ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
የሰው ልጅ በእነዚህ ኃጢአቶች እንዳይወድቅ እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን አዋቂ ነውና አንድ ለአንድ በመወሰን ጸንቶ እንዲኖር ጋብቻን ባርኮ ቀድሶ ሰጥቶታል፡፡ «መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፣ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፡፡» እንዲል፡፡ /ዕብ.13፡4፣ 1ቆሮ.7፡1/ ዝሙት ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚለይ መራራ ሥር ነው የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሶምሶንም ጸጋውን እንዲገፈፍ ያደረገው ይህው በውስጡ የበቀለው መራራ ሥር ነው፡፡ /መሳ.17፡1/ ይህ ታላቅ ሰው ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ቢሆንም አንድ ናዝራዊ ማድረግ የሌለበትን የዝሙትን ተግባር ፈጽሞ በመገኘቱ ከክብሩ ተዋርዷል ኀይሉ ተነፍጎታል፡፡ /ዘኁ.6፡1/ ዛሬም ትእዛዛተ እግዚአብሔርን በመጣስና ዝሙት በመሥራት ከክብር እየተዋረድን ያለን ሰዎች ራሳችንን ልንመረምርና መራራውን ሥር በንስሐ በጣጥሰን በመጣል ወደ እግዚአብሔር ልንቀርብ ይገባል፡፡ ለሶምሶን እግዚአብሔር አምላክ ታላላቅ ውለታዎችን ቢውልለትም፤ እሱን ያስጨነቀው አምላክ ያደረገለት ውለታ ሳይሆን ከደሊላ በዝሙት የመውደቅ መንፈስ አእምሮውን አሳጥቶት ነበር፡፡ /መሳ.16፡17/ ይህች ሴት ቃሏን አጣፍጣ የዚህን የተመረጠ ሰው ሕይወት እንዳጠመደችው ዛሬም የብዙዎቹን ሕይወት በዝሙት የሚያጠምዱ እርኩስ መንፈስ ያደረባቸው መራራ ሥር የበቀለባቸው እንዳሉ ማስተዋል ይገባል፡፡
ከክብራችን እንዳንዋረድ የቅዱሳን አባቶቻችንን ፈለግ በመከተል ሥጋችንን ለነፍሳችን አስገዝተን መኖር ያስፈልጋል፡፡ ዓይኖቻችን ወደ ቅዱስ ሥጋውና ወደ ቅዱስ ደሙ የሚመለከቱ መሆን አለባቸው፡፡ «ልጄ ሆይ ወደ ጋለሞታ ሴት ልብህ አይባዝን በጐዳናዋ አትሳት፡፡ ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፡፡» /ምሳ.7፡24/ በዝሙት ተወግተው ከወደቁት ወገኖች እንዳንደመር በየትኛውም ቦታ ጥንቃቄ ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡

2.ትዕቢት

ሳጥናኤልን ያህል ታላቅ መልአክ ከክብሩ ያዋረደው ሌላው መራራ ሥር ትዕቢት ነው፡፡ ትዕቢት በመራራ ሥር የተመሰለውም ከኔ በላይ ማን አለ በማለት የማይገባውን ይገባኛል እያሰኘ ሌላውን የመናቅ፤ ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ መራራ መንፈስ ስለሚያበቅል ነው፡፡ «አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ አንተ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፣ ዙፋኔንም ከሰማይ ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ አልህ፡፡ ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጉድጓድም ጥልቅ ትወርዳለህ፡፡» /ኢሳ.14፡12-16/ ብሎ የተናገረለት ሳጥናኤል በትዕቢቱ ምክንያት ነው፡፡ «ትዕቢተኛ የሆነውና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም፡፡» /መዝ.3፡5/ ተብሎ የተነገረውን የእግዚአብሔርን ቃል ልናስብ ይገባል፡፡
ይሁን እንጂ ትናንት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ቅዱስ ሥጋውንና ቅዱስ ደሙን እየበላና እየጠጣ አድጎ በትዕቢት ምክንያት የበላበትን ወጭት ሰባሪ የሆነ ብዙ ነው፡፡ ክርስቲያን ነኝ እያለ በሀብቱ በጉልበቱ በእውቀቱ፣ በወገኑ የሚኩራራና የሚታበይም አለ፡፡ ይሁን እንጂ ሀብታሙ በደሃው ላይ፣ የተማረው ባልተማረው ላይ አሠሪ በሠራተኛው ላይ የሚታበይ ከሆነ ክርስቲያን ነው ሊባል ከቶ አይችልም፡፡ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ፤ ያለው የሌለውን መርዳት፣ የተማረውም ላልተማረው ደሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ማለት፣ ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲባል ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የማገልገል ጸጋ ቢሰጠንም በቸርነቱ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል እንጂ ልንታበይ አይገባም፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምናገለግል ሁሉ የምናቀርበው የአገልግሎት መስዋዕት በእግዚአብሔር ቸርነት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ልክ «… የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ፡፡» እንደተባለ፡፡ /ሉቃ.17፡1ዐ/
ስለዚህ ፈሪሃ እግዚአብሔር ሊኖረን እንጂ ልንታበይ አይገባም፡፡ «እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው፡፡» /ምሳ.22፡4/ እንዳለ ጠቢቡ በምሳሌው፡፡

3. ማስመሰል

መመሳሰልና መስሎ መታየት፣ ለመመሳሰል መጣር የብዙዎች ችግር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳች ፍሬ ባገኝባት ብሎ ወደ አንዲት ዛፍ ሲጠጋ ፍሬ ያፈራች መስላ እንጂ አፍርታ ባለመገኘቷ ምክንያት ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ ወዲያውም ደረቀች፡፡ /ማቴ.21፡18/  ከዚህ ኀይለ ቃልም የምንረዳው በመስሎ መኖርና ሆኖ አለመገኘት የሚያመጣውን ርግማን ነው፡፡ ማስመሰል መራራ ሥር ነውና ሊነቀል ይገባዋል፡፡ ዛሬም ብዙ ሰው በአፉ የሃይማኖት ሰው ይመስላል፣ እውነታው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያን የሚሔዱ ጾም የሚጾሙ፣ ነገር ግን ከኃጢያት ያልተለዩ፣ በንስሐ መመለስን ችላ የሚሉ፣ ታቦት ሲነግሥ እልል ስለተባለ ብቻ እልል የሚሉ ከዚያ ሲወጡ ግን ኃጢአት ለመሥራት የሚጣደፉና በልባቸው የሸፈቱ ሰዎች የማስመሰሉን መራራ ሥር ከውስጣቸው በንስሐ ነቅለው መጣል አለባቸው፡፡ ሆኖ መገኘት እንጂ መስሎ መታየት አያድንምና፡፡ «ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከኔ በጣም የራቀ ነው፡፡ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል፡፡» /ኢሳ.29፡13፣ ማቴ.5፡8/ እንደተባለው ዛሬም የብዙ ሰው አምልኮ የዚህ ትንቢት መፈጸሚያ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ጥዋት ቤተ ክርስቲያን፤ ከሰዓት ቤተ ጣኦት በመሔድ ጊዜን በከንቱ ከማሳለፍ መቆጠብ ያሻል፡፡ ክርስቲያን ነኝ እያለ ጨሌውን፣ የዐውደ ነገሥቱን ጥንቆላ ማመን፣ መናፍስትን መጥራትና የመሳሰሉትን እየፈጸሙ መገኘት በልብ መሸፈት ነውና ልንመለስ ይገባል፡፡ «በሰማያት ያለው የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ የሚሉኝ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡ አይደሉም፡፡» /ማቴ.7፡21/ ተብሏልና፡፡
መስለው ለመኖር የሞከሩ ብዙ ሰዎች ሲጎዱ እንጂ ሲጠቀሙ አላየንም፡፡ ግያዝ ከኤልሳዕ ጋር መስሎ ሲኖር ልቡ ግን ወደ ገንዘብ ሸፍቶ ስለነበር በለምጽ ተመታ፡፡ /2ኛ ነገ.5፡2ዐ/ የይሁዳንም ታሪክ ስንመለከት ከሐዋርያት ጋር ተመሳስሎ እየኖረ ልቡናው በፍቅረ ንዋይ ተነድፎ እንደነበር ነው፡፡ እናም እነዚህንና የመሳሰሉትን የፍቅረ ንዋይ፣ የስስት፣ የእምነት ጎደሎነት ወዘተ መራራ ሥሮች በቶሎ በንስሐ መነቃቀል ያስፈልጋል፡፡
ካህኑም፣ ዲያቆኑም፣ ሰባኪውም፣ ዘማሪውም በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነኝ የሚል ሁሉም አገልግሎቱ ዋጋ የሚያገኘው ከእግዚአብሔር መሆኑን ከልብ በማጤንና ራሱን በመመርመር የጐደለውን ሊያስተካክል ይገባል፡፡ እያንዳንዷ ሥራችን የምትበጠርበት ጊዜ ይመጣልና፡፡ «መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፡፡ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደሥራቸው መጠን ተከፈሉ፡፡ … እያንዳንዱ እንደሥራው መጠን ተከፈለ፡፡» እንዲል፡፡ /ራእ.2ዐ፡12/
ስለዚህ መልካም ዋጋ ለማግኘት መልካም ሥራ ለመሥራት መጣር ይገባል፡፡ «አምላካችሁ እግዚአብሔርን ተከተሉ እርሱንም ፍሩ ትእዛዙንም ጠብቁ ቃሉንም ስሙ እርሱንም አምልኩ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ» /ዘዳ.13፡4/ ስለተባልን ለመልካም ሥራ እሺ እንድንል ያስፈልጋል፡፡ «እሺ ብትሉ፣ ለእኔም ብትታዘዙ፣ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምጹ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህንን ተናግሯል» ተብሏልና፡፡ /ኢሳ.1፡19/

4. ዓላማ ቢስነት

ዓላማ የሌለው ሰው ከየት ተነሥቶ ወዴት መሔድ እንዳለበት የማያውቅ፣ ካሰበበት የማይደርስ ነው፡፡ ማንም ወደነዳው የሚነዳ፣ በጭፍን የሚጓዝ ሰው ዓላማ ቢስ ሊባል ይችላል፡፡ ዓላማ የሌለው ሰው በጀመረውና በተሠማራበት ተግባር ላይ ጸንቶ አይቆይም፡፡ በተለይ ክርስቲያን ዓላማ ከሌለው በትንሽ ነገር የሚፈተን፣ ሥጋዊ ፍላጐቱ ካልተሟላለት የማያገለግል፣ የሚያማርር፣ በሆነ ባልሆነው የሚያኰርፍ፣ መንፈሳዊነትን ያዝ፣ ለቀቅ የሚያደርግ የጸሎቱ፣ የጾሙ ዋጋ ዛሬውኑ እንዲከፈለው የሚፈልግ ይሆናል፡፡ የሚያገለግልበትንም ዓላማ ያልተገነዘበ ሰው በየደቂቃው እንዲመሰገን ይፈልጋል፡፡ ሰዎች ዓላማቸውን እንዲስቱ በልባቸው ውስጥ የማዘናጋትን ተግባር የሚፈጽም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ቅዱሳን አባቶች በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ቢያልፉም ዓላማን የመሳት መራራ ሥር በውስጣቸው አልበቀለም፡፡ በሁሉም ጸንተው በመቆማቸው ለክብር አክሊል በቅተዋል፡፡
ሙሴ እስራኤልን በምድረ በዳ ይመራ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ከዓላማው አልተዘናጋም፡፡ ይልቁንም ያህዌህ ንሲ /እግዚአብሔር ዓላማዬ ነው አለ እንጂ፡፡ /ዘዳ. 12፡15/
ዮሴፍ ጽኑ ዓላማ ስለነበረው የተዘጋጀለትን የዝሙት ግብዣ እምቢ አለ፡፡ /ዘፍ. 39/
ሶስና ልትሸከመው የማትችል የሚመስል ፈተና ቢያጋጥማት ንጽሕናዋን ክብሯን ጠብቃ፣ ለአምላኳ ታምና መኖርን ዓላማዋ ስላደረገች የመጣባትን ፈተና በጽናት፣ በታማኝነት፣ በንጽሕና በቅድስና ልታልፍ ችላለች፡፡ /መጽሐፈ ሶስና/  ኢዮብ ዓላማው እግዚአብሔር ስለነበር ይፈራረቅበት የነበረውን መከራ፣ ሥቃይና ችግር ሊያልፍ ችሏል፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ ተፈትኖ፣ ነጥሮ ታላቅነቱን አስመስክሯል፡፡ /ኢዮ.2፡10/ በአንጻሩ ደግሞ ዓላማቸውን የሚያስት መራራ ሥር በውስጣቸው በመብቀሉ ምክንያት የተጐዱ ከክብራቸው ያነሡ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ለምሳሌ ሳኦልን ብንመለከት እግዚአብሔር አምላክ ከሕዝበ እስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ቢሾመውም የቅንዓት መንፈስ በውስጡ ስለበቀለ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር ሲሠራ እናያለን፡፡ /1ኛሳሙ. 11፡9፣15፡35/
ዛሬም ትናንት የቤተ ክርስቲያን ልጆች የነበርን፣ እግዚአብሔር ከፍ ስላደረገን፣ ስለሾመን ዓላማችንን የዘነጋን አንታጣምና ራሳችንን ልንመረምር ይገባል፡፡ ከዓላማችን እንድንስት የሚያዘናጉ ነገሮች በርካቶች ናቸው፡፡ ሰው ለገንዘብ፣ ለሥልጣን፣ ለሓላፊ ጠፊ ሀብት ብሎ ዓላማውን ይስታል፡፡ ይሁዳ ምንም እንኳን ከሐዋርያት አንዱ ሆኖ ቢቆጠርም ዓላማው መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ሳይሆን ገንዘብን ማሳደድ ስለነበረ አምላኩን እስከ መሸጥ ደረሰ፡፡ «እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ፡፡» ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመበት፡፡ /መዝ.4ዐ፡9/ ይሄው ዛሬ የነፍሰ ገዳዮችና የክፉዎች ተምሳሌት ሆኖ ይነገራል፡፡ ስለዚህ «ከመልካም ሽቱ መልካም ስም ይሻላል፡፡» እንደተባለ ስማችን በክፉ እንዳይጠራ በዓላማችን እንጽና፡፡ /መክ. 7፡1/ ዓላማችን መንግሥቱን ለመውረስ፣ ስሙን ለመቀደስ ይሁን፡፡ እንደ ዴማስ ወደ ዓለም የሚመለስ መራራ ሐሳብ በውስጣችን እንዳይበቅል ጥንቃቄ እናድርግ፡፡ /2ኛጢሞ. 4፡9/

5. የጥርጥር መንፈስ

«የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባህርን ማዕበል ይመስላል፡፡ ሁለት ሐሳብ ላለው፣ በመንገድም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች የሚያገኝ አይምስለው፡፡» /ያዕ. 1፡6/ በማለት እንደተነገረው ተጠራጣሪ ሰው ከጌታ አንዳች ነገር አያገኝም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከጽናታችን እንድንናወጥ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የተጠራበትን ዓላማ ጠንቅቆ የማያውቅ ክርስቲያን በጥርጥር ነፋስ ተነቅሎ ይገነደሳል፡፡ ስለዚህ ጊዜው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻው በመሆኑ በማስተዋል መራመድ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ይመጣ ዘንድ ስላለው ክህደትና ሐሳዊ መሲህ «… የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየተሳቡ የሚያጠፉ ኑፋቄን አሾልከው ያገባሉ፤ … በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል፡፡» /2ጴጥ.2፡1/ በማለት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የክርስቶስን አምላክነት የሚጠራጠርና የሚያጠራጥር፣ በቅዱሳን ላይ አፉን የሚከፍት ሐሳዊ መሲህ ቢነሣ የሚያስደንቅ መሆን የለበትም፡፡ ለምን ቢሉ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነውና፡፡ ዮሐንስም ስለዚህ ነገር «አውሬው ታላቅ ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው … እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም፣ በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ፡፡» ብሎ ጽፏል፡፡ /ራእ.13/ ስለዚህ በልባችን የሚበቅለውን የጥርጥር መንፈስ ከውስጣችን ነቅለን ልንጥል ያስፈልጋል፡፡ «ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፡፡ /2ጴጥ.3፡17/ እንደተባልነው ጥንቃቄ ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ መራራ ሥር ኃጢአትና ክርስቲያናዊ ምግባር በአንድ ሰውነት ላይ ሊበቅሉ የማይገባቸው እንክርዳድና ፍሬ ናቸው፡፡ በመሆኑም በንስሐ መከር መለየት ይኖርብናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የመራራ ሥራ ፍሬዎችን የሥጋ ሥራ በማለት ገልጿቸዋል፡፡ «አስቀድሜ እንዳልኩ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ብሏል፡፡ ገላ. 5፡21» ስለዚህ ክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲያብብ የክፋት ሥራ የሆኑ ኃጢአቶችን በንስሐ እና በተጋድሎ በተለይም ዝሙት፣ ትዕቢት፣ ማስመሰል፣ ዓላማ ቢስነትና የጥርጥር መንፈስ የመሰሉ መራራ ስሮች በጥንቃቄ መንቀልና ማራቅ ያስፈልገናል፡፡ መራራ ሥሮችን ነቅለን የመንፈስ ፍሬያትን በሰውነታችን እናበቅል ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

commitiee

30ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጀመረ

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}smg30{/gallery}

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 30ኛው መደበኛ መንፈሳዊ ጉባኤ ጥቅምት 7 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከጠዋቱ 3 ሰዓት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጸሎተ ቡራኬ ተጀምሯል፡፡

 

የ48ቱ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በከፊል የተገኙ ሲሆን ሁሉም የሀገር ውስጥ ሥራ አስኪያጆች ፣የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች ፣በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ በኢትዮጵያ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ፣ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሓላፊዎች የጉባኤው ተሳታፊዎች ናቸው።

የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት “ስምዐነ አምላክነ ወመድኃኒነ ተስፋሆሙ ለኩሎሙ አጽናፈ ምድር” የሚለው የዳዊት መዝሙር ተሰብኮ “በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድርም የምትፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆናል፡፡…. ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና” የሚለው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 18 ቁጥር 18 በቅዱስነታቸው ተነቧል፡፡

 

ቅዱስነታቸው በጸሎተ ወንጌል ጉባኤውን ባርከው ከከፈቱ በኋላ በሰጡት ቃለ ምእዳን ሰው መግባባት የሚችለው እግዚአብሔር በሰጠው አእምሮ ሲጠቀምበትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ሲኖር ነው። ፈሪሃ እግዚአብሔር ካለ ሰላም፣ ፍቅር፣ መግባባት፣ መዋደድና መከባበር ይኖራል ብለው በሰላማዊ መንገድ ሓላፊነትን መወጣት እንዲገባ አሳስበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘው በ2003 ዓ.ም በሞት የተለዩንን ብፁዕ አቡነ በርናባስን፣ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅንና ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን በጸሎት እናስባቸው ብለው ጸሎት አድርሰዋል፡፡

 

ሊቀትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜ፣ መጋቤ ሰናያት አሰፋ ስዩም፣ ሊቀ ስዩማን ራደ አስረስ፣ ንቡረ እድ ተስፋዬ ተወልደና መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት የአቋም መግለጫ ረቂቅ እንዲያዘጋጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ለጉባኤው አቅርበው ጉባኤው የተመረጡትን አርቃቂዎች በሙሉ ድምጽ አሳልፈዋል፡፡commitiee

 

ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ ለ45 ደቂቃ ያህል የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አጠቃላይ ሪፓርት በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክርህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የኢሉባቡርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ቀርቧል፡፡ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሪፖርት ቀጥሎ የትግራይ ማዕከላዊ ዞን /አክሱም/ ሀገረ ስብከት ሪፖርት መቅረብ የነበረበት ቢሆንም የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ለሌላ ተልእኮ ወደ ሱዳን ሀገረ ስብከት መሔድ እንዲችሉ ፈቃድ ጠይቀው ቅድሚያ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡

 

በጠዋቱ መርሃ ግብር የትግራይ ማዕከላዊ ዞን፣ የሲዳማ፣ የሰሜን ጎንደር፣ የምሥራቅ ሀረርጌ፣ ሀገረ ስብከት ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ከሰዓት በኋላ በተያዘው መርሃ ግብር ከቀኑ 8 ሰዓት እስከ 11፡30 ድረስ የጅማ ዞን ሀገረ ስብከት፣ በትግራይ ክልል ሀገረ ስብከት የመቀሌ፣ የኢሊባቡር፣ የድሬዳዋ፣ የጋሞጎፋ፣ የሰሜን ወሎ፣ የባሌ፣ የደቡብ ጎንደርና የምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሪፖርት ቀርቧል፡፡

 

ረቡዕ ጥቅምት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 እስከ 6፡30 በነበረው መርሐ ግብር የአርሲ፣ የትግራይ ምሥራቅ /አዲግራት/፣ የምዕራብ ጎጀም፣ የከፋ ቦንጋ፣ የሰሜን ሸዋ፣ የአሶሳና የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሪፖርት ቀርቦ እንዳበቃ የቆሜ አቋቋም ሊቃውንት ወረብ አቅርበዋል፡፡

 

በሊቃውንቱ የቀረበው ወረብ እንደተጠናቀቀ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ፣ የምሥራቅ ጎጃም፣ የምዕራብ ሐረርጌና የትግራይ ደቡባዊ ዞን /ማይጨው/ አህጉረ ስብከት ሪፖርት በንባብ ተሰምቷል፡፡

 

ከሰዓት በኋላ በተያዘው መርሃ ግብር የደቡብ ኦሞ፣ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ የሰላሌ ሀገረ ስብከት የሐዲያና ስልጤ፣ የዋግ ሕምራ፣ የምዕራብ ሸዋ፣ የአፋር፣ የአዊ ዞን፣ የሶማሊያ፣ የምዕራብ ወለጋ፣ የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሽሬ ሀገረ ስብከትና የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሽሬ ሀገረ ስብከትና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ውይይት ተካሒዷል፡፡

 

30 ዓመት ያስቆጠረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ካሳለፈው ረዥም ጉዞ ጋር ሲነጻጸር የሚጠበቅበትን ውጤት እያስመዘገበ እንዳልሆነ በመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የቀረበው ሪፓርት ያስረዳል፡፡

 

አጠቃላይ ጉባኤው እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ውይይቶችና የውሳኔ ሐሳቦች እንደሚቀርቡበት ይጠበቃል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የደረሰችበት ወቅታዊ ሁኔታ

ዲ/ን ታደሰ ወርቁ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰማያዊ ሥርዓት በምድር ያለች ሰማያዊት ተቋም ነች፡፡ በምድር ያለነውን ልጆቿን በሰማያዊው ሥርዓት በምድር አዘጋጅታ በሰማይ የምታኖር ናት፡፡ “አሐቲ” ተብላ የምትጠራ የክርስቲያኖች መገናኛ በመሆኗ ወደሷ ለሚመጣው ሁሉ በረኛ፣ ጥበቃ፣ ከልካይ፣ አሰናካይ የሌለባት ነፃ እልፍኛችን ናት፡፡ እንዲሁም ከበሉ መራብ፤ ከጠጡ መጠማት የሌለበት ሰማያዊውን መና፣ በሰማያዊ ሥርዓት የምታስገኝልን አማናዊ የእናት ጓዳ በመሆኗ መታመኛችንና መመኪያችን ናት፡፡
ከሁሉ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን በማይነዋወጥ ወለድ ዋሕድ በሚለው መሠረተ እምነት፤ ነቢያት፣ ሐዋርያት ሊቃውንት ስለወልድ ዋሕድ በአስተማሩት ትምህርት መሠረት ላይ የታነፀች እውነተኛ የሕግና የትክክለኛ ሥርዓት መገኛ ናት፡፡ በየጊዜው የነበረው ፈተና የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ጥቃት አስተዳደራዊ ጉዞዋን ቅርቃር ውስጥ የከተተው ቢሆንም የዘመኑን ተልእኮዋን ለማሳካት በቂ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ፣ ሐዋርያዊት፣ ኩላዊት ሁና ሳለች በጥቂቶች ከላሽነት የተነሣ የውጭና የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ በሚል ተከፋፍላለች፡፡ ተቋማዊ አስተዳደራዊ ፋይናንሳዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ የዚህ ድምር ውጤትም የምእመናንን ሕሊናም እየከፈለ፣ እያደማም ይገኛል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በአስተምህሮዋ በአስተዳደሯ፣ በፋይናንስ አያያዟና አጠቃቀሟ የከፋና ውስብስብ ጊዜ ጠየቅ ችግሮችና ፈተናዎች ተጋርጠውባታል፡፡ አንዳንዶቹ ፈተናዎችና ችግሮች ሥር የሰደዱ አዝማናትን ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ዘመንና መስክ ወለድ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ከኅልፈተ ዓለም በፊት ይቆማሉ ተብሎ የሚታሰቡ አይደሉም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግን ለዘመንና መስክ ወለድ ችግሮቻችን መፍትሔ ማፈላለግ የዘመናችን የቤተ ክርስቲያኒቱ ላአላይና ታህታይ መዋቅር መሪዎች ተናጥላዊና የወልዮሽ ሓላፊነት ነው፡፡
እናም በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በአባቶቻችን የመንፈስ ልዕልናና ጽናት ተጠብቆ የቆየው የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነት፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ትውፊት ለመጪው ትውልድ ያለ እንከን መተላለፍ የሚችለው፣ በጉልህ የሚታዩትን አስተምህሯዊ ቅሰጣ፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ችግሮችን ማረም፣ ማስተካከል፣ ሥርዓታዊና ሕጋዊ መሠረት ማበጀት ስንችል ብቻ ነው፡፡
ይህ ሆኖ እንድናይ ደግሞ በታሪክ መስታወትነት ወደ ኋላ ሔደን አሁን ያለንበትን ከአለፈው ጋራ በማዛመድ ከየት ተነሥተን ያለንበት ደረስን? ወዴትና በምን ያህል ፍጥነት እየመራን ነው? ምን ዓይነት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በምን ያህል ፍጥነት ብናስቀምጥ የተጋረጠብንን አደጋ እንቀንሳለን? ለሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ተግባራዊና ተጨባጭ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህን ሦስት መሠረታዊ እና የነባራዊው ሁኔታ ነጸብራቅ የሆኑትን ጥያቄዎች ከግንዛቤ በማስገባት ጽሑፉን በሦስት ዓበይት ክፍሎች ለማቅረብ መርጠናል፡፡ በመጀመሪያው ክፍል ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዘመናት በሚለው ርእስ ሥር ከየት ተነሥተን ያለንበት ደረስን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክራለን፡፡ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ በሚለው ርእስ ሥር ወዴትና በምን ያህል ፍጥነት እያመራን ነው? የሚለውን ጥያቄ ከምንገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ለማየት እንጥራለን፡፡ በሦስተኛውና የመጨረሻው ክፍል የመፍትሔ አቅጣጫ ጥቁምታ በሚለው ርእስ ሥር በሁለቱ ቀደምት ክፍሎች ትንታኔ ላይ በመመሥረት ምን ዓይነት የመፍትሔ አቅጣጫዎች፣ በምን ያህል ፍጥነት ብናስቀምጥ የተጋረጡብንን አደጋዎች እንቀንሳለን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክራለን፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን
ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበረችበት ታሪካዊ ሁኔታ /Historical condition/ ጥርት ባለ እና በተስተካከለ ገጽታ ለመረዳት ተልእኮዋን እንደ አንድ ማንጸሪያ /parameter/ መጠቀሙ አስፈላጊ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምድራዊውን ሰው በሰማያዊ ሥርዓት ወደ ሰማያዊ ኑሮ እንድታሸጋግር ከመሥራቿና ራሷ ከሆነው ክርስቶስ ሦስት መሠረታዊ ተልእኮ ተሰጥቷታል፡፡ በወልድ ዋሕድ መሠረተ እምነት ማጥመቅ፣ ማጽናትና መከታተል ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊ ሁኔታ የምንፈትሸውም አንዱ ከእነዚሁ ተልእኮዎቿ ተነሥተን ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያዊ ጃንደረባና በሶሪያዊው ፍሬምናጦስ ዘመን

ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ “The Religious Life In Ethiopia” በሚል ርእስ እ.ኤ.አ. በ1970 በአቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው ላይ እንዳመለከቱት፣ የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ የገባበት መንገድ ከሌላው ዓለም በእጅጉ ይለያል፡፡ በሌላው ዓለም ክርስትና የተጀመረው ከተርታው ሕዝብ ነው፡፡ በመንግሥት የታወቀና የተረዳ ሃይማኖት አልነበረም፡፡ በእኛ ሀገር ግን የመጀመሪያዎቹ አማኞች ከተርታው ሕዝብ አይደሉም፡፡ ነገሥታቱና መኳንንቱ ከነቤተሰቦቻቸው ነበሩ፡፡ ሃይማኖቱም ብሔራዊ ሃይማኖት ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በሌሎች የዓለም ሀገሮች የክርስትና ታሪክ ውስጥ አልሆነም፡፡ በኢትዮጵያ ግን ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክርስቲያን የሆነውም በዚህ ሁኔታ ነው፡፡
የክርስትና ሃይማኖት አገባብ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱም አደረጃጀት ከሌላው ዓለም እንዴት እንደሚለይ ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ በዚሁ የጥናት ወረቀታቸው ሲገልጹ፤ “…. የቤተ ክርስቲያኒቱ አደረጃጀትም ከሌላው የክርስትና ዓለም የተለየ ነበር፡፡ ክርስትናን ያስተዋወቀው የመጀመሪያ ሰው ሶሪያዊው ፍሬምናጦስ ነው፡፡ ይሁንና ከእርሱ በኋላ አስተዳደሩ ይመራ የነበረው በኢትዮጵያውያን አልነበረም፡፡ በግብጻውያን ጳጳሳት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያም በአንድ ጳጳስ ብቻ እንድትመራ በሕግ ደንግገዋል፡፡ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዘመን በአንድ ግብጻዊ ጳጳስ ሥር እንዲወሰኑና ተጨማሪ አስተዳደራዊ ነፃነት እንዳይኖራቸው ተደርጓል” በማለት ነበር፡፡
በእርግጥ ክርስትናው የገባበት መንገድና የቤተ ክርስቲያኒቱ የአደረጃጀት መነሻ ከላይ የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ሥርግው እንደአስቀመጡት ቢሆንም ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባውና ወይም ኢትዮጵያና የክርስትና ሃይማኖት የተዋወቁት መጽሐፍ ቅዲስ እንደሚያስረዳው / ሐዋ.8፥26-40/ ሐዋርያው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ባጠመቀው ጊዜ ነው፡፡ ይህም የሆነው ከጌታ ልደት በኋላ በ34 ዓ.ም ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በተባለው መጽሐፋቸው ከላይ በጠቀስነው አግባብ የኢትዮጵያና የክርስትና ሃይማኖት ትውውቅ ከአሰፈሩ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ የፍሬምናጦስ /አባ ሰላማን/ ሚና ሲገልጹ፤ “ኢትዮጵያዊው /ጃንደረባው/ ተጠምቆ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ አዲሱን ሃይማኖት ለሀገሩ ሕዝብ አስተምሯል፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ፍሬምናጦስ /አባ ሰላማ/ ሥርዓተ ክርስትናን በትምህርት ያጠናከረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በመሠረተው ነው፡፡ ፍሬምናጦስ ጵጵስናውን ተቀብሎ ከተመለሰ በኋላ በኢትዮጵያ የክርስትናን ሥርዓት አስፋፈቶ ሰበከ፤ የክህነትና የቁርባንን ሕግ አጠናከረ፡፡ በኢትዮጵያ ግዛት በሙሉ የወንጌልን ትምህርት ለማዳረስ የሚረዱ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስት፣ ከዕብራይስጥና ከጽርእ ወደ ግእዝ ቋንቋ መለሰ፡፡ በዚህ አኳኋን በ330 ዓ.ም ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነ” ይላሉ፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የሐዋርያነት ሥራ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አጭር መግቢያ” በሚለው የጥናት ወረቀቱ እንዳመለከተው ኢትዮጵያዊው ጀንደረባ ከአክሱም ቀጥሎ ኑብያን፣ ከኑብያም በኋላ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ በየመንና በፐርሽያ ወንጌልን ሰብኳል፡፡
ከእርሱም በኋላ ደግሞ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንድ ሊቅ በአምስተኛ መቶ ክፍለ ዘመን በሊቢያ የኢትዮጵያን ሰዎች ማየቱን ገልጧል፡፡ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ዘመንም አባታችን ወደ ኑብያ፣ አኑኖ እና መርዌ አምስት ቆሞሳትን ልከው እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አብርሃና አጽብሐ ክርስትናን ተቀብለው ከተጠመቁ በኋላ በሸዋ፣ በጎጃም ብሎም እስከ ጋሞ ጎፋ ብርብር ማርያም ድረስ ወንጌል ሰባክያን እየተላኩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ “The Establish event of the Ethiopian church” በሚል ርእስ ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው ላይ፤ ከላይ በአቡነ ጎርጎርዮስ የተገለጠውን ዘመነ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ ያለውን ታሪካዊ ቦታ ሲያብራሩ፤ “የክርስትና ሃይማኖት እንደመንግሥታዊ ሃይማኖት መተዋወቁ በኢትዮጵያ ታሪክ ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ያሳያል” ካሉ በኋላ “ክርስትና በሀገሪቱ የሚያካትተው ንጹሕ ሃይማኖታዊ ክስተቶችን ብቻ አይደለም፡፡ በሁሉም ሀገራዊ ኑሮ ላይ ዘርፈ ብዙ ሚና አለው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳትሆን ለበርካታ ዘመናት የአገሪቱ ሕዝብ የባህል፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ ኑሮ ግምጃ ቤት መሆኗን ያሳያል” ይላሉ፡፡
ዘመነ ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲየን መንበረ ጵጵስና ታሪክ ውስጥ ያለውን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሪስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው “ከርሱ /ከቅዱስ ፍሬምናጦስ/ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ከሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ጋር እኩል ሆነች፡፡” ብለው ሲገልጹ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትናንትናና ዛሬ” በሚል ርእስ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባኤ የተዘጋጀው መጽሐፍ ደግሞ “…. ቅዱስ ፍሬምናጦስ በዚህ ሁሉ ሥራው ከሣቴ ብርሃን ሰላማ የሚል ቅጽል ተሰጠው፡፡ ከእርሱ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ደረጃ ታወቀች” በማለት ነው፡፡

የኢትዮጵያን ዕሥራ ምዕት ምክንያት በማድረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም” በሚል ርእስ የተዘጋጀው መድበል ይህንኑ ሐሳብ ሲያጠናክር፤ “ቅዱስ አባ ሰላማ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ ከሣቴ ብርሃን ተባለ” ይልና “በዚሁ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል” ይላል፡፡

የኢትዮጵያን ታሪክ ስንመለከት የአንድም ሐዋርያ ደም ሳታፈስ፣ የአንድም ሰማዕት አጥንት ሳትከሰክስ ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖትን የተቀበለች ሀገር ነች፡፡ ይኼ እንዲሆን ደግሞ ከሕዝባችን ጨዋነት ባሻገር የመንግሥት እና ቤተ ክህነት ግንኙነትም ወሳኝ ታሪካዊ አጋጣሚም ነበር፡፡ ቀደም ብሎ የንግሥተ አዜብ ወደ ሰሎሞን መሔድና የቀዳማዊ ምኒልክ ከሰሎሞን መወለድ ለሥርዓተ ጽዮን አገባብና ለሕገ ኦሪት አመጣጥ ምክንያት ሆነ፡፡ እንዲሁም ደግሞ በሕንደኬ ንግሥት ጊዜ የበጅሮንዷ ወደ ኢሩሳሌም መሔድና ከሐዋርያው ፊልጶስ ጋራ ተገናኝቶ የወንጌልን ዜና ጽድቅ ለማምጣት መሪ ሆነ፡፡ ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት አማካኝነት ተመርጦ ወደ እስክንድርያ ሔዶ ጵጵስና ተሹሞ መጠቶ እስካሁን ሲያያዝ የመጣውን የወንጌል መክሊት በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ምእመናን አተረፈ፡፡ ይኼ ደግሞ ሌላኛው ቤተ ክርስቲያናችን የተገነባችበት የታሪክ ገጽታችን ነው፡፡
የዚህ ዓይነቱ ታሪካዊ ትስስር በወቅቱ ከነበረው ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበረችበትን ታሪክዊ ቦታ ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ “The Establishment of the Ethiopian church”  በሚለው ጥናታቸው ሲተነትኑ “የክርስትና ሃይማኖት እንደ መንግሥት ሃይማኖት በኢትዮጵያ መግባቱ በተደራጀ በሌላ ሀገር የስብከት ውጤት ሳይሆን የነገሠታቱ /አማኝነት/ ነው” ካሉ በኋላ “ክርስትና በኢትዮጵያ የተዛመተው እንደ ግሪክ ሮማውያን ዓለም ዓይነት የክርስትና ተዛምቶ መንገድ አይደለም፡፡ ክርስትና በእነዚህ ሀገሮች ለሦስት ምእት ዓመታት በታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ቢታቀብም ወዲያው የገዢው መደብ ተቃውሞታል፡፡ በእርግጥ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎች በጣም ጥቂት የሚሆኑ የነገሥታት ቤተሰቦች የክርስትና ሃይማኖትን መቀበል ቢጀምሩም በኢትዮጵያ ግን መቀበሉ ከምር ነበር፡፡ ክርስትናው በመጀመሪያ በቤተ መንግሥቱ ገባ፣ ከዚያ ቀስ በቀስ ወደመላው ሕዝብ ተዛመተ፡፡ በሮማ ግዛት ዐፄ ሕዝቡን በክርስትና ሃይማኖት ለማሳመን ሐዋርያትና የኋላ ዘመን አባቶች ሲሳተፉ፣ በኢትዮጵያ ክርስትና በፈቃደኝነት ገባ” ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ሐዋርያዊ፣ አገልግሎት አልነበረም ለማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡
ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ትንታኔያቸውን በመቀጠል፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ መንግሥት ሃይማኖት ከርስትናን ስትቀበል ስለነበረው ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ሁኔታም ሲያብራሩ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷ እየተጠናከረ በምትቋቋምበት ወቅት የአርዮስ ክህደት ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ቅዱስ ፍሬምናጦስ በቅዱስ አትናቴዎስ በሚመራው የእስክንድርያ መንበር ሥር ሆኖ በኒቅያ ጉባኤ አርዮስን ከሚቃወሙ የኦርቶዶክሳውያኑ ወገን ነበር፡፡ ይህም የሆነው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በብሔራዊነት ከመመሥረቷ በፊት ነው፡፡ ነገር ግን የጉባኤው ውሳኔ አስገዳጅ ባይሆንም ኢትዮጵያ ከአትናቴዎስ እና ከኒቅያ እምነት ነች ካሉ በኋላ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከአርዮሳውያን የገጠማትንም ፈተና ሲገልጹም፤ “የታላቁ ቆስጠንጢኖስ ልጅ ቆንስጣ ወደ አርዮስ ምንፍቅና ለማምጣት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም ለኢዛና እና ሳይዛና ቅዱስ ፍሬምናጦስን ወደ እስክንድርያ እንዲልከውና የእርሱም ሃይማኖት እንዲፈተሽ ደብዳቤ በመላክ ጠይቆ ነበር፡፡ ዓላማውም የኦርቶዶክሳዊነትን ዓለም ተቀፋዊ ተቀባይነት ማረጋገጥ ነበር፡፡ በዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ላይ ያደረጉት ተልእኮ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ቅዱስ ፍሬምናጣስም ከአትናቴዎስ የተማረውን ትምህርት እያስተማረ በአክሱም ቀረ፡፡” በማለት ነው፡፡ ይኼ እንግዲህ አንዱ የታሪኳ አካል ነው፡፡

ዘመነ ተሰዓቱ ቅዱሳን

ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ “The Expansion and consolidation of Christianity” በሚል ርእስ በአሰፈሩት መጣጥፋቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያነት አገልግሎት ምን እንደሚመስል ያስቃኙናልና፡፡ “እንደ ኢትዮጵያ ጳጳሳት ታሪካዊ ቅደም ተከተል ዝርዝር ከሆነ ቅዲስ ፍሬምናጦስ የተተካው በአቡነ ሚናስ ነው፡፡ መካነ ልደቱም ከግብጽ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመታት የግብጻውያን ልዩ የሆነው አገዛዝ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተጫነ፡፡ በዚህ ዘመን በግብጻውያን ዘንድ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ለሢመተ ጵጵስና ብቁዎች ተደርገው አይወሰዱም፡፡ ሚናስ ስለራሱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጥቂት የሥነ ጽሑፍ መረጃ ቢተውም በሐዋርያዊ አገልግሎት በከፍተኛ አስተዋጽኦነቱ የሚጠቀሰው የዘጠኙ ቅዱሳን አገልግሎት ነው” ይላሉ ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ከላይ በጠቀስነው ጽሑፋቸው፡፡
እኚህ የታሪክ ምሁር “The Religious Life in Ethiopia” በተባለው የጥናት ወረቀታቸው ደግሞ እነዚህ ቅዱሳን ሐዋርያነትን መሠረት በአደረገው አስተዳደራዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ቤተ ክርስቲያኒቱን በየትኛው የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንደአስቀመጡ ሲገልጹ “በዘጠኙ ቅዱሳን ቤተ ጣዖትንና የቆዩ ማእከለ ሁሉን አምላኪዎች /Pagan centers/ ወደ ክርስትና ማእከልነት ለወጡ፡፡ በዚህ ሒደት ከሕዝቡ ምንም ተቃውሞ አልገጠማቸውም፤ አንድም ቅዱስ አልተሰዋም” ይላሉ፡፡
ይህ ሒደት በሀገሪቱ የክርስትና ታሪክ ውስጥ አንዱ አስደሳች ክስተት ነው፡፡ በዘጠኙ ቅዱሳን መምጣት ምክንያት የተስፋፋው የክርስትናው ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱም ባህል ክርስቲያናዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም የጥንቱ የክርስትና አገባብ ጠባይ ነው፡፡ የሚሉት ዶክተር ሥግግው ሐብለ ሥላሴ “ይኼ ሃይማኖታዊ ክስተት ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ አገልግሎት፣ የኅብረተሰቡ የማኅበራዊ ኑሮ አካል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ማምለኪያ ሥፍራ ብቻ ሳትሆን የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች መፍቻ ቦታ መሆኗም በእነዚህ ቅዱሳን ተግባር ተረጋግጧል፡፡” ይላሉ፡፡ ከዚያም በመቀጠል “በጥቅሉ እነዚህ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱ ወይም ክርስትና እንደ ሃይማኖት ክስተት ሃይማኖታዊ ተቋም እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ደግሞ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ እንድትሆን አድርገዋታል” ይላሉ፡፡
ብፁዕ አበኑ ጎርጎርዮስ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን ታሪክ” በተባለው መጽሐፋቸው እነዚህ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታችንን እንዴት እንደ አጸኑም ሲገልጹ “… በእነዚህ ዘጠኙ ቅዱሳን የጸናችልን ሃይማኖታችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትባላለች፡፡” በማለት ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱን ያጸኑበትን የአገልግሎት ትሩፋታቸውን “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትናንትናና ዛሬ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው መጽሐፍ ሲዘረዝር “ሥርዓተ ምንኩስናን፣ ገዳማዊ ሕይወትንና ምናኔን ማስተማር፣ ገዳማትን በየቦታው ማቋቋም፣ በቅዱስ ፍሬምናጦስ ጊዜ ያልተተረጎሙ መጻሕፍትን መተርጎም፤ በከሣቴ ብርሃን ሰላማ ጊዜ የተቋቋመችውን ቤተ ክርስቲያን ማጠናከር” በማለት ነው፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የሐዋርያት ሥራ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አጭር መግቢያ” በሚል ርእስ በጻፈው መጣጥፉ እንደገለጸው፣ ዘጠኙ ቅዱሳን በትግራይና አካባቢዋ ወንጌልን በማስፋፋት ቅዱስት መጻሕፍትን በመተርጎምና ገዳማትን በማስፋፋት ለሐዋርያነት ተልእኮ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በዚህም የመጀመሪያው ዘመን በኤርትራ፣ ትግራይ፣ ወሎ፣ ጎንደር ጎጃምና ሸዋ ሀገረ ስብከት ወንጌልን ማስፋፋት ተችሏል፡፡ በትግራይ የተሰዐቱ ቅዱሳን ገዳማት፣ በወሎ የተድባበ ማርያም ደብር፣ በሸዋ በጥንቱ ዞረሬ በዛሬው ደረሳ ብርቴ ጥረት የተደረገው በዚህ ዘመን ነው፡፡
ከተግባራቸው ተንሥተው የዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለውን አንድምታ ዶክተር ሥርግው “The Expansion and consolidation of Christianity” በተባለው የጥናት መጣጥፋቸው ሲጠቅሱ “…. የዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሕይወት እና በሀገሪቱ የባህል ዕድገት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው” በማለት ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም” የተባለውም መድበል ከላይ የጠቀስነው የዶክተር ሥርግውን ሐሳብ በማጠናከር እንዲህ ይላል፡፡
“ከዘጠኙ ቅዱሳን መምጣት በኋላ የአክሱም ቤተ መንግሥትና መላው የኢትዮጵያ ግዛት በክርስትና ሃይማኖት ትምህርትና ስብከት ተደርሶ ነበር፡፡ ተሰዐቱ ቅዱሳን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ጥንካሬ ከፍተኛ ተልእኮን ፈጽመው ስለዐረፉ ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን ብላ ታከብራቸዋለች”
በዚሁ መጽሐፍ ብፁዕ አቡነ ገሪማ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሪስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና መንግሥት በየዘመናቱ” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሑፍ ተሰዓቱ ቅዱሳን በአመራራቸው በሕዝበ ክርስቲያኑ እንደሚወደዱ ገልጸዋል፡፡
እንግዲህ ከነዚህ የመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት ክንዋኔዎች ተነሥተን ቤተ ክርስቲያኒቱ በወቅቱ ተልእኮዋን ለመወጣት የሚያስችላት የወቅቱ አደረጃጀት እንደነበራት መደምደም ይቻላል፡፡ ይኼንም አደረጃጀት ዶክተር ሥርግው ከላይ በጠቀስነው የጥናት ጽሑፋቸው ላይ የጠቀሱት “ከክርስትና መስፋፋት በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ አራት አህጉረ ስብከት ነበር፡፡ እያንዳንዱ የሚመራው በጳጳስ ነበር፡፡ የእነዚህም ርእስ የአክሱም ሊቀ ጳጳስ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አስቀድመን እንደገለነጽነው ሁሉም ጳጳሳት መካነ ልደታቸው ግብጽ ወይም ግብጻውያን ናቸው፡፡ በዶግማም ሆነ በአስተዳደር ከግብጹ ፓትርያርክ ጋራ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስፈጽሙት የግብጽን ፍላጎት ነበር፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ልዩ ክስተት ነው” በማለት ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር የነበረበት ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ከላይ በጠቀስነው መጽሐፍና ርእሰ ጉዳይ ላይ “አራተኛው መቶ ዓመት በቅዱሳን ነገሥተ ኢትዮጵያ አብርሃ ወአጽብሐ ዘመን መንግሥት፤ በቅዱስ ፍሬምናጦስ ዘመን ክህነት ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር አምሮ፣ ሰምሮ፣ የታየበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክረስቲያን ብሔራዊት የሆነችበት ጊዜ ነበር” ይላሉ፡፡
ከዚህም ጋር አያይዘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአራተኛው መቶ ዓመት እስከ ዐሥራ አምስተኛው መቶ ዓመት እስከ ዐሥራ አምስተኛው መቶ ዓመት በነበሩት በዘመናት በመካከሉ በየጊዜው ችግር ቢያጋጥምም ሁለንተናዊ የሆነ አርኪ የቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ አስተዳደር የተፈጸመበት ዘመን መሆኑን አበክረው ይገልጻሉ፡፡
እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን በፊት በኢትዮጵያው ጃንደረባ የተሰበከችልን በቅዱስ ፍሬምናጦስ እና በዘጠኙ ቅዱሳን የጸናችልን ነች፡፡ ከዚያም በኋላ የእስልምና መነሳት፣ የዮዲት ጉዲት ጥፋትና የግራኝ አህመድ ውድመት በቤተ ክርስቲያኒቱ በየዘመኑ ቢፈራረቁም በርካታ ወርቃማ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ከአለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ በላይ መሔድ አንችልም፡፡ የት ነበርን የሚለውን ለማሳየት የክርስትና የመጀመሪያዎቹን ዘመናት አይተናል፡፡ ቦታ ኖሮን እያንዳንዱን ዘመን ብናይ አሁን ከአለንበት ጋራ ስናነጻድር እጅግ ያስቆጭ ነበር፡፡ ይሁንና አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማየት ያነሳናቸው ማሳያዎች በቂ ናቸው፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ
እንግዲህ ቤተ ክርስቲያኒቱ በየዘመናቱ የተለያዩ ፈተናዎች ቢገጥሟትም አስቀድመን እንደተመለከትነው ተልእኮዋን በአግባቡና ሥርዓታዊ በሆነ መልኩ ትወጣ ነበር፡፡ በዚህ መልኩም ከእኛ ዘመን ደርሳለች፡፡ ይሁንና አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተወሳሰበ ከመምጣቱ የተነሣ ተልእኮዋ ላይ አደጋዎች ተጋርጠዋል፡፡ እነዚህን በሦስት ከፍለን እናቀርባለን፡፡
ሀ. አስተምህሯዊ ቅሰጣ
ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው ወልድ ዋሕድ በሚለው መሠረተ እምነት እና ነቢያት፣ ሐዋርያት ስለ ወልድ ዋሕድ መሠረተ እምነት በአስተማሩት ትምህርት ላይ ነው፡፡ እነዚህን የመሠረተ እምነት ትምህርቶች ከምእመናን ልቡና የማራቅና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት የማስወገድ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ የእርሷ ነን በሚሉ በተግባራቸው ግን ባልሆኑት እየተሠራ ነው፡፡ ይኼም ሥራ እየተሠራ ያለው በተሐድሶ ኑፋቄ አንቀንቃኞች፣ ሰባክያንና የስሕተት ትምህርት ባዘሉ መጻሕፍት ጸሐፊያን ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓተ አምልኮ፣ ትውፊትና ታሪክ የመከለሱና የመበረዙ ሥራ በነዚሁ አካላት ተጧጡፏል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን አደጋ በአግባቡ የተረዳና ተገቢውን የመፈትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የስብከተ ወንጌል ዕቅድና ግብ የላትም፡፡ ለዚሁ ተግባር ማስፈጸሚያ ተገቢ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና በጀት አትመድብም፡፡ ይኼ ደግሞ ችግሩ እጅግ አሳሳቢና የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ በማሳካት ረገድ መጪውን ዘመን ጨለማ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ የሚጠቀሰው በ1999-2000 ዓ.ም በተካሔደው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት በግልጽ የታየው እውነታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናንን ቁጥር ከ50.6 በመቶ ወደ 43.5 በመቶ ወርዷል፡፡  በከተማ ቤተ ክርስቲያናችን ያላት የምእመናን ድርሻ እየቀነሰ መጥቶ ወደ 59.1 በመቶ ሲሆን በገጠር ደግሞ 40.5 በመቶ ነው፡፡ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ድርሻ ቁልቁል እየወረደ መሆኑን ያሳያል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የ7.1 በመቶ መቀነስ አሳይቷል፡፡ ይኼ ሁኔታ በዚህ መልኩ ከቀጠለ የቤተ ክርስቲያን ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን ለመጠቆም ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ደግሞ የእርሷን እንጀራ እየበሉ በሌላው ደጅ የሚጠኑ ሰዎቿ ድርሻውን ይወስዳሉ፡፡
ለ. አስተዳደራዊ ችግር
የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ ተልእኮዎች የሆኑት ማጥመቅ፣ ማጽናትና መከታተል መሆኑ እየታወቀ ይህን ተልእኮ ማሳካት የሚያስችል የተጠናከረ አስተዳደራዊ አደረጃጀትና የሰው ኃይል የለም፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ አደርጃጀትና አወቃቀር ወቅቱ ከሚጠይቀው፣ አሁን ካሉት ሥራዎች ስፋትና ከልማትና ማኅበራዊ እንቅስቅሴዎች ጋር አብሮ የሚጓዝ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ወቅቱን በመዋጀት ከጊዜው ጋራ እንዳትራመድ አድርጓታል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፖሊሲ በማውጣትና ስትራቴጀ በመንደፍ የመምራት ሓላፊነቱንና አደራውን በብቃት ለመወጣት በሚያስችል ሁኔታ አልተደራጀም፡፡ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች አፈጻጸም የሚከታተልበትና የሚገመግምበት መከታተያና መገምገማያ እንዲሁም የአሠራር ሥርዓት የለውም፡፡
እንደሚታወቀው የአሠራር መዋቅር ተቋማዊ ግብን የማስፈጸም ሥርዓት እና ብቃት እንዲኖረው ተደርጎ ይዘጋጃል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ የአሠራር ሥርዓትን ጠብቆ ጉዳይን በወቅቱ ማስፈጸምም ሆነ መፈጸም አስቸጋሪ ነው፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክህነቱ አሠራር መዋቅሮች የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔዎች የማስፈጸምም ሆነ የመፈጸም ግዴታ ቢኖርባቸውም መዋቅራዊ የአሠራር ሥርዓቱ ልል ከመሆኑ የተነሣ ይህ ሲሆን አይታይም፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ከአስፈለገ አንድ የአጥቢያ አስተዳዳሪ የሚጥስበት፣ የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅን የሥራ መመሪያ አንድ የመምሪያ ሓላፊ ተገቢና ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የማይቀበልበት እና የማያስፈጽምበት ሁኔታ አለ፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚታየው የአስተዳደራዊ አሠራር ክፍተት እንዲህ መሆኑ የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ አካላት ምቹ መስፈንጠሪያ ሆኖላቸዋል፡፡ በየትኛውም አግባብ በየትኛውም የአሠራር መዋቅር የሚፈልጉትን ያስወስናሉ፤ ያልፈለጉትን ውሳኔ ያሽራሉ፡፡
ገዳማቱና የአብነት ትምህርት ቤቶቹም የሚገኙበት አስከፊ ገጽታም የአስተዳደራዊ ችግሩ ነጸብራቅ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ በሚፈጠሩ የተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች የተነሣ ገዳማቱ ያላቸውን ጥቂት ገቢ፣ መሬት፣ የሰው ኃይልና ሌሎች ሀብቶችን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ገዳማቱን ወደ ቁሪት ገዳምነት እንዲቀየሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በገዳማት ሊኖር ይችል የነበረውንም የልማት ተሳትፎ በእጅጉ ጎድቶታል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶች ለደቀ መዛሙርቱ እና ለመምህራኑ ምግብና መጠለያ ማግኘት ተስኗቸው ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉና እንዳይስፋፉ የሆነውም የአስተዳደራዊው ችግር ውጤት ነው፡፡ በዚህ መልኩ በየገዳማቱና የአብነት ትምህርት ቤቶቹ የሚታየው ችግር በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የነገይቱን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተካ ትውልድ ማግኘትን ከባድ ያደርገዋል፡፡
የአስተዳደሪዊው ችግር ውጤት /Effect/ ያረፈው በገዳማቱና በአብነት ትምህርት ቤቶቹ ብቻ ሳይሆን በካህናቱም ኑሮ ላይ ነው፡፡ ካህናት የሚያገኙት ደመወዝ አሁን ካለው የገበያ ሁኔታ አንጻር ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር በቂ አይደለም፡፡ ተምረው ነገ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ፣ ኑሯችንን ያሻሽላሉ፤ ጧሪ ቀባሪያችን ይሆኑናል የሚሏቸውን ልጆቻቸውን ዘመናዊ ትምህርት ማስተማር እንዳይችሉ ተፅዕኖ አድርጎባቸዋል፡፡ ከዚህ ሲብስም “እኔ በየአብነት ት/ ቤቱ ብዙ ደክሜ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ተምሬ ምን አገኘሁ” በሚል ልጆቻቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት እንዲያርቁ አድርጓቸዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብት /የሰው ኃይል፣ ገንዘብ፣ ንብረት/ አመራር ሠራተኞችን፣ ገንዘብንና ንብረትን በአግባቡና ዘመኑ በሚጠይቀው የአሠራር ዘይቤ በማቀናጀት የቤተ ክረስቲያኒቱ ዋነኛ ተልእኮ ማስፈጸሚያ የሆነውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋትና ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል ዕውቀትና ልምድ ያለው የሰው ኃይል እና አስተዳደር ሥርዓት የላትም፡፡ ይህ ደግሞ የመጪው ዘመን ቀጣይ አገልግሎቷን በሚፈለገውና ወቅቱ በሚጠይቀው መጠን ውጤታማ አያደርገውም፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/    ቤትና በየአህጉረ ስብከት የሓላፊዎች ምደባ የትምህርት ዝግጅትን ሙያና ችሎታን ወይም ብቃትን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ ይኼ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የሆነ የአመራር እና አስተዳደር ችግር የሀብት ብክነትና ዝርፊያ፣ ውዝግብና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን አንሰራፍቷል፡፡ ይህ ሁኔታ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለቤተ ክረስቲያኒቱ ተልእኮ ግድ የሌላቸው ሰዎች መጠራቀሚያ ትሆናለች፡፡ ምእመኑም ባለው አመራር ላይ እምነቱን እያጣ ሲሔድ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ማበርከት የሚገባውን በጎ አስተዋጽኦ ከማበርከት ሊታቀብ ይችላል፡፡
ሐ. ዘመናዊ የፋይናንስ አስተዳደር አለመኖር
ቤተ ክርስቲያኒቱ  ተልእኮዋን መፈጸም የሚያስችላት በማእከላዊነት የሚተዳደር ዘመናዊ የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት የላትም፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ከምፅዋት ከሚያገኙት ገንዘብ ባሻገር የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሕንፃዎች እየገነቡ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት ቢያደርጉም የፋይናንስ አያያዛቸውና አጠቃቀማቸው ለብክነትና ምዝበራ የተጋለጠ ነው፡፡ በቤተ ክርስሪቲያኒቱ ውስጥ ጠንካራ የፋይናንስና የኦዲት ሥርዓት እንዲሁም ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት በዕቅድና ሪፖርት የታገዘ የአሠራር ሥርዓት የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ለልማት ሊውል የሚችለው የቤተ ክርስቲያኒቱ አንጡራ ሀብት ሊባክን ከመቻሉም በላይ ጠንካራ ልማት ሊመጣ አልቻለም፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የፋይናንስ አያያዟና አጠቃቀሟ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ ተልእኮ ከማደናቀፉም በላይ የራሷን አገልጋዮች በአመዛኙ ከችግር ማሳቀቅ ያልቻለበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያኒቱ በሐዋርያዊ ተልእኮዋ አፈጻጸሟ እንድትደክም ከማድረጉም ባሻገር የሙስናው ጽንፍ ቤተ ክርስቲያኒቱን በምእመናን ዘንድ ያላትን አመኔታና ከበሬታ እያሳጣት ነው፡፡
በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ የሆነ የፋይናንስ አስተዳደር ባለመኖሩ አገልጋዮቿ ገጠሩን እየተው ገቢ ይገኝባቸዋል ወደሚሏቸው ከተሞች እንዲጎርፉ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በገጠር የሚገኙትን ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ያለ አገልጋይ በማስቀረቱ እንዲዘጉ ሆነዋል፡፡ እዚህ ላይ ሆነን የነገይቱን የገጠሪቱን ቤተ ክርስቲያን ስናስብ ስጋት ላይ ይጥለናል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲሁም በማኅበራዊ አገልግሎትና ልማታዊ ሥራዎች ሊደግፏት የሚችሉት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በምዝበራና ብኩንነት እየተዳከሙና የሚጠበቅባቸውን ያህል ፍሬያማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሥር እየሰደደና እየጸና ከሔደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለማትወጣው አዘቅት ሊዳርጋት ይተላል፡፡ የጥቂት ግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት እየጨመረ መዋቅራዊ ውሳኔዎችና አፈጻጸሞች እየከሰሙ ከሔዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ዕጣ ፋንታ በግለሰቦች እጅ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል፡፡ አሁን እየታየ ያለውም በአመዛኙ የዚሁ ተመሳሳይ ነው፡፡
የመፍትሔ አቅጣጫ ጥቁምታ
በአደጋ ቁልቁለት ላይ ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሯዊ ቅሰጣ-አስተዳደራዊ ፋይናንሳዊ ችግሮች ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጧን በአስቸኳይ የምትፈትሽበት መፍትሔና አፋጣኝ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አለባት፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ቤተ ክርስቲያናችን ዋናና ተቀዳሚ ዓላማዋ የሆነውን ሐዋርያዊ አገልግሎት በማስፋፋት፣ የምእመናንን ክርስቲያናዊ ሕይወት የማጽናትና የማጠናከር እንዲሁም ያላመኑትን በማስተማርና በማሳመን ተልእኮዋን ማሳካት የሚያስችላትን ተገቢውን አደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና በጀት ሥርዓትም እንዲኖር በማድረግ ረገድ ቀዳሚ ሓላፊነት እንዳለበት ይተወቃል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከውስጥ ሆነው የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ በማደናቀፍ ከሌሎች የተለየ ዓላማ ካላቸው ጋር ሽርክና መፍጠር ምእመናንን ከበረታቸው እያስኮበለሉ ባሉት ላይም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት እርምጃ የሚወስድበትን አቅጣጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ማስቀመጥ አለበት፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በአስቸኳይ ውስጧን በመፈተሽ ጊዜ እና መስክ ወለድ ለሆኑ መሠረታዊ ፈተናዎችና ችግሮች ዘለቄታ ያለው፣ ተጨባጭና ችግር ፈቺ መፍትሔ ማስቀመጥ አለባት፡፡ ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረታዊ ተልእኮዋን ለማስፈጸም፣ ቀልጣፋ አሠራርን፣ ግልጽ፣ ሓላፊነትና ተጠቃቂነት ሊያሰፍን በሚያስችል መልኩ አስተዳደራዊ የመዋቅር ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ሙሉ ሥልጣንና ሓላፊነት ያለው በብፁዓን አበው የሚመራ፣ በሥሩ የተለያዩ ባለሙያ ምሁራንን ያካተተ የአማካሪ ቡድን የሚዋቀርበት አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅራዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮችን አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚጠቁም አካል እንዲቋቋም ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የገዳማቱ ሥሪት ገቢያቸውን በራሳቸው እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል በመሆኑና ወደ ሀገረ ስብከቶች ወይም ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገቢ ፈሰስ እንዲያስገቡ የሚጠይቁ ባለመሆናቸው፤ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የልማት ፕሮጀክቶችን በየገዳማቱ በተናጠል የሚሠራበትን አቅጣጫ ማስቀመጥ ለዚህም ሥራ ተስማሚ የሰው ኃይልና በጀት መመደብ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልማት የሚመራው አካል መንፈሳዊውን አገልግሎት ከሚመራና ከሚያከናውነው አካል ተለይቶ የልማት አስተደደሩ በቂ ዕውቀትና ልምድ ባለው የሰው ኃይል የሚመራበትን አስተዳደራዊና መዋቀራዊ ሁኔታዎች ማመቻቸት እና ማጠናከር ይኖርበታል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት ዘመናዊና ወቅታዊ ድርብ የሒሳብ አያያዝን የተከተለ እንዲሁም የበጀት ሥርዐቱም በመደበኛና የካፒታል በጀት ተለይቶ በየዘመኑና በየሥራ ዘርፉ የበጀት ሥርዓት ተግባራዊ የሚሆንበትን፤ በየወቅቱ ሪፖርት እየቀረበበት ግምግማና ክትትል የሚደረግበትን አቅጣጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም ጋር አያይዞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በማእከላዊነት የሚተዳደር የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት እንዲኖራት ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አሠራር በመሆኑ በተገቢው ሙያዊ ጥናት መሠረት ተግባራዊ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ላእላይ መዋቅር የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ መፍትሔ ይሆናሉ በማለት የተጠቆሙትን ሐሳቦች እንዳላቸው ተጨባጭነትና ተግባራዊነት እንዲጠቀምባቸው አበክረን እንገልጻለን፡፡ ምክንያቱም አደጋው በዚሁ ከቀጠለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዐይናችን እያየ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀሳጮች ተውጣ፣ ታሪካዊና ወቅታዊ ልዕልናዋን አጥታና ሊኖራት የሚገባው ተደማጭነት ተሸርሽሮ አነስተኛ ቁጥር ተከታይ ያላት እንዳትሆን ስለምንሰጋ ነው፡፡ አሁን ያለው ነባራዊ እውነታም የሚያሳየው ይህንኑ ነውና፡፡
እንግዲህ ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሁን ያለችበት ሁኔታ በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት ከነበረችበት ደረጃ ምን ያህል በችግር የተተበተበ እንደሆነ ብዙ የሚያከራክር አይመስለንም፡፡ ከዚህም በላይ ግን አሁን በምንንደረደርበት አቅጣጫ ከቀጠልን ከዚህም የከፋ ውስብስብና ዘመን ተሻጋሪ ችግሮችን ለመጪው ትውልድና ለነገይቷ ቤተ ክርስቲያን እንዳናስተላልፍ ያሰጋል፡፡ ይህም እንደትውልድ ከታሪክ፣ ከሕሊናና ከእግዚአብሔር ተጠያቂነት አያድነንም፡፡
ይህ ማለት ግን የተሻሉ ዕድሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በቅዱስ ሲኖዶስ የመፍትሔ እርምጃዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላትን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ወደፊት ሊገጥሙን የሚችሉ አደጋዎችን በተሻለ ብቃት መሻገር እንችላለን፡፡ ይህ ሆኖ እንድናይ ደግሞ አሁን ያለንበትን አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ድባብ በመሠረታዊነት ሊቀይሩ የሚያስችሉ ምሁራዊ እይታዎችንና ሒሶችን ማስፋትም ይጠበቅብናል፡፡
ውጤቱም የተጋረጡብንን መሠረታዊ ችግሮች መሻገር ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላእላይና ታህታይ የሥልጣን መዋቅር የሚቀመጡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በብቃታቸው፣ በሥነ ምግባራቸው፣ በመንፈሳዊ ተጋድሎ የታወቁ፣ ቤተ ክርሰቲያኒቱን ካለችበት አሰክፊ ችግር በዘላቂነት ለማውጣት ችሎታ፣ እልሁና ርእይ ያላቸው ይሆናሉ ብለን እናምናለን፡፡ አምላከ ቅዱሳን ይህንኑ ያድለን፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ፣ 19ኛ ዓመት ቁጥር 2

መስቀል ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

መስከረም 28/2004 ዓ.ም.

ምን አልባት አንድ ሰው የእውነትን እውቀት ቢያስተምር በእውቀቱ ለመማረክ ከጠቢቡ ይልቅ አላዋቂው በጣም የቀረበ ነው፡፡ እርሱንም ወደዚህ እውቀት ለማምጣት ከጠቢቡ ይልቅ አላዋቂው በጣም ይቀላል፡፡ ይህን እውቀት እረኞችና ባላገሮች ፈጥነው ለመቀበል የበቁት እውቀት ነው፡፡ እነርሱ ለሁልጊዜውም አንዳች ጥርጣሬ በልቡናቸው ሳያሳድሩ እውቀቱን እንደ ጌታ ቃል አድርገው ተቀብለውታል፡፡ በዚህ መልክ ጌታችን የአሕዛብን ማስተዋልና ጥበብ አጠፋው፡፡ ይቺ የአሕዛብ ማስተዋልና ጥበብ አስቀድማ ራሱዋን አዋርዳለችና ለዘለዓለም ለምንም የማትጠቅምና የማትረባ አደረጋት፡፡ ይቺ ማስተዋልና ጥበብ ምንም እንኳ የእርሱዋን አቅምና ችሎታ በጌታችን ሥራ ላይ ለመግለጥ ብትሞክርም አልሆነላትም፡፡ ስለዚህም አሁን ራሱዋን ለማላቅ አልተቻላትም፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ የተገለጠው እውቀት እርሱዋን የሚሻ አይደለምና፡፡ ይህ አዲስ የተገለጠው እግዚአብሔርን የማወቅ መንገድ ከእርሱዋ በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ወደ ዚህ ወደ እግዚአብሔር የእውቀት ከፍታ ለመምጣት እምነትና የዋሃት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ከውጭ በትምህርት ከምናገኛቸው ይልቅ ሊኖሩን የሚገቡ መንፈሳዊ ሀብታት ናቸው፡፡ ምክንያቱም “እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እድርጎአታል ብሎናልና፡፡

ነገር ግን “እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አድርጐታል” ሲል ምን ማለቱ ነው? ምክንያቱም ሞኝነትን በእምነት ካለመቀበል ጋር አቆራኝቶ ነውና ያስተማረው፡፡ የዚህ ዓለም ጥበበኞች የሚባሉት በዚህ እውቀታቸው አብዝተው የሚመኩ ቢሆንም ጌታችን ግን እነርሱን ለመጋፈጥ ጊዜውን አላጠፋም ነበር፡፡ መልካም የሆነውን ነገር ፈጽማ ለይታ ማወቅ የተሳናት ይህች ጥበብ ምን ዓይነት ጥበብ ናት? ስለዚህ አስቀድማ የእርሱዋ ጥበብ የማይጠቅምና የማይረባ መሆኑን ከተረዳች በኋላ ጌታችን ደግሞ ሞኝነት እንደሆነ ገለጠው፡፡ ይህች ሰዋዊት ጥበብና ማስተዋል የእግዚአብሔርን ሕልውና በእውቀቱዋ ተደግፋ ማረጋገጥ አልተቻላትም፤ እንዴት ታዲያ ከዚህ በእጅጉ የሚልቀውንና የሚሰፋውን የእግዚአብሔርን ሥራ መረዳትና ማስረዳት ይቻላታል? ስለዚህም ከዚህ እንደምንረዳው የእግዚአብሔርን ጥበብ ለመረዳት የግድ እምነት እንጂ ብዙ ምርምርና ድካም አለማስፈለጉን ነው፡፡ በዚህ መልክ እግዚአብሔር አምላክ የዓለምን ጥበብ ሞኝነት እንዳደረጋት ማስተዋል እንችላለን፡፡

 

እርሱ በወንጌል ሞኝነት ዓለሙን ለማዳን ወድዶአል፡፡ ነገር ግን ሞኝነት ሲል በአላዋቂነት ማለቱ ግን አይደለም በወንጌል ሞኝነት ሲል በሰው ዘንድ እንደ ሞኝነት በሚቆጠር መልኩ ሲለን ነው፡፡ በእርሱ የተገለጠችው ጥበብ ታላቅ የሆነች ጥበብ ናት፤ ነገር ግን ለዓለሙ የገለጠባት መንገድ ግን ሞኝነት ይመስላል፡፡ ከእግዚአብሔር ሞኝነት የሚልቅ ጥበብ ፈጽሞ የለም፡፡ ከዓለሙም ሲያስተዋውቃት ሞኝነት በሚመስል መንገድ ነበር፡፡ ይህችን ጥበብ ወደ ዓለም ሲያገባት ለምሳሌ ልክ እንደ አፍላጠን አሪስጣ ጣሊስ፣ ሶቅራጠስ በፍልስፍና በተካኑት ወገኖች በኩል አልነበረም ፡፡ ነገር ግን በተናቁ ዓሣ አጥማጆች በኩል ነው እንጂ፡፡ እንዲህ ስለሆነም ድሉ እጅግ ታላቅና አንጸባራቂ ሆነ፡፡

ሐዋርያው በመቀጠል ስለመስቀሉ ኃይል ሲገልጽ “መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፣ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፣ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ፣ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፤ የተጠሩት ግን አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎች ቢሆኑ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡” (ቁ.፳፪-፳፬) አለ፡፡

ለዚህ ኃይለ ቃል ሰፊ ትንታኔን መስጠት ይቻላል፡፡በዚህ ቦታ ሐዋርያው ሊገልጠው የፈለገው ነገር እንዴት እግዚአብሔር አምላክ ሰው ከሚያስበው በተቃራኒው መንገድ ሞትን ድል እንደነሣውና ወንጌል ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠች ስለመሆኑዋ ነው፡፡ ስለዚህ ሲናገር ምን አለ?፡- አይሁድን በክርስቶስ እመኑ ስላቸው እነርሱ ደግሞ የሞተውን አስነሡትና በአጋንንት ቁራኛ የተያዘውን ፈውሱትና አሳዩን እነዚህን ምልክቶችን ብታሳዩን በእርሱ እናምናለን፡፡ እኛ ግን በምላሹ ስንመልስላቸው እኛስ “የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብክላችኋለን” እንላቸዋለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ቃላችን ፈቃዱ የሌላቸው ትእቢተኞችን ብቻ አይደለም የሚያሸሻቸው፣ ነገር ግን በእርሱ ለማመን ፈቃዱ ያላቸው አይሁድ እንኳ የሚያስበረግግ ቃል ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ቃሉ ያን ያህል የሚያስበረግግ ቃል ሆኖ ግን አይደለም፡፡ ይልቁኑ የጠፉትን ወደ እርሱ የሚያቀርብና ለእግዚአብሔር ምርኮን የሚያመጣና ድል የሚነሣ ቃል ነበር፡፡

 

አሕዛብ ደግሞ ቃሉን በንግግር ጥበብ አሳምረን በፍልስፍና መንገድ እንድናቀርብላቸው ይሻሉ፡፡ እነርሱ እንዲህ እንዲቀርብላቸው ቢወዱም እኛ ግን ስለ መስቀሉ እንሰብክላቸዋለን፡፡ ስለዚህም በአይሁድ ዘንድ እንደ ደካሞች ተደርገን እንደተቆጠርን እንዲሁ በእነዚህም ዘንድ እንደሞኞች እንቆጠራለን፡፡ እኛን ከመስማት የሚመለሱት እነርሱ በጠየቁን መልክ ባለማቅረባችን ብቻ ግን አይለደም፤ እኛን ከመስማት የሚመለሱት፣ ነገር ግን እነርሱ ከጠየቁን በተቃራኒው አድርገን በማቅረባችንም ጭምር ነው እንጂ፡፡ ለእነርሱ ለእኛ የመዳን ምልክታችን መስቀል ስለመሆኑ በምክንያት አለመግለጻችን ብቻ አይደለም እኛን ከመስማት እንዲመለሱ የሚያደርጋቸው ነገር መስቀሉ ለእነርሱ የደካማነት ምልክት እንጂ የኃያልነት ምልክት አለመሆኑም ጭምር እንጂ፡፡ በእነርሱ ዘንድ ይህ ጥበብ ሳይሆን ሞኝነትን የሚያሳይ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡

ስለዚህም እነርሱ ኃይልን የሚሰጣቸውን ምልክትንና ጥበብ ሲሹ የጠየቁትን አለማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን እነርሱ ከሚመኙት ምልክት በተቃራኒ በማቅረባችንና ክርስቶስን እንዲከተሉት በመስበካችንም ይሰነካከላሉ፡፡ እንዴት ታዲያ እኛ የምንሰብከው የመስቀሉ ኃይል ከመረዳት ያለፈ አይሆን? አንድ በመከራ ውስጥ ላለና ከስቃዩ ለማረፍ መጠጊያ ለሚፈልግ ሰው እኛ እጅግ አደገኛ ወደሆነው የባሕር ማዕበል ውስጥ እርሱን የምንመራውና በዚያ ውስጥ የምናድነው መሆናችንን የገለጽንለት ብንሆን እንዴት እኛን አምኖን ደስ ብሎት ሊከተለን ይችላል? ወይም አንድ ሐኪም የታመመነውን ቁስለኛ ሰው ሕማሙን በመድኃኒት ሳይሆን ቁስሉን ራሱን ደግሞ በማቃጠል እንደሚያድነው እየማለ ቢነግረው እንዴት ሊቀበለው ይችላል? ይህ በእርግጥ ልዩ የሆነ ኃይል ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቶስ ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሁሉ ሲልካቸው ያለ ምልክት አልሰደዳቸውም፡፡ ነገር ግን ከሚታወቁት ምልክቶች በተቃራኒው የሆኑ ምልክቶችን ያደርጉ ዘንድ ነበር ሥልጣንን የሰጣቸው ፡፡

 

በሥጋው ወራት ጌታችን እንዲህ ዓይነት ከተፈጥሮአዊ ሥርዓት በወጣ መልኩ ምልክቶችን ያደርግ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሲወለድ ጀምሮ ዐይነ ስውር በነበረው ላይ ኃይሉን በመፈጸም አሳይቶናል፡፡ የዚህን ሰው የታወሩትን ዐይኖች ጌታችን ሲፈውሳቸው ዐይነ ስውርነትን በሚያባብስ ጭቃ ቀብቶ ነበር፡፡ (ዮሐ.9፥6) በጭቃው ጌታችን ይህን እውር የሆነው ሰው እንደፈወሰው እንዲሁ በመስቀሉ ዓለሙን ወደ እርሱ አቀረበው፡፡ ተቃዋሚዎችን ድል መንሣት የማይቻለውን ኃይልን በማስታጠቅ ድል የሚነሣ አደረገው፡፡

እንዲህ ዐይነትን ተግባር በሥነፍጥረትም ላይ ፈጽሞት እናገኘዋለን፡፡ ፍጥረታትን ሲፈጥራቸው እነርሱኑ መልሶ በሚያጠፋ ነገር ነው ፈጥሮአቸው የምናገኘው፡፡ ለምሳሌ የባሕር ማዕበልን በአሸዋ በመገደብ ለኃይለኛው ማዕበል ደካማ የሆነው አሸዋ ይጠብቀው ዘንድ መሾሙን እናስተውላለን፡፡ ምድርን በውኃ ላይ አጸናት፡፡ ውኃን እጅግ ስስና ቀላል በሆነ ደመና እንዲቁዋጠር አደረገው፡፡ በነቢያትም በኩል በአነስተኛ የእንጨት ቅርፊት ከውኃ ውስጥ ዘቅጦ የነበረውን ብረት አወጣ፡፡ (2ነገሥ.6፥ 5-7) እንዲሁ በመስቀሉ ዓለሙን ወደ እርሱ አቀረበ፡፡ ታላቅ ስለሆነው ኃይልና ጥበብ አታስተውሉምን? እነሆ ከእኛ መረዳት በተቃራኒው በሆነ ኃይል እኛን ወደ እምነት ሲያቀርበን አትመለከቱምን? እንዲሁ መስቀልም ደካማ ሊመስለን ይችላል፤ ነገር ግን በእጅጉ ብርቱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ወደራሱ የሚስብ ኃይል በላዩ እንዳደረበት ማስተዋል እንችላለን፡፡

ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህን ሁሉ በአእምሮ ውስጥ ሲያመላልሳቸው ቆይቶ በመደነቅና በመገረም “ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታል”(ቁጥ.፳፭) አለ፡፡ ከመስቀሉ አንጻር ሞኝነትናና ደካማነትን አስቀመጠ ነገር ግን አማናዊ የሆነውን ሞኝነትንና ደካማነት ሳይሆን የሚመስለውን ነገር ነበር የገለጠልን፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ስለመስቀሉ ኃይል ሲሰብክ በተቃራኒ ጎራ ያሉትን ወገኖች አመለካከታቸውን ሳይጎዳ ነበር የሰበከው፡፡ ፈላስፎች በምክንያት ይህን ኃይል መረዳት እንደማይችሉ ነገር ግን በእነርሱ ዘንድ ሞኝነት የሚመስለው የመስቀሉ ነገር ታላቅ የሆነ ኃይል ያለው መሆኑን ነበር ያስገነዘባቸው፡፡ ስለዚህ ብዙ ወይም ጥቂት ወይም አንድ ተከታይ ያለው ጠቢብ ሰው የት አለ? ፕላቶና ተከታዮቹ እንዴት ያለ አድካሚ በሆነ መንገድ ጥበብን ማግኘት ሻቱ! እነርሱ ለእኛ ስለ መስመር፣ ስለማዕዘን(angle)፣ ስለ ነጥቦች፣ ስለቁጥሮች፣ ተመጣጣኝ ስለሆኑትና ስላልሆኑት ሒሳባዊ ቀመሮች ልክ እንደ ሸረሪት ድር እያወሳሰቡ አስተምረውን ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ ድሮች በዚህ ምድር ስንኖር አያስፈልጉንም ማለታችን ግን አይደለም ሆኖም ከዚህ ከሚልቀው ጋር ሲተያዩ እምብዛም አስፈላጊዎች አይሆኑም፡፡ ፈላስፋው ፕሉቶ ነፍስ ሕያዊት እንደሆነች ለማስረዳት እንዴት ደከመ! ሲወጣም ሲገባም ስለነፍስ ሕያዊነት ትንታኔ ለመስጠት ሞከረ ነገር ግን ስለነፍስ እርግጠኛውን ነገር ለማስተማር አልበቃም፡፡ ይባስ ብሎ በዚህ ጉዳይ ሰሚ አጣ፡፡

ነገር ግን መስቀል ባልተማሩት ሐዋርያት በኩል ብዙ ሰዎችን ወደ እርሱ አቀረበ፡፡ ዓለሙ ሁሉ ተገልብጦ ክርስቶስን ወደ መከተል ተመለሰ፡፡ የተለመዱትን ብቻ አልነበረም ሲያስተምሩ የነበሩት ነገር ግን ስለእግዚአብሔር፣ እውነተኛ ስለሆኑት አንድ ክርስቲያን ሊላበሳቸው ስለሚገቡ መልካም ምግባራት እንዲሁም በወንጌል ሕይወት እንዴት መመላለስ እንዲገባን በተጨማሪም ስለዓለም ምጽአት በሰፊው ሰብከዋል፡፡ በትህምርታቸውም የተከተሏቸውን ሁሉ ፈላስፎች አደረጉዋቸው፤ ያልተማሩትንም በጥበብ ቃል የሚያስተምሩ መምህራን አደረጓቸው፡፡ ወዳጄ ሆይ ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት እንዴት እንደሚልቅ ተመልከት፡፡ ምክንያቱም በዚህ ታላቅ በሆነ በመስቀሉ በተገለጠው ኃይል ዓለሙ ሁሉ ድል ተነሣ፤ ብዙዎች የተሰቀለውን ክርስቶስን እየሰበኩ ብዙዎችን ለእርሱ ማረኩ፡፡ እነዚህ እየሰፉና ዓለምን እየከደኑዋት ሲመጡ በተቃራኒ ጎራ ያሉ ወገኖች ግን እየጫጩና እየጠፉ ሄዱ፡፡ ሕያው የሆነው ቃሉ ከሙታን ጋር ውጊያን ገጠመ ድል ነሣቸውም፡፡

ስለዚህም አንድ ፈላስፋ እኔን ሞኝ ሲል የእርሱን እጅግ የበዛውን ሞኝነቱን ይመለከታል፡፡ ምንም እንኳ እኔ በእርሱ አንደበት ሞኝ ብባልም መረጃዎች ግን የሚያሳዩት እኔ ከእርሱ ይልቅ ጠቢብ መሆኔን ነው፡፡ እርሱ እኔን ደካማ ቢል እንዲህ ባለበት ንግግሩ የእርሱን ደካማነት ይረዳል፡፡ ከዓሣ ማጥመድ የመጡት ሐዋርያት በእግዚአብሔር ጸጋ ለመፈጸም የተቻላቸውን ከአሕዛብ ፈላስፎች፣ ንግግር አዋቂዎችና፣ ገዥዎች ወይም በአጭሩ ዓለም ሁሉ ከዚህ ወደዚያ ብዙ ሺህ ጊዜ ቢታትር በእነርሱ ያደረውን ሀብት በድካማቸው ለማግኘት ቢጥሩ አይደለም ማግኘት ሐዋርያት የስተማሩትን ደግመው መናገር አይቻለውም፡፡ በመስቀሉ ያልተሰበከ ምን ነገር አለ? ስለነፍስ ሕያውነት ፣ ስለሥጋ ትንሣኤ ፣ ስለዚች ዓለም አላፊነት፣ ተስፋ ስለምናደረጋት ሕይወት፣ ሰዎች መላእክነትን ስለመምሰላቸው፣ ራስን ባዶ ስለማድረግ እንዲሁም ሌሎችም ወደ ፍጹምነት የሚያደርሱ አስተምህሮዎች የተላለፉበት በመስቀሉ ነው፡፡….

ከዚህ በላይ እኛ ምን ልንል እንችላለን ? ነገር ግን በተግባር እርስ በእርሳችን ያለንን ድንቅ የሆነ መተሳሳሰብን እናጠንክር ፡፡ የጽድቅም ብርሃን ደምቆ እንዲታይ እናድርግ፡፡ ሐዋርያውም እናንተን ለዓለም የምታበሩ ብርሃናት ናችሁ ይላችኋል(ፊልጵ.፪፥፲፭)፡፡ መንፈሳዊው ተግባር ከዓለማዊው ተግባር እንደመላቁ እግዚአብሔር አምላክ ከፀሐይም ከሰማይም ከውቅያኖስም በላይ ታላቅ ሥራን ለዚህች ምድር እንድንፈጽም ሓላፊነትን ሰጥቶናል፡፡ እኛ በሰማይ ላይ የምታበራውን ፀሐይንና ክበቡዋን አይተን እናደንቃለን፡፡ ይልቁኑ ከእርሱዋ በእጅጉ የሚልቀው ብርሃን በእኛ ውስጥ እንዳለ እናስተውል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን እኛ ይህን ብርሃን ካልሠራንበት የዚህ ብርሃን ተቃራኒ የሆነ ድቅድቅ ጨለማ እንደሚነግሥብንም ልብ እንበል፡፡ ጽኑ የሆነው ጨለማ ዓለምን ሲውጣት ዓለም በጭንቅ ውስጥ ትሆናለች፡፡ በእኛ ውስጥ ድቅድቅ ጨለማ ሰፍኖ ሲገኝ ነፍሳችን በጭንቅ ትያዛለች፡፡ ጨለማው በከሃዲያን ወይም በአሕዛብ ላይ ብቻ ያለ አይደለ ነገር ግን በእኛም መካከል ባሉት ክርስቲያናዊ እውቀቱና ሕይወቱ በሌላቸው ላይ ነግሦም ይታያል፡፡

 

ከመካከላችን አንዳንዶች ትንሣኤውን አይቀበሉም፣ አንዳንዶች ደግሞ በጥንቆላና በኮከብ ቆጣሪዎች የሚታመኑ እነርሱ ባሉዋቸውም የሚመሩ ወገኖች ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከክፉ ይጠብቀናል ሲሉና አጋንንትንም እንስብበታለን በማለት አሸን ክታቦችን በአንገታቸው ላይ የሚያንጠለጠሉ ናቸው፡፡

ስለዚህም ጉዳይ ጦምን እንያዝ በውጊያውም ረዳት ሁኑኝ፡፡ በእናንተ ክርስቲያናዊ ምልልስ እነርሱን ወደዚህ ወደተቀደሰ ሕይወት ማምጣት ይቻላልና፡፡ እኔ ሁልጊዜ እንደማስተምረው አንድ ሰው ክርስቲያናዊ ስብዕናን አስመልክቶ ሌሎችን ከማስተማሩ አስቀድሞ ራሱን ሊያስተምር ይገባዋል እላለሁ፡፡ እርሱን የሚሰሙት ከቅድስና ሕይወት ወጥተው እንዳይመላለሱ አርዓያ ሊሆናቸው ይገባል፡፡ በዚህም መልክ በመመላለሰ አሕዛብ ስለእኛ በጎ የሆነ አመለካከት እንዲኖራቸው እናድርግ፡፡ ወንጌልን በሕይወታችን ለእነርሱ በመስበካችን ከእነርሱ የምንቀበለው መከራ ይኖራል ነገር ግን አላፊ ነው፡፡

ይህን በሕፃናት አታስተውሉትምን፡፡ አንዳንዴ ልጆች በአባታቸው እቅፍ ሳሉ በቁጣ የአባታቸውን ጉንጭ በጥፊ ሊመቱት ይችላሉ፤ ነገር ግን አባት ልጁ ቁጣውን በእርሱ ላይ በመግለጡ በልጁ አይቆጣም ይልቅኑስ በእርሱ ዘንድ እጅግ ጣፋጭ ይሆንለታል፡፡ ቁጣው ከልጁ ላይ ባለፈ ጊዜ ደግሞ አባት ይበልጥ ደስ ይለዋል፡፡ እንዲሁ እኛም ለኢአማንያን እናድርግ ልክ ልጅ እንዳለው አባት እንሁን፡፡ ይህን እንደስንቅ ይዘን ለእነርሱ የክርስቶስን ወንጌል እንስበክላቸው፡፡ ሁሉም አሕዛብ በእኛ ዘንድ እንደ ሕፃናት ናቸውና፡፡ እንዲህም እንደሆነ የእነርሱ አንዳንድ ጸሐፍት “ይህ ሕዝብ እንደ ሕፃን ነው ከአሕዛብም አንድም አረጋዊ ሰው የለም” ብለው ቃላችንን ያረጋግጡልናል፡፡ ሕፃናት የሚጠቅማቸውን ነገር ሊለዩ አይችሉም፤ አሕዛብን ሁል ጊዜ እንደ ሕፃናት ጨዋታ ወዳዶች ናቸው፡፡ በአፈር ላይ ይንደባለላሉ በከንቱ ነገር በቀላሉ ይወሰዳሉ ከንቱ በሆነም ነገር በፍቅር ይወድቃሉ፡፡ ለሕፃናት የሚጠቅም ነገርን ስንነግራቸው ጆሮ ሰጥተው አያዳምጡንም ከዚህ ይልቅ እኛ ስንናገር እነርሱ ይስቃሉ፡፡ አሕዛብም እንዲሁ ናቸው፡፡ እኛ ስለመንግሥተ ሰማያት ስንሰብክላቸው እነርሱ ይስቃሉ፡፡ ከሕፃናት አፍ በብዛት የሚወርደው ለሃጭ ምግቡ ላይ ሲያርፍ ምግቡን እንዲያበላሸው እንዲሁ ከአሕዛብ አንደበት የሚወጡ ቃላት ከንቱዎችና የረከሱ ናቸው፡፡

ለሕፃናት የሚስፈልጋቸውን ምግብ እንኳ ብንሰጣቸው ክፉ የሆነ ቃላት ከአንደበታቸው እያወጡ ሊነጫነጩብን ይችላሉ እኛም እነርሱን በመታገሥ እናሳልፋቸዋለን፡፡ ሕፃናት አንድ ሌባ ወደቤታቸው ገብቶ የቤቱ ቁሳቁሶችን እየወሰደ ቢያዩት ዝም ብለው ከመመልከትና እንደ ተባባሪ ወገን ሆነው ሲስቁ ከመገኘት ባለፈ እርሱን አይቃወሙትም፡፡ ነገር ግን እነርሱ ከሚጫወቱበት እቃ አንዱ የተወሰደባቸው እንደሆነ የወሰደባቸው ሰው ለመጉዳት ሲጥሩ ሲያለቅሱና በንዴት መሬቱን ሲጠበጥቡት እናስተውላቸዋለን፡፡ አሕዛብም እንዲሁ ናቸው፡፡ ሰይጣን ነፍሳቸውን የሚጠቅመውን መንፈሳዊ ሀብት ሲዘርፋቸው ከዚህም አልፎ ለሕይወታቸው አስፈላጊ የሆነውን ሲያሳጣቸው እያዩ ይስቃሉ፡፡ እንዳውም ከእርሱ ጋር እንደ ጓደኛ ሲተባበሩት ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ከእነርሱ እንደ ሕፃን መጫወቻ የተናቀን እቃን ሲወስድባቸው ቢመለከቱ ልክ እንደ ሕፃን ይጮኻሉ ያነባሉ፡፡ ሕፃናት ራቁታቸውን ስለመሆናቸው እንደማያስተውሉ አሕዛብም እንዲሁ ናቸው፡፡ ስለዚህም ሕጋዊው ተራክቦው እነርሱን ሲያሳፍራቸው ሕገወጡ መዳራት ግን አያሳፍራቸውም፡፡

እናንተ በዚህ ትምህርቴ ልትረኩና ደስታችሁን በእልልታ ልትገልጡልኝ ትችሉ ይሆናል ነገር ግን ከደስታችሁ ጋር በእነርሱ ተግባር ተስባችሁ እንዳትወሰዱ ለራሳችሁ ጥንቃቄን እንድታደርጉ ልመክራችሁ እወዳለሁ፡፡ ስለዚህም አዋቂዎች ትሆኑ ዘንድ እለምናችኋለሁ፡፡ እኛ እንደ እነርሱ ሕፃናት ከሆንን እንዴት አዋቂዎች እንዲሆኑ እነርሱን ማስተማር ይቻለናል? እንዴትስ እነርሱን ሞኝነት ከሆነው ከሕፃናዊ ድርጊታቸው መመለስ እንችላለን? ስለዚህ ተዋዳጆች ሆይ ወደ ክርስቶስ የእውቀቱ ከፍታ እንድንደርስና የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን እራሳችንን አዋቂዎች እናድርግ፡፡ ሰው እንሁን፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየስሱ ክርስቶስ ፍቅርና ርኅራኄ ለእግዚአብሔርና መንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

 

 

ዘመነ ጽጌ

ስሞት እጸልይላችኋለሁ

በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ

“ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ!”2ኛ ጴጥ.1÷13-15

ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በመጣበት ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መሥርቶአል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያቱን “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ መልሶ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ “አንተ ዓለት ነህ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፤ የሲኦልም ደጆች ሊያናውጿት አይችሉም፡፡” በማለት ቤተ ክርስቲያንን በሐዋርያት መሠረት ላይ መሠረተ/ማቴ.16÷16-18/፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በአምሳ አምስት ዓመቱ ወደ ሐዋርያት የተጠራ፣ በሁሉም ስፍራ በሐዋርያት ስም ዝርዝርም፣ መልስ በመስጠትም፣ በመካድም፣ ንስሓ በመግባትም ፈጣን እንደነበር ቅድመ ትንሣኤ ክርስቶስ የተጻፈው ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ከትንሣኤ በኋላ ሦስት ጊዜ ክዶት መጸጸቱን የተመለከተለት ጌታ አንዳች የሚቆጠቁጥ የወቀሳ ቃል ሳይኖረው በጭቃ ላይ የወደቀ ዕንቁን ወልውለው ወደ ቦታው አንደሚያስቀምጡት ወደ ክብር ስፍራው መለሰው፡፡ አልፎ ተርፎም ለምሕረቱ ወሰን የሌለው አምላክ ይህን ሐዋርያ “ ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ” ብሎ ምእመናንን ከሕፃናት እስከ አረጋውያን አደራ ሰጠው /ዮሐ.21÷15-17/፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በተቀበለበት ዕለት በአንድ ቀን ሦስት ሺህ ነፍሳትን በትምህርቱ ማርኮ “ምን እናድርግ?” በማሰኘት ጠብቅ አሰማራ የተባለውን መንጋ ወደ በረቱ ማስገባት ጀመረ፡፡ /ሐዋ.2÷31/ በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ምእመናንን በአፍም በመጽሐፍም ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ በኋላም ጠብቃቸውና አሠማራቸው የተባለውን ግልገሎች፣ ጠቦቶችና በጎች ሲጠብቅና ሲያሠማራ ከተኩላ ታግሎ ነፍሱን ሰጠ፡፡ የእረኝነት ሥራውን ሊፈጽም ቁልቁል ተሰቅሎ “የእረኞች አለቃ” /1ኛጴጥ.5÷4/ ብሎ በመልእክቱ የጠራውን የጌታውን ፈቃድ ፈጸመ፡፡

ይህ ሐዋርያ በመልእክታቱ ምእመናንን ሲገሥጽና ሲመክር ሲያስተምር የኖረ ሲሆን በሁለተኛይቱ መልእክቱ ላይ ግን ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነ ኃይለ ቃልን ጽፏል፡፡ “ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ብትጸኑ ስለ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም፡፡ ሁል ጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና፡፡ ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ” /2ኛጴጥ. 1÷13-15/

ብታውቁም፤ ብተጸኑም ማሳሰቤን ቸል አልልም!

ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክታቱ ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትና ስለ ሰው ልጅ ብሎ ስለተቀበለው መከራ፣ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው ስለሚገባ መንፈሳዊ አኗኗር፣ አለባበስ፣ ስለ ጋብቻና ቤተሰባዊ ጉዳዮች፣ በምእመናን ላይ ስለሚመጡ መከራዎችና የዲያብሎስ ውጊያዎች፣ ድል ሲያደርጉም ስለሚያገኙት ጸጋና ዋጋ፣ ስለሚደርሱበት መዓርግ በአጠቃላይ በቀላሉ ተዘርዝሮ የማያልቅ ሰፊ ትምህርትን በመልእክቱ አስተምሯል፡፡ ይሁንና ሐዋርያው አውቀውታል፣ ጸንተዋል ብሎ ማሳሰቡን አላቆመም፡፡ ሰው ከመንገድ የሚስተው በእውቀት ጉድለት ብቻ አይደለም፡፡ እያወቁ መሳት፣ ጸናሁ ሲሉም መጥፋት አለ፡፡ ስለዚህም “አሳስባችሁ ዘንድ ቸል አልልም፡፡” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መንጋውን ጠብቅና አሰማራ የተባውን አደራ የማይረሳ፣ በጥበቃ ተሰላችቶ ቸል የማይል፣ ትናንት የበሉት የጠጡት ይበቃቸዋል የማይል በመሆኑ ያውቁታል ብሎ ከመናገር ሳይቆጠብ “ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም፡፡” አለ፡፡

በዚህ ማደሪያ ሳለሁ!

ሥጋ የነፍስ ማደሪያ ናት፤ አዳሪዋ ነፍስ ከማደሪያዋ ሥጋ ስተለይ ሰው ያን ጊዜ ሞተ ይባላል፡፡ “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ ነው” እንዲል /ያዕ.2÷26/ ጻድቁ ኢዮብም “ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ÷ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ፡፡” ኢዮ.19÷26/ ያለው ሥጋ ጊዜያዊ ማደሪያ መሆኑን ሲያስረዳና ራሱን ከነፍስ አንጻር አድርጎ በሞት ሥጋውን ጥሎ እንደሚሄድ ሲናገር ነበር፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ ማደሪያዬ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ ይገባኛል፡፡” ሲል በሥጋዬ ሳለሁ፣ ነፍሴ ሳትወሰድ ማለቱ ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ቀሪ ዕድሜውን በችኮላ የሚጠቀመው ለሌላ ሥጋዊ ተርታ ጉዳዮች ሳይሆን ምእመናን ያስተማረውን ትምህርት እንዳይገድፍና አንዳይጠፉበት በማሳሰብ ማንቃት ነው፡፡

ጌታዬ እንዳመለከተኝ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁ!

“በእግዚአብሔር ፊት የቅዱሳኑ ሞት የከበረ” ስለሆነ ሞት ለቅዱሳን ድንገተኛና ያልተጠበቀ አይሆንባቸውም፡፡ እርግጥ ነው ሰው ሁሉ ሟች እንደ ሆኑና የሞትን አይቀሬነት በመጥቀስ ሁሉም ሰው እንደሚሞት ያውቃል ሊባል ይችላል፡፡ ቅዱሳን ግን የሚሞቱ መሆናቸውን የሚያውቁት ሞት አይቀርም ብለው ሳይሆን የሚሞቱበትን ጊዜና ሁኔታ ለመረጣቸው ለባሪያዎቹ የሚያደርገውን የማይሠውር እግዚአብሔር ገልጣላቸው ነው፡፡ የሚከተሉት የሊቀ ነቢያት ሙሴንና የቅዱስ ጳውሎስን ንግግሮች እንመልከት፡-

“እኔ ግን በዚህች ምድር እሞታለሁ ዮርዳኖስንም አልሻገርም” /ዘዳ.4÷22/

“በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና የምሄድበትም ጊዜ ደርሷል” /2ኛጢሞ.4÷6/

እነዚህ ታላላቅ ቅዱሳን የሚሞቱ መሆናቸቸውን ብቻ ሳይሆን የሚሞቱበትን ቦታ ጊዜ አስቀድመው መናገራቸው ከእግዚአብሔር ስለተነገራቸው ነው፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችንን እና የቅዱሳት እናቶቻችንን ገድላት ስንመረምር ቅዱሳን ዕለተ እረፍታቸው ቀድሞ በእግዚአብሔር እንደሚነገራቸው እንረዳለን፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ሰው እንደመሆኑ “መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ” ብሎ ጌታ ለሁሉ ካመለከተው ጥሪ በተጨማሪ ከቅዱሳን አንዱ እንደመሆኑ ከመሞቱ በፊት እንደሚሞት ያውቅ ነበር፡፡ ጌታችን ከዕርገቱ በፊትና ከዕርገቱ በኋላ ሁለት ጊዜ ተገልጦ ስለሞቱ ነግሮታል፡፡

ከዕርገቱ በፊት ከላይ የጠቀስነውን የእረኝነት አደራ ከሰጠው በኋላ “እውነት እውነት እልሃለሁ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል፡፡” ብሎታል፡፡ ወንጌልን ጽፎ በብዙ ቦታዎች የጻፈውን ሲተረጉምና ሲያትት የምናገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ትርጓሜን ሳንሻ ንባቡ ላይ “በምን ዓይነት ሞት  እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ፡፡” ብሎ የጌታን ንግግር ትርጓሜ አስከትሎ ጽፎልናል፡፡

በእርግጥም ቅዱስ ጴጥሮስ በሸመገለ ጊዜ እጆቹን በተዘቀዘቀ መስቀል ላይ ዘርግቶ ቁልቁል መሰቀል ትንቢተ ክርስቶስን ፈጽሟል፡፡

ጌታችን ከዐረገ በኋላ ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሲያስተምር “ልበ ንጹሖች ብጹዓን ናቸው፡፡” ብሎ ባስተማረው ትምህርት ሚስቶቻችንን አሸፈተብን ያሉ ሰዎች ተነሡበት፡፡ በዚህን ወቅት ሴቶቹ ተማክረው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲሸሽ ነገሩት ከከተማይቱ ወጥቶ ሊሄድ ሲል ጌታችን ተገልጦ ታየው “ጌታ ሆይ ወዴት ትሄደለህ” ቢለው “ዳግም በሮም ልሰቀል” በማለት ነገረው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ልቡ ተነክቶ ወደ ሮም ተመለሰና የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ፡፡ “ጌታችን እንዳመለከተኝ” ያለው ይህን ነበር፡፡

ከመውጣቴም በኋላ አንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ!

ከላይ የተመለከትናቸው ሃሳቦች ቅዱስ ጴጥሮስ ጊዜ ሞቱ እንደቀረበ አውቆ መናገሩን እና ምእመናን የተማሩትን በማሳሰብ ሲያነቃቸው እንደነበር የሚያስረዱ ናቸው፡፡ እስካሁን የተመለከትናቸው የሚያወሱት ይህ ሐዋርያት በሕይወት ሳለ ስለሚያደርጋቸው ነገር ነበር፡፡ በመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ግን “ከመውጣቴ በኋላ የሚል ሐረግ እናገኛለን፡፡ “ከመውጣቴ በኋላ” ሲል ምን ማለቱ ነው?

ቀደም ባሉት ዐረፍተ ነገሮች እንደሚሞትና ይህንንም ጌታችን እንዳመለከተው ተናግሮ ነበር፡፡ ስለዚህ መውጣቴ ያለው ሞቱን እንደ ሆነ እሙን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ሞት መውጣት ተብሎ ሲነገር የቅዱስ ጴጥሮስ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ በታቦር ተራራ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ስለመነጋገሩ በተጻፈበት ስፍራ “በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር” ይላል፡፡ በኢየሩሳሌም የተፈጸመው መውጣቱ ደግሞ ሞቱ ነው፡፡ /ሉቃ.9÷31/ ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስ ባስተማርኳችሁ እንድትጸኑ “ከሞትኩም በኋላ እተጋለሁ!” እያለ ነው፡፡ “ከሞትኩ በኋላ” የሚለውን እናቆየውና “እተጋለሁ!” የሚለውን ቃል በጥቂቱ እናብራራው፡፡

ትጋት ምንድርን ነው? ትጋት አንድ ነገር ያለማቋረጥ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ ያለመታከት ማድረግ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ታካች ሰው ምንም አደን አያድንም፤ የሰው የከበረ ሀብቱ ትጋት ነው” በማለት ትጋት የታካችነት ተቃራኒ መሆኑንና ጥቅሙን ተናግሯል /ምሳ.12÷27/፡፡ ጌታችን በምሴተ ሐሙስ ቅዱሳን ሐዋርያቱን “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳን ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ብሎ ገሥጿቸው ነበር /ማቴ.26÷30/፡፡ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ግን ሐዋርያት ትጉሐን ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ መሰከረላቸው “ወደዚህም ወደ ተሰፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው” /ሐዋ.26÷7/ በዚህ ሁሉ ትጋት አለመታከት፣ አንድን ነገር ሌሊትና ቀን ማድረግ መሆኑን ተረዳን፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ “ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ” ሲል የሚተጋው በምንድርን ነው? እየዞረ በማስተማር ይሆን? ይህማ ቢሆን ከመሄዴ በፊት  ላሳስባችሁ ባላለን ነበር፡፡ ደግሞም ማስተማሩን በሚገባ ፈጽሞ በሰማዕትነት አርፏል፡፡ ታዲያ ከሞተ ወዲያ የሚተጋው ምን በማድረግ ነው? የትስ ነው የሚተጋው? መቼስ በመቃብር ያለሥጋው ሊተጋ አይችልም፡፡ “የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትህን ይናገራሉን?” ብሏል ቅዱስ ዳዊት /መዝ.87÷15/ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስም “ከማደሪያዬ እለያለሁ፡፡ ብሎ ከሞተ ወዲያ እኔ የሚላት ነፍሱን እንደሆነ አስረድቶናል፡፡ ታዲያ በነፍሱ በሰማይ ምን እያደረገ ይሆን የሚተጋው? መቼስ በሰማይ እርሻ ቁፋሮ፣ ጽሕፈት፣ ድጒሰት የለም፡፡ ሐዋርያው በምን ይሆን የሚተጋው? በጸሎት ነዋ!

ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስ “እንደተማራችሁት መኖርን እንዳትዘነጉ በየጊዜው /አንድ ጊዜ ብናስብ አንድ ጊዜ መዘንጋት አለና/ ትችሉ ዘንድ ከሞትኩም በኋላ ያለማቋረጥ ያለመሰልቸት ስለ እናንተ በመጸለይ እተጋለሁ! ማስተማርና መልእክትን ጽፎ መተው ብቻ ሳይሆን በተማራችሁት መገኘት እንድትችሉ በአጸደ ነፍስም ብሆን እለምናለሁ፣ እማልዳለሁ! እያለ ነው፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ዓለትነት የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ስለእርሷ የተጻፋላት፣ በደሙ የዋጃት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሷ ነው፡፡ እርሱ በሁሉ የሞላ ሲሆን “ሁሉን በሁሉ ለሚሞላ ለእርሱ ሙላቱ የሆነች” አካሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት /ኤፌ.1÷22/፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ስትሆን ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራሷ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የሰውነት አካል ክፍሎች ነን፡፡ “እንግዲህ እናንተ የክርስቶስ አካሉ ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁ የአካሉ ክፍሎች ናችሁ፡፡” ተብለናል /1ኛቆሮ.12÷27/፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሕይወትን የሚሰጡ ጥምቀትን፣ ንስሐን፣ ቊርባንን የመሳሰሉ ምስጢራትን በመፈጸም ራሳችን ከሆነው ከመድኃኔዓለም ጋር አንድ እንሆናለን፡፡

ክርስቲያኖች ሲሞቱ ከዚህ ኅብረት ይነጠላሉ ማለት አይደለም፡፡ ራሷ ክርስቶስ በሰማይም በምድርም ስላለ ቤተ ክርስቲያንም በምድርም በሰማይም አለች፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ ወደ ሰማያዊቱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል፡፡ የሰማይዋ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ድል በነሱ ቅዱሳን የተሞላች ፍጹም መንፈሳዊ የሆነ ሥርዓት ያለባት፣ ሥጋዊ ደማዊ አሳብ የማይሰለጥንባት ናት፡፡ ከእኛ ተለይተው ወደዚያ ኅብረት የተደመሩ ወገኖቻችን በላይ ያሉ የክርስቶስ አካላት ናቸው፡፡ ከእኛ በምድር ካለነው የክርስቶስ አካላት ጋር አንድነታቸው አይቋረጥም፡፡ የክርስቶስ አካል አይከፈልማ! ስለዚህ በሰማይ ካሉት ድል የነሡ ቅዱሳን ጋር እኛ ደካሞቹ በጸሎት እንገናኛለን፡፡

“ዐይን እጅን አልፈልግሽም ልትላት አትችልም፤ ደካሞች የሚመስሉህ የአካል ክፍሎች ይልቁንም የሚያስፈልጉህ ናቸው፡፡ ተብሎ እንደተነገረ እኛ ኃጢአተኞቹ የቤተ ክርስቲያን የአካል ክፍሎች ብንሆንም ቅዱሳኑ ስለ እኛ ይጸልያሉ /1ቆሮ.12÷21/፡፡ ምክንያቱም ደካማ ብንሆንም ለቅዱሳን እናስፈልጋቸዋለን፡፡ ቅዱሳን ኃጥአንን ካልወደዱ ቅድስናቸውን ያጣሉ፡፡ እኛን ካልወደዱ “እኔ ክርስቶስን እንደመሰልሁ እናንተም እኔን ምሰሉ” “አሁን እኔ ሕያው ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፡፡” ብለው ለመናገር እንደምን ይችላሉ? /ገላ.2÷20/  

እኛ በሥጋ ድሆች የሆኑ ነዳያንን በመመጽወት እንደምንከብር ቅዱሳንም በነፍስ ድሆች የሆንን እኛን በአማላጅነት ጸሎታቸው እየመጸወቱ ይከብራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉን ነው፡፡” ይላልና በምግባር ድሆች ለሆንን ለእኛ መራራት የቅዱሳን ግብር ነው፡፡ “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል” ተብሎ እንደተነገረላቸው ቅዱሳን ክቡር ሆነን ሳለን ለማናውቅ እንደሚጠፉ እንስሶች ለመሰልን ለእኛ ለኃጢአተኞች ይራራሉ፤ ይማልዱማል /ምሳ.12÷10፣ 14÷21/፡፡

ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋ እያሉ መከራን ታግሠው ስለ ሌሎች በደል ይለምናሉ፡፡ ሳይበድሉ ራሳቸውን በኃጢአትኛው ቦታ አርገው፣ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ሆነው ይማልዳሉ፡፡ ታዲያ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለይታ “ሲሄዱና ከክርስቶስ ጋር ሲኖሩ” /ፊል.1÷23/ ምንኛ ይለምኑ ይሆን?

በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሕይወተ ሥጋ ለሌሉና ወደ ሰማዩ ኅብረት ለሄዱ ምእመናን ጸሎተ ፍትሐትን፣ መታሰቢያን በማድረግ፤ ለዚያ የሚያበቃ ቅድስና ያላቸውን ደግሞ በዓላቸውን በማክበር ታስባቸዋለች /2ጢሞ.1÷17-18/፡፡ በሰማይ ያሉት ቅዱሳን ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው ስለ እኛ ይተጋሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን መከራና የምእመናንን ስቃይም በዝምታ አይመለከቱም፡፡ በዙፋኑ ፊት ቆመው “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ስለ ደማችንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” እያሉ ያማልዳሉ፡፡ /ራእ.6÷10/ የቅዱስ ጴጥሮስ በረከቱ አይለየን! አሜን፡፡

/ምንጭ፡ ሐመር  ሐምሌ 2002 ዓ.ም./

ክርስቶስን መስበክ እንዴት?

ሚያዚያ 25፣ 2003ዓ.ም

/ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ሚያዝያ 2003ዓ.ም/

ፕሮቴስታንቶችና ፕሮቴስታንታዊ መንገድ የሚከተሉ አንዳንዶች  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን አልሰበከችም የሚል ክርክር ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ዝግጅት ክፍላችን ጥያቄያቸውን ለመመለስ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን በምላሹ እንዲሳተፉበት ጋብዘናል፡፡ ለዚህ እትም የያዝነውን እነሆ!

ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ“ቤተክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ወንጌል ነው”

ቤተክርስቲያን ወንጌልን ስትሰብክ ሁለት ሺሕ ዓመታት አልፏታል። ይህንንም ሊቃውንቱ ምእመናንም ያስረዱትና የተረዱት ነው። ወንጌል ካልተሰበከ ክርስቲያኖች እንዴት ለአሁን ዘመን ደረሱ? ወንጌል መሠረት፣ በጎ እርሾ ሳይሆነው፣ ወንጌል ብርታት ሳይሆነው ይህን ሁሉ ዘመናት አቆራርጦ፣ ድልድዩን አልፎ እንዴት እዚህ ደረሰ? ወንጌል ቤተ ክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ነው፡፡

 

በቤተክርስቲያን ሊቃውንቱ የሚያነቧቸው፣ የሚተረጉሟቸው፣ ምእምናን የሚሰሟቸው፣ የሚታነጹባቸው ድርሳናት፣ ተአምራት ወንጌል ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት ወንጌልን የሚፈቱ፣ የሚተረጉሙ፣ የሚያመሰጥሩ ናቸው። ከዚህ ውጭ የሆኑ መጻሕፍት በቤተክርስቲያን አይነበብም፣ አይተረጎምም፣ አይሰማም። ቤተክርስቲያን ወንጌልን የምትሰብከው በቃል፣ በመጽሐፍ ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው። ጥምቀት ወንጌል ነው። ቤተክርስቲያንም ጥምቀት የዘወትር ሥራዋ ነው። ወንጌል ስለ ጥምቀት ነው የሚነግረን። የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙም በየዕለቱ ይቀርባል፤ ይህ ወንጌል ነው። ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን የተቀደሰውን ጋብቻቸውን በተቀደሰው ቦታ፣ በተቀደሰው ጸሎት በምስጢረ ተክሊል ይፈጽማሉ። ይህም ወንጌል ነው። እናቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን ከዚህ ዓለም ሲሸኙ በሥርዐተ ፍትሐት፤ ብሉያትና ሐዲሳት እየተነበቡ፣ ያሬዳዊ ዜማ እየተዜመ ነው። ይህ ወንጌል ነው። አላዛርን ከመቃብር ተነሥ እንዳለው፤ የታሰረበትን ፍቱት እንደተባለ እንደተ ፈታ ሁሉ፤ ካህናትም ከኃጢአት እስራት እየፈቱ ሕዝባቸውን መሸኘት፤ “አቤቱ እግዚኦ ይቅር በለው ሲያውቅ፣ ሳያውቅ በሠራው ኃጢአት ይቅር በለው” እያሉ መሸኘት ወንጌል ነው።

ቤተክርስቲያን ራሷም፣ እግሯም፣ መሠረቷም፣ ጉልላቷም ወንጌል ነው። ይህን በቅንነት፣ በበጎ ነገር፣ በምስጢር፣ በትርጓሜ ለሚያዩት ነው። በጥላቻ ካዩት ነጩም ጥቁር ነው፤ ብርሃኑ ጨለማ ነው፤ በጥላቻ ማየትና በፍቅር ማየት፤ በሐሰት መናገርና በእውነት መናገር መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። የቤተክርስቲያን ጥንተ ጠላቶች ለቤተክርስቲያን በጎ ይመሰክራሉ ብለን ከጠበቅን የተሳሳትን ይመስለኛል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን “እግዚአብሔር ከእናንተ  ምስክርነትን አይፈልግም” ነው ያላቸው። ጸሐፍት ፈሪሳውያን ስለ ክርስቶስ በጎ ስለማይመሰክሩ ስለማይናገሩ ነው። ምክንያቱም በጭፍን፣ በቅናት፣ ስለጠሉት ነው። ቤተክርስቲያንም ከጠላቶቿ የእውነት ምስክርነትን አትጠብቅም፤ በበጎ ለሚያዩአት ግን ምስክርነቱ በእጅ የሚጨበጥ (የሚዳሰስ) በዐይነ የሚታይ ነው።

ቤተክርስቲያን ወንጌል ያልሰበከችበት ዘመንም፣ ጊዜም የለም። ወንጌል አልተሰበከም ለሚሉ ሰዎች ትናንት አለነበሩም፣ ዛሬም የሉም። ለነገሩስ የት ሆነው ያዩታል? ቢኖሩም አይገባቸውም፤ ውስጣቸውም በብዙ ችግር የተተበተበ፤ በቅራኔ የተሞላ ነው። በቅራኔ የተሞላ ደግሞ ከውጭ የሚነገረውን በጎ ነገር ለመቀበል ዝግጁ አይደለም።

 

ሊቀ ትጉኀን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜ“ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው”

ሰው በተሰጠው የፈቃድ ነጻነት መሠረት የፈለገውን የመናገር መብት አለው። ፍሬ ነገሩ እውነቱ የቱ ነው? ሐሰቱስ? የሚ ለው ነው። ዲያብሎስ ስለ ቅዱስ ሚካኤል የብርሃን መላክነት አይመስክርም፤ ሊመሰክርም አይችልም። «ሚካኤል ደካማ ነው» እያለ የፈለገውን መናገር ይችላል። የዲያብሎስን ምስክርነትም ሚካኤል አይፈልገውም፣ አይቀበለውምም። ዲያበሎስ የፈለገውን ቢናገር ሚካኤልን አይከፋውም፤ ከጠላቱ ቡራኬ ስለማይጠብቅ። እንደዚሁ ሁሉ የእኛም ቤተክርስቲያን የሌሎችን ቤተእምነቶች ምስክርነትም ሆነ ክስ አታደንቀውም፤ አትደነግጥበትምም የእኛ ቤተክርስቲያን ጨርቅ ሰጥታ ጉቦ ሰጥታ እንዳልተስፋፋች ሁሉም ያውቁታል፤ ታዲያ ወንጌልና ክርስቶስን ሳትሰብክ ቤተክርስቲያን ሆና ሁለት ሺሕ ዓመታትን እንዴት ተሻገረች? አሸናፊ ስለሆነች በእውነቷ ብቻ ቆማ የምትኖር ናት። ጉቦ አይከፈልባትም፣ ማባበያም አትጠይቅም።

 

ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ልብን አሻክሮ ምላስን አለዝቦ በማነብነብ አይደለም፤ በድርጊት በማሳየትም እንጂ። በአንድ ታላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓል በአንድ ቤተክርስቲያን በአንድ ቀን ብቻ የምናደርገው ስብሐተ እግዚአብሔር፤ ስብከቱ፣ ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ዋዜማው በተግባርም ታቦት ይዘን ቆመን ያስተላለፍነው ትምህርት በጠቅላላው መናፈቃኑ ለአንድ ዓመት ከጮኹበት፣ ብዙ ነገር ካወጡበት «አገልግሎት» እጅግ ብልጫ አለው። የዚህ አጠቃላይ አገልግሎታችን ዋነኛ ማእከልም ወንጌልና የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ድኅነት ነው፡፡ ንዋያተ ቅድሳቶቻችን በሙሉ ስብከቶች ናቸው። በቅዳሴ ላይ ቄሱ፣ ዲያቆኑ መስቀል ይዞ የሚዞረው ምን  ለማሳየት ነው? ቀሳውስት ዕጣን እያጠኑ “ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ” እያሉ ሲያመሰግኑ ምስጢረ ሥላሴ እና ምስጢረ ሥጋዌን መስበከ፣ ማስተማራቸው ነው። ልብሰ ተክህኖዎቹ ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ንዋያተ ቅድሳቱ ሁሉ መስቀል የሚደረግበት ለጌጥ አይደለም። ይህ ስብከት አይደለም እንዴ? መቅደስ ውስጥ ስንቀድስ በአራቱ ማእዘን የምንቆመው ጽርሃ አርያምን እያሳየን ነው። እነርሱ የማያስተውሉትን ሰባቱ ሰማያትን አምጥተን መቅደሱ ላይ ቁጭ አድርገን የምናሳያቸው ለስብከት ነው። ኪሩቤል እንዴት አድርገው ጌታን እንደተሸከሙት ታቦቱን መንበሩ ላይ አስቀምጠን ስንቀደስ እናሳያለን። በተጨባጭ እያሳየን እያሰተማርን ነው።

 

ደስ ሊለን ይገባል፤ ለሁለት ሺሕ ዘመን ወንጌል ሳይነበብባት በተለያየም መንገድ ሳይሰበክባት የማትውል የማታድር እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እንደ ቤተክርስቲያንም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነች። ቢያንስ በቅዳሴ ላይ ሰባኪ ያልቆመባቸው፣ ወንጌል ያልተሰማባቸው፣ ሃይማኖት አበው የማይነበብባቸው ገዳማትና አብያተክርስቲያናት የሉም። ስለዚህ ስብከት መንዘፍዘፍና ዓላማ የሌለው ጩኸት አይደለም። በእርጋታ፣ በማስተዋል፣ በጥንቃቄ የሚፈጸም በብዙ ዓይነት መንገድ የሚከናወን፤ ያልነበሩትን የምናመጣበት የነበሩትን የምናጸናበት አገልግሎት መሆኑን ሁሉም ይረዳ።

?

በዲ/ን እሸቱ

ሚያዝያ 26፣2003ዓ.ም

ሰው ማነው?ሰው ማነው? ብሎ ለጠየቀ “ሰው ንግግሩን ይመስላል” እንዳትለኝ ንግግሩ እምነቱን የሚያመለክት ዕውቀት አይሆነውምና ነው፡፡ ለሰው ባሕርያዊ ተፈጥሮና ዕውቀት ምስክሩ ውስጣዊ የአዕምሮ አቋምና የሕሊና ሕግ ነው ብለንም አንደመድምም፡፡ ሰው እንዲያውቅ የተመደበለት የሕግ ተፈጥሮ ዕውቀት መጀመሪያ ክፍል መልካምን ማወቅ፡፡ ሁለተኛ ክፋትን ንቆ መልካምን ገንዘብ ማድረግ፡፡ ሦስተኛ መልካምን በግብር መግለጽ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቱያን ሊቃውንት ይሁዳን ሲገልጹ “በአፍ አምኖ በልቡ የካደ” ይሉታል፡፡ ባህላችን “አፈ ቅቤ፤ ሆደ ጩቤ” እንዲል፡፡

 

የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሠረት ያለ ትምህረት በተፈጥሮ የሚሰጥ ሲሆን ይህም ሕገ ልቦና፤ ሕገ ህሊና፤ ሕገ ተፈጥሮ ወይንም ሕገ ጠብዓያዊ በመባል ይታወቃል፡፡ ሕገ ኦሪትና ሕገ ወንጌል፤ ሕገ ሕሊናን ይተረጉማሉ፡፡ ለአብነት ብንጠቅስ አዳምና ሔዋን ቅዱስ ዳዊትና ይሁዳን፤ ከመጸጸት ክፉዎችን ከማዘን የምታደርሳቸው የሕሊና ኮሽታ ነች፡፡ በኑሮ ሂደት ሀዘን፣ ጸጸት ርትዕ በምናደርግበት ጊዜ ልዩ መንፈሳዊ ጥበብ አልያም ዕውቀት በመታደል ሳይሆን ሰው በመሆናችን በሕሊና ውስጥ የተቀረጸ በህሊና ሚዛን የሚሰጥ ፍርድ በመኖሩ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕገ ሕሊና በጽሑፍ ከተሰጡን ሕግጋት /ሕገ ኦሪት፣ ሕገ ወንጌል፣ ማሕበራዊ ሕግ/ በላይ ሰማያዊና ምስጢርን ለመጠበቅ ሲያገለግል እናገኘዋለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሀገር የግል ምስጢር ይጠበቅ ዘንድ መንፈሳዊ ሕግና ማህበረሰባዊ ሕግ ይደነግጋል፡፡ የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ያለ ምድራዊ ሕግ አስገዳጅነት በሕገ ልቦና ዳኝነት ለሰማያዊ ምስጢር የታመነች ነበረች “እናቱ ማርያም በልቧ ትጠብቀው ነበር” እንዲል፡፡ /ሉቃ.2÷19/፡፡

 

 

ሰው ራሱ መጽሐፍ ነው” የሚለው የአነጋገር ስልት የሚያስተላልፈው ሰው ይነበባል፤ ይጠናል፤ ይተነተናል ይጸድቃል፤ ይሻራል ለማለት ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ለድርጊታችን ብያኔ ፍርድ ለመስጠት ረቂቅ የሕሊና ልጓም እንደ መሠረት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሰው በውስጡ የሚያረጋግጣት እውነት በክበበ አዕምሮ በሚጨበጥ ሕገ ባሕርይ ከመገለፅ እምቢ አትልም፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እምነት በቅድሚያ እንዲገኝ ግድ ቢሆንም በተግባር ወይንም በድርጊት ካልተዋሃደ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ፍሬ ቢስ፤ ረብ የሌለው ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ እምነታችን ከድርጊታችን ለምን ተዛነፈ? በጽናት የምናምነውን እምነት አጥቦ የመውሰድ ብቃት ያለው ሃይል ይኖር ይሆን? በዕለት ተዕለት ማኅበራዊ መስተጋብር የምንወስናቸው መጠነ ሰፊ ጥቃቅን ውሳኔዎች ውህደ ሃይማኖት ምግባር የታሹ ወይስ የስሜት ውጤቶች ናቸው? እርግጥ ነው ስሜት አልባ ሰብአዊ ፍጡር ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ነፍስን ደስ የሚያሰኝ ሰማያዊ እውነት ከስሜት በላይ ነው፡፡ በገሃዱ ዓለም በብዙዎቻችን ሕይወት የሚታየው ውሳኔዎቻችን በድካም ባካበትነው ዕውቀት፤ መንፈሳዊ አስተምህሮ፤ ዓለማዊ ጥበብ፤ የቅዱሳን ሕይወት ሳይሆን ለስሜት ያጋደለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻልም የሚለውን ኃይለ ቃል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማረው ይሁዳ ለ30 ብር ሸጦታል ለምን ትለኝ እንደሆን ሰው ክፉን ነገር እስኪሰራ ሰው ልበ ሙሉ ይሆናልና ነው፡፡ ሁለተኛው የህሊና ዓይን ከነፍስ ባይለይም በኃጢአት ምክንያት ይጨልማል ይደክማልና ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ድርጊታችንን የሚቆጣጠረው በዕለቱ ስሜታችንን ያቀጣጠለው ኃይል እንጂ በጥረት ያካበትነው ትምህርት ወይም ዕውቀት ሆኖ አይታይም፡፡ ሰው ሆይ ለምን ይሆን